እብድ መነኲሲት

ስለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ውለታና ፍቅር ራሷን እብድ  ያደረገችው መነኲሲት

ቅዱስ ጳኩሚስ ከመሠረታቸው የታቤኔዝ (ታቤኔሲዮት) ገዳማት መካከል ከወንዶች ገዳማት ራቅ ብሎ የተመሠረተ የሴቶች ገዳም ነበር። በዚያም ውስጥ አራት መቶ ሴቶች መነኮሳይያት ይኖሩ ነበር። በዚያ ገዳም ውስጥ ራሷን እንዳበደችና ርኲስ መንፈስ እንደያዛት የምታስመስል ድንግል ሴት ነበረች።

ሌሎቹ እርሷን ከመጸየፋቸው የተነሣ አብረዋት እንኳን አይበሉም ነበር ፤ እርሷ ግን ይህን ወደደችው። በምግብ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ወዲያ እና ወዲህ ትንከራተታለች፣ ሌሎች የተዉትንና የተናቀውን ማንኛውም ሥራ ትሠራለች፣ እነርሱ እንደሚሉት “የገዳሙ ቆሻሻ አስወጋጅ” ነበረች።

በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ከእህቶች መነኮሳይያት መካከል ማንም በአፏ ስታላምጥ አይተዋት አያውቁም፣ በማዕድም ተቀምጣ አታውቅም ነበር። ከማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪና የማዕድ ቤት እቃዎችን ስታጥብ ከዚያ በሚገኘው ነገር ብቻ ትኖር ነበር። ማንንም ተሳድባ ወይም ትንሽም ሆነ ብዙ አውርታ አታውቅም፤ ምንም እንኳ ብዙ ትሰደብ፣ ትነቀፍና ትረገም የነበረች ብትሆንም።

የእግዚአብሔር መልአክ ፒተሮአም ለሚባል ታላቅና ታዋቂ ለነበረ ታላቅ ባሕታዊ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፦ “እንዲህ ባለ ቦታ ስለመኖርህና ስለ ሃይማኖተኛነትህ ለምን በራስህ ትመካለህ? ከአንተ የበለጠ ሃይማኖተኛና ፍጹም የሆነችን ሴት ማየት ትፈልጋለህ? ወደ ታቤኔሲዮት ገዳም ሴቶች ሂድ በዚያም በራሷ ዘውድ የደፋች ሴት ታገኛለህ። እርሷ ከአንተ የበለጠች ናት፤ በብዙዎች መካከል ብትሆንም ልቧ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር ውጪ እንዲሄድ ፈጽሞ ፈቅዳለት አታውቅምና፣ አንተ ግን እዚህ ተቀምጠህ በሃሳብ በተለያዩ ቦታዎች ትዞራለህና” አለው።

ይህን ሲሰማ ከበኣቱ ወጥቶ የማያውቅ የነበረው ባሕታዊ ወደዚያ ገዳም ሄደና ወደ ገዳሙ ለመግባት ጠየቀ። የታወቀና በዕድሜው የገፋ አረጋዊ ባሕታዊ ስለነበር ወደ ሴቶቹ ገዳም እንዲገባ ፈቀዱለት። በዚያም ሁሉንም መነኮሳይያት ያያቸው ዘንድ ጠየቀ። ሆኖም እርሷ አልመጣችም። በመጨረሻም፦ “የቀረች አንዲት አለችና ሁሉንም አምጡልኝ” አላቸው።

እነርሱም፦ “በማዕድ ማዘጋጃ ቤት ያለች አንዲት እብድ ብቻ ናት የቀረችው” አሉት። እርሱም፦ “እርሷንም ጭምር አምጡልኝና ልያት” አላቸው። ሊጠሯት ሄዱ እርሷ ግን ነገሩን አውቃው ይሁን ወይም ጉዳዩ ተገልጦላት መልስ አልሰጠቻቸውም።

በግድ ጎተቷትና፦ “ታላቁ ፒተሮአም ሊያይሽ ይፈልጋል” አሏት። በመጣች ጊዜ ከራሷ ላይ ያለውን ብጣሽ ጨርቅ አሰበና ከእግሯ ላይ ወድቆ “ባርኪኝ” አላት። እርሷም እንዲሁ ከእግሩ ላይ ወድቃ “አባቴ ሆይ አንተ ባርከኝ” አለችው። ሁሉም መነኮሳይያት ተገረሙና፦ “አባ እንዳትሰድብህ ተጠንቀቅ እብድ ናት” አሉት። አባ ፒተሮአምም ሁሉንም፦ “እብዶችስ እናንተ ናችሁ እርሷ ግን የእኔም የእናንተም እናት ናት። በፍርድ ቀንም እንደርሷ የተዘጋጀሁና የተገባሁ ሆኜ እገኝ ዘንድ ምኞቴ ነው” አላቸው።

እነዚህን ነገሮች ከዚህ አባት ሲሰሙ ሁሉም ያደረጉባትን ነገር እየተናዘዙ ከእግሩ ላይ ወደቁ። አንዲቱ የውኃ እጣቢ አፍስሼባታለሁ ትላለች፣ ሌላዋ ደግሞ መትቻታለሁ ትላለች፣ ብቻ ብዙዎች አንዷ አንድ ሌላዋ ደግሞ ሌላ ነገር እንደፈጸሙባት በመናገር ይናዘዙ ጀመር። እርሱም ከጸለየላቸው በኋላ ሄደ።

ከጥቂት ቀናት በኋላ በእህቶቿ መነኮሳይያት የሚደረግላትን ክብር መሸከም ስለከበዳት እንዲሁም ፊት በበደሏት ነገር ሁሉ ይቅርታ አድርጊልን የሚሉት ነገራቸው ስለበዛባት ገዳሙን ጥላ ጠፋች። ወዴት እንደሄደችም ሆነ የት እንደተሰወረች ወይም እንዴት እንደሞተች ግን ማንም ያወቀ የለም።

በረከቷ ይደርብን!

በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ