ማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አመራር ጠቅላላ ስብሰባውን አካሔደ፡፡

02/08/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የ2004 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ጉባኤ መጋቢት 22 እና 23 ቀን 2004 ዓ.ም. አካሒዷል፡፡sera amerare meeting 2004

ጉባኤው የሥራ አመራሩ ባለፉት 6 ወራት ያከናወናቸውን የስብሰባና የውሳኔ ቃለ ጉባኤ ማጽደቅ፣ የሥራ አስፈጻሚ 6 ወር ክንውን ሪፖርት፤ በሀገር ውስጥ 42 እና ከሀገር ውጪ የሚገኙ 3 ማእከላትና 4 ግንኙነት ጣቢያዎች፣ የቅዱሳን መካናትና ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ቦርድ፣ የልማት ተቋማት አስተዳደር ቦርድ የ6 ወር ክንውን ሪፖርት ገምግሞአል፡፡

ጉባኤው አክሎም የሥራ አመራር ጉባኤ ጽ/ቤት ያከናወናቸው ተግባራት፣ የኤዲቶሪያል ቦርድ ሪፖርት ያደመጠ ሲሆን የማኅበሩ ኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት አጠቃላይ የማኅበሩን አገልግሎት የተመለከተም የኦዲትና የኢንስፔክሽን ሪፖርት አቅርቧል፤ በቀረበው ሪፖርት ላይም ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

የ2004 ዓ.ም. የመጀመሪያው የ6 ወር ጉባኤ ላይ በአጀንዳነት በቀረቡት የኤዲቶሪያል ቦርድ ፖሊሲ፣ የጽ/ቤት ግንባታ ሒደት፣ የሒሳብና ገቢ አሰባሳቢ፣ የቀጣይ 4 ዓመት ስልታዊ እቅድ መነሻና የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም እና የማኅበሩ 20ኛ ዓመት የበዓል አከባበር በተመለከተ ውይይት አድርጓል፡፡
በሁለተኛው ቀን ጉባኤ ላይ ለተወሰነ ሰዓት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ በጉባኤው ላይ ተገኝተዋል፡፡ ሓላፊው ቆሞስቆሞስ መላከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው መላከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድ ይፍራው በቀረቡት ሪፖርቶችና አጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ማኅበሩ እያደረገ ያለውን አገልግሎት የቤተ ክርስቲያናችን ሕግና ሥርዓት የማኅበሩም ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መሥራትና አጠናክሮ እንዲቀጥል አባታዊ ምክር አስተላልፈዋል፡፡ በተጨማሪም “ከዚህ በኋላ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያውን ችግር እንደችግር አያነጋግርም፡፡ መፍትሔው ሕጉን በመጠበቅ በመምሪያው እየተሰጠ ነው የሚሔደው፡፡ ሌላው ጥቃቅን የቤተ ክርስቲያን ችግር ቢፈጠር እንኳን በውይይት ይፈታል በወረቀት የሚፈታ አይደለም ይህንን እኔ አምናለሁ…”
ለሁለት ቀናት በታየው በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ከሀገር ውስጥ የ39 ማእከላት ተወካዮችና ከሀገር ውጪ የካናዳ ማእከል እና የማኅበሩ ሥራ አመራርና ሥራ አስፈጻሚን ጨምሮ የኦዲትና ኢንስፔክሽንና የኤዲቶሪያል ቦርድ ሓላፊዎች ተገኝተዋል፡፡