ግቢ ጉባኤያት እና የጊዜ አጠቃቀም

በእንዳለ ደምስስ

እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይጠቀሙበት ዘንድ ከሰጣቸው ሥጦታዎች ውስጥ አንዱ ጊዜ ነው፡፡፡ ሁሉንም በሥርዓት አበጅቶታልና የተሰጠውን ሥጦታ በአግባቡ የመያዝና የመጠቀም ኃላፊነት ደግሞ ከሰው ልጆች ሁሉ ይጠበቃል፡፡ “የሠራው ሥራ ሁሉ በጊዜው መልካም ነው” እንዲል (መክ.፫፥፲፩)፡፡

ጊዜ ቆሞ አይጠብቀንም፡፡ ሴኮንድ ወደ ደቂቃ፣ ደቂቃ ወደ ሰዓት፣ ሰዓታት ወደ ቀን፣ ቀን ወደ ሳምንት፣ ሳምንታት ወደ ወራት፣ ወራት ወደ ዓመት፣ …. ዘመን ዘመንን እየተካ ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል፡፡ ጊዜ ይመጣል ጊዜ ይሄዳል፡፡ በዚህ እግዚአብሔር እንኖርበት ዘንድ በሰጠን ዕድሜአችን ደግሞ ለተፈጠርንበት ዓላማ መኖር ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ተጠቅመንበታል? ስንል ከተጠቀምንበት ይልቅ ጊዜአችንን በዋዛ ፈዛዛ እንዳሳለፍነው እንረዳለን፡፡

ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ጠብቀው እንደ ቃሉም ተመላልሰው በሥራ በመግለጥ ወደዚህች ምድር የመጡበትን ተልእኮ አጠናቀው ለትውልድ አርአያ ሆነው ያለፉ አበው ዛሬም ድረስ በቅዱሳት መጻሕፍቶቻችን፣ በኑሯችን ሁሉ ስንጠቅሳቸው እንኖራለን፡፡ ጊዜአቸውን በአግባቡ መልካምን በማድረግ አልፈውበታልና በቃል ኪዳናቸው ተጠቃሚዎች ነን፡፡ ሌላው ግን በቀልድና በጨዋታ፣ እንዲሁም ከጽድቅ ይልቅ ለኃጢአት በመትጋት ዘመኑን ይጨርሳል፡፡ ሁለቱም በበጎነትና በመጥፎነት ለእኛ እንደ ምሳሌ ሆነው የምናነሳቸው ናቸው፡፡ “እናንተም ልትድኑበት የተማራችሁትን የእውነት ቃል ሰምታችሁና አምናችሁ ተስፋ ባደረገላችሁ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፡፡” (ኤፌ. ፩፥፲፫) እንዲል በፍቅር እግዚአብሔርን በማገልገል ጊዜያቸውን ለመልካም ነገር ተጠቅመው ለተጠሩበት ታምነው ለሌሎች ምሳሌ ሆነው አልፈዋል፡፡

በተቃራኒው ደግሞ “ለኃጠአት ትገዙ በነበረበት ጊዜ ከጽድቅ ነጻ ነበራችሁና፤ በዚያን ጊዜ ሥራችሁም እነሆ ዛሬ ታፍሩበታላችሁ፤ መጨረሻው ሞት ነውና” ይላል እግዚአብሔር በሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ላይ አድሮ፡፡ (ሮሜ. ፮፥፳፩)፡፡ ስለዚህ ጊዜአችንን በአግባቡ ተጠቅመን በረከት እንድናገኝ መትጋት ከኦርቶዶክሳውያን ይጠበቃል፡፡

ወደ መነሻ ሐሳባችን ስንመለስ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ከሁሉም የሚጠበቅ ቢሆንም በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ላይ ትኩረታችንን እናደርጋለን፡፡

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ወጣቶች ከሚቸገሩበት ጉዳይ አንዱ የጊዜ አጠቃቀማቸውን መቆጣጠር አለመቻላቸው ነው፡፡ ከቤተሰብ መራቃቸው ነጻነት ስለሚሰጣቸው ለተለያዩ ችግሮች በመጋለጥ ውጤታማ ሳይሆኑ ይቀራሉ፡፡ ከትምህርታቸውም ሆነ ከመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሳይሆኑ ባክነው ይቀራሉ፡፡

“ወደ ግቢ ጉባኤያት ገብታችሁ ለምን አትማሩም?” ሲባሉም የተለያዩ ምክንያቶችን ያቀርባሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹን ብንመለከት፡-

፩.የጥናት ጊዜአችንን ይሻማብናል፡-

ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከገቡ በኋላ በግቢ ጉባኤ ላይ እንዳይሳተፉ በዋነኛነት የሚጠቅሱት “ጊዜአችንን ይሻማብናል” በማለት እንደ ማምለጫ የሚጠቀሙበት አባባል ነው፡፡ ግቢ ጉባኤ ገብተው ለሥጋዊም ሆነ ለነፍሳቸው የሚሆን ስንቅ ይዘው እንዲወጡ ለሚመክሯቸው ሁሉ እንደ ኋላ ቀር በመቁጠር ሲያላግጡ ይስተዋላል፡፡ እግዚአብሔርን መፍራት በውስጣቸው ስለሌለ ዓለም ትናፍቃቸዋለች፡፡ ከትምህርት በኋላም ለጥናት ጊዜአቸውን ከመስጠት ይልቅ ሥጋዊ ፍላጎታቸው ወደሚመራቸው በመሄድ የሚሹትን ያከናውናሉ፡፡

“የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ” (መክ.፲፪፥፩) የሚለውን ቃል ይዘነጋሉ፡፡ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር በመለየት በተሰጣቸው የንስሓ ጊዜ ሁሉን ልጨብጥ፣ ሁሉን ላድርግ በማለት በወጣትነት ዘመናቸው ኃጢአት ለመሥራት ይተጋሉ፡፡ ፍጻሜአቸውም ያማረ አይሆንም፡፡ በትምህርታቸው የሚፈለገውን ያህል ሳይሆኑ፣ ከእግዚአብሔርም ጋር ያላቸው ግንኙነት ተቋርጦ ተመርቀው ቢወጡም በተመደቡበት ሁሉ ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ራሳቸውን የሚወዱ፣ ለክፉ ሥራ የሚተጉ ሆነው ይገኛሉ፡፡

በአግባቡ በግቢ ጉባኤ ውስጥ የተሚሳተፉ ተማሪዎች ግን ጊዜአቸውን በአግባቡ በመጠቀማቸው፣ ለማገልገልና ለመገልገል ራሳቸውን ያዘጋጁ በመሆናቸው እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገው በማስተዋል ስለሚጓዙ ውጤታማ ሆነው ለመውጣት አይቸገሩም፡፡

፪. የመዝናኛ ጊዜ ያስፈልገናል፡-

በትርፍ ጊዜያቸው የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማትና ከማንበብ በመራቅ “አእምሯችንን እናድስ” በሚል ፈሊጥ ጊዜአቸውን ለጨዋታና ለማኅበራዊ ሚዲያ በመስጠት ባክነው የሚቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ለሥጋዊ ምኞታቸው የሚቀርባቸውን በማየትና በመስማት ኃጢአትን ይለማመዳሉ፡፡ ከተቃራኒ ጾታ አልፈው ለተመሳሳይ ጾታ እስከመጋለጥ የሚደርሱ በርካቶች ናቸው፡፡

ከትምህርት በኋላ ራሳቸውን ለማዝናናት በሚያደርጉት ጥረትና ሩጫ ውስጥ በተቋሙ ዙሪያ የሚገኙ የመዝናኛ ሥፍራዎች ማለትም ጫት ቤቶች፣ ከሲጋራ ጀምሮ ሐሺሽ፣ ጭፈራ ቤቶችና የአልኮል መጠጥ መሸጫ ቦታዎች በስፋት በመኖራቸው ጊዜአቸውን እንዲሁ በማይጠቅምና ዓላማን በሚያስረሳ አካሄድ እንዲጓዙ ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ገና አንደኛ ዓመት ሳይጨርሱ ለመባረር ሲገደዱ መመልከት የተለመደ ነው፡፡ ቤተሰብ ልጄ ተምሮና ሥራ ይዞ ራሱንም ቤተሰቡንም ይረዳል ብሎ ሲጠብቅ መልሶ የቤተሰብ ሸክም ሆነው ይቀራሉ፡፡ ለዚህ ሁሉ ችግር ለመጋለጣቸው ዋነኛው ምክንያት ጊዜአቸውን መልካም ለሆነ እና ለተጠሩበት ዓላማ ባለማዋላቸው የተነሣ ነው፡፡

. የጓደኛ ተፅዕኖ፡-  

በተለያየ ምክንያት በሚኖረን አብሮ የመኖር መስተጋብር ውስጥ ጓደኛ ልናፈራ እንችላለን፡፡ ጓደኛ ያልነው ሰው ምን ዓይነት ሰው ነው? ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት፣ በመልካም ጎዳና የሚጓዝና አርአያ ሊሆነን የሚችል ሰው ነው? ብለን መፈተሽ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል፡፡ በተለይም ወጣቶች የጓደኛ ምርጫ ላይ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በግቢ ጉባኤያት ውስጥ የሚሳተፉ ተማሪዎችም ከማይመቹ ጓደኞች ሊርቁና ክፉውንና ደጉን በመለየት ትክክለኛውን መንገድ እግዚአብሔር እንዲያሳያቸው በጸሎት በመትጋት በአገልግሎት በመጽናትና ለዓላማቸው ታማኝ በመሆን በማስተዋል ሊጓዙ ይገባቸዋል፡፡

በጓደኛ ተፅዕኖ ምክንያት ከዓላማቸው እንዳይዘናጉ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጠለል፣ ድምጿንም ለመስማት ራሳቸውን ማዘጋጀት፣ ለትምህርታቸውና ለአገልግሎት ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

፬. የቴክኖሎጂ ውጤቶች፡-

ዓለም ዓላማን ሊያስቱ የሚችሉ፣ ትውልድን ከማነጽ ይልቅ በቴክኖሌጂ ስም ወጣቶችን ሊያማልሉና ወደ ጥፋት ጎዳን ሊወስዱ የሚችሉ ነገሮችን በመፈብረክ ተጠምዳ ትውላለች፡፡ በዚህም ምክንያት ወጣቶች ጊዜአቸውን እንዲያባክኑ ዕድሉን ታመቻቻለች፡፡ አንድን የቴክኖሎጂ ውጤት በተገቢው ጊዜና ቦታ ለአስፈላጊ ነገር ብቻ መጠቀም መልካም ቢሆንም ይህንን በመዘንጋት ቀኑን ሙሉ ለሚረባውም፣ ለማይረባውም ነገር ተጠምዶ መዋል ለሱሰኝነት ያጋልጣል፡፡ በተለይም የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ጊዜአቸውን ከማባከንና ለሱሰኝነት ሊያጋልጧቸው ከሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መራቅ፣ አስፈላጊ ሲሆን ለትምህርታቸው እገዛ ሊያደርጉላቸው የሚችሉትን ብቻ በተገቢው ጊዜ መጠቀም ይገባቸዋል፡፡

ከላይ በጥቂቱ ለማንሳት የሞከርናቸው ጉዳዮች በአብዛኛው በወጣቶች ላይ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጎልተው የሚታዩ ችግሮች እንደመሆናቸው መጠን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ ናቸው፡፡

በግቢ ጉባኤያት ውስጥ የሚሳተፉ ወጣቶችም ጊዜአቸውን ለትምህርታቸውና ለአገልግሎት በመስጠት በጾም፣ በጸሎትና በስግደት በመጽናት ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ያለቻቸውን ጊዜ በዕቅድ በመምራት ተጠቃሚ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለትምህርት፣ ለጸሎት፣ ለአገልግሎት የሚያውሉትን ጊዜ በመንደፍ በዕቅድ ራሳቸውን የሚመሩ ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ለዚህም ትልቁ ምስክርና ማረጋገጫ የሚሆነን በየ ከፍተኛ ተቋማቱ በቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የዋንጫና የሜዳልያ ተሸላሚዎች መሆናቸውና ቁጥራቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ነው፡፡

በከፍተኛ ውጤት ለመመረቃችሁ ምክንያት ምንድነው ተብለው ሲጠየቁም በግቢ ጉባኤያት ውስጥ በመሳተፋቸው በሥነ ምግባር እንዲታነጹና ጊዜአቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እንደረዳቸው ይናገራሉ፡፡ ጊዜአቸውን በአግባቡ ተጠቅመውበታልና ከኅሊና ወቀሳ ነጻ ናቸው፡፡ በዚህም ድርጊታቸው ከራሳቸው አልፈው ቤተ ክርስቲያንንና ወላጆቻቸውን ያስመሰግናሉ፡፡ ተመርቀውም ሲወጡ በዕውቀት የበለጸገ፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ትውልድ ሆነው ስለሚወጡ በተሠማሩበት የሥራ መስክም ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ በዚህም ጊዜን በአግባቡ መጠቀም የሚያስገኘውን ጥቅም ሌሎች እንዲረዱት አርአያነታቸውን ያስመሰክራሉ፡፡ ከእነርሱ በኋላ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚገቡ ተማሪዎችም ምሳሌ ይሆናሉ፡፡

በአጠቃላይ ራስን በሃይማኖት አቅንቶ፣ በአገልግሎት አንጾና በጾም ጸሎት በርትቶ ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ለውጤት እንደሚያበቃ ከግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ተሞክሮ እንረዳለን ማለት ነው፡፡ ወደፊትም ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገቡ ተማሪዎችም ይህንን በመረዳት ጊዜአቸውን በአግባቡ በመጠቀም ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *