“ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ “ (ኤፌ ፭፥፲፮)

አዲሱ ዓመትን ለመሸጋገር በነፍስ ወከፍ አሰፍስፈንናል ምኑን ጥለን ምኑን አንጠልጥለን እንደምንሸጋገር ግን ብዙዎቻችን አናውቅም፤ ምናልባት ጥቂቶች ለባውያን (ልባሞች) ያውቁ ይሆናል ይህም ሲባል ባለፈው ዘመን ካከናወኑት ተግባር መካከል ወደ ኋላ የጎተታቸውንና ከዘመን ጋር ያጋጫቸውን ክፉ ነገር ትተው ወደ ፊት እንዲራመዱ ያደረጋቸውንና ከዘመን ጋር ያፋቀራቸውን ደግ ደጉን ይዘው መሸጋገርን ማለት ነው፡፡  ወይም ባለፈው ዘመን ከክፉ ሥራና ከስንፍና በስተቀር ጥቂት በጎ ሥራ እንኳን ያልሠሩበት ከሆነ ከወዲሁ ከአዲሱ ዘመን ዋዜማ ጀምሮ ንስሓ ገብተው ያንን ክፉ ሥራቸውንና ስንፍናቸውን ርግፍ አድርገው በመተው በጎ ሥራ ለመሥራት አቅደው መሸጋገርን ማለት ነው፡፡

ዘመን ተሸከርካሪ ነው ራሱ ሊሽከረከር አብሮት የሚሽከረከር ይፈልጋል፡፡ ጊዜና ውኃ ሙላት ሰውን አይጠብቅም›› እንደ እንደሚባለው ወደ ኋላ የሚጎተተውን ግን  ቀድሞት ይሄዳል እንጂ ከእሱ ጋር አብሮ በመጎተት አይጠብቀውም። ይህ ደግሞ  የዘመን ጉዳተኛ ሆኖ መቅረትን ያስከትላል። ነቢየ  እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል›› በማለት እንደተናገረው  ከስንፍናው ብዛት የተነሣ ሃይማኖቱን እስከመካድና እግዚአብሔር የለም እስከ ማለት ይደርሳል(መዝ፲፫፥፩) ይህ እንዳይሆን ግን  ዘመንን ቀድሞ  በመገኘት፣ የክብር አክሊልን መቀዳጀት የሰው ልጆች ግዴታ  አምላካዊ ትእዛዝም ነው ።

ሩጫችን ከዘመን ጋር መሆኑን  በአግባቡ መረዳት  ዘመንን ቀድመን መገኘት  ሲገባን  በዘመን ተቀድመን  መገኘት የለብንም ቅዱስ ጳውሎስ ዘመኑን ዋጁ ሲለንም  መልካም ስበእና መንፈሳዊ ትጋትና ንቃተ ሕሊና የዘመን ተግዳሮቶችን የሚያሻግር መንፈሳዊ ጥበብና ዕውቀት  ያለው ሰው ሁኖ መገኘት እንዳለብን  ሲመክረን ነው። ስለሆነም ዘመኑን በአዲስ የሥራ መንፈስ ልንቀበለው ይገባናል። በዘመኑ የሠራ በዘመን ይደሰታል።በዘመን የሰነፈ ደግሞ በዘመን ያዝናል።ያለፈውን ዘመን ያልሠራበትና በእንቅልፍ ወይም በወሬ ብቻ ያሳለፈው ሰነፍ አዲስ ዘመን በመለወጡ ብቻ አዲስ ነገር ሊያገኝ አይችልም። አሮጌውም አዲሱም ነገር ያለው ከራሱ ነው፤ ደስታውም ሆነ ኅዘኑ የሚመነጨው እሱ ራሱ በሠራው ሥራ እንጂ ከዘመን መለወጥ የሚገኝ ምንም ነገር የለም ዝም ብሎ የሚገኝ ድህነት ብቻ ነው። እሱም ቢሆን በቂ ምክንያት አለው፣ ይኸውም የአስተዳደር ድክመንት ወይም የዕውቀት ማነስ አለዚያም እንዲሁም ጦርነትና መቅሰፍት በታዘዘ ጊዜ  ሊሆን ይችላል፣ ከዚህ ሁሉ ውጭ ምንም ነገር የለም፡፡

ዘመንን በዘመናችን እንደታዘብነው የራሱ የሆነ ጫና አለው በአንዱ ዘመን ድርቅና ጦርነት ይበረታል። ለሌላው ዘመን  ዳግመ አዳዲስ የበሽታ ዓይነቶች ሊከሠቱ  ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ማለት ነው። በፖለቲካ ቀውስ ምክንያትም ሕዝቦች የችግር ሰለባ የሚሆንበት ዘመን አለ። ይህም ሁሉ አልፎ በሌላው ዘመን ደግሞ ጦርነትና በሽታም  ከምድር  ይጠፋና ሰው ልጆች  የሰላምና የጤና ባለቤት የሚሆኑበት ዝናመ ምሕረቱ፣ ጠለ በረከቱ  የሚወርድበት የምድር በረከትም የሚትረፈረፍበት ፤ሕዝቡ ረኀብ ቸነፈርም ከሰው ልጆች  የራቀበት ዘመን ይመጣል ታዲያ በእንዲህ ያለው ደግ ዘመን ያተረፈበት ብልህ ደግሞ አልፎ አልፎ የሚከሠተውን የመከራ ዘመን በሰላምና በጤና ይሸጋገራል፣ በመልካሙ ዘመን ያገኘው በረከት ለመከራው ዘመን ይረዳዋልና፡፡

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ ዘመን ወይም የዘመን አቆጣጠር ሥርት  መሠረት  ዘመን ጉዞውን የሚገፋባቸው የተለያዩ ስያሜዎች አሉት። ማቴዎስ፣ ማርቆስ ሉቃስና ዮሐንስ የሚባሉ አራቱ ወንጌላውያን እየተፈራረቁ የዘመንን ጉዞ ይቆጣጠራሉ፣ሄልሜል ሜሌክ ብርኤል ምልኤልና ናፔኤል የሚባሉ አራት ከዋክብትም እየተፈራረቁ የዘመንን ጉዞ በየተራ ይመራሉ። ክረምት፣ ሐጋይ፣ መፀውና ፀደይ የሚባሉት ወቅቶች ደግሞ ዓመቱን ለአራት ተከፋፍለው የያዙ የዘመን መረማመጃዎች ናቸው። ሁሉም ተደምረው በየተመደቡበት ወራት የየራሳቸውን ኃላፊነትና ድርሻ ይወጣሉ። በኃጢአታችን ምክንት የእግዚአብሔር መቅሰፍት በእኛ ላይ ካልሆነ በስተቀር የተጠቀሱት ሁሉ የተመደቡበትን ኃላፊነት ቸል ብለውት አያውቁም፤ ሁሉም የየራሳቸውን ተልእኮ በሚገባ ይፈጽማሉ፡፡

የዘመንን ዑደት ተቁጣጥሮ ሥራ ለመሥራት ሥልጣን የተሰጠው የሰው ልጅ ይህን የተሰጠውን ዘመን በሥራ ሊዋጀው ይገባዋል።የተወደዳችሁ ምእመናን ዘመን በወለዳቸው የጥላቻ እና የዘረኝነት ክፋቶች እንዲሁም የመጤ ባሕሎችነ አስተሳሰቦች ሰዎች ሳንሆነ ዘመንን  በመዋጀት  ክፉዎቹነ ቀኖች  አልፈን መልካም ቀኖችን  ለማየት  ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ሕይውትን ሊወድ መልካም ቀኖችንም ሊያይ የሚሻ ምላሱነ  ከንፈሮችንም ተንኮልን ከመናገር ይከልከል ከክፉ ነገር ፈቀቅ በል  መልካም ያድርግ ሰላምንም ይሻ ይከተለውም “በማላት እንተናገረው ዘመንን ቀድመን በቅንነት መትጋት ይኖርብናል (፩ጴጥ፫፥፲) አዲስን ዓመት ስንቀበል ከክፉ ሥራዎች በመራቅ የተጣላነውን ታርቀን የቀማነውንም መልሰን በንስሓ ሳሙና ታጥበን ሥጋውንና ደሙን በመቀበል አዲሱን ዓመት መልካም ዘመን እንዲሆንልን አምላካችን እግዚአብሔርን በጸሎት በመጠየቅ እንጂ በጭፈራ  በዘፈን መሆን የለበትም (፩ጴጥ፬፥፫)

አዲሱን ዓመት እውነተኛ አዲስ ዓመት እንዲያደርግልንና ዘመኑን እንድንዋጀው በሀገራችን ኢትዮጵያ ጦርነት ረኀብ ስድትና በሽታ የሚያበቃበት ሰላም ደስታ የሚበሠርበት ዘመን ይሆንልን ዘንድ  የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁልን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *