በማሞ አየነው
በተደጋጋሚ ከሚያጋጥሙኝ ክስተቶች አንዱ ይህ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከምተዋወቀው አንድ ልጅ ጋር ቁጭ ብለን እየተጨዋወትን ነው፡፡ ልጁን የማውቀው ሰ/ት/ቤት ውስጥ ታታሪ አገልጋይ በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁን ከመንፈሳዊ አገልግሎቱ ራሱን አግልሏል፡፡ እንደድሮው ስለመንፈሳዊ ሕይወቱ የሚያወያየው ለአገልግሎት የሚጋብዘው፣ ሲደክም የሚያበረታው፣ ሲሰለች መንፈሱን የሚያድስለት፣ ጓደኛ የለውም፡፡
ከሚሳተፍባት አጥቢያ ሰ/ት/ቤት መራቁን እንደ ትልቅ ምክንያት እያነሳ በተደጋጋሚ ነገረኝ ምክንያቱ አልተዋጠልኝም፤የራቀው ከአንድ አካባቢ እንጂ ቤተ ክርስቲያንና ሰ/ት/ቤት አሁን ካለበት አካባቢ እንዳለ አውቃለው፤ ከተለያየን በኋላ ስለጉዳዩ በደንብ አሰብኩበት፡፡ ይህ ችግር የብዙ ሰዎች ችግር እንደሆነ በተደጋጋሚ እናያለን፤ ራስን ከሚያገኛቸው ሁኔታዎች ጋር አስማምቶ ክርስቲያናዊ ሕይወትን በጊዜና በቦታ የመገደብ፣ ራስን ከሚያገኛቸው ሁኔታዎች ጋር አስማምቶ ክርስቲያናዊ ሕይወትንና አገልግሎትን የማስኬድ ችግር የብዙዎች ችግር ነው፡፡ ይህም አንድ ነገር እንዳለ ያመላክተናል።ይህም ክርስትናችን የቆመበት መሠረት በነፋስና በጎርፍ ተጠራርጎ ለመውደቅ ቅርብ መሆኑን ነው። ለዚህ ነው ጥቃቅን ምክንያቶች ግዙፍ የሚመስለንን ግን ያልሆነውን ክርስትናችንን አደጋ ላይ የሚጥሉት የሁሉም ነገር መነሻ መሠረቱ ነውና፡፡ ክርስትናም የራሱ መሠረት አለው፡፡ እስኪ በተረጋጋ መንፈስ ክርስትናችን የተገነባበትን እንመርምር፡፡ በክርስቲያናዊ ሕይወታችን ውስጥ ልብ ልንላቸው የሚገቡ ነገር ግን እንደዋዛ የምናያቸውን ነጥቦችን እንደሚከተለው እንመለከታለን፡-
ሀ. በሌሎች ጫንቃ ያረፈ ክርስትና ነው ያለዎት?
ሁሌም ልብ ልንለው ከሚገቡ ነጥቦች አንዱ ክርስትናችን ማንን ተስፋ እንዳደረገና በማንስ ላይ ተስፋውን እንደጣለ መረዳት ነው፡፡ የብዙዎቻችንን መንፈሳዊ አይን ሸፍኖ ዋናውን ነጥብ እንዳናይና የሚያደርጉ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ በአካባቢያዊና በአጥቢያ ላይ የተመሠረተ የአገልግሎተ ፍቅር፣ በማኅበራት ትክሻ ላይ የተንጠላጠለ ሱታፌ፣ ከጓደኝነትና ከመላመድ የመነጨ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ዋናውን የክርስትና ዓላማ እንዳንረዳ ከሚያደርጉን መሰናክሎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ነጥቦች ለክርስትናችን እንደ ግብዓት የሚታዩ እንጂ የአገልግሎታችንና የክርስቲያናዊ ሕይወታችን መሠረቶች ሊሆኑ አይገባም፡፡ ልብ ብሎ ራስን መመርመር የሚገባም ለዚሁ ነው፡፡
ግድግዳና ጣሪያ ብቻ ለቤት መሠረት ሊሆኑ እንደማይችሉ ሁሉ በሰው በማኅበር መሠባሰብ ላይ የተመሠረተ ክርስትናም ዘላቂነት የለውም፡፡ ብዙዎች ከሚያገለግሉበት አጥቢያ ሲርቁ፤ በክርስትና ከሚያውቋቸው ጓደኞቻቸው ሲለዩ ከቤተክርስቲን ለመራቅ ያስባሉ፡፡ ክርስትና እዚያና እዚህ ብቻ ያለ ይመስላቸዋል፤ ክርስቲያናዊ ሕይወት የእነ እገሌ ተሰጥዖ ብቻ አድርገው ይወስዳሉ፤ ቀስ በቀስም ተስፋ የመቁረጥና የብቸኝነት ስሜት በልባችን ሰርጾ ይገባል፡፡ ከለመድነው አሰራርና አካሄድ የተለወጠ ነገር ባየን ቁጥር እየበረገግንና እየራቅን እንመጣለን። ስለዚህ በድሮው ክርስትናችን መቀጠል ይከብደናል፡፡ ዴማስ ከለመደው ከተማና ሁኔታ የተለየ ሁኔታ ስለገጠመው ነበር በተሰሎንቄ ተስቦ የቀረው /2ኛ ጢሞ/ ብዙዎች የተሰናከሉት የሰው ልጆችን ኑሮ በማየታቸውና ከለመዱት የአኗኗር ዘየ የተለየ ነገር ስለገጠማቸውና ስለተሸነፉለትም ነበር። /ኩፋ 6፥9 ዘፍ 6፥1/ የያዕቆብ ልጅ ዲናም ከክብር ያነሰችው የለመደችውን የአህዛብ አኗኗር መቋቋም አቅቷት ነበር፡፡ ዘፍ 34፥1 የብዙዎቻችንም ክርስትና እንዲሁ ለፈተና የተጋለጠ ነው፡፡ አካባቢን ከመለወጥ ይልቅ እኛው ተለውጠን ክርስትናችን ደብዛው የጠፋብን ብዙዎች ነን፡፡ የማኅበረ እስጢፋኖስ መበታተን ክርስትናን የበለጠ እንዲስፋፋ አደረገ እንጂ ክርስትናቸውን አላጠፋባቸውም፡፡ በጊዜና በቦታ ሳይወሰኑ አሐቲ የሆነችውን ቤተክርስቲያን ማገልገል የቤተክርስቲያንን የአገልግሎት ሁኔታ የመረዳትና የክርስትናንም ውል የመያዝ ምልክት ነው፡፡ ከመንፈሳዊ ሩጫችን ጎን ለጎን ልናስተውለውና ልንረዳው የሚገባን ቢኖር እያገለገልኩና እየሮጥኩ ያለሁት ከራሴ በሚመነጭ መንፈሳዊ ግፊት ነው ወይስ በስብሰባ ድምቀት ልምድ ስለሆነብኝ? ወይንም ከሰ/ት/ቤት ልጆች መራቅ ስላልፈለግሁ ነው የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡
ለ. ከአፍአዊ አገልግሎትና ምስጢራት ከመሳተፍ የቱን ያስቀድማሉ?
በሚገባ አስተውለንና አጢነን ከሆነ ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ ሩጫ ውስጥ የገቡ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ምስጢራት መሳተፍ ያቆማሉ፡፡ ከኪዳን፣ ከቅዳሴ፣ ከሥጋ ወደሙ የራቁ ነገር ግን ሩጫ የሚያበዙ፣ መረጋጋት የማይታይባቸው፣ በአፍአ (በውጭ) ያሉ ብዙ ጓደኞች አሉን፡፡ መንፈሳዊ በሆነ ኃይልና ዕውቀት ከማገልገል ይልቅ በስጋ ድካም ማገልገል የበለጠ ውጤት የሚስገኝ ስለሚመስላቸው ቅዳሴና ኪዳን ለነሱ ቦታ የላቸውም፤ እንደዚህ ዓይነት አገልጋዮች ይህን ከመሰለው እንቅስቃሴ ሲለዩ የክርስትና መስመር የተበጠሰ ይመስላቸዋል፡፡ የዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ ዓላማ ሰውን ምስጢራት ወደ ማሳተፍ ማምጣት መሆኑን ይዘነጉታል፡፡
የማርታና የማርያምም ታሪክ የሚያስተላልፍልን መልእክት ይህንን ነው፡፡ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት የሚቻለው ከቅዳሴው ምስጢር መሳተፍ ስንችል ነው፡፡ በቅዳሴ ቃለ እግዚአብሔርን ሰምተን ብቻ አንበተንም፤ ለሥጋ ወደሙ ያዘጋጀናል፡፡ ዋናው የክርስትና ግብም ይህን ምስጢር መሳተፍ ነው። ጌታችንም ሐዋርያትን ካስተማረና አእምሮአቸውን ካዘጋጀ በኋላ በመጨረሳ ሰዓት የተናገራቸው ታላቅ ነገር ቢኖር ምስጢራትን እንዲፈጽሙ ማድረግ ነበር፡፡ ስለዚህም ነው በምሴተ ሐሙስ ሥጋውና ደሙን ያቀበላቸው፡፡ማቴ 26፥26 መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ያለን ሰዎችም ልናስተውለው የሚገባን ታላቅ ምስጢርም ይህ ነው፡፡ ዕውቀትን ከማጎልበት፣ ለሌሎች መዳን ደፋ ቀና ከማለት በተጨማሪ ምስጢራትን መሳተፍና መፈፀም ይገባናል፡፡ በምስጢራት መሳተፍ ያልለመደ አገልጋይ ክርስትና ሰ/ት/ቤት፣ ማኅበራት ጋር፣ ከጓደኞቹ ዘንድ ብቻ ያለ ስለሚመስለው ከነዚህ ሲርቅ ክርስትናው ከገደል አፋፍ ላይ ይቆማል፡፡ ከምንም ነገር በላይ በምስጢራት መሳተፍ መልመድ ከቤተክርስቲያን እንዳንርቅ የሚያስተሳስረን ሕቡር ገመድ ነው፡፡ ይህን የለመደ ሰው የትም ሄደ የት ከምስጢሩ አይርቅም፡፡ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ማስተካከል የሚገባንም ከዚህ መሠረታዊ ነጥብ ጋር ነው፡፡
ሐ. እውን ሕይወትዎን እየመሩ ያሉት ለሰው ወይስ ለእግዚአብሔር?
ህገ እግዚአብሔርን እየፈጸ ምን ያለነው በእውነተኛ የእግዚአብሔር ፍቅር ተመክረን ነው ወይስ ከመንጋው ላለመለየትና ከነቀፌታ ለመራቅ ብለን ነው? ቤተ እግዚአብሔር የምንሄደው፣ የምናስቀድሰው፣ የምናገለግለው፣ … ከሰው ምላሽን ጠብቀን ከሆነ ጽድቃችን ከፈሪሳዊያን በምን ይለያል? ፈሪሳውያንና ጸሐፍት ህጉን የሚፈጽሙት ለጽድቅ ብለው ሳይሆን የሙሴን ህግ ይፈጽማሉ ለመባል ብቻ ነበር፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን ‹‹ ጽድቃችው ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ….›› ብሎ ያስተማረ፡፡ እያንዳንዱ የሕይወታችን ጥቃቅን ነገር መመርመር ያለብንም ያደርጋሉ ይፈጽማሉ ለመባል ሳይሆን የጌታ ፍቅር ገብቶንና ደስ እያለን በፍጹም ተመስጦ መሆን ይገባል፡፡ ፍፁም በሆነ ፈቃድ ያለተርእዮ ህግን መፈጸም ግን ጽድቃችንን ከሰው ተጽእኖ የጸዳ ያደርገዋል፡፡ ጌታም በወንጌሉ ‹‹ ቀኝህ የሚያደርገውን ግራህ አይመልከት›› ያለው ለታይታና ለሆይ ሆይታ ተብሎ ጽድቅን መፈጸም እንደማይገባን ሲያስረዳን ነው፡፡ በዚህ መነሻነት ጽድቅን አለመፈጸም ከጓደኛ ሲለዩ’ ከሚያውቁት ማኅበረሰብ ሲወጡ ክርስትናችንን ፈተና ላይ ይጥላቸዋል፡፡ ህግ የተሰጠ ከእግዚአብሔር ስለሆነ መፈጸም ያለበት ስለእግዚአብሔርና ለእግዚአብሔር ተብሎ ብቻ ነው፡፡ መጽሐፍም ‹‹ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ›› ይላል ለሰው’ ለጓደኛ’ለማህበረሰብ ብሎ ህግን መፈጸም የእግዚአብሔርን ለሌላ እንደመስጠት ይቆጠራል። ነገሮችን ለእግዚአብሔር ብሎ መፈጸም ክርስትናችን በጊዜ፣ በቦታና በሁኔታ እንዳይወሰን ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ የለምና ነው፡፡ ስለዚህም የትም ሆን የት ከእግዚአብሔር እቅፍ መውጣት አንፈልግም፡፡ ከእግዚአብሔር መራቅ ለሰከንዶች እንኳን ሳናቋርጥ ከምንወስደው አየር እንደመለየት ነው፤ አየር ለመውሰድ ጊዜና ቦታን እንደማንመርጥ ሁሉ ከእግዚአብሔር ከአገልግሎት ላለመራቅም ጊዜና ቦታ መምረጥ አይገባም፡፡
ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች በማስተዋል ክርስትናችንን በጎ ካልሆነ ተጽእኖ ማጽዳት አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ መንፈሳዊ ሕይወታችን በጊዜና በቦታ እንዳይወሰን ለማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህን ሀሳቦች እናስተውል ዘንድ አስተውለንም እንተገብራቸው ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ልቦናችንን ያነቃቃል!! አሜን።