ግቢ ጉባኤያትን ለማጠናከር በጋራ እንሥራ

በእንዳለ ደምስስ

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ለማነጽ በምታደርገው ጥረት ውስጥ የእግዚአብሔርን ቃል ማስታጠቅ ዋነኛ ተግባሯ ነው፡፡ ለዚህም ከላይ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እስከ አጥቢያ ድረስ ባለው መዋቅር ምእመናን ስለ እምነታቸው እንዲረዱ፣ ሕይወቱንም እንዲኖሩት በማድረግ ላለፉት ፳፻ ዓመታት ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ስታከናውን ቆይታለች፡፡ በእነዚህ ዘመናት ሁሉ መውደቅ መነሣት ቢያጋጥማትም በክርስቶስ ደም በዐለት ላይ ተመሥርታለችና ፈተናውንና መከራውን ተቋቁማ ዘልቃለች፤ እስከ ዕለተ ምጽአትም ትቀጥላለች፡፡

ወንጌልን መሠረቷ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን የሚገጥሟትን ፈተናዎች ለመቋቋምና አገልግሎቷን ለማስፋፋት ደግሞ የኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ሚና ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በሃይማኖት የጸኑ፣ በሥነ ምግባር የታነጹ ወጣቶች ለማፍራትም ዘመኑን የዋጀ ትምህርት በየሰንበት ትምህርት ቤቶች ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ከዚህም አልፎ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ የሚማሩ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች ላይ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ ካለፉት ፳9 ዓመታት ጀምሮ ማኅበረ ቅዱሳን ከቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ፈቃድ መሠረት ኃላፊነት ወስዶ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም ከሰባት መቶ ሺሕ በላይ ተማሪዎችን አስተምሮ ለማስመረቅ ችሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን መንፈሳዊ ትምህርቱን ለመስጠት ጥረት ቢደረግም የሀገራችን የፖለቲካና የመንግሥት መለዋወጥ በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ውስጥ በሚማሩ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ያለመረጋገትና ጫና ፈጥሯል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተማሪዎች በጎሰኝነትና፣ በብሔር በመከፋፈል አንዱ አንዱን ማጥቃት በመበራከቱ የበርካቶች ሕይወት አልፏል፣ እንዲሁም ቆስለዋል፡፡ ለስደትና እንግልት የተዳረጉትም ቁጥራቸው ከፍተኛ ነው፡፡ መደበኛ ትምህርታቸውንም ሆነ መንፈሳዊ ትምህርቱን መከታተል የሚያስችሉ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ብዙዎች ከችግሩ ስፋት አንጻር ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ለመመለስ ተገደዋል፡፡

ይህ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ከ፳፻፲2 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ ዓለምን እያስጨነቀ የሚገኘውና የሰውን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው ኮቪድ ፲9 (ኮሮና ቫረስ) በመከሠቱ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ሁሉ ተዘግተው ቆይተዋል፡፡ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች በኮቪድ ፲9 ሕመም ለተጠቁ ወገኖቻችን ማገገሚያ እንዲሆኑ ተደርጎ ነበር፡፡

በ፳፻፲፫ ዓ.ም መጀመሪያ ግን ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በማገገሚያ ማእከልነት አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት ተቋማቱ መደበኛ ትምህርት እንዲቀጥል ለማድረግ የዓለም ጤና ድርጅት፣ የኢትያጵያ ጤና ኢንስቲቲዩትና የጤና ሚኒስቴር በሚሰጡት አቅጣጫ መሠረት ዝግጁ የሆኑ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች የመጨረሻ ዓመት ተማሪዎችን ከመስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም ጀምሮ መቀበል እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ቅድመ ዝግጅት በማድረግ አንዳንዶቹ ተማሪዎችን ለመቀበል ጥሪ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡና ያለፉት ዓመታት ችግሮች መልሰው እንዳያገረሹ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከተማሪዎች፣ ከአስተዳደር አካላትና ከመንግሥት የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡-

ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ጽንፈኛ የፖለቲካ ማእከላት እንዳይሆኑ መሥራት፡-

ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች የተቋቋሙበት የራሳቸው የሆነ ዓላማ አላቸው፡፡ በሥነ ምግባርና በዕወቀት የታነጸ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራት፣ በተሰማራበት የሥራ መስክም ብቁና የኅብረተሰቡን ችግር መፍታት የሚችል፣ ሀገር ወዳድና ወደ ተሻለ የዕድገት ጎዳና መምራት የሚችል ትውልድን የመፍጠር ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ነገር ግን ዩኒቨርስቲዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በተፈጠሩ አደገኛ የሃይማኖትና የፖለቲካ ጎራዎች ምክንያት ተማሪዎች ጠርዝ የረገጠ ስሜታዊነት ውስጥ ገብተው እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል የረብሻና የግድያ ማእከላት እስከመሆን ደርሰው እንደነበር ይታወቃል፡፡ ዓላማቸውን የሳቱ ግብሮችም ሲፈጸሙባቸው ቆይተዋል፡፡

ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት በመሥራት ዩኒቨርስቲዎችን ለተቋቋሙለት ዓላማ ብቻ በማዋል ብቁ የተማረ የሰው ኃይል በማፍራት ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ተፈጥረው የነበሩ ችግሮችን በመለየት፣ በመወያየት፣ በችግሮቹም ላይ ጥልቅ ጥናቶችን በማድረግ፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማቅረብና ወደ ተግባር በመለወጥ ተማሪዎችም ከሥጋት ውስጥ በመውጣት ጤናማ የተምሮ ማስተማር ሂደቱ ሊቀጥል ይገባል፡፡

ከብሔርና ጎሰኝነት የጸዱ ማድረግ፡-

ላለፉት በርካታ ዓመታት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ በመንደር፣ በብሔርና ጎሰኝት ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ በሀገሪቱ ላይ ጎልቶ በመታየቱ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ከዚህ ችግር አላመለጡም፡፡ እርስ በእርስ የእኔ እበልጥ የእኔ እበልጥ ሽኩቻ በርካቶች ተጎድተዋል፣ ሕይወታቸውንም አጥተዋል፣ በብሔር ጥላ ሥር በመከለል ኢትዮጵያዊ አንድነትን ዘንግተዋል፡፡

ለተለያዩ ጽንፈኝነት ላይ ያተኮሩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በመጋለጣቸውም በሚያገኙአቸው የተሳሳቱ አመለካከትን ባዘሉ መረጃዎች በመታለል ከትምህርታቸው ይልቅ ሃይማኖትና ብሔር ተኮር እንቅስቃሴ ውስጥ በመግባት የመማር ማስተማሩን ሂደት እንቅፋት እንዲገጥመው አድርገዋል፡፡

እነዚህ ተቋማት በተለያዩ ክልሎች እንደመገኘታቸው ከሌሎች ክልሎች ለሚመጡ ተማሪዎች ስጋት ሲሆኑም ተስተውሏል፡፡ ክልሎች በብሔርና በቋንቋ ላይ የተመሠረቱ በመሆናቸው ለብሔርና ጎሰኝነት ልዩ ትኩረት በመስጠት የእልቂት መነሻ ማእከላትም ሆነዋል፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን ለግቢ ጉባኤያት ሲሰጥ የነበረው መንፈሳዊ ትምህርትም የብሔርና የቋንቋ፣ እንዲሁም አክራሪ የእምነት ተቋማት በሚፈጥሩት ትንኮሳና ጥቃት ምክንያት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡

በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተፈጠሩትን ችግሮች ለማስወገድ በቅድሚያ ሰላምና መረጋገትን ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ከትምህርት ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ተቋማቱ ድረስ የዘለቀ ውይይት በማድረግ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማስቀጠል ችግር ፈቺ አሠራር መዘርጋት ይገባልና ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ዩኒቨርስቲዎች ከብሔርና ጎሳ እንዲሁም ከአከራሪ የሃይማኖት እንቅስቃሴ ወጥተው የዕውቀት መገብያ ማእከላት ሊሆኑ ይገባል፡፡

በሃይማኖታቸው ምክንያት ተማሪዎችን ከማግለልና ከማሳደድ መቆጠብ፡-

ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በመሆናቸው ብቻ እየተመረጡ የተለያዩ አድሎና ጥቃት ሲፈጸምባቸው የቆየ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ይህ ችግር ድጋሚ አገርሽቶ ወደ ግጭትና ጥቃት እንዳያመራ ሁሉም የበኩሉን በመወጣትና ዩኒቨርሲቲዎችን የሰላምና የአንድነት ተምሳሌት ማድረግ ይጠበቃል፡፡ በተለይም በአንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች አስተዳደር አካላት በግልጽና በስውር በኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ላይ ከሚያደርሱት የማግለልና የጥላቻ ዘመቻ መሰል ጥቃት መታደግ ያስፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ስለ ልጆቿ መብት ልትከራከርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ልታሰጥ ይገባል፡፡

ለዚህም ተማሪዎች ከተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባሕልና ሃይማኖት ይዘው ወደ ዩኒቨርስቲዎች ስለሚገቡ አንዱ በአንዱ ላይ ጫና ከማድረግ ይልቅ ተግባብቶና ተፋቅሮ ሰላማዊ እንቅስቃሴን በማስፈን ዓላማቸውን ማሳካት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የሃይማኖት ነፃነታቸው ተጠብቆ በሥነ ምግባር የታነጹና ውጤታማ እንዲሆኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ መሥራትን ይጠይቃል፡፡

ተማሪዎችን ከሥነ ልቡናዊ ጫና መታደግ፡-

ባለፉት ዓመታት በሀገራችን በተፈጠረው አለመረጋጋት ከተጎዱ አካላት መካከል የዩኒቨርስቲና የኮሌጆች ተማሪዎች ትልቁን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከዚህ ቀደም ወደማያውቁትና አዲስ አካባቢ ሲሄዱ የሚፈጠረው ጫና ቀላል አይደለም፡፡ አዲስ ጓደኛ፣ አዲስ አካባቢ፣ ውጥረት የበዛበት ትምህርት፣ በዚህ ላይ ደግሞ ሰላምና መረጋጋት በማጣት በሚደርሱ ጥቃቶች የባይተዋርነት ስሜት ስለሚሰማቸው ለሥነ ልቡና ቀውስ ይዳረጋሉ፡፡ ፍርሃትና ሁሉንም የመጠራጠር ስሜት ውስጥ ስለሚገቡ ውጤታማ የመማር ማስተማሩ ሂደት በተጠበቀው መንገድ እንዳይጓዝ እንቅፋት ይሆናል፡፡

ተማሪዎችን ከዚህ የሥነ ልቡና ውጥረትና ጫና ለመታደግ ሰላማዊ አካባቢን መፍጠር፣ ከተማሪዎች ጋር ውይይቶችን ማድረግ፣ በተለይም በባለሙያ የተደገፈ ሥልጠና በመስጠት በራስ መተማመናቸውን ማዳበር ያስፈልጋል፡፡

ከሚመለከታቸው አካላት ምን ይጠበቃል?

ከመንግሥት፡-

መንግሥት ሀገርን በሰላም የማስተዳደርና የመምራት ኃላፊነት አለበት፡፡ ችግሮች ከመከሠታቸው በፊት የመፍትሔ እርምጃ የመውሰድ፣ ችግሮች ከተፈጠሩም በኋላ በፍጥነት ፍትሓዊ የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ እንዳይደገም ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በተለይም በየክልሉ የሚገኙ አንዳንድ የፖሊስና የመከላከያ ኃይላት ከሚወስዱት ያልተገባና ተመጣጣኝ ያልሆነ ወንጀለኛንና ንጹሐኑን ሳይለዩ በጅምላ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ ይገባቸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት እነዚህ ችግሮች ጎልተው የታዩ በመሆኑ አሁንም እንዳይቀጥሉ መንግሥት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

ከአስተዳደር አካላት፡-

የዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች አመራር አካላት ችግር ፈቺ እንጂ የችግሩ አባባሽ ከመሆንና በእሳት ላይ ነዳጅ ከመጨመር መታቀብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአንዳንድ ተቋማት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመዘንጋት ተማሪዎችን በጎሳና በብሔር በመከፋፈል ኦርቶዶክስ ጠል የሆኑ አመራሮች በፈጸሙት ችግር በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡

ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲዎች በሚገቡበት ወቅት ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩት ችግሮች እንዳያገረሹ ሁሉንም ተማሪዎች በእኩል ዓይን በማየትና ሚዛናዊ አስተዳደር በማስፈን ሰላማዊ የማመር ማስተማር ሂደትን መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥት የሚመድባቸውን ኃላፊዎች ማንነት በማጥራት የተሻለ አስተዳደር እንዲሰፍን ተግቶ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

ከወላጆች፡-

ወላጆች ልጆቻቸው የግጭት አካል እንዳይሆኑ የመምከር፣ የመገሠጽና ትክክለኛውን ጎዳና የመምራት ኀላፊነት አለባቸው፡፡ ዓላማቸው ትምህርት ብቻ እንደሆነ በማስረዳት ከሁሉም ጋር በሰላም ተግባብተው በመኖር የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ አቅጣጫ ማሳየት ይገባቸዋል፡፡ ልጆች መነሻቸው ቤተሰብ ነውና እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ በሃይማኖታቸው የጸኑ ሆነው እንዲያድጉ ቤተሰብ፣ በተለይም የኦርቶዶክሳውያን ወላጆች ሚና ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ዩኒቨርስቲዎች ከመላካቸው በፊትም ሆነ በኋላ የመምከር፣ የመከታተል ግዴታ አለባቸው፡፡ ከጽንፈኛ አስተሳሰብ በመውጣት ለሥነ ምግባር ትልቅ ትኩረት እንዲሰጡ ማበረታታት፣ ከነፈሰው ጋር እንዳይነፍሱና በስሜታዊነት እንዳይነዱ በመቆጣጠር የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡

ከማኅበረ ቅዱሳን፡-

ማኅበረ ቅዱሳን ላለፉት ፳9 ዓመታት ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን ሃይማኖታቸውን እንዲያውቁ፣ በሥነ ምግባር ታንጸው ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፣ በዕውቀት የበለጸጉ፣ በመንፈሳዊ ሕይወት ያደጉ እንዲሆኑ መንፈሳዊውን ትምህርት እንደሚሰጥ ይታወቃል፡፡ ይህን አገልግሎቱን በቀጣይነት በማጠናከር፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን በመስጠት የድርሻውን ሊወጣ ያስፈልጋል፡፡

ብቁ መምህራንን በመመደብ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ሆነው እንዲወጡ፣ ከወጡም በኋላ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ለሌሎች አርአያነታቸውን እንዲያሳዩ በማበረታታት የተሰጠውን ኀላፊነት መወጣት ይገባዋል፡፡

ከተማሪዎች፡-

ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለምን እንደገቡ መረዳት፣ የገቡበትንም ዓላማ ፈጽመው ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በተማሩበት የትምህርት መስክ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸውና በገንዘባቸው በመርዳት ያስተማራቸውን ኅብረተሰብ መልሰው የማገልገል ግዴታ አለባቸው፡፡ ዋነኛ ዓላማቸውም ይህ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡

ከውጪም ከውስጥም ለሚነዙ ውዥንብር ለበዛባቸው መረጃዎች ሳይንበረከኩ ከብሔርና ከጎሣ አደገኛ አስተሳሰብ ራሳቸውን በማግለል ሰላማዊ የተምሮ ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ ተማሪዎች ወደ የኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች መመለሳቸው የማይቀር በመሆኑ ሰላማዊ የትምህርት ማእከላት እንዲሆኑ ከጽንፈኛ አስተሳሰብ በመራቅ፣ በዕውቀትና በሥነ ምግባር የታነጸ የተማረ ትውልድ በመፍጠር ረገድ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ይጠበቃል፡፡ ሁሉም የድርሻውን ከተወጣ ደግሞ ለሀገርና ለወገን የሚቆረቆር፣ ለአንድነትና ለሰላም የሚተጋ ማኅበረሰብ መፍጠር ያስችላልና ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ለዚህም የግቢ ጉባኤያት ድርሻ ከፍተኛ ነውና ከዚህ በፊት ከነበረው አገልግሎት በተሻለ ተጠናክሮ መቅርብ ያስፈልጋል፡፡ የግቢ ጉባኤያት መጠናከር ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ ትልቅ ድርሻ አለውና በተለይም ቤተ ክርስቲያንና ማኅበረ ቅዱሳን ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላምንና አንድነቱን ያድልልን፡፡ አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *