ሰባቱ ኪዳናት

ክፍል ሁለት

ጥር ፳፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም

ኪዳነ ኖኅ

ሰው በጥንተ ተፈጥሮ ለክብርና ለቅድስና ሕይወት ቢፈጠርም አምላኩ እግዚአብሔርን ክዶ ለጠላቱ ተገዢ ሲሆን ኃያሉ ፈጣሪ በረቀቀ ጥበቡ ሥጋን ለብሶ አድኖታል፡፡ ይህን ቃል የፈጸመበት ጥበቡ ሥጋን መልበስና መከራን መቀበል ነበር፡፡ ለዚህም ድንቅ ሥራው ከሰው ልጅ ከትውልድ ሐረግ መወለድ ስለ ሆነ ቃል ኪዳን ገባለት፡፡ ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው›› እንዲል፤ (መጽሐፍ ቀሌሜንጦስ ፪፥፳፫)

አዳም ይህን ቃል እንዲፈጸም በተስፋ የጠበቀ ቢሆንም ከአዳም እስከ ኖኅ ዘመን ድረስ ባሉት ፲ ትውልድ ዓለም ደግሞ በዓመፃ ተሞልታ ነበር፤ ‹‹ምድርም በእግዚአብሔር ፊት ተበላሸች፤ ምድርም ግፍን ተመላች›› ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈ አምላካችን በዚህ ጊዜ ለኖኅ እንዲህ አለው፤ ‹‹የሰው ሁሉ ጊዜው በፊቴ ደርሶአል፤ ከእነርሱ የተነሣ ምድር በግፍ ተመልታለችና፤ እኔም እነሆ፥ ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ፡፡›› (ዘፍ.፮፥፲፩-፲፫) ጻድቁን ሰው ኖኀን ግን አምላካችን በመርከብ ከልሎ አድኖታል፡፡ ‹‹እግዚአብሔርም ኖኅን አለው፦ “አንተ ቤተ ሰቦችህን ሁሉ ይዘህ ወደ መርከብ ግባ፤ በዚህ ትውልድ በፊቴ ጻድቅ ሆነህ አይቼሃለሁና›› እንዲል፡፡ (ዘፍ.፯፥፩)

የጥፋትን ውኃ ዳግም ምድር ላይ እንዳያመጣ እግዚአብሔር ለኖኅ በገባለት ቃል ኪዳን ድኅነትን አግኝቶአል፡፡ “ኪዳነ ኖኅ” የሰው ዘር ከአምላክ ዳግም በውኃ ሙላት እንዳይጠፋ የተገባለት ቃል ኪዳን ነው፤ ይህም የዘለዓለም ምልክት ነው፡፡ ያ ቃል ኪዳን መለኮታዊ ጥበቃ ሆኖለት ሰዎችን ከጥፋት ውኃ ጠላት የሚጠብቃቸው ነው፡፡

ጻድቁ ኖኅ ይኖር በነበረበት ዘመን የሰው ዘር በሙሉ አምላኩን በመበደሉ የፈጣሪያችን ቁጣ በማየሉ ምድርን በውኃ አጠፋት፡፡ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በዘነበው ዝናብም የሰዎች እንዲሁም የሌሎች ፍጥረት ሁሉ ዕልቅት ሆኗል፡፡ ኖኅ ወደ መርከቡ ይዞአቸው እንዲገቡ የታዘዘው የእንስሳት ዓይነቶች ብቻ ተረፉ፤ ኖኅ ጻድቅ ሰውና አምላኩን የሚያመልክ ስለ ነበር ከፈጣሪ ታዞ መርከብ በመሥራት ቤተ ሰቡን ሲያተርፍ ዓለም ግን በማየ ሥራዌ (ማየ አይህ) ጠፋች::

ከዚህም በኋላ ኖኅ ከመርከቡ ሲወጣ እግዚአብሔር በቀስተ ደመና ምልክትነት ቃል ኪዳን ገብቶለታል:: “ዳግመኛ በጥፋት ውኃ አይጠፋም፤ ምድርንም ለማጥፋት ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም” እንዲል:: (ዘፍ.፱፥፲፪)

ኪዳነ መልከ ጼዴቅ

ድኅነተ ዓለም የተፈጸመበት ድንቅ የአምላካችን ጥበብ በሥጋ መከራን መቀበልና በመልዕልት መስቀል ነበር፡፡ እርሱ ሞቶ ለእኛ ሕይወትን ሰጥቶናል፤ በቅዱስ መስቀሉ ላይ የቆረስልን ሥጋውና ያፈሰሰልን ደሙ ለነፍሳችን ፈውስ ሆኖልናል፡፡

ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይህን ድንቅ ሥራውን አስቀድሞ ለአባታችን አብርሃም አመልክቶታል፡፡ ለዚህም ግብር መፈጸም ለሰው የተገባለት ቃል ኪዳን “ኪዳነ መልከ ጼዴቅ” ነው፡፡ መልከ ጼዴቅ የተባለው ጻድቅ ሰው አባታችን አብርሃም በነበረበት ዘመን የኖረ ሰው ነው፡፡

አባታችን አብርሃም በእግዚአብሔር አምላክ በታዘዘው መሠረት ዐሥራቱን፣ በኩራቱንና ቀዳምያቱን ይዞ መልከ ጸዴቅ ይኖርበት ወደ ነበረው ተራራ ሲደርስ ባሕታዊ መልከ ጸዴቅ ይኖርበት ከነበረው ዋሻ በመውጣት ኅብስተ አኮቴት ጽዋ በረከት ይዞ ተቀብሎ መረቀው፡፡ አብርሃምም ዐሥራቱን በኩራቱን አቅርቦለታል፡፡ መልከ ጼዴቅም የሰጠው ኅብስተ አኮቴት ጽዋዕ በረከት የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ምሳሌ ነው፡፡ (ኦሪት ዘፍጥረት አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፲፬)

መልከ ጼዴቅ ደግሞ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌው የሆነ የሳሌም ንጉሥ ነው:: በ፲፭ ዓመቱ መንኖ፣ አጽመ አዳምን ይዞ፣ በቀራንዮ በኀብስትና በወይን ያስታኩት ነበር:: አምላካችን እግዚአብሔር ለሚሠራው ክህነትና ምሥጢረ ቁርባን ምሳሌ አድርጐ በቃል ኪዳን አትሞታል:: ካህኑ መልከ ጼዴቅ በዚህ ተሠውሮ የሚይኖር ሆነ እንጂ ሞትን እስካሁን አልቀመሰም:: ይህም ከአብርሃም ጋር በተገናኙበት ጊዜ ተገልጧል:: (ዘፍ.፲፬፥፲፯፣ ዕብ.፯፥፩)

በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን እኛ የሐዲስ ኪዳን ምእመናን ደግሞ በንስሓ ሕይወት በመመላለስ፣ በምግባር ጸንተን በመኖርና ለቅዱስ ቁርባን በመብቃት ድኅነተ ነፍስን እናገኛለን፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ሥጋና ቅዱስ ደሙ ለነፍሳችን መድኃኒት ነውና፡፡

ይቆየን!