• እንኳን በደኅና መጡ !

ዜናዎች፣ ወቅታዊ ክንውኖች እና ልዩ ልዩ ይዘቶች

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከቤተ ክርስቲያን በውግዘት ተለይተው የነበሩትን የዐሥራ ሰባቱ አባቶች ውግዘት ማንሳቱን በመግለጫው አሳወቀ።

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ ቀደም ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ክህነት ውጭ በሆነ መንገድ በራሳቸው ሥልጣንና በይገባናል ስሞታ የኦሮሚያ ሲኖዶስ መሥርተናል በሚል ተልእኮ ሲንቀሳቀሱ ቢቆዮም በይቅርታ መመለሳቸውን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ይህን ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሰጠ መግለጫ

በቅርቡ በተቋቋመው በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ በአገልጋዮቿ እና በምእመናን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ እና በደል አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተሰጠ መግለጫ።

“መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው?” (ቅዱስ ያሬድ)

ፈልፈለ ማኅሌት ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው እንዲህ እያለ ይዘምራል፤ “ገብር ኄር ወገብር ምእመን ገብር ዘአሥመሮ ለእግዚኡ፣ መኑ ውእቱ ገብር ኄር ወገብር ምእመን ዘይረክቦ እግዚኡ በምግባረ ሠናይ ወይሠይሞ ዲበ ኵሉ ንዋዩ ወካበ ይቤሎ እግዚአብሔር ገብር ኄር ወምእመን ዘበውኀድ ምእመነ ኮንከ ዲበ ብዙኅ እሠይመከ ባእ ውስተ ፍሥሓሁ ለእግዚእከ፤ጌታው በመልካም ሥራ የሚያገኘው በሐብቱ ሁሉ ላይ የሚሾመው የታመነ በጎ አገልጋይ ማን ነው? ዳግመኛም እግዚአብሔር አንተ የታመንክ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለኾንህ በብዙ እሾምሃለሁ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ ይለዋል፡፡” (ጾመ ድጓ) ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት ገብር ኄር ልጆቿን ስለ አገልግሎትና የአገልግሎት ዋጋ በስፋት የምታስተምርበት ሳምንት ነው።

ግብጻዊቷ ቅድስት ሣራ

ባለጸጋ ከሆኑ ግብጻዊ ወላጆቿ የተወለደቸው ቅድስት ሣራ በምንኩንስና ሕይወት የኖረች ተጋዳይ እንደነበረች ገድሏ ይናገራል፡፡ የመጋቢት ፲፭ (ዐሥራ አምስት) ቀን መጽሐፈ ስንክሳር እንደሚገልጸው ከልጅነት ጀምሮ በምንኩስና ሕይወት ቅንዓት ኖራለች፡፡ ወላጆቿ ክርስቲያናች ስለነበሩና ቅዱሳት መጽሐፍትን ማንበብና መጻፍ ስላስተማሯት በተለይም የመነኰሳትን ገድል ማንበብ ታዘወትር ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ ከላይኛው ግብጽ ወደ ሚገኝ ገዳም በመሄድ ለረጅም ዓመታት ደናግልን ስታገለግል ኖሯለች፡፡

ታማኝነት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁ? ታላቁ ዐቢይ ጾም እንዴት ነው? እንደ አቅማችሁ እየጾማቸችሁ ነው? የወላጆቻችሁ ድካማቸውና ክፍያቸው እናንተ ጎበዝ፣ ብልህ፣ አስተዋይና፣ ታማኝ ስትሆኑ ማየት ነውና በርቱ! ልጆች! ለዛሬ የምንማማረው ባለፈው የጀመርነውን ትምህርት የክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ቀጣዩን ክፍል “ታማኝነት” በሚል ርእስ ይሆናል፤ መልካም ቆይታ!

ዜና ዕረፍት

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት እና የውጪ ግንኙነት መምሪያ የበላይ ኃላፊ እንዲሁም የድሬዳዋና የጅቡቲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል። ብፁዕነታቸው ለረጅም ጊዜ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሊሻላቸው ባለመቻሉ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል።

በመንግሥትህ አስበኝ!

በሚያስፈራ ግርማህ በምጽዓት ቀን ስትገለጥ

በፊትህ የሚቆም ጠፍቶ ዓለም ሁሉ ሲንቀጠቀጥ

መልካሙን ዘር ከክፉው አበጥረህ ስትለያቸው

በፍርሃት ያርዳል የጽድቅ ፍሬ ለሌላቸው

ለእኔም ጨንቆኛል ዳግም የምትመጣበት

በደሌ ተቆጥሮ በሥራዬ የምመዘንበት

ዝክረ ግማደ መስቀሉ!

በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን (በ፫፻፳፯ ዓ.ም) የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ቅድት እሌኒ መስቀሉን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ ቅድት ዕሌኒ መስከረም ዐሥራ ስድስት ቀን በታሪክ አዋቂው አረጋዊው ኪራኮስ አማካኝነት ዕጣን እንዲጤስ አድረጋ በዕጣኑም ጢስ አመልካችነት መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ለማውጣት በመስከረም ፲፯ ቀን ቍፋሮ አስጀምራለች፡፡ ንግሥት እሌኒ ከመስከረም ፲፯ ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት ፲ ቀን ሌሊትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል የጉድፍን ኮረብታ ቆፍረው ቆሻሻውንም ካስወገዱ በኋላ ሦስት መስቀሎች ተገኙ፡፡ የጌታም መስቀል ሙት በማስነሣቱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ መስቀሉ የተገኘው መጋቢት ፲ ቀን ፫፻፳፮ ዓ.ም. ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ መስቀሉ ከተቀበረበት ተራራ ተቈፍሮ የወጣበት መጋቢት ፲ ቀንም በቤተ ክርስቲያን በደማቅ ሥርዓት ይከበራል፡፡ በተጨማሪም መስከረም ፲፯ ቀን ንግሥት ዕሌኒ ቅዳሴ ቤቱን ያከበረችበትን የመታሰቢያ በዓል ታቦት አውጥተው ዑደት በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ያከብሩታል፡፡ ከሦስቱ መስቀሎች መካከል ጌታችን የተሰቀለበት መስቀል የተለየው ተአምራት በማድረጉና ብዙ ድውያንን በመፈወሱ ነው፡፡

የበረሓው ኮከብ

በሕግ በሥርዓቱ ተጉዘው፣ ተጋድሏቸውን ፈጽመው፣ ዓለምን ንቀው፣ ከኃጢአት ሥራ ርቀው፣ በጽቅ ሥራ ደምቀው፣ የባሕሪው ቅድስናውን በጸጋ ተቀብለው፣ በቤቱና በቅጽሩ መታሰቢያ ከሰጣቸው አባቶቻችንን መካከል አንዱ ርእሰ ባሕታዊ ጻድቁ አባታችን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አንዱ ናቸው፡፡

በፌስቡክ የትስስር ገጽ ያግኙን

ስለ ማኅበረ ቅዱሳን መሰረታዊ መረጃዎች

ስያሜ

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያከበራቸው የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከርበት በመሆኑ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› የሚል ስያሜውን አግኝቷል፡፡

የማኅበሩ ርእይ

ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ የመሪነት ሚናዋን ስትወጣ ማየት

ተልእኮ

ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ መሳካት እና ለሕልውናዋ የሚተጋ፣ የተደራጀ ፣ ምሉዕ ኦርቶዶክሳዊ፤ ርቱዕ ዘመናዊ፤ ሁለገብ መሪ ትውልድ ማፍራት እና ማሰማራት

እሴቶች

  • መንፈሳዊነት

    ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
  • አገልጋይነት

    የማኅበሩ አባላት አገልግሎትን የክርስቲያናዊ ሕይወታቸው መገለጫ አድርገው በመቀበል በበጎ ፈቃድ ሰማያዊውን ክብርና ጸጋ በመሻት፣ ምድራዊ ክብርና ውዳሴ ከንቱን ሳይፈልጉ፣ በትሕትና እና በክርስቲያናዊ ፍቅር በታማኝነት ያገለግላሉ::
  • የሐሳብ መሪነት

    ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ አገልግሎት የሚያስፈልጉ፣ ኦርቶዶክሳዊ እሳቤን የተከተሉና ዘመኑን የዋጁ የመሪነት ሐሳቦችን በማፍለቅ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር በመመካከር ይሠራል::
  • ተባባሪነት

    ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሁሉም የቤተ ክርስትያን አካላት የወል ተግባር ነው ብሎ ያምናል:: በመሆኑም እንደየጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ባለ ድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመግባባት፣ በመመካከር እና በቅንነት ለተልእኮ አንድነት ብዝኃ ጸጋን በማክበር አብሮ ይሠራል::
  • ሙያ አክባሪነት

    የማኅበሩ አባላት ባላቸው ልዩ ልዩ ሙያ /ዕውቀት/ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተሰባሰቡ በመሆናቸው፣ በማኅበሩ አሠራሮች ሁሉ ከኦርቶዶክሳዊው ትምህርተ ሃይማኖት ጋር በማይጋጩ በእውነተኛ መረጃ ለሚደገፉ ሙያዊ ምክረ ሐሳቦች ተገቢውን ክብርና ቅድሚያ ይሰጣል:: በቤተ ክርስቲያንም ለመንፈሳዊ እና ለዘመናዊው (አስኳላ) ሙያ ተገቢው ክብር እንዲሰጥ ይሠራል::
  • ምክንያታዊ ሞጋችነት

    ማኅበሩ በእውነተኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ቤተ ክርስቲያንን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚፈትኑ አስተሳሰቦችን፣ አሠራሮችን፣ ልማዶችን እና ትርክቶችን በግልጽና በመንፈሳዊ ጥብዓት እና በእውነት እንዲሞገቱና መፍትሔ ላይ እንዲደረስ ይሠራል::
  • ተጠያቂነት

    የማኅበሩ አገልግሎት ግብ ሰማያዊ ዋጋ ማግኘት ስለሆነ ኀላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት በእግዚአብሔር እና በሰዎች ዘንድ የሚያስጠይቅ በመሆኑ በየትኛውም እርከን ላይ ያለ አባል እና አመራር በማኅበሩ አሠራር መሠረት በተሰጠው ኀላፊነት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ዓላማዎች

  • የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ አስተዳደር፣ የአሠራር ሥርዐትና አስተሳሰብ፣ በቴክኖሎጂ እና በልዩ ልዩ መንገዶች በመደገፍ ዘመኑን ለዋጀ ጠንካራ አገልግሎት ማብቃት፤
  • የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ሙሉ ሰብእናን የሚገነባ ሥርዐተ ትምህርት በማስተማር ዘመኑን የዋጁ ምሉዕ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያገለግሉ እንዲሁም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ በፖለቲካዊ እና በሀገር አስተዳደር ጉዳዮች መሪ/ንቁ ተሳታፊ አገልጋዮችን ማፍራት እና ማሠማራት፤
  • የተተኪውን ትውልድ ምንጭ ለማጎልበት የሰ/ት/ቤቶችን አቅም በማጠናከር የሕጻናት እና የወጣቶችን የተተኪነት ሚና ማሳደግ፤
  • ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነትን በተግባር የሚገልጽ ቤተሰብ እና አንድነቱን የጠበቀ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበረሰብ በመገንባት የተደራጀ እና የተናበበ አገልግሎት መስጠት፤
  • በተደራጀ እና ተደራሹን ማእከል ባደረገ መንገድ ስብከተ ወንጌልንና ሐዋርያዊ ተልእኮን ዘርፈ ብዙ በሆኑ መንገዶች በመላው ዓለም ማስፋፋት፤
  • በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነዙትን የርእዮተ ዓለም፣ የሐሰት ትርክቶች እና የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ ጥናት እና ምርምር ላይ ተመርኩዞ መሞገት እና የተሳሳቱትን በማረም፣ በጠንካራ የዕቅበተ እምነት አገልግሎት የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ማስጠበቅ፤
  • በተመረጡ ገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች የልኅቀት ማእከል እና የተለየ ክርስቲያናዊ ተልእኮ የሚፈጽሙ እንዲሆኑ የሚያስችል ሁለገብ የአእምሮ ልማት ድጋፍ ማድረግ፤
  • ማኅበሩ ዘመኑን የዋጀ ተቋማዊ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ተልእኮውን ማሳካት የሚችልበት አቅም መፍጥር ( በአመራር፣ በሰው ኃይል፣ በመንፈሳዊነት፣ በግንኙነት፣ በዕውቀት፣በልማት፣ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ)፤
  • ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የትብብር አገልግሎትን መርሕ ያደረገ የኦርቶዶክሳውያን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማሳደግ፣

አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
የሸዋ ሊቀ ጳጳስ ፲፱፻፴፪-፲፱፻፹፪ዓ.ም.

የማኅበሩ ህንጻ