በዓላማ መጽናት

በቀሲስ ዐቢይ ሙሉቀን

“ምክር ሠናይት ለኵሉ ዘይገብራ፤ ለሚያደርጋት ሁሉ ምክር መልካም ናት” በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት እንደተናገረው ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሊቃውንት በአጠቃላይ እግዚአብሔር ድንቅ ሥራውን የሚሠራባቸው ቅዱሳን አባቶቻችን እኛ ከእግዚአብሔር ጋር ሊኖረን የሚገባው ኅብረት መሰናክል እንዳይገጥመውና በአግባቡ ጸንተን እንድንኖር ይመክሩናል። የአበው ምክር እኛ ላሰብነው ዓላማ ታማኝ እንድንሆን፣ በዚች ውጣ ውረድ በበዛባት ዓለም ስንኖር ሊደርስብን በሚችለው መከራ ሳንሸነፍ በዓላማችን ጸንተን ልንደርስበት ካሰብነው ግብ መድረስ እንዳለብን ነው።

በዓላማ መጽናት ማለት ምክንያት እየፈለጉ ያቀዱትንና ሊያከናውኑት ያሰቡትን ከመተው መቆጠብ ነው። ሰዎች በዓላማቸው ሲጸኑ ዓላማቸውን ሊያሰናክል የሚመጣባቸውን መሰናክል ሁሉ ጥበበኛው ሰሎሞን “ትዕግሥት ታላቁን ኃጢአት ያስተሠርያልና የገዢ ቁጣ የተነሣብህ እንደሆነ ሥፍራህን አትልቀቅ” በማለት እንደገለጸው በትዕግሥት ያልፉታል። (መክ. ፲፣፬) የገዢ ቁጣ ከባድ ነው፤ ይሁን እንጂ በትዕግሥት ሲያልፉት ሥርየተ ኃጢአትን፣ በክብር ላይ ክብርን፣ በጸጋ ላይ ጸጋን ያጎናጽፋልና ጥበበኛው በዓላማህ ጽና፣ ስፍራህን አትልቀቅ እያለ ይመክረናል።

ሐዋርያው ያዕቆብም “መከራን የሚታገሥ ሰው ብፁዕ ነው፤ ተፈትኖ እግዚአብሔር ለሚወዱት ተስፋ ያደረገላቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና።” በማለት በዓላማ ብንጸናና የሚመጣውን መከራ ብንታግሥ ልናገኘው የምንችለውን የሕይወት አክሊል እንደሚሰጠን ያስረዳናል። (ያዕ. ፩፥፲፪)

ከዓላማ ጽናት ጋር ተያይዞ መልካም አርአያ የሚሆኑን ታሪኮች በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የተጠቀሱ ሲሆን ጥቂቶቹን እንመልከት፡-

“ጌታችን ኢየሱስም በቢታንያ በለምጻሙ በስምኦን ቤት ሳለ ዋጋው እጅግ ብዙ የሆነ ሽቱ የሞላበት የአልባስጥሮስ ብርሌ የያዘች ሴት ወደ እርሱ መጣች፤ ጌታችን ኢየሱስም በማዕድ ተቀምጦ ሳለ በራሱ ላይ አፈሰሰችው፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ ተቆጥተው እንዲህ አሉ፡፡ ይህች ሴት ይህን ያህል ሽቱ አጠፋች ይህ በብዙ ዋጋ ተሸጦ ለድኾች ምጽዋት ይሰጥ ዘንድ ይቻል ነበርና፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ዐወቀባቸውና እንዲህ አላቸው “ይህችን ሴት ለምን ታዳክሟታላችሁ ለእኔ መልካም ሥራን ሠርታልኛለችና፤ ድሆችንስ ዘወትር ታገኟቸዋላችሁ በወደዳችሁም ጊዜ በጎ ታደርጉላቸዋላችሁ፤ እኔን ግን ዘወትር የምታገኙኝ አይደለም፡፡ እርሷ ይህን በራሴ ላይ ያፈሰሰችውን ሽቱ ለቀብሬ አደረገችው፡፡ እውነት እላችኋለሁ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት ቦታ ይህች ሴት ያደረገችው ለእርሷ መታሰቢያ ሆኖ ይነገራል፡፡” (ማቴ.፳፮፥፮-፲፫)፤ (ማር.፲፬፥፫-፱)፤ (ዮሐ. ፲፪፥፩-፰)

ይህች ሴት ያሰበችውን ዓላማ ለማሳካት እጅግ የሚደንቅ ጽናት የሚታይባት ናት፡፡ የተጠራችው በክብር ነው “ኃጥኣንን ወደ ንስሓ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም” እንዲል። (ሉቃ. ፭፥፴፪) ስለዚህ ሰው ደግሞ በክብር ሲጠራ “ጠሪዬ አክባሪዬ” እንዲሉ አበው አክባሪዋን ሰማያዊውን ሙሽራ ሊያከብር የሚችል ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሽቱ ይዛ ሄደች፡፡

ይህች ሴት ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሄዷ በፊት ግን ዲያብሎስ ያዘጋጃቸውን መሰናከያ ፈተናዎችን አልፋለች፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ይህች ሴት ዘማ የነበረችና ዝሙትን መተዳደሪያዋ ያደረገች ነበረች፡፡ ውበቷና ደም ግባቷ ብዙዎችን ያንበረከከ፣ ፈላጊዋ ስፍር ቁጥር የሌለው ሆኖ ሳለ ወደ ልቧ ስትመለስ ስትሠራ የነበረው ሥራ ጸያፍና በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ የተጠላ እንደነ ተረዳች፡፡ የዘወትር መተዳደሪያዋን ዘግታ፤ ዳግም ወደ ዝሙት ሥራዋ ላለመመለስ የወሰነችው ውሳኔ ጽናቷን ያለመክታል፡፡ ዓላማና ፍላጎቷ ያንን የተጠላና ነውር የሆነውን ሥራ መተውና ወደ ፈጣሪዋ መመለስ ነበርና ወሰነች፡፡

ቀጥላ ያደረገችው ግን የሚገርም ነው፡፡ ስትፈጽመው የነበረው የዝሙት ሥራ ከእግዚአብሔር እንደለያት ስትረዳ በዝሙት ያጠራቀመችውን ገንዘብ ሰብስባ ውድ ሽቱ ገዝታ ለጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትቀባው ዘንድ ወደ ገበያ ወጣች፡፡ መውጣቷ መልካም ቢሆንም በመንገድ የጠበቃት ግን እጅግ ፈታኝ ባላጋራ ስለነበር በዓላማዋ ጸንታ ማለፍን ከእርሷ ይጠበቅ ነበር፡፡

ዲያብሎስ በለመደችው ወንድ መልክ ተገልጦ በመንገድ ጠብቆ ዝም ብሎ አላሳለፋትም፡፡ “እንግዳ ወንድ መጥቶብሽ ለእርሱ ልትቀቢው ሽቱ ልትገዢ ትሄጃለሽ?” አላት፡፡ እርሷም “አዎን፡፡ ከዚህ ዓለም ልዩ የሚሆን ጌታ መጥቷል” በማለት መለሰችለት፡፡ ዲያብሎስ በመልሷ እየተናደደ ሌላ ጥያቄ ደግሞ እንዲህ ሲል አቀረበላት “ፍቅሩ ያላለቀለት ወንድ መጥቶብሽ ለዚያ ልትቀቢው ሽቱ ልትገዢ ትሄጃለሽ?” አላት፡፡ እርሷም መልሳ “አዎን፡፡ ፍቅር ሰሐቦ ለወልድ ኃያል እመንበሩ ወአብጽሆ እስከ ለሞት፤ የሰው ፍቅር አገብሮት ሊሞት መጥቷል” ስትል መለሰች፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ተስፋ ሳይቆርጥ ”በጥቂት ገንዘብ ብዙ ገንዘብ የሚሰጥ ነጋዴ መጥቶብሽ ለእርሱ የምትቀቢው ሽቱ ልትገዢ ትሄጃለሽ?” ሲል ጠየቃት፡፡ እርሷም መልሷ “አዎን፡፡ በጥቂት ትሩፋት ብዙ ክብር የሚሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቷልና ለእርሱ የምቀባው ሽቱ ልገዛ እሄዳለሁ” ብላ ስሙን ስትጠራበት እንደ ትቢያ በኖ፣ እንደ ጢስ ተኖ ጠፍቶላታል፡፡

ዲያብሎስ ከአንድም ሦስት ጊዜ ሊያሰናክላት ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን ዓላማዋ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት፣ በፊቱም መንበርከክና ስለ ኃጢአቷ እያለቀሰች ሽቱውን ትቀባው ዘንድ ነውና ዲያብሎስ ያቀረበላትን የማሰናከያ መንገዶችን ሁሉ በዓላማዋ በመጽናት በአምላኳ በጌታዋ ስም ድል ነሳችው፡፡

ስጦታውንም ስንመለከት ውድ የሚያደርገው ከእሷ ጥረትና ቅንነት አንጻር እንጂ ለጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህ የሚመጥን ሆኖ አይደለም፡፡ ዙፋኑ እንኳ በሰማያውያን ሱራፌል በሰማያዊው ማዕጠንት የሚታጠን ጌታ ምድራዊ ሽቱ እንዴት ሊመጥነው ይችላል? ሊሆንም አይችልም፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ከምስጋና የማይለዩ ንጹሐን፣ ቅዱሳን፣ ትጉኃንና ሰማያውያን መላእክት በሚያቀርቡት ሰማያዊ ሽቱ የሚታጠን አምላክ ዕድሜ ዘመኗን በሙሉ በዝሙት የኖረች ሴት በምታቀርበው ሽቱ ለዚያውም በዝሙት በተሰበሰበ ብር በተገዛ ሽቱ እንዴት ሊወሰን ይችላል?  ግን እሷ መሐሪነቱን ተረድታለች፤ የኃጢአተኛን መመለሱን እንጂ ሞቱን የማይሻ ቸርና ይቅር ባይ አምላክ እንደሆነ ዐውቃለች፤ የዛሬ መመለሷን እንጂ የትናንትና ማንነቷን እየተመለከተ እሷን የማያሸማቅቅ ይልቁንም ቸር አባት እንደሆነ አምናለች ፡፡ ስለዚህ አደረገችው፤ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የአመጣችለትን ሽቱ ደስ ብሎት ተቀበላት፡፡

እጅግ የሚገርመው ግን እሷ ያልተቆጨችበትን ውድ ሽቱ ተመልካቾችን አላስደሰታቸውም ነበር፡፡ ይህ እኮ ተሸጦ ለድኾች ቢሰጥ ይቻል ነበር በማለት አጉል ተቆርቋሪ መሰሉ፡፡ ግን ለምን ተቃወሟት የሚለውን በተወሰነ መንገድ ማየቱ የተሻለ ነው፡፡ ከተቃዋሚዎች አንዱና ዋነኛው ይሁዳ ነበር፡፡ ይሁዳ ደግሞ በዚያን ሰዓት ገንዘብ ቤት ነበርና ወደ ከረጢቱ ከሚገባው ሁሉ ከዐሥር አንድ ይደርሰው ነበር፡፡ ሽቶው የተገዛበት ዋጋ ሦስት መቶ ወቄት ወርቅ ነው፡፡ ስለዚህ ሠላሳ ወቄት ወርቅ ይደርሰው ነበር ግን ስጦታው በብር ሳይሆን በዓይነት ስለቀረበ ያን ድርሻ ማግኘት አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ለድኾች ያዘነ በመምሰል ለሱ የቀረበትን ድርሻ እያሰላሰለ ተቃውሞውን አቅርቧል፡፡

ጊዜው መልካም ነገር የሚደረግበት፣ ሰዎች ከኃጢአት ወደ ሥርየት የሚመለሱበት፣ ለበጎ ሥራ የሚነሳሱበት ነበር፡፡ በአንጻሩ ደግሞ መንፈሳዊውን ቅናት የሚያደበዝዝና ተስፋ የሚያስቆርጥ፣ ተቃውሞ የበዛበትና ሰይጣናዊው ቅናት የሰፈነበትም ነበር፡፡ በመሆኑም እግዚአብሔር የፈቀደላቸው ያላቸውን ሁሉ የሚሰጡበት፣ ለገንዘባቸው ቀርቶ ለሰውነታቸው የማይሳሱበት፣ በአንጻሩ ደግሞ ሰዎች ስለ ሰጡ የሚናደዱበት “ነጋዴ አያዝንም እሱ ስለ ከሰረ ወንድሙ እንጂ ስለ ቀረ” እንዲሉ ይህ ዓይነት ከንቱ ምኞት የሰፈነበት ነበርና በጎ በሚያደርጉት ላይ ተቃዋሚዎች በዝተው ነበር፡፡ መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሁሉን አዋቂ ነው ምን ለምን እንደሚሆን ያውቃልና በመሆኑም አክብሮ ተቀበላት። ነገር ግን ሰዎች ሲቃወሙ እሱ እንዲህ አክብሮ የተቀበለበት ምክንያት ምን ይሆን ስንል የሚከተሉትን ምክንያቶች ማየት ይቻላል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ እርሱ የሚገኘው በዚያ ዕለት ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ “ድሆችንስ ዘወትር ታገኟቸዋላችሁ በወደዳችሁም ጊዜ በጎ ታደርጉላቸዋላችሁ እኔን ግን ዘወትር የምታገኙኝ አይደለም፡፡” በማለት እንደተናገረው በአካለ ሥጋ ሆኖ ሽቱ የሚረበረብለት የሚጨበጥ የሚዳሰስ ሆኖ የምታገኝበት ጊዜ ያን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ከዚያ በኋላ ከሥጋው ይለያል ማለት አይደለም፡፡ በአይሁድ እጅ ተይዞ ወደ ፍርድ የሚቀርብበት፣ ወደ መስቀል የሚወጣበት ጊዜ እንደ ደረሰና እሷ የማታገኝበት ቀን እንደሚመጣ ለማመልከት ነው፡፡

በሁለተኛ ደረጃ እሷ ወጣኒ ናትና እንዳትሰናከል ነው፡፡ በጀማሪነት ደረጃ ያለን ሰው የሚያስተምሩትን ሊመጥኑለት፣ ምን ማድረግ እንደሚገባ የቅደም ተከተል ጉዳይ ላይ ማተኮር እንደሚገባ፣ ቀስ እያለ ወደ ምን መሄድ እንዳለበት ሲያስተምር ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስትና ቀስ በቀስ የሚለማመዱት ሕይወት ነውና፡፡ ብርሃነ ዓለም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞቼ ሆይ እኔስ የሥጋና የደም እንደ መሆናችሁ ክርስቶስንም በማመን ሕፃናት እንደ መሆናችሁ እንጂ እንደ መንፈሳውያን ላስተምራችሁ አልቻልሁም፤ ወተትን ጋትኋችሁ ጽኑዕ መብልም ያበላኋችሁ አይደለም፤ ገና አልጠነከራችሁና፡፡” (፩ቆሮ ፫፥፩-፪) በማለት እንዳስተማረን በጀማሪነት ያለን ሰው በለመደው፣ በሚችለውና በሚወደው ነገር መሳብ ተገቢ ስለሆነ ሰማያዊው ሙሽራ ኢየሱስ ክርስቶስም የአመጣችውን ስጦታ በደስታና በአክብሮት ተቀበላት፡፡

በሦስተኛ ደረጃ አንድ ሰው ቀድሞ ምን ማድረግ እንዳለበት የሚያማክር ከሆነ እዲህ አድርግ ሊሉት ይገባል ከሆነ በኋላ ግን እንዲህ ማለት ያሰናክላልና ተዉዋት አላቸው፡፡ ተዉዋት ብቻም አይደል ያላቸው ለምን ታሰናክሏታላችሁ ነበር ያላቸው፡፡ ይህም ማለት በትርጓሜ ወንጌል እንደተጻፈው አንድ ሰው ምጽዋት መስጠት ቢፈልግና ለቤተ ክርስቲያን ልስጥ ወይስ ለነዳያን ልስጥ ብሎ ቢያማክር ሕንፃ እግዚአብሔር የሆነው የሰው ልጅ በርኀብ በጥም እየተሠቃየ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ገንባ ከማለት ቅድሚያ ለሰው ልጅ መስጠት እንዳለበት ማስገንዘብ ይገባል፡፡ ሰውየው በራሱ ተነሳሽነት ካደረገው በኋላ ግን እንዲህ ማድረግ አልነበረብህም ቢሉት ጭራሽ በጎ ሥራ በመሥራቱም ተጸጽቶ ለወደፊቱም መልካም ነገርን ከማድረግ ሊቆጠብ ስለሚችል የሠራውን መልካም ሥራ ጥሩ እንዳደረገ ማበረታታት ይገባል፡፡ እንግዲህ ይህን ሁሉ ምሥጢር የሚያውቀው ማዕምረ ኅቡአት ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣለትን ክቡር ስጦታ አክብሮ ተቀብሏል፡፡

ከማርያም እንተ እፍረት የምንማራቸው በርካታ ቁም ነገሮች አሉን፡፡ እነርሱም፡- ለበጎ ነገር መሽቀዳደምን፣ የዓላማ ጽናትን ይልቁንም ለንስሓ መዘናጋት እንደሌለብን መረዳት እንችላለን፡፡ ትርጓሜ ወንጌል እንደሚነግረን ማርያም እንተ እፍረት ይህ ቀረሽ የማትባል መልከ መልካም ነበረች፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን መላ ሰውነቷን በሚያሳይ በቁም መስተዋት ራሷን እየተመለከተች ግን ያን የሚመስል ውበት እንደሚያልፍ እንደሚረግፍ ተረዳች፡፡ ለዚህ መድኃኒቱ ደግሞ ንስሓ መግባት እንደ ሆነ ተረዳችና ዘመኗን ሙሉ በዝሙት የአጠራቀመችውን ገንዘብ በመያዝ ሥርየትን ለሚያድለው፣ ኃጢአትህ/ሽ ተሰርዮልሃል/ሻል ለሚለው ሊቀ ካህናት መድኅን ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገባውን ሽቱ ገዝታ ወደ እሱ ሄደችና ማድረግ የሚገባትን አደረገች፡፡

ማርያም እንተ እፍረት ወደ ልቧ በተመለሰች ጊዜ ሳትውል ሳታድር ፈጥና ነው ንስሓን ወደሚቀበለው ሊቀ ካህናት የሄደችው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በመንገድ ላይ የዲያብሎስን ፈተና በድል ብትወጣውም ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደረሰችም በኋላ በደቀ መዛሙርቱ በተለም በአስቆርቱ ይሁዳ መሰናክሎች ገጥመዋታል፡፡

ከደቀ መዘሙርቱ መካከል አዛኝ ለድሆች በጎ አሳቢ በመምሰል ይህ ተሸጦ ለድሆች ሊሰጥ በተገባ ነበር በማለት ያደረገችውን ሥራ እንደ ጥፋት ቆጥረውት ነበር፡፡ ነገር ግን በፈጣሪዋ ፊት ተንበርክካለችና የዓላማዋን ጽናት፣ የልቧን መሻት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አውቋልና እርሷ ሳትሆን ስለ እርሷ ክርስቶስ “መልካም አደረገች ለምን ታሰናክሏታላችሁ” በማለት ሥራዋን አደነቀላት፡፡ እንዲያውም ይህ የእሷ ሥራ በአራቱም ወንጌላውያን ሲነገር እንደሚኖር በመግለጽ አስረዳቸው፡፡ ማሰናከያዎቹንም ሁሉ አስወገደላት፡፡

ስለዚህ እኛም ወደ መልካም ነገር ስንሄድ በየመንገዱ እየጠበቀ ለዚያውም በምናውቀውና በምንወደው አካል ዲያብሎስ እያደረ እንዳያሰናክለን ትጥቃችንን ልናጠብቅ፣ በዓላማችንም ልንጸና ይገባል፡፡

በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ በዓላማቸው ጸንተው በእግዚአብሔር የተመሰከረላቸው፣ በክብር ላይ ክብር የታደላቸው፣ በርካታ ሰዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ዮሴፍ በምድረ ግብፅ ያውም በስደት ላይ ሳለ በዓላማው በመጽናቱና በወጣትነት ዘመን እያለ እንኳን የወጣትነት ስሜት ሳያሸንፈው በፈርዖን ሚስት የቀረበለትን የዝሙት ጥያቄ ሳያመነታ በድል ተወጥቶታል፤ በንጉሡ ፈርዖን ዘንድም እንዲከበር፣ ቤተሰቦቹን ከነበረው ረኀብ እንዲታደግ ዛሬም ሕያውና ዘለዓለማዊ ስም ከፈጣሪው ዘንድ ተሰጥቶት በመልካም አርዓያነቱ ስንጠራው እንኖራለን። ይህ ማለት ግን መከራውን በትዕግሥት አልፎት እንጂ ምንም ዓይነት ፈተና ሳይገጥመው ስለ ኖረ አልነበረም።

ሌላው በዓላማ ስለ መጽናት ከሚያስገነዝቡን ታሪኮች መካከል የፃድቁ የኢዮብ ሕይወት ነው፡፡ ዲያብሎስ ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር አስጥሎ ልጆቹን በሞት፣ ሀብት ንብረቱን በማውደም፣ እርሱንም ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ በደዌ ቢመታም፤ ሚስቱንና ወዳጆቹን ቢያስነሳበትም እግዚአብሔርን ረግሞ እንዲሞት ቢገፋፉትም በዓላማው በመጽናት “እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን” በማለት ከዲያብሎስ ወጥመድ አምልጧል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ባለ ታሪኮችና ታሪካቸውን ጠቀስን እንጂ ጌታችን መድኀኒታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም  ወደዚህ ምድር የመጣበት ዋናው ዓላማ የሰውን ልጅ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመስና የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲሆን በሥጋው በዲያብሎስ ተፈትኗል፡፡ ዲያብሎስ ሦስት ዋና ዋና ፈተናዎችንም አቅርቦለታል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድረ በዳ ሄዶ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጾመና ከጸለየ በኋላ ተራበ፡፡ የሚፈታተነውም ዲያብሎስ ቀርቦ “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ እነዚህን ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልሶ ሰው የሚኖረው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ እንዳይደለ ተጽፏል፡፡” በማለት ድል ነስቶታል፡፡ ነገር ግን ዲያብሎስ ስልቱን በመቀየር በሌላ ፈተና ደግሞ መጣበት፡፡ ወደ ቅድስት ከተማ ወስዶ በቤተ መቅደሱ ጫፍ ላይ አቁሞት “አንተ በእውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህስ ከዚህ መር ብለህ ወደ ታች ውረድ ይጠብቁህ ዘንድ ስለ አንተ መላእክቱን ያዝዝልሃል፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰነካከል በእጃቸው ያነሱሃል ተብሎ ተጽፏልና” አለው፡፡ ጌታችንም “አምላክህ እግዚአብሔርን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፏል” ሲል ድል ነሣው፡፡ ዲያብሎስ ለሦስተኛ ጊዜ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ አውጥቶት “የዓለሙን ሁሉ መንግሥታት ክብራቸውንም ሁሉ አሳየው፡፡ ብትሰግድልኝ እጅ ብትነሳኝም ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን ከአጠገቤ ሂድ ለጌታህ ለእግዚአብሔር ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፋል” አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ዲያብሎስ ተወው እነሆም መላእክት ሊያገለግሉት መጡ ይለናል መጽሐፍ ቅዱስ፡፡ (ማቴ.፬፥፩-፲፩)፡፡

ዛሬም እኛ በእግዚአብሔር ቸርነት ፈተናውን ሁሉ እናልፋለን እንጂ ሰው በራሱ ምንም ማድረግ እንደማይችል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ በመዋዕለ ሥጋዌው ሳለ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና” ብሎ እንዳስተማረን ፈተናውን ያርቅልን ዘንድ እየተማጸንን በሥራም እየገለጥን እርሱን መስለን ልንኖር ይገባናል፡፡ እንደ ቃሉ ተመላልሰን፣ የሚፈታተነን ዲያብሎስ በመንፈሳዊ ጦር ማለትም በጾም፣ በጸሎት እና በስግደት እንዲሁም መንፈሳዊ ትሩፋትን በመሥራት ንስሓ ገብተን እግዚአብሔር አምላካችንም ንስሓችንን ተቀብሎ መሰናክሎችን ሁሉ የምናልፍበትን ኃይል እንደሚሰጠን አምነን እስከ መጨረሻው በዓላማችን ጸንተን መንግሥቱን እንወርስ ዘንድ መበርታት ይገባናል፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዳሳን ቃል ኪዳንና በረከት አይለየን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *