ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

የሰው ልጅ በዚህች ምድር በሚኖረው ቆይታ ብዙ ትጋት፣ ብዙ ኃይልና ብዙ መነሳሳት የተሞላበት ዘመን የወጣትነት ዘመን ነው፡፡ የሰው ልጅ ከሌላው ጊዜ በተለየ አዲስ ግኝቶችን ለማግኘት፣ እጅግ ከባድና ውስብስብ የሚመስሉ ጉዳዮችን በድፍረት ለመጀመርና ለመሞከር ታላቅ ወኔና ድፍረት የታጠቀበት ዘመን የወጣትነት ዘመን ነው፡፡ የማወቅ፣ የመመራመር ጉጉት፣ የማገልገል ልዩ ትጋትና ቁርጠኝነትን የተላበሰ ዘመንም የሚታየው በወጣትነት ነው፡፡ አካላዊ፣ ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ፣ ብሎም ምጣኔ ሀብታዊ ለውጦች በስፋት የሚስተናገዱበት፣ በውስብስብ ፈተናዎች የተሞላበት ዘመን ቢኖር የወጣትነት ዘመን ነው፡፡ ችኩልነት፣ እብሪተኝነት፣ አልታዘዝ ባይነት የሚፈታተኑት በወጣትነት ነው፡፡ ሉላዊነት አስተሳሰብ፣ ለረቀቀ የቴክኖሎጂ አቅርቦት፣ ለባህል ብረዛ፣ ሥራ አጥነት፣ ለቤተሰብ ጫና የሚጋለጠውም በወጣትነት ዘመን ላይ ነው፡፡

ይህንን ወጣትነት ብዙዎች እንደተጠቀሙበት ሁሉ ብዙዎችም መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ተብለው “እንግዲህስ ምድራችንን እንዳታቦዝን ቁረጣት” (ሉቃ.፲፫፥፮) እንደተባለች እንደዚያች በለስ የመቆረጥ ፍርድ ተፈርዶባቸዋል፡፡ በዚህ የወጣትነት ዘመን አቤል የፈጣሪውን ንጹሐ ባሕርይነት ተረድቶ ቀንዱ ያልከረከረውን፣ ጥፍሩ ያልዘረዘረውን፣ ጸጉሩ ያላረረውን ንጹሕ የመሥዋዕት ጠቦት በንጽሕና አቅርቦ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን እንዳተረፈበት ሁሉ፤ ወንድሙ ቃየልም በንዝሕላልነትና ግድየለሽነት ከሕይወት መስመር ወጥቶ ተቅበዝባዥነትን ተከናንቧል።(ዘፍ.፬፥፫፲፭)፡፡ በወጣትነት ዮሴፍ እንደ ወርቅ በእሳት ተፈትኖ ንጽሕናውን አሳይቶበታል፤ በዚሁ ወጣትነት ራሱን ለታይታና ለይስሙላ ባለሆነ ፍጹም ትሕትና ከወንድሞቹ ሁሉ በታች ዝቅ አድርጎ በንግሥና ከፍ ከፍ ብሎበታል፡፡(ዘፍ.፴፱፥፩)፡፡ በዚያም በምድርና በሰማይ ሠላሳ፣ ስድሣ፣ መቶም ያማረ ፍሬ አፍርቶ ዝገት የማይበላውን፣ ሌቦች የማይሰርቁትን መዝገብ አከማችቶበታል፡፡

በዚሁ የወጣትነት ዘመን እንደ ጢሞቴዎስ ያሉት ትጉሃን ደቀ መዛሙርት በትጋት የመምህራቸውን ፈለግ ተከትለው ለክርስቲያን ወገኖቻቸው ተርፈውበታል፣ በመምህራቸውም እንዲህ ተወድሰዋል “በአንተ ያለውን ግብዝነት የሌለበትን እምነትህን አስባለሁ” (፪ኛጢሞ. ፩፥፲፭):: ወጣትነት ከሰማያዊው ክብር ይልቅ ምድራዊውን ድሎት የመረጡ እነ ዴማስም እንዲህ ተብለዋል “ዴማስ ይህንን የዛሬውን ዓለም ወድዶ እኔን ተወኝ፤ ወደ ተሰሎንቄም ሄደ”  (፪ኛጢሞ. ፬፥፲)፡፡ በዚሁ የወጣትነት ዘመን ነው እንደ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሉት መከራና ግፍን ሳይፈሩ በጥብአትና በእምነት ለታላቅ ድልና መንፈሳዊ አክሊል የበቁት፡፡ እንዲያው በጥቅሉ ይህንን የወጣትነት ዘመን ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ አስገዝተው ለክብር ሞት፣ ለዘለዓለም ሕይወት የበቁ ብዙዎች እንደሆኑ ቅዱሳት መጻሕፍት ይዘክራሉ፣ አበው ሊቃውንትም ያስተምራሉ፡፡

በውኑ የኛስ የወጣትነት ዘመን የትጋት ነው? ከላይ እንደተጠቀሱት ደጋግ አበው ቅዱሳን የተሰጠንን መክሊት ሠርተን፣ ደክመን፣ ወጥተን ወርደን ለማትረፍ እየጣርንበት ነው? ወይስ የተሰጠንን ጸጋና መክሊት ቀብረን ያው ያለን እንኳ ተወስዶብን ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደማይጠፋ እሳት ለመጣል እየጠበቅን ነው? በእውኑ በወጣትነቱ ደግና ታማኝ አገልጋይ (ገብር ሔር) ማን ነው? ወጣቶች ወደ መንፋሳዊ አገልግሎት እንዳይቀርቡስ እንቅፋት የሆናቸው ምንድን ነው? ተግተው ለአገልግሎት የመጡት ወጣቶችስ እየገጠማቸው ያለው ፈተናና ተግዳሮት ምንድን ነው? ወጣትና ታማኝ መንፈሳዊ አገልጋይ ለመሆንስ ምን ማድረግ አለባቸው?

የመንፈሳዊ አገልግሎት እንቅፋቶች በዘመናችን አብዛኛዎቹ ወጣቶች ከእግዚአብሔር ቤት እየሸሹ ውሎና አዳራቸው ለመንፈሳዊ ሕይወታቸው ብቻ ሳይሆን ለሥጋዊ (ዓለማዊ) ሕይወታቸው እንኳ ወደማይጠቀሙበት አቅጣጫ በማምራት ከዓላማቸው ተሰናክለው ለጤና መታወክ በሚያበቋቸው አልባሌ ቦታዎች ሆኗል፡፡ ድምጿን ከፍ አድርጋ ለምታጠራ ቤተ ክርስቲያን ልባቸውን ከመስጠት ይዘገያሉ፡፡ ወጣቶች ወደ አገልግሎት እንዳይገቡ እንቅፋት ከሚሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ ነው፡፡

፩. ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ፡- ብዙ ወጣቶች ለስብከተ ወንጌል ልብ ሰጥቶ ከመታደም፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ጊዜ ሰጥቶ በተመስጦና በጥልቀት አንብቦ ከመረዳት፣ መምህራነ ወንጌልን፣ ሊቃውንትንና ካህናትን ቀርቦ ከመጠየቅ ይልቅ በተለያየ ሰበብና ምክንያት ራሳቸውን ስላሸሹ ቤተ ክርስቲያንን በውል ማወቅ፣ መረዳት ሲከብዳቸው ይስተዋላል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እናውቃለን ብለው የሚያስቡት እንኳን ዓለም ከምታቀርብላቸው ሥጋዊ ፍላጎትን ከሚያነሣሱ፣ ከማኅበራዊ የትስስር ገጾች ባለቃቀሟቸውና በቃረሟቸው የተቆራረጡና ምሉእ ያልሆኑ ሕጸጽና ግድፈት ከበዛባቸው መረጃዎች ተመስርተው ስለሆነ ቤተ ክርስቲያንንና ሐዋርያዊ ተልኮዋን በውል ተረድተዋል ለማለት ይቸግራል፡፡

ብዙኃኑ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን ምንድን ናት? ተልዕኮዋስ ምንድን ነው?  ቤተ ክርስቲያን ከእኔ ምን ትፈልጋለች? እኔስ ከቤተ ክርስቲያን የማገኘው ጥቅም ምንድን ነው? እነዚህን ለመሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለኅሊናቸው በውል ምላሽ መስጠት ሲቸግራቸው ይስተዋላል፡፡ ለአንዳድ ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን አቡነ አገሌ፣ አባ እገሌ፣ ሰባኪ/ዘማሪ እገሌ ናቸው። እነዚህ ዓይኑንና ተስፋውን የጣለባቸው ሰዎች ፈተና አድክሟቸው የዓለም አንጸባራቂ ውበት ስቦ፣ አታልሏቸው እንደ ዴማስ (፪ጢሞ. ፬፥፲) ወደ ኋላ መጓዝ፣ መሰናከል፣ በጀመሩ ጊዜ ቀድሞውኑ ቤተ ክርስቲያንን በእነዚህ ሰዎች ትከሻ ላይ ወስነዋት ነበርና የእነሱን ድካምና ጥፋት ከቤተ ክርስቲያን ለይቶ ማየት ያቅታቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከሕይወት መንገድ ተደናቅፈው ይወድቃሉ፡፡

ለዚህም ነው በየአድባራቱ፣ ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶች “የእገሌ መዝሙር ካልተዘመረ፣ እገሌ የተባለ ሰባኪ ካልመጣ፣ አባ እገሌ ካልተሾሙ፣ አቡነ እገሌ ካልተሻሩ አላገለግልም፣ አልመጣም” ወዘተ በማለት ቀስ በቀስ ከቤተ ክርስቲያን እቅፍ የወጡና እየወጡ ያሉ ምእመናን ቁጥራቸው እየበዛ የመጣው። ነገር ግን በእውነት ያለ ሐሰት ቤተ ክርስቲያን ከነዚህ ሁሉ ነገሮች በላይ የሆነች አንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ኩላዊት (ዓለም አቀፋዊት) ናት፡፡ (ሊቀ ጉባኤ አባ አብራ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት)። ለዚህም ነው አበው በሃይማኖት ጸሎት ደግመን ደጋግመን እንዘክረው ዘንድ “ከሁሉ በላይ በምትሆን ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” ብለው ያስቀመጡልን።

ቤተ ክርስቲያንን አለማወቅ በሦስት ክፍሎች ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡

የመጀመሪያው ስለ ቤተ ክርስቲያን ምንም ዓይነት ዕውቀትና ግንዛቤ አለመኖር ነው፡፡ አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው በልጅነታቸው ካመላለሷቸው በኋላ እግሮቻቸው ደጀ ሰላም አልረገጡም፡፡ ነገር ግን በአንገታቸው ማዕተብ አጥልቀው፣ በስማቸውም ክርስቲያን የክርስቶስ ወገን ተሰኝተዋል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች ቤተ ክርስቲያን ምን እንደሆነች፣ ተልእኮዋ ምን እንደሆነ፣ በዚህ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ምን ሁኔታ ላይ እንደሆነች አያውቁም፤ የማወቅ ፍላጎታቸውም የደከመ ነው፡፡ እናም መቼም ቢሆን ውስጣቸው በቤቱ ቅናት ተቃጥሎ “እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤ የቤትህ ቅንዓት በልቶኛልና” (መዝ.፷፰፥፱)  ብለው ለአገልግሎት ይነሡ ዘንድ፣ የሀገር፣ የቤተ ክርስቲያን መጥፋት አሳዝኗቸው ወደ መንፈሳዊ ቁጭት ውስጥ ይገቡ ዘንድ ኢታርእየነ ሙስናሃ፣ ለኢየሩሳሌም የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየን ሊሉ አይችሉም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ቤተ ክርስቲያንን (አስተምህሮዋን፣ ዶግማና ቀኖናዋን) በግል ምልከታቸው በሥጋዊ ድካማቸው ደረጃ ዝቅ አድርገው “ምን አለበት፣ ምን ችግር አለው፣ ብዙ ባናካብድ” በሚሉ ሰበቦች ታስረው ቤተ ክርስቲያንን ያወቁ የሚመስላቸው ነግር ግን ያላወቁ ወጣቶች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ዓይነቶቹ ምእመናን ቤተ ክርስቲያን  የምታስፈልጋቸው ሥጋዊ ፈተናዎች ( ሥራ ማጣት፣ ከወዳጃቸው ጋር መጋጨት፣ የሥጋዊ ደዌ፣ ሕመም፣ የኑሮ መክበድ፣ የትምህርት ጉዳይ) ሲያስጨንቃቸው ብቻ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሰማያዊና ዘለዓለማዊ ሕይወት ሰጭነት፣ የቤተ ክርስቲያን የነፍስ መጋቢነት አይታያቸውም፡፡

ሩጫቸው ምድራዊ ስኬት እስከ ማግኘትና መጎናጸፍ ብቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንተ ደካሞች፣ ሸክማቹሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ” (ማቴ.፲፩፥፳፰) ሲል እንዳስተማረን በድካማችን ጊዜ እግዚአብሔርን መጥራት በችግራችን ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን ደጅ መጥናት በጎና ተገቢ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን  የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አሳስቧቸው ሳይሆን ለአገልግሎት የሚመጡት ለሥጋዊ ዓላማ ብቻ ነውና ያ ጥያቄቸው መልስ ሲያገኝ (ሥራ ወይም ትዳር ሲይዙ) ከወላጆቻቸው ቤት ብቻ ሳይሆን ከቤተ ክርስቲያንም ይኮበልላሉ፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ቤተ ክርስቲያንን ባልተረጋገጠና በተምታታ መረጃ በአላዋቂዎች ትምህርት ተመርኩዘው እናውቃለን የሚሉት ናቸው፡፡ በዚህኛው የዕውቀት ደረጃ ብዙ ወጣት ምእመናን ቤተ ክርስቲያን ለዘመናዊነት፣ ሠርቶ ለመለወጥ፣ ራስን ለማሳደግ ጠላት አድርገው ይስሏታል። መንፈሳዊነትንና ለቤተ ክርስቲያን አሳቢነትን ራስን ካለመንከባከብ፣ ንጽሕናን ካለመጠበቅ እና ሥራና ትምህርትን እርግፍ አድርጎ ትቶ የብሕትውናን ኑሮ ከመኖር ጋር የሚያዛምዱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ እግዚአብሔርን በፈራጅነቱ በቀጭነቱ ፈርተው ያመልኩታል እንጂ  ከፍቅር የመነጨ ፈሪሃ እግዚአብሔር አይኖራቸውም፡፡ የእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ሌላው መለያ ባሕርያቸው በመንፈሳዊ መንገዳቸው ፊት ለፊት የሚታያቸው የክርስቶስ ሕይወት፣ አልያም የአበው ቅዱሳን ተጋድሎ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ በቅርብ የሚያገኙትን አገልጋይ የፍጹምነት ምሳሌ አድርገው ይስሉታል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ እነዚህን ሰዎች ከማምለክ ባልተናነሰ ሲያደምጡ ይስተዋላል፡፡ በአጠቃላይ ሦስቱም ትክክለኛ መንገዶች አይደሉም፡፡

.አልችልም/”አይገባኝም” ማለት ትሕትናና ራስን ዝቅ ማድረግ፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በተግባር ሠርቶ፣ በቃል አብራርቶ፣ በምሳሌ አጉልቶ ያስተማረን፣ አባቶቻችን በመንፈሳዊ ክብር ከፍ ከፍ ያሉበት ታላቅ ጸጋ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱሳት መጻሕፍት ደግመው ደጋግመው ስለ ትሕትናና ራስን ዝቅ ስለማድረግ በአጽንዖት የሚነግሩን “ትሕትናና  እግዚአብሔርን መፍራት ባለጠግነት፣ ክብር፣ ሕይወትም ነው”  እንዲል(ምሳ.፳፪፥፬)፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ራስን ዝቅ አድርጎ ቅድሚያ ለሌሎች መስጠት የተገባ እንደሆነ ብርሃነ ዓለም ቅዱሰ ጳውሎስ “እያንዳንዱ ባልንጀራው ከርሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር”  (ፊልጵ.፪፥፫) ሲል ይነግረናል፡፡

ነገር ግን ትሕትናችን፣ ራስን ዝቅ ማድረጋችን ለእታይ እታይ ባይነትና ከንቱ ውዳሴ ሰለባ ከሆነ፣ በልቦናችን አንዳች የትሕትና ፍሬ ሳይኖር ውስጣችን በትዕቢት ወደ ላይ ተወጥሮ ውጫዊ አካላችን ለብቻው የሚያጎነብስ ከሆነ፣ ትሕትናችን ለምድራዊ ክብር መሻት፣ ዓለማዊ ሀብትን በማየት አለዚያም ራስችንን ከኃላፊነት፣ ከአግልግሎትና መታዘዝ ለማሸሽ የመደበቂያ ምሽግ ሆኖ ካገለገለ በውኑ ይህንን በቅዱሳት መጻሕፍት ሚዛንነት ትሕትና ነው ማለት አይቻልም፡፡ በዘመናችን ብዙ ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርበው፣ በአገልግሎት ተሳትፈው የበረከት ተቋዳሽ እንዳይሆኑ ትልቅ እንቅፋት እየሆነባቸው ያለ ጉዳይ ትሕትናን የሚመስል ነገር ግን ትሕትና ያልሆነ ያልችልም ባይነት ስሜት፣ ራስን ዝቅ በማድረግ የተደበቀ ከኃላፊነትና ከአገልግሎት የመሸሽ ልማድ ነው፡፡

የሰው ልጅ በአስተሳሰቡና በአመለካከቱ አልችልም፣ ደካማ ነኝ የሚል ስሜት ካሳደረ፤ የእግዚአብሔርን ረዳትነት ተማምኖ “ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችሁማል፣     ፊታችሁም አያፍርም” (መዝ.፴፫፥፭) እንዲል መዝሙረኛው ቅዱስ ዳዊት ወደ ቤተ ክርስቲያን ቀርቦ ለተግባር፣ ለድርጊት መቸም ቢሆን ውስጣዊ መነሣሣትና ቁርጠኝነት አይኖረውም፡፡ ሰው የሚያስበውን ያንኑ ይመስላል እንዲል አስተሳሰባችን ከተግባራችን ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ይህ የአስተሳሰብ ደካማነት፣ እምነተ ጎደሎነት ወይም የጥርጥር መንፈስ ተብሎ ይገለጻል፡፡ በውኃ ላይ መራመድን ሽቶ በመሐል በመጠራጠሩ ሊሰምጥ የነበረውን ቅዱስ ጴጥሮስን ማሰብ ያሰፈልጋል፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በጥብዓት ከተጓዘ በኋላ በመሐከል ግን የጥርጥር መንፈስ ወደ እርሱ እንደገባና እምነተ ጎደሎ በመሆኑ እንደተገሠጸ ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል (ማቴ. ፲፬፥፳፬)፡፡

በእርግጥ አበው ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሊቃውንት፣ ጻድቃን ሰማዕታት ለታላቅ አገልግሎትና ተልእኮ ከፈጣሪ ጥሪ ሲደረግላቸው ከልብ በመነጨ መንፈሳዊ ትሕትና ይህንን ጥሪ እቀበል ዘንድ እኔ ማን ነኝ፤ ይህንን ተልእኮስ እቀበል ዘንድ እኔ ምንድን ነኝ ፤ እኔ ደካማ ሰው ነኝ ሲሉ የተሰጣቸው ተልእኮ ታላቅነትን፣ የእነርሱን ደካማነት አሳይተዋል፡፡ ነገር ግን ይህንን ብለው ከኃላፊነትና ከአገልግሎት አልሸሹም ይልቅ ሰማያዊ ተልእኳቸውን በትጋትና በብቃት ተወጡ እንጂ፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ከፈርዖን ግፍና ባርነት ነጻ ያወጣ ዘንድ መመረጡን በሰማበት በዚያች ቅጽበት “እኔ ኮልታፋ ምላሴም ጸያፍ የሆነ ሰው ነኝ ትናንት ከትናንት ወዲያ ባርያህንም ከተናገርከኝ ጀምሮ አፈ ትብ ሰው አይደለሁምን” (ዘጸ. ፬፥፲) በማለት የእርሱን ደካማነት የተሰጠውን አደራና ኃላፊነት ታላቅ መሆን ይገልጻል። ነገር ግን የሙሴ ትሕትና ልባዊ ነበርና፤ “ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ነበር” (ዘኊ.፲፪፥፫) እንዲል፡፡ ይህንን ማለቱ ተልእኮውን ከመወጣት አላስቀረውም፡፡

ከሁሉም በላይ ብዙ ወጣቶች እኔ ገና ጀማሪ ነኝ፣ እኔ ምንም አልጠቅምም፣ እኔ ለቤተ ክርስትያን የምሆን ሰው አይደለሁም ሲሉ ለሰውም ለራሳቸው ኅሊናም እየነገሩ በትሕትና ሰበብ በቅድሚያ ከአገልጋይነት እየቆዩም ከጾም ጸሎት ሸሽተው የጠፉ ሰዎች ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድ አገልጋይ “ሁልጊዜም ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝ“ (፪ኛቆ፲፪፥፲) በማለት ሐዋርያው እንዳስተማረን እርሱም ለበለጠ ትጋት፣ ለበለጠ አገልግሎት መነሣሣት ይገባዋል። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ቤት ታናሽና ታላቅ ኃላፊነት ያለበትና የሌለበት ሰው የለም አምላካችን በሁላችንም ደጅ ቁሞ “እነሆ በደጅ ቁሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደርሱ እገባልሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” (ራዕ ፫፥፳) እያለ ለበረከት ይጠራናልና፡፡ ስለዚህ እያንዳንዳችን ይህን ጥሪ አክብረን የሚጠበቅብንን ተወጥተን የስሙ ቀዳሽ የመንግሥቱ ወራሽ እንድንሆን ልንተጋ ይገባል፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ ይቆየን፡፡

ምንጭ፡- ከሐመር መጽሔት ሰኔ (ሰኔ ፳፻፲፩ ዓ.ም)

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *