መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፮
የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በፍቅርና በአንድነት መኖርን የሚሰብክ በመኾኑ ፍቺን አጥብቆ ይከለክላል፡፡ ከተጋቡ በኋላ የሕይወት መሰናክሎችን በመፍታት አብሮ መኖር እንጂ መለያየት ክርስቲያናዊ ሥርዓት አይደለምና፡፡ በመኾኑም ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ በመመካከርና በመፈቃቀር ተስማምቶ እስከ ሞት ድረስ መኖር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በትዳር ሕይወት እጅግ የከበደና መፍትሔ የሌለው ችግር ሊመጣ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ለጉዳዩ መፍትሔ በሚያመጣ መልኩ መወያየት፣ ከንስሓ አባት ጋር መመካከር፣ በጾም በጸሎት መትጋትና እግዚአብሔርን መማጸን ይገባል፡፡
ኾኖም በመካከላቸው በሃይማኖት ወይም ሊፈታ በማይችል ልዩ ልዩ ምክንያት ለጉዳትና ለሞት የሚያደርስ ግጭት በተደጋጋሚ ከተከሠተ፤ አንዳቸው ወይም ሁለቱም ከትዳር ውጪ ከሔዱ (ዝሙት ከፈጸሙ) እነዚህን ችግርች በምክክር መፍታት፣ በንስሓም ማጽዳት ካልተቻለ መፋታት ይፈቀዳል፡፡ ከዂሉም በላይ ከሁለቱ አንዱ በሞት ከተለየና በሕይወት የቀረው አካል ጋብቻ መመሥረት ከፈለገ ሁለተኛ ማግባት ይቻላል፡፡ ያም ኾኖ ግን በሕገ ቤተ ክርስቲያን ከተጠቀሰው ምክንያት በቀር መፋታት አይገባም (ፍትሐ ነገ. አን. ፳፬፣ ቍ. ፲፩-፲፯)፡፡
የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፭
ምሥጢረ ተክሊል ለደናግል ማለትም ክብረ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ለኖሩ ክርስቲያኖች ብቻ የሚፈጸም ሥርዓት ነው፡፡ ሥርዓቱ በዓላማ ጸንተው ክብራቸውን ጠብቀው ለቆዩ ዲያቆናትና ምእመናን ይፈጸማል፡፡ ከዚህ ላይ የዲያቆናት የጋብቻ ሥርዓት ከምእመናን የተለየ መኾኑን ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ምክንያቱም ወደ መዓርገ ቅስና የሚሸጋገሩበት አንዱ መሥፈርት ነውና፡፡ በሕግ የተወሰኑ ማለትም ትዳር የመሠረቱ ዲያቆናት (ቀሳውስት) በሞት ወይም በሌላ አስገዳጅ ምክንያት ከትዳር አጋራቸው ጋር ቢለያዩ ሁለተኛ ሚስት ማግባት አይፈቀድላቸውም፡፡ ካገቡም በመዓርገ ክህነት ማገልገል አይችሉም፡፡ ስለዚህም ዲያቆናት ሚስት በሚያጩበት ጊዜ ከምእመናን በተለየ መልኩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
በእርግጥ ምእመናን እንዲሁ ሳይጠናኑ ይጋቡ ለማለት ሳይኾን የክህነት ሕይወት ከምእመንነት ሕይወት ስለሚለይ ዲያቆናት አስተውለው ወደ ሕይወቱ እንዲገቡ ለማስታዎስ ነው፡፡ ምእመናን ከትዳር አጋራቸው ጋር በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ቢለያዩ ሁለተኛ ማግባት ይፈቀድላቸዋል፤ ዲያቆናት (ቀሳውስት) ግን ከአንድ ጊዜ በላይ ሚስት ማግባት አይችሉም፡፡ በክህነታቸው ለመቀጠል የግድ መመንኰስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕጉን ተላልፈው ወይም ፈቃደ ሥጋቸዉን ማሸነፍ አልችል ብለው ሁለተኛ ጋብቻ ከመሠረቱም ሥልጣነ ክህነታቸው ይያዛል (ይሰረዛል)፡፡ ከቀሳውስት (ዲያቆናት) በተለየ ሥርዓት ምእመናን ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር ቢፋቱ የተለያዩበት ምክንያት ተጣርቶ ሁለተኛ ጋብቻ መመሥረት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁለተኛ ጋብቻ በቍርባን እንጂ በተክሊል አይፈጸምም፡፡ ምክንያቱም ምሥጢረ ተክሊል ተጋቢዎቹ (ሁለቱም) ድንግልናቸውን አክብረው ከቆዩ ብቻ የሚፈጸምና የማይደገም ሥርዓት ነውና፡፡
የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፬
ጋብቻ ለመመሥረትና የትዳር አጋር ለመምረጥ የሚያስችል ዕድሜ ላይ የደረሱ ሰዎች ለጋብቻ ከተፈቃቀዱና ከተስማሙ በኋላ በቅድሚያ ለመምህረ ንስሓቸው ይነግራሉ፡፡ ከዚያም ለወላጆቻቸው (ለአሳዳጊዎቻቸው) ያሳውቃሉ፡፡ ጋብቻ የሚመሠረተው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ግንኙታቸው ወደ ኀጢአት እንዳይወስዳቸውና ከመጋባታቸው በፊት በሩካቤ ሥጋ እንዳይወድቁ መጠንቀቅ ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም እጮኛ መምረጥ ማለት መጋባት ማለት አይደለምና፡፡ የመተጫጨት ባህልና ሥርዓትን መጠበቅም ይገባል፡፡ ይህም ፈቃድና ስምምነትን፣ ዕድሜን፣ ዝምድናን፣ እንደዚሁም ሃይማኖትን ያገናዘበ መኾን ይኖርበታል፡፡
በመተጫጨት ጊዜ ሊታሰብበት የሚገባው ሌላኛው ጉዳይ የሚጋቡት ጥንዶች የዕድሜ ደረጃ ነው፡፡ የመተጫጫና የመጋቢያ ዕድሜም የወንዶች ከሃያ ወይም ከሃያ አምስት፤ የሴቶች ደግሞ ከዐሥራ አምስት ወይም ከዐሥራ ስምንት ዓመት በላይ ሊኾን እንደሚገባው በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተደንግጓል (ፍት. ነገ. አን. ፳፬፣ ምዕ. ፫፣ ክፍ. ፪)፡፡ ተጋቢዎቹ በዕድሜ ብዙ የተራራቁ ከኾነ በጋብቻቸው ላይ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ በተጋቢዎች መካከል ምንም ዓይነት ዝምድና እንዳይኖርም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ሥጋዊና መንፈሳዊ ዝምድናን ለማስጠበቅ ሲባል እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ መጋባት አይፈቀድም፡፡
የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፫
በሰርግ ቤት ደስታ፣ ጨዋታ፣ መብልና መጠጥ፣ የሙሽራውና የሙሽሪት አንድነት ይከናወንበታል፤ የሙሽራውና የሙሽሪት ዘመዶች አንድ ይኾኑበታል፡፡ መብልና መጠጡ የትምህርተ ወንጌል (የሥጋ ወደሙ)፤ ደስታና ጨዋታው የተአምራት፤ የሙሽራውና የሙሽሪት ተዋሕዶ የትስብእትና የመለኮት አንድነት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በሰርግ የሙሽራውና የሙሽሪት ዘመዶች አንድ እንደሚኾኑባት ዂሉ፣ በድንግል ማርያምም ሰውና መላእክት፣ ሰውና እግዚአብሔር፣ ነፍስና ሥጋ፣ ሕዝብና አሕዛብ አንድ ኾነውባታል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ‹‹ሙሽራዋ ንጹሕ የሚኾን የሰርግ ቤት›› ይላታል (የረቡዕ ውዳሴ ማርያም፣ አንድምታ ትርጓሜ)፡፡
ቅዱስ ኤፍሬም ዳግመኛም “ከመ ከብካብ ዘአልቦ ጥልቀት መንፈስ ቅዱስ ኀደረ ላዕሌኪ፤ እንደ ሰርግ ቤት አደፍ፣ ጉድፍ የሌለብሽ ኾነሽ ቢያገኝሽ መንፈስ ቅዱስ አድሮብሻል” በማለት እመቤታችንን ጋብቻ በሚፈጸምበት ንጹሕ የሰርግ ቤት መስሎ አመስግኗታል፡፡ ይህም በተመሳሳይ መልኩ የጋብቻን ክቡርነት የሚያመለክት ነው (ውዳሴ ዘቀዳሚት)፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እላለሁ” በማለት ጋብቻ የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ተዋሕዶ ምሳሌ መኾኑን ያመሠጠረልን (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡ በአጠቃላይ ጋብቻ፣ ይከብርበትና በጋራ ይኖርበት ዘንድ እንደዚሁም ራሱን ከኃጢአት ይጠብቅበት ዘንድ እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጅ ያዘጋጀው መንፈሳዊ ሥርዓት ነው፡፡
የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፪
የጋብቻ ክቡርነትና ምሥጢር ይህ ኾኖ ሳለ አንዳንዶቻችን ለጋብቻ የምንሰጠው ትርጕም ግን ዝቅ ያለ ይመስላል፡፡ በስውር ከጋብቻ ውጪ ፈቃዳቸዉን የሚፈጽሙ ምእመናን መኖራቸውም ከዚህ አመለካከት የመነጨ ነው፡፡ ከዚህ የተሳሳተ ግንዛቤ በመውጣትና ንጽሕናን በመጠበቅ አንድም ጋብቻ መመሥረት፤ ካለዚያም ራስን ጠብቆ በድንግልና ጸንቶ መኖር ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ ግዴታ ነው፡፡ ስለ ጋብቻ ሕይወት ሲነገር ከጋብቻ ዓላማዎች አንደኛው ከዝሙት ጠንቅ ለመሸሽ ነው፡፡ ይህም በሕጋዊ ሥርዓት ሩካቤ ሥጋን ለመፈጸም ያስችላል፡፡
ሩካቤ ሥጋ የተለየ ዓላማና ምሥጢር አለው፡፡ አፈጻጸሙም በሥርዓተ ተክሊል ወይም በሥርዓተ ቍርባን ይጸናል፡፡ በሕጋዊ ጋብቻ ተወስነን ካልኾነ በቀር ከጋብቻ በፊትም ኾነ በኋላ ካገኘነው ዂሉ ጋር ፆታዊ ግንኙነት መፈጸም ክቡራን ኾነን ተፈጥረን ሳለ በግብራችን ግን ከእንስሳት ጋር እንድንመሳሰል ያደርገናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ሰብእሰ እንዘ ክቡር ውእቱ ኢያእመረ ወኮነ ከመ እንስሳ ዘአልቦ ልብ ወተመሰሎሙ፤ ሰውስ ክቡር ኾኖ ሳለ አላወቀም፤ ልብ እንደሌላቸው እንስሳትም መሰለ” በማለት እንደ ተናገረው (መዝ. ፵፰፥፲፪)፡፡
የጋብቻ ሕይወት እና የሩካቤ ሥርዓት – ክፍል ፩
ቅዱስ ጳውሎስ የጋብቻን ታላቅነትና ልዩ ምሥጢር ባስተማረበት መልእክቱ “ይህም ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔም ይህንኑ ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ እናገረዋለሁ፤” በማለት የባልና የሚስት ጥምረት ወይም አንድነት የክርስቶስና የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መኾኑን ይናገራል (ኤፌ. ፭፥፴፪)፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ጋብቻ የመለኮት እና የትስብእት (የሰውነት) ምሳሌ መኾኑን መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ በዓለ ኀምሳ፣ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረታት የመድኀኒታችን ክርስቶስ ትንሣኤ የሚታሰብበት፣ ምሥጢረ ሥጋዌና ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን በስፋት የሚሰበክበት ወቅት ከመኾኑ አኳያ በእርግጥም በዚህ የደስታ ሰሙን የተዋሕዶ ምሳሌ የኾነውን ጋብቻን በቤተ ክርስቲያን መፈጸም ለምሥጢር የተመቸ መልእክት አለው፡፡
የዛሬዉን ትምህርታዊ ጽሑፍ በጋብቻ ዙርያ ያደረግነው ወቅቱን ለመዋጀት በማሰብ ነው፡፡ በእርግጥ ስለ ጋብቻ በልዩ ልዩ መንገድ ብዙ ጊዜ ተምረናል፡፡ ኾኖም ጉዳዩ የሕይወት ጉዳይ ነውና ደጋግመን መማማሩ ይጠቅመናል፡፡ አንዳዶቹ በማወቅም፣ ባለማወቅም ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ጋብቻቸውን ሲፈጽሙ ይስተዋላል፡፡ ስለ ጋብቻ በተደጋጋሚ መማማራችንም በማወቅ ወይም በግድየለሽነት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ትዳር የሚመሠርቱ ምእመናንን ለመመለስና ሌሎችም እንዳይስቱ ለመጠቆም ይረዳናል፡፡ ስለዚህም በዚህ ዝግጅት ስለ ጋብቻ አመሠራረት፣ ክቡርነት፣ ምሥጢር እና ዓላማ የሚያትት ተከታታይ ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን ትከታተሉ ዘንድ መንፈሳዊ ግብዣችንን እናስቀድማለን፡፡
አቡነ እስትንፋሰ ክርስቶስ
በረከት ለመቀበል ወደ ገዳሙ ለመሔድ ከወልድያ እስከ ዳውንት በመኪና የስምንት ሰዓታት መንገድ ይወስዳል፡፡ ከዳውንት ከተማ ወደ ገዳሙ አቅራቢያ የሚያደርሱ አነስተኛ ተሸከርካሪዎችም ይገኛሉ፡፡ ወደ ገዳሙ ለመግባት ለጠነከሩ የአንድ ሰዓት ያህል የእግር ጕዞ ይኖረዋል፡፡ የጻድቁ በዓለ ዕረፍት በሚከበርበት ዕለት (ሚያዝያ ዘጠኝ ቀን) ከወልድያ እስከ ገዳሙ የሚያደርሱ መጓጓዣዎች ስለሚገኙ ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ ገዳሙ በመሔድ ከበረከቱ ተሳታፊ እንዲኾኑ ገዳሙ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
ነገረ ትንሣኤ – ሦስተኛ ክፍል
ዕፅዋትና አዝርዕት ከፈረሱ፣ ከበሰበሱ በኋላ አንዱ በራሱ፣ ሌላው በጎኑ፣ ሌላው በሥሩ ያፈራል፡፡ ከሥሩ የሚያፈራው የባለ ሠላሳ፣ ከጎኑ የሚያፈራው የባለ ስልሳ፣ ከራሱ የሚያፈራው የባለ መቶ ምሳሌ ነው፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ዳግም ልደት›› ተብሎ ይጠራል፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮዎች ሁለት ዓይነት ሲኾኑ፣ እነዚህም ጥንተ ተፍጥሮና ሐዲስ ተፈጥሮ ይባላሉ፡፡ ጥንተ ተፈጥሯችን በአዳም በኩል የተደረገው ተፈጥሯችን ሲኾን፣ ሐዲስ ተፈጥሮ የምንለው ደግሞ በክርስቶስ በኩል የተደረገውን የባሕርያችንን መታደስ ነው፡፡ ልደታችን ግን ሦስት ወገን ነው፡፡ አንደኛው ሥጋዊ፣ ሁለተኛው መንፈሳዊ፣ ሦስተኛው ደግሞ ትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ ይህም “ልደተ ሙታን እመቃብር” ይባላል፡፡ ይኸውም የሙታን ከመቃብር መወለድ ማለት ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት ማለትም በትንሣኤ ዘጉባኤ ከሞት የምንነሣውም በዚህ መልኩ ነው፡፡
ነገረ ትንሣኤ – ሁለተኛ ክፍል
ለማርያም መግደላዊት መጀመሪያ ትንሣኤውን የገለጠውና ‹‹ሒደሽ ለወንድሞቼ ንገሪያቸው›› ብሎ የላካት ለምንድን ነው? ከተባለ ሞት ወደ ዓለም ሲገባ የተሰበከው በሴት አንደበት ነበር፤ በሴት እጅ በተቈረጠ ዕፀ በለስ፣ በሴት አንደበት በተሰበከ ስብከት ሞት ወረሰን፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቶቹ ርስት አይካፈሉም፤ ከቍጥር ገብተው አይቈጠሩም ነበር፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም ችግሮች በእርሱ ቤዛነት እንዳስቀረላቸው ለማጠየቅ ጌታችን ለሴቶች ተገለጠ፡፡ ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ ሴት፣ ሞትን በሰበከችበት አንደበቷ ትንሣኤውን እንድትነግር፤ ወደ ዕፀ በለስ በሮጠችባቸው እግሮቿ ወደ ሐዋርያት እንድትገሰግስ አደረገ፡፡ በዚያውም ላይ ቀዳማዊ አዳም ከእንቅልፉ ሲነቃ ከጎኑ ያገኛት ሔዋንን ነበር፡፡ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስም ከሞት በተነሣ ጊዜ ከመቃብሩ በአፍኣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶች ተገኝተዋል፡፡
ነገረ ትንሣኤ – የመጀመሪያ ክፍል
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ሞተ ወልደ እግዚአብሔርን በገለጸበት ቅዳሴው ‹‹ኦ አእዳው እለ ለኃኳሁ ለአዳም ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ኦ አእጋር እለ አንሶሰዋ ውስተ ገነት ተቀነዋ በቅንዋተ መስቀል ኦ አፍ ዘነፍሐ ውስተ ገጹ ለአዳም መንፈሰ ሕይወት ሰረበ ብሒአ፤ አዳምን የሠሩ እጆች በቀኖት ተቸነከሩ፤ በገነት የተመላለሱ እግሮች በቀኖት ተቸነከሩ፤ በአዳም ላይ የሕይወት እስትንፋስን እፍ ያለ አፍ መራራ ሐሞትን ጠጣ›› በማለት ያደንቃል፡፡ አዳምን የሠሩ የመለኮት እጆች ወይስ የትስብእት? በገነት ሲመላለሱ አዳም የሰማቸው እግሮች የመለኮት ወይስ የትስብእት? በአዳምስ ላይ የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ብሎ ልጅነትን ያሳደረበት ማን ነው? ሥጋ ነው እንዳንል ሊቁ እየተናገረ ያለው ቅድመ ተዋሕዶ ስለ ተፈጸመ ታሪክ ነው፤ መለኮት ነው እንዳይባል የመለኮት እጅና እግር በችንካር የሚመታ፣ አፉም እንኳን መራራውን ጣፋጩን ሊጠጣ የማይችል ንጹሐ ባሕርይ ነው፡፡ የሊቁ ቃል ይመልሰንና መለኮት በሥጋ መከራን እንደ ተቀበለ ያስረዳናል፡፡ እንደ ሰውነቱ ‹‹ተቸነከረ፤ መራራ ጠጣ›› እንላለን፡፡ እንደ አምላክነቱ ደግሞ የአዳም ፈጣሪ እንደ ኾነ እንናገራለን፡፡