እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ስቅለቱ መታሰቢያ በዓል አደረሳችኹ።

ጥቅምት ሃያ ሰባት በዚህች ዕለት የአምላካችን የመድኃኔዓለም የስቅለቱ መታሰቢያ ነው። መድኃኒታችን ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና በቸርነቱ ስለኹላችን ድኅነት ሲል ራሱን ወድዶ ፈቅዶ ለሞት አሳልፎ በመስጠት ፍጹም ፍቅሩን አሳይቶናል። በቅዱስ ወንጌልም እርሱም መድኃኒታችን “ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም” ብሎ ነግሮናል። እውነት ነው፣ ራስን አሳልፎ ከመስጠት በላይ ምን ድንቅ ነገርና ምን ድንቅ ፍቅር አለ?

ቸሩ አምላካችንን የአስቆሮቱ ይሁዳ ሊያስይዘው የሊቃነ ካህናቱን አገልጋዮች እየመራ አመጣቸው። እነርሱንም ማንን ትፈልጋላችሁ ሲላቸው የናዝሬቱ ኢየሱስን አሉት፣ እኔ ነኝ ቢላቸው የቸሩን አምላክ ድምጽ ሰምቶ አይደለም መቆም በሕይወት መጽናት የሚቻለው የለምና ወደ ኋላቸው ተስፈንጥረው ወደቁ። ደጋግሞም እንዲህ ኾነ። በኋላ ይሁዳ ስሞ አሳልፎ ሰጣቸው።

ከያዙት በኋላ እያዳፉና እየጎተቱ በሰንሰለት አስረው ወደ ቀያፋና ሐና ግቢ ወሰዱት፣ እስከ ሦስት ሰዓትም አላሳረፉትም ሲያሰቃዩት አድረዋል፣ በራሱም ላይ ሰባ ሦስት ስቊረት ያለው ወደ ሦስት መቶ እሾኾችን የያዘ የእሾህ አክሊል ጎንጉነው ቢያደርጉበት የራስ ቅሉን ቀዶ ገብቶ እስከ ልቡ ዘልቋል። እንደምን ጭንቅ ነው? እንዲህም አድርገው ደግሞ እያፌዙ ርኲስ ምራቃቸውን ይተፉበትና በዘንግም ደጋግመው ይመቱት ነበር። እየተፈራረቁ ያለ ምንም ርኅራኄ ቸሩን አምላክ ሥጋው እየተቆረጠ እስኪወድቅ ድረስ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጽኑዕ ግርፋትን ገርፈውታል። የገረፉበትም ጅራፍ በላዩ ላይ ሥጋን እየጎመደ የሚጥል፣ ሕመሙ አንጀት ሰርሥሮ የሚገባ ስለት የተያያዘበት ነበር።

በኋላም አላሳረፉትም እንዲህ አድርገውትም በሊቶስጥራ አደባባይ ያንን ዕርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት። እርሱ ግን ይህን ኹሉ ግፍ ሲያደርሱበት አንድም አልተናገረም ነበር። በቀራንዮም በአምስት ጽኑዕ ቅንዋት (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ) ቸንክረው ዕርቃኑን ሰቀሉት።

በዚህች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተሰበረ መጽናናትንም አልፈለገች ነበር፤ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ እናቱንም እናት ትሆነው ዘንድ በእግረ መስቀሉ አደራን ተቀበለ። ቅዱሳት አንስት በፍጹም ሀዘንና በዋይታ ዋሉ። በስልጣኑም ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ። ሰባት ድንቅ የኾኑ ተአምራትንም አድርጎ አምላክ መኾኑን ገለጠ። ይህም ጽኑዕ የኾነ ለሰማይ ለምድር የከበደ ነገር ሲከሰት ፀሐይ አምላኬን ዕርቃኑ እንዴት አያለሁ ብላ ጨለመች። ጨረቃ ደም ኾነች፣ ከዋክብቱም ረገፉ፣ ንዑዳን ክቡራን ንጹሐን መላእክትም ትዕግስቱን እያደነቁ በጽኑዕ ሐዘንና መደነቅ ከዕፀ መስቀሉ ፊት እንደሻሽ ተነጠፉ።

አስራ አንድ ሰዓት በሆነም ጊዜ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር ቅድስት ሥጋውን ከመስቀሉ አውርደው በክብር ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት። በሦስተኛውም ቀን እንደተናገረ ተነሳ።

በዛሬዋ ቀን ቤተ ክርስቲያን የመድኃኔዓለምን የስቅለት በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው መጋቢት 27 ቀን ነው። ይህ በዓል ግን በዐቢይ ጾም ስለሚውል በዐቢይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለና በዓል ማክበር ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን እንድናከብረው ቤተ ክርስቲያን ስርዓት ሰርታልናለች።

እንዲሁም ይች ዕለት የጻድቁ አባ መብዓ ጽዮን የቃልኪዳን ቀን፣ የማህሌተ ጽጌ ደራሲው አባ ጽጌ ድንግል የእረፍታቸው መታሰቢያ ናት።

ምንጭ:- ዘወርኃ ጥቅምት ፳፯ ስንክሳር