ሰሙነ ሕማማት (በመ/ር ኃይለ ማርያም ላቀው)

ሰሙነ ሕማማት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ስለ ተገለጠበት፣ የመሥዋዕትነት ሥራ የተሠራበት፣ የሰው ልጆች ድኅነት ስለ ተፈጸመበት፣ መድኃኔ ዓለም በመስቀል ተሰቅሎ ለእኛ ቤዛ መኾኑ በስፋት ስለሚነገርበት ‹ቅዱስ ሳምንት› ይባላል፡፡ በተጨማሪም ‹የመጨረሻ ሳምንት› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በመዋዕለ ሥጋዌው ለፈጸማቸው የቤዛነትና የአርአያነት ተግባራት ፍጻሜ በመኾኑ ነው፡፡

በዚህ ልዩ ሳምንት ካህናትና ምእመናን በነግህ፣ በሠልስት፣ በቀትር፣ በተሰዓትና በሠርክ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጓዝ ስለ ጌታችን ኢየስስ ክርስቶስ ሕማማተ መስቀል የሚያዘክረውን ምዕራፍ ከቅዱሳት መጻሕፍት በማንበብና በመጸለይ ሕማሙንና ሞቱን ይዘክራሉ፤ ቅዱስ ያሬድ በመጨረሻው ሳምንት በየዕለቱ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተፈጸመውን ነገረ መስቀል በተመለከተ ያዘጋጀውን መዝሙር ይዘምራሉ፤ አብዝተው ስግደትን ይሰግዳሉ፡፡

ሰሙነ ሕማማትን ከሌሎች የዐቢይ ጾም ሳምንታት ልዩ የሚያደርገው ሥርዓት አለ፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ከጸሎተ ሐሙስ በስተቀር ቅዳሴ አይቀደስም፤ ስብሐተ ነግህ አይደረስም፤ ጸሎተ ፍትሐት አይጸለይም፤ ጸሎተ አስተስርዮም አይደረግም፡፡ ጥምቀተ ክርስትናም አይፈጸምም፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች አስቀድሞ በዕለተ ሆሣዕና ይከናወናሉ፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም ክብረ በዓል በዚህ ሳምንት ቢውል ከትንሣኤ በኋላ ይከበራል፡፡ ይህም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የጸና ኦርቶዶክሳዊ ሥርዓት ነው፡፡

ሕማምና ሞት የማይገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛን ሕማምና ሞት ለራሱ በማድረግ በዚህ ሳምንት ለእኛ ቤዛ መኾኑ ይነገራል፡፡ ‹‹ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕማማችንንም ተሸከመ፡፡ ከዓመፀኞችም ጋር ተቈጠረ፡፡ እርሱ ግን ግፍን አላደረገም፤ ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ኢሳ. ፶፫፥፬-፲፪)፡፡ ምእመናን ክርስቶስ የተቀበለው የእኛን ሕማም መኾኑን በመዘከር፤ ከማንኛውም የሥጋ ሥራ በመታቀብ ዋዛ ፈዛዛ ባለመነጋገር ሰሙነ ሕማማትን ልናከብር ይገባል፡፡ ብድራትን የማያስቀረው አምላካችን እግዚአብሔር መተላለፋችንና በደላችንን በመደምሰስ የመንግሥቱ ወራሽ አድርጎናልና፡፡

ሰሙነ ሕማማት አስከ አራተኛው ምዕተ ዓመት ድረስ ከዐቢይ ጾም ተለይቶ ለብቻው ይከበር ነበር፡፡ በኋላ ግን በባሕረ ሐሳብ ቀመር መሠረት ጾሙም፣ ሕማማቱም፣ ትንሣኤውም ተከታለው እንዲከበሩ ተደረገ፡፡ ምዕራባውያን ከዐርባ ጾም ውስጥ የመጨረሻውን ሳምንት ሰሙነ ሕማማት ያደርጉታል፡፡ የምሥራቃውያን (ኦርየንታል) ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ግን ዐርባውን ጾም ጨርሰን ከኒቆዲሞስ በኋላ ያለውን ተከታዩን አንድ ሳምንት ሰሙነ ሕማማት አድርገን እናከብራለን፡፡ ከእነዚህ የሕማማት ሳምንት ውስጥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስቱ ዕለታት (በሰኞ፣ ማክሰኞ እና ረቡዕ) ያከናወናቸው የድኅነት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

ሰኞ
ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ኾኖ በዚህ ዓለም ሲመላለስ በሆሣዕና ማግሥት ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሁለት ነገሮችን አከናውኗል፤ አንደኛ ከቅጠል በስተቀር ፍሬ ያልተገኘባትን ዕፀ በለስ ረግሟል፡፡ ሁለተኛ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ የሚሸጡትንና የሚለውጡትን አስወጥቷል (ማቴ. ፳፩፥፲፪-፲፯፤ ማር. ፲፩፥፲፯፤ ሉቃ. ፲፱፥፵፭-፵፮)፡፡ በቅዱስ ማቴዎስ አገላለጥ ‹‹በማግሥቱ ተራበ›› የሚል ቃል እንመለከታለን፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹እግዚአብሔር ለዘለዓለም አይራብም፤ አይጠማም፤ አይደክምም›› ይላል (ኢሳ. ፵፮፥፳፭)፡፡ በቅዱስ ወንጌል በመጀመሪያ ቃል እንደ ነበር፤ ያ ቃል ቀዳማዊ እንደ ኾነ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ እንደ ነበር፤ ያም ቃል እግዚአብሔር እንደ ኾነ ተጽፏል (ዮሐ. ፩፥፩-፪)፡፡ ጌታችንም በመዋዕለ ትምህርቱ ሲያስተምር፡- ‹‹የእኔስ መብል የላከኝን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ፤ ሥራውንም እንፈጽም ዘንድ ነው፤›› ሲል ተናግሯል (ዮሐ. ፬፥፴፬)፡፡ ታዲያ ጌታችን ለምን ተራበ? ሰማያውያን መላእክት እንዳይራቡ አድርጎ የፈጠረ፤ እስራኤልን ገበሬ በማያርስበት፣ ዘር በሌለበት፣ ዝናብ በማይጥልበት ምድረ በዳ የመገበ፤ ድኅረ ሥጋዌ በአምስት አንጀራና በሁለት ዓሣ ከአምስት ሺሕ የሚበልጡ ሰዎችን የመገበ ጌታ ‹‹ተራበ›› ተብሎ ሲነገር እጅግ ይደንቃል፡፡ በእርግጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው በመኾኑ አልተራበም አንልም፡፡ የጌታችን ረኃብ የድህነት (የማጣት) አይደለም፡፡ የክርስቶስ ረኃቡ የበለስ ፍሬ ሳይኾን የሃይማኖትና የመልካም ሥነ ምግባርን ፍሬ የሻ መኾኑን ለማጠየቅ ‹‹ተራበ›› ተባለ፡፡ ‹‹በለስ ብሂል ቤተ እስራኤል እሙንቱ›› እንዲል፡፡ ጌታችን የፈለገውን ባለማግኘቱ ጉባኤ አይሁድን ረግሟል፡፡ በአይሁድ ጉባኤ የነገሠውን ኃጢአት፤ በበለስ አንጻር መርገሙን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹በአንጻረ በለስ ረገማት ለኃጢአት፤ በበለስ አንጻር ኃጢአትን ረገማት›› ብሏል፡፡

እስራኤልም በአንድ ወገን የተጠበቀባቸውን ፍሬ ባለማፍራታቸው ተረግመዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እስራኤል ከፍቅር ይልቅ እርግማን እንዳገኛቸው፤ አሕዛብ ደግሞ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ያመኑበትን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጁ ለመኾን መብቃታቸውን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፤ ‹‹አሕዛብ አስተጋብኡ ጽጌሬዳ በኂሩቱ ወሶኩሰ ተርፈ ኀበ አይሁድ ዘውእቱ ሕፀተ ሃይማኖት፤ አሕዛብ በእግዚአብሔር ቸርነት አበባ ሰበሰቡ፤ በአይሁድ ዘንድ ግን እሾኹ ተረፈ፡፡ ይኸውም የሃይማኖት ጉድለት ነው፤›› ብሎ ተርጕሞታል፡፡ እሾኽ የእርግማን፤ አበባ የእግዚአብሔር ጸጋ ልጅነት ምሳሌ ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቤተሰቦች! ዛሬ ጌታችን ወደ መቅደስ ሕይወታችን ቢመጣ ምን ያገኝ ይኾን? ፍሬ ወይስ ቅጠል? የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤›› ይለናልና እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገውን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ እናፍራ (ማቴ. ፫፥፰፤ ገላ. ፭፥፳፪)፡፡ ጌታችን በዳግም ልደት ሲመጣ ከሰው ልጅ ሃይማኖት መገኘቱ አጠራጣሪ እንደ ኾነ ተናግሯል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ሃይማኖት ያገኝ ይኾንን?›› ሕይወታችንን በአምላካዊ ሥልጣኑ የቃኘ አምላክ ለፍርድ በመጣ ጊዜ የእምነት ፍሬ አፍርተን እንዲያገኘንና ዘላለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን የጽድቅ ሥራ ለመሥራት እንትጋ፡፡

 

ማክሰኞ
በማቴዎስ ወንጌል ፳፩፥፳፰፤ ፳፭፥፵፮፤ ማርቆስ ወንጌል ፲፪፥፲፪፤ ፲፫፥፴፯፤ በሉቃስ ወንጌል ፳፥፱፤ ፳፩፥፴፰ የሚገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማክሰኞ ዕለት የሚነገሩ ትምህርቶችን ይዘዋል፡፡ በዚህ ዕለት ጌታችን በቤተ መቅደስ ረጅም ትምህርት ስላስተማረ ዕለቱ ‹የትምህርት ቀን› ይባላል፡፡ ክርስቲያን የኾነ ዅሉ ከሥጋዊ ነገር ርቆ በዚህ ሰሞን የሃይማኖት ትምህርት ሲማር፣ ሲጠይቅ መሰንበቱ መጽሐፋዊ ሥርዓት ነው፡፡

በዚህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሥልጣኑ ተጠይቋል፡፡ ጠያቂዎቹ የካህናት አለቆችና የሕዝብ አለቆች ሲኾኑ፣ ጥያቄውም፡- ‹‹በማን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን የሰጠህ ማነው?›› የሚል ነበር፡፡ ይህ ጥያቄ ጌታችን ሰኞ ዕለት ሁለት ነገሮችን ማከናወኑን ተከትሎ የተነሣ ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን ሲያደርጋቸው የነበሩ ተአምራትና ድንቅ ድንቅ ሥራዎች የካህናት አለቆችን ስላስቀኗቸው ጌታችንን ከሮማ መንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለማጋጨት የቀየሱት ስልት ነው፡፡ ጌታችን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ነጋዴዎችን አባሯል፤ መደባቸውን ገለባብጧል፡፡ ነጋዴን ማባረርና መደብን ማስለቀቅ መንግሥታዊ ሥራ ነው፡፡ ጌታችን ‹‹በራሴ ሥልጣን›› ቢላቸው ፀረ መንግሥት አቋም አለው በማለት ከሮማ መንግሥት ዘንድ ለማሳጣት ነበር ዕቅዳቸው፡፡

ጌታችን ግን የፈሪሳውያንን ጠማማ አሳብ ስለሚያውቅ ‹‹የዮሐንስ ጥምቀት ከየት ነው? ከሰማይ ነው ወይስ ከምድር?›› ሲል ጠይቋቸዋል፡፡ ጌታችን ፈሪሳውያን ላቀረቡለት ጥያቄ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው ለከሳሾቹ ዓላማ መሳካት አመቺ ኹኔታን ስለሚፈጥር ጥያቄውን በጥያቄ መልሶላቸዋል፡፡ እነርሱም ‹‹ከሰማይ ነው›› ቢሉት ‹‹ለምን አላመናችሁበትም?›› እንዳይላቸው፤ ‹‹ከሰው ነው›› ቢሉት ደግሞ ሕዝቡ ዮሐንስን እንደ አባት ይፈሩት፣ እንደ መምህር ያከብሩት ነበርና ሕዝቡ እንዳይጣሏቸው ስለፈሩ ‹‹ከወዴት እንደ ኾነ አናውቅም›› ብለው መለሱለት፡፡ እርሱም ‹‹እኔም በማን ሥልጣን እነዚህን እንደማደርግ አልነግራችሁም›› አላቸው፡፡ ይህን ጥያቄ መጠየቃቸውም እርሱ የሚያደርጋቸውን ተግባራት ዅሉ በራሱ ሥልጣን እንዲያደርግ አጥተውት አልነበረም፤ ልቡናቸው በክፋትና በጥርጥር ስለተሞላ ነበር እንጂ፡፡

ዛሬም ቢኾን መልካም ሥራን በሠራን ጊዜ ከልዩ ልዩ ወገኖች የሚመጡ ፈተናዎች ለመልካም ሥራችን እንቅፋት ሊኾኑ እንደሚችሉ መገንዘብ አለብን፡፡ ብዙ ወገኖች ‹‹ለቅን አሳባችን ለምን ሰዎች ክፉ ነገር ይመልሱልናል?›› በማለት ሲጠይቁ ይሰማል፡፡ ለቅን አሳባችን ከዓለም ዘንድ ተቃራኒ ነገር እንደሚጠብቀን ለመረዳት ‹‹ዓለም የሚወደው የገዛ ወገኑን ነው›› የሚለውን የጌታችንን ትምህርት ልብ ይሏል፡፡ በዘመናችን አሳልፈው ሊሰጡን የሚፈልጉ ሰዎች ፈታኝ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልንም ከወዲሁ ልንገነዘብ ይገባል፡፡

ረቡዕ
በቅዱስ ማቴዎስና በቅዱስ ማርቆስ አመዘጋገብ መሠረት በዕለተ ረቡዕ የሚከተሉት ሦስት ነገሮች ተፈጽመዋል፤
• አንደኛ የካህናት አለቆች፣ የሕዝብ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ፈሪሳውያን በጌታችን ላይ ተማክረዋል፤
• ሁለተኛ ጌታችን በስምዖን ዘለምጽ ቤት ሳለ አንዲት የተጸጸተች ሴት ሽቱ ቀብታዋለች፡፡
• ሦስተኛ ከዳተኛው ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠት ከጸሐፍት ፈሪሳውያንና ከካህናት አለቆች ዘንድ ሠላሳ ብር ለመቀበል ተስማምቷል፡፡

የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሹማምት በጌታችን ላይ ይሙት በቃ ለመወሰን የሰበሰቡት ሸንጐ ‹ሲኒሃ ድርየም› ይባላል፡፡ በዚህ ሸንጐ ላይ በአብዛኛው የተሰየሙት ሰዱቃውያን ሲኾኑ ሌሎቹ ደግሞ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ነበሩ፡፡ ሸንጐው በአጠቃላይ ሰባ ሁለት አባላት የነበሩት ሲኾን የሚመራውም በሊቀ ካህናቱ በቀያፋ ነበር፡፡ በዕለቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዴት ይዘው እንደሚገድሉት አይሁድ በዚህ ሸንጎ መክረዋል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳም ጸሐፍት ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች በጌታን ላይ የነበራቸውን ጥላቻ ያውቅ ስለነበር ‹‹ምን ልትሰጡኝ ትወዳላችሁ? እኔም አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤›› በማለት ጌታችን አሳልፎ ሊሰጣቸው እንደሚችል ተስማቷል፡፡

ጌታችን ያስተምር በነበረበት ወቅት የአስቆሮቱ ይሁዳ ከምእመናን ለሚገባው ገንዘብ ሰብሳቢ (ዐቃቤ ንዋይ) ነበር፡፡ ከሚሰበሰበው ሙዳየ ምጽዋት ለግል ጥቅሙ እየቀረጠ የማስቀረት የእጅ አመል ነበረበት፡፡ ይሁዳ ፍቅረ ንዋይ እንደሚያጠቃው ድብቅ አመሉ ጎልቶ የወጣው ጌታችን በለምጻሙ በስምዖን ቤት ሳለ አንዲት ሴት ዋጋው ውድ የኾነ ሽቱ በቀባችው ጊዜ ነው፡፡ በዚያች ዕለት ይሁዳ የተቃውሞ ድምፅ ካሰሙት አንዱ ነበር፡፡

‹‹ይህ ሽቱ ተሽጦ ለድሆች ቢሰጥ መልካም ነበር፤›› በማለት ያቀረበው አሳብ ‹‹አዛኝ መሳይ ቅቤ አንጓች›› እንደሚባለው ነበር፡፡ ሽቱ ሲሸጥ የሚያገኘው ጥቅም አለ፤ ሽቶው በጌታችን እግር ሥር ከፈሰሰ ለእርሱ የሚተርፈው የለም፡፡ ይሁዳ ተቆርቋሪ መስሎ ያቀረበው አሳብ ተቀባይነት በማጣቱም ማኩረፊያ ያገኘ መስሎት በቀጥታ ከካህናት አለቆች ዘንድ ሔዶ ጌታንን በሠላሳ ብር ለመሸጥ ተዋዋለ፡፡ ይህ ታሪክም በሦስቱ ወንጌላት ውስጥ በሚከተሉት ምዕራፎች ተመዝግቦ እናገኛዋለን፤ ማቴ. ፳፮፥፫-፲፮፤ ማር. ፲፬፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፪፥፩፮፡፡

የአስቆሮቱ ይሁዳ እንደ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ተምሯል፡፡ በረከተ ኅብስቱን ተመግቧል፡፡ ልዩ ልዩ ተአምራት በጌታችን እጅ ሲደረጉ ዅሉ ተመልክቷል፡፡ ጌታችንም ከሌሎች ሐዋርያት ሳይለየው እግሩን አጥቦታል፡፡ ከዳተኛው ይሁዳ ግን ለሐዋርያነት የጠራውን፣ ተንበርክኮ እግሩን ያጠበውን ጌታ ለሞት አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ‹‹የሰው ልጅስ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈ ይሔዳል፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አልፎ ለሚሰጥበት ለዚያ ሰው ወዮለት!›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፮፥፳፬)፡፡ ሌሎች ሐዋርያት ከጌታችን ዘንድ ፍቅሩን ገንዘብ ሲያደርጉ ይሁዳ ግን እርግማንን ነው ያተረፈው፡፡ ‹‹ገንዘብ የኃጢአት ሥር ነው፤›› ተብሎ አንደ ተነገረ የኃጢአት ሥር የተባለው ገንዘብ የክርስቲያኖችን ሕይወት ያዳክማልና ምእመናን እንደ ይሁዳ በገንዘብ ፍቅር እንዳንወድቅ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ሰው ‹‹ይህን ዓለም ቢያተርፍ ነፍሱን ከጐዳ ምን ይጠቅመዋል?›› ተብሎ የተነገረውን ቃል ልብ ማለት ጠቃሚ ነው፡፡
ክርስቲያን ነን በማለት የክርስትናውን ስም በመያዝ እምነታቸውን፣ የቆሙበትን ዓላማ በመገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ዛሬም እንደ ይሁዳ ጌታችንን እየሸጡት እንደ ኾነ ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ ለድሆች መመጽወት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ዳሩ ግን በድሆች ስም የሰውን ገንዘብ ለግል ጥቅም ማዋል እጅግ የከፋ ኃጢአት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ለገንዘብ ብለው ድሆችን ለረኃብ ለችግር ባልንጀራቸውን ለመከራ እና ለሞት አሳልፈው ሲሰጡ ምንም አይጸጽታቸውም፡፡ እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ሕይወታችንን ለገንዘብ ፍቅር ሳይኾን ለእምነታችንና ለባልንጀራችን አሳልፈን መስጠት ይኖርብናል፡፡ በፍቅረ ንዋይ ተጠምደን ሰዎችን አሳልፎ በመስጠት ለአይሁዳዊ ሸንጐ ምቹ ኾነን መገኘት እንደሌለብን መገንዘብ አለብን፡፡

ይቀጥላል …

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡– ስምዐ ተዋሕዶ (ልዩ ዕትም ዘሰሙነ ሕማማት)፣ ከሚያዝያ ፩ -፲፭ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም፣ ገጽ ፬-፮፤ ማኅበረ ቅዱሳን፣ አዲስ አበባ፡፡

ሆሳዕና 🌿🌿🌿

(በመምህር ኃይለ ማርያም ላቀው)

ሆሳዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ሆሼዕናህ የሚል ሲሆን ትርጉሙም እባክህ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው (መዝ.117፡25-26)። የሆሳዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሳዕና በአርያም በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሳዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ይህ ዕለት የጸበርት እሑድ/ Palm Sunday/ ይባላል፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ሆኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ይኸውም ሣራ የወላድነት ዕድሜዋን ጨርሳ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ የጎበኛትን አምላክ አመስግነዋል፡፡ እስራኤል ከአስከፊው የግብፃውያን አገዛዝ ተላቀው ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገሩ የተሰማቸውን እጥፍ ድርብ ደስታ በገለጡ ጊዜ፣ እንዲሁም ዮዲት የተባለች ንግሥተ እስራኤል ሆሎፎርኒስ የተባለ አላዊ ንጉሥን ድል ባደረገች ጊዜ ቤተ እስራኤል እንደ ሰንደቅ ዓለማ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ አደባባይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከሲኦል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ዙፋን መስቀሉ /ሉቃ.22፤18/ በተጓዘ ጊዜ ሕፃናት እና አእሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እነርሱ ሳያውቁ እግዚአብሔር ባወቀ ዘንባባ በመያዝ ዘምረዋል፡፡ እስራኤል ዘንባባ በመያዝ እንዳመሰገኑት እኛም እስራኤል ዘነፍስ ዕለቱን ዘንባባ በግንባራችን በማሰር በዓሉን በየዓመቱ እያስታወስን እናከብራለን፡፡ በዚህ ዕለት ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡

ሕፃናትና አእሩግ “ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል” እያሉ ዘምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው አቀባበል ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ ጌታችንም መልሶ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ ሲል መልሶላቸዋል፡፡ ቅናት አቅላቸውን ያሳታቸው ፈሪሳውያንም የዋህ የሆነው ሕዝብ ምስጋና ወደ ጥላቻ እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው በዕለተ ሆሳዕና እሑድ ዘንባባ ይዘው የዘመሩለትን ጌታ ዓርብ ይሰቀል ዘንድ ይገባል ብለዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህም በነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል (ዘካ.9፡9፤ ማቴ.21፡4፤ ማር.11፡1-10፤ ሉቃ.19፡28-40፤ ዮሐ.12፤15)፡፡ ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲሆንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ የኅሊና ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል፡፡

መላእክት በዕለተ ልደቱ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል በምድር ሰላም ለሰው ሁሉ ይሁን/ሉቃ.2፡13/ እያሉ የዘመሩለት የሰላም ባለቤት ነው፡፡ በመዋዕለ ትምህርቱም ሰላሜን እሰጣችኋለሁ/ዮሐ.14፡27/ ብሎ እንዳስተማረ ያን ሰላም የሚሰጥበትን ዕለት መቅረቡን ለማመልከት ነው፡፡ በሌላ በኩልም በአህያ ጀርባ መቀመጡ ኅቡዕ ምሥጢር አለው፡ በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፣ እርሱም ሮጦ አያመልጥም፡፡ በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ ቅርብ ሲሆን በእምነት ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ፀሐይ ዕድሜያችን ሳትጠልቅ በእምነት እንፈልገው፡፡ የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፣ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅም (ኢሳ.66፡2፤ መዝ.50፡17)፡፡ በሰሙነ ሕማማት ጸሎተ ፍትሃት ጸሎተ አስተስርዮ ስለማይፈጸም ጸሎተ ፍትሃትና አስተስርዮ የሚደረገው በዚሁ ዕለት ነው።

በሆሣዕና ዕለት ዘንባባ በእጃችን እንደ ቀለበት ማሰራችን የምን ምሳሌ ነው?
✍️ጌታ ለአዳም የሰጠው ቃል ኪዳን ለማስታወስ፦ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድነሃለሁ ያለውን የተስፋ ቃል ለማስታወስ፡፡
✍️ጌታ ለእመቤታችን የገባላትን ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው።
✍️ጌታ ለእስራኤላውያን የሰጣቸው ቃል ኪዳን ተምሳሌት ነው።
✍️ ጌታ አዳምን ከሰይጣን ግዛት ነጻ እንዳወጣው ሁሉ እኛም ከሰይጣን ግዛት፣ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ፣ ከክፋት፣ ከኃጢአት አውጣን ማረን ለንስኃ ሞት አብቃን ከቤትህ አትለየን እንደ ቸርነትህ ይቅር በለን ስንል ለጌታ ዳግም ላናጠፋ ቃል የምንገባበት ነው፡፡

ጌታችን በዕለተ ሆሳዕና ለምን በፈረስ ወይም በበቅሎ ላይ አልተቀመጠም?
ትንቢቱንና ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፡፡ “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ሆይ፥ እልል በዪ፤ እነሆ፥ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፥ በአህያይቱ ግልገል በውርጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል”(ትንቢተ ዘካርያስ 9:9)።

በአህያ መቀመጡ፦ ትሕትናን ለማስተማር፣ የሰላም ዘመን ነው ሲል፣ ለፈለጉኝ ሁሉ የቅርብ አምላክ ነኝ ሲል፣ በንጽሕና በየዋህነት ለሚኖሩ ምዕመናን አድሬባቸው እኖራለሁ ሲል፡፡አህያዎች ትሑታን ናቸው ረጋ ብለው ነው የሚሄዱት፤ በቀላሉ ትወጣበታለህ፤ በቀላሉ ትይዘዋለህ፤ እንደፈለክም ታዝዋለህ፤ ጌታችን እኔም ትሑት ነኝ ሲል ነው።

ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ዘንባባ የመነጠፉ ምሥጢር የምን ምሳሌ ነው?
አብርሃም ይሐስቅ በተወለደ ጊዜ ደስ ብሎት ዘንባባ ይዞ እግዚአብሔርን አመስግኗል፡፡ ዘንባባ ደርቆ እንደገና ሕይወት ይዘራል። የደረቀ የምታለመልም አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዘንባባ የሰላም ምልክት ነው፡- የሰላም አምላክ ነህ ሲሉ ነው። ዘንባባ የደስታ መግለጫ ነው፡- አንተ ደስ የምታሰኝ ኃዘናችንንም የምታርቅልን አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዘንባባ እሾሃማ ነው፡- አንተ ሕያው አሸናፊ አምላክ ነህ ሲሉ ነው፡፡ ዘንባባ እሳት አይበላውም ለብልቦ ይተወዋል እንጂ፡፡ ጌታም አንተ ባሕርይህ የማይመረመር ነው ሲሉ ነው፡፡

ሕዝቡ ልብሳቸውን ማንጠፋቸው ለክብሩ መግለጫ ነው፡፡ ልብስ አይቆርቁርም ጌታ የማትቆረቁር ሕግ ሠራሁላችሁ ሲል፡፡ ሌሎችም ሦስት አይነት ቅጠል አነጠፉለት፦ የዘንባባ ዛፍ፣ የቴመር ዛፍ እና የወይራ ዛፍ ቅጠል፡፡ የዘንባባ ዛፍ፦ እሾሀማ ነው። ትእምርተ ኃይል፣ ትእምርተ መዊዕ አለህ ሲሉ ነው፡፡ የቴምር ዛፍ፦ ቴምር ልዑል ነው። ልዑለ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ ፍሬው አንድ ነው – ዋህደ ባሕርይ ነህ ሲሉ፤ ፍሬው በእሾህ የተከበበ ነው – ባሕርይህ አይመመረመርም ሲሉ፡፡ የወይራ ዛፍ ጽኑዕ ነው – ጽኑዓ ባሕርይ ነህ ሲሉ፡፡ ብሩህ ነው ብሩሃ ባሕርይ ነህ ሲሉ፡፡ ዘይት መሥዋዕት ይሆናል – አንተም መሥዋዕት ትሆናለህ ሲሉ፡፡

ታላቋ አህያ በምን ትመሳለለች? ውርንጭላዋስ? ታላቋ አህያ የኦሪት ምሳሌ ናት፡፡ ታላቋ አህያ ሸክም የለመደች ናት፤ ሕገ ኦሪትም የተለመደች ሕግ ናትና፡፡ የእስራኤል ምሳሌ ነው፤ ታላቋ አህያ ሸክም እንደለመደች ሁሉ እስራኤልም ሕግ ለመፈጸም በሕግ ለመራመድ የለመዱ ናቸው፡፡ የአዳም ምሳሌ ነው፡- አዳም ሸክም የበዛበት ነበርና፡፡ የፍጹማን ምሳሌ ናት፡፡ ውርጭላዋ በሕገ ወንጌል ትመሰላለች። ምክንያቱም ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ የመሰረታት የሠራት አዲሷ ህግ ናትና። በአሕዛብ ትመሰላለች፡- ትንሿ አህያ ሸክም የለመደች አይደለችም እንዲሁም አሕዛብም ሕግን ለመቀበል የለመዱ አይደሉም፡፡ ለሕግ አዲስ ናቸውና፡፡ የእመቤታችን ምሳሌ ናት፡- የዓለም ሸክም አቅላለችና በእመቤታችን ትመሰለላለች፡፡ እመቤታችን ድኅነተ ምክንያታችን ጌታን የተሸከመች ንጽሕት እንከን የሌላት እናት ናትና፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ያልታሰሩ አህዮች እያሉ ለምን የታሰሩትን መረጠ? አህዮቹ የታሰሩት ሌባ ሰርቆ ነው ያሰራቸው፡፡ ወንበዴ ሰርቆ ነው ያሰራቸው። አህዮቹ ለጌታ ውለታ ሰርተዋል፡፡ ጌታ ሲወለድ አሙቀውታልና ለጌታ ውለታ ልንመልስ ያልቻልንው እኛ ሰዎች ብቻ ነን፡፡ የታሰሩት እዲፈቱ የመረጠበት ምሥጢር፡-እኔ ከኃጢአታችሁ ልፈታችሁ የመጣሁ ነኝ ሲል ነው፡፡ ወንበዴው አህዮቹን ሰርቆ በመንደር እንዳሰራቸው ዲያብሎስም የሰው ልጆችን በኃጢአት ሰንሰለት ከሲኦል መንደር አስሯቸው ነበርና፡፡ ሐዋርያቱ ሲልካቸው ምን ታደርጋላችሁ የሚላችሁ ሰው ቢኖር ጌታቸው ይሻቸዋል በሏቸው አላቸው በተፈጥሮ ጌታቸው ነውና፡፡ ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የሆነ ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደተቀመጠ ሁሉ ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት ዛሬም ያድራል፤ የኅሊና ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ንስሐ ገብተን ጌታችንን ሆሳዕና በአርያም እያልን ልናመሰግነው ይገባል፡፡

ምንጭ፦ ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ መጋቢት/ሚያዝያ 1996 ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን የሩቅ ምሥራቅ ማእከል አባላት ዕለተ አኮቴትን (የምስጋና ቀን) አከበሩ

በሀገር ውስጥና በውጪ ባሉ የማኅበረ ቅዱሳን ሁሉም መዋቅሮች የሚከበረው ዕለተ አኮቴት (የምስጋና ቀን) በሩቅ ምሥራቅ ማእከል ተከብሯል፡፡ ዕለተ አኮቴት በየዓመቱ ከሆሳዕና በዓል ቀድሞ በሚውለው ዕለተ ዐርብ የሚከበር ሲሆን መርሐግብሩ ማኅበሩ በሚያከናውናቸው አገልግሎቶች ውጤታማ እንዲሆን የረዳውን እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት ነው፡፡ መርሐግብሩ በሩቅ ምሥራቅ ማእከል ስር ባሉ የተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች በኦንላይን በተገኙበት የተከናወነ ሲሆን በአባቶች ጸሎት ከተጀመረ በኋላ በቀሲስ ሙሉቀን ብርሃኑ ትምህርተ ወንጌል ተሰጥቷል፡፡ ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል፡፡ በአገልግሎታቸው አርኣያ ለሆኑ ወንድሞች እና እህቶች የምስጋና መርሐግብር በማእከሉ ሰብሳቢ ዲ/ን አያናው ፀጋ መሪነት የተከናወነ ሲሆን የበለጠ እንዲያገለግሉ አደራ ጭምር የተሰጠበት ነው፡፡ የሩቅ ምሥራቅ ማእከል ፀሀፊ ዲ/ን ፋንታሁን ትኩ የማኅበሩን መልእከት ያስተላለፉ ሲሆን የቤተ ክርስቲያናችን መከራ በየዘመኑ መልኩን እየቀያየረ መጠኑን እያሰፋ እንደመጣ ገልጸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አካል የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ባለፉት ፴፪ ዓመታት በእግዚአብሔር አጋዥነት በአውሎና በወጀብ ውስጥ አልፎ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸው ለዚህም አምላካችንን እግዚአብሔርን ልናመሰግን፤ ለቀጣዩ ደግሞ በጸሎትና በአገልግሎት ተግተን በፍቅርና በእንድነት ተባብረን የበለጠ በመሥራት የቤተክርስቲያንን ችግር ለመቅረፍ ሁላችንም በቁርጠኝነት እንድንዘጋጅ አሳስበዋል።

የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሙተዋልና÷ ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ። ማቴ. 2÷20

ኅዳር ፮ በዚህች ዕለት ክብርት እመቤታችን ከተወደደ ልጇ ጋር ከስደት በሚመለሱበት ጊዜ ደብረ ቁስቋም ገብተው ካገኛቸው ድካም ያረፉበት ነው። ይህ የቍስቋም ተራራ በግብጽ ከሚገኙ ተራራዎች አንዱ ሆኖ እመቤታችን በሚጠቷ (ከስደት በምትመለስ ጊዜ) ከተወደደ ልጇና ከቅዱስ ዮሴፍና ቅድስት ሰሎሜ ጋር ያረፈችበት ቦታ ነው።

መዘምር ወመተርጕም ቅዱስ ያሬድ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከእናቱ ከእግዝእትነ ማርያም ጋር በዚህ ቦታ ላይ ማረፉንና የቦታውን ታላቅነት በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ይናገራል። ቅዱስ ያሬድ ስለቦታው ታላቅነት ሲናገር <<ይቤ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጳጳሳት ሶበ ቦዕኩ ውስተ ዝንቱ ቤት አዕረፈት ነፍስየ እምጻማ ዘረከበኒ በፍኖት ኀበ ኃደረት ቅድስት ድንግል ምስለ ፍቁር ወልዳ ኢየሱስ ክርስቶስ : የጳጳሳት አለቃ ቴዎፍሎስ ቅድስት ድንግል ከተወደደ ልጇ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳረፈችበት ወደዚህ ቦታ በገባሁ ጊዜ በመንገድ ካገኘኝ ድካም ሰውነቴ አረፈች አለ>> ይልና <<መንግሥቱ ሰፋኒት ዘእምቅድመ ዓለም ወልደ ቅድስት ማርያም ኃሠሠ ምዕራፈ ከመ ድኩም ንጉሥ ዘለዓለም ግሩም እምግሩማን ብርሃነ ሕይወት ዘኢይጸልም ኃደረ ደብረ ቍስቋም ኃይል ወጽንዕ ዘእምአርያም : ዓለም ሳይፈጠር በመንግሥቱ ያለ በንግሥናው የነበረ (መዝ.፸፫÷፲፫) ቅድስት የምትሆን የማርያም ልጅ እንደ ደካማ ማረፊያን ፈለገ (ማረፍን የሚሻ ሥጋን ለብሷልና) ፍጥረታቸው ግሩም ከሆነ ከቅዱሳን መላእክት እጅግ የረቀቀ ግሩም : የማይጨልም ብርሃኑ ዘለዓለማዊ የሆነ የሕይወት ብርሃን(ዮሐ. ፩÷፱) በአርያም ላሉ ለሰማያውያን መላእክት ሁሉ ኃይላቸው ብርታታቸው የሆነ እርሱ በቍስቋም ተራራ ላይ አደረ>> በማለት እርሱ የመላእክት ንጉሣቸው (ሃይ. አበ ዘሄሬኔዎስ ምዕ. ፯÷፯) የሆነ በዚህ ተራራ ላይ ራሱን ዝቅ አድርጎ በትሕትና መገለጡን ይመሰክራል።

ይህች ዕለት ቅዱሳን መላእክት በቍስቋም ተራራ ላይ ክንፋቸውን በእመቤታችንና በተወደደ ልጇ ላይ የዘረጉበትና በሰማይ ምስጋና በምድርም ሰላም ይሁን እያሉ የዘመሩባት ናት።

ዳግመኛም በኋለኛው ዘመን ጌታችን በዚህ በደብረ ቍስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቶቹን ሰበሰባቸውና ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንን አክብሮ የቍርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለወገኖቹ ሰጣቸው፡፡ ለዚህም ነገር የእስክንድርያ አገር ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱሳን አባቶቻችን ቄርሎስና ቴዎፍሎስ ምስክሮቹ ሆኑ፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እኛንም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን። በረከቷም ከሁላችን ጋር ይኑር። ለዘለዓለሙ አሜን።

ምንጭ፦ ስንክሳር ዘኅዳር ፮፣ ዝክረ ቃል ዘቅዱስ ያሬድ (ዘቍስቋም)

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ጥንተ ስቅለቱ መታሰቢያ በዓል አደረሳችኹ።

ጥቅምት ሃያ ሰባት በዚህች ዕለት የአምላካችን የመድኃኔዓለም የስቅለቱ መታሰቢያ ነው። መድኃኒታችን ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና በቸርነቱ ስለኹላችን ድኅነት ሲል ራሱን ወድዶ ፈቅዶ ለሞት አሳልፎ በመስጠት ፍጹም ፍቅሩን አሳይቶናል። በቅዱስ ወንጌልም እርሱም መድኃኒታችን “ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም” ብሎ ነግሮናል። እውነት ነው፣ ራስን አሳልፎ ከመስጠት በላይ ምን ድንቅ ነገርና ምን ድንቅ ፍቅር አለ?

ቸሩ አምላካችንን የአስቆሮቱ ይሁዳ ሊያስይዘው የሊቃነ ካህናቱን አገልጋዮች እየመራ አመጣቸው። እነርሱንም ማንን ትፈልጋላችሁ ሲላቸው የናዝሬቱ ኢየሱስን አሉት፣ እኔ ነኝ ቢላቸው የቸሩን አምላክ ድምጽ ሰምቶ አይደለም መቆም በሕይወት መጽናት የሚቻለው የለምና ወደ ኋላቸው ተስፈንጥረው ወደቁ። ደጋግሞም እንዲህ ኾነ። በኋላ ይሁዳ ስሞ አሳልፎ ሰጣቸው።

ከያዙት በኋላ እያዳፉና እየጎተቱ በሰንሰለት አስረው ወደ ቀያፋና ሐና ግቢ ወሰዱት፣ እስከ ሦስት ሰዓትም አላሳረፉትም ሲያሰቃዩት አድረዋል፣ በራሱም ላይ ሰባ ሦስት ስቊረት ያለው ወደ ሦስት መቶ እሾኾችን የያዘ የእሾህ አክሊል ጎንጉነው ቢያደርጉበት የራስ ቅሉን ቀዶ ገብቶ እስከ ልቡ ዘልቋል። እንደምን ጭንቅ ነው? እንዲህም አድርገው ደግሞ እያፌዙ ርኲስ ምራቃቸውን ይተፉበትና በዘንግም ደጋግመው ይመቱት ነበር። እየተፈራረቁ ያለ ምንም ርኅራኄ ቸሩን አምላክ ሥጋው እየተቆረጠ እስኪወድቅ ድረስ ስድስት ሺህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ጽኑዕ ግርፋትን ገርፈውታል። የገረፉበትም ጅራፍ በላዩ ላይ ሥጋን እየጎመደ የሚጥል፣ ሕመሙ አንጀት ሰርሥሮ የሚገባ ስለት የተያያዘበት ነበር።

በኋላም አላሳረፉትም እንዲህ አድርገውትም በሊቶስጥራ አደባባይ ያንን ዕርጥብ መስቀል አሸክመው ወደ ቀራንዮ ወሰዱት። እርሱ ግን ይህን ኹሉ ግፍ ሲያደርሱበት አንድም አልተናገረም ነበር። በቀራንዮም በአምስት ጽኑዕ ቅንዋት (ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ እና ሮዳስ) ቸንክረው ዕርቃኑን ሰቀሉት።

በዚህች ቀን ድንግል ማርያም ልቧ በሐዘን ተሰበረ መጽናናትንም አልፈለገች ነበር፤ ወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስም ፍፁም ለቅሶን አለቀሰ እናቱንም እናት ትሆነው ዘንድ በእግረ መስቀሉ አደራን ተቀበለ። ቅዱሳት አንስት በፍጹም ሀዘንና በዋይታ ዋሉ። በስልጣኑም ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው ለየ። ሰባት ድንቅ የኾኑ ተአምራትንም አድርጎ አምላክ መኾኑን ገለጠ። ይህም ጽኑዕ የኾነ ለሰማይ ለምድር የከበደ ነገር ሲከሰት ፀሐይ አምላኬን ዕርቃኑ እንዴት አያለሁ ብላ ጨለመች። ጨረቃ ደም ኾነች፣ ከዋክብቱም ረገፉ፣ ንዑዳን ክቡራን ንጹሐን መላእክትም ትዕግስቱን እያደነቁ በጽኑዕ ሐዘንና መደነቅ ከዕፀ መስቀሉ ፊት እንደሻሽ ተነጠፉ።

አስራ አንድ ሰዓት በሆነም ጊዜ ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከታላቅ ክብርና ሐዘን ጋር ቅድስት ሥጋውን ከመስቀሉ አውርደው በክብር ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት። በሦስተኛውም ቀን እንደተናገረ ተነሳ።

በዛሬዋ ቀን ቤተ ክርስቲያን የመድኃኔዓለምን የስቅለት በዓል በደማቁ ታከብራለች፤ ይህም የለውጥ በዓል ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው መጋቢት 27 ቀን ነው። ይህ በዓል ግን በዐቢይ ጾም ስለሚውል በዐቢይ ጾም ሀዘን እንጂ ደስታ ስለሌለና በዓል ማክበር ስለማይፈቀድ፤ ወደ ጥቅምት 27 ተዛውሮ ደስ ብሎን እንድናከብረው ቤተ ክርስቲያን ስርዓት ሰርታልናለች።

እንዲሁም ይች ዕለት የጻድቁ አባ መብዓ ጽዮን የቃልኪዳን ቀን፣ የማህሌተ ጽጌ ደራሲው አባ ጽጌ ድንግል የእረፍታቸው መታሰቢያ ናት።

ምንጭ:- ዘወርኃ ጥቅምት ፳፯ ስንክሳር

እግዚአብሔር የመረጠው ጾም

ለተወሰነ ሰዓት ከምግበ ሥጋ የመከልከላችን ዓላማ ራሳችንን መግዛት እንድንችል ነው፡፡ ስለዚህ ‘እየጾምኩ ነው’/የሚል ሰው ካለ ከምንም በፊት ትዕግሥተኛ ፣ ልበ ትሑትና የዋህ ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ልቡና ያለው ፣ የፍትወታትን ጅረት ከኹለንተናው የሚያስወግድ ፣ ዘወትር በልቡናው ዕለተ ምጽአትን የሚያስብ ፣ በእግዚአብሔር የፍርድ ዙፋን ፊት እንደሚቆም የማይረሳ ፣ በፍቅረ ንዋይ ወጥመድ ተይዞ ምጽዋትን የማይጠላ፣ ወንድሙን ከልቡ የሚወድ ይኹን፡፡ እውነተኛ ጾም ማለት ይኽ ነውና፡፡

“ሰው ራሱን ቢያሳዝን ፣ አንገቱንም እንደ ቀለበት ቢያቀጥን ፣ ማቅ ለብሶ በአመድ ላይ ቢተኛም ይህ ጾም እግዚአብሔር ዘንድ የተመረጠ አይደለም” “ታዲያ እግዚአብሔር የመረጠው ጾም እንዴት ያለ ነው?” ትሉኝ እንደ ኾነም ነቢዩ ኢሳይያስ የእግዚአብሔር አፈ ንጉሥ ኾኖ እንዲህ ሲል ይመልስልናል፡

“የበደልን እስራት ፍታ ፡ ለተራበው እንጀራህን አጥግበው ፡ ድኾችን ወደ ቤትህ አስገብተህ አሳድራቸው ” እንዲህ ስታደርግ ፡- “ያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ይበራል፡፡ ፈውስህም ፈጥኖ ይወጣል” ትን.ኢሳ.58 ፥ 5-8

†ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ†

ምንጭ -ኦሪት ዘፍጥረት መፅሐፍ – በገብረ እግዚአብሔር ኪደ

ጰ ራ ቅ ሊ ጦ ስ

¹ በዓለ ሐምሳ የተባለውም ቀን በደረሰ ጊዜ፥ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥

² ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምፅ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው።

³ እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዩአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው።

⁴ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው ፥ መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር።

እ ን ኳ ን ለቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊ በዓል በሰላም አ ደ ረ ሳ ች ሁ።

ተአምራትን በሚያደርግ በከበረ በቅዱስ ሚካኤል በዓል ቀን መታሰቢያን የሚያደርግ ኹሉ ለቤተክርስቲያን ዕጣን የሚሰጥ ቢኾን መስዋዕትን የሚያቀርብ ቢኾን የተራበውን ያበላ የተጠማውን ያጠጣ ቢኾን የታረዘም ያለበሰ ቢኾን ያዘነውን ያረጋጋ የተከዘውን ደስ ያሰኘ የታመመውን የጎበኘ ቢኾን ስለከበረ ስለ መላእክት አለቃ ስለ ቅዱስ ሚካኤል ስም በጭንቅ በመከራ ያለውን እሥረኛን የጠየቀም ቢኾን ገሃነምን አያያትም።

በዚኽ ዓለም እግዚአብሔር ከበጎ ነገር ኹሉ አያሳጣውም። በሞተ ጊዜም ነፍስን እያካሰሱ ወደ ሲዖል የሚያደርሱ አጋንንት በሰማይ በር ሊከራከሩት አይችሉም።

ይኸው ቅዱስ ሚካኤል በብሩሃን ክንፎቹ ተሸክሞ የእሳት ባሕርን ያሻግረዋል። በልዑል እግዚአብሔር ዙፋን ፊት ያቆመዋል። ነፍስ ለልዑል እግዚአብሔር ትሰግዳለች። ከዚኽ በኋላ ወደ ተድላ ገነት ይወስዳታል። እርሱ ራሱ ጌታችን በማይታበል ቃሉ ተናግሯልና። ለወዳጆቹም ኹሉ ቃል ኪዳን ሰጥቶአቸዋልና እንዲኽ ብሎ ከወዳጆቼ ጋር ቃል ኪዳን አደረግኹ።”

† ድርሳነ ሚካኤል †

ሰላም ለዝክረ ስምከ ምስለ ልዑል ዘተሳተፈ ፣ ወልደ ያሬድ ሄኖክ በከመ ጸሐፈ ፣ ሶበ እጼውእ ስመከ ከሢትየ አፈ ፣ ረዳኤ ምንዱባን ሚካኤል በከመ ታለምድ ዘልፈ ፣ ለረዲኦትየ ነዓ ሰፊሐከ ክንፈ ።

የቅዱስ ሚካኤል ምልጃና ረዳትነቱ አይለየን

ይ ቅ ር ታ

በአንዲት ሀገር አንድ ንጉሥ ነበር ። ይህ ንጉሥ በቤተ-መንግስት ውስጥ ብዙ አገልጋዮች አሉት – ያሉት አገልጋዮችም ምንም አይነት ስህተት እንዲሰሩ አይፈቅድም ። ትንሽ ጥፋት ሲያጠፉ ተለይቶ በተዘጋጀው ስፍራ ሰው እያያቸው ታስረው በተራቡ ጨካኝ የጫካ ውሾች ተበልተው እንዲሞቱ ያደርግ ነበር ። ከእለታት በአንዱ ቀን ንጉሡን ለ25 ዓመታት ያገለገው ባርያ ጥፋት ያጠፋና በንጉሡ ፊት ያቀርቡታል ። ንጉሡም በውሾች ተበልቶ እንዲሞት ፈረደበት ። ይህ ባርያ በተፈረደበት ፍርድ ከመሞቱ በፊት አሥር ቀን በቤተ-መንግስት ውስጥ እንዲያገለግል ንጉሡን ለመነ እናም ተፈቀደለት ።

ታዲያ ይህ ባርያ በተሰጠው አሥር ቀን ንጉሡን ብቻ ሳይሆን ውሾቹን ማገልገል ጀመረ ፣ ምግብ ይሰጣቸዋል ፣ ውኃ ይሰጣቸዋል ፣ ያጫውታቸዋልም ። ከዚያም በኋላ የተፈቀደለት አሥር ቀኑ አልቆ ያ ባርያ ለፍርድ በተዘጋጀው ስፍራ ታስሮ ቀረበ ፣ ውሾቹም ባርያውን እንዲነክሱት ተለቀቁ ነገር ግን አልነኩትም – ይልቅ ይልሱትና ያጫውቱት ጀመር።

በዚህ የተገረመው ንጉሡ ባርያውን አስጠርቶ ለምን እንዳልበሉት ጠየቀው ። ባርያውም “ንጉሥ ሆይ ሺ ዓመት ይንገሡ ፣ በቤተመንግሥትዎ ውስጥ 25 ዓመታትን በታማኝነት አገልግያለሁ በዚህም እርስዎ ደስተኛ እንደነበሩ በስጦታዎ ገልጸውልኛል ነገር ግን አንድ ቀን በሰራሁት ጥፋት ምክንያት እንድሞት ፈረዱብኝ ፤ ከአሳለፍናቸው 25 ዓመታት የአንድ ቀን ጥፋቴን አስበው ለሞት ሰጡኝ ። እነዚህን ውሾች ግን ለአሥር ቀን ብቻ አገለገልኳቸው ነገር ግን እርቧቸው እንኳ ሊበሉኝና ሊገድሉኝ አልወደዱም” አላቸው። ንጉሡም እስከ ዛሬ የሰራው ስራ ልክ እንዳልነበረ አስተዋለ ተጸጸተ ባርያውንም በይቅርታ አለፈው!

ለዘመናት ከእኛ ጋር በፍቅር ከኖሩ ወዳጆቻችን ፣ ቤተሰዎቻችን ፣ ዘመዶቻችን ፣ ጓደኞቻችንና ጎረቤቶቻችን ጋር ተጣልተን ሳለ በፍቅር የኖርንበት ጣፋጭ ዘመንን ነው የምናስበውና የምናወራው ወይንስ የተጣላንበትን ቀንና ምክንያት?  እነሆ ልባችን ለይቅርታ እንዲከፈት በፍቅር የኖርንበትን ዘመን ፣ መልካም ጊዜያትን በማሰብ ብንነጋገር ምክራችን ነው።

ኃጢአተኛዋ/ውን ማረኝ

በድሮ ዘመን ወንጀል የሚሠሩ አመጸኞች ተይዘው ሲታሰሩ በግራና ቀኝ እጃቸው መቅዘፊያ ይዘው በጉልበታቸው ኃይል እየቀዘፉ የመንግስትን መርከቦች በባህር ላይ እንዲነዱ ይገደዱ ነበር።

አንድ ቀንም አንድ ንጉሥ ክፉ ሥራ የሠሩ ወንጀለኞች ታሥረው ወደ ሚገኙበት መርከብ ገባ። እስረኞቹም የታሰሩበትን ከባድ ሰንሰለት ሲመለከት እጅግ አዘነላቸው። በልቡም “ከእነዚህ አንዱን ልፍታ” ሲል አሰበ።

መፈታት የሚገባውንም ለማግኘት “አንተ ወደዚህ የመጣህበት ምክንያት ምንድነው?” እያለ እያንዳንዱን ሲጠይቅ እና ሲመረምር እያንዳንዳቸው እያዘኑ “ምንም ሳላጠፋና ሳልበድል ክፉ ሰዎች ነገር ሠርተው ወደ ሹማምንት አደረሱኝ እንጂ ከተባለብኝ ነገር ንጹህ ነኝ ጌታዬ ሆይ ምሕረት አድርጉልኝ ከዚህም ሥፍራ ያውጡኝ እያሉ አጠንክረው ለመኑ ።

ንጉሡም እያለፈ ሲመረምር ወደ አንድ ወጣት ደረሰና “አንተ ምን አድርገህ ነው” ቢለው ወጣቱ መልሶ “ምሕረተኛ ጌታዬ ሆይ እኔ እጅግ ክፉ አሽከር ነኝ ለአባቴና ለእናቴ አልታዘዝም በማለት ብዙ ጊዜ ኮበልኩባቸው፤  እጅግ ክፉ ሥራም ሠራሁ ፣ ሰረቅሁ ፣ አታለለሁም ፣ ያደረግሁትን ክፋት ሁሉ ዘርዝሬ ለመተረክ እጅግ ብዙ ነው።  የተገባኝን አግኝቻለሁ ይህን ቅጣት ደስ እያለኝ እሸከማለሁ ከዚህ ሺህ ጊዜ የሚበልጥ እንደሚገባኝ ተረድቻለሁ” ብሎ ኃጢአቱን ተናዘዘ።

ንጉሡ ግን እያንዳንዱ እስረኛ ለጥፋቱ የተገባውን ቅጣት እንደተቀበለ አረጋግጦ በቀልድ ሲዘልፋቸው “ኧረ በእነዚህ ደጋግ ሰዎች መካከል ይህ ክፉ እንዴት ገባ! እነዚህን ደህና ሰዎች እንዳያበላሽ ቢወጣ ይሻላል” በማለት በክፉ ሥራው አፍሮ ለተናዘዘው ምሕረት አደረገለት ፤ እርሱም ደስ ብሎት ሄደ።

የሠራነውን ኃጢአት ለመደበቅ ፣ ራሳችንን ለማጽደቅ የምንወድ ሰዎች ዛሬም አለን። ልባችንን የሚያውቅ አምላካችን ግን በቃሉ ንስሐ እንድንገባ ፣ ኃጢአታችንን እንድንናዝ ፣  ክፉ ማድረግንም እንድንተውና መልካም ማደረግን እንድንማር አዝዞናል።

ስለዚህ የሚያጸድቀው ከልብ “እኔን ኃጢአተኛዋ/ውን ማረኝ” የሚለው ብቻ ነው።

“ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም ፣ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል”

ምሳ 28 ፣13