‹‹ተራራውን ጥግ አድርጉ›› (ኢያ.፪፥፲፮)

በመ/ር ለይኩን አዳሙ(ከባሕር ዳር ማእከል) 

ይህን ኃይለ ቃል የተናገረችው ሀገረ ሙላዷ ብሔረ ነገዷ በኢያሪኮ ከተማ የነበረች የወጣ የወረደውን ያለፈ ያገደመውን በኃጢአት እያስተናገደች በመጥፎ ግብር ተሰማርታ እንደ መንገድ  እሸት ሁሉ ያለፈ ያገደመው የወጣ የወረደው ሁሉ  ይቀጥፋት  የነበረች ራኬብ ወይም ረዓብ የተባለች ሴት ናት፡፡ ይህ የምክር ቃል የተነገራቸው ደግሞ የኢያሱ መልእክተኞች ካሌብና ሰልሞን ነው፡፡

የእስራኤል ቅዱስ ልዑል እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በዘጠኝ መቅሠፍት በዐሥረኛ ሞተ በኵር በዐሥራ አንደኛ ስጥመት ጠላት ገድሎ ባሕር ከፍሎ በጸናች እጅ በተዘረጋች ክንድ  ሌሊቱን በብርሃን ቀኑን በደመና እየመራ አሻገራቸው፡፡ ካሻገራቸው በኋላም ያችን በተስፋ የሚጠበቋትን ከሩቅ አሻግረው የተመለከቷትን የአባቶቻቸውን ርስት የተስፋዋን ምድር ሳይወርሷት ያ ከፈርዖን መንጋጋ ከግብጽ ባርነት በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ የኤርትራን ባሕር በተአምረኛ በትሩ ከፍሎ ያሻገራቸው የነቢያት አለቃ የእግዚአብሔር ባለሟል የሆነው ሙሴ ናባው ተራራ ላይ በክብር ዐረፈ፡፡

መንጋውን ያለ እረኛ ያለ መሪ የማይተው እግዚአብሔር ከመካከላቸው በሃይማኖት በዓላማ በቅድስና በታማኝነት መምህሩን አህሎና መስሎ ሆኖም በመገኘቱ እስራኤላውያንን  እንዲመራ እንዲያስተምር መምህሩ ሙሴም አስቀድሞ ‹‹ነቢየ ያነሥእ ለክሙ እምአኀዊክሙ ዘከማየ ወሎቱ ስምዕዎ፤እንደ እኔ ያለ ነቢይን ያስነሣላችኋል እሱን ስሙት›› (ዘኁ.፲፰፥፰) በማለት ትንቢት የተናገረለት ኢያሱ እስራኤልን በእግዚአብሔር ተመርጦ ይመራ ጀመር፡፡ ኢያሱን እግዚአብሔር ‹‹አይዞህ በርታ ከሙሴ ጋር እንደነበርሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ›› በማለት የማይለወጥና የማይናወጽ የጸና ቃል ገባለት፡፡

ኢያሱ መንፈሳዊ ደስታን በልቡ ተሞልቶ  ካሌብና ሰልሞንን ኢያሪኮን ሰልሉ ብሎ ሰደዳቸው፡፡ ካሌብና ሰልሞንም በጥብዓት ሁነው ኢያሪኮን ቆላማውን ቦታ ሲሰልሉ አድረው ደጋማው ቦታ ላይ ነጋባቸው፡፡ በዚህ ጊዜ አሕዛብ ሰላዮች መሆናቸውን አይተው ማለት አለባበሳቸውን አካሄዳቸውን ተመልክተው ለዩአቸው፡፡ እነሱም በረዓብ ወይም ራኬብ ዘማ ቤት ገብተው ተደበቁ፡፡ ተከታትለው ገብተው የእስራኤል ጉበኞች አልመጡምን ? አሏት፡፡ እርሷም መጥተው ነበር ነገር ግን እህል በልተው ውኃ ጠጥተው ጥቂት ቀደሟችሁ አለቻቸው፡፡እነርሱም መግባታቸውን ስላመነች  መው ጣታቸውንም አመኗት፡፡ እርሷ ግን በውስጥ ደብቃቸው ነበር፡፡ ራኬብም ካሌብንና ሰልሞንን እንዲህ አለቻቸው ‹‹ትበውኡ ሀገረነ ወትቀትሉ ነገሥታቲነ ፤ ወደሀገራችን ትገባላችሁ ነገሥታቱንም ትገድላላችሁ አለቻቸው፡፡›› እነርሱም‹‹በምን አወቅሽ?  ›› አሏት ‹‹ወወደየ ፍርሀተ ውስተ ልበ ኃያላኒነ፤ኃያላኑ ሲፈሩ ሲደነግጡ ለኅምሳ ለስሳ የሚከፈተው በር በራሱ ጊዜ ይከፈታል ›› አለቻቸው፡፡

‹‹እንደምታዩት እኔ ከወገኖቼ ጋር ተድላ ደስታ አላደረግሁምና በምትገቡ ጊዜ እንዳታጠፉኝ ማሉልኝ ወይም ቃል ግቡልኝ›› አለቻቸው፡፡ እነርሱም በዚያን ጊዜ ‹‹አንችም ሆነ ወገኖችሽ ከቤታችሁ ተቀመጡ ቤትሽ ላይ ምልክት አድርጊበት›› አሏት፡፡ እርሷም እሽ ብላ በቤቷ መስኮት ላይ ቀይ ሐር አንጥፋ በሐሩ ላይ አሳልፋ  በሉ ‹‹አሕዛብና ጉንዳን መንገድ ከያዙ አይለ ቁምና ተራራውን ጥግ አድርጉ›› ብላ መክራ ሰደደቻቸው፡፡ እነርሱም እሽ ብለው ተራራውን ጥግ አደርገው ሦስት ቀን ከቆዩ  በኋላ ተጉዘው  ኢያሱን አገኙት እርሱም ‹‹እንዴት ሁናችሁ መጣቸሁ››?  አላችው፡፡

እነርሱም ‹‹ረዓብ ወይም ራኬብ የተባለች ሴት አግኝታን በቤቷ ከሸሸገችን በኋላ  አምላካችሁ ይችን ሀገር አሳልፎ ሰጥቷችኋል በመጣቸሁ ጊዜ አብሬ እንዳልጠፋ አስቡኝ ››ብላ መክራ ሰደደችን በማለት ለኢያሱ ነገሩት፡፡ ኢያሱም የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ተረድቶ ‹‹በሉ ተነሡ›› ብሎ ታቦተ ጽዮንን አስይዞ  ካህናት ማዕጠንተ ወርቅ ይዘው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው ኃያላኑ በቀኝ በግራ ተሰልፈው  ዮርዳኖስ ደረሱ፡፡

ዮርዳኖስ መልቶ ነበርና ታቦት የተሸከሙ የካህናት እግር ሲነካው ውኃው መልቶ  ቆመና ተከፈለ፡፡ ከዚያ በደረቅ ተሻግረው የኢያሪኮን ግንብ ስድስት ጊዜ ከዞሩ በኋላ ታቦተ ጽዮንን በመሃል አድርጎ ‹‹የነጋሪት ድምጽ ስትሰሙ አውኩ ደንፉ›› አላቸው፡፡ እነርሱም እንዳላቸው አደረጉ እየደነፉ ሲዞሩት የኢያሪኮ ቅጽር ከአራት ወገን ተናደ፡፡ አሕዛብም ወጡ ገጠሟቸው እስራኤላውያን አሸነፉ ፡፡ ኢያሱም አሕዛብን  ድል ነሥቶ ኢያሪኮን ገንዘቡ አደረጋት፡፡ ኢያሱ እንደገባ ካሌብና ሰልሞንን ‹‹በሉ ያች ሴት የት ላይ ነች›› በማለት ጠየቃቸው እነርሱም ይዘውት ሄዱ  እርሷም ከቤቷ መስኮት ላይ ቀይ ሐር ከቤቷ በር ላይ ሰንደቅ ዓላማ አድርጋ ጠበቀቻቸው፡፡ኢያሱም መረቃትና ሰልሞንን አግብታ እንድትኖር አደረጋት፡፡ይህ ሁሉ ምሳሌ ነው፡፡

ኢያሱ ማለት ስመ ትርጉሙ መድኃኒት ማለት ነው፡፡ ምሳሌነቱ ለኢየሱስክርስቶስ ነው፡፡ ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ነውና፡፡ (ማቴ ፩፤፳-፳፪ )

ኢያሱ የኢያሪኮን አጥር ቅጥር ንዶ አሕዛብን አጥፍቶ ዕብራውያንን ምድረ ርስት እንዳወረሳቸውና ኢያሪኮን ገንዘብ እንዳደረጋት ሁሉ፡፡ አማናዊው ኢያሱ ክርስቶስ ደግሞ አጋንንትን በሥልጣኑ ድል ነሥቶ ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት ተከምሮ የነበረውን የኃጢአት ክምር በመስቀሉ ንዶ ነፍሳትን ከሲኦል ወደ ገነት አስገብቷቸዋልና፡፡ ኢያሱ የአጋንንት ምሳሌ የሆኑ  አሕዛብን ድል አድርጎ ኢያሪኮን ገንዘብ እንዳደረገ ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶም ምእመናንን ገንዘቦቹ ያደረጋቸው አጋንንትን በመስቀል ተሰቅሎ ድል በማድረግ ነው፡፡

ቀይ ሐር የሥጋው የደሙ ምሳሌ ሲሆን መስኮት ደግሞ  የከናፍረ ምእመናን ምሳሌ ነው፡፡ ካሌብና ሰልሞን ሰላይነታቸው ለዚህ ዓለም ነው፡፡ ምሳሌነታቸው ደግሞ ለኦሪትና ለወንጌል ነው፡፡ ኦሪትና ወንጌል የተሠሩት በዚህ ዓለም ላለን ሰዎች ነውና ፡፡ ራኬብ ምሳሌነቷ የአሕዛብ ነው፡፡ ራኬብ  ብዙ ወንድ ስታወጣና ስታገባ ኑራ በኋላ ግን በአንድ በሰልሞን ጸንታ እንደኖረች አሕዛብም ብዙ ኃጢአት ሲሠሩ ብዙ ጣዖት ሲያመልኩ ኑረው በአንድ ጌታ አምነው  ለመኖራቸው ምሳሌ ነው፡፡ የተወደዳችሁ አንባብያን ረዓብ ወይም ራኬብ ለጊዜው ለኢያሱ መልእክተኛ ለሆኑት ለካሌብና ለሰልሞን ትናገረው እንጂ ፍጻሜው ግን አሁን በዚህ ዘመን ሁነን በአማናዊው ኢያሱ በክርስቶስ አምነንና ታምነን ለምንኖር ኦርቶዶክሳውያን የሚያገለግል ዘመን የማይሽረው ሕያው ቃል ነው፡፡

ለመሆኑ  ተራራ ምንድን ነው?    

ድንቅ የሆነው እግዚአብሔር በየዘመናቱ የሚደነቁ ነገሮችን እንደሠራ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተጻፈው ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ አህያ በባሕርይዋ መናገር አይስማማትም  እግዚአብሔር ግን አንደበት አውጥታ እንድትናግር አድርጓል፡፡ የቢታንያ ድንጋዮችንም ያለ ባሕርያቸው ድንቅ የሆነ ሰማያዊ ምስጋና እንዲያመሰግኑ አድርጓል፡፡ ረዓብ ዘማንም አንደበቷን ከፍቶ ፊቷን ጸፍቶ ሳታስበው ከሞት ለታደገቻቸው ለኢያሱ መልእክተኞች ለካሌብና ለሰልሞን ተራራውን ጥግ አድርጉ ብላ እንድት ናገር ድንቅ የሆነው አምላክ የሚደነቅ የሚተረጎም የሚመሠጠር ነገር  አናጋራት፡፡ ለመሆኑ ተራራ ምን ድን ነው?

፩ኛ. ተራራ የተባለው ረድኤተ እግዚአብሔር ነው

ተራራ በመከራ ቀን መጠጊያ መሸሸጊያ ይሆናል፡፡ ይጋርዳል ይሸፍናል፡፡ ተራራ እንደሚጋርድ ሁሉ እግዚአብሐርም ፍጥረቱን በረድኤቱ አጥር ቅጥር ሆኖ ከልሎ ይዞ ይኖራልና ተራራ ይባላል፡፡ ተራራውን ጥግ አድርጉ ማለት ረድኤተ  እግዚአብሐርን  ተስፋ አድርጉ ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር መኖር አይችልም፡፡ ‹ተራሮች በኢየሩሳሌም ዙሪያ እንደሆኑ ከዛሬ ጀምሮ ለዘለዓለም እግዚአብሔር በሕዝቡ ዙሪያ ነው›› (መዝ ፻፳፬፥፪) ይላል፡፡ አንድ ተክል አጥር ቅጥር ሲኖረው ከዘራፊ ከቀጣፊ ከወራሪ ይከላከልለታል፡፡ ረድኤተ እግዚአብሔርም የሰው ልጆችን አጥር ቅጥር ሆኖ ከሰይጣን ይጠብቀናልና፡፡

፪ኛ. ተራራ የተባለች ድንግል ማርያም ናት

አንድ ሁና ተወልዳ አንድ ወልዳ ሰማይና ምድርን የመላች መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ የሌለባት በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስን ዘወትር እያማለደች የምታሰጥ ድንግል ማርያም የጽዮን ተራራ ትባላለች፡፡ ‹‹አንሰ ተሰየምኩ ንጉሠ በላዕሌሆሙ በጽዮን በደብረ መቅደሱ፤እኔ ግን በእነርሱ ላይ ንጉሥ ሁኜ ተሾምሁ በተቀደሰው ተራራ በጽዮን ላይ››(መዝ.፪፥፮) ይላል የእግዚአብሔር ነቢይ ዳዊት፡፡ ስለዚህ ትውልድ ሁሉ ድንግል ማርያምን አንባ መጠጊያ ያድርግ ማለት ነው፡፡

ድንግል ማርያምን ጥግ ያደረጉ አባቶቻችንና እናቶቻችን የመከራን ባሕር ተሻግረው ዲያብሎስን ድል አድርገዋል፡፡ ተራራ በደን የተከበበ እንደሆነ ሁሉ እመቤታችን በቅድስና  በንጽሕና የተከበበች ናት፡፡ ተራራ ልምላሜ እንደማይለየው ሁሉ እመቤታችንም ከልምላሜ ጸጋ ተለይታ አታውቅም፡፡

ሊቁ ተራራ ያላት እመ አምላክ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያምን ነው፡፡ ስለሆነም ኑ እመቤታችንን ጥግ እናድርጋት እርሷን ጥግ ያደረጉ የሲኦልን ባሕር በጥላዋ ተጠልለው በታመነው ቃል ኪዳኗ ቀዝፈው ተሻግረዋል፡፡ ለዚህም ነው ሊቁ በድርሰቱ ‹‹ሶበ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም ኢያስጠመ ኵሎ፤የታመነው ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኑሮ  ሁሉንም የእሳት ባሕር ባሰጠመው ነበር›› በማለት የተናገረው፡፡ በሀገረ ቅምር ይኖር የነበረው ሰይጣን ቀንቶ ከበጎ ሥራ ያስወጣው  ስምዖን ወይም በላዔ ሰብእ ከሲኦል እሳት የዳነው የሲኦልን ባሕር ቀዝፎ መሻገር የቻለው  ድንግል ማርያምን ጥግ በማድረግ ነው፡፡ወዳጄ አንተስ ማነን ጥግ አደረግህ? እኅቴ አንችስ ማነን ጥግ አደረግሽ ?

፫ኛ. ተራራ የተባሉ ቅዱሳን አባቶቻችን ናቸው

ከጣዕመ ዓለም ከተድላ ዓለም ተለይተው ከዘመድ ይልቅ ባዕድ ከሀገር ይልቅ ምድረ በዳ ይሻለናል ብለው እከብር ባይ ልቡናን አሸንፈው ክርስቶስን የተከተሉ ቅዱሳንን በተራራ ይመሰላሉ፡፡ተራራውን ጥግ አድርጉ ማለት በተሰጣቸው ቃል ኪዳን በአማላጅነታቸው አምናችሁ ተማጸኑ ለምኑ ማለት ነው፡፡ ቅዱሳን ተራራ እንደሆኑ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፤መሠረቶቿ  የተቀደሡ ተራሮች ናቸው (መዝ ፹፮፤፩) በማለት ይገልጣል፡፡

ተራራ ከፍ ያለ እንደሆነ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን እግዚአብሔር በረድኤት ያደረባቸው በጸጋ የተዋሐዳቸው ቅዱሳን ክብራቸው ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ ጊዜያዊ ያይደለ ዘለዓለማዊ ነው ተራራ በማለት ክብራቸውን ይገልጣል፡፡ እግዚአብሔር ከተራርች ሁሉ መርጦ በሲና ተራራ፣ በታቦር ተራራ፣ በሞርያ ተራራ፣ በቀርሜሎስ ተራራ፣ ልዩ ልዩ ተአምራትን እንዳደረገ ሁሉ ከሰው ልጆችም መርጦ በሙሴ በአብርሃም፣ በዳዊት፣በሰሎሞን ላይ በኤልያስ በኤልሳዕ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት በአቡነ አረጋዊ በአቡነ ተክለ አልፋ በአቡነ ተከሠተ ብርሃን እና በሌሎችም  ቅዱሳን ላይ አድሮ ከሰው ልጆች አእምሮ በላይ  ድንቅ የሆነ ተአምራቱን አሳይቷል፡፡

ቅዱሳንን ጥግ አድርገው ከኃጢአት የነጹ ለመንግሥተ ሰማያት የበቁ እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ በሊቃውንቱ ትርጓሜ  በታሪክ መጻሕፍት ላይ ተጽፎ እንደምናነበው ከነገሥታቱ ወገን የሆነች መልክን ከደም ግባት አስተባብራ የያዘች ኃጢአቷ የበዛ አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ይች ሴትም ውበቷን ደም ግባቷን ተጠቅማ ኃጢአትን መሥራት ጀመረች ይች ሴት በየዕለቱ የምትሠራውን ኃጢአቷን እየመዘገበች ታስቀምጠው ጀመር በየዕለቱ የምትጽፈው ኃጢአቷም ስንክሳር አከለ፡፡ እርሷም በደሏን አስታውሳ ይቅር ባይ ወደ ሆነው እግዚአብሔር በንስሓ ተመልሳ ሰማያዊ ሥልጣንን ገንዘብ ወዳደረገው ወደ ቅዱስ ባስልዮስ በእግዚአብሔር ቃል ወልውሎ ሰንግሎ ንጹሕ ያደርጋት ዘንድ ሄደችና ‹‹አባቴ ሆይ በዚህ ያለው ኃጢአትሽ ይፋቅልሽ በለኝ›› አለቸው፡፡

እርሱም ‹‹ይፋቅልሽ›› አላት ኃጢአቷም ተፋቀላት፡፡ ግልጣ ብታይ አንዲት ኃጢአት ቀርታ አገኘች ‹‹ዘዕፅብት ለነቢብ ለገቢርም›› ይላታል፡፡ ‹‹አባቴ ይልቁንም ሳስባት የምታስጨንቀኝ እንዳ ልናገራት የምታሳፍረኝ ይችስ ኃጢአቴ እንዴት ትሁን››? አለችው፡፡ቅዱስ ባስልዮስም ‹‹ለኔ መቼ ይቻለኛል ለልጄ  ለኤፍሬም ነው እንጂ›› አላት፡፡ አሁን ቅዱስ ባስልዮስ የማይቻለው ሆኖ አይደለም ቅዱሳን የእነርሱ ክብር ከሚገለጥ የባልጀራቸው ክብር ቢገለጥ ይወዳሉና ‹‹ወደ ኤፍሬም ሂጂ›› አላት፡፡ እርሷም ቅዱስ ኤፍሬምን ጥግ ልታደርግ አቀበት ወጥታ ቁልቁለት ወርዳ ሄደች ‹‹ከአባቴ ከቅዱስ ባስልዮስ ዘንድ መጥቻለሁ በዚህ ያለው ኃጢአትሽ ይፋቅልሽ በለኝ›› አለችው፡፡

ቅዱስ ኤፍሬምም ‹‹አባቴ ትሕትና ልማዱ ሆኖ ነው እንጂ ለእርሱ ለሊቀ ካህናቱ ያልተቻለ ለእኔ እንዴት ይቻለኛል? አይሆንልኝም ወደ እርሱ ሂጂ ››አላት፡፡ አሁን ለእርሱ የማይቻለው ሆኖ አይደለም ቅዱሳን የእነርሱ ክብር ከሚገለጥ የባልጀራቸው ክብር ቢገለጥ ፣ እነርሱ ከሚከበሩ ባልን ጀሮቻቸው ቢከብሩላቸው ይወዳሉና እንዲህ አላት፡፡

ነገር ግን አሁን በሕይወተ ሥጋ አታገኝውም በክብር አርፎ ካህናት በአጎበር አድርገው ወደ ቤተ እግዚአብሔር ይዘውት ሲሔዱ ታገኝዋለሽ በእምነት ሳትጠራጠሪ ከበድኑ ላይ ጣይው ይፋቅልሻል አላት፡፡ ብትሄድ እንዳላት ሆኖ አገኝች፡፡ ከከበረ አስከሬኑ አጠገብ ቁማ እንዲህ አለች ‹‹የእግዚአብሔር አገልጋይ ባስልዮስ ሆይ! የአገልጋይህን ኃጢአቷን አስተስርይላት ›› ብላ አምና አስከሬኑ ላይ ጣለችው ኃጢአቷም ተሰረየላት ንጹሕ ሁና ኃጢአቷ ተሰርዮላት ሸክሟ ቀሎላት ወደ ቤቷ እንደተመለሰች ሊቃውንት ተርጉመዋል፡፡(ውዳሴ ማርያም ትርጓሜ መግቢያ)

ይች ሴት ነውሯ የተወገደላት ሕይወቷ የተስተካከለላት ቅዱሳኑን ጥግ በማድረጓ እንደ ሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል ፡፡ ይህች እናት አሁን  ያለው ትውልድ ከተቀመጠበት የኃጢአት ዙፋን ወርዶ ራሱን እኔ ማን ነኝ?  ሰዎች ማን ይሉኛል?  ብሎ ጠይቆ ኃጢአቱን ተናዞ ጥግ ያደረገውን  ስካር፣ ዝሙት ፣ ስግብግብነት፣  ውሸት ፣ ዘረኝነት ረግጦና ጠቅጥቆ ንስሓ ገብቶ መንፈሳውያን  የሆኑ ቅዱሳን አባቶቹን ጥግ አድርጎ መኖር እንዳለበት ምሳሌ የምትሆን ብርቱ ሴት ናት ፡፡

፬ኛ. ተራራ የተባለች ወንጌል ናት

ተራራ ከሩቅ ሲያዩት ያስፈራል ያስደነግጣል፡፡ ሲወጡት ያደክማል  ላብ ጠብ ይላል ወገብ ይጎብጣል፡፡ ይህን ሁሉ ታግሶ ከወጡት በኋላ ግን ከላይ ወደታች ሲመለከቱ ሁሉን  ተራራውን ሸለቆውን አባጣውን ጎባጣውን ሲያሳይ ያስደስታል፡፡ ተራራ ላይ የወጣ ሰው የሚሰወርበት ነገር የለም ቢጣራ ከሩቅ ይሰማል ፡፡ ወንጌልም ከርቀት ሆኖ ሲሰሟት ታስፈራለች ታስደነግጣለች፡፡ በረኃብ በጥም በእናት አባት በዘመድ ናፍቆት ታደክማለች ይህን ሁሉ ታግሶ ከመምህራን እግር ሥር ቁጭ ብሎ  ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅና ኃጢአትን ሞትና ሕይወትን ክፋትና ደግነትን ለይታ ስታሳይ ታስደስታለች::

ወንጌል መከራውን ታግሶ ከተማሯት በኋላ የመናፍቃኑን የጎረበጠ የጠመመና የሻከረ አስተምህሮ የአባቶቻችንን የበሰለና የለሰለሰ የቀና ትርጓሜ ለይታ ስታሳይ  ለልቡና ሰላምን ለአእምሮ ርካታን ለነፍስ ሐሴትን ታጎናጽፋለች፡፡ ስለሆነም በዘመናችን የበግ ለምድ የለበሱ በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኵላዎች የሆኑ የመናፍቃኑ የክሕደት ቅርሻት ነፍሳችንን እንዳያበላሻት ለነፍሳችን ምግብ ጌጥና ውበት ሆና ከአምላካችን የተሰጠችንን ወንጌልን ጥግ እናድርግ፡፡ የመናፍቃኑን ክሕደት መለየት የምንችለው ነቅዕ የሌለባትን ወንጌል ጥግ ስናደርግ ነውና፡፡

፭ኛ. ተራራ የተባለች ጉባኤ ቤት ናት

ጉባኤ ቤት የቤተ ክርስቲያን ማሕፀን ናት፡፡ ተራራ ላይ የወጣ ሰው ሁሉን ይመለከታል የሚሰወርበት የለም፡፡ ጉባኤ ቤት የዋለ ሰውም ምድራዊውን ከሰማያዊው ጊዜያዊውን ከዘለዓለማዊው በትርጓሜ  ለይቶ አበጥሮ አንጠርጥሮ ገለባ የሆነውን የዚህን ዓለም ክፉ ሥራ ለይቶ ያወቃል፡፡ ተራራ ላይ ያልወጣ ሰው ሁሉን ማየት እንደማይችል ሁሉ ጉባኤ ቤት ያልዋለ ሰውም ደጉን ከክፉው፣መራራውን ከጣፋጩ፣ሥጋዊውንና ከመንፈሳዊው፣ለይቶ ማወቅ አይችልም፡፡ ስለዚህ የተወደዳቸሁ ኦርቶዶክሳውያን ኑ በምግባር ወልደው በሃይማኖት ኮትኩተው ያሳደጉን በቸገረን ጊዜ እንደ ዕንቊ በጨለመብን ጊዜ እንደ መቅረዝ የሚያበሩ ሊቃውንት ወደ ፈለቁባትና የምናኔ ቤተ ሙከራ የቅድስና ምንጭ የጥበብ መገኛ የክርስትናው አሻራ ያለባትን ጉባኤ ቤት ጥግ እናድርግና የድንቁርናን ማቅ አውልቀን ጥለን የዕውቀትና የጥበብ ካባን እንደርብ፡፡ ዛሬ ትውልዱ ዕድገቱ እንደ ካሮት ቁልቁል ጉዞው እንደ ዔሊ ከዚያው ከዚያው መርገጥ የጀመረው እንደ ንሥር ከሩቅ የሚያዩ ዐይናማ ሊቃውንት የወጡባትን ጉባኤ ቤት ትቶ አእምሮውን ድግሪ በሚባል ቁልፍ ብቻ ቆልፍ የፈረንጅ ምርኮኛ በመሆን መልአካዊ ባሕርይን የምታጎናጽፈውን ጉባኤ ቤት ጥግ አላደርግ በማለቱ ነው፡፡

፮ኛ ተራራ የተባለች ቤተ ክርስቲያን ናት

በተራራ የተመሰለች ሥሯ በሰማይም በምድር ያለች ክርስቶስ በወርቀ ደሙ ዋጅቶ በማይለወጥና በማይናወጥ ጽኑዕ በሆነ መሠረት ላይ የመሠረታት የጸጋው ግምጃ ቤት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ተራራውን ጥግ አድርጉ ማለት ቤተ ክርስቲያንን ጥግ አድርጉ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ጥግ ያደረገ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ይድናል፡፡ ለዚህም ምሳሌ የምትሆነን  የኖኅ መርከብ ናት፡፡

በኦርቶዶክሳውያን አስተምህሮ የኖኅ መርከብ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ሆኗ ትጠቀሳለች፡፡ በኖኅ  ዘመን የነበረው ትውልድ ከታናሽ እስከ ታላቅ በአንድነት ተካክለው ሲበድሉ ኖኅ ግን በሚያየውና በሚሰማው ነገር እያዘነ ሳለ እግዚአብሔር ኖኅን መርከብ እንዲሠራ አዘዘው፡፡ ኖኅም እሺ በጀ ብሎ መርከቡን ከሠራ በኋላ ደወል ደውሎ  እግዚአብሔር የፈደላቸው ፍጥረታት በመርከቧ እንዲጠለሉ አደረገ፡፡ መርከቧን ጥግ ያደረጉትን  ከታች የሚገለባበጠው ከላይ ደግሞ የሚልጠው የቁጣ ውኃ አልጎዳቸውም፡፡

መርከቧን ጥግ ያላደረጉትን ግን ሥጋቸውን ልጦ አጥንታቸውን ቆርጦ እንዳጠፋቸው  የነቢያት አለቃ የሆነው ሙሴ በቅዱስ መጽሐፍ ጽፎልናል፡፡ (ዘፍ ፮) በፈቃደ እግዚ አብሔር የተሠራችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንም ጥግ ያደረጉ ምእመናን ከላይ የጥንተ ጠላት ዲያብሎስ ከታች የዓላውያን ነገሥታትና የሠራዊታቸው የተሳለ ሰይፍ የነደደ እሳት ነፍሳቸውን አይጎዳውም፡፡ እኛም የተዋሕዶ ልጆች ቤተ ክርስቲያንን ጥግ አድርገን አምላካችን ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ እንዲታደገን አማናዊቷን ተራራ ቤተ ክርስቲያንን እናታችን ክርስቶስን አባታችን በማለት ዘወትር እንጠራለን፡፡

ሊቁ አምብሮስ በሃይማኖተ አበው ‹‹ቤተ ክርስቲያን እናቱ ያልሆነችለት ክርስቶስ አባቱ ሊሆን አይችልም›› እንዳለ፡፡ ስለዚህ ኑ እናታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን  ጥግ እና ድርግ፡፡

ማጠቃለያ:- ወንድሜ እኅቴ አንተ አንቺ ማነን ጥግ አደረግህ ማነን ጥግ አደረግሽ ረድኤተ እግዚአብሔርን ፣ድንግል ማርያምን ፣ቅዱሳንን ፣ወንጌልን ፣ጉባኤ ቤትን ፤ ቤተ ክርስቲያንን  ወይስ አንተም አንችም እንደ ዘመኑ ሰው ዘረኝነትን፣ቋንቋን ብሔርን፣ፖለቲካን ፣ገንዘብን፤ ሥልጣንን ነው ጥግ ያደረግኸው?  ያደረግሽው?  ከነዚህ ሁሉ ማነን ጥግ አደረግህ?  ማነን ጥግ አደረግሽ? ልብ በል ወንድሜ ልብ በይ እኅቴ ይህማ  ጊዜ የሚገታው መቃብር የሚጠቀልለው አይደለምን ? ኦርቶዶክስ የሆንኸው  የግቢ ጉባኤ አባላት ፣ሥራ አስፈጻሚ የሆንኸው የሆንሽው ዐውደ ምሕረት ላይ ሁል ጊዜ ሕይወት የሆነ ቃሉን የምትማረው የምትማሪው  ኪዳን የምታስደርሰው የምታስደርሽው  ቅዳሴ የምታስቀድሰው የምታስቀድሽው  ለዚህ ነበርን ? እግዚአብሔር ክብሩን ወደሚያድልባቸው ለቅዱሳን ቃል ኪዳን ወደ ተገባላቸው ቦታ  መሄድህ መሄድሽ ለዚህ ነበረን?

የምትዘምረው መዝሙር የምትሰብከው ስብከት ከዘረኝነት ከመለያየት ከዝሙት ከስካር  ከፍቅረ ንዋይ ካላወጣህ ካላወጣሽ ኦርቶዶክሳዊነቱ ትርፉ ምኑ ላይ ነው? ሃይማኖት ከሌላቸው በምን ተለየህ? በምን ተለየሽ? እውነት ነው ክፉ የሆኑ ምዕራባውያን ክብር ያለበት በሚመስል ውርደት ማወቅ ያለበት በሚመስል ድንቁርና ነጻነት ያለበት በሚመስል ባርነት በስተጀርባ መኖሩን ሳይነግሩን ዘረኝነትን፣ መለያየትን ፍቅረ ንዋይን ራስ ወዳድነትን በሥልጠና ጽዋ በጥብጠው በመጋት የኦርቶዶክሳዊነቱን አንድነት የኢትዮጵያዊነቱን በጎ መንፈስ ጥለን ባልተፈቀደልን  መስመር እንድንነ ጉድ አድርገውናል፡፡

የሰከረ ሰው ደግሞ ሜዳና ገደል አይለይም፡፡ ለዚህም እኮ ነው አሁን ያለው ወጣቱ ትውልድ በዘረኝነት ስለሰከረ አምላኩን የማይፈራ ሰውን የማያፍር የሆነው፡፡ ብዙዎቹ ንጹሓን ሰዎች ሳይበድሉ የተበደሉ ሳይገሉ  እንደ አቤል ደማቸው በምድር ላይ በግፍ የፈሰሰ የተሰደዱ  የዘረኝነትን ጽዋ በተጋቱ ሰዎች ምክንያት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ኑ ከዚህ ሁሉ ነገር እንውጣና ‹‹ተራራውን ጥግ እናድርግ›› እግዚአብሔር ሆይ የቤተ ክርስቲያንን መደፈር የኢትዮጵያን መጥፋት አታሳየን፡፡

             ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *