በዓለ ደብረ ቁስቋም

እንኳን አደረሰን

ዲያቆን ዘካርያስ ነገደ

ደብረ ቁስቋም በደቡብ ግብፅ የሚገኝ ተራራ ነው፡፡ ደብረ ቁስቋም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍንና ቅድስት ሰሎሜን ይዛ ከስደት ሲመለሱ ያረፉበት ቦታ ነው፡፡

ይህም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ ሄሮድስ ክርስቶስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊው ዮሴፍ በሕልሙ ‹‹ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ›› ባለው መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፫-፲፭)

የክርስቶስ ስደቱ ቀድሞ በነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹. . . እነሆ፥ እግዚአብሔር በፈጣን ደመና ተቀምጦ ወደ ግብፅ ይመጣል፡፡ የግብፅም ጣዖታት በፊቱ ይዋረዳሉ›› ተብሎ በተነገረው መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ ነቢዩ ፈጣን ደመና ያለው ጌታችን በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ጀርባ ላይ ሆኖ ወደ ግብፅ መውረዱን ለመግለጽ ነው፡፡ (ኢሳ. ፲፱፥፩) በስደቱም ጣዖታተ ግብፅ እየተሰባበሩ ሲወድቁ፤ በእነርሱም አድረው ሰውን ሲያስቱ የነበሩ አጋንንትም ሲሸሹ ታይተዋል፡፡

ደግሞም ጌታችን ዳግማዊ አዳም ነውና በምክረ ከይሲ (ዲያብሎስ) ምክንያት ተሰዶ የነበረው ቀዳማዊ አዳምን ለመካስ ተሰደደ፤ በዚህም አጋንንትን ከሰው ልቦና አውጥቶ አሳደደ፡፡

እመቤታችንም ልጇን ይዛ ከስደት ስትመለስ ያረፈችበትን ተራራ ደብረ ቁስቋምን ባረከችው ቀደሰችውም፤ ይህ ተራራ የተቀደሰ ተራራ ስለመሆኑ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ታኦፊሎጎስ በድርሳነ ማርያም እንዲህ አለ፤ ‹‹ይህም ከሀገሮቹ ሁሉ ተራሮች የሚበልጥ (የተለየ) ከፍ ያለ ተራራ ነው፡፡ በውስጡ ቅዱስ አግዚአብሔር ያድራል፡፡ ይህንን ተራራ የእግዚአብሔር ልጅ ወዶታል፤ አክብሮታልምና፤ ከዓለም ሀገሮች ሁሉ ከተቀደሰች እናቱ ጋር አድሮባታልና፡፡ ከመላእክት ቤት ያድር ዘንድ አልወደደም፤ ቢታንያንም አልመረጠም፡፡ ከተራራው ላይ ባለች ገዳም ቤት ውስጥ አደረ እንጂ፤ ነቢዩ ዳዊት፤ የጽዮንን ተራራ ወደደ፤ በአርያምም መቅደሱን ሠራ እንዳለ፡፡››

‹‹አንተ ተራራ ሆይ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆንህ ጊዜ በኪሩቤልና በሱራፌል መካከል ፍጹም ደስታ ተደረገ፡፡ የመላእክት ሠራዊት ቅዱስ የሆነ ፈጣሪያቸውንና ጌታቸውን ይታዘዙ (ያገለግሉ) ነበር፡፡ አንተ ተራራ ሆይ ያደረብህ ጌታችን ስለሆነ ከተራሮች ሁሉ ከደብረ ሲናም ይልቅ ከፍ ከፍ አልህ፤ ጌታችን በደብረ ሲና ባረፈ ጊዜ ፍጹም ደስታ፣ ታላቅ ብርሃንም በሆነ ጊዜ መቅረብና መመልከት ከሙሴ በቀር የቻለ የለም፡፡ እርሱም ቢሆን ፊቱን ማየት አልቻለም፡፡ ሥጋ ለባሽ ሁሉ እርሱን ዐይቶ በሕይወት መኖር የሚቻለው የለምና፡፡ እኛ ግን አየን፤ ከዚህ ማደሩንም ተረዳን፤ ዳግመኛም ንጽሕት በሆነች በማርያም ዘንድ አየነው፡፡ ቅድስት ከሆነች ከእመቤታችን ማርያም ዘንድ በቤተልሔም ስለ እኛ በተዋሐደው ሥጋ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ያለን እኛን ከቸርነቱና ሰውን ከመውደዱ የተነሣ መጥቶ አዳነን፤ ከዓለም ሁሉ ይልቅ ጣዖትን በማምለክ ሲበድሉም ወደ ግብፅ  ሀገር ወርዶ በእነርሱ ላይ የመለኮትነት ብርሃኑን በማብራት ታላቅ የሆነ ክብሩን ገለጠ››፡፡ (ድርሳነ ማርያም)

ኅዳር ፮ ቀንን የሚነበበው የመጽሐፈ ስንክሳር ክፍል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግመኛም በኋላ ዘመን ሐዋርያትን በደብረ ቁስቋም ሰብስቦ፤ ታቦትንና ቤተ ክርስቲያኑን አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋው ክቡር ደሙን እንደ ሰጣቸው፤ እኛንም ለዚህ ክብር የበቃን እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ ድርሳነ ማርያም መጽሐፍ ትርጉም በመምህር ተስፋ ሚካኤል፤ ፳፻፫ ዓ.ም.