የተከበራችሁ አንባብያን ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በቤተክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ በተለይም ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት የተፈጸመውን ግፍ የሚገልጽ ተከታታይ ጹሑፍ በማቅረብ ላይ መሆናችን ይታወቃል፡፡ የቤተክርስቲያን ይዞታ ነጠቃ፤ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና የምእመናን ግድያ ዋናዎቹ የግፍ ተግባራት ናቸው፤ ከባለፈው የቀጠለውን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡ መልካም ንባብ!
ክርስቲያኖች መከራ ቢገጥማቸውም ፈርተው ከእምነታቸው እንደማያፈገፍጉ፣ ከራሳቸው ሕይወት ይልቅ ለታቦታቱና ለንዋያተ ቅድሳቱ ቅድሚያ እንደሚሰጡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያነበብነው፤ በቅርብም ሲፈጸም ያየነው ተግባር ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ከመከራ እንዲሰውራቸው ብቻ ሳይሆን በሰማዕትነት እንዲያበረታቸውም ይለምኑ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ለሁለት ሺህ ዘመናት ያልተፈተነችበት የመከራ አይነት፣ያልተፈጸመም ተአምር አለመኖሩን ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን አሕዛብም የሚመሰክሩት እውነታ ነው፡፡ አሕዛብ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ሲነሡ ክርስቲያኖች ታቦታትና ንዋያተ ቅድሳትን ይዘው እንዲሸሹ ከማድረግ በተጨማሪ እግዚአብሔር አምላክ በማይታበል ቃሉ ታቦታቱም ሆኑ አብያተ ክርስቲያናቱ እንዲሰወሩ ሲያደርግ ኖሯል፡፡ በግብጽ የነበረ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ታቦት በእስላሞች በፈረሰ ጊዜ እግዚአብሔር አምላክ ጽላቱን ሰውሮት ከብዙ ዘመን በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአባ ተክለ ሃይማኖት የትውልድ አካባቢ ጽላልሽ ቤተክርስቲያን ሲተከል ታቦቱን ሰጥቷቸው አክብረውታል፡፡ እንዲህ አይነት ተአምራት በየዘመናቱ ተፈጽመዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያንን ሊያቃጥሉ፤ ክርስቲያኖችን ሊገድሉ የተሰለፉ ወገኖች ሲጋፉት ለነበሩት ሃይማኖት ጠበቃ እንዲሆኑም አድርጓል፡፡ ከጥፋታቸው አልመለስ ካሉም ተቀስፈው እንዲሞቱ ሲያደርግ ኖሯል፡፡ ይህንን የምንጽፈው በአንድ በኩል በእምነት ያሉትን ለማጽናናት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ታሪክን መጥቀስ እንጂ ከታሪክ መማር የማይፈልጉ ወገኖች አንብበው እንዲጠቀሙበት በማሳብ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን እየተሳደደች ትዕግሥቷን አሕዛብ አይተው እንዲማሩ ለማስተማር ጭምር ነው፡፡
የምዕራባውያን ተልእኮ አስፈፃሚ የሆኑ መናፍቃንና ግብረ አበሮቻቸው ኢትዮጵያውያንን የአስተሳሰብ ድሃ ለማድረግና የነጮችን የበላይነት አምነው እንዳይቀበሉ እንቅፋት የሆነችባቸውንና የሰውን ልጅ ለሁሉም እኩልነትን የምታስተምረውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ለመበቀል የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ ዝናራቸውን ቢያራግፉና ቀስታቸውን ቢጨርሱም ለማሸነፍ እንደማይችሉ እያወቁት ራሳቸውን የሚጎዳ ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ በዐድዋ በማይጨውና በሌሎች ከውጭ ወራሪዎች ጋር በተደረጉ ጦርነቶች የተሳተፉት ኦርቶዶክሳውያን ብቻ ባይሆኑም ቤተክርስቲያን ለሀገር መሞት ክብር መሆኑን በማወጅ፤ ምሕላ በመያዝ፤ ለዘማቾች የቁም ፍትሐት በማድረግ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በማሰብ መልካቸው እና ቋንቋቸው የሚመስሉንን አሠልጥነው ይልካሉ፡፡ ገንዘብ ማግኝት የሃይማኖተኝነት መስፈርት አስመስለው የዋሃንን ያሳስታሉና በቻሉት ሁሉ የቤተክርስቲያንን አስተዋጽኦ ከትውልድ አእምእሮ አጥበው ለማውጣት ብቻ ሳይሆን የፈጠራ ታሪክ እየፈበረኩ ጥላቻ ሲነዙ ይሰማሉ፡፡የሚያስፈልግውም ይህን የሐሰት ጽሑፍ እውነተኛ መረጃ ይዞ መንግሥት በፍርድ ቤትም መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡
ኅዳር ፯ እና ፰ በ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ኮፈሌ አንሻ በተባለ ቦታ የእስልምና እምነት ተከታዮች ስድስት ክርስቲያኖችን ማረዳቸው እስልምና ባለበት ሀገር ሁሉ ተገዳዳሪያቸውን የማጥፋት ተግባራቸው ማሳያ ነው፡፡በምእመናን ብዛት ከፍተኛውን ቊጥር ያላትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ማጥቃት፤ ማዳከምና ምእመናንን አስገድዶ ማስለም የሚፈጸሙ ተግባራት ናቸው፡፡ በእምነት ስም የተደራጁ ቡድኖች እና የእምነቱ ተከታዮች ቤተክርስቲያንን ሲያጠቁ እና በተለያዩ ጊዜያት ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ ክርስቲያኖችን አስገድዶ በማስለም፤ ፈቃደኛ ካልሆኑ ደግሞ የመግደል ተልኳቸውን ሲፈጽሙ ለደረሰው ጥፋት ክርስቲያኖች ለሚመለከተው አካል አቤቱታ ሲያቀርቡ ፍትሕ አለመሰጠቱ ወደፊት መስተካከል ይርበታል፡፡ይህ ድርጊት በወቅቱና በጊዜው ካልታረመ መጨረሻ ለሌለው ብጥብጥ እንደሚዳረግ መታወቅ ይኖርበታል፡፡
በቡርቃ ጉዲና እና በአዲስ ልማት ቀበሌዎች ከ፪፻ በላይ ክርስቲያን አባወራዎች ይኖሩ የነበሩ ሲሆን በ፳፻፲፩ ዓ.ም በተደረገው የክርስቲያኖች ቈጠራ ፻፹፭ ሆነዋል፡፡ ይህም የሆነው የክርስቲያኖች ግድያና ስደት ስለተባባሰና ድርጊቱ ሲፈጸም እየታየ ተው ባይ በመጥፋቱ ነው፡፡ ጥፋቱ ተጠናቅሮ በመቀጠሉም ከሚያዚያ ወር መጀመሪያ እስካሁን ፲፭ አባወራዎች በጋሌ ሰረጡ ቅድስት ኪዳነምሕረት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ቄስ ጋር በድንኳን ተጠልለው እየኖሩ ነው፡፡ በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው ጥፋት ይቁም የምንለውም እንዲህ አይነት ኢሰብአዊ ተግባራት ሲፈጸሙ ሰለምንመለከት ነው፡፡ ሀገራችን ለውጥ ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ ለውጡን ያልፈለጉት ወገኖች ኢትዮጵያውያን ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ የሀገራችንን ገጽታ እያበላሹ መሆኑን ባንዘነጋውም በአንዳንድ አካባቢዎች ክርስቲያኖች ላይ ብቻ ያነጣጠረ ጥቃት ሥልጣን ላይ በተቀመጡ አካላት ጭምር ሲፈጸም መታየቱ ለሰላም ሳይሆን ለብጥብጥ እየተሠራ ያስመስላልና መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል፡፡
የመንግሥት አካላት ሕዝብን ለማገልገል ኃላፊነት እንዳለባቸው ከተረዱ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዘር፣ቋንቋ፣ቀለም፤ ሃይማኖት፣ሳይለዩ ማገልገል ይኖርባቸዋል፡፡ለሚያልፍ ሥልጣን ታሪክ የማይረሳው ጠባሳ ትቶ ማለፍ ተገቢ አይደለም፡፡ በየቦታው ለሚከሠቱ ግጭቶች መፍትሔ ከመፈለግ ተቆጥበው ተረጋግቶ ለሥራ የተሰማራንና ስለሀገሩ የሚጸልይን ክርስቲያን መነካካት ጥፋት እንጂ ሰላምን አያመጣም፡፡
ሐምሌ ፲፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በባሌጎባ በተፈጠረ የሃይማኖት ግጭት ፭ ምእመናን ተገድለዋል፡፡ እንዲህ አይነት ጥፋቶች አሁንም ቀጥለዋል የሃይማኖት ግጭቶች ሲከሠቱ ግጭቶችን ማን እንዳስነሣቸው ማጣራትና ተገቢ የሆነ እርምጃ መስጠት ይገባል፡፡ እየታየ ያለው ግን እየተሰደዱ፣ እየተገደሉ ታቦታችሁን ይዛችሁ ውጡ የሚባሉትን ክርስቲያኖች መብታቸውን ሲጠይቁ ማሰርና ያለፍርድ ማጉላላት ነው፡፡ ይህን ተግባር ለማስታገስ በየአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ ከሆነ የክርስቲያኖችን ችግር የፈጠረው ማን እንደሆነ፤ እነ ማን ያላግባብ እንደታሰሩ፤ ማን የሚባል ፖሊስ እንዳሰራቸው፤ ለምን ፍርድ ቤት እንዳላቀረባቸው፤ ፍርድ ቤት ለማቅረብ ጠበቃ የማግኘት መብታቸውን ማን እንዳስከለከለ መረጃውን አደራጅተው ለመንግሥት አካላትም በየደረጃው ለሚገኙ የቤተ ክህነት አገልጋዮችም ማሳወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥትንም በሕጋዊ መንገድ ለመጠየቅ ያግዛል፡፡ አጥፊዎች እናምንበታለን ከሚሉት የእምነት ተቋማት ጋር ለመወያየትና አሳማኝ መረጃ ይዞ በፍርድ ቤት ለመጠየቅ ይጠቅማል፡፡ይህ ሁሉ እየተደረገ ጎን ለጎን መረሳት የሌለበት ጉዳይ እግዚአብሔር አምላክ፤ችግሩን እንዲያስወግደው በጾም በጸሎት መጠየቅ ይገባል፡፡ እግዚአብሔርን በንጹሕ ልቡና ሆነን ከጠየቅነው የተፈጠረው ችግር ይርቃል፡፡ በኃጢአታችን ምክንያት ከመጣም ይቅር ይለናል፡፡ ለክብር ከሆነም ያጸናናል፡፡ በእምነት ጸንተን ብንሞት እንኳ ገዳዮቻችንን ማርኮ ያመጣል፡፡ የሰማዕትነት ደም ደርቆ አያውቅም የተባለው ሞታቸው አሕዛብን ማርኮ የሚያመጣ በመሆኑ ነው፡፡
በክርስቲያኖችና በቤተ ክርስቲያን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥፋት አለመቆሙ ያሳሰበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰ/ት/ቤት ወጣቶች፤ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርትና ምሩቃን እንዲሁም የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዩች ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ መግለጫው በአንድ በኩል አጥፊዎች ሕግና ሥርዓት ባለበት ሀገር ከእኩይ ድርጊታቸው እንዲታገሡ ጥፋታቸውን የደረስንበት መሆኑን እንዲረዱ የሚያሳስብ ሲሆን በሌላ በኩል መንግሥትም አጥፊዎችን ለሕግ ማቅረብ እንዳለበት ለማሳሰብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ክርስቲያኖች አንድነትና ትብብር የሚያደርጉበትና ከፊት ይልቅ መትጋት የሚገባቸው መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ያለችበት ሁኔታ ያሳሰበው የቤተክርስቲያን አካል የቅድስት ቤተክርስቲያናችን ውለታና እያደረገችው ያለው አስተዋጽኦ ተረስቶ ለሀገራዊ ጥፋት ባለቤት ተደርጋ መኮነኗን በጽኑ እንቃወማለን፤ ቤተክርስቲያን ከትላንት እስከ ዛሬ የሰላም መልእክተኛ እንጂ አጥፊዎች የሐሰት ታሪክ ፈጥረው እንደሚያወሩት ሕዝብን ከሚያስጨፈጭፉ አካላት ጋር ተባብራ ያጠፋች አይደለችም፡፡ በእውነት ለመናገር ካስፈለገ በደቡብ፤ በምሥራቅ፤ በኦሮምያም ጭምር ክርስትና ያበበው በሀገሩ ባህል ላይ መሆኑን መረዳት አይሳነውም፡፡ በአንጻሩ ሌሎች እምነቶች በገቡበት ቦታ ግን ነባሩ ባሕል ተደምስሶ ሀገራችን እስከማይመስል ደርሷል፡፡ አስተዋይ አእምሮ ላለው ሰው በታሪክ ተወቃሽ የሚሆነው ነባሩን ባህል አስገድዶ ሃይማኖት ያስለወጠ እንጂ ባህላችሁን ጠብቃችሁ ዘላለማዊ ርስትን የምትወርሱበትን ወንጌልን መቀበል ትችላላችሁ የምትለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሆን አይደለችም፡፡
ይቆየን
ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ፳፮ኛ ዓመት ቁጥር ፲፯