የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የልምድ ልውውጥ አደረጉ
ታኅሣሥ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ኅሩይ ባየ

ከታኅሣሥ 11-15 ቀን 2005 ዓ.ም. ለአምስት ተከታታይ ቀናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የልምድ ልውውጥ አደረጉ፡፡ የልምድ ልውውጡ የተከናወነው በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ሲሆን በአምስቱ ዕለታት በየቀኑ እስከ አንድ ሺሕ ለሚሆኑ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መካፈላቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ታኅሣሥ 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በጉባኤው መክፈቻ ዕለት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ እና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የኢሊባቡርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ ጸሐፊና የአዲስ አበባ ምዕራብ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የበላይ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቢመን የላዕላይ ግብፅ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ቄስ ዳውድ ለሜይ የግብፅ መንበረ ማርቆስ ካቴድራል ካህን፣ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የአድባራት የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊዎች፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና የቅዱስ ጳውሎስ ሰዋሰወ ብርሃን ከፈተኛ ትምህርት ቤት ደቀ መዛሙርት፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ተገኝተዋል፡፡
“ተዘከር ማኅበረከ ዘአቅደምከ ፈጢረ ወአድኀንከ በትረ ርስትከ ደብረ ጽዮን ዘኀደርከ ውስቴታ… አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን የተቤዥሃትንም የርስትህን በትር በእርስዋ ያደርህባት የጽዮንን ተራራ አስብ” /መዝ.73፥2/ የሚለው የዳዊት መዝሙር በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅድሳን ገዳም ዲያቆናት ተሰብኮ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከተነበበ በኋላ የኪዳን ጸሎት ደርሷል፡፡ በመቀጠልም ዐቃቤ ርእሰ መንበሩ ግብፅና ኢትዮጵያ እኅትማማች ዓብያተ ክርስቲያናት መሆናቸውን አስታውሰው የቆየ ቤተሰባዊ ግንኙነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የመጡ ግብፃውያንንና የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን አመስግነዋል፡፡
ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ በመሸፈን በአሜሪካና በግብፅ የሚገኙ የበጎ ፈቃደኛ አገልጋዮች ልዑካንን በመመደብ የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት አምስት ቀናት የልምድ ልውውጥ እንዲደረግ ላደረገችው አስተዋጽኦ ምሥጋናቸውን የገለጡት የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን የኤች አይቪ መከላከያና መቆጣጠሪያ መምሪያ ሓላፊ ቄስ ሶምሶን በቀለ ልማት ኮሚሽኑ በማስተባበር እና የቋሚ ተሳታፊ ሠልጣኞችን የትራንስፓርት ወጪ መሸፈኑን ገልጠዋል፡፡
በሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኮረው የልምድ ልውውጥ በከፍተኛ መነቃቃትና ፍላጎት ተካሂዷል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እነዚህን ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለማስተማር ያላቸው ብቃት እንደተጠበቀ መሆኑን የገለጡት ቄስ ዳውድ ለሜይ በሥርዓት አፈጻጸሙ ላይ የልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል በተጨማሪም ምእመናን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት፣ የሚታይና የማይታይ ጸጋ ለማግኘት እነዚህ ምሥጢራት ከሕይወታቸው ጋር አስተሳስረው ሁል ጊዜ በማንኛውም ቦታ በየትኛውም ጊዜ የምስጢራት ተካፋይ መሆን እንደሚያስፈልግ ሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው ልዑኩ በአጽንኦት ገልጠዋል፡፡
“ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ለእኛ አዲስ ናቸውን?” የሚሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አሳባቸውን ያቀረቡ ሲሆን ቄስ ዳውድ በምሳሌ እንዳስረዱት በጉባኤ የተገኘ አንድን ሕፃን ልጅ ጠርቼ አባትህ አለ? ብዬ ብጠይቀው ካለ አለ ማለቱ አይቀርም አሁንም ተጨማሪ ጥያቄ እንድጠይቀው ፍቀድልኝ አሉ አባትህ ስንት ብር በኪሱ ይዟል? አላውቅም አለ፡፡ የት ነው የሚሠራው? አላውቅም፡፡ ደመወዙ ስንት ነው? አላውቅም፡፡ የሚገርም ነው ሕፃኑ አባቱን ያውቃል ስለ አባቱ ግን የማያውቀው ብዙ ነገር አለ፡፡ … በማለት ምላሻቸውን በምሳሌ አስቀምጠዋል፡፡ በዚህ መነሻነት ሰባቱ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በጥልቀትና በዝርዝር ማወቅ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን በማብራራት ይልቁንስ በመንፈሳዊ ሕይወት ለመጠንከር፣ ከዲያብሎስ ቀስት ለማምለጥ፣ በመንፈስ ቅዱስ ለመቃኘት፣ ምስጢራቱን ማወቅ ሳይሆን መጠቀም እንዲገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኩል የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት፣ ከአዲስ አበባ ደቡብ ሀገረ ስብከት የተውጣጡ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ከማኅበረ ቅዱሳን ዘማርያን ያሬዳዊ መዝሙር ያቀረቡ ሲሆን ሦስት ወጣቶችም በገና እየደረደሩ ዝማሬያቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዝማሬ ስሰማ ንጉሥ ዳዊት በዓይነ ኅሊናዬ፤ ይመጣል በመጽሐፍ ቅዱስ የተዘረዘሩት የዜማ ዕቃዎች መልካቸቹውን ሳይቀይሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገሩ መዝለቃቸውን አድንቀው ለወደፊት ይህ ትውፊት ሳይቋረጥ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በእነሱ በኩል ከሁለት የዘለለ የዜማ ዕቃ እንደሌላቸው ያስታወሱት ቄስ ዳውድ የእኛ ዜማ ጣዕም እጅግ የሚመስጥ ደስ የሚል እንደሆነ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል፡፡ በዝማሬያችን የተመሰጡት ግብፃውያን የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች በፍጹም ተመስጦ ለመዘመር ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡
የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝማሬ አቅርበዋል፡፡ በአረብኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተለያዩ መዝሙራትን በማቅረብ የዝማሬውን መልእክት ቄስ ዳውድ አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ በጉባኤው የተለያዩ ጥያቄዎች ተነሥተዋል፡፡ ተገቢና ግልጽ ምላሾች ተሰጠተዋል፡፡ ሆኖም በሁለቱ ዓብያተ ክርስቲያናት ያለው መሠረታዊ አንድነት የዶግማ እንጂ የሥርዐት ስላልሆነ በልምድ ልውውጡ የተገለጡ እንግዳ ሥርዓቶች ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንፃር መታየት እንዳለባቸው ሊቃውንቱ አሳስበዋል፡፡ ትምህርተ ኖሎት፣ ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ በጎ አስተዳደርና የግጭት አፈታትን በሚመለከቱ የጥናት ጽሑፎች በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ቀርቦ ሰፊ ውይይትና በቂ ግንዛቤ ተገኝቶበታል፡፡
የልምድ ልውውጡ በጎ ገጽታ እንዳለው እና ለወደፊቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በዕለቱ ከተሰጡ አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡







የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማሳካት የገማት ድርሻ በሚል መሪ ቃል ማኅበረ ቅዱሳን ባዘጋጀው ዐውደ ጥናት ላይ ለመገኘት ከ65 ገዳማት የመጡ አበምኔቶችና እመምኔቶች ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ጠዋት በማኅበሩ ሕንጻ ላይ ስለ ማኅበሩ ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል በተዘጋጀው መርሐ ግብር ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበር ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን እንደተገኙም ዐውደ ጥናቱ ተከፍቷል፡፡
በጥናታቸው ማጠቃለያም “እነዚህ ቅርሶች የእኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ የሁላችንም የኢትዮጵያውን /ሃይማኖታችን ምንም ቢሆን/፤ የመላው ጥቁር ሕዝቦች እንዲሁም የሰው ልጆችና የዓለማችን ቅርሶች ናቸው፡፡ ጥቁር ሕዝቦች እጅግ የረዘመ የሥእልና የኪነ ጥበብ ቅርስ የላቸውም የሥእልና የኪነ ጥበብ ቅርስ ያለው ሕዝብ እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፡፡ እነዚህን ቅርሶች ያቆየችልን ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት” ብለዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ከገዳማት ጋር ባደረገው የተቀራረበ ሥራ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍተኛ አፈጻጸም ላሳዩ ገዳማት የዋንጫ ሽልማት ማበርከቱ አንዱ የመርሐ ግብሩ አካል ነበር፡፡ ለሽልማት የበቁትም የባሌ መካነ ሕይወት አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም፣ የአቃቂ ደብረ ገነት አባ ሳሙኤል ቤተ ደናግል ገዳምና የደቡብ ጎንደር ገዳመ ኢየሱስ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
ሁለቱንም መጻሕፍት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበር በመመረቅና በመባረክ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለማርያም ተረክበዋል፡፡ ደራሲት ጸሐይ መላኩ “እመምኔት” የተሰኘው መጽሐፋቸው ለማኅበሩ ሕንፃ ግንባታ እንዲውል ከዚህ ቀደም ማበርከታቸው ይታወሳል፡፡



ማእዱን እንደተመገቡ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ለማስተላለፍ ቅድሚያውን ወሰዱ፡፡ “የቤተ ክርስቲያን መሠረቷ ገዳማት ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ጠነከረች የሚባለውም የገዳማት ጥንካሬ የሚያመጣው ነውና በዚህ ሁኔታ ላይ እንድንወያይ፤ ነገ ምን ማድረግ እንደሚገባን እንድንነጋገር፤ እኛም የምናስበውን ለማሳየት እንድንችል እንድትመክሩን፤ እንድተጸልዩልን ነው የተሰባሰብነው፡፡ እናንተን ለማየት በመታደላችን እጅግ ደስተኞች ነን፡፡ ቀሪውን ጊዜም መልካም ነገር የምናቅድበትና የምንፈጽምበት እንዲሆን እንመኛለን” ያሉ ሲሆን ደጆችሽ አይዘጉ መንፈሳዊ የአገልግሎት ማኅበር ላከናወነው አርአያነት ያለው ተግባር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ቢሰማቸው የማኅበሩ አባላት የሆኑ የሕክምና ዶክተሮችና ነርሶች 24 ሰዓት እነሱን ለማገልገል መመደባቸው ተገለጸላቸው፡፡ እንዲሁም ማንኛውንም አገልግሎት ቢፈልጉ እነሱን ለማገልገል የተመደቡ ወንድሞችና እኅቶች ስለሚገኙ የሚሹትን ነገር ሳይሰቀቁ እንዲጠይቁ በማሳሰብ የምሽቱ መርሐ ግብር በአባቶች ቡራኬ ተጠናቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ለማሳካት የገዳማት ድርሻ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ አውደ ጥናት ታህሣሥ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀኑ 7፡00 ሠዓት ጀምሮ 6 ኪሎ በሚገኘው በኢትዮጵያ ስብሰባ ማእከል ከሃምሳ በላይ የሚደርሱ ከታላላቅ ገዳማት የተውጣጡ አበምኔቶች በተገኙበት እንደሚካሄድ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር ዲያቆን አእምሮ ይሔይስ ገለጹ፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮግራም አስተባበሪነት፤ በደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሥር የሚገኙና በልዩ ልዩ ቤተ እምነቶች ውስጥ የነበሩ ከሰባት መቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ሥርዓተ ጥምቀት ተፈጽሞላቸው ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን ተመለሱ፡፡ በሜጸር የቅዱስ ሚካኤል እንዲሁም በቶልታ የቅድስት ሥላሴ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ኅዳር 23 ቀን 2005 ዓ.ም. በተከናወነው ሥርዓተ ጥምቀት ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ያገኙ ሰዎች በማኅበረ ቅዱሳን የጂንካ ማእከልና በሰንበት ትምህርት ቤት ጥምረት በሁለት ልዩ ልዩ የስብከት ኬላዎች አማካኝነት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ሲማሩ የቆዩ ናቸው፡፡
አዳዲስ ተጠማቂያኑ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አተያየት ፡ በተፈጸመላቸው ሥርዓት ጥምቀት እጅግ በጣም መደሰታቸውን ገልጸው፤ በአቅራቢያቸው ቤተ ክርስቲያን እንዲታነፅላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል “የምእመናኑ ጥያቄ ተገቢ ነው፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱ ሲቋቋሙ አብሮ መተዳደሪቸውም ሊታሰብ ይገባዋል፤ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንዳስተዋልነው ምእመናን በቅንነት በዚህ ቦታ እንዲህ ያለ ታቦት ይተከልልን እኛ ሙሉ ወጪውን እንሸፍናለን በማለት ያሳነፅዋቸው አብያተ ክርስቲያናት ምእመናኑ በሕይወት እስካሉ ድረስ ያገለግሏቸውና፤ እነሱ ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ሲለዩ አገልግሎቱ እየተቋረጠ አብያተ ክርስቲያናቱ እስከ መዘጋት የደረሱባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለሆነም ቤተ ክርስቲያኗ እንዴት ትገለገላለች? በሚለው ላይ ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ የቤተ ክርስቲኒቱ ልጆች ሊያስቡበት ይገባል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትም ሁል ጊዜ በልመና መተዳደር የለባቸውም” ብለዋል፡፡
የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያው በቶልታና ሜጠር ቀበሌዎች ላስጠመቃቸው አዳዲስ ምእመናን በቀጣይ ለሚፈጽምላቸው እገዛ አስመልክተው ሊቀ ብርሃናት ሃማኖት ተስፋዬ እንዲህ ብለዋል፡፡ “የልጅነት ጥምቀት አግኝተው በቅርቡ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለገቡ ምእመናን በአቅራቢያቸው ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙባቸውን አብያተ ክርስቲያናትን ማነፅና እነሱንም ማጽናት ይጠበቅብናል፡፡”