ነገረ ትንሣኤ

እንኳን አደረሳችሁ!!!

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ሚያዚያ ፲፩፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት ሰነበታችሁ? እንኳን አደረሳችሁ! የትንሣኤ በዓል እንዴት እያከበራችሁ ነው? ልጆች! አሁን ያላችሁበት ወቅት የዓመቱ የትምህርት ዘመን መገባደጃ ወቅት  ነው! መምህራን የሚሰጧችሁን የቤት ሥራ በደንብ አድርጋችሁ መሥራት አለባችሁ! መቼም በርተታችሁ ስታጠኑ ያልገባችሁን ስተጠይቁ እንደ ነበር ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በዓል (ዓመት በዓል) ነው ብላችሁ ከትምህርታችሁ እንዳትዘነጉ  ሁል ጊዜ ደጋግመን የምንነግራችሁን አስታውስ! ዕውቀት ማለት በተግባር መተርጎም መሆኑን እንዳትዘነጉ! መልካም! ልጆች! ዛሬ ስለ ጌታችንን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ እንማራለን፡፡ ከዚያ በፊት ግን ከትንሣኤ በዓል ጀምሮ እስከ በዓለ ሃምሣ ድረስ ስንገናኝ የምንለዋወጠውን ሰላምታ እናስቀድም!

  • ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን                                    ክርስቶስ ከሙታን ተነሣ
  • በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን                                      በታላቅ ኃይልና ሥልጣን
  • አሰሮ ለሰይጣን                                                       ሰይጣንን አሠረው
  • አግዐዞ ለአዳም                                                       አዳምን ነጻ አወጣው
  • ሰላም                                                                             ሰላም
  • እምይእዜሰ                                                             ከእንግዲህ
  • ኮነ                                                                                  ሆነ
  • ፍስሐ ወሰላም                                                        ደስታና ሰላም

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ‘ትንሣኤ’ ማለት ‘መነሣት’ ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ከኃጢአት ነጻ ሊያጣ በፈቃዱ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ፤ ጌታችንን ቅዱስ ዮሴፍና ቅዱስ ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው በክብር ጎልጎታ በተባለ ማንም ባልተቀበረበት በአዲስ መቃብር በክብር አሳረፉት፤ ለሦስት መዓልትና ለሦስት ሌሊት በመቃብር ውስጥ አደረ፤ በሦስተኛውም ቀን በገዛ ሥልጣኑ በዝግ መቃብር ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፤  የጌታችንን መቃብር ሽቱ ለመቀባት  ሄደው ለነበሩ ለነ መግደላዊት ማርያም የእግዚአብሔር መልአክ እንዲህ ሲል ትንሣኤውን አበሠራቸው፡፡ ‹‹…እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁ፤ እንደ ተናገረ ተነሥቷልና በዚህ የለም፤ የተኛበትን ሥፍራ ኑና እዩ፡፡›› (ማቴ.፳፰፥፭)

ቀድሞ ጌታችን መከራ እንደሚቀበል፣ በመስቀል ላይ እንደሚሰቀል ነግሯቸው ስለነበር ቅዱሳን መላእክም ‹‹እንደተናገረ ተነሥቷል›› ብለው ትንሣኤውን አበሠሯቸው፤ ጌታችን አስቀድሞ እንዲህ ብሎ ነበር፤ ‹‹.. የሰው ልጅም ለካህናት አለቆችና ለጻፎች አልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል፤ ለሕዝብም አሳልፈው ይሰጡታል፤ ይዘብቱበታል፤ ይተፉበታልም፤ ይገርፉትማል፤ ይገድሉትማል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል፡፡›› (ማር.፱፥፴፫)  በቃሉም መሠረት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሦስተኛው ቀን ሞትን ድል አርጎ ተነሣ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዓለ ትንሣኤ ትንሣኤያችን የተበሠረበት ታላቅ በዓል ነው! ሞትን ድል አድርጎ በመነሣት በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አበሠረን፤ እኛም ለማንም በማይቀረው የሥጋ ሞት የምንወሰድ ብንሆንም ሕያዋን ሆነን ለመኖር የሚያስችለን የክብር ትንሣኤ እንዳለን መድኃኒታችን አብነት ሆኖናል፤ ይህ በዓል የማይሞተው ስለእኛ  ሞቶ የሞትን ቀንበር ሠብሮ ትንሣኤያችንን ያበሠረበት የደስታ ዕለት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዲያቢሎስን ድል አድርጎልን፣ በእናታችን በሔዋንና በአባታችን አዳም በደል በሱራፌል የእሳት ሰይፍ የታጠረች ገነትን ከድንግል ማርያም የተወለደው የአብ ኅሊናው፣ የአብ ጥበቡ፣ የአብ ኃይሉ፣ ቀኝ እጁ የሆነ እግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሣኤው ትንሣኤያችንን አብሥሮ የሱራፌልን የእሳት ሰይፍ አስጥሎ ገነትን ከፈተልን፡፡ ትንሣኤው ትንሣኤያችን ነው፤ይህንን በዓል ውለታ ፍቅሩን እያሰብን፣ በምስጋናና በደስታ ሆነን እናከብረዋለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዓሉን ስናከብር ለሰዎች መልካም እያደረግን ለእኛ ሲል መከራ የተቀበለልንን የጌታችንን መከራውን እንዲሁም ደግሞ ትንሣኤውን እያዘከርን በምሥጋና ሊሆን ይገባል፤ ሌላው ደግሞ ልጆች ትንሣኤ ማለት መነሣት እንደሆነ በመግቢያችን ላይ ገልጻናል፤ ታዲያ መነሣት ስንል ከሞት ብቻ አይደለም፤ አባቶቻችን በትምህርታቸው የልብ መነሣት ነው እንዲሉ! በስንፍና፣ በክፉ ሥራ የተያዘው እኛነታችን ወደ ጽድቅ፣ ወደ መልካም፣ ወደ ማስተወዋል ሊነሣ ያስፈልጋል፤ ደክመን ከነበረ በርትተን፣ ሰንፈን ከነበረ ጎብዘን፣ ቸልተኞች ከነበርን ታታሪዎች ለመሆን ከልባችን መነሣት እንደሚገባን እንማራለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ሌላው ልብ ማለት ያለብን በጾሙ ወራት የነበረን መንፈሳዊ ተግባር መቀጠል አለባቸው፤ መጸለይ፣ ካለን ለሌላቸው እናካፍል የነበረውን አሁንም ማድረግ አለብን፤የጌታችን ትንሣኤ ለ ፶፻፭፻ (አምስት ሺህ አምስት መቶ) ዘመን በሲዖል ባርነት ለነበሩ ሰዎች ተስፋቸው ተቀጥሎ ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገሩበት ነው፤ በጌታችን ሞት ሞታችን ተገደለ፤ በጌታችን ትንሣኤ ግን ትንሣኤያችን ተበሠረ፤ ባርነት ተወግዶ ነጻነታችን ታወጀ፤ ፋሲካችን ክርስቶስ ተሰውቶልን ሰላማችን ታወጀ፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በሕይወታችን በማንኛውም ነገር ተስፋ መቁረጥ የለብንም፤ ከሰሙነ ሕማማት በኋላ ትነሣኤን እንዳከበርን በሕይወታችንም ነገ ከዛሬ የተሸለ እንደሚሆን ልናውቅ ይገባል! መከራም ያልፋል፤ የጨለመውም ይነጋል፤ ከድካም በኋላ ዕረፍት፣ ካቀበቱና ከዳገቱ በስተጀርባ ለምለም መስክ አለ! መልካም ትንሣኤ ይሁንላችሁ፡፡

አምላካችን ፈጣሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከበዓለ ትንሣኤው ረድኤት በረከቱን ይክፈለን (ይስጠን) አሜን!!! ቸር ይግጠመን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!