ከጉራጌ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

በአሁኑ ወቅት ኤጲስ ቆጶሳትን ሾምን፤ በሚያገለግሉበትም ቦታ መደብን የሚሉ ሕገ ወጥ አካላት የሕግና የሥርዓት ምንጭ የሆነችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክብር የሚያቃልል፤ አንድነቷን የሚከፋፍል፤ ቀኖናዋንና ትውፊቷን የሚሸረሽር ተግባር ፈጽመዋል፡፡ የጉራጌ ሶዶ ሀ/ስብከት ጳጳስና የምሁር ኢየሱስ ገዳም የበላይ ጠባቂ ጳጳስ ተደርገው ሁለት ሰዎች ለጉራጌ ሀ/ስብከት መመደባቸውንም በአግራሞት ተመልክተናል፡፡
በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን የማታውቃቸው ሕገ ወጥ ሿሚና ተሿሚዎች እኛን የሰበሰበችንን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለመበተን የሚያደርጉትን የቀኖና ጥሰት ለማውገዝ የጉራጌ ሀ/ስብከት አስተዳደር ጉባኤ አስቸኳይ ስብሰባ አድርገናል፡፡
በመሆኑም፡-
፩) የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆናችሁ አባቶቻችን የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማጽናት በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት የምትወስኑትን የአንድነት ውሳኔ በአንቃዕድዎ ሆነን እየጠበቅን መሆናችንን በታላቅ አክብሮት እንገልጻለን፤
፪) የጉራጌ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት፣ የሀ/ስብከቱ ወረዳ አብያተ ክህነት ጽ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀ/ስብከቱ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኗ ካህናትና ምእመናን በሙሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ከወትሮው በተለየ ንቃትና ታማኝነት በመጠበቅ፤ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግና መረጃዎችን በመለዋወጥ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ አጥብቀን እናሳስባችኋለን፤
፫) በጉራጌ ዞን በየደረጃው ያላችሁ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅና በማስጠበቅ ሀገራዊ አደራችሁን እንድትወጡ እንጠይቃለን፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
የጉራጌ ሀ/ስብከት ጽ/ቤት
ወልቂጤ-ኢትዮጵያ
ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም.
0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *