ሥርዓተ ንባብ
ውድ አንባብያን ባለፈው ትምህርታችን ስለወዳቂ ንባብ መጻፋችንና ከላይ የቀረበውን ምንባብ መሠረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥያቄዎችንም ማቅረባችን ይታወቃል። መልሱን እንደሚከተለው እናቅርብና ወደሚቀጥለው ትምህርት እናመራለን።
ውድ አንባብያን ባለፈው ትምህርታችን ስለወዳቂ ንባብ መጻፋችንና ከላይ የቀረበውን ምንባብ መሠረት በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ጥያቄዎችንም ማቅረባችን ይታወቃል። መልሱን እንደሚከተለው እናቅርብና ወደሚቀጥለው ትምህርት እናመራለን።
ውድ አንባብያን በአለፈው ትምህርታችን ከምንባቡ ላይ ተነሽ ንባባትን እንድትጽፉ መልመጃ መስጠታችን ይታወቃል። እንደሠራችሁትም ተስፋ እናደርጋለን። ለማረጋገጥ ያህል ምንባቡንና መልሱን እንደሚከተለው እናቀርባለን።
ውድ አንባብያን በባለፉት ትምህርታችን ስምና የስም ዓይነቶች በሚል ርእስ በተከታታይ ማቅረባችን ይታወሳል፤ በዛሬውና በሚቀጥሉት ተካታታይ ትምህርታችን ደግሞ ስለ ንባብ ምንነት፣ ዓይነትና ስልት እንመለከታለን፤ መልካም ንባብ!
የስም ሙያ
ቃላት በዐረፍተ ነገር ላይ ያለ ሙያ ሊገቡ አይችሉም፡፡ ስምም ከቃል ክፍሎች እንደመሆኑ መጠን ያለ ሙያ በዐረፍተ ነገር ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ስም በዐረፍተ ነገር ውስጥ ሦስት ሙያዎች አሉት፡፡ እነሱም ባለቤትነት፣ ተሳቢነትና ቅጽልነት ናቸው፡፡
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
……ካለፈው የቀጠለ
ባለፈው ጽሑፋችን የስም ክፍሎችን አውጥተን እንድንዘረዝር መልመጃ ሠርተን ነበር፡፡ እንዲሁም ያወጣናቸውን ስሞች ዐረፍተ ነገር እያስገባን ሠርተን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ መራሕያን(ተውላጠ ስሞች)ን በመደብ፣ በቁጠርና በጾታ ከፋፍለን እንመለከታለን፡፡
መራሕያንን (ተውላጠ ስሞችን) በመደብ፣ በቁጥር እና በጾታ ከፋፍሎ ማጥናት ይቻላል፡፡
መደብ | ቀዳማይ (ቅሩብ) | አነ፣ ንሕነ |
ካልዓይ (ቅሩብ) | አንተ፣ አንትሙ፣ አንቲ፣ አንትን | |
ሣልሳይ (ርኁቅ) | ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ ይእቲ፣ ውእቶን |
ከላይ የሚያመለክተው ሠንጠረዥ መራሕያንን በመደብ የሚያሳይ ሲሆን ከቊጥር አንጻር ደግሞ እንደሚከተለው ይሆናል፡፡
ቊጥር | |
ነጠላ | ብዙ |
አነ | ንሕነ |
አንተ | አንትሙ |
አንቲ | አንትን |
ውእቱ | ውእቶሙ |
ይእቲ | ውእቶን |
ከላይ የሚያመለክተው ሠንጠረዥ መራሕያንን በቁጥር የሚያሳይ ሲሆን ከጾታ አንጻር ደግሞ እንደሚመለከተው ይሆናል፡፡
ጾታ | |
ተባዕታይ | አንስታይ |
አነ | አነ |
ንሕነ | ንሕነ |
አንተ | አንቲ |
አንትሙ | አንትን |
ውእቱ | ይእቲ |
ውእቶሙ | ውእቶን |
እንደማንኛውም የቋንቋ ትምህርት በግእዝ ቋንቋም የመደብ የጾታና የቊጥር ስምምነት አለ፡፡ ለምሳሌ አንተ ብለን ተሴሰየ ልንል አንችልም፡፡ እንዲሁም አንተ ብለን ተሴሰይኪ ልንል አንችልም፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያው ዐረፍተ ነገር የመደብ በሁለተኛው ዐረፍተ ነገር ደግሞ የጾታ መፋለስ ያስከትላል፡፡ መራሕያንን በመደብ በጾታና በቊጥር ከፋፍለን ስናጠናም ይህን ሁሉ መገንዘብ እንዲቻል ነው፡፡ በቋንቋ ባለሙያዎችም ሩቅና ቅርብን፣ አንድና ብዙን፣ ሴትና ወንድን ጠንቅቆ ማወቅ እንደሚገባ በሚገባ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ፡-
አንተ ካልን ተሴሰይከ
ውእቱ ካልን ተሴሰየ
አንቲ ካልን ተሴሰይኪ
ውእቶን ካልን ተሴሰያ
አንትን ካልን ተሴሰይክን ወዘተ እንላለን፡፡
የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ጸሐፈ የሚለውን ግስ እናንሳና በዐሥሩም መራሕያን እንመልከተው፡፡
አነ ጸሐፍኩ አንትን ጸሐፍክን
ንሕነ ጸሐፍነ ውእቱ ጸሐፈ
አንተ ጸሐፍከ ውእቶሙ ጸሐፉ
አንትሙ ጸሐፍክሙ ይእቲ ጸሐፈት
አንቲ ጸሐፍኪ ውእቶን ጸሐፋ
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
የተከበራችሁ አንባብያን ባለፈው ትምህርታችን ላይ የቤት ሥራ የሰጠናችሁ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በመሆኑም መልሱን እንደሚከተለው እንሥራ፡፡
፩. ምት፡- ሠናይት ብእሲት ታቀርብ ማየ እግር ለምታ፤ መልካም ሴት ለባሏ የእግር ውኃ ታቀርባለች፡፡
፪. ብእሲት፡- ብእሲ ወብእሲት አሐዱ አካል እሙንቱ፤ ባልና ሚስት አንድ አካል ናቸው፡፡
፫. ሥእርት፡- ሥዕርት ይትረከብ እምላዕለ ርእስ፤ ፀጒር ከራስ ላይ ይገኛል፡፡
፬. ምክዳን፡- ለብሓዊት ገብረት ምክዳነ ለጽሕርታ፤ ሸክላ ሠሪ ለማድጋዋ መክደኛን ሠራች፡፡
፭. ክሣድ፡- ጊዮርጊስ ወሀበ ክሣዶ ለሰይፍ፤ ጊዮርጊስ አንገቱን ለሰይፍ ሰጠ፡፡
፮. ገቦ ፡- ገቦ ኢየሱስ አውሐዘ ደመ ወማየ ለመድኃኒተ ኵሉ ዓለም፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ጎን ለዓለም ሁሉ መድኃኒት ደምና ውኃን አፈሰሰ፡፡
ማስታወሻ ፡- ከላይ ለተሰጡት ጥያቄዎች መልሱ ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ በዚህ አንጻር ሌላም ተስማሚ ዐረፍተ ነገር እንደሠራችሁም ተስፋ እናደርጋለን፡፡
መራሕያን
መራሕያን ማለት፣ መሪዎች ዋናዎች ማለት ነው፡፡ በነጠላው መራሒ የሚለው መራሕያን ብሎ ይበዛል፡፡ መራሕያን በሌላ አገላለጽ ተውላጠ ስሞች ማለት ነው፡፡
አነ እኔ አንትን እናንተ
ንሕነ እኛ ውእቱ እርሱ
አንተ አንተ ውእቶሙ እነሱ
አንትሙ እናንተ ይእቲ እሷ
አንቲ አንቺ ውእቶን እነሱ
የግእዝ መራሕያን በቊጥር ዐሥር ሲሆኑ ሁሉም በዐረፍተ ነገር እየገቡ የየራሳቸውን አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ መራሕያን (ተውላጠ ስሞች) በስም ቦታ እየገቡ የስምን ተግባር ያከናውናሉ፡፡ በስም ቦታ ብቻ ሳይሆን በግስ ቦታም እየገቡ ማሰሪያ አንቀጽ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ነባር አንቀጽ ይባላሉ፡፡ ማሰሪያ አንቀጽነታቸውን (ነባር አንቀጽነታቸውን) በሌላ ክፍል የምናይ ይሆንና በስም ቦታ እየገቡ የስምን አገልግሎት መያዛቸውን በዚህ እትም እንመለከታለን፡፡
፩. አነ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም፤ ለዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፡፡ (ዮሐ.፰፥፲፪)
፪. ንሕነ አባል ወውእቱ ርእስ፤ እኛ ሕዋሳቶች ነን እርሱም ራስ ነው፡፡
፫. አንተሰ አንተ ክመ ወአመቲከኒ ኢየኃልቅ፤ አንተ ግን ያው አንተ ነህ ዓመትህም ከቶ አያልቅም፡፡ (መዝ.፻፩፥፳፯)
፬. አንትሙ ውእቱ ፄዉ ለምድር፤ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፡፡ (ማቴ.፭፥፲፫)
፭. አንቲ ተዐብዪ እምብዙኃት አንስት፤ ከብዙ ሴቶች አንቺ ትበልጫለሽ፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘዐርብ)
፮. አንትን አንስት አሠንያ ማኅደረክን እናንተ ሴቶች ቤታችሁን አሣምሩ፡፡
፯. ውእቱ የአምር ኵሎ፤ እርሱ ሁሉን ያውቃል፡፡
፰. ውእቶሙ ተሰዱ እምሀገሮሙ፤እነርሱ ከሀገራቸው ተሰደዱ፡፡
፱. ይእቲ ተዐቢ እምኪሩቤል፤እርሷ ከኪሩቤል ትበልጣለች፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ)
፲. ውእቶን ደናግል ዐቀባ ማኅፀንቶን እነዚያ ደናግል አደራቸውን ጠበቁ፡፡
መራሕያንን ከዐረፍተ ነገር በዘለለ በአንድ አንቀጽ እንዴት አገልግሎት ላይ እንደሚውሉ እንመልከት፡፡
አነ ሶበ እጼሊ ወትረ አአኵቶ ለእግዚአብሔር እንዘ እብል አምላክ አንተ ለኵሉ ዘሥጋ ወለኵላ ዘነፍስ፤ ወንጼውዐከ በከመ መሐረነ ቅዱስ ወልድከ እንዘ ይብል አንትሙሰ ሶበ ትጼልዩ ከመዝ በሉ፤ ካዕበሂ እኄሊ ከመ አንትሙ ትብሉ ከመ ንሕነኒ ንሕድግ ለዘአበሰ ለነ::
ወኤፍሬምኒ ወደሳ ለድንግል እንዘ ይብል አንቲ ውእቱ ሰዋስው ዘርእየ ያእቆብ፤ እስመ ይእቲ ተነግረት በሕገ ኦሪት፡፡ ነቢያት ወሐዋርያት ሰበኩ ክርስቶስሃ፡፡ እስመ ውእቱ ከሠተ ሎሙ ወውእቶሙ አእመሩ በእንቲአሁ፡፡ ውእቱሂ ከሠተ ምሥጢረ ለአንስት ወይቤሎን አንትን ሑራ ንግራሆሙ ለአርዳእየ፡፡ ወውእቶን ሰበካ ትንሣኤሁ ለወልድ፡፡
ከላይ በተገለጸው ምንባብ ዐሥሩም መራሕያን አገልግሎት ላይ እንደዋሉ መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ይቆየን
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
ስም “ሰመየ፤ ስም አወጣ፣ ጠራ፣ ለየ” ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጉሙም መጠሪያ መለያ፣ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስም ማለት መጠሪያ፣ መለያ፣ አንድን አካል ከሌላው አካል የምንለይበት ማለት ነው፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም የምድር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ሁሉ ደግሞ ከምድር ፈጠረ፤በምን ስም እንደሚጠራቸውም ያይ ዘንድ ወደ አዳም አመጣቸው፤ አዳምም ሕያው ነፍስ ላለው ሁሉ በስሙ እንደጠራው ስሙ ያው ሆነ፡፡ አዳምም ለእንስሳት ሁሉ ለሰማይ ወፎችም ሁሉ ለምድር አራዊትም ሁሉ ስም አወጣለቸው” (ዘፍ፪፥፲፱-፳) እንዲል፡፡ በመጽሀፈ ቀሌምንጦስም “ወሰመዮሙ ለኵሎሙ በበአስማቲሆሙ ወተአዘዙ ሎቱ ኵሉ ፍጥረት ወዓቀቡ ቃሎ፤ አዳም ለሁሉም በየስማቸው ሰየማቸው፣ ስም አወጣላቸው፤ ፍጥረት ሁሉ ለአዳም ይታዘዝና ቃሉንም ይጠብቅ ነበር” (ቀሌ፩፥፵፪) በማለት ተጽፎ እናገኛለን
የስም ዓይነቶች ፡-
ባለፈው እትማችን እንደገለጽነው ስም ከቃል ክፍሎች አንዱ ሲሆን በውስጡ ደግሞ የራሱ የሆኑ ክፍፍሎች አሉት በስም ውስጥ የሚካተቱትን የስም ዓይነቶች ከተለያየ አንጻር የተለያየ አከፋፈል አለ፡፡ ለምሳሌ ከአገልግሎት አንጻር፣ከአመሠራረት አንጻር እና ሌሎችም ሁለቱን በዚህ ርእሰ ጉዳይ እንደሚከተለው እንመለከታለን፡፡
የስም ዓይነቶች ከአመሠራረት አንጻር በሁለት ይከፈላሉ፡፡ እነሱም፡-
፩. ዘር(ምሥርት ስም)፡-
ከግስ የሚመሠረቱት ስሞች ምስርት ስሞች ይባላሉ፡፡ የግስ ዘር ያላቸው ወይም አንቀጽ ያላቸው ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ፡- አምላክ፣ ፈጣሪ፣መልአክ፣ ሐራሲ፣ ሐናጺ፣ ቤት፣ ወዘተ
፪. ነባር ስም፡-
አንቀጽ የሌለው ሁሉ ነባር ይባላል፡፡ ነባር ማለት እርባታ የሌለው በቁም ቀሪ ማለት ነው፡፡ እቤርት፣ ዕብን፣ ዳዊት፣ ወዘተ
ማስታወሻ፡- ነባር ስም የሚባል እንደሌለ አንዳንድ ሊቃውንት ያስረዳሉ ከእነዚህ መካከል ኪዳነ ወልድ ክፍሌ አንዱ ናቸው፡፡ ምንጩ ማለት ቃሉ የተመሠረተበትን ግስ ስለማይታወቅ፣ ስላልተለመደ እንጂ ነባር የሚባል ስም የለም፡፡ ሁሉም የግሰ አንቀጽ አለው ባይ ናቸው፡፡
፪. የስም ዓይነቶች ከአገልግሎት አንጻር በአምስት ይከፈላሉ፡፡ እነሱም፡-
፩. ስመ ባሕርይ (የባሕርይ ስም)
፪. ስመ ተቀብዖ (የሹመት ስም)
፫. ስመ ግብር (የግብር ስም)
፬. ስመ ተጸውኦ (የመጠሪያ ስም)
፭.ስመ ተውላጥ (መራሕያን)
የባሕርይ ስም ፡- አምላክ፣ ፈጣሪ፣ እግዚእ፣ወዘተ
ስመ ተጸውዖ (የመጠሪያ ስም) ፡-
ይህ ስም እያንዳንዱ ሰው፣ እንስሳ፣ አራዊት፣ ዕፅዋት፣ ቦታ፣ ወዘተ ተለይቶ የሚጠራበት ስም ነው፡፡ “ፍጡር የሆነ ሁሉ ለግሉ የሚጠራበት ሰውም እያንዳንዱ ከእናት ከአባቱ ተሰይሞ እገሌ፣ እገሊት ተብሎ የሚጠራበት ይህን የመሰለ ሁሉ ነው” (መጽሐፈ ሰዋስው መጽሔተ አእምሮ፣ ገጽ ፮) እንዲል፡፡ ለምሳሌ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኢሳይያስ፣ ይድራስ፣ ሲና፣ ታቦር፣ ዘይት፣ ኢትዮጵያ፣ ኢየሩሳሌም፣ ከነአን
ስመ ተቀብዖ (የሹመት ስም) ፡-
ሰዎች ሲሾሙ የሚያገኙት ወይም የሚሰጣቸው የክብር ስም ነው፡፡ “የተቀብዖ ስም ሹመት ያለው ሁሉ …በመንፈሳዊና በሥጋዊ ነገር የሹመት ስም እርሱን የመሰለ ሁሉ ነው” ((መጽሐፈ ሰዋስው መጽሔተ አእምሮ፣ገጽ ፮) እንዲል፡፡ ለምሳሌ፡- ንጉሥ፣ ጳጳስ፣ ካህን፣ ዲያቆን፣ ሀቤ ምእት፣ መልአከ ሰላም፣ መለአከ ኃይል ወዘተ
ስመ ግብር (የግብር ስም) ፡-
ሥራን የሚገልጽ ስም ነው፡፡ “ፍጥረት ሁሉ በሥራው በግብሩ በአካሄዱ በነገሩ ሁሉ የሚጠራበት ነው ነው” (መጽሐፈ ሰዋስው መጽሔተ አእምሮ፣፮) እንዲል፡፡ ሐራሲ፣ ሐናጺ፣ መምህር፣ ለብሀዊ፣ ነጋዲ፣ ጸራቢ፣ ወዘተ
ስመ ተውላጥ፡- (መራሕያን) በስም ፈንታ የሚገቡ እንደስም የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
አነ፣ ንሕነ፣ አንተ፣ አንትሙ፣ አንቲ፣ እንትን፣ ውእቱ፣ ውእቶሙ፣ ይእቲ፣ ውእቶን ናቸው፡፡ መራሕያን
ከላይ የተገለጸውን ጽንሰ ሐሳብ በምሳሌ እንመልከተው፡፡
ጉባኤ ቃና
ኢክህለ ሞት ሐራሲ ዐዲወ ዕርገት ቀላይ፤
እስመ ለቀላይ ዕርገት ይመልኦ ደመና ዘቦ ሰማይ፡፡
ትርጉም
ሞት ገበሬ በዕርገት ወንዝ መሻገርን አልቻለም፤
ዕርገት ወንዝን ያለ የሆነ የሰማይ ደመና ይመላዋልና፡፡
ምሥጢሩ
ሰሙ፡- አንዳንድ ወንዝ እርሱ እንኮ ገና በደመና ነው የሚመላ ይባላል፡፡
ወርቁ፡- ጌታችን በደመና ማረጉን ለማስረዳት ነው፡፡
በዚህ ጉባኤ ቃና ከላይ በተመለከትነው ማብራሪያ መሠረት ነባርና ዘር(ምሥርት) ብለን በስም ክፍል ብቻ የሚመደቡትን እንጥቀስና የስም ክፍሎቻቸውን እንገልጻለን፡፡
ስም፡- ሞት፣ ሐራሲ፣ ቀላይ፣ ደመና፣ ዕርገት፣ ወልድ፣ አብ፣
ከአመሠራረት አንጻር የስም ዓይነት
ነባር ስም፡- ቀላይ
ምሥርት ስም፡- ሐራሲ፣ ደመና፣ ዕርገት፣ ወልድ፣ አብ፣
ከአገልግሎት አንጻር የስም ዓይነት
ስመ ተጸውዖ ፡- ወልድ፣ አብ፣
የግብር ስም ፡- ሐራሲ
እንዲሁ ሌላም እንጨምር
ሰላም ለኪ ፤እንዘ ንሰግድ ንብለኪ፤ ማርያም እምነ ናስተበቊዐኪ፤ እምአርዌ ነዐዊ ተማኅፀነ ብኪ፤ በእንተ ሐና እምኪ፤ ወኢያቄም አቡኪ፣ ማኅበረነ ዮም ድንግል ባርኪ፡፡
ስም፡- ማርያም፣ እምነ፣ አርዌ፣ ነዐዊ፣ ሐና፣ ኢያቄም፣ አቡኪ፣ ድንግል፣
ከአመሠራረት አንጻር የስም ዓይነት
ነባር ስም፡- ማርያም፣ ሐና፣ ኢያቄም ፣እምነ
ምሥርት ስም፡- አርዌ፣ ነዐዊ፣ አቡኪ፣ ድንግል፣
ከአገልግሎት አንጻር
ስመ ተጸውዖ ፡- ማርያም፣ ሐና፣ ኢያቄም
የግብር ስም ፡- ነዐዊ
የስምን ምንነትና የስም ዓይነቶችን ለአሁኑ እንዲህ ዓይተናል፡፡ በሚቀጥለው ደግሞ በየወገኑ በየወገኑ ከፋልፈልን የስምን ዓይነት ለምሳሌ ተዘምዶን የሚያመለክቱ፣ የአካል ክፍሎችን የሚያመለክቱ፣ የቁሳቁስ ወዘተ በማለት ከምሳሌ ጋር እንመለከታለን፡፡ እስከዚያው ግን ውድ አንባቢ የሚከተለውን መልመጃ ሠርተው እንዲቆዩ እናሳስባለን፡፡
መልመጃ
በሚከተለው ምንባብ ውስጥ ያሉትን ስሞች አውጥተህ/ሽ የስም ክፍላቸውን ዘርዝር/ሪ
ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ ታዐብዮ ነፍየ ለእግዚአብሔር ወትትሐሠይ መንፈስየ በአምላኪየ ወመድኃኒየ እስመ ርእየ ሕማማ ለአመቱ ናሁ እምይእዜሰ ያስተበፅዑኒ ኵሉ ትውልድ እስመ ገብረ ሊተ ኃይለ ዐቢያተ ወቅዱስ ስሙ ወሣህሉኒ ለእለ ይፈርህዎ ወገብረ ኃይለ በመዝራዕቱ ወዘረዎሙ ለእለ የዐብዩ ኅሊና ልቦሙ ወነሰቶሙ ለኃያላን እመናብርቲሆሙ አዕበዮሙ ለትሑታን ወአጽገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን ወፈነዎሙ ዕራቆሙ ለብዑላን ወተወክፎ ለእስራኤል ቊልዔሁ ወተዘከረ ሣህሎ ዘይቤሎሙ ለአበዊነ ለአብርሃም ወለዘርዑ እስከ ለዓለም፡፡
ስም………………………….
የስም ዓይነት
ስመ ተጸውዖ ………………..
ስመ ግብር …………………..
ስመ ባሕርይ…………………….
ስመ ተቀብዖ፡………………….
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
ቃል የፊደላት ስብስብ ሆኖ ልናስተላልፈው የፈለግነውን ሐሳብ የሚሸከም የሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው፡፡ ቃል የማይታይ፣ የማይዳሰስ፣ በጆሮ ብቻ የሚደመጥ ሲሆን ቋንቋ ትዕምርታዊ በመሆኑ እና ቃል ደግሞ የቋንቋ አንድ መዋቅር በመሆኑ በፊደላት አማካኝነት ይታያል፡፡ ይህ ጸሐፊ ብዕር ቀርጾ፣ ብራና ዳምጦ፣ ቀለም በጥብጦ በልቡናው ያለውን ሐሳብ ሲጽፈው ረቂቁ ይገዝፋል፤ የሚታይ፣ የሚዳሰስም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነው ቃል የፊደላት ስብስብ ሆኖ በልቡናችን ላለና ልናስተላልፈው ለፈለግነው ሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው የተባለው፡፡
ቃል ከምልክትነት ወይም ከቋንቋ መዋቅር ብቻ ሳይሆን ከትርጉም ሰጭ መዋቅርነት አንጻር የነገር ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ ፕሮፌሰር ባየ ይማም በመጀመሪያም ቃል ነበረ የሚለውን በዮሐንስ ወንጌል ዮሐ.፩፥፩ መሠረት አድርገው የቋንቋ ፍች ወይም ትርጉማዊነት መነሻ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ትርጉማዊ መዋቅር ከመመሥረት አንጻር ቃልን የሚቀድመው መዋቅር የለም፡፡ ፊደል ብንል ብቻውን ትርጉም ሊሰጠን አይችልም፡፡ ምዕላድ ብንልም ትርጉም አዘል እንላለን እንጂ ሙሉ ትርጉም ሊሰጠን አይችልም፡፡ ሙሉ ትርጉም ሊሰጠን የሚችል መዋቅር ቃል ስለሆነ የትርጉማዊ መዋቅር መነሻ እንለዋለን፡፡
የቃልን ምንነት ፕሮፌሰር ባየ ይማም የአማርኛ ሰዋስው በሚባል መጽሐፋቸው ከቃል የሚያንሰውን የቋንቋ ቅንጣት (ምዕላድን) ከአስረዱ በኋላ ቃልንም እንዲህ ይገልጹታል፡፡
-ትርጉም አዘል አሐድ ነው፡፡
-ራሱን ችሎ መቆም የሚችል ነው፡፡
-በውስጡ ብዙ ጥገኛ ምዕላዶችን ሊይዝ ይችላል፡፡
-ከቃላት ክፍሎች ውስጥ ባንዱ ሊመደብ ይችላል፡፡ ባየ (፳፻፱፥፸፭)
ከላይ የተገለጸው የቃል ብያኔ እንደ ማንኛውም ቋንቋ ነው፡፡ ግእዝም የራሱ የሆነ መለያ ባሕርይ ቢኖረውም እንደማንኛውም ቋንቋ የጋራ የሆኑትን የቋንቋ ባሕርይን፣ ብያኔንና መዋቅርን ይጋራልና የቃል ብያኔ በግእዝ ቋንቋም ከላይ የተገለጸውን እንጠቀማለን፡፡ በራሱ ሥርዓትና አገባብ ለመግለጽ አንድ ምንባብ እንጥቀስና በምሳሌ እናስረዳ፡፡
አቡነ ዘበሰማያት ይትቀደስ ስምከ ትምጻእ መንግሥትከ ወይኩን ፈቃድከ በከመ በሰማይ ከማሁ በምድር ሲሳየነ ዘለለእለትነ ሀበነ ዮም ኅድግ ለነ አበሳነ ወጌጋየነ ከመ ንሕነኒ ንሕድግ ለዘአበሰ ለነ ኢታብአነ እግዚኦ ውስተ መንሱት አላ አድኅነነ ወባልሀነ እምኵሉ እኵይ እስመ ዚአከ ይእቲ መንግሥት ኃይል ወስብሐት ለዓለመ ዓለም፡፡
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ ዕለት ዕለት እንድናመሰግነው ባዘዘንና ዘወትር በምንጸልየው ጸሎት (አቡነ ዘበሰማያት) በርካታ ቃላትን እናገኛለን፡፡ ሐሳብ በቃል ይገለጻል ብለናልና ሐሳባችንን ለመግለጽ ቃላትን ተጠቅመናል፡፡ ቃላቱ በሥርዓት ተዋቅረው ሙሉ መልዕክት እንድናስተላልፍ አድርገውናል፡፡ ቃላቱን በተወሰነ መልኩ ዘርዘር አድርገን እንመልከት፡፡
አቡነ፣ ሰማያት፣ ይትቀደስ፣ ስምከ፣ ትምጻእ፣ መንግሥትከ፣ ይኩን፣ ፈቃድከ፣ ሰማይ፣ ምድር፣ሲሳየነ፣ ዕለት፣ ሀበነ፣ ዮም፣ ኅድግ፣ ለነ፣ አበሳነ፣ ጌጋየነ፣ ንሕነ፣አበሰ፣ ኢታብአነ፣ እግዚኦ፣ ውስተ፣ መንሱት……..ወዘተ እነዚህ ሁሉ ከላይ ፕሮፌሰር ባየ ይማም በገለጹት መንገድ ቃል ለመባል የሚያስችለውን መስፈርት የሚያሟሉ የሐሳባችን ወካዮች ናቸው፡፡
ለምሳሌ አቡነ የሚለው ቃል መልእክት አለው አባታችን የሚለውን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ይቆማል፤ማለትም ፍች ይሰጣል፤ ምዕላድ ያስጠጋል፡፡ ይህ ማለት በዐሥሩ መራሕያን መርባት ይችላል፡፡ በዐሥሩ መራሕያን ሲረባ ጾታን፣ መደብን፣ ቁጥርን፣ ወዘተ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ዋና ቃሉ አብ የሚለው ሲሆን “ነ” የሚለውን ዘርፍ አመልካች ምዕላድ አስጠግቷል፤ ከቃላት ክፍሎች ባንዱ ይመደባል፤ ይህም ስም በሚለው የቃል ክፍል ገብቶ ይቆጠራል፡፡
“ይትቀደስ” የሚለውንም ቃል ብንወስድ መልእክት አለው ይመስገን የሚለውን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ይቆማል፤ ሌላ ፊደል ወይም ምዕላድ ሳይፈልግ ፍች ይሰጣል፤ ምዕላድ ያስጠጋል፡፡ ይህም ዋና ቃሉ ቀደሰ የሚለው ሲሆን በግስ እርባታ ሥርዓት “ይት” የሚለውን የሣልሣይ (የትእዛዝ) አመልካች ምዕላድ አስጠግቷል፤ በዐሥሩ መራሕያን መርባት ይችላል፡፡ በዐሥሩ መራሕያን ሲረባ ጾታን፣ መደብን፣ ቁጥርን፣ ጊዜን ወዘተ ያመለክታል፡፡ ከቃላት ክፍሎች ባንዱ ይመደባል፤ ይህም ግስ በሚለው የቃል ክፍል ገብቶ ይቆጠራል፡፡
ሐሳቡ ግልጽ እንዲሆን አንድ ተጨማሪ ምሳሌ እንጥቀስ፡፡ “እኩይ” የሚለው ቃል መልእክት አለው “ክፉ” የሚለውን ሐሳብ የተሸከመ ነው፡፡ ራሱን ችሎ ይቆማል፤ ሌላ ፊደል ወይም ምዕላድ ሳይፈልግ ፍች ይሰጣል፤ ምዕላድ ያስጠጋል ይህም “እምኵሉ” ከሚለው ቃል ኵሉ “እኩይ” ላይ ተቀፅሎ “እም” የሚለው አገባብ (ምዕላድ) የሚያርፈው እርሱ ላይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በራሱ የአረባብ ሥርዓት እየረባ መደብን፣ ቁጥርን፣ ጾታን ወዘተ መግለጽ ይችላል፡፡ ከቃላት ክፍሎች ባንዱ ይመደባል፤ ይህም ቅፅል በሚለው የቃል ክፍል ገብቶ ይቆጠራል፡፡
የቃል ክፍሎች
በማንኛውም ቋንቋ ቃላት ምድብ ( ክፍል) አላቸው፡፡ የቃላት አከፋፈል እንደየቋንቋው የተለያየ ነው፡፡ በግእዝ ቋንቋ ውስጥ የሚገኙት ቃላት በአምስት ይከፈላሉ እነሱም፡- ስም፣ ቅፅል፣ ግስ፣ ተውሳከ ግስ፣ አገባብ ናቸው፡፡ በእያንዳንዳቸው የቃል ክፍሎች በርካታ ክፍሎች አሉ፡፡ የቃል ክፍሎችን በተናጠል ስናይ የምንመለከታቸው ይሆናል፡፡ ከላይ በጠቀስነው ምንባብ ውስጥ የዘረዘርናቸውን ቃላት በቃላት ክፍል እየዘረዘርን እንመልከታቸው፡፡
ስም፡- አቡነ፣መንግሥትከ፣ ሰማይ፣ ምድር፣ ሲሣይ፣ አበሳ፣ ጌጋይ፣ ወዘተ
ቅፅል፡- እኩይ፣ መንሱት፣ ይእቲ፣ ኵሉ፣ ወዘተ
ግስ፡- ይትቀደስ፣ ትምጻእ፣ ይኩን፣ ሀበነ፣ ኅድግ፣ ንኅድግ፣ ኢታብአነ፣ ወዘተ
ተውሳከ ግስ፡- ዮም፣ ዓለም፣ ኵሉ
አገባብ፡- እስመ፣ ዘ፣ ወ፣ በ፣ ከመ፣ ከማሁ፣ አላ፣ እም፣ ለ፣ ወዘተ
በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አቡነ ዘበሰማያት አምስት መሠታዊ ጉዳዮችን ይይዛል፡፡ እነሱም ሃይማኖት፣ ተስፋ፣ ፍቅር፣ ተአምኖ ሐጣውዕ (ትሕትና) እና ጸሎት(ልመና) ናቸው፡፡ ይህን ጥልቅና ዘርፈ ብዙ ጽንሰ ሐሳብ ማስተላለፍ የቻልነው፣ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር የበቃነው በቃል አማካኝነት ነው፡፡ በእርግጥ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ለመግባባት የተዋቀሩ ቃላት፣ የሰዋስው ሥርዓት፣ የቋንቋ ጉዳይ ያስፈልገዋል ማለት አይደለም፡፡ እንደኛ ግን እርስ በእርስ ሰዎች እንድንግባባ ቋንቋ ያስፈልገናል፡፡ ከሰዎች ጋር በመናደርገው ተግባቦት ቋንቋ እንዳስፈለገን ሁሉ በመዋዕለ ስብከቱም እንደኛ ሰው በሆነበት ጊዜ በቋንቋ ከሰው ጋር ተግባብቷል፡፡ ዛሬም በዚህ አንጻር ሐሳባችንን በቃላት አማካኝነት ወደ እግዚአብሔር እናቀርባለን፡፡ ስለዚህ እርስ በእርሳችን ለመግባባት፣ ለእግዚአብሔር ያለንን ታዛዥነት፣ አምልኮታችንን ወዘተ ለሰዎች ለመግለጽ ቋንቋ መሠረት ነው፡፡የቋንቋ መሠረት ደግሞ ቃል ነውና ቃል ማለት ልናስተላልፈው የፈለግነውን ሐሳብ የሚወክልልን የሐሳብ ወካይ መግለጫ ነው በሚል እናጠቃልላለን፡፡
የቃልን ምንነትና የቃላት ክፍሎችን በአጭሩ እንዲህ ከተመለከትን በእያንድዳንዱ የቃላት ክፍሎች ውስጥ የሚኖረውን ክፍፍል (ዓይነት)፣ የቃላቱን ሙያ፣ መዋቅራዊ ሥርዓት ወይም የአገባብ ሥርዓታቸውን በሰፊው በዝርዝር የምንመለከት ይሆናል እስከዚያው ቸር እንሰንብት፤ አሜን፡፡
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
ሞክሼ ማለት ተመሳሳይ ስያሜ ኖሮት ተመሳሳይ ትርጉም ሲያስተላልፍ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአንድ ቋንቋ ውስጥ ሁለት የተለያዩ ምልክቶች በአንድ ድምፅ እየተጠሩ የትርጉም ለውጥ የማያመጡ ከሆነ ሞክሼ (ዘረ ድምፅ) ተብለው ይጠራሉ፡፡ ዘረ ድምፅ የሚባለው አንድ ድምፅ ከሌላ ድምፅ ጋር በተመሳሳይ ስያሜ እየተጠራ ነገር ግን የፍች ለውጥ የማያመጣ ከሆነ አንዱ ለሌላኛው ዘረ ድምፅ ይባላል፡፡ ለምሳሌ በአማርኛ ቋምቋ በድምፅ ቁጥር ውስጥ የሚጠናው “ህ” ሲሆን ሌሎች በተመሳሳይ ስያሜ የሚጠሩ “ሕ” እና “ኅ” አሉ እነዚህ በአማርኛ ቋንቋ ዘረ ደምፅ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ምክንያቱም የፍች ለውጥ ስለማያመጡ ነው፡፡
የቋንቋ ምሁራን የግእዝ ሞክሼ ፊደላትን በተመለከተ የተለያየ አመለካከት አላቸው፡፡
የሞክሼነትን ሁኔታ ከላይ በገለጽነው መሠረት አንድ ድምፅ በቅርጽ፣ በድምፅ፣ የሚለይ ከሆነና የፍች ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ዘረ ድምፅ ሊባል አይችልም፡፡ በግእዝ ቋንቋ ሞክሼ ፊደል የለም የሚሉት ምሁራን ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ ምክንያቱም በግእዝ ቋንቋ ተመሳሳይ ድምፅ፣ ተመሳሳይ ፍች፣ ተመሳሳይ ቅርጽ ያለው ድምፅ (ፊደል) ስለሌለ ነው፡፡ ይህ ሲባል ሀ፣ ሐ እና ኀ፣ ሰ እና ሠ፣ ጸ እና ፀ በተመሳሳይ ድምፅ ይጠሩ የለም የሚል ጥያቄ ቢነሳ ከጊዜ በኋላ ድምፀታቸውን አጥተው ነው እንጂ ተመሳሳይ አልነበሩም፡፡ በመሆኑም የሚፈጠሩበት ቦታ ( መካነ ፍጥረት)፣ ድምፆቹ ሲፈጠሩ በመካነ ፍጥረታቸው በሚያሳዩት ባሕርያት (ባሕርየ ፍጥረት)፣ እና የንዝረት ሁኔታ ማለትም በነዛሪነትና ኢ ነዛሪነት የተለያዩ እንደነበሩ ልብ ማለት ይገባል፡፡
ይህን ሐሳብ በአጽንዖት ከሚያስረዱን ምሁራን መካከል አንዱ መምህር ዘርዐ ዳዊት አድሐና እንደገለጹት ሐሳባቸውን እንደሚከተለው እንጥቀስ “በልሳነ ግእዝ ውስጥ ፊደል የሌለው ድምፅ፣ ድምፅ የሌለው ፊደል የለም፡፡ ወይም የተዳበለ ሞክሼ ፊደልና ድምፅ የለም፡፡ እያንዳንዱ ፊደለ ግእዝ የየራሱ ድምፅ አለው፡፡ ይሁን እንጂ “የሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ አ፣ ዐ፣ ሠ፣ ሰ፣ ጸ፣ ፀ ፊደላት ድምፃቸው ተዘንግቷል፡፡” ይሉንና የታሪክ ምሁራን ከሆኑት መካከል አክሊለ ብርሃን ወልደ ቂርቆስን (፲፱፻፵፰) መጽሔተ ጥበብ ስለ ግእዝና አማርኛ ቋንቋ ታሪክ በሚል የጻፉትን በመጥቀስ የእነዚህ ፊደላት ድምፆች እስከ ፲፭፻፴ ዓ.ም ድረስ ማለትም እስከ ዐፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት ድረስ የእነዚህ ፊደላት ድምፅ ተለይቶ ሲነገር እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ (ልሳናተ ሴም ገጽ፲፭)፡፡
በመሆኑም ዛሬ ላይ ድምፀታቸውን አጥተው በተመሳሳይ ድምፅ እየተጠሩ ስለሆነ ሞክሼ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ተመሳሳይ ድምፅ ስላላቸው ሞክሼ ግን ሊባሉ አይችሉም፡፡ ሞክሼ ፊደላት (ድምፅ) የምናገኘው በአማርኛ ቋንቋ እንጂ በግእዝ አይደለም፡፡ አማርኛ የድምፅ ሥርዓቱን ከግእዝ ሲዋስ በመካነ ፍጥረትና በባሕርየ ፍጥረት የተለያዩ ሆነው የየራሳቸው ንጥረ ድምፆች የነበሩትን፣ ነገር ግን ከጊዜ በኋላ ድምፀታቸውን ያጡትን ድምፆች ከነጠፋ ድምፃቸው ተውሷቸዋል፡፡ የፍች ሥርዓታቸውንም ትቶ እንዲሁ ከንጥረ ድምፆቹ ጋር በዘረ ድምፅነት እየተጠቀመባቸው ይገኛል፡፡
ከላይ እንደገለጽነው በግእዝ ቋንቋ ድምፀታቸውን ቢያጡም ማለትም መካነ ፍጥረታቸው፣ ባሕርየ ፍጥረታቸው፣ የንዝረት ሁኔታቸውን አጥተው በተመሳሳይ ድምፅ ቢጠሩም የፍች ለውጥ ያመጣሉ፡፡ በቋንቋ ጥናት ደግሞ የፍች ለውጥ ካመጣ ሞክሼ (ዘረ ድምፅ) አይባልም፡፡ ስለዚህ ከላይ በተገለጸው አገባብ ከሆነ በግእዝ ቋንቋ ሞክሼ ድምፅ የለም የሚለውን ሐሳብ እንድናጸና እንገደዳለን፡፡
ነገር ግን በተመሳሳይ ድምፀት በመጠራታቸው ሰዎች በጽሑፍ ሥርዓት ላይ አንዱን በአንዱ ቦታ እያቀያየሩ ይጽፏቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ስሕተቶች ይፈጠራሉ፡፡ በርከት ያሉ ምሳሌዎችን እያነሳን ስሕተቶችንም ለማሳየት እንሞክራለን፡፡
ቃል ፍች/ትርጉም
በርሀ ብርሃን ሆነ
በርሐ በራ ሆነ
ሠረቀ ወጣ፣ ተወለደ
ሰረቀ ሰረቀ
ኀለየ አሰበ
ሐለየ ዘፈነ
ኀመየ አሰረ፣ ቀፈደ
ሐመየ አማ
ሀደመ አንቀላፋ
ሐደመ አወጋ፣ ተረተ
ፈፀመ ዘጋ፣ አሰረ
ፈጸመ ጨረሰ
ከላይ የተዘረዘሩት በትክክለኛው አጻጻፍ የተቀመጡት ሲሆኑ የፊደላቱ መቀያየር ሊሰጠን የሚችለው ፍች እኛ ልናስተላልፈው ከፈለግነው የተገለበጠ ይሆናል፡፡
ለምሳሌ ሠረቀ በሥጋ እምድንግል ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ፣ ወአድኃነነ በሚለው ላይ ሰረቀ በሥጋ እምድንግል ዘእንበለ ዘርዐ ብእሲ ወአድኃነነ ብለን ብንጽፍ የምናገኘው ፍች፣ ከድንግል ያለ ወንድ ዘር በሥጋ ተወልደና አዳነን የሚለውን ሳይሆን፤ ከድንግል ያለ ወንድ ዘር በሥጋ ሰረቀና አዳንን የሚለውን ይሆናል፡፡ ከድንግል ያለ ወንድ ዘር መወለዱን ሳይሆን ሌብነትን የሚገልጽ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ይህንንስ አይሁድም አላሉት የተባለውን ነገር ይፈጠርብናል፡፡ የአንዲት ፊደል መለወጥ ይህን ያህል ስሕተት ትፈጥርብናለች፡፡
ሌላም ምሳሌ እናንሳ፡፡ ፈፀመ፣ ነጨ፣ አሰረ በሚለው ቦታ ፈጸመ የሚለውን “ጸ” ለመጠቀም ብንፈልግ የሚሰጠን ፍች እኛ ካሰብነው የተለየ ይሆናል፡፡ በምሳሌ ቢቀመጥ “ኦ ባዕል ሶበ ታከይድ እክለከ ኢትፍፅሞ አፉሁ ለብዕራይከ፤ እህልህን በምታበራይበት ጊዜ በሬውን አፉን አትሰረው፣ ለሚሠራ ደሞዙ ይገባዋልና” (፩ጢሞ.፭፣፲፰) በሚለው ቦታ ኢትፍጽሞ አፉሁ የሚለውን ብንጠቀም የምናገኘው ፍች ባለጸጋ ሆይ እህልህን በምታበራይበት ጊዜ የበሬህን አፉን አታፍነው የሚለውን ሳይሆን የበሬህን አፉን አትጨርሰው የሚለውን ይሆናል፡፡
በአጠቃላይ የግእዝ ቋንቋ ፊደላት እያንዳንዳቸው ሀልዎተ እግዚአብሔርን የሚያስረዱ፣ ሥርዓተ አምልኮን የሚያሳውቁ፣ የየራሳቸው ጥልቅ መልእክትን የሚያስተላልፉ ናቸው፡፡ እንዲሁም ፊደላቱ መግባት በሌለባቸው ቦታ ሲገቡም የሚፈጠረው ስሕተት የዚያን ያህል እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ ስለሆነም የፊደላቱን ትርጉም ጠንቅቀን አውቀን በየራሳቸው ቦታ እንድንጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ሁሉ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ይገልጽልን ዘንድ መልካም ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡ ይቆየን
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
የአበገደ ፊደላት የየራሳቸው መጠሪያ ስም እና ትርጉም አላቸው፡፡ በመጀመሪያ ፊደላቱን ከዚያም መጠሪያቸውን፤ ማለትም የሚወከሉበትና ትርጉማቸውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡-
አ ፡- አልፍ፤ አሌፍ ብሂል አብ ፈጣሬ ኵሉ ዓለም፤ አ፤ አልፍ፤ አሌፍ ማለት ዓለምን
ሁሉ የፈጠረ አብ ማለት ነው፡፡
በ፡- ቤት ፡- ቤት ብሂል ባዕል እግዚአብሔር፤ በ፤ ቤት፤ ማለት ባለጸጋ እግዚአብሔር
ማለት ነው፡፡
ገ፡- ጋሜል፡- ጋሜል ብሂል ግሩም እግዚአብሔር፤ ገ፤ ጋሜል ማለት የሚያስፈራ እግዚአብሔር
ማለት ነው፡፡
ደ፡- ዳሌጥ፡- ዳሌጥ ብሂል ድልው እግዚአብሔር፤ ደ፤ ዳሌጥ ማለት «ዝግጁ የሆነ» እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡
ሀ፡- ሄ ፡- ሄ ብሂል ህልው እግዚአብሔር፤ ሀ፤ ሄ ማለት እግዚአብሔር ህልው ዘለዓለማዊ ነው ማለት ነው፡፡
ወ፡- ዋው፡- ዋው ብሂል ዋሕድ እግዚአብሔር፤ ወ፤ ዋው ማለት እግዚአብሔር አንድ ነው
ማለት ነው፡፡
ዘ፡- ዛይ፡- ዛይ ብሂል ዝኩር እግዚአብሔር፤ ዘ፤ ዛይ ማለት እግዚአብሔር አሳቢ ነው
ማለት ነው፡፡
ሐ፡- ሔት፡- ሔት ብሂል ሕያው እግዚአብሔር ፤ሐ፤ ሔት ማለት ሕያው፤ ዘለዓለማዊ
እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡
ጠ፡- ጤት፡- ጤት ብሂል ጠቢብ እግዚአብሔር፤ ጠ፣ ጤት ማለት ጠቢብ፤ ጥበበኛ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡
የ፡- ዮድ፡- ዮድ ብሂል የማነ እግዚአብሔር፣እደ እግዚአብሔር፤ የ፤ ዮድ ማለት የእግዚአብሔር
ቀኝ ፤ የእግዚአብሔር እጅ ማለት ነው፡፡
ከ፡- ካፍ፡- ካፍ ብሂል ከሃሊ እግዚአብሔር፤ ከ፤ ካፍ ማለት ሁሉን ቻይ እግዚአብሔር
ማለት ነው፡፡
ለ፡- ላሜድ፡- ላሜድ ብሂል ልዑል እግዚአብሔር፤ ለ፤ ላሜድ ማለት እግዚአብሔር ታላቅ ነው
ማለት ነው፡፡
መ፡- ሜም፡- ሜም ብሂል ምዑዝ እግዚአብሔር፤ መ፤ ሜም ማለት ጣፋጭ እግዚአብሔር
ማለት ነው፡፡
ነ፡- ኖን፡- ኖን ብሂል ንጉሥ እግዚአብሔር፤ ነ፤ ኖን ማለት እግዚአብሔር ንጉሥ ነው ማለት ነው፡፡
ሠ፡- ሣምኬት፡- ሣምኬት ብሂል ሰፋኒ እግዚአብሔር፤ ሠ፤ ሣምኬት ማለት ገዥ እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡
ዐ፡- ዔ፡- ዔ ብሂል ዐቢይ እግዚአብሔር፤ ዐ፤ ዔ ማለት እግዚአብሔር ታላቅ ነው ማለት ነው፡፡
ፈ፡- ፌ ፡- ፌ ብሂል ፍቁር እግዚአብሔር፤ ፈ፤ ፌ ማለት እግዚአብሔር የሚወደድ ነው ማለት ነው፡፡
ጸ፡- ጻዴ፡- ጻዴ ብሂል ጻድቅ እግዚአብሔር፤ ጸ፤ ጻዴ ማለት እግዚአብሔር እውነተኛ ነው ማለት ነው፡፡
ቀ፡- ቆፍ፡- ቆፍ ብሂል ቅሩብ እግዚአብሔር ፤ ቀ፤ ቆፍ ማለት እግዚአብሔር ቅርብ ነው
ማለት ነው፡፡
ረ፡- ሬስ ፡- ሬስ ብሂል ርኡስ እግዚአብሔር፤ ረ፤ ሬስ ማለት እግዚአብሔር አለቃ ነው
ማለት ነው፡፡
ሰ፡- ሳን፡- ሳን ብሂል ስቡሕ እግዚአብሔር፤ ሰ፤ ሳን ማለት እግዚአብሔር ምስጉን ነው
ማለት ነው፡፡
ተ፡- ታው፡- ታው ብሂል ትጉህ እግዚአብሔር፤ ተ፤ ታው ማለት እግዚአብሔር ትጉህ ነው ማለት ነው፡፡
ኀ የሐ፤ እና ፀ የጸ ድርቦች ተደርገው የግእዝ ፊደል በቊጥር ፳፪ እንደሆኑ የሚገልጹ ሊቃውንት አሉ፡፡ ለምሳሌ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ኀ የሐ እና ፀ የጸ ድርቦች እንደሆኑ ሁለቱ ፊደላት ፐ እና ጰ ደግሞ ከጊዜ በኋላ እንደተጨመሩ ይገልጻሉ፡፡ የተጨመሩበትንም ምክንያት ሲያስረዱ ሁለቱ ፊደላት በጽርእ፣ በቅብጥና በሮማይስጥ ያሉ ፊደሎች ናቸው፡፡ አብዛኛዎቹ መጻሕፍት ደግሞ የተተረጎሙት ከእነዚህ ነውና መጻሕፍቱ ከተተረጎሙበት ቋንቋ ጋር ለማስማማት እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ፊደላት ነገረ እግዚአብሔርን እንደሚያስረዱ በሀለሐመ እንዲሁም በአበገደ አስረድተናል፡፡ የጥንቱ የግእዝ ፊደል የአበገደ እንደሆነ በአለፈውም ገልጸናል፡፡ ይህ የአበገደ የፊደል ቊጥር ፳፪ ነው ይህም የ፳፪ቱ ሥነ ፍጥረት ምሳሌ ነው፡፡ ስለዚህ ፊደል የዕውቀት ሁሉ መሠረት፤ የጥበብ ምንጭ ነውና ምርምራችንን ከፊደል እንድንጀምር ከሚል እሳቤ ይህን አቅርበናል፡፡
ማስታወሻ፡- ኀ የሐ፣ ፀ የጸ ድርቦች ናቸው ስለተባለ ግን የትርጉም ልዩነት አያመጡም ወይም ተመሳሳይ ድምፆች ( ዘረ ድምፆች) ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ሠረቀ፡- ወጣ፤ ተወለደ፤ ሰረቀ፡- ሰረቀ፤ በንጉሡ «ሠ» እና በእሳቱ «ሰ» ሲጻፍ የትርጉም ልዩነት እንደሚያመጣ ሁሉ ኀ እና ፀም የትርጉም ልዩነት ያመጣሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ፈፀመ በፀሐዩ “ፀ” ሲጻፍ አሰረ፤ ለጎመ፤ የሚል ትርጉም ሲሰጥ፤ ፈጸመ በጸሎቱ «ጸ» ሲጻፍ ደግሞ ጨረሰ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ እንዲሁም ነስሐ በሐመሩ «ሐ» ሲጻፍ ተጸጸተ፣ ተመለሰ የሚል ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን ነስኀ በብዙኃን «ኀ» ሲጻፍ ደግሞ ሸተተ፤ ከረፋ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡ ስለዚህ በቋንቋ ሥርዓት አንድ ድምፅ የፍች (የትርጉም) ለውጥ ካመጣ ሞክሼ ወይም ዘረ ድምፅ ሊባል አይችልም፡፡ በመሆኑም ራሳቸውን የቻሉ የግእዝ ድምፆች እንደሆኑ ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡
ምንጭ፡- ሐመር ፳፮ኛ ዓመት ቁጥር ፲