በዚህ ምድር እንደ ክርስቲያን ሆነን ስንኖር የሚገጥሙን ፈተናዎችና አጣብቂኞች ይኖራሉ፡፡ የሚገጥሙንም አንዳንድ ፈተናዎችም ከማስጨነቃቸው የተነሣ በእግዚአብሔር ተአምር እናመልጣቸው ዘንድ እንመኝ ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ፈተናዎቹ ጸጋና ክብር ሊያሳጡንም ጭምር ስለሚችሉ ተአምራት ተደርገውልን ከምናመልጣቸው በሃይማኖትና በምግባር ጸንተን፣ በጾም በጸሎት ታግሠናቸው ድል ብንነሣቸው የበለጠ ክብርን ልናገኝባቸው እንችላለን፡፡ ከጻድቁ ኢዮብ፣ ከሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፣ ከደቀ መዝሙሩ ከቅዱስ ጢሞቴዎስም ተግባራዊ ሕይወት ይህን እንማራለን፡፡
እግዚአብሔርን ለማመን በቤቱ ጸንቶ ለመኖር ለሚገጥሙን የዚህ ዓለም መሰናክሎች ሁል ጊዜ ተአምራትን መሻት እግዚአብሔር የሚወደው መንገድ አይደለም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌ በሚያስተምርበት ወራት ጻፎችና ፈሪሳውያን ወደ እርሱ ቀርበው ‹‹መምህር ሆይ ከአንተ ምልክት እንድናይ እንወዳለን›› አሉት፡፡ እርሱ ግን መልሶ ‹‹ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ ዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፤ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሓ ገብተዋልና፤ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡ ንግሥተ አዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፡፡ አነሆም ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ›› አላቸው፡፡ (ማቴ.፲፪፥፴፰‐፵፪)
ምልክትን (ተአምርን) የሚፈልግ ትውልድ ለምን ክፉና አመንዝራ ተባለ? ‹ክፉ› የተባለው እምነቱን በተአምራት ላይ ስላስደገፈና ስለሚያስደግፍ ነው፡፡ ‹አመንዝራ› የተባለበትም ምክንያት አመንዝራ ሰው ነገሩ አንድ ሲሆን ዕለት ዕለት ሴት (ወንድ) ሊለወጥለት እንዲወድ አይሁድና የአይሁድን መንገድ የሚከተሉ ሰዎችም ዕለት ዕለት ትምህርትና ተአምራት ሊለወጥላቸው ይወዳሉና ነው፡፡