የዘይቱ ነገር

አንድ ሰው በጣም የሚወደው ልጅ ነበረው፡፡ ለዚህ ልጁ ሕይወትን ሃይማኖትን ከምግባር አስተባብሮ እንዴት መኖር እንደሚችል ሊያስተምረው ይጥር ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙም የተሳካለት አልመሰለውም፡፡ ልጁ በፊቱ የመጣለትን ነገር በማድረግ የሚነዳና ምንም አይነት መንፈሳዊነትና ጥበብ የሞላው ሕይወት እንዳላዳበረ ገባው፡ በአካባቢው በጥበቡ የታወቀ አንድ አባት ነበረና የሕይወት ጥበብ እንዲማር ወደዚያ ጠቢብ አባት ላከው፡፡

ልጁ ወደጠቢቡ አባት በመሄድ እንዲህ አለው፣ “ሕይወቴን መንፈሳዊነትና ጥበብ በተሞላው ሁኔታ እንዴት መምራት እንዳለብኝ ለመማር ነው የመጣሁት”፡፡ ጠቢቡ “አሁን ትንሽ ስራ አለብኝ ፣ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ቆይተህ ተመለስ፡፡ እስከዚያው ግን አንድን ነገር እንድታደርግ ስራ ልስጥህ” በማለት፣ በእጁ አንድን የሻይ ማንኪያ ሰጠውና በማንኪያው ላይ ዘይትን ሞላበት፡፡ ከዚያም እንዲህ አለው ፣ “በቤተክርስቲያን ውስጥ እየተዘዋወርክ ያሉትን ድንቅ ቅርሶች በመመልከት ሁለት መጠበቅ ያለብህን ሰዓታት አሳልፍ፡፡ አንድ ነገር ግን ተጠንቀቅ፣ በፍጹም ይህ በማንኪያው ላይ ያለው ዘይት መፍሰስ የለበትም”፡፡ ልጁ አደራውን ተቀብሎ፣ ስንት ሰዓት እንደሆነ ከቃኘ በኋላ ቤተክርስቲያኑን ለመጎብኘት በእጁ ዘይት የሞላበትን ማንኪያ ይዞ በቀስታ በመራመድ ወጣ፡፡

ልጁ ከሁለት ሰዓት በኋላ ወደ ጠቢቡ አባት ተመለሰ፡፡ ጠቢቡ ካስገባው በኋላ ፣ “በቤተክርስቲያኑ ውስጥ በግድግዳው ላይ የተሰቀለውን የጥንት ስእል አየኸው? የታወቁ የገዳሙ አባቶች አስር ዓመት የፈጀባቸውን የአትክልት ስፍራ አየኸው? የዓለምን እውቀት በሙሉ የያዘውንስ የመጽሐፍት ቤት አየኸው?” ልጁ አፍሮ አንገቱን አቀረቀረ፡፡ ለካ ለሁለት ሰዓታት ሲዘዋወር ትኩረቱ ሁሉ በእጁ የያዘው ማንኪያ ላይ የተቀመጠው ዘይት እንዳይፈስ ነበር፡፡ ጠቢቡ ሊያስተምረው የፈለገው ነገር እንደተሳካለት ገባውና፣ “እንደገና በማንኪያ ያለውን ዘይት ይዘህ ሂድና እነዚህ የነገርኩህንና ሌሎችም አስገራሚ ቅርሶች እንደገና ተመልክተህ ተመለስ” አለው፡፡

ሁለተኛ እድል ስላገኘ ትንሽ ተንፈስ ያለው ወጣት ተመልሶ ወጣ፡፡ ለሁለት ሰዓታት ጉብኙቱን ካጧጧፈ በኋላ በፈገግታ ተመለሰና ያየውን ሁሉ ለጠቢቡ ነገረው፡፡ እስኪጨርስ ጠብቆ ጠቢቡ፣ “እንዳይፈስስ ያልኩህ ዘይት የት አለ?” አለው፡፡ ልጁ፣ ጎንበስ ብሎ በእጁ የያዘውን ማንኪያ ሲያየው ለካ ዙሪያውን በመመልከት ሲደነቅ ዘይቱን ችላ ስላለው ዘይቱ ሙልጭ ብሎ ፈስሷል፡፡ ጠቢቡ አባትም እንዲህ አለው፣ “ስኬታማ ሕይወት ማለት እምነትና ምግባር የተሞላውን ሕይወት መኖር ማለት ነው፡፡

እምነትና ጥበብ የተሞላበት ሕይወት ማለት ዙሪያህን እያየህ በማድነቅ ስትኖር በእጅህ ላይ ያለውን አደራ አለመዘንጋት ነው”፡፡ በሕይወታችን ልክ እንደ ዘይቱ በጥንቃቄ መያዝ ያለብን አደራዎች አሉን፡፡ ከዚያው ጋር ደግሞ ልክ በቤተክርስቲያኑ ውስጥ እንዳሉት አስደሳች ጥንታዊ ቦታዎች የመደሰትን እድል የሚሰጡን ሁኔታዎች አሉ፡፡ እውነተኛ ሰው እነዚህን ሁለቱን በሚዛናዊነት የያዘ ሰው ነው፡፡

ስንጫወት ፣ ስንዝናና ፣ ስንደሰትና በማሕበራዊው ግንኙነታችን ውስጥ ያለውን ደስ የሚያሰኝ ሁኔታ ስንፈነድቅበት ፣ ከዚያ የተነሳ በእጃችን ላይ ያለው አደራ ችላ እንዳይባልና ዘይቱ እንዳይፈስ መጠንቀቅ የጥበብ ሁሉ ጥበብ ነው፡፡ ልክ ይህ ወጣት በእጁ ያለውን ዘይት በዙሪያው ካለው ታላላቅ ነገርን የማየት እድል ጋር አስታርቆና ሚዛናዊ አድርጎ መውጣትና መግባት እንደነበረበት እኛም እንዲሁ! በዙሪያችን ካለው ጨዋታና መዝናናት ብዛት የተነሳ የተለመዱ ችላ በማለት ማፍሰስ የማይገቡን የአደራ “ዘይቶች” . . .

” ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።”

†የማቴዎስ ወንጌል 25:4†

ምንጭ-ቬነሲያ ገጽ

ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ

ቅዱስ ያሬድ ውልደትና እድገቱ ኢትዮጵያ ወስጥ ፤ አክሱም ከተማ ከአባቱ ከአብዩድና ከእናቱ ታውክሊያ ነው ፤ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ እናቱ መምህር ወደ ሆነው አጎቱ አባ ጌዲዬን ትወስደዋለች፡፡ እርሱ ግን በመጀመሪያ ትምህርት ሊገባው አልቻለም፡፡ ከዕለታት በአንድ ቀን መምህር ጌዲዬን ያሬድን ሲገርፈው በምሬት አለቀሰ ፤ ማይኪራህ ወደምትባል ቦታም ተጓዝ፤ በመንገድ ላይ ሳለ ውሃ ስለጠማ በዚያች ስፍራ ካለ ምንጭ ውሃ ጠጥቶ በዛፉ ሥር ለማረፍ ቁጭ አለ፤ ወደ ላይም በሚመለከትበት ጊዜ ከዛፉ ላይ አንዲት ትል ከታች ወደ ላይ ስትወጣ ስትወርድ ተመለከተ፡፡ እርሱም ትኩር ብሎ አያት ፤ ትሏም ያለመሰልቸት ከወጣች ከወረደች በኋላ ዛፉ ላይ መድረስ ቻለች፡፡
በዚያን ወቅት ቅዱስ ያሬድ አሰበ ፤ እንዲህም አለ፤ «ይህች ትል ዛፉ ላይ ለመድረስ እንዲህ ከተጋች እኔም ትምህርት ለመማር ብታጋ እግዚአብሔር አምላክ ይገልጽልኛል»፡፡ ወደ ጉባኤው ተመልሶ መምህሩን ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ መማር ጀመረ ፤ እግዚአብሔር አምላክም የ፹፤፩ መጽሐፍትንና የሊቃውንት መጽሐፍትን እንዲሁም ሌሎች ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን የቅዱሳት መጻሕፍትን ምሥጢር ገለጸለት ፤ መምህር ጌዲዬን ሲሞት የእርሱን ቦታ ተረክቦ ማሰተማር ቀጠለ፡፡
በ534 ዓ.ም. ኅዳር 6 ቀን ፤ ወደ ሰማይ ተመነጠቀ፤ በሰማይ ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን ልዩ በሆነ ጣዕመ ዝማሬ ሲያመሰግኑ ሰማ፡፡ ወደ ምድርም በተመለሰ ጊዜ አክሱም ጽዮን ውስጥ ወደ ምስራቅ በኩል በመዞር ከሰማይ የሰማውን ዝማሬ ዘመረ፤ አርያም ብሎም ሰየመው፡፡ በዚሁም በ538 ዓ.ም. ቅዱስ ያሬድ ማኅሌትን ጀመረ፡፡ ታህሳስ 1 ፤ በዕለተ ሰኞ ምህላ ያዘ ፤ እሰከ ታህሳስ 6 ፤ ቀዳሚት ሰንበት ድረስም ዘለቀ ፤ በዚያች ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል አንደተሰቀለ ሆነ ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገለጸለት፡፡
ቅዱስ ያሬድም ጌታ የተገለጸለትን የመጀመሪያውን ሳምንት ‹ስብከት› ብሎ ሰየመው ፤ በሳምንቱም እንደገና በብርሃን አምሳል ስለተገለጸለት ያን ዕለት ‹ብርሃን› ብሎ ሰየመው፤ በሶስተኛው ሳምንት እንዲሁ በአምሳለ ኖላዊ ስለተገለጸለት ‹ኖላዊ› ብሎ ሰየመው፤ በመጨረሻም ሳምንት በአምሳለ መርዓዊ ሲገለጽለት ዕለቱን ‹መረዓዊ› ብሎ ሰይሞታል፡፡
ከዚህም በኋላ ቅዱስ ያሬድ 5 የዜማ መጻሕፍትን ደረሰ ፤ እነዚህም ድጓ ፤ ጾመ ድጓ ፤ ምዕራፍ ፤ ዝማሬና መዋሥዕት ናቸው፡፡ ከደረሳቸው የዜማ መጻሕፍትም ውስጥ ትልቁ ድጓ ነው ፤ በሦስትም ይከፈላል ፤ ዮሐንስ፤ አስተምህሮና ፋሲካም ይባላሉ፡፡በንባባት ብቻ ይቀደስባቸው የነበሩትን ፲፬ቱ ቅዳሴያት በዜማ የደረሳቸው ቅዱስ ያሬድ ነው፤ ዝማሬም በ5 ይከፈላል ፡ ኅብስት ፡ ጽዋዕ ፡መንፈስ ፡ አኮቴትና ምሥጢር ይባላል፡፡
ይህ ቅዱስ ደራሲ በተወለደ በ75 ዓመቱ በሰሜን ተራራ ውስጥ ደብረ ሐዊ ከሚባል ገዳም ግንቦት 11 ቀን ተሠውሯል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ ቅዱስ ያሬድ መምህር ወሐዋርያ ፤ መጻሕፍትን በጣዕመ ዜማ የደረሰ ፤ መዝሙረ ዳዊትን ጨምሮ ሌሎችንም ቅዱሳት መጻሕፍትን በዜማው ያመሠጠረ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነው፡፡

እብድ መነኲሲት

ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ውለታና ፍቅር ራሷን እብድ  ያደረገችው መነኲሲት

ቅዱስ ጳኩሚስ ከመሠረታቸው የታቤኔዝ (ታቤኔሲዮት) ገዳማት መካከል ከወንዶች ገዳማት ራቅ ብሎ የተመሠረተ የሴቶች ገዳም ነበር። በዚያም ውስጥ አራት መቶ ሴቶች መነኮሳይያት ይኖሩ ነበር። በዚያ ገዳም ውስጥ ራሷን እንዳበደችና ርኲስ መንፈስ እንደያዛት የምታስመስል ድንግል ሴት ነበረች።

ሌሎቹ እርሷን ከመጸየፋቸው የተነሣ አብረዋት እንኳን አይበሉም ነበር ፤ እርሷ ግን ይህን ወደደችው። በምግብ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ወዲያ እና ወዲህ ትንከራተታለች፣ ሌሎች የተዉትንና የተናቀውን ማንኛውም ሥራ ትሠራለች፣ እነርሱ እንደሚሉት “የገዳሙ ቆሻሻ አስወጋጅ” ነበረች።

በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ከእህቶች መነኮሳይያት መካከል ማንም በአፏ ስታላምጥ አይተዋት አያውቁም፣ በማዕድም ተቀምጣ አታውቅም ነበር። ከማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪና የማዕድ ቤት እቃዎችን ስታጥብ ከዚያ በሚገኘው ነገር ብቻ ትኖር ነበር። ማንንም ተሳድባ ወይም ትንሽም ሆነ ብዙ አውርታ አታውቅም፤ ምንም እንኳ ብዙ ትሰደብ፣ ትነቀፍና ትረገም የነበረች ብትሆንም።

የእግዚአብሔር መልአክ ፒተሮአም ለሚባል ታላቅና ታዋቂ ለነበረ ታላቅ ባሕታዊ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “እንዲህ ባለ ቦታ ስለመኖርህና ስለ ሃይማኖተኛነትህ ለምን በራስህ ትመካለህ? ከአንተ የበለጠ ሃይማኖተኛና ፍጹም የሆነችን ሴት ማየት ትፈልጋለህ? ወደ ታቤኔሲዮት ገዳም ሴቶች ሂድ በዚያም በራሷ ዘውድ የደፋች ሴት ታገኛለህ። እርሷ ከአንተ የበለጠች ናት፤ በብዙዎች መካከል ብትሆንም ልቧ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር ውጪ እንዲሄድ ፈጽሞ ፈቅዳለት አታውቅምና፣ አንተ ግን እዚህ ተቀምጠህ በሃሳብ በተለያዩ ቦታዎች ትዞራለህና” አለው።

ይህን ሲሰማ ከበኣቱ ወጥቶ የማያውቅ የነበረው ባሕታዊ ወደዚያ ገዳም ሄደና ወደ ገዳሙ ለመግባት ጠየቀ። የታወቀና በዕድሜው የገፋ አረጋዊ ባሕታዊ ስለነበር ወደ ሴቶቹ ገዳም እንዲገባ ፈቀዱለት። በዚያም ሁሉንም መነኮሳይያት ያያቸው ዘንድ ጠየቀ። ሆኖም እርሷ አልመጣችም። በመጨረሻም፦ “የቀረች አንዲት አለችና ሁሉንም አምጡልኝ” አላቸው።

እነርሱም፦ “በማዕድ ማዘጋጃ ቤት ያለች አንዲት እብድ ብቻ ናት የቀረችው” አሉት። እርሱም፦ “እርሷንም ጭምር አምጡልኝና ልያት” አላቸው። ሊጠሯት ሄዱ እርሷ ግን ነገሩን አውቃው ይሁን ወይም ጉዳዩ ተገልጦላት መልስ አልሰጠቻቸውም።

በግድ ጎተቷትና፦ “ታላቁ ፒተሮአም ሊያይሽ ይፈልጋል” አሏት። በመጣች ጊዜ ከራሷ ላይ ያለውን ብጣሽ ጨርቅ አሰበና ከእግሯ ላይ ወድቆ “ባርኪኝ” አላት። እርሷም እንዲሁ ከእግሩ ላይ ወድቃ “አባቴ ሆይ አንተ ባርከኝ” አለችው። ሁሉም መነኮሳይያት ተገረሙና፦ “አባ እንዳትሰድብህ ተጠንቀቅ እብድ ናት” አሉት። አባ ፒተሮአምም ሁሉንም፦ “እብዶችስ እናንተ ናችሁ እርሷ ግን የእኔም የእናንተም እናት ናት። በፍርድ ቀንም እንደርሷ የተዘጋጀሁና የተገባሁ ሆኜ እገኝ ዘንድ ምኞቴ ነው” አላቸው።

እነዚህን ነገሮች ከዚህ አባት ሲሰሙ ሁሉም ያደረጉባትን ነገር እየተናዘዙ ከእግሩ ላይ ወደቁ። አንዲቱ የውኃ እጣቢ አፍስሼባታለሁ ትላለች፣ ሌላዋ ደግሞ መትቻታለሁ ትላለች፣ ብቻ ብዙዎች አንዷ አንድ ሌላዋ ደግሞ ሌላ ነገር እንደፈጸሙባት በመናገር ይናዘዙ ጀመር። እርሱም ከጸለየላቸው በኋላ ሄደ።

ከጥቂት ቀናት በኋላ በእህቶቿ መነኮሳይያት የሚደረግላትን ክብር መሸከም ስለከበዳት እንዲሁም ፊት በበደሏት ነገር ሁሉ ይቅርታ አድርጊልን የሚሉት ነገራቸው ስለበዛባት ገዳሙን ጥላ ጠፋች። ወዴት እንደሄደችም ሆነ የት እንደተሰወረች ወይም እንዴት እንደሞተች ግን ማንም ያወቀ የለም።

በረከቷ ይደርብን!

በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ

አንፀባራቂና የደስታ በዓል

እግዚአብሔርን የሚያምንና የሚወድ ቢኖር ፥ እርሱ በዚህ አንፀባራቂና የደስታ በዓል ደስ ይበለው፡፡ ብልህ አገልጋይ ቢኖር ፥ እርሱ ወደ ጌታው ሐሴት ገብቶ እልል ይበል፡፡ በጾም የደከመ ቢኖር፥ አሁን ደመወዙን ይቀበል፡፡ በመጀመሪያው ሰዓት ወደ አምላኩ የቀረበ ቢኖር ፥ ዛሬ ሽልማቱን ይውሰድ፡፡

በሦስተኛው ሰዓት የመጣ ቢኖር ፥ እርሱ በዓሉን በምስጋና ያክብር፡፡  በስድስተኛው ሰዓት የደረሰ ቢኖር ፥ አይጎድልበትምና አይጠራጠር፡፡ እስከ ዘጠነኛ ሰዓት የዘገየ ቢኖር ፥ ሳይጠራጠር ይቅረብ፡፡ እስከ ዐሥራ አንደኛዋ ሰዓት የዘገየ ቢኖር፥ ስለ መዘግየቱ አይደንግጥ፡፡ ጌታ ቸር ነውና ፤ በመጨረሻ የመጣውንም እንደ መጀመሪያው አድርጐ ይቀበሏልና፡፡ በዐሥራ አንደኛው ሰዓት ለመጣው ከመጀመሪያው ሰዓት አንሥቶ ሲደክም ከነበረው ጋራ እኩል ይሰጧልና። መጨረሻ ለመጣው ጌታ ምሕረቱን ይለግሰዋል፤ መጀመሪያ ለመጣውም ያስብለታል፡፡ ለአንደኛው ይሰጠዋል፤ ለሌላኛውም ጸጋውን ያድለዋል፡፡ ለአንደኛው መልካም ምግባሩን ይቀበልለታል፡፡ ለሌላኛውም መልካም ፍቃዱን ይቀበልለታል፡፡ ለአንዱ ምግባሩን ያከብርለታል፤ ለሌላኛውም በቅን ልቡና የሚያደርገውን ጥረት ያደንቅለታል፡፡ ስለዚህ ኹላችሁም ወደ ጌታችሁ ደስታ ግቡ፡፡

ፊተኞች ኋለኞችም ሆይ! እኩል ደመወዛችሁን ተቀበሉ፡፡ ባለጸጐች ድኾችም ሆይ! በአንድነት ዘምሩ፡፡ እናንተ ብርቱዎች ደካሞችም ሆይ! በዓሉን አክብሩት፡፡ እናንተ የጾማችሁ መጾም ያልቻላችሁም ሆይ! ዛሬ ላይ ደስ ይበላችሁ፡፡መሠዊያው ሙሉ ነውና ኹሉም በማዕዱ ደስ ይበለው፡፡ ፍሪዳው የሰባ ነውና አንድ ሰው ስንኳ እንደ ተራበ እንዳይሔድ፡፡ ኹላችንም የእምነት በዓሉን እንካፈል፤ ከቸርነቱና ከፍቅሩ ሀብትም እንቋደስ፡፡

ማንም ስለ ድኽነቱ አይዘን ፥ ኵላዊቷ መንግሥት ተገልጣለችና፡፡ ማንም በኃጢአቱ አያንባ፥ ከመቃብሩ የይቅርታ ብርሃን ተንቦግቧልና፡፡ ማንም ሞትን አይፍራ፥ የመድኃኒታችን ሞት ከዚህ ነጻ አውጥቶናልና፡፡ ለእርስዋ  በመታዘዝም ጌታ አጥፍቷታልና፡፡ በሞቱ ሞትን ገደለው፡፡ ወደ ሲዖል በመውረድ ሲዖልን በዘበዘው፡፡

ኢሳይያስም አሰምቶ እንደ ተናገረ ሲዖል ከጌታችን ጋር ፊት ለፊት ተገናኘች ፤ መረራትም! ከንቱ አድርጓታልና መረራት! ሸንግሏታልና መረራት! ሽሯታልና መረራት! ነፍሳትን ይዛ እንዳታስቀር አስሯታልና መረራት! [መቃብር የዕሩቅ ብእሲ] ሥጋ አገኘሁ ብላ ዋጠችው ፤ ስትውጠው ግን እግዚአብሔር ኾኖ አገኘችው – መረራትም!

ሞት ሆይ! መውጊያህ ወዴት አለ? ሲዖል፥ መቃብርም ሆይ! ድል መንሣትህ ይዞም ማስቀረትህ ወዴት አለ?

ክርስቶስ ተነሣ፤ ሞት ሆይ፥ አንተም ጠፋህ!

ክርስቶስ ተነሣ፣ አጋንንትም አዘኑ!

ክርስቶስ ተነሣ፤ መላእክትም ሐሴት አደረጉ!

ክርስቶስ ተነሣ፤ የሰው ሕይወትም ነጻ ወጣች!

ክርስቶስ ተነሣ፤ መቃብርም ባዶ ኾነች!

ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ለአንቀላፉት ኹሉ በኵር ኾኖላቸዋልና፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

ምንጭ-@beteafework