• እንኳን በደኅና መጡ !

ዜናዎች፣ ወቅታዊ ክንውኖች እና ልዩ ልዩ ይዘቶች

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

“ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ” (ኢዩ.፩፥፲፬)

ከጾም የሥጋ ንጽሕና፣ የነፍስ ቅድስናና ድንግልና ይወለዳሉ።  ይህች ጾምም የጽድቅ ሥራዎች ሁሉ መርከብ ናት፤ በውስጧ የተከበሩ ዕቃዎች ሁሉ ይኖራሉ። ሩቅ ሀገር የሚሄዱት ያለ መርከብ በባሕር ላይ ፈጽሞ መሄድ እንዳይቻላቸው ሁሉ እንዲሁ ስለጽድቅ የሚጓዙትም በመንፈሳዊት ሐመር ካልታሳፈሩ አንዲት እርምጃ ስንኳን መራመድ አይቻላቸውም።” (ርቱዓ ሃይማኖት ገጽ ፺፩-፺፪)

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ

ግሩማን ፍጥረታት

ከአዳም ትውልድ ሰባተኛ የሆነው ነቢዩ ሄኖክ ያልተመረመሩ እጅግ አስደናቂ (ግሩማን) ፍጥረታትና አዕዋፍ ስለመኖራቸው ጨምሮ ሲጽፍ “ከዚያም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሄድኹ፤ በዚያም ታላላቅ አውሬዎችን አየሁ፤ አንዱ ከሌላው ልዩ ነው፤ የወፎቹም ፊታቸው ይለያያል፤ መልካቸው ቃላቸውም አንዱ ከሌላው ይለዋወጣል” ይላል፡፡ (ሄኖክ ፰፥፳፱)

ሥርዓተ አምልኮ

አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ፍጥረት ሁሉ እንዲያመልከውና እንዲመሰግነው ነው፤ በአርአያውና በአምሳሉ የተፈጠርን ሰዎች ብቻም ሳይሆን በደመ ነፍስ የሚንቀሳቀሱ እንስሳት ሳይቀር ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ፡፡ በተለይም በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን ሰዎች የምናመልክበት የቅድስና ሕይወት ሰጥኖናል፡፡ ሕጉን ጠብቀን በሥርዓቱ ለምንኖር ለእኛ እርሱ ምሕረቱ የበዛ በመሆኑ በሕይወታችን ውስጥ ሊኖር ይወዳል፤ በቤቱም ስንገኝ ደስ ይሰኛል፡፡ እርሱን በዓይን ለማየት ባይቻለንም መኖሩን የምናውቀበትና የምናመሰግንበት፣ ለእርሱም የአምልኮት ስግደት የምናቀርብበትና የምናዜምበት በአጠቃላይ የምናመልክበት መንገድ ፈጥሮልናል፡፡ ለዚህም የከበረ ተግባር መፈጸሚያ ባርኮና ቀድሶ ንዋያተ ቅድሳትን ሰጥቶናል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥር ፳፱ እስከ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም ለ ፫ ተከታታይ ቀናት በመላው ዓለም የታወጀው የነነዌ ፆም እና ምሕላ መጠናቀቅን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ፡፡

“መንፍስ ቅዱስ እናንተን ጳጰስ አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ …ተጠንቀቁ” (ሐዋ.፳፥፳፰)

ከዚህ ኃይለ ቃል ሦስት ነገሮችን እንማራለን፤ አንደኛ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር አምላክ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት መሆኑን፣ ሁለተኛ ጳጰስ አድርጎ የሚሾም መንፈስ ቅዱስ መሆኑን፣ ለመንጋውና ለራሳችን መጠንቀቅ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን መሰነባባቻ ባደረገው ንግግር ይህን ኃይለ ቃል ተናግሯል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሦስት ሺህ ዘመናት ውስጥ የቆየው ቀኖና፣ሥርዓተ ሢመት፣ ትውፊት ቅብብሎሽ በአሁኑ ዘመን ለመሻር መንጋውን እየበተነ አባቶችን እየሸረሸረ ያለውን ክስተት ሁሉ በየደረጃው ያለው የድርሻውን ለመወጣት ከማንኛውም ጊዜ በላይ በቁርጠኝነት የምንነሣበት ጊዜ መሆኑን ነው፡፡

በፌስቡክ የትስስር ገጽ ያግኙን

ስለ ማኅበረ ቅዱሳን መሰረታዊ መረጃዎች

ስያሜ

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያከበራቸው የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከርበት በመሆኑ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› የሚል ስያሜውን አግኝቷል፡፡

የማኅበሩ ርእይ

ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ የመሪነት ሚናዋን ስትወጣ ማየት

ተልእኮ

ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ መሳካት እና ለሕልውናዋ የሚተጋ፣ የተደራጀ ፣ ምሉዕ ኦርቶዶክሳዊ፤ ርቱዕ ዘመናዊ፤ ሁለገብ መሪ ትውልድ ማፍራት እና ማሰማራት

እሴቶች

  • መንፈሳዊነት

    ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
  • አገልጋይነት

    የማኅበሩ አባላት አገልግሎትን የክርስቲያናዊ ሕይወታቸው መገለጫ አድርገው በመቀበል በበጎ ፈቃድ ሰማያዊውን ክብርና ጸጋ በመሻት፣ ምድራዊ ክብርና ውዳሴ ከንቱን ሳይፈልጉ፣ በትሕትና እና በክርስቲያናዊ ፍቅር በታማኝነት ያገለግላሉ::
  • የሐሳብ መሪነት

    ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ አገልግሎት የሚያስፈልጉ፣ ኦርቶዶክሳዊ እሳቤን የተከተሉና ዘመኑን የዋጁ የመሪነት ሐሳቦችን በማፍለቅ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር በመመካከር ይሠራል::
  • ተባባሪነት

    ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሁሉም የቤተ ክርስትያን አካላት የወል ተግባር ነው ብሎ ያምናል:: በመሆኑም እንደየጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ባለ ድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመግባባት፣ በመመካከር እና በቅንነት ለተልእኮ አንድነት ብዝኃ ጸጋን በማክበር አብሮ ይሠራል::
  • ሙያ አክባሪነት

    የማኅበሩ አባላት ባላቸው ልዩ ልዩ ሙያ /ዕውቀት/ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተሰባሰቡ በመሆናቸው፣ በማኅበሩ አሠራሮች ሁሉ ከኦርቶዶክሳዊው ትምህርተ ሃይማኖት ጋር በማይጋጩ በእውነተኛ መረጃ ለሚደገፉ ሙያዊ ምክረ ሐሳቦች ተገቢውን ክብርና ቅድሚያ ይሰጣል:: በቤተ ክርስቲያንም ለመንፈሳዊ እና ለዘመናዊው (አስኳላ) ሙያ ተገቢው ክብር እንዲሰጥ ይሠራል::
  • ምክንያታዊ ሞጋችነት

    ማኅበሩ በእውነተኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ቤተ ክርስቲያንን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚፈትኑ አስተሳሰቦችን፣ አሠራሮችን፣ ልማዶችን እና ትርክቶችን በግልጽና በመንፈሳዊ ጥብዓት እና በእውነት እንዲሞገቱና መፍትሔ ላይ እንዲደረስ ይሠራል::
  • ተጠያቂነት

    የማኅበሩ አገልግሎት ግብ ሰማያዊ ዋጋ ማግኘት ስለሆነ ኀላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት በእግዚአብሔር እና በሰዎች ዘንድ የሚያስጠይቅ በመሆኑ በየትኛውም እርከን ላይ ያለ አባል እና አመራር በማኅበሩ አሠራር መሠረት በተሰጠው ኀላፊነት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ዓላማዎች

  • የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ አስተዳደር፣ የአሠራር ሥርዐትና አስተሳሰብ፣ በቴክኖሎጂ እና በልዩ ልዩ መንገዶች በመደገፍ ዘመኑን ለዋጀ ጠንካራ አገልግሎት ማብቃት፤
  • የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ሙሉ ሰብእናን የሚገነባ ሥርዐተ ትምህርት በማስተማር ዘመኑን የዋጁ ምሉዕ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያገለግሉ እንዲሁም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ በፖለቲካዊ እና በሀገር አስተዳደር ጉዳዮች መሪ/ንቁ ተሳታፊ አገልጋዮችን ማፍራት እና ማሠማራት፤
  • የተተኪውን ትውልድ ምንጭ ለማጎልበት የሰ/ት/ቤቶችን አቅም በማጠናከር የሕጻናት እና የወጣቶችን የተተኪነት ሚና ማሳደግ፤
  • ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነትን በተግባር የሚገልጽ ቤተሰብ እና አንድነቱን የጠበቀ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበረሰብ በመገንባት የተደራጀ እና የተናበበ አገልግሎት መስጠት፤
  • በተደራጀ እና ተደራሹን ማእከል ባደረገ መንገድ ስብከተ ወንጌልንና ሐዋርያዊ ተልእኮን ዘርፈ ብዙ በሆኑ መንገዶች በመላው ዓለም ማስፋፋት፤
  • በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነዙትን የርእዮተ ዓለም፣ የሐሰት ትርክቶች እና የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ ጥናት እና ምርምር ላይ ተመርኩዞ መሞገት እና የተሳሳቱትን በማረም፣ በጠንካራ የዕቅበተ እምነት አገልግሎት የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ማስጠበቅ፤
  • በተመረጡ ገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች የልኅቀት ማእከል እና የተለየ ክርስቲያናዊ ተልእኮ የሚፈጽሙ እንዲሆኑ የሚያስችል ሁለገብ የአእምሮ ልማት ድጋፍ ማድረግ፤
  • ማኅበሩ ዘመኑን የዋጀ ተቋማዊ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ተልእኮውን ማሳካት የሚችልበት አቅም መፍጥር ( በአመራር፣ በሰው ኃይል፣ በመንፈሳዊነት፣ በግንኙነት፣ በዕውቀት፣በልማት፣ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ)፤
  • ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የትብብር አገልግሎትን መርሕ ያደረገ የኦርቶዶክሳውያን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማሳደግ፣

አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
የሸዋ ሊቀ ጳጳስ ፲፱፻፴፪-፲፱፻፹፪ዓ.ም.

የማኅበሩ ህንጻ