ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ

በሊቀ ትጉሃን ኃይለ ጊዮርጊስ ዳኘ

ሚያዝያ   ቀን ፳፻፲ .

ከዕለተ ትንሣኤ እስከ ዳግም ትንሣኤ ባሉት ዕለታት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ልክ እንደ መጀመሪያው የትንሣኤ ሥርዓት ኾኖ ይከናወናል፡፡ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ እሑድ ድረስ የሚገኙት ዕለታትም ‹ሰሙነ ፋሲካ› ወይም ‹ትንሣኤ› እየተባሉ ይጠራሉ፤ የየራሳቸው ምሥጢራዊ ስያሜም አላቸው፡፡ ስያሜአቸውንም በአጭሩ እንደሚከተለው እንመለከታለን፤

ሰኞ

የትንሣኤው ማግሥት ዕለተ ሰኞ ‹ፀአተ ሲኦል› ወይም ‹ማዕዶት› ትባላለች፡፡ ይህቺውም ጌታችን በትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ናት (ዮሐ. ፲፱፥፲፰፤ ሮሜ. ፭፥፲-፲፯)፡፡

ማክሰኞ 

ይህቺ ዕለት፣ ለሐዋርያው ቶማስ መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቶማስ› ተብላ ትጠራለች፡፡ የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ከእነርሱ ጋር አልነበረም፡፡ በመጣ ጊዜ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት ‹‹ሳላይ አላምንም›› ብሎ ነበር፡፡ በሳምንቱ እርሱ በተገኘበት ጌታችን በድጋሜ ለሐዋርያት ተገለጸ፡፡ ስለዚህም ይህቺ ዕለት በሐዋርያው ቶማስ ስም ተሰይማለች (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡ 

ረቡዕ 

ጌታችን ከሞተና ከተቀበረ ከአራት ቀናት በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላስነሣው ለአልዓዛር መታሰቢያ ናት፡፡ በክርስቶስ ሥልጣን የአልዓዛርን ከሞት መነሣት አይተው ብዙ ሕዝብ በጌታችን ስለ አመኑ ዕለቲቱ (ረቡዕ) ‹አልዓዛር› ተብላ ትታሰባለች (ዮሐ. ፲፩፥፴፰-፵፮)፡፡ 

ኀሙስ 

ይህቺ ዕለት ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ (አምስት ሺሕ ከአምስት መቶ ዓመት ሲፈጸም) ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ተብሎ ቃል የተገባለት የአዳም ተስፋው ተፈጽሞ ከነልጅ ልጆቹ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ኾና ‹የአዳም ኀሙስ› ወይም ‹አዳም› ተብላ ትከበራለች (ሉቃ. ፳፬፥፳፭-፵፱)፡፡ 

ዐርብ

የትንሣኤ እሑድ ስድስተኛዋ ዐርብ ደግሞ በክርስቶስ ደም ለተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቤተ ክርስቲያን› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱፤ ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት

በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበያይባት ‹የቁራ ገበያ፣ የገበያ ጥፊያ› ተብላ ትጠራለች፡፡ በቤተ ክርስቲያን ደግሞ ጌታችን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጕልበታቸው ላገለገሉት፤ በስቅለቱ ጊዜ እስከ ቀራንዮ ድረስ ለተከተሉት፤ በትንሣኤው ዕለት በሌሊት ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው ለገሰገሱት፤ በትንሣኤውም ጌታችንን ከዅሉ ቀድሞ ለማየት ለበቁት ሴቶች መታሰቢያ ትኾን ዘንድ ‹ቅዱሳት አንስት› ተብላ ትጠራለች (ማቴ. ፳፭፥፩-፲፩፤ ሉቃ. ፳፫፥፳፯-፴፫፤ ፳፬፥፩-፲)፡፡

እሑድ ሰንበት

በዋናው ትንሣኤ ሳምንት የምትመጣዋ ዕለተ እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብላ ትዘከራለች፡፡ ከላይ እንደ ተጠቀሰው ጌታችን በትንሣኤው ዕለት ማታ በዝግ በር ገብቶ፣ በቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ተገኝቶ ‹‹ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!›› በማለት ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ ጌታችን እንደ ተነሣ እና እንደ ተገለጸላቸው ሐዋርያት በደስታ ሲነግሩት ‹‹በኋላ እናንተ ‹አየን› ብላችሁ ልትመሰክሩ፤ ልታስተምሩ፤ እኔ ግን ‹ሰምቼአለሁ› ብዬ ልመሰክር፤ ላስተምር? አይኾንም፡፡ እኔም ካላየሁ አላምንም›› አለ፡፡

ስለዚህም የሰውን ዅሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው የወዳጆቹን የልብ ዐሳብ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ልክ እንደ መጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በተዘጋ ቤት በአንድነት ተሰባስበው እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ ‹‹ሰላም ለዅላችሁ ይኹን!›› በማለት በመካከላቸው ቆመ፡፡ ቶማስንም ‹‹ያመንህ እንጂ ተጠራጣሪ አትኹን፤ እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ፤›› ብሎ አሳየው፡፡

እርሱም ምልክቱን በማየቱ፣ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደ ፍላጎቱ በመረዳቱ ‹‹ጌታዬ፣ አምላኬ ብሎ መስክሮ›› የክርስቶስን ትንሣኤ አመነ፡፡ የሳምንቷ ዕለተ ሰንበት፣ የትንሣኤው ምሥጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት በመኾኑ የትንሣኤው ሳምንት እሑድ ‹ዳግም ትንሣኤ› ተብሎ ይጠራል፤ ይከበራል (ዮሐ. ፳፥፳፬-፴)፡፡

ብርሃነ ትንሣኤውን የገለጸልን አምላካችን ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን”

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

መጋቢት ፴ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

 “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን አሰሮ ለሰይጣን አግዐዞ ለአዳም ሰላም እምይዕዜሰ ኮነ ፍሥሐ ወሠላም፤ ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ዲያብሎስን አሰረው፤ አዳምን ነጻ አወጣው፡፡ ሰላም! ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ኾነ፡፡”

ይህ ኃይለ ቃል የትንሣኤው የምሥራች ለምእመናን የሚታወቅበት ኃይለ ቃል ነው፡፡ የሚቀድስ ካህን፣ ሰባኪ በዘመነ ትንሣኤ ከስብከቱ አስቀድሞ በዚህ ኃይለ ቃል የክርስቶስን መነሣት ያውጃል፡፡ የሚቀድሰው ካህንም በኪዳን ጊዜ ሕዝቡን ከመባረኩ አስቀድሞ ይህንኑ ቃል ይናገራል ሰላምታ የሚቀባበሉ ምእመናንም ሰላምታ ከመስጠት አስቀድሞ ይህን ቃል በመናገር የትንሣኤውን አዋጅ ማወጅና መመስከር ይገባቸዋል፡፡

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን! አደረሳችሁ!

የክርስቶስ ትንሣኤ እንደ እንግዳ ደራሽ፣ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም፡፡ ከጥንት በነቢያት የተነገረ፤ በኋላም እርሱ ክርስቶስ ከመሞቱ አስቀድሞ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማረው፤ ደግሞም በመነሣት የገለጠው፤ ሐዋርያትም በግልጥ ለዓለም የመሰከሩት ምሥጢር ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ በትንቢተ ነቢያት

  • “እኔ ተኛሁ፤ አንቀላፋሁም፡፡ እግዚአብሔር አስነሥቶኛልና ተነሣሁ፤” (መዝ. ፫፥፭)፡፡
  • “እግዚአብሔር ይላል፤ ‹አሁን እነሣለሁ፤ መድኀኒት አደርጋለሁ፤ በእርሱም እገልጣለሁ፤›” (መዝ. ፲፩፥፭)፡፡
  • “እግዚአብሔር ይነሣል፤ ጠላቶቹም ይበተናሉ፡፡ … እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፡፡ ጠላቶቹንም በኋላው መታ፤” (መዝ. ፸፯፥፷፭)፡፡

ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ የክርስቶስን ከሙታን መነሣት አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ እርሱን መሰል ነቢያት ክርስቶስ እንደሚሞት በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ ገልጸዋል፡፡ ምሳሌ ተመስሏል፤ ትንቢትም ተነግሯል፡፡ ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በዓሣ አንበሪ ሆድ እንደ አደረ ክርስቶስም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር አድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ብርሃነ መለኮቱን ገልጾ እንደሚነሣ ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ወልድ ተናግሯል (ዮና. ፪፥፩፤ ማቴ. ፲፪፥፵)፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ሆሴዕም “ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፡፡ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል፡፡ በፊቱም በሕይወት እንኖራለን፤” በማለት የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛም ትንሣኤያችን፤ ሕይወታችን መኾኑን ገልጾ ተናግሯል (ሆሴ. ፮፥፪)፡፡ በተጨማሪም “ሞት ሆይ፥ መውጊያህ ወዴት አለ? ሲኦል (መቃብር) ሆይ፥ ድል መንሳትህ ወዴት አለ?” ብሎ ሞት እና መቃብር ሥልጣናቸው በክርስቶስ እንደ ተሻረ፤ በክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆች ትንሣኤ እንደ ተገለጸ ነግሮናል (ሆሴ. ፲፫፥፲፬)፡፡

በኦሪት ዘፍጥረት ፵፱፥፱ ላይ “ልጄ ሆይ፥ ከመሰማሪያህ (ከመቃብር) ወጣህ፡፡ እንደ አንበሳ ተኛህ፤ አንቀላፋህም፡፡ እንደ አንበሳ ደቦል የሚቀሰቅስህ የለም፤” የሚል ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡ በዚህ ኃይለ ቃል “የሚቀሰቅስህ የለም” የሚለው ክርስቶስ በገዛ ሥልጣኑ አስነሽ ሳይሻ ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ የሚያስረዳ ነው፡፡ ጌታችንም በራሱ ሥልጣን እንደሚነሣ እንዲህ በማለት አስተምሯል፤ “እንደ ገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና ከእኔ ማንም አይወስዳትም፤ ነገር ግን እኔ በፍቃዴ እሰጣታለሁ፡፡ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ፤ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና፤” (ዮሐ. ፲፥፲፯)፡፡ ይህ የሚያስረዳን ክርስቶስ ለዓለም ቤዛ ኾኖ በፈቃዱ እንደ ሞተና በሥልጣኑ እንደ ተነሣ ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ በሐዲስ ኪዳን

አራቱም ወንጌላውያን እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ኾነው የክርስቶስን ትንሣኤ በወንጌል ጽፈውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ምዕራፍ ፳፰፥፩-፲፮ “በሰንበትም ማታ ለእሑድ አጥቢያ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ፡፡ እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ኾነ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዷልና፡፡ ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ” ይላል፡፡ በዕለተ ትንሣኤ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማየት መላእክት እንደዚሁም ቅዱሳት አንስት ተገኝተዋል፡፡ ሲወለድ የመወለዱን ዜና ለእረኞች የተናገሩ መላእክት በትንሣኤው ዕለትም ዜና ትንሣኤውን ለቅዱሳት አንስት ለማብሠር ከመቃብሩ ተገኝተው የትንሣኤው ምስክሮች ኾነዋል፡፡

ጌታችን ከሙታን ተለይቶ በተነሣ ጊዜም መቃብር ጠባቂዎቹ ከመለኮቱ ግርማ የተነሣ ታውከዋል፤ እንደ በድንም ኾነዋል፡፡ “ወእምግርማሁ ተሀውኩ ወኮኑ ከመ አብድንት እለ የዐቅቡ መቃብረ፤ እርሱን ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁት ታወኩ፤ እንደ በድንም ኾኑ፤” እንዳለ ቅዱስ ማቴዎስ (ማቴ. ፳፰፥፬)፡፡ መልአኩ “እናንተስ አትፍሩ! የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና፡፡ በዚህ የለም፤ እርሱ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል፡፡ ነገር ግን ኑና የተቀበረበትን ቦታ እዩ፤ ፈጥናችሁም ሒዱ፡፡ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤” ብሎ የትንሣኤውን የምሥራች ለሴቶች መግለጡንም ማቴዎስ በወንጌሉ ጽፎአል፡፡

ቅዱስ ማርቆስም በምዕራፍ ፲፮፥፩-፲፮ ትንሣኤውን አስመልክቶ ከቅዱስ ማቴዎስ ጋር የሚመሳሰል መልእክት ተናግሯል፡፡ ቅዱስ ሉቃስም እንደዚሁ በምዕራፍ ፳፬፥፩-፳፬ የክርስቶስን ዜና ትንሣኤ ጽፎልናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በአጻጻፍ ስልቱ ከሦስቱ ወንገላውያን ረቀቅ ያለ ቢኾንም ትንሣኤውን በመመስከር ከሦስቱ ወንጌላውያን ጋር ተባብሯል፡፡ በወንጌሉ ምዕራፍ ፳ ከቍጥር ፩ ጀምሮ ማርያም መግደላዊትና ሌሎች ሴቶች ወደ መቃብሩ ገስግሰው በመሔድ ትንሣኤውን ለማየት እንደ በቁ፤ ለደቀ መዛሙርቱም የምሥራቹን እንደ ተናገሩ ዘግቦልናል፡፡

ከሦስቱ ወንጌላውያን በተለየ መልኩ ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ በዝግ ደጅ ደቀ መዛሙርቱ ወደ አሉበት እንደ ገባ፤ ትንሣኤውን እንደ ገለጠላቸው፤ “ሰላም ለእናንተ ይኹን!” ብሎ የሰላም አምላክ ነውና ከሐዘናቸው እንዳጽናናቸው፤ ፍርሃታቸውንም እንዳራቀላቸው፤ “አይዞአችሁ! አትፍሩ! እኔ ነኝ፤ እጄን፣ እግሬን እዩ፤” በማለት ፍጹም ፍቅሩን እንደ አሳያቸው ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ ገልጾልናል፡፡

ትንሣኤው ምትሐት አለመኾኑን ይገልጥላቸውም ዘንድም “ደቂቅየ ቦኑ ብክሙ ዘንበልዕ፤ ልጆቼ፥ ጥቂት የሚበላ አላችሁን?” በማለት ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን ጠይቋቸዋል፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በሕቱም መቃብር የተፈጸመ፤ አምላካዊ ኀይሉ የገለጠበት ትንሣኤ ነው፡፡ የተነሣውም “መግነዝ ፍቱልኝ፤ መቃብር ክፈቱልኝ፤” ሳይል ነው፡፡

ጌታ ባረገ በስምንት ዓመት የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስም ሐዋርያትን መስሎ እንዲህ ሲል ትንሣኤውን መስክሮአል፤ “ስለ ኃጢአታችን የተሰቀለውን፤ ሊያስነሣንና ሊያጸድቀን የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ ባስነሣው ስለምናምን ስለ እኛም ነው እንጂ፤” (ሮሜ. ፬፥፳፬)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ የጌታችን ትንሣኤ ለእኛም ትንሣኤያችን መኾኑን ይነግረናል፡፡

ትንሣኤው ለእኛ ሕይወት መኾኑን ሲነግረን ደግሞ “እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን ተለይቶ እንደ ተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን፤” በማለት አስተምሮናል (ሮሜ. ፮፥፬)፡፡ ይህም ጌታችን በሞቱ ሞትን እንደ ሻረ፤ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን እንዳበሠረ፤ እርሱ የትንሣኤያችን በኵር እንደ ኾነ፤ እኛም በሞቱ ብንመስለው የትንሣኤው ተካፋዮች እንደምንኾን ያሳየናል፡፡

ጌታችን በሚከተሉት አምስት ነገሮች በኵራችን መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይነግሩናል፤

፩ኛ በጥንት፣ ገና ዓለም ሳይፈጠር፣ ዘመን ሳይቈጠር በመኖርና እኛን ፈጥሮ በማስገኘት በኵራችን ነው፡፡

፪ኛ በተቀድሶ (በመመስገን) በኵራችን ነው፡፡ ቅዱሳን የጸጋ ምስጋና የሚመሰገኑት እርሱን በኵር አድርገው ነውና፡፡

፫ኛ በትንሣኤው በኵራችን ነው፡፡ እርሱን በኵር አድርገን እንነሣለንና፡፡ “አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ዂሉ አስቀድሞ ተነሥቶአል፡፡ በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአል፤ በሁለተኛው ሰው ትንሣኤ ሙታን ኾነ፤” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፳)፡፡

፬ኛ በዕርገቱ በኵራችን ነው፡፡ ቅዱሳን ዐረጉ መባሉ እርሱን በኵር አድርገው ነውና፡፡ “ዐርገ ከመ ያሌቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሓን፤ የንጹሓን ጻድቃንን ዕርገት ያስረዳ ዘንድ አረገ” እንዲል (ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ)፡፡

፭ኛ ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ምርኮን ማርኮ ገነት መንግሥተ ሰማያት በመግባት በኵራችን ነው፡፡

ስለዚህ በዓለ ትንሣኤውን ስናከብር የእኛም ትንሣኤያችን መኾኑን ዐውቀን ተረድተን ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን መልካም ሥራ በመሥራት መኾን አለበት፡፡ እኛ ትንሣኤ ልቡና ሳንነሣ በየዓመቱ ትንሣኤውን ብናከብር ፈሪሳውያንን ወይም “ትንሣኤ ሙታን የለም፤ ፈርሰን፣ በስብሰን እንቀራለን” ብለው የሚያምኑ ሰዱቃውያንን መምሰል ይኾናል፡፡

ትንሣኤውን እንዴት ማክበር እንደሚገባን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ሲል ይመክረናል፤ “ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን ሹ፡፡ የላይኛውን ዐስቡ፤ በምድር ያለውንም አይደለም፡፡ እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና፡፡ ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ፤” (ቈላ. ፫፥፩-፬)፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ትንሣኤያችን ነው ብለን ለምናምን ዂሉ ከምድራዊ ዐሳብ ነጻ ኾነን ተስፋ የምናደርገው ትንሣኤ እንዳለን በማሰብ ከሞት በኋላ ሕይወት፣ ከትንሣኤም በኋላ የዘለዓለም ሞት መኖሩን ሳንዘነጋ በዓሉን ማክበር እንደሚገባን ሐዋርያው አስተምሮናል፡፡

ላይኛውን (ሰማያዊዉን መንግሥት) ለማያስቡ፤ መልካም ሥራ ለማይሠሩ ሰዎች ትንሣኤ ምን እንደሚመስል መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፤ “በመቃብር ያሉ ዂሉ ቃሉን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ስለዚህ አታድንቁ፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ፤” (ዮሐ. ፭፥፳፰)፡፡

ምእመናን፣ የትንሣኤያቸውን በኵር ክርስቶስን አብነት አድርገው፣ ቃሉን ሰምተው፣ ሕጉን ጠብቀው፣ ትእዛዙን አክብረው፣ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተው የትንሣኤን ዕለት ቢያከብሩ፤ ሥጋውን በልተው፣ ደሙን ጠጥተው፣ በንስሐ ተሸልመው፣ በፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ (ባልንጀራን በመውደድ) ጸንተው ቢኖሩ ላይኛውን ማሰብ ትንሣኤውን ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ እንደዚህ ካደረጉ የትንሣኤውን ትርጕም ዐውቀዋል፡፡

ከትንሣኤ ሥጋ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን መንግሥቱን እንድንወርስ ስሙን እንድንቀድስ እግዚአብሔር አምላካችን ይፍቀድልን፡፡ መልካም የትንሣኤ በዓል ይኹንልን!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የትንሣኤው ብሥራት

በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በጥንተ ጠላታችን ዲያቢሎስ አሳሳችነት አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላላፋቸው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ካለው ፍጹም ፍቅር የተነሣ የተፈረደባቸውን ሞት በሞቱ ሊደመስስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ (ዮሐ. ፩፥፩)፡፡ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡ እንደ ተጠመቀም ልዋል ልደር ሳይል ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ ሔደ፡፡ በዚያም ጾመ፤ ጸለየ፡፡ በዲያቢሎስም ተፈተነ፡፡

ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማረ በኋላ የአዳምና የሔዋንን ዕዳ ደምስሶ ነጻ ሊያደርጋቸው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መከራ ተቀበለ፡፡ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቆመ፤ ምራቅ ተተፋበት፤ ተገረፈ፤ በገመድ ታሥሮ ተጎተተ፤ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ፡፡ በሞቱ ሞትን ድል አድርጎ የአዳምን፣ የሔዋንንና የልጆቻቸውን ዕዳ በደል ደመሰሰ (ማቴ. ፳፯፥፳፰)፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ “ሞቱንም በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን፤” በማለት እንደ ገለጸው (ሮሜ. ፮፥፭)፣ ሞቱ ሞታችን፤ ትንሣኤው ትንሣኤያችን ነውና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች በየዓመቱ ጌታ የጾመውን ጾም በመጾም፣ በሰሙነ ሕማማት ደግሞ መከራውንና ስቃዩን በማሰብ የክርስቶስን ቤዛነት እንዘክራለን፤ የነጻነትና የድል በዓላችንንም እናከብራለን፡፡

“በጥንተ ጠላታችን ምክንያት አይሁድ ክብርህን ዝቅ ቢያደርጉ፣ ቢያዋርዱህ፣ ቢገርፉህ፣ ርቃንህን ቢሰቅሉህና ቢገድለህ እኛ ግን ‹ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም – ኃይሌ፣ መከታዬና ረዳቴ ለኾንኸው ለአንተ ለአምላኬ ለአማኑኤል ለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ጽናትም ለዘለዓለሙ ይገባሃል›፤” እያልን አምላካችንን እናመሰግነዋለን፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ፫፥፲ ላይ “እርሱንና የትነሣኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራወም እንድካፈል ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢኾንልኝ በሞቱ እንደመስለው እመኛለሁ፤” በማለት እንደ ተናገረው ምእመናን እንደ አቅማቸው እያዘኑ፣ እያለቀሱ፣ ከምግብ እየተከለከሉ፣ ጸጉራቸውን እየተላጩ የአምላካንን መከራ ያስባሉ፡፡

“ሞትን ድል አድርጎ ተነሥቷል!” የሚለውን የምሥራች ከቤተ ክርስቲያን ለመስማት በናፍቆት ይጠባበቃሉ፡፡ የትንሣኤውን ብሥራት ሰከሙ በኋላም “ጌታ በእውነት ተነሥቷል!” እያሉ ትንሣኤዉን ይመሰክራሉ፡፡ የጌታችን ትንሣኤ፣ የድኅነታችን ብሥራት በመኾኑ ለአምሳ ቀናት ያህል በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በወንጌሉ፣ በሌሎችም ቅዱሳት መጻሕፍት በልዩ ሥርዓት ይዘከራል፡፡ በየአብያተ ክርስቲያኑ “ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን በዓቢይ ኃይል ወሥልጣን አሠሮ ለሰይጣን አግዐዞ ለአዳም ሰላም እምይእዜሰ ኮነ ፍሥሐ ወሰላም” እየተባለ ሞት መደምሰሱ፣ ነጻነት መታወጁ ይበሠራል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በሰሙነ ሕማማት ጠቅለል ባለ መልኩ የምናስባቸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ‹ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል› ይባላሉ፡፡ ለክርስቲያኖች እነዚህን ሕማማተ መስቀል ማወቅና ዘወትር ማሰብ ተገቢ በመኾኑ እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል፤

፩. ተኰርዖተ ርእስ (ራስና በዘንግ መመታት)

‹ተኰርዖት› የሚለው ቃል ‹ኰርዐ – መታ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹ርእስ› ደግሞ ራስ ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ አገረ ገዥው ጲላጦስ ‹‹እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቶት ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም፡፡ እርሱ ጲላጦስ ግን ከገረፈው በኋላ፣ የበደል በደል፣ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው (ማቴ. ፳፯፥፳፬፤ ማር. ፲፭፥፲፭፤ ሉቃ. ፳፫፥፳፭፤ ዮሐ. ፲፰፥፴፱)፡፡

አይሁድ የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በጌታችን ራስ ላይ ደፍተውበታል፡፡ ራሱንም በዘንግ መትተውታል (ማር. ፲፭፥፲፱)፡፡ የሰው ዘር ከአዳም ጀምሮ በጠላቱ በዲያብሎስ በተጐነጐነ የኃጢአት እሾኽ ራሱ ተይዞ ነበርና ይህንኑ ለማስወገድ ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ የኾነ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ አክሊለ ሦክ እንደ ዘውድ ደፋ፡፡ በሲኦል ወድቆ በዲያብሎስ ተረግጦ ራሱ የሚቀጠቀጠውን የሰውን ልጅ ለማዳን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ፡፡ ከራሱ ላይ በሚወርደው ደም ፊቱ ተሸፈነ፡፡

፪. ተፀፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)

‹ተፀፍዖ› የሚለው ቃል ‹ፀፍዐ – በጥፊ መታ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲኾን፣ ‹መጥፊ መመታት› ማለት ነው፡፡ ‹መልታሕት› ደግሞ ‹ፊት፣ ጉንጭ› ማለት ነው፡፡ ይኸውም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጃቸው በደም፣ ጣቶቻቸው በበደል በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ለሊቀ ካህናት ቀያፋ እውነትን መናገር እንደ ስድብ ተቈጥሮበት አይሁድ ጌታችን መላልሰው ፊቱን በጥፊ መትተውታል፡፡ ፊቱንም በጨርቅ ሸፍነው ‹‹ክርስቶስ ሆይ! በጥፊ የመታህ ማነው? ትንቢት ተናገርልን!›› እያሉ ዘብተውበታል፡፡

በጠላት ዲያብሎስ እጅ ወድቆ በነፍሱ ይቀለድበትና ይንገላታ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ብሎ መድኀኒታችን ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተጐሰመ፤ ተንገላታ፤ በጥፊም ተመታ (ማቴ.  ፳፯፥፳፯)፡፡ ጲላጦስ አሳልፎ ከሰጠው በኋላም አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ አኑረው ቀይ ልብስ አልብሰው ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይኹን!›› እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መትተውታል (ዮሐ. ፲፱፥፪)፡፡ አላወቁትም እንጂ እርሱ በመንግሥቱ ሽረት፣ በባሕርዩ ሞት የሌለበት የዘለዓለም አምላክ ነው፡፡

፫. ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መተፋት)

‹ወሪቅ› የሚለው ቃል ‹ወረቀ – እንትፍ አለ፤ ተፋ› ካለው ግእዛዊ ግሥ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ‹እንትፍ ማለት፣ መትፋት› ማለት ነው፡፡ ‹ምራቅ› በቁሙ ‹ምራቅ› ማለት ነው፡፡ ወሪቀ ምራቅ፣ አይሁድ በብርሃናዊው በክርስቶስ ፊት ላይ በሚያስጸይፍ ኹኔታ ምራቃቸውን እንደ ተፉበት የሚገልጥ ነው፡፡ በትንቢት ኢሳይያስ ፶፥፮ ላይ ‹‹ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም›› ተብሎ እንደ ተነገረ፣ አይሁድ እየዘበቱ በአምላካችን ላይ ምራቃቸውን ተፍተውበታል (ማቴ. ፳፯፥፳፱-፴፤ ማር. ፲፭፥፲፱)፡፡

በኃጢአት የቆሸሸውን የሰውን ሕይወት ለማጥራት የመጣው ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ምራቅ ተተፋበት፡፡ በሥራው ከገነት ተተፍቶ፤ ተንቆ፤ ተዋርዶ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ኃጢአትን ይቅር የሚል እርሱ ጌታችን ያለ ኃጢአቱ ተተፋበት፤ ተናቀ፤ ተዋረደ፡፡ እንኳን በአምላክ ፊት በሰው ፊት እንኳን መትፋት እጅግ ያስነውራል፡፡ እርሱ ግን የኃጢአታችንን ነውር ከእኛ ሊያጠፋ ነውር የኾነውን ምራቅ በትዕግሥት ተቀበለ፡፡

፬. ሰትየ ሐሞት (አሞት መጠጣት)

‹ሰትየ› ማለት በግእስ ቋንቋ ‹ጠጣ› ማለት ሲኾን፣ ‹ሰትይ› ደግሞ ‹መጠጣት› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ‹ሐሞት› የሚለው የግእዝ ቃልም ‹አሞት› ተብሎ በቁሙ ይተረጐማል፡፡ ቃላቱ በአንድ ላይ ‹ሰትየ ሐሞት› ተብለው ሲናበቡ ‹አሞት መጠጣት› የሚል ትርጕም ይሰጣሉ፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሳለ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ መራራ አሞት መጠጣቱን የሚገልጥ ነው፡፡

‹‹ለመብሌ አሞት ሰጡኝ፤ ለጥማቴም ኾምጣጤ አጠጡኝ›› ብሎ ነቢዩ ዳዊትን በመዝሙረ ዳዊት መዝሙር ፷፰፥፳፩ ላይ ትንቢት ያናገረ የነቢያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ ኾምጣጤ በሰፍነግ ሞልተው ወደ አፉ አቀረቡለት፡፡ ውኃ አጠጡኝ ቢላቸው በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፡፡ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም (ማቴ. ፳፯፥፴፬)፡፡ ጌታችንም ኾምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ‹‹ተፈጸመ›› አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን በፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ (ማቴ.፳፯፥፵፰፤ ማር. ፲፭፥፴፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፴፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፳፱)፡፡

ቢጠጡት ለዘለዓለም የማያስጠማ ውኃ የሚሰጥ አምላክ፤ የተጠማችውን ነፍስ የሚያረካ ጌታ፤ ለዘለዓለም የሚፈልቅ የሕይወት ውኃን የሚያድል ፈጣሪ በተጠማ ጊዜ የፈጠረውን ውኃ እንኳን የሚያጠጣው የሚያቀምሰውም አላገኘም (ኢሳ. ፶፭፥፩)፡፡ ዐርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ሲጓዙ ለነበሩ አባቶቻቸው ከሰማይ መና አውርዶ የመገባቸው፤ ከዐለት ላይ ውኃ አመንጭቶ ያጠጣቸው ክርስቶስ በተጠማ ጊዜ አይሁድ ቀዝቃዛ ውኃ ነፈጉት (ዘዳ. ፲፮፥፩-፳፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፥፫)፡፡ የዝናማት፤ የባሕርና የውቅያኖስ ጌታ በውኃ ጥም ተቃጠለ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል በረሃ ወድቀው በሕይወት ውሃ ጥም የተቃጠሉትን ነፍሳት ለማርካት ሲል እርሱ ተጠማ፡፡ በኃጢአት ወድቀው፣ በበደል ረክሰው፣ በነፍሳቸው ተጐሳቁለው፣ መራራ መከራን የሚቀበሉትንና ምረረ ገሃነም አፉን ከፍቶ ሆዱን አስፍቶ የሚጠብቃቸውን ዂሉ ለማዳን መራራ ሐሞትን ቀመሰ፤ ኾምጣጣውንም ጠጣ፡፡ የመረረውን የሰው ልጆችን ሕይወት ለማጣፈጥ የመረረውን መጠጥ ተቀበለ፡፡

፭. ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)

‹ተቀሥፎ› የሚለው ቃል ‹ቀሠፈ – ገረፈ› ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን፣ ‹መገረፍ› ማለት ነው፡፡ ‹ዘባን› ደግሞ ‹ጫንቃ፣ ትከሻ፣ ጀርባ› የሚል ትርጕም አለው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀርባው እስኪላጥ ድረስ ያለ ርኅራኄ የመገረፉን ነገር የሚገልጥ ነው፡፡ ከላይ እንደ ተጠቀሰው በዘመኑ የቅጣት ሕግ መሠረት የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም ነበር፡፡ ቅጣቱን ለማቅለል ዐስቦ ጲላጦስ ኢየሱስ ክርስቶስን ቢያስገርፈውም አይሁድ ግን በግፍ ሰቅለውታል፡፡ ጲላጦስ ‹‹ከደሙ ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችንን ለአይሁድ አሳልፎ በመስጠት ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› እንዲሉ የታጠበ እጁን መልሶ አቆሸሸው (ማቴ. ፳፯፥፳፰፤ ማር. ፲፭፥፲፭፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ›› ተብሎ እንደ ተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፤ ጽሕሙንም ተነጨ፡፡ በመንፀፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ በእሳት አለንጋ የሚገረፈውን የሰው ልጅ ለማዳን ሲል ጌታችን ጀርባውን ለግርፋት ሰጠ፡፡ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቈጠር ድረስም ተገረፈ፡፡ አይሁድ አገረ ገዥያቸው ጲላጦስ ላቀረበላቸው ምርጫ ይፈታላቸው ዘንድ ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣውን ክርስቶስን ሳይኾን ራሱን እንኳን ከምድራዊ ወኅኒ ማውጣት ያልቻለውን ወንበዴውን በርባንን መረጡ፡፡ መገረፍ ይገባው የነበረ በርባን ተለቀቀ፡፡ ይህ ዂሉ የኾነውም የሰው ልጅ ከሚያድነው አምላክ ይልቅ የሚገርፈውንና የሚዘርፈውን ወንበዴ መርጦ ስለተገኘ ነው፡፡ በእርግጥ ክርስቶስ ካልሞተ ዓለም አይድንምና ሳያውቁም ቢኾን መድኃኒታቸውን መርጠዋል፡፡

፮. ተዐርቆተ ልብስ (ከልብስ መራቆት)

‹ተዐርቆተ› ማለት በግእዝ ቋንቋ ‹መታረዝ፣ መራቆት› ማለት ነው፡፡ ይኸውም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልብሱን መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላክ ለእኛ ሲል ተራቆተ፡፡ ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ ለዓለም ድኅነት ሲል ራቁቱን ለፍርድ ቆመ፡፡ ጨለማን ለብሶ ጨለማን ተንተርሶ ይኖር የነበረውን ሰው መልሶ ብርሃን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ፣ የዓለሙ ዂሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገፈፈ፤ ተራቆተ፡፡ የሲኦል ወታደሮች አጋንንት የሰውን ልጅ ጸጋ ገፍፈውት ነበርና ይህን ጸጋ ለማስመለስ ሲል ጌታችን በአይሁድ ወታደሮች ልብሱን ተገፈፈ፡፡

፯. ርግዘተ ገቦ (ጎንን በጦር መወጋት)

‹ርግዘት› የሚለው ቃል ‹ረገዘ – ወጋ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲኾን ‹በጦር መወጋት› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ‹ገቦ› ማለት ‹ጎን›፤ ‹ርግዘተ ገቦ› ደግሞ ‹ጎንን በጦር መወጋት› ማለት ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር ተወግቷል፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፡፡ በዚህ ጊዜ ድኅተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ የሚሰጥ ደምና ውኃ ከጎኑ ፈሰሰ (ዮሐ. ፲፱፥፴፫)፡፡ መላእክትም ደሙን ተቀብለው በዓለም ረጭተውታል፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ፤ የሰው ልጅ በዘለዓለማዊ ሞት ተይዞ ነበርና፡፡ ትልቁ ሞት በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በጌታችን ሞት ግን ሞት ራሱ ድል ተነሣ፡፡ የሞት መውጊያ በኾነ ኃጢአት የሞተውን ሰው ለማዳን ሲል አምላካችን ጎኑን በጦር ተወጋ፡፡ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውን ኃጢአት ከነሥሩ ነቅሎ ስለ ጣለው ‹‹ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ?›› ተብሎ ተዘመረ፡፡ የሞት መውጊያው ኃጢአት በክርስቶስ ሞት ድል ተደርጓልና (ኢሳ. ፳፭፥፰፤ ሆሴ. ፲፫፥፲፬፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፶፬-፶፭)፡፡

ከተወጋው ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደምና ውኃም የእግዚአብሔርን ልጅነትና የዘለዓለምን ሕይወት አጥቶ የነበረው ሰው ልጅነቱና ሕይወቱ እንደ ተመለሰለት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቆ ልጅነትን፣ ደሙንም ጠጥቶ የዘለዓለም ሕይወትን ማግኘት ይቻላልና (ዮሐ. ፫፥፭፤ ፮፥፶፬)፡፡

፰. ተአሥሮተ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሠር)

‹ተአሥሮት› የሚለው ቃል ‹አሠረ (ሲነበብ ይላላል) – አሠረ› ወይም ‹ተአሥረ – ታሠረ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ‹መታሠር› ማለት ነው፡፡ ‹ድኅሪት› የሚለው ቃል ደግሞ ‹ተድኅረ – ወደ ኋላ አለ› ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ ሁለቱ ቃላት በአንድ ላይ (ተአሥሮተ ድኅሪት) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት እጆቹን ወደ ኋላ የፊጥኝ መታሠሩን የሚገልጥ ትርጕም ይሰጣሉ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት በዚያች ዕለት ሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች እጁን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎትተውታል (ዮሐ. ፲፰፥፲፪)፡፡ በኃጢአት ሰንሰለት የኋሊት ታሥሮ ጠላት ዲያብሎስ የሚያፍገመግመውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ ሰውንም ከኃጢአት እሥራት ለመፍታት ሲል መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡

ከ ፱ – ፲፫ ያሉት የሕማማተ መስቀል ክፍሎች ደግሞ አምስቱ ቅንዋተ መስቀል ናቸው፡፡

በስምንቱ ሕማማት ላይ ሲደመሩ ዐሥራ ሦስት ይኾናል፡፡ ‹ቅንዋት› የሚለው ቃል ‹ቀነወ – ቸነከረ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹መስቀል› ማለት ደግሞ የተመሳቀለ ዕንጨት ማለት ነው፡፡ ‹ቅንዋተ መስቀል› – መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸውን አምስቱን ጠንካራ የብረት ችንካሮች (ምስማሮች) የሚገልጥ ነው፡፡ አምስቱ ቅንዋተ መስቀል፡- ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ፤ ሮዳስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህም የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌዎች መኾናቸውን አበው ያስተምራሉ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ቀዳም ሥዑር

መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.

የሰሙነ ሕማማቷ ቅዳሜ ‹ቀዳም ሥዑር› ወይም ‹ቀዳሚት ሥዑር› ትባላለች፡፡ ትርጕሙም ‹የተሻረች ቅዳሜ› ማለት ነው፡፡ የማትጾመዋ ቅዳሜ ከቀድሞው በተለየ መልኩ የጌታችንን መከራ በማሰብ በጾም ታስባ ስለምትውል ‹የተሻረችው ቅዳሜ› ተብላ ተጠርታለች፡፡ ነገር ግን ቃሉ ጾምን እንጂ በዓል መሻርን አያመለክትም፡፡ በቀዳም ሥዑር  ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኅሌቱም እዝሉ እየተቃኘ፣ እየተመጠነ፣ እየተዘመመ፣ እየተመረገደ፣ እየተጸፋ ያድራል፡፡ ጠዋት አቡን፣ መዋሥዕት፣ ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ‹‹ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ›› በሚለው ሰላም ሥርዓተ ማኅሌቱ ይጠናቀቃል፡፡

ካህናቱ ለምእመናን ለምለም ቀጤማ የሚያድሉበት ዕለት ስለ ኾነ ዕለተ ቅዳሜ ‹ለምለም ቅዳሜ› ተብላም ትጠራለች፡፡ በቀዳም ሥዑር ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ቃጭል (ቃለ ዓዋዲ) እየመቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ትንሣኤሁ አግሃደ›› የሚለውን ያሬዳዊ ዜማ በመዘመር፤ ጌታ በመስቀሉ ሰላምን እንደ ሰጠን እና ትንሣኤውንም እንደ ገለጠልን በማብሠር፤ ቄጠማውን ለምእመናን ይሰጣሉ፡፡ ምእመናኑም በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ገጸ በረከት ያቀርባሉ፡፡ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ ካህናትና ዲያቆናት ቄጠማ ተሸክመው ቃጭል ሲያቃጨሉ መታየታቸው ዕለተ ትንሣኤውን ለሚናፍቅ ምእመን ትልቅ ብሥራት ነው፡፡

ቀጤማውንም ምእመናን እስከ ትንሣኤ ሌሊት ድረስ በራሳቸው ላይ አሥረውት ይቆያሉ፡፡ ይህም አይሁድ በጌታችን ራስ ላይ የእሾኽ አክሊል ማሠራቸውን የሚያስታውስ ነው፡፡ የቀጤማው አመጣጥና ምሥጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምድር በማየ አይኅ (በጥፋት ውኃ) በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሠረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ‹‹የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ፤ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ፤ ታወጀ፤›› በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡

ዕለተ ቅዳሜ ‹ቅዱስ ቅዳሜ› እየተባለችም ትጠራለች፡፡ ቅዱስ መባሏም ቅዱስ እግዚአብሔር በጥንተ ተፈጥሮ ፍጥረታትን አከናውኖ ከፈጠረ በኋላ በዚህ ቀን ከሥራው ዅሉ ስላረፈባት ነው፡፡ በዘመነ ሐዲስ ደግሞ የማዳን ሥራውን ዅሉ ፈጽሞ በሥጋው በመቃብር ሲያርፍ፤ በነፍሱ ሲኦልን በርብሮ ባዶዋን አስቀርቷታል፡፡ በዚያ ለነበሩት ነፍሳትም የዘለዓለም ዕረፍትን ያወረሰበት ዕለት ስለ ኾነ ከሌሎቹ ዕለታት የተለየች ዕለት መኾኗን ለማመላከት ‹ቅዱስ› (ቅድስት) ተብላለች፡፡

ምእመናን ሆይ! በአጠቃላይ የጌታችንን የመከራ ሳምንት ‹ሰሙነ ሕማማት› ብለው ሰይመው፣ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ያቆዩልንን ትውፊት ልንጠብቀውም፣ ልንጠቀምበትም ይገባል፡፡ የዕለታቱን ክብርና ስያሜ ከማወቅና ከመረዳት ጋር በዕለታቱ የታዘዙትን ሃይማኖታዊ ግዴታዎችን መወጣት ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፡ ስምዐ ተዋሕዶ፣ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ከሚያዝያ ፲፭ ቀን ፳፻፬ .ም፣ አዲስ አበባ፡፡

ቀዳሚት ሥዑር

በመምህር ቸርነት አበበ

መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር አምላካችን የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሔዱትን፣ በክንፍ የሚበሩትን እና በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን፣ በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈባት ዕለት ነች፡፡ የመጀመሪያዋ ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፡፡ እግዚአብሔርን ፍጥረታትን ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ ስላረፈባት ‹ሰንበት ዐባይ› (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች፡፡ ይህቺን ዕለት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ እግዚአብሔር ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንዳደረገባት ዅሉ፣ የፍጥረት ርእስ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው አምላካችን ክርስቶስ በመቃብር አርፎባታል (ማቴ. ፳፯፥፷፩)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር አርፎ የዋለባት ዕለት በመኾኗ ‹ቀዳሚት ሥዑር› ትሰኛለች፡፡ ‹ሥዑር› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም (የጾም ቀን በመኾኗ) ነው፡፡ የጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እኽል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

እመቤታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾምና በመጸለይ ዕለቷን እንዳከበሯት ዅሉ የተዋሕዶ ልጆችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው በማክፈል (በመጾም) እኽል ውኃ ሳይቀምሱ ለሁለት ቀናት ያድራሉ፡፡ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡ በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸምም ካህናቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ›› እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡ ምእመናን የምሥራች ቄጠማ ያድላሉ፡፡

ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ኾነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል (ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)፡፡

ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደ ኾነ ዅሉ፣ አሁንም ‹‹በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤›› ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የኾነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ዅሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከዋዕየ ሲኦል (የሲኦል ቃጠሎ) ወደ ጥንተ ማኅደራቸው ገነት መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የእመቤታችን ኀዘን ስለ ጌታችን መከራ

መጋቢት ፳፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

… ለእኔስ በተሰቀለው ላይ ልቅሶ አለኝ፤ ‹‹በመስቀል ላይ ሞትህን?›› እላለሁ፡፡ የመስቀልህ ጥላ ሙታንን ሲያስነሣም ዐውቃለሁ፤ በመስቀል ላይ ዘንበል ማለትህን አደንቃለሁ፡፡ የሲኦልን መታወክ፣ በውስጧ ያሉ ሰባት መቶ የብረት በሮች እንደ ተሰበሩ አስታውሳለሁ፡፡ በዚያ ታስረው የነበሩትንም ከአባታቸው ከአዳም ጋር አወጣሃቸው፡፡ በዚያች ዕለትም ወደ ርስታቸው ወደ ገነት አስገባሃቸው፡፡ ነፍስህ ከሥጋህ በተለየች ጊዜም አለቅስሁ፡፡ በቀኝ ተሰቅሎ ለነበረው ወንበዴ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ሠላሳ ሦስት ዘመን ተዘግታ የኖረች ገነትን በከፈትህ ጊዜም ተደሰትሁ፡፡

በዕንጨት መስቀል በሰቀሉህ ጊዜ ላልቅስ? ወይስ ፀሐይ በጨለመ ጊዜ ልደንግጥ? በመስቀል ላይ ራቁትህን ኾነህ በተመለከትሁህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ቀኑ ሌሊት በኾነ ጊዜ ልደነቅ? ‹‹ክርስቶስ ሆይ! ማን መታህ? ንገረን!›› እያሉ በመቱህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ‹‹ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው የማይሞት፤ በመስቀል የተሰቀለ›› እያሉ ለማመስገን እልፍ አእላፍ ፍጥረታት ሲወድቁልህ ልደሰት? መጣጣዉን ከሐሞት ጋር ቀላቅለው ባጠጡህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ አምላካዊ የኾነች ደም፣ ከመስቀሉ ታችም ንጹሕ ውኃ በፈሰሰ ጊዜ?

የመለኮት ደም ዐለቱን ሰንጥቆ የአባታችን የአዳምን መቃብር አልፎ በአዳም አፍ ስለ መግባቱ ስለ ማዳኑም አደንቃለሁ፡፡ ስለዚህም ወንጌላዊው ‹‹ዐለቱ ተሰነጠቀ፤ የጻድቃን በድኖች ተነሡ፤›› አለ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡ በፊትህ ምራቅ በተፉብህ ጊዜ ላልቅስ? ወይስ ዕውር ኾኖ የተወለደዉን በማዳንህ ልደሰት? በአንገትህ ሐብል ባደረጉብህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ሰይጣን ያሰራቸዉን ስትፈታቸው ላመስግንህ? ታስረህ በጲላጦስ ፊት ሲያቆሙህ ላልቅስን? ወይስ በባሕሩ እንደ የብስ ሔደህ ነፋሳትን እንደ ሎሌ በመገሠፅህ ላድንቅ? ወይስ ነቢያት አንተን ለማየት በመመኘታቸው ልደሰት?

ዛሬ በሁለት ወንበዴዎች መካከል ባየሁህ ጊዜ ላልቅስን? ከሌቦች፣ ከወንበዴዎች፣ ዓለሙን ዂሉ ካስለቀሱት ጋር በመስቀል በሰቀሉህ፣ በቸነከሩህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በሙሴና በኤልያስ መካከል የመንግሥትህ ግርማ በታወቀ፤ የመለኮትህ ብርሃን ባንጸባረቀ ጊዜ ልደሰት? በቀራንዮ መስቀልን በተሸከምህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ መጻጕዕን ‹‹ኀጢአትህ ተሰረየልህ፤ ተነሥና አልጋህን ተሸከም፤ ሔደህም ወደ ቤት ግባ፤›› (ዮሐ. ፭፥፰) በማለትህ ልደሰት? ሐና እና ቀያፋ ‹‹ደሙ በእኛና በልጆቻችን ይኹን›› ባሉህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ዐሥራ ሁለት ዓመት ደም ሲፈሳት የነበረችዉን ሴት በልብስህ ጫፍ በማዳንህ ልደሰት? በይሁዳ አማካይነት በሠላሳ ብር በመሸጥህ ላልቅስን? ወይስ ከዓሣ ሆድ ዲናር ያወጣ ዘንድ፣ በአንተ እንዳያጕረመርሙም ለቄሣር ግብር ይሰጥ ዘንድ ጴጥሮስን ባዘዝኸው ጊዜ ልደሰት?

በመስቀል ላይ ሳለህ ‹‹ተጠማሁ›› (ዮሐ. ፲፱፥፳፰) ስትል ላልቅስን? ወይስ በቃና ዘገሊላ ውኃዉን ወይን በማድረግህ ልደሰት? እናትህ እኔ በጉባኤው መካከል የፊቴን መሸፈኛ ገልጬ ስመለከት፣ ዮሐንስ ‹‹ልጅሽ ሞተ›› ባለኝ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ገብርኤል ‹‹ከአንቺ የሚወለደው የእግዚአብሔር ቃል በግብረ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፤›› (ሉቃ. ፩፥፴-፴፫) እያለ በነገረኝ ጊዜ ልደሰት? ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ሥጋህን ለመገነዝ ሽቱ ሲገዙ ባየኋቸው ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ምድራዊ ሳሙና እንደዚያ አድርጎ ማጽዳት የማይቻለው ፀዓዳ የኾነ የመንግሥት ልብስህን ባየሁ ጊዜ ልደሰት?

ሥጋህን ለመቅበር አዲስ መቃብር በፈለጉ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ከአራት ቀናት በኋላ አልዓዛርን ከመቃብር ባስነሣኸው ጊዜ (ዮሐ. ፲፩፥፵፫-፵፬) ልደሰት? በአፍህ መራራ ሐሞትን በጨመሩብህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ከሴቶችና ከሕፃናቱ ሌላ በአምስት እንጀራ ለአምስት ሺሕ ሕዝብ በማጥግብህ፣ ተርፎም ዐሥራ ሁለት ቅርጫት በመነሣቱ (ማቴ. ፲፭፥፲፯-፳፩) ልደሰት? በመቃብርህ ላይ ድንጋይ በገጠሙበት ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በአህያና ላም ባሟሟቁህ ጊዜ ላድንቅ? በሙታን መካከል በተኛህ ጊዜ ላልቅስን? ወይስ በጦር የወጋህን ሰው የታወረ ዓይኑን በመዳሰስ ባዳንኸው ጊዜ ልደሰት?

በመስቀል በምትጨነቅበት ጊዜ ላልቅስን? ወይስ ወንበዴዉን ‹‹ዛሬ እውነት እልሃለሁ፤ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ፡፡ ፈጽመህ እመን፤›› (ሉቃ. ፳፫፥፵፫) ባልኸው ጊዜ ልደሰት? የተረገሙ አይሁድን ምን እንላቸዋለን? በዮርዳኖስ ውኃ ዓለሙን የሸፈነዉን ራቀቱን ሰቅለውታልና፡፡ ዓለምን ከኀጢአት ሞት ያዳነ እርሱን ገድለውታልና፡፡

ምንጭ፡- ርቱዐ ሃይማኖት፣ መ/ር ተስፋ ሚካኤል ታከለ፤ ፳፻፬ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ 211-214)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

በጸሎተ ሐሙስ የሚፈጸም ሥርዓት

መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባቡ እንደ ተለመደው ይከናወናል፡፡ መንበሩ (ታቦቱ) ጥቁር ልብስ ይለብሳል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል፤ ቤተ ክርስቲያኑም በማዕጠንት ይታጠናል፡፡ ኅፅበተ እግር ይደረጋል፡፡ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ በየቤቱ ደግሞ ጉልባን ይዘጋጃል፡፡

ኅፅበተ እግር

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ‹ጸሎተ አኰቴት› በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የኅፅበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ኅፅበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው፤

ወይራ ጸኑዕ ነው፡፡ ይህም ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ ባሻገር እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ኅፅበቱን በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ኅፅበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ኀፀበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ምእመናን ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡

 ቅዳሴ

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲኾን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልዑካኑ የድምፅ ማጉያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለማመልከት ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡

ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡

ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ዅሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ነገረ ስቅለቱ ለክርስቶስ

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና

የሊቃውንት ጉባኤ አባል

መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ሰሙነ ሕማማት (የሕማማት ሰሙን መከራ) ባለቤቱ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አቅዶ፣ ወስኖ እስከ መስቀል ድረስ በፈቃዱ መከራ የተቀበለበት ጊዜ ነው፡፡ ከሰሙነ ሕማማት ዕለታት መካከል ዕለተ ዓርብ የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹ዕለተ ድኅነት (የድኅነት ቀን)› ይባላል፡፡ አምላካችን ሥራውን ያለ ምክንያት አይሠራውምና ለሕማሙና ለሞቱ መንሥኤ ከኾኑት ጉዳዮች መካከል የተወሰኑት የሚከተሉት ናቸው፤

አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱ

‹‹የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያንም ጉባኤውን ሰብስበው እንዲህ አሏቸው፤ ‹እነሆ ይህን ሰው ብዙ ተአምራትን ያደርጋል፡፡ ምን እናድርግ? እንዲሁ ብንተወውም ዅሉ ያምንበታል፡፡ የሮም ሰዎችም መጥተው አገራችንንና ወገናችንን ይወስዱብናል›፡፡ ሊቀ ካህናት ቀያፋም ‹ሕዝቡ ዅሉ ከሚጠፋ ስለ ሕዝቡ አንድ ሰው ቢሞት ይሻላል› አላቸው፤›› (ዮሐ. ፲፩፥፵፯-፶) ተብሎ እንደ ተጻፈ ለጌታችን መከራ መቀበል አንዱ ምክንያት አልዓዛርን ከሞት ማስነሣቱ ነው፡፡

በምስጋና ወደ ቤተ መቅደስ መግባቱና ተአምራትን ማድረጉ

በዕለተ ሆሣዕና በሕፃናት አንደበት ሳይቀር በሕዝቡ ዅሉ እየተመሰገነ ጌታችን ወደ ቤቱ መቅደስ መግባቱና በዚያ ወቅት ያደረገው ተአምራት ሌላው የመከራው ምክንያት ነው፡፡ ‹‹ያን ጊዜም የካህናት አለቆችና ጻፎች ያደረገውን ተአምራት፤ ልጆችንም በቤተ መቅደስ ‹ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ› እያሉ ሲጮኹ ባዩ ጊዜ ደስ አላላቸውም፤›› እንዲል (ማቴ. ፳፩፥፲፭)፡፡

ስለዚህም በሆሣዕና ማግሥት (ሰኞ ዕለት) የአይሁድ ባለ ሥልጣናት ጌታችንን ለመግደል የአድማ ስብሰባ አድርገው ሳይስማሙ ተለያዩ፡፡ በድጋሜ ማክሰኞ ዕለት ተሰብስበው አሁንም ሳይስማሙ ተለያዩ፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ረቡዕ ተሰባሰቡ፤ በዚህ ዕለት ዅሉም አንድ ኾነው ይሙት በቃ የሚል ፍርድ በጌታችን ላይ ወስነው ስበሰባቸውን ደመደሙ (የመጋቢት ፳፫ እና ፳፬ ቀን ስንክሳር)፡፡

በዚህ ጊዜ ጌታችንን አሳልፎ የሚሰጣቸው ምሥጢረኛ ቤተሰብ የኾናቸውን ይሁዳን በማግኘታቸው ደስ አላቸው፡፡ ሠላሳ ብር ሊሰጡትም ተስማሙ፡፡ እርሱም ደስ ብሎት ሰው ሳይኖር አሳልፎ ሊሰጣቸው ምቹ ቦታ ይሻ ነበር፤ ከዚያም ጌታችንን ለአይሁድ አሳልፎ ሰጠው (ሉቃ. ፳፪፥፫-፮)፡፡

ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ‹‹ይህን አጥፍቶአል›› የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡ ‹‹ክፉ የሠራ ባይኾንስ ወደ አንተ ባላመጣነውም ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ ‹‹እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም፤ እናንተ ወስዳችሁ እንደ ሕጋችሁፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡

አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል ብእሴ ጻድቀ ወኀጥአ ኢታሕዩ፤ ጻድቅን ሰው አትግደል፤ ኀጥኡንም ከፍርድ አታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤›› ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡ ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን ጻድቀ ባሕርይ ክርስቶስን መግደል አይገባንም፤ ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡

ጌታችን በተሰቀለ ጊዜ የተፈጸሙ ተአምራት

ጌታችን በተሰቀለ ጊዜም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤

፩. ፀሐይ ጨለመ፤

፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤

፫. ከዋክብት ረገፉ፤

፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤

፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤

፮. መቃብራት ተከፈቱ፤

፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤

፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤

፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤

፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤

፬. እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ››፤ ደቀ መዝሙሩንም ‹‹እናትህ እነኋት›› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤

፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››

፮. ‹‹ተጠማሁ››፤

፯. ‹‹ዅሉ ተፈጸመ›› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡

ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቆየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ጌቴሴማኒ ይዞ ከሔደ በኋላ ከእነርሱ ፈቀቅ ብሎ ‹‹ሰውነቴ እስከ ሞት ድረስ አዘነች፤›› እያለ ወዙ እንደ ውኃና እንደ ደም እስኪወርድ ድረስ እየወደቀ እየተነሣ በስግደት በኀዘን እንደ መሠረተው ዅሉ፣ የክርስቶስ ተከታይ በሙሉ በኀዘን፣ በለቅሶ እየሰገደ የፈጣሪውን ውለታ የሚያስብበት፤ ለፈጣሪው ያለውን ፍቅር የሚገልጥበት ወቅት ነው – ሰሙነ ሕማማት (ማቴ. ፳፮፥፴፰፤ ማር. ፲፬፥፴፬፤ ሉቃ. ፳፪፥፵፬)፡፡

‹‹… ክርስቶስ ተሰቅለ በሥጋሁ በእንቲአነ ወአንትሙኒ ተወልተዉ በይእቲ ሕሊና እስመ ዘሐመ በሥጋሁ ድኅነ እምኃጣውኡ፤ ክርስቶስ ስለ እኛ በሥጋው ከተሰቀለ እናንተም ይህችን አሳብ ጋሻ አድርጋችሁ ኑሩ፡፡ በሥጋው መከራ የተቀበለ ከኃጢአት ድኖአልና፤›› በማለት ቅዱስ ጴጥሮስ አጥብቆ የመከረን ስለዚህ ነው (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፩)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የሐዋርያት አማናዊ ጥምቀት እንዴትና መቼ ተከናወነ?

በሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና

የሊቃውንት ጉባኤ አባል

መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ አስቀድሞ ‹‹የሙት ልጆች ትኾኑ ዘንድ አልተዋችሁም፡፡ እኔ ወደ እናንተ እመጣለሁና ገና ጥቂት ጊዜ አለ፡፡ ከእንግዲህ ወዲህም ዓለም አያየኝም፡፡ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፡፡ እኔ ሕያው ነኝና እናንተም ሕያዋን ትኾናላችሁ፤›› በማለት ለአባቶቻችን ቅዱሳን ሐዋርያት የማይለወጥ አምላካዊ ጽኑ ተስፋ ሰጥቶአቸው ነበረ (ዮሐ. ፲፬፥፲፰-፲፱)፡፡ ይኸውም ‹‹እንደ ሙት ልጆች እንድትኾኑ ሐሙስ ማታ እንደ ተለያኋችሁ አልቀርም፡፡ እኔ ከጥቂት ቀን (ከሁለት ቀናት) በኋላ በትንሣኤ ወደ እናንተ እመጣለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ዓለሙ አያየኝም፤ እኔ በማይራብ፣ በማይጠማ፣ በማይታመም፣ በማይሞት ሕያው ሥጋ እነሣለሁና እናንተም በልጅነት ሕይወት ልዩ ሕያዋን ትኾናላችሁ›› ሲላቸው ነው፡፡

ከዚያ በፊት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን ‹‹ዅላችሁ በዚህች ሌሊት እንደማታውቁኝ ትክዱኛላችሁ›› በማለት ትተውት እንደሚሸሹና ከመካከላቸው የሚክደውም እንደ ነበረ ደጋግሞ ነግሯቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ዅሉም ቢክዱህ እኔ ፈጽሜ አልክድህም›› ብሎታል፡፡ ጌታችንም የልብን ያውቃልና ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዶሮ ሳይጮኽ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ›› ሲል እንደሚክደው አስረግጦ ነግሮታል፡፡ የአምላክ ቃል አይታበይምና የአይሁድ ጭፍሮች ጌታችንን በያዙት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ዅሉ ትተው ሸሽተዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹አንተ የእርሱ ደቀ መዝሙር ነህ›› ሲሉት ‹‹የምትሉትን ፈጽሞ አላውቀውም›› ብሏል (ማቴ. ፳፮፥፶፮፤ ማር. ፲፬፥፳፯-፶)፡፡

ጌታችን ከሙታን ተለይቶ በተነሣ ጊዜም ቅዱሳን መላእክት ‹‹ተነሥቶአል፤ ከዚህ የለም፤›› ብለው ለቅዱሳት አንስት እንደ ነገሩአቸውና ራሱ ጌታችንም በመንገድ ተገልጦ እንዳነጋገራቸው ለቅዱሳን ሐዋርያቱ ሲያበሥሯቸው ሙቶ ይቀራል ብለው ተስፋ ቈርጠዋልና እንደ ተነሣ አላመኗቸውም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ከእነርሱ መካከል ለሁለቱ ወደ ገጠር ሲሔዱ በሌላ መልክ ተገልጦላቸዋል፡፡ እነርሱም ጌታችን እንደ ተገለጠላቸው ሔደው ለባልንጀሮቻቸው ነግረዋል፡፡ እነርሱንም ቢኾን አላመኗቸውም፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት በማዕድ ተቀምጠው ሳሉ ተገልጦላቸዋል፡፡ አሁንም መነሣቱን ያዩ ደቀ መዛሙርትን አላመኗቸውም ነበር፡፡ ጌታችንም ስለ ሃይማኖታቸው ጉድለት ገሥፆአቸዋል፤ የልባቸውንም ጽናት ነቅፏል (ማር. ፲፮፥፲፪-፲፬)፡፡ በዚህ ኹኔታ ለቅዱሳን ሐዋርያት ካሣ ሳይፈጸም ከስቅለት በፊት በኅፅበተ እግር ተጠመቁ ቢባል እንኳ ትንሣኤውን አላመኑም ነበር፡፡ እንዳውም የክርስቶስ ትንሣኤ ተረት እንደ መሰላቸው ተጽፋል (ሉቃ. ፳፬፥፲፩)፡፡ አንድ ሰው ከካደ ደግሞ ልጅነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ስለ ኾነም የሐዋርያት ጥምቀት እግር በመታጠብ እንዳልኾነ እንረዳለን፡፡

እርግጠኛው የቅዱሳን ሐዋርያት ጥምቀት ግን ካሣ ከተፈጸመ በኋላ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከሃሊነቱ ዲያብሎስን ድል ነሥቶ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ በተነሣ ጊዜ ነው፡፡ ቀድሞውንም አምስት ሺሕ ከአምስት መቶው ዘመን ሲፈጸም ‹‹ከልጅ ልጅህ ተወልጄ፣ በአደባባይህ ተመላልሼ፣በመስቀል ተሰቅዬ አድንሃለሁ፤›› ብሎ ለአዳም በሰጠው ተስፋ መሠረት ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ዅሉንም በእርሱ ይቅር ብሎ በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በምድርና በሰማይ ላሉ ሰላምን አደረገ (ቆላ. ፩፥፳)፡፡ ‹‹በውኂዘ ደሙ ቅዱስ አንጽሖሙ ለመሐይምናን ወለሕዝብ ንጹሓን፤ በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋ በዓለመ ነፍስ ያሉትን አዳነ፤›› እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም (የእሑድ ውዳሴ ማርያም)፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹ክርስቶስም ስለ ሰው ኃጢአት አንድ ጊዜ ሙቶአልና ጻድቅ እርሱ እኛን ወደ እግዚአብሔር ያቀርበን ዘንድ ስለ እኛ ኃጢአት በሥጋ ሞተ፤ በመንፈስ ግን ሕያው ነው፡፡ በእርሱም በወኅኒ ወደሚኖሩ ነፍሳት ሒዶ ነጻነትን ሰበከላቸው›› በማለት ጌታችን በዕለተ ዓርብ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በገዛ ሥልጣኑ መለየቱንና በሲኦል የነበሩ ነፍሳትን ማውጣቱን አስረድቶናል (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፰-፲፱)፡፡

መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ በዓለመ ነፍስ በሲኦል ሥቃይ ውስጥ የነበሩትን ነፍሳት ሕያው በኾነ ደሙ አንጽቶና ቀድሶ ወደ ገነት ከመለሰ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹እግዚአብሔርነቱ ግን የሞትን ማሰሪያ ፈቶ ከሙታን ለይቶ አስነሣው፡፡ ሞት እርሱን ሊይዘው አይችልምና፤›› እንዳለው ጌታችን ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ሞትን ድል ነሥቶ እሑድ በመንፈቅ ሌሊት ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡ እንደ ተነሣም በቀጥታ ወደ ቅዱሳን ሐዋርያት ነው የሔደው፡፡

ደቀ መዛሙርቱም አይሁድን ስለ ፈሩ ደጁን ቈልፈው ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ሳይከፈት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እነርሱ ገብቶ በመካከላቸው ቆመና ‹‹ሰላም ለእናንተይኹን!›› አላቸው፡፡ እነርሱም ፈሩ፤ ደነገጡ፡፡ ጌታችንም ‹‹እኔ ነኝ፤ አትፍሩ፤›› አለና እጆቹንና እግሮቹን፣ ጎኑንም አሳያቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ጌታችንን ባዩት ጊዜ ደስ አላቸው፡፡ ማለትም ፍርኃቱ ተዋቸው፤ ጥርጣሬው ተወገደላቸው፡፡ ፈጣሪያቸው ሙቶ እንደ ተነሣ አመኑ፤ ተረዱ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዚህ መልኩ ካሳመናቸው በኋላ ዳግመኛ ‹‹ሰላም ለእናንተ ይኹን! አብ እኔን እንደ ላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኋለሁ፤›› አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እፍ አለባቸው፤ መንፈስ ቅዱስንም ተቀበሉ (ዮሐ. ፳፥፳፩-፳፪)፡፡

‹‹እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር ፈጠረው፤ በፊቱም ሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፡፡ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ኾነ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዘፍ. ፪፥፯)፣ አዳም በተፈጠረ በዐርባ ቀኑ እግዚአብሔር አምላክ በፊቱ እፍ ብሎ ያሳደረበትን ልጅነት ዕፀ በለስን በልቶ ቢያስወስዳት ዳግማይ አዳም ክርስቶስ አዳም ስላጠፋው ጥፋት ደሙን በመስቀል ላይ አፍስሶ፣ ውድ ሕይወቱን ክሦ በቅዱሳን ሐዋርያት ፊት ‹‹እፍ›› በማለት ልጅነትን ዳግመኛ አሳደረባቸው፡፡ በዚህም ቀድሞ በዕፀ በለስ ምክንያት የሔደች ልጅነት በዕፀ መስቀል ምክንያት ተመለሰች፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት የትንሣኤ ዕለት እንደ ተጠመቁ ራሳቸው በመጽሐፈ ኪዳን እንደሚከተለው ገልጸውታል፤

‹‹… ኮነ እምድኅረ ተንሥአ አስተርአየነ ወተገሠ እምቶማስ ወማቴዎስ ወዮሐንስ ወተፈወስነ (ወአእመርነ) ከመ ተንሥአ እግዚእነ … ወይቤለነ ‹አማን አማን እብለክሙ ኢትከውኑ ውሉደ እግዚአብሔር ዘእንበለ በመንፈስ ቅዱስ›፡፡ ወተሰጠውናሁ ወንቤ ‹እግዚኦ ሀበነ መንፈሰ ቅዱሰ› ወነፍሐ ላዕሌነ ኢየሱስ፡፡ ወእምድኅረ ነሣእነ መንፈሰ ቅዱሰ ይቤለነ ‹አንትሙ እለ መንግሥተ ሰማያት ዘእንበለ ኑፋቄ ልብ›፤ … እንዲህ ኾነ፤ ጌታችን ከተነሣ በኋላ ተገለጠልን፡፡ በቶማስ በማቴዎስና በዮሐንስ እጅ ተዳሰሰ፡፡ ጌታችን እንደ ተነሣም አወቅን፡፡ እርሱም ‹እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ቅዱስ ካልተወለዳችሁ የእግዚአብሔር ልጆች አትኾኑም› አለን፡፡ እኛም ‹መንፈስ ቅዱስን ስጠን?› ስንል መለስንለት፡፡ ኢየሱስም በእኛ ላይ ‹እፍ› አለ፡፡ መንፈስ ቅዱስን ከተቀበልን በኋላ ‹እናንተ ጥርጥር በሌለው ልብ የመንግሥተ ሰማያት ባለቤቶች ናችሁ› አለን፤›› (መጽሐፈ ኪዳን አንቀጽ ፩)፡፡

‹‹ማን ይናገር የነበረ›› እንዲሉ ቅዱሳን ሐዋርያት እስከ ትንሣኤ ድረስ መንፈስን (ልጅነትን) ሳይቀበሉ ቆይተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተነሥቶ ወደ እነርሱ በመጣ ጊዜ በንፍሐት መንፈስ ቅዱስን እንዳሳደረባቸው ራሳቸው በግልጥ ተናግረዋል፡፡ በጌታችን ቀኝ ተሰቅሎ የነበረው ወንበዴ በክርስቶስ ደም ካሣ እንደ ተፈጸመ፣ ልጅነት እንደ ተመለሰ ሲያረጋገጥ ጌታችንን ‹‹ዳግመኛ በመጣህ ጊዜ በመንግሥትህ አስበኝ?›› ቢለው ጌታችን ኢየሱስም መልሶ ‹‹እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ትኖራለህ፤›› ብሎታል (ሉቃ. ፳፫፥፵፫)፡፡ ወገኔ ሆይ! ስለዚህ የሐዋርያት ጥምቀት የትንሣኤ ዕለት ለመኾኑ ከዚህ የበለጠ ማስረጃ ምን አለ? ማወቅ ለሚሻ ቅን ልቡና ላለው ከዚህ በላይ የቀረበው ማስረጃ በቂ ነው፡፡ ተጨማሪ ማስረጃ ካስፈለገ ደግሞ ከዚህ ቀጥሎ ያስቀመጥናቸውን ጥቅሶች መመልከት ይቻላል፤

  • ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ›› (ሐዋ. ፳.፳፰)፤ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል፤›› (ዕብ.፲.፲)፡፡
  • ‹‹ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ ለተመረጡ …፤›› (፩ኛ ጴጥ. ፬፥፪)፡፡
  • ‹‹በክቡር በክርስቶስ ደም እንደ ተዋጃችሁ እናንተ ታውቃላችሁ፤›› (፩ኛ ጴጥ. ፲፰፥፲፰)፡፡
  • ‹‹… ከኃጢአታችን ላጠበን፤ በደሙ ላነጻን …፤›› (ራእ. ፩፥፮)፡፡
  • ‹‹… ተገድለሃልና በደምህም ከሕዝብና ከአሕዛብ ከነገድም ዅሉ፤ ከወገንም ዅሉ ሰዎችን ለእግዚአብሔር ዋጅተሃልና፤›› (ራእ. ፭፥፱)፡፡

እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች የልጅነት ክብር (ጥምቀት) ለሐዋርያት የተሰጠው የክርስቶስ ደም ከፈሰሰ በኋላ ነው እንጂ ከዚያ በፊት በኅፅበተ እግር እንዳልኾነ በግልጥ ያስረዳሉ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡