ብርሃነ ትንሣኤ

ዓለም በጨለማ ተውጣና የሰው ዘር በሙሉ በኃጢአት ቁራኝነት ተይዞ የዲያብሎስ ባሪያ በነበረበት ዘመን ብርሃናተ ዓለም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ሞትን አጥፍቶ ብርሃንን ለገለጠበት ለትንሣኤው አድርሶናል ክብር ምስጋና ይገባዋል!!!

ይህንን ድንቅ ጥበብም ቅዱስ መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ ‹‹በሰንበትም ማታ ለእሑድ አጥቢያ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ። እነሆም፥ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወረዶአልና፤ ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋዩን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ፥ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። እርሱንም ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁ ታወኩ፤ እንደ በድንም ሆኑ። መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፤ “እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድምትሹ አውቃለሁና፡፡ እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም፤ ነገር ግን ተቀብሮበት የነበረውን ቦታ እዩ። ፈጥናችሁም ሂዱና ‘ከሙታን ተነሣ፥ እነሆ፥ ወደ ገሊላ ይቀድማችኋል፤ በዚያም ታዩታላችሁ’ ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሩአቸው፤  እነሆም፥ ነገርኋችሁ።”

በፍርሃትና በታላቅ ደስታም ፈጥነው ከመቃብር ሄዱ፥ ለደቀ መዛሙርቱም ይነግሩአቸው ዘንድ  ሮጡ።  እነሆም፥ ጌታ ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው፤ እነርሱም ቀርበው እግሩን ይዘው ሰገዱለት። ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፥ “አትፍሩ፤ ሄዳችሁ ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፥ በዚያም ያዩኛል፡፡” …. ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ግን ኢየሱስ ወዳዘዛቸው ተራራ ወደ ገሊላ ሄዱ፥ ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት››  (ማቴ.፳፰፥፩-፲፯)

መልካም ዘመነ ትንሣኤ!!!