የትንሣኤ 2 መዝሙርና ምንባባት

የትንሣኤ 2 መዝሙር (ከመጽሐፈ ዚቅ)
ትትፌሣሕ ሰማይ ወትታኃሠይ ምድር ወይንፍሑ ቀርነ መሠረታተ ሕምዝ ወይጸውዑ አድባር ወአውግር ወኩሉ ዕፀወ ገዳም ወዮምሰ ዐባይ ፍሥሐ በሰማያት ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐፂባ በደመ ክርስቶስ፡፡

ትርጉም: ሰማይ ይደሰታል ምድርም ትደሰታለች የምድር መሠረቶችም ቀንደ መለከትን ይንፉ /ይደሰቱ/ ተራሮችና ኮረብቶችም /ነገሥታት መኳንንት/ ይጩኹ/ይደሰቱ/ የምድረ በዳ እንጨቶችም ይጩኹ ዛሬ በሰማያት ታላቅ ደስታ ሆነ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካን/ደስታን/ ታደርጋለች።

 
 
መልዕክታት
1ቆሮ. 15፥20-41
አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአል፡፡ በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአልና፥ በሁለተኛው ሰው ትንሳኤ ሙታን ሆነ፡፡ ሁሉ በአዳም እንደሚሞት እንዲሁ በክርስቶስ ሁሉ ሕያዋን ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን ሰው ሁሉ በየሥርዐቱ ይነሣል፤ በመጀመሪያ ከሙታን የተነሣ ክርስቶስ ነው፤ ከዚያ በኋላ በክርስቶስ ያመኑ እርሱ በሚመጣበት ጊዜ ይነሣሉ፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
 

1ጴጥ.1፥1-13
ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ ከጴጥሮስ፥ በጳንጦስ፥ በገላትያና በቀጰዶቅያ፥ በእስያና በቢታንያ ሀገሮች ለተበተኑ ስደተኞች፥ እግዚአብሔር አስቀድሞ እንዳወቃቸው፥ በመንፈስ ቅዱስም እንደሚቀደሱ፥ ይታዘዙና በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ይረጩ ዘንድ፥ ለተመረጡት፥ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
ግብረ ሐዋርያት
ሐዋ.2፥22-37
እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ነገር ስሙ፤ እንደምታውቁት በመካከላችሁ እግዚአብሔር በእጁ ባደረገው በከሃሊነቱ በተአምራቱና በድንቅ ሥራዎቹ እግዚአብሔር የገለጠላችሁን ሰው የናዝሬቱን ኢየሱስን ስሙ፡፡ እርሱንም በተወሰነው በእግዚአብሔር ምክርና በቀደመው ዕውቀቱ እናንተ አሳልፋችሁ በኃጥኣን እጅ ሰጣችሁት፤ ሰቅላችሁም ገደላችሁት፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
 
ምስባክ
 

ዛቲ ዕለት እንተ ገብረ እግዚአብሔር
ንዑ ንትፌሣሕ ወንትሐሠይ ባቲ
ኦ እግዚኦ አድኅንሶ

 

ትርጉም፦

ይህች እግዚአብሔር የፈጠራት /የሠራት/ ቀን ናት
ፈጽሞ ተድላ ደስታን እናድርግባት
አቤቱ አድነን

ወንጌል
ዮሐ.20፥1-19 ከሳምንቱም በመጀመሪያዉ ቀን ማርያም መግደላዊት በማለዳ ገና ጨለማ ሳለ ወደ መቃብር መጣች፤ ድንጋዩንም ከመቃብሩ አፍ ተነሥቶ አገኘችው፡፡ ፈጥናም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ጌታተን ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደዚያ ወደ ሌላዉ ደቀ መዝሙር መጥታ፥ “ጌታዬን ከመቅብር ወስደውታል፤ ወዴትም እንደ ወሰዱት አላውቅም” አለቻቸው፡፡ (ተጨማሪ ያንብቡ)
ቅዳሴ
ቅዳሴ ዘዲዮስቆሮስ

ሰበር ዜና ከአሰቦት ገዳም

መጋቢት 12/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የአብነት ተማሪው በታጣቂዎች ተገደለ

በምዕራብ ሐረርጌ ሜኤሶ ወረዳ በአሰቦት ሥላሴና አባ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ ገዳም የአብነት ተማሪ የሆነው የ7 ዓመቱ ሕፃን ናታን አንበስ ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በ3 ጥይት ተመትቶ መገደሉን የገዳሙ ዋና መጋቢና ምክትል አበምኔት አባ ዘወልደ ማርያም ገለጹ፡፡ ከአባ ሳሙኤል ገዳም በተወሰኑ ሜትሮች ርቀት ላይ ከእናቱ ጋር ወደ ገዳሙ በመውጣት ላይ እያለ ከእናቱ እጅ ቀምተው በመውሰድ ፊት ለፊቷ በሦስት ጥይት ገድለውት ሊያመልጡ ችለዋል፡፡ በእናትየው ጩኸትና በጥይት ድምጽ የተደናገጡት መነኮሳት ገዳዮቹን ለመያዝ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

 

የገዳሙ መነኮሳት እንደገለጹት ጉዳዩን ለፖሊስ በስልክ ያሳወቁ ሲሆን ፖሊስ “መኪና አግኝተን እስክንመጣ ድረስ ሟቹን  ቅበሩት” በማለታቸው ከቀኑ 8፡00 አካባቢ ሊቀበር ችሏል፡፡ ባቲ በተባለው አካባቢ በአሰቦት ቅድስት ከሥላሴ ገዳም ጀርባ ከሚገኘው አካባቢ ታጣቂ አርብቶ አደሮች ተሰባስበው ወደ ገዳሙ በመቃረብ ላይ መሆናቸውንና መነኮሳቱ ስጋት ላይ እንደሚገኙ ጨምረው ገልጸውልናል፡፡

 

መጋቢት 1 ቀን ባቀረብነው ዘገባ መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች እሳቱን በሚያጠፉት ምእመናን ላይ ተኩስ ከፍተው እንደነበርና የፌደራል ፖሊስ አባላት ምላሽ ሰጥተው ከአካባቢው እንዳራቋቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የዝቋላ ገዳም እንዴት አደረ?

መጋቢት 12/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

 

በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን ላይ ከቅዳሜ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ቃጠሎ እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ የዘለቀ ሲሆን ሌሊቱን ግን በሰላም እንዳደረና የመርገብ ሁኔታ እየታየበት መሆኑን በስፍራው የሚገኙ ምእመናን ገለጹ፡፡ ቃጠሎው ቢበርድም የተዳፈነው ፍም ነፋሱ እያራገበZeqwala 4ው በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ጭስ እየታየ እንደሆነ በተለይም የቅዱሳን ከተማ የተሰኘው የአባቶች የጸሎት ሥፍራ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ጪስ በመጨስ ላይ መሆኑን በስጋት በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ቃጠሎው ዳግም ካገረሸ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ሊያመራ እንደሚችል መነኮሳቱ ይናገራሉ፡፡

 

ከሥፍራው በደረሰን መረጃ መሠረት ምእመናን የመዳከም ሁኔታ የሚታይባቸው ሲሆን የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ሌሎችም ምእመናን ወደየመጡበት በመመለስ ላይ ናቸው፡፡ የፌደራል ፓሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ከቀሩት ምእመናን ጋር በመሆን የሚጨሰውን ፍም በማጥፋት ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ወደ ዝቋላ ገዳም ከተለያዩ አቅጣጫዎች ምእመናን እየሔዱ ሲሆን በሥፍራው የሚገኙ ምእመናን አሁንም ተጨማሪ የሰው ኀይል እንዲደርስላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡

የመነኮሳቱ የድረሱልን ጥሪ ከዝቋላ ገዳም

መጋቢት 11/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ቃጠሎውን መቆጣጠር አልተቻለም

ከገዳሙ ጸሐፊ የደረሰን መረጃ፡-

ቃጠሎው ከአቅም በላይ ሆኗል፡፡ መነኮሳቱና ምእመናን በመዳከም ላይ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር በረከትን የምትሹ ምእመናን ድረሱልን፡፡ እሳቱ በአንድ አቅጣጫ ጠፋ ሲባል በሌላ በኩል እየተነሣ ተሰቃይተናል፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመገሥገሥ ላይ ስለሆነ የቅዱስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ ማኅበራት፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና የኮሌጅ ተማሪዎች፣ እንዲሁም ምእመናንና ወጣቶች፣ አቅም ያለው ሁሉ እሳቱን ለማጥፋት በተቻላችሁ አቅም ድረሱልን፡፡ መምጣት የማትችሉ በጸሎት አትለዩን በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

 

የዝቋላ ደን ቃጠሎ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገለጠ፡፡

መጋቢት 11/2004 ዓ.ም

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን ቃጠሎ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገለጠ፡፡

በቦታው የተገኙት የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም እንደገለጡልን በቦታው በርካታ ምእመናን ተገኝተው እሳቱን ለማጥፋት ጥረት ቢያደርጉም በአስቸጋሪው የአየር ጠባይ የተነሣ ፍህሙ እየተነሳ እንደገና እንዲያገረሽ ስለሚያደርገው ከፍ ያለ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ከመንገዱ አስቸጋሪነት እና ከፀሐዩ ግለት አንፃር ከእሳቱ ቃጠሎ ጋር ለሚታገሉ ምእመናንም  የጥም ማስታገሻ የሚሆን ውሃ በመኪና ለማድረስ እንዳልተቻለ ከስፍራው የደወሉልን ምእመናን ገልጠውልናል፡፡

በአሁኑ ወቅት የእሳት አደጋው አርብ ረቡዕ በሚባለው ቦታ እየነደደ እንደሆነና የገዳሙን ደን የምሥራቁን ክፍል እየጨረሰ ወደ ደቡብ አቅጣጫ እየዞረ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በአካባቢው ያለው ማኅበረሰብ ትብብር አነስተኛ እንደሆነባቸው ያልሸሸጉት ምእመናኑ፣ ለእርዳታ የሚመጡ ምእመናንም በተቻላቸው አቅም መጥረቢያ፣ አካፋና መቆፈሪያ ይዘው ቢመጡና ምእመናኑም እሳቱን ለማጥፋት አቅም ያላቸው ቢሆኑ ይመረጣል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በቅርብ ሰዓት በደረሰን መረጃ መሠረት፣ ከሌሊቱ 8፡00 አካባቢ እሳት ወደሚነድበት አካባቢ ለቅኝት የተጓዙ ምእመናን መሬት ላይ ያለው ፍሕም ነፋሱ በመራው አቅጣጫ እየተነሳ እንደሚያቀጣጥል መመልከታቸውንና ከቦታው አስቸጋሪነት አንፃር ምንም ማድረግ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

ለእርዳታ የተጓዘውን ምእመን የማስተናገድ ሸክም በገዳሙ ጫንቃ ላይ እንደወደቀ መነኮሳቱ የተናገሩ ሲሆን፣ ከጊዜ በኋላ ከዐቅም በላይ ሊሆን ስለሚችል ስንቅ በማቅረብ በኩልም ቢሆን ሊተባበሩ የሚችሉ ምእመናንን እርዳታ እንደሚሹ ገልጠዋል፡፡

አምላክ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በይቅርታው ይታደገን!!!

በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የደን ቃጠሎ በባሰ ሁኔታ ላይ ይገኛል!

መጋቢት 10/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ


እሳት ወይስ መአት?


በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የደን ቃጠሎ በባሰ ሁኔታ ይገኛል፡፡ ቅዳሜ መጋቢት 8/2004 ዓ.ም. ከቀኑ 6፡00 በኋላ ልዩ ስሙ አዱላላ ከሚባለው አቅጣጫ የተቀሰቀሰው ቃጠሎ በመነኮሳትና በአካባቢው ምእመናን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት  እያደረጉ እንደሚገኙና ከደብረ ዘይት የአየር ኀይል አባላት ትላንት ምሽት መጥተው እገዛ ለማድረግ ጥረት ማድረጋቸውን የገዳሙ ጸሐፊ አባ ወ/ሩፋኤል ቢገልጹም መፍትሔ እንዳልተገኘ ታውቋል፡፡

 

የቃጠሎው መንስኤ ለማወቅ ያልተቻለ ሲሆን “የቅዱሳን ከተማ” የተሰኘው የአባቶች የጸሎት ሥፍራ በከፍተኛ ሁኔታ በመቃጠል ላይ እንደሚገኝና በሥፍራው ውኃ የሌለ በመሆኑ ቃጠሎውን ለማጥፋት አፈሩን በመቆፈርና በመበተን እንጨቶችን በመቁረጥና በቅጠል በማጥፋት ርብርቡ የቀጠለ ቢሆንም ቃጠሎውን መግታት እንዳልተቻለ አባ ወልደ ሩፋኤል ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ወደ ጸበሉ ቦታ እንዳይደርስ ጥረት እየተደረገ ሲሆን ምእመናን ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ገዳሙ በመሔድ ቃጠሎውን ለማጥፋት እየተረባረቡ ይገኛሉ፡፡ የገዳሙ ጸሐፊ አባ ወልደ ሩፋኤል ቃጠሎው ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ መጠኑን ለመግለጽ መቸገራቸውንና ለመንግሥት አካላትና ለምእመናን የድረሱልን ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ተመሳሳይ ቃጠሎ በተለያዩ ቤተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ በመሆኑ “እሳት ወይስ መአት?! በማለት በጭንቀትና በስጋት ምእመናን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

 

በ2000 ዓ.ም. በዚሁ ገዳም ቃጠሎ ተከስቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በቅርቡም በጎንደር የሰለስቱ ምእት መጻሕፍተ መነኮሳት ጉባኤ ቤት፣ እንዲሁም የጥንታዊው የሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ ትምህርት ቤት ቃጠሎ የደረሰባቸው ሲሆን በምዕራብ ሐረርጌ የሚገኘው የአሰቦት ገዳም ደን ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱም ይታወቃል፡፡

 

የዝቋላ የሰኞ መጋቢት 10 ቀን 2004 ዓ.ም. ውሎ

ቃጠሎው እጅግ አሳሳቢ  ሆኗል፡፡


ከጧት ጀምሮ ምእመናን ከደብረ ዘይት፣ ከአዲስ አበባ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ በማኅበረ ቅዱሳን የሚመራው የዩኒቨርሲቲዎች የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ቃጠሎውን ለማጥፋት ቦታው ድረስ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከገዳሙ በደረሰን መረጃ መሠረት እስከ ቀኑ 12፡00 ሰዓት ድረስ ቃጠሎው በፀሐይና በንፋስ በመታገዝ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ ይገኛል፡፡ መነኮሳቱ ለኦሮሚያ ፖሊስ፣ ለፌደራል ፖሊስና ለአየር ኀይል እንዲሁም ለምእመናን የድረሱልን ጥሪ በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡ በተለይም ቦታው እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ውኃ ማግኘት ባለመቻሉ የደኑን ውድመት እያባባሰው ስለሚገኝ ውኃ የሚያመላልሱ ቦቴ መኪናዎች ያሏቸው ምእመናን ውኃ በማመላለስ እንዲደርሱላቸው በመማጸን ላይ ናቸው፡፡

 

ከተለያዩ አካባቢዎች የተንቀሳቀሱት ምእመናን ከአስቸጋሪ ጉዞ በኋላ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ላይ ቦታው የደረሰ ሲሆን ለማጥፋት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ዜና እስካጠናቀርንበት 12፡00 ሰዓት ድረስ ቃጠሎው እንዳልጠፋና ከሌላ አቅጣጫ ሌላ አዲስ ቃጠሎ መቀስቀሱን በቦታው ከሚገኙ ምእመናን ለመረዳት ችለናል፡፡ ቃጠሎው በዚሁ ከቀጠለ ከፍተኛ የደን ሀብት ያለበት ቦታ መያዙ እንደማይቀር ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

 

በቃጠሎ ጉዳት የደረሰባቸው ምእመናን እንደሚገኙ ከቦታው የደረሰን መረጃ የሚያመለክት ሲሆን በከፍተኛ ጥምና ረሃብ ላይ ለሚገኙ ምእመናን ውኃና ምግብ እንደሚያስፈልጋቸው ጭምር ገልጸዋል፡፡

የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ደን እየተቃጠለ ነው፤ የምእመናንን እገዛ ይሻል፡፡

መጋቢት 10/2004 ዓ.ም.


በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ


ቅዳሜ መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 በኋላ የጀመረው የገዳሙ ቃጠሎ እየተባባሰ እንደሆነ የገለጹልን ያነጋገርናቸው የገዳሙ መነኮሳት እሳቱን ለማጥፋት የምእመናንን እርዳታ እንደሚሻ አሳስበዋል፡፡

 

አያይዘውም ለእርዳታ የሚመጡ ምእመናን ስንቅ እንዲይዙና በውኃ ጥም እንዳይቸገሩ ከቻሉ ውኃ እንዲይዙ፤ ቦቴ መኪና ያላቸውም እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ምእመናን ከደብረ ዘይትና አዲስ አበባ ዙሪያ ወደ ገዳሙ ለእርዳታ እየተጓዙ እንደሆነ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

ዝርዝር ሁኔታውን በቀጣዩ እናቀርባለን፡፡

አምላከ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በምሕረቱ ይታረቀን፡፡

ቦጅ ትጮሀለች!

መጋቢት 10/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

ኘሮቴስታንቲዝም በምዕራቡ ዓለም ተጸንሶ ተወልዶና አድጐ የጐለበተ ከካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ያፈነገጠ የእምነት ተቋም ነው፡፡ ተወልዶ ባደገበት ሀገር ይዞታውን አንሰራፍቶ ለጊዜው የዘለቀው ኘሮቴስታንቲዝም በሀገሩ ባይተዋር ሲሆን “ጅብ ባለወቁት ሀገር ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” እንደሚባለው ወደ ድሃ ሀገሮች በመዝመት ባንድ እጁ ዳቦ በአንድ እጁ እርካሽ እምነቱን ይዞ ገባ፡፡ በዚህ እኩይ ተልዕኰ የተወረሩ በርካታ የአፍሪካ ሀገሮች ባሕላቸውን ትተው፣ ቋንቋቸውን እረስተው ዘመን አመጣሽ የሆነውን አዲስ እምነት ለመቀበል ተገደዋል፡፡

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}bogi{/gallery}

ሀገራችን ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስጠብቃ በጠላት እጅ ሳትወድቅ አንድነቷ ተከብሮ የኖረች ስሟ በቅዱስ መጽሐፍ ተደጋግሞ የተነሣ ቅድስት ሀገር ናት፡፡ ግማደ መስቀሉ ያረፈባት ታቦተ ጽዮን የከተመባት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የታነጹባት ያለመታከት ስመ እግዚአብሔር የሚጠራባት ልዩ ሀገር ናት፡፡ በባእዳን እጅ አለመውደቋ በቀኝ ግዥ አለመያዟ የእግር እሳት የሆነባቸው ምዕራባውያን ድንበሯን ጥሰው መግባት ባይችሉም የአእምሮ ቅኝ ግዛታቸውን አላቋረጡም፡፡

 

በዚች ሀገር ውስጥ ይህ ዘመቻ በስፋት ከሚካሔድባቸው ቦታዎች አንዱ ሰፊ የሆነው የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡

 

ቦጅ ቅድስት ማርያም ጠላቶቿን ስታስታውስ

የፕሮቴስታንቱን ተፅዕኖ ለመግታት ማኅበረ ቅዱሳን ባዘጋጀው የካህናት ሥልጠና የካቲት 17 ቀን 2004ዓ.ም ረፋዱ ላይ በቤተ ክርስቲያኗ ቅጽር ግቢ ስንገኝ ማንም ሰውbogi 1 አልነበረም፡፡ በቅጽሩ ጥግ ለጥግ ያረጁ የመካነ መቃብር ሐውልቶች ይታያሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ፊት ለፊት በስተቀኝ በኩል ፈንጠር ብለው በክብር የተሠሩ አጥራቸው የተከበረ የቄስ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ ዘመስቀል /1865-1905/፣ የአቶ ዳንኤል ዲባባ /1966-1904/ እና የአቶ ገብረ ኢየሱስ ተስፋዬ /12877-1925ዓ.ም./ መካነ መቃብር ይታያል፡፡ እነዚህ ሐውልቶች ለኘሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ባለ ውለታ ለሆኑት ሦስት ግለሰቦች ለመታሰቢያ እንዲሆን የተሠራ ሐውልት እንደሆነ ነዋሪዎች አጫውተውናል፡፡ በተለይ ከሦስቱ ሰዎች አንዱ ቄስ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ በርካታ ካሕናትን አስኮብልሎ የእኛ ቤተ ክርቲያን እንድትዘጋ ስላደረገ ኘሮቴስታንቱ ስሙን ይዘክሩታል፡፡ በዚች ጠባብ ከተማ 130 ዓመታት ያስቆጠረች የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ትገኛለች፡፡ በከተማዋ ያደረግነው ቆይታ ከሀገረ ስብከቱ ስራ አስኪያጅ ከመጋቤ ሀዲስ ሀዲስ ዓለማየሁ እና ከወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት ምሥጢሩ ዘለቀ ጋር ነበርን፡፡

 

በቦጂ ድርመጂ ወረዳ ዐሥር አድባራት ይገኛሉ፡፡ ከሕዝቡ በመቶኛ ዘጠና አምስት በመቶ የኘሮቴስታንት እምነት ተከታዮች እንደሆኑ ይገመታል፡፡ በጥንታዊነቷ የምትታወቀው የቦጂ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን አንድ መቶ ሠላሳኛ ዓመቷን የምታከብረው የፊታችን ግንቦት 1 ቀን 2004 ዓ.ም ነው፡፡

 

bogi 2ሊቀ ካህናት ምሥጢሩ ስለ ቦጂ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ታሪክ በአጭሩ ነግረውናል፡፡ እኛም እድሜ ጠገብነቷ አስደምሞን ልቡናችን በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ መዋለል ዓይኖቻችን በሕንፃዋ መንቀዋለል ጀመሩ፡፡ ከወፍ ድምጽ በቀር ምንም የማይሰማባት ቤተ ክርስቲያን ናት ማህሌቱ፣ቅዳሴው፣ጸሎተ እጣኑ ከተቋረጠ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይህቺ ደብር የወላድ መካን የሆነች ካሕናቷ በኘሮቴስታንት ሰባኪያን የተወሰዱባት ቤተ ክርቲያን ናት፡፡ በልጆቿ መጥፋት ያዘነችው ቦጂ ቅድስት ማርያም ልጆቼን! እያለች ትጮኸለች፡፡

 

ተሐድሶ በዚያን ዘመንም

ከቦታው ያገኘነው ታሪክ እንደሚያስረዳው በ1890 ዓ.ም ከሲዊዲን ሀገር የመጡ የኘሮቴስታንት እምነት ሰባኪዎች ፊት ለፊት ከሚታየው ከርከር ተራራ ጸሎት ቤት ከፈቱ፡፡ እነዚህ ነጭ ሰባኪያን የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት የእኛን ቤተ ክርስቲያን ካሕናት መለወጥ ነበር፡፡ ኘሮቴስታንቶች በኢትዮጵያ ያደረጉት ተልእኮ መሠረት የተጣለው በዚህች ከተማ ነው፡፡ የመካነ ኢየሱስ ምዕራብ ሲኖዶስ ጽሕፈት ቤት የሚገኘው በዚህች ከተማ ነው፡፡

 

በቤተ ክርስቲያኗ ያኔ በርካታ ካህናትና ዲያቆናትና ነበሩ፡፡ ከካህናቱ መካከል ከኤርትራ ሀገር የመጣ ቄስ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ የሚባል “ካህን” ነበር፡፡ መናፍቃኑ ይህን ቄስ ቀስ በቀስ ሰብከው ከለወጡት በኋላ አሠልጥነው የውስጥ ዘመቻቸውን አቀጣጠሉ፡፡

 

ቄስ ገብረ ኤዎስጣቴዎስ ለበርካታ ጊዜያት ራሱን ሰውሮ ጠዋት በእኛ ደብር እየቀደሰ ከሰዓት በኃላ በመናፍቃኑ አዳራሽ እየተገኘ የመናፍቃኑን ተልእኮ ይፈጽማል፡፡ /ምን አልባት ተሐድሶዎቹ የዚያን ጊዜም እንቅስቃሴያቸውን ጀምረው ይሆን?/ ይህ ቄስ ለ15 ዓመታት በዚህች ደብር ሲያገለግል የነበረ ሰው ነው፡፡ በኋላ ወደ አምስት የሚሆኑ ካህናትን ሰብኮ ወደ መናፍቃኑ አንድነት ቀላቀላቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያኗ በካህናት እጥረት አገልግሎቷ ታጐለ፡፡ አሁን ቤተ ክርስቲያኗ  ልጆቿ የሉም፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ምን ያህል እንደሆኑ ትክክለኛ ቁጥራቸውን መናገር ባይቻልም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች 14 የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አባወራዎች አብዛኛዎቹ ሚስቶቻቸው ኘሮቴስታንት የሆኑባቸው አባቶች ናቸው፡፡ በሃይማኖት ተለያይቶ በአንድ ቤት መኖር ከባድ ቢሆንም አማራጭ ስለጠፋ አብረው ለመኖር እንደተገደዱ አባወራዎቹ ይናገራሉ፡፡

 

ሚስቶቻቸው በኘሮቴስታንቶች ተሰብከው ከተነጠቁባቸው አባወራዎች መካከል አቶ ተሰማ ደበበ አንዱ ናቸው፡፡ በኦሮምኛ የነገሩንን ወደ አማርኛ እነዲህ ተርጉመነዋል፡፡ “ ወደ ኘሮቴስታንት እምነት ከሔዱት ሰዎች በጣም በርካታ ቁጥር ያላቸው ከዚህች ቤተ ክርስቲያን የወጡ ምእመናን ናቸው፡፡ ይህቺ ቤተ ክርቲያን ወጣት የሚባል ተተኪ የላትም፤ ሚስቶቻችን ወደ ቀድሞ የኦርቶዶክስ እምነታቸው እንዲመለሱ ጥረት ብናደርግም እሺ ሊሉን አልቻሉም፡፡ አሁንም የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን፤ ማን ያውቃል አንድ ቀን ሊመለሱ ይችላሉ” በማለት ተስፋቸውን ነግረውናል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኗ ለ4 ዓመታት ያህል ተዘግታ መኖሯን የገለጠልን አንድ ዲያቆን ከ1982 ጀምሮ ዲቁና ተቀብሎ እያገለገለ ቢሆንም ካለበት bogi 4የመንግሥት ሥራ ጋር አጣጥሞ አገልግሎቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳልቻለ ገልጦልናል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎችም ሥራ ለማግኘትና በኘሮጀክት ታቅፈው የእለት ኑሮአቸውን ለመግፋት ሳይወዱ በግድ ወደ ኘሮቴስታንት እምነት ለመሔድ እንደሚገደዱ ነዋሪዎች ይገልጣሉ፡፡

 

በአሁኑ ሰዓት የቤተ ክርስትያኗን ቁልፍ ይዞ ካህንም ፣ዲያቆንም፣ ሰንበት ተመማሪም፣ አስተማሪም፤ ጠባቂም ሆኖ የሚያገለግለው ዲያቆን አበበ ኅሩይ በኘሮቴስታንቱ የደረሰባቸውን  ከፍተኛ ጉዳት እንዲህ ይናገራል፡፡ “እኔ እንደማስታውሰው በ1988 ዓ.ም የተወሰኑ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች ነበሩ፡፡ በዚያን ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያስተምር ሰባኪ ስላልነበረን የነበሩት ምእመናን በአንድ ላይ ተሟጥጠው ወደ ኘሮቴስታንቱ የጸሎት ቤት ገቡ፡፡ ሌላው ይቅርና የቤተክርስቲያኗ ቁልፍ ያዥ የነበረው ቄስ አዳሜ ገብረ ወልድ በጠዋት መጥቶ ‘በል ይህን የቤተ ክርስቲያን ቁልፍ ተረከበኝ ወደ ኘሮቴስታን የጸሎት ቤት መሔዴ ነው’ ብሎ ጥሎልኝ ሔደ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቁልፉን ይዤዋለሁ፡፡ በአጥቢያዋ የሚኖሩ 14 የሚሆኑ ምእመናን አቅመ ደካሞች ናቸው፡፡ እነሱ ሲያልፉ ማን እንደሚተካ ሳስበው ይጨንቀኛል፡፡” ይላል፡፡

 

መፍትሔ

የአከባቢው ተጽእኖ የኘሮቴስታንቱ ድባብ የዋጣቸው በርካታ ወገኖቻችን አሉ፡፡ስለ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሳያውቁ በጭፍኑ የኮበለሉ ብዙ ነፍሳት አሉ፡፡ በቅርቡ በተደረጉ ሁለት መንፈሳዊ ጉዞዎች ባለፈው ክረምት ለ2 ወራት በተደረገው ጠንካራ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ አርባ ሁለት ሰዎች ወደ ኦርቶዶክስ እምነታቸው እንደተመለሱ የምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ያብራራሉ፡፡ የአካባቢው ፕሮቴስታንታዊ ተጽእኖ ከባድ መሆኑ ስለታመነበት የካህናት ሥልጠና እንዲሰጥ ታምኖበታል፡፡ ይህ በመሆኑ በማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል አዘጋጅነት በምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት በጊምቢ ከተማ መንበረ ጵጵስና ከየካቲት 12-16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከአሶሳ፣ ከቄለም እና ምዕራብ ወለጋ አህጉረ ስብከት ለተውጣጡ 150 ካህናት ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ በብፁዕ አቡነ ሄኖክ ጸሎተ ቡራኬ የተጀመረው የካህናት ሥልጠና በነገረ ሃይማኖት መግቢያ፣ በአእማደ ምሥጢራት፣ በነገረ ድኅነት፣ በነገረ ቅዱሳን፣ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ በሕግጋተ እግዚአብሔር፣ በትምህርተ ኖሎት እና በወቅታዊ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

 

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ዕለት ካህናቱ በሰጡት አስተያየት የተሰጠው ሥልጠና ለቀጣዩ የስብከተ ወንጌል አገልግሎታቸው ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጠዋል፡፡ በተለይ በምዕራብ ወለጋ የሚታየውን የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ለመፍታት በንቃትና በትጋት እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የሰጠው ይህ ሥልጠና እጅግ ጠቃሚና ወቅታዊ በመሆኑ ለወደፊቱ ተደጋጋሚ የሆነ የካህናት ሥልጠና ቢደረግ በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ከፍተኛ የሆነ ስኬት ሊመጣ እንደሚችል ካህናቱ አስተውቀዋል፡፡

 

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ምሥጢሩ እና በዕለቱ ያገኘናቸው ምእመናን እንዲሆንላቸው የሚመኙትን እየተማጸኑ ነግረውናል፡፡

 

  1. በዚህች ከተማ መናፍቃኑ መሠረታቸውን ጥለው የእኛን ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን አስከልክለውብናል፡፡ የነገሩን ምንጭ ለማድረቅ በዚህች ከተማ የተጠና ፕሮጀክት ቢጀመር በሥራ እጦት እየተጨነቁ ሃይማኖታቸውን ጥለው የሔዱት ወገኖቻችን ሊመለሱ ይችላሉ፡፡
  2. በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ሰባኪያነ ወንጌል ቢመደቡልን
  3. ተተኪ ወጣቶችን የሚያስተምሩ የአብነት መምህራን ቢቀጠሩልን እና
  4. በመጪው ግንቦት 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ለምናከብረው ዓመታዊ በዓል ሰፊ ጉባኤ እንዲደረግልን ለመምህራን ትራንስፓርት፣ ለድምጽ ማጉያ፣ እና ለአንዳንድ ወጪዎች የሚሆን ገንዘብ የሚደግፉን በጎ አድራጊ ምእመናን ቢገኙ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ይመጣል፡፡ የስብከተ ወንጌል ጉባኤ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተከታታይ የሚሰጥ ከሆነ ባለፈው ጊዜ የተመለሱት ምእመናን በእምነታቸው ይጸናሉ ያልተመለሱትም ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ይመጣሉ ይላሉ፡፡

 

bogi 5ቦጂ ቅድስት ማርያም ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ያጣቻቸውን ልጆች መልሳ ለማግኝት በሯን ከፍታ ትጠብቃለች፤ ተከታታይ ጉባዔያት ቢካሔዱ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚያስተምራቸው ሰባኬ ወንጌል ቢመደብላቸው የጠፉት ነፍሳት ሊመለሱ እንደሚችሉ ምእመናን በመሉ ተስፋ ይናገራሉ፡፡ እኛም ታሪክ ተቀይሮ መናፍቃኑ መሠረት ከጣሉበት ቦታ አንድ ለውጥ ይመጣ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ በውስጣችን ይዘን ተመልሰናል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያንን ከመገንባት ሕንጻ እግዚአብሔር ሰውን ማነጽ ይበልጣል፡፡ የጠፉት በጐች ወደ በረታቻው ካልተመለሱ እዳው የቤተክርስቲያን መሆኑ አያጠያይቅም ስለዚህ ባለ ድርሻ አካላት የምንችለውን ሁሉ እንድናደርግ ቦጂ ትጮሀለች፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ 3ኛ አረፉ፡፡

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ
የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ 3ኛ አረፉ፡፡
የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ማርቆስ መንበር 117ኛ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ሲኖዳ ትናንት መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም. አረፉ፡፡
ቢቢሲ የግብፅን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጠቅሶ እንደዘገበው ቅዱስነታቸው በካንሰር ሕመም ምክንያት በ88 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡
በሰሜናዊ ግብፅ፣ አስዩት ውስጥ ሐምሌ 27 ቀን 1915 ዓ.ም ሲወለዱ ናዚር ጋይድ የሚል መጠሪያ ከቤተሰባቸው የተሰጣቸው ቅዱስነታቸው፣  ቅስናን ሲቀበሉ አባ እንጦንስ ተብለው ይጠሩ የነበር ሲሆን አቡነ ሲኖዳ የተባሉት በ1955 ዓ.ም የክርስትና ትምህርት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው በተሸሙበት ወቅት ነበር፡፡
ቅዱስነታቸው አቡነ ሲኖዳ የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 117ኛ ፓትርያርክ ሆነው በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ የተሾሙት ከተአምር ሠሪው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ 6ኛ በኋላ ኅዳር 4 ቀን በ1964 ዓ.ም ነበር፡፡፡
ቅዱስነታቸው ከ5ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የቲዎሎጂ ሴሚናሪ ዲን የሆኑ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሲሆኑ በአገልግሎት ዘመናቸው ከ3 የአሜሪካን እንዲሁም ከ1 የጀርመን ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ተቀብለዋል፡፡
ቅዱስነታቸው ሕይወታቸው የትሕርምት፣ የጸሎትና የአገልግሎት እንደነበር የሕይወት ታሪካቸውን የሚዘግቡ ድርሳናት የሚገልጹ ሲሆን ባለፉት 20 ዓመታት የዓለምን ሕዝብ ያስተማሩባቸው 80 መጻሕፍትን ደራሲና የቤተ ክርስቲያኗ ኦፊሴላዊ መጽሔት ኤል-ኬራዛ ዋና አዘጋጅ ነበሩ፡፡
በግብፅ ርዕሰ ብሔር አንዋር ሳዳት ጊዜ አክራሪ ሙስሊሞች በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት መጨመርና መፋፋም ያሳሰባቸው ቅዱስነታቸው በመንግሥቱ ላይ ባነሱት ተቃውሞ፣ ለ40 ወራት ከመንጋዎቻቸው ተለይተው ወደ ቅዱስ ቢሶይ ገዳም ተግዘው የአባቶቻቸውን በረከት ተካፍለው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በኋለኛው መሪ ሆስኒ ሙባረክ ዘመን ወደ መንበራቸው ተመለሰው እስከ ዛሬ ድረስ ጠቦቶችን ሲጠብቁ፣ ግልገሎችና በጎችን ሲያሰማሩ ቆይተው አርፈዋል፡፡
በግብፅ ሕዝብ በተለይም በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ተወዳጅ አባት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ቅዱስነታቸው በግብፃውያን ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልና ሰላማዊ ለማድርግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እንደደከሙ ይመሠከርላቸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ ኢትዮጵያን  ሁለት ጊዜ የጎበኙ ሲሆን ከመጀመሪያው ጉብኝታቸው 30 ዓመታት በኋላ በ2000 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ላይ ያደረጉት ጉበኝት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር፡፡
ጸሎታቸው ከሁላችን ጋር ይሁን፣ ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ለግብፃዉያን ወንድም እህቶቻችንና ቅዱስነታቸውን ለሚወዱ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል፡፡
መጋቢት 9/2004 ዓ.ም.

በተ/ሥላሴ ጸጋ ኪሮስ

የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ 3ኛ ዐረፉ፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳትና የቅዱስ ማርቆስ መንበር 117ኛ ፓትርያርክ የቅዱስነታቸው ዕረፍት የታወቀው ትናንት መጋቢት 8 ቀን 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡

 

ቢቢሲ የግብፅን ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጠቅሶ እንደዘገበው ቅዱስነታቸው በካንሰር ሕመም ምክንያት በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡
baba shenouda
በሰሜናዊ ግብፅ፣ አስዩት ውስጥ ሐምሌ 27 ቀን 1915 ዓ.ም ሲወለዱ ናዚር ጋይድ የሚል መጠሪያ ከቤተሰባቸው የተሰጣቸው ቅዱስነታቸው፣  ቅስናን ሲቀበሉ አባ እንጦንስ ተብለው ይጠሩ የነበር ሲሆን አቡነ ሲኖዳ የተባሉት በ1955 ዓ.ም የክርስትና ትምህርት ኤጲስ ቆጶስ ተብለው በተሸሙበት ወቅት ነበር፡፡ ቅዱስነታቸው አቡነ ሲኖዳ የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 117ኛ ፓትርያርክ ሆነው በወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ የተሾሙት ከተአምር ሠሪው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቄርሎስ 6ኛ በኋላ ኅዳር 4 ቀን በ1964 ዓ.ም ነበር፡፡
ቅዱስነታቸው ከ5ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የቲዎሎጂ ሴሚናሪ ዲን የሆኑ የመጀመሪያው ፓትርያርክ ሲሆኑ በአገልግሎት ዘመናቸው ከ3 የአሜሪካን እንዲሁም ከ1 የጀርመን ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክትሬት ተቀብለዋል፡፡ቅዱስነታቸው ሕይወታቸው የትሕርምት፣ የጸሎትና የአገልግሎት እንደነበር የሕይወት ታሪካቸውን የሚዘግቡ ድርሳናት የሚገልጹ ሲሆን ባለፉት 20 ዓመታት የዓለምን ሕዝብ ያስተማሩባቸው 80 መጻሕፍትን ደራሲና የቤተ ክርስቲያኗ ኦፊሴላዊ መጽሔት ኤል-ኬራዛ ዋና አዘጋጅ ነበሩ፡፡

 

በግብፅ ርዕሰ ብሔር አንዋር ሳዳት ጊዜ አክራሪ ሙስሊሞች በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት መጨመርና መፋፋም ያሳሰባቸው ቅዱስነታቸው በመንግሥቱ ላይ ባነሱት ተቃውሞ፣ ለ40 ወራት ከመንጋዎቻቸው ተለይተው ወደ ቅዱስ ቢሶይ ገዳም ተግዘው የአባቶቻቸውን በረከት ተካፍለው እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በኋለኛው መሪ ሆስኒ ሙባረክ ዘመን ወደ መንበራቸው ተመለሰው እስከ ዛሬ ድረስ ጠቦቶችን ሲጠብቁ፣ ግልገሎችና በጎችን ሲያሰማሩ ቆይተው ዐርፈዋል፡፡

 

በግብፅ ሕዝብ በተለይም በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ተወዳጅ አባት እንደሆኑ የሚነገርላቸው ቅዱስነታቸው በግብፃውያን ክርስቲያኖችና ሙስሊሞች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልና ሰላማዊ ለማድርግ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ እንደደከሙ ይመሠከርላቸዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ ኢትዮጵያን  ሁለት ጊዜ የጎበኙ ሲሆን ከመጀመሪያው ጉብኝታቸው 30 ዓመታት በኋላ በ2000 ዓ.ም ሚያዝያ ወር ላይ ያደረጉት ጉበኝት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነበር፡፡

ጸሎታቸው ከሁላችን ጋር ይሁን፣ ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን ለግብፃዉያን ወንድም እህቶቻችንና ቅዱስነታቸውን ለሚወዱ ሁሉ መጽናናትን ይመኛል፡፡