ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ? ሉቃ. ፳፬፥፭

ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ

በኦሪት ዘፀአት ፲፪፥፳፩-፳፰ እንደተጻፈው ይህ ዕለት በብሉይ ኪዳን ፋሲካ በመባል ይታወቃል፡፡ ትርጉሙም መሻገር ማለት ነው፤ ይህም ሕዝበ እሥራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ ወጥተው ወደ ምድረ ርስት የተሸጋገሩበት ዕለት ነው፤ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ትንሣኤ ይባላል፡፡ በዓለ ትንሣኤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሞቱ ድል ነሥቶ ነጻነትን ለሰው ልጆች ሰጥቶ ከሞት ወደ ሕይወት፤ ከኀሳር ወደ ክብር የተሸጋገርንበት ዕለት በመሆኑ ትንሣኤ እንለዋለን፤ ቅዱስ ሉቃ.  ፳፬፥፭ የጻፈውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ስለ በዓለ ትንሣኤ ጥቂት ዐበይት ነገሮችን እንመልከት፡፡

ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጋላችሁ? ይህንን ጥያቄ የጠየቀው በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር አጠገብ የነበረው የእግዚአብሔር መልአክ ሲሆን ጥያቄው የቀረበላቸው ደግሞ በማለዳ ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር የሄዱት ቅዱሳት አንስት ነበሩ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዋለበት ውለው ባደረበት አድረው የቃሉን ትምህርት የእጁን ተአምራት ያዩት ቅዱሳት እናቶች የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በተባለች በዕለተ እሑድ በማለዳ የመቃብሩን ጠባቂዎችና የሌሊቱን ጨለማ ሳይፈሩ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ ሽቱ ለመቀባት ገሰገሡ፡፡ መልአከ እግዚአብሔር ይህንን ጥያቄ  በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር አጠገብ አቀረበላቸው፤ ቅዱሳት አንስት የመልአኩን ጥያቄ እንደሰሙ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን ከሙታን እንደሚነሣ የተናገረውን ቃል አስታወሱ፡፡ ከዚያም ቅዱሳት አንስት ወደ ሐዋርያት ሄደው ያዩትንና የሰሙትን ሁሉ ተናገሩ፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤውን አበሠሩ፤ ቅዱሳን ሐዋርያትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አለመሆኑን በግልጽ ተረዱ፡፡ የተሰቀለውን የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ ሕማሙንና ትንሣኤውን፤ በአባቱ ዕሪና በልዕልና መቀመጡን  ዞረው አስተምረዋል፡፡

በዓለ ትንሣኤ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት አንዱ ነው፤ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ተስፋ አበውና ትንቢተ ነቢያት ተፈጽሞ በትንሣኤው የሞት ሥልጣን በመሻሩ የቤተ ክርስቲያን አበው በዓለ ትንሣኤን «የበዓላት በኵር» በማለት ይጠሩታል፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕማምና ሞት አሳዛኝ ታሪክ ሳይኾን ሕያው እውነት ነው፤ የዓለም መድኃኒት የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ የሐዋርያት ስብከት፤ የቤተ ክርስቲያን መሠረት ነው፡፡ ስለዚህም ዘወትር በጸሎተ ቅዳሴያችን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መሞታችንን፤ ከእርሱ ጋር መነሣታችንንና ሕያው መሆናችንን እንገልጻለን፤ ሕማሙንና ሞቱን፤ ትንሣኤውን፤ ዕርገቱንና ዳግም ምጽአቱን እንሰብካለን፡፡ በበዓለ ትንሣኤ በዕለተ ስቅለት የነበረው የኀዘን ዜማ በታላቅ የደስታ ዜማ ይተካል፤ በዚህ ዕለት ቤተ ክርስቲያን ነጭ ልብስ ለብሳ የደስታ ዝማሬ ታሰማለች፡፡

ከነቢያት ወገን ታላቁ ነቢይ ኤልያስ እንዲሁም ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕም በእግዚአብሔር ኃይል ሙታንን እንዳስነሡ ይታወቃል፤ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ ፰ ቍጥር ፲፬ ታሪኳ የተጻፈው የምኵራብ አለቃ የነበረችው ልጅ፤ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፯ ቍጥር ፲፪ ታሪኩ የተጻፈው ናይን በምትባል ሥፍራ የነበችው የድሃዪቱ ልጅ እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፩ ታሪኩ የሚነበበው አልአዛር በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራት ከሙታን ተነሥተዋል፡፡ ዳግመኛም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ በቀራንዮ ኮረብታ ተሰቅሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ሥጋው በለየበት ሰዓት ቍጥራቸው ከስድስት መቶ የሚያንስ ከአምስት መቶ የሚበልጥ ሰዎች ከሙታን ተነሥተዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ዳግመኛ ሞተዋል፤ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ግን ከሁሉ ይለያል፤ እርሱ ከሙታን ለመነሣት አሥነሽ አላስፈለገውም፣ ከሙታን የተነሣው በራሱ ሥልጣን ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  በማይሞት፤ በማይለወጥ ሥጋ በመነሣቱ እንደሌሎች ዳግመኛ ሞትና ትንሣኤ የለበትም፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በቀዳማዊ ቆሮንቶስ ምዕራፍ ፲፭ ቍጥር ፳፫ እንደተናገረው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ሙስና መቃብርን አጥፍቶ(በማይሞትና በማይበሰብስ ሥጋ) በሞቱ ሞትን ድል ነሥቶ፤ የሞት መውጊያን አሸንፎ፤ ሲኦልን በዝብዞ ከሙታን በመነሣቱ የትንሣኤያችን በኵር(መሪ) ተብሏል፡፡ ዳግመኛም ይህ ሐዋርያ በቆላስይስ መልእክቱ ምዕራፍ ፩ ቁጥር ፲፰ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን «የሙታን በኵር» በማለት ጠርቶታል፡፡

የድኅነታችን አለኝታ የእግዚአብሔር ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በሕማሙና በሞቱ የዲያብሎስን ቁራኝነት በማጥፋት አጋንንትን ድል የመንሣትን ኃይል ሰጥቶናል፡፡ ከጥንት ዠምሮ የሰውን ነፍስ የሚጎዳ የዲያብሎስን ሥልጣን ያጠፋ ዘንድ ፤ የፈጠረውን ዓለም ያድን ዘንድ የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ፈቃድ፤ በአባቱ ፈቃድና በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ወደዚህ ዓለም መጥቷል፡፡ የክብር ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን  ለመስቀል ሞት አሳልፎ በመስጠት በሥጋው ሞቶ በመለኮቱ ሕያው ሆነ፡፡ የሞት አበጋዝን ዲያብሎስን ኃይል ያጠፋ ዘንድ የማይሞተው የሕያው እግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሞተ፤ ሕይወት መድኃኒት በምትሆን ሞቱ ሞትን ያጠፋ ዘንድ፤ ሙታንን ያድን ዘንድ እርሱ የሕያው አምላክ ልጅ ሞተ፡፡ በኪሩቤል ላይ ያለው እርሱ በከርሠ መቃብር ሦስት መዓልትና ሌሊት አደረ፡፡ ያን ጊዜ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአባታችን በአዳም በደል ተግዘው ወደ ሲኦል የወረዱት ነፍሳት በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ነጻ አወጥቷቸዋል፡፡ ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱና ለንጹሐን ሐዋርያቱ እንደተናገረው በሦስተኛው ዕለት በሥልጣኑ ከሙታን ተነሥቷል፤ በዚህም ሙስና መቃብርን(በመቃብር ውስጥ መፍረስ መበስበስን) አጥፍቶልናል፤ ዳግመኛ ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ በመነሣቱ ለትንሣኤያችን በኵር ኾኖልናል፤ ቆላ.  ፩ ፥ ፲፰፡፡ በትንሣኤውም ትንሣኤያችንን ገልጦልናል፤ ከሞት ወደ ሕይወት መልሶናል፤ ፀሐየ ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ለሰውነታችን ትንሣኤን፤ ለነፍሳችን ሕይወትን ሰጥቶናል፤ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ፲፩ ቍጥር ፳፭ እንዳስተማረን እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ነው፤ እርሱ የሕይወታችን መገኛ ነው፡፡

በዓለ ትንሣኤን ስናከብር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አለመሆኑን ማስተዋል ይገባናል፤ የእግዚአብሔር መልአክ በመቃብሩ አጠገብ ለተገኙት ሴቶች እንደነገራቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሕያዋን መካከል እንጂ በሙታን መካከል አይገኝም፡፡ አባታችን አዳም የማይገባውን አምላክነት ሽቶ ዕፀ  በለስን በመብላቱ ሞተ ሕሊና፤ ሞተ ሥጋ እንዲሁም ሞተ ነፍስ አግኝቶታል፡፡ ዳግመኛም በርደተ መቃብር ላይ ርደተ ሲኦል ተፈርዶበት ነበር፡፡ ሞተ ሕሊና በኃጢአት መኖር ነው፡፡ ንዋይ ኅሩይ ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ ፪ ቁጥር ፩ «በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ሙታን ነበራችኹ» በማለት እንደጻፈው በኃጢአት መኖር ሞት ነው፤ ዳግመኛም ሐዋርያው እንዳስተማረን የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው፤ ሞተ ሥጋ የሥጋ ከነፍስ መለየት ነው፤ ሞተ ነፍስ ደግሞ የነፍስ ከጸጋ እግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በአንጻሩ ትንሣኤም በሦስት ወገን ይታያል፤ ትንሣኤ ሕሊና(ልቡና) በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ፤ ትንሣኤ ዘሥጋ እንደወለተ ኢያኢሮስ፤ እንደአልአዛር ከሞት መነሣት በኋላም በትንሣኤ ዘጉባኤ ከሞት መነሣት ነው፤ ትንሣኤ ነፍስ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት በቀኝ መቆም ነው፡፡

ከንስሐ ሕይወት ተለይቶ ከቅዱስ ሥጋውና ከክቡር ደሙ ርቆ ስለኃጢአታችን የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት ከእርሱም ጋር መኖር አይቻልም፡፡ ሞትን ድል አድራጊው የሕይወት ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ ጋር የሚሆነው እኛም ከእርሱ ጋር መኖር የምንችለው ለኃጢአታችን ሥርየት በቀራንዮ አደባባይ የተቆረሰውን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ተቀብለን ሕያዋን ስንሆን ነው፡፡ ፋሲካን መፈሰክ የሚገባን የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ በተሠዋው በእግዚአብሔር በግ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋና ደም እንጂ በእንስሳት ሥጋና ደም ሊሆን አይገባም፡፡ ለትንሣኤ በዓል ሊያስጨንቀን የሚገባው በገንዘባችን የምንገበየው ምድራዊ መብል መጠጡ ሳይሆን በጥበበ እግዚአብሔር ጸጋ ሆኖ የተሰጠን ቅዱስ ሥጋውንና ክብር ደሙን አለመቀበላችን ነው፡፡ በዓለ ትንሣኤ ሕያው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን ይገኝ ዘንድ በትንሣኤ ልቡና ሕያዋን የምንሆንበት መንፈሳዊ በዓል ነው፤ ስለዚህም በዓለ ትንሣኤን ስናከበር በትንሣኤ ሕሊና ሕያዋን ሆነን ቅዱስ ቍርባን መቀበል ይገባናል፡፡

 ተስፋ ትንሣኤን የምናምን ክርስቲያኖች ዘመናችን ሳይፈጸም የምሕረትና የፍቅር እጆቹን ዘርግቶ ወደሚጠራን ሕያው አምላክ በንስሐ እንቅረብ፤ በፈሪሃ እግዚአብሔር በፍጹም ፍቅር የተሰጠንን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንቀበል፡፡ ያንጊዜ ትንሣኤ ልቡና እናገኛለን፤ ያን ጊዜ በምሕረቱና በፍቅሩ በትንሣኤ ዘጉባኤ በክብር ተነሥተን በቀኙ እንቆማለን፤ የሰው ዐይን ያላየውን፤ ጀሮ ያልሰማውን፤ የሰው ልብ ያላሰበውን ዓለም ሳይፈጠር ለወዳጆቹ ያዘጋጀውን ተድላ ነፍስ የሚገኝበትን ገነት መንግሥተ ሰማያትን እንወርሳለን፡፡

 ለመንግሥቱ ጥንት ወይንም ፍጻሜ የሌለው የሕያው አምላክ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኒት በምትሆን ሞቱ የእኛን ሞት ወደ ሕይወት ለውጦ ቅድስት ትንሣኤውን ገልጦልናል፤ ብርሃነ ትንሣኤውን አሳይቶናል፡፡ የቆጵሮሱ ኤጲስ ቆጶስ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ መልሕቅ በሚባል መጽሐፉ «በትንሣኤውም የትንሣኤያችንንም ተስፋ ምሥጢር እንናገራለን» በማለት እንደተናገረው ዳግመኛም በኒቅያ የተሰበሰቡ አበው «የሙታንን መነሣት የሚመጣውንም ሕይወት ተስፋ እናደርጋለን» በማለት በቀኖና ሃይማኖት እንደጻፉልን ክርስቲያኖች በመቃብር ያሉ፤ በተለያየ አሟሟት የሞቱ ሙታን ሁሉ የሚነሡበት ትንሣኤ ሙታን መኖሩን እናምናለን፡፡

 ሕያው አምላካችን ሕያዋን ሆነን እንኖር ዘንድ በመስቀሉ ወደ ሰማያዊ አባቱ አቅርቦናል፤ በእርሱና በእኛ መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ አፍርሶልናል፤ በቅድስት ትንሣኤው ትንሣኤ ልቡና የንስሐ በር ከፍቶልናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማኅየዊት በምትሆን ሞቱ የገነት ደጅን ከፍቶልናል፤ ፍሬዋንም ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሰጥቶናል፤ ስለዚህም ሕያዋን እንሆን ዘንድ ወደ ሕይወት መድኃኒት ቀርበን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንቀበል፡፡ በሕይወታችን ሞተ ሥጋ ሞተ ነፍስ እንዳይሠለጥንብን፤ ትንሣኤ ሕሊና ትንሣኤ ነፍስን እናገኝ ዘንድ የትንሣኤን በዓል በሕያውነት ጸንተን እንኖር ዘንድ ምግባር ትሩፋት በመሥራት እናክብር፡፡

የትንሣኤን በዓል ስናከበር ጽኑ ድቀትን፤ ኀፍረትንና ውርደትን አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት፤ በጭፈራና በዳንኪራ፤ በጣፋጭ መብልና መጠጥ ሰውነትን ማድከምና ልዩ ልዩ ኅብረ ኃጢአት ከመሥራት እንራቅ፤ ክብረ በዓልን ምክንያት በማድረግ በኃጢአት በፍዳ እንዳንያዝ እንንቃ፡፡ በኃጢአት የተነሣ ተስፋ ትንሣኤ እንዳናጣ ዛሬ በንስሐ እንታጠብ፤ ትንሣኤ ሕሊና እናገኝ ዘንድ እንፍጠን፤ በትንሣኤ ዘጉባኤ እጥፍ ዋጋ የምናገኝበትን ለሌሎች በጎ ማድረግን፤ ለድሆች ማካፈልን፤ ሕሙማን መጎብኘትን ገንዘብ እናድርግ፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታውና ቸርነቱ ለዘለዓለሙ ከእኛ ጋር ይሁን፤  የአባቶቻችን ጥርጥር የሌለባት የቀናች ሃይማኖታቸው፤ ድል የማትነሣ ተጋድሏቸው የመንግሥቱ ወራሽ እንድንሆን ያብቃን፤ አሜን፡፡