በዓለ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል

ጥር ፳ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.

ዑራኤል የሚለው ስም “ዑር” እና “ኤል” ከሚሉ ሁለት ቃላት የተመሠረተ ነው። ዑራኤል ማለት ትርጉሙ “የብርሃን ጌታ”፣ ”የአምላክ ብርሃን” ማለት ነው። ቅዱስ ዑራኤል ከሰባቱ ሊቃነ መላእክት አንዱ ሲሆን ከፍጥረተ ዓለም ጀምሮ በመብረቅና በነጎድጓድ ላይ የተሾመ መልአክ ነው። ይህም የሆነው በከበረች ዕለት ጥር ፳፪ ነው፡፡

አምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ዑራኤልን በመባርቅት እና ነጎድጓድም ላይ ሾሞታል። (ሄኖክ ፮፥፪) መባርቅት ለጥጋብና ለበረከት እንዲበርቁ ነጎድጓድም ለሰላም እንዲሆን ይሰማራል። ምሥጢረ ሰማይና እውቀትንም ሁሉ ለሄኖክ የገለጸለትም የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትንና የሰማይ ሠራዊትን ብርሃንን የሚመራ እርሱ መሆኑን ለነቢዩ ሄኖክ ነግሮታል።

ቅድስት ድንግል ማርያምን ከልጇ ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወደ ግብጽ ስትሰደድ መንገድ የመራ፣ ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ በተሰቀለ ጊዜ ክቡር ደሙን በብርሃን ጽዋ ተቀብሎ በብርሃነ መነሳንስ በዓለም ላይ የረጨ፣ ለነቢዩ ዕዝራ ሱቱኤል ጽዋ ጥበብን ያጠጣ፣ ኢትዮጵያዊውን ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በርካታ ቅዱሳት መጻሕፍትን አንዲደርሱ ያገዘ፣ የረዳና የዕውቀት ጽዋን ያጠጣ መልአኩ ቅዱስ ዑራኤል ነው፡፡

የቅዱስ ዑራኤል ዓመታዊ ክብረ በዓላቱ የሚከበርባቸው ቀናትም እነዚህ ናቸው፤ ጥር ፳፪ በዓለ ሲመቱ፣ መጋቢት ፳፯ የጌታ ደሙን ለዓለም የረጨበት፣ ሐምሌ ፳፩ እና ፳፪ ቅዳሴ ቤቱ የሚከበርበት ነው።

የሊቀ መላእክት ቅዱስ ዑራኤል አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤ አሜን!!!