በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ
ባለፈው ዕትማችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በዝርወት /ከኢትዮጵያ ውጪ/ ያደረገችውን ረዥም ሐዋርያዊ ጉዞ የሚዳስስ ጽሑፍ ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ ቀጣዩን ደግሞ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
1.1. ውስጣዊ ችግሮች
ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የታሪክ ጉዞዋ ያጋጠሟት ችግሮች ወደ ኋላ ሲቃኙ በብዛት ከልዩ ልዩ አረማውያንና አላውያን ነገሥታት የመጡባት ውጫዊ ፈተናዎች በርከት ብለው ይታያሉ፡፡ እሷን ለመፈተን የማይታክተው ዲያብሎስ በዚህ ዘመን ደግሞ ከውጫዊው ፈተና ባልተናነሰ መልኩ አንዳንድ ክፍተቶችን በመግቢያነት እየተጠቀመ ቤተ ክርስቲያኗ በተለያዩ ውስጣዊ ችግሮች እንድትፈተን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህን ችግሮች አንድ በአንድ እንደሚከተለው እንዳስሳለን፡፡
ሀ. አስተዳደራዊ ችግር
በዝርወት ያለችዋ ቤተ ክርስቲያናችን በስደት ካሉ ልጆቿና አካባቢው ከሚፈጥረው ምቹ ሁኔታ ሊገኝ የሚችል ኃይሏን በአግባቡ ተጠቅማ አገልግሎቷን እንዳታጠናክር በተለይ ከ1958 ዓ.ም ጀምሮ የገጠማት የአስተዳደር መለያየት ዕንቅፋት ሆኖባታል፡፡ ዛሬ በምንገኝበት ሰፋ ሰፋ ባለ ሁኔታ ብንከፍለው በውጭው ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሦስት ዓይነት አስተዳደር አላት፡፡ የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያኗ በየአካባቢው ባቋቋመቻቸው አህጉረ ስብከት በኩል በማእከላዊው የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ታቅፎ /በእርግጥ ይህም ቢሆን ያለው አስተዳደራዊ ቁርኝት የሚያረካ አይደለም/ አገልግሎት የሚሰጠው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሀገራችን ከተከሠተው የመንግሥት ለውጥ ጋር ተያይዞ ወደ ሰሜን አሜሪካ የተሰደዱትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛ ፖትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን በመያዝ ዘግይተው እሳቸውን የተቀላቀሉት ሌሎች ብፁዓን አበው መሠረትነው ባሉት ስደተኛ ሲኖዶስ ሥር ያሉ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ከሁለቱም አይደለንም ገለልተኛ ነን በማለት የተቀመጠው ክፍል ነው፡፡ ይህ የአስተዳደር ልዩነት ሌሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረከቱ የመጡ ችግሮችን እየወለደ አንዲት ቤተ ክርስቲያን ተጠናክራ ሐዋርያዊ አገልግሎቷን እንዳትሰጥ ዕንቅፋት ሆኖባታል፡፡
ለ. የተቀመጠ ግብና ዓላማ አለመኖር
ዓለም ዛሬ በደረሰበት የአሠራር ደረጃ አንድ ተቋም በሰፊው መክሮና ተችቶ ያስቀመጣቸው ዓላማዎችና ግብ ሊኖረው ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ የዕለትም ይሁን የዓመት እንቅስቃሴውን እየገመገመ የደከመውን የማጠናከር በጠነከረው የመቀጠል እርምጃ የሚወስደው አስቀድሞ ካስቀመጣቸው ዓላማዎችና ግብ አንጻር ነውና፡፡ ይህንን አጠቃላይ መርሕ በጥንቃቄ ተግባራዊ የሚያደርግ ሕዝብና መንግሥታት ባሉበት በውጭው ዓለም የምትንቀሳቀስ ቤተ ክርስቲያናችን ለምትሰጠው አገልግሎትና በሰው ዘንድም ይሁን በደሙ በመሠረታት ክርስቶስ ዘንድ ለሚጠበቅባት ሰማያዊ አገልግሎት መሪ የሚሆኑ በግልጽ የተቀመጡ ዓላማዎችና ግብ ሊኖራት ሲገባ እንቅስቃሴዎቿ ሁሉ በየጊዜው በሚፈጠሩ ሁኔታዎች መሠረትነት የሚመራ ሆኗል፡፡
ሐ. የአሠራር መመሪያ አለመኖር
አንድ ተቋም የቆመለትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንዲችል ከሚያደርጉት መሠረታውያን ነገሮች አንዱ ግልጽና ለአሠራር የሚያመች አንድ መሠረታዊ መመሪያ መኖሩ ነው፡፡ ከዚህ መሠረታዊ መመሪያ በመነሣትም በየደረጃው እንዲያገለግሉ ሆነው የሚቀረጹ መመሪያዎች ሊኖሩት ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ መመሪያዎች አማካይነት ተቋሙ እየተንቀሳቀሰ ድካሙንና ጥንካሬዉን በየዕለቱ እየገመገመ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡
በውጭው ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስጠት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ አገልግሎቷን በተቀላጠፈ መልኩ እንድትፈጽም የሚያስችላት የአገልግሎት ፖሊሲም ይሁን መመሪያ የላትም፡፡ ድንገት ከውስጥም ይሁን ከውጭ የሚመጡ የአገልግሎት አሳቦች ወዲያው በሚመነጩ ደግም ይሁኑ መጥፎ ዘዴዎች ይፈጸማሉ እንጂ ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት ቃለ ዐዋዲውን መሠረት በማድረግ ቤተ ክርስቲያን ያዘጋጀችው የውጭ ሀገር አገልግሎት መመሪያ የለም፡፡ ለማዘጋጀትም ፍላጎቱ ያለ መስሎ አይታይም፡፡
መ. በዕቅድና ሪፖርት አለመመራት
በውጭው ዓለም ያለችዋ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን በሚመሩ ዕቅዶችና አፈጻጸሟን በሚገመግሙ ሪፖርቶች አትመራም፡፡ በእርግጥ ይህ ችግር የማእከላዊው የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ነፀብራቅ መስሎ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም በሥርዓት በሚመራበት ሀገር ካለች ቤተ ክርስቲያን ተመሳሳይ ኋላ ቀርነት አይጠበቅም፡፡
ሠ. ወደ ባዕዳኑ ለመድረስ ያለው ጥረት አናሳ መሆን
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባላት የተስተካከለ ትምህርተ ሃይማኖትና ሰማያዊ ሥርዓት ብዙዎች ባዕዳን ከማድነቅ አልፈው በጥምቀት የሥላሴን የጸጋ ልጅነት አግኝተው ወደሷ ለመጠቃለል ይማልላሉ፡፡ ነገር ግን በአንጻሩ በየደረጃው ያለው የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር ይህንን ተረድቶ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ሲንቀሳቀስ አይታይም፡፡
ረ. ራሷን ለሌሎች ያለማስተዋወቅ ችግር
ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የታሪክ ዘመኗ በመንፈሳውያን ልጆቿ የዳበሩ በቃልም በመጣፍም እየተወረሱ የቆዩ ልዩ ልዩ የሥነ ዜማ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ሕንፃ፣ የሥነ ፍልስፍና ወ.ዘ.ተ. ዕውቀቶች አሏት፡፡ እነዚህ ዕውቀቶች በመልክ በመልኩ እየሆኑ ለማያውቀው ዓለም ቢቀርቡ ቤተ ክርስቲያኗን በማስተዋወቅና ገንዘብም በማስገኘት በኩል ቀላል የማይባል ሚና ይጫወታሉ፡፡ ነገር ግን በውጭው ዓለም ምናልባት አልፎ አልፎ እዚህና እዚያ ሊጠቀሱ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ካልሆነ በስተቀር በተጠናከረ መልኩ ሲፈጸም አይታይም፡፡ ይህንን ተግባር በማከናወን በኩል ሰፊ ሚና ሊጫወቱ በሚችሉ ኢንተርኔት ሬድዮ ቴሌቪዥን ፓልቶክ በመሳሰሉት መገናኛ ብዙኃን ቤተ ክርስቲያናችን ከሌሎች ኋላ ብትሰለፍ እንጂ ለውድድር የምትደርስ አትመስልም፡፡
ሰ. በአካባቢው ተወልደው የሚያድጉ ሕጻናትን ለማስተማር የሚያገለግል ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት አለመኖር ምእመናን በስደት ሕይወት የሚወልዷቸውን ልጆች የሀገራቸውን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዐተ እምነት እንዲሁም ቋንቋ ባሕልና ታሪክ ተምረው ያድጉ ዘንድ ከቤተሰባቸው ቀጥሎ ሐላፊነት ያለባት ተቋም ቤተ ክርስቲያናችን ናት፡፡ ነገር ግን ይህንን ሐላፊነቷን እንድትወጣ የሚያስችላት ወጥ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት የላትም፡፡
1.2. ውጫዊ ችግሮች
ሀ. የቦታ እጥረት
በአካባቢው ከሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በንብረትነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሆነ ሕንፃ ያለው አንድም የለም፡፡ ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ስጦታ ሊባል በሚችል ሁናቴ በሀገሩ ከሚኖሩ የእምነት ድርጅቶች ሕንፃ ያገኙ ቢሆንም እንደራሳቸው ቆጥረው ሊገለገሉበት አልቻሉም፡፡ በመሆኑም በአካባቢው የምትገኘዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቦታ ችግር አለባት ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡
ለ. የመናፍቃን ጥቃት
ወቅታዊው የቤተ ክርስቲያናችን በመናፍቃን የመጠቃት ችግር በሀገር ቤት ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ በልዩ ልዩ ችግር የተነሣ ሀገሩን ለቆ በስደት በአውሮፓ የሚገኘው ምእመንም በመናፍቃኑ ልዩ ልዩ ሴራ እየተነጠቀና እየተደናገረ ይገኛል፡፡ በጥናቱ ሒደት ለመረዳት እንደተቻለው መናፍቃኑ በእናት ቤተ ክርስቲያኑ ጉያ ያለውን ምእመን ለመንጠቅ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ውስጥ የምእመናኑን የማኅበራዊ ሕይወት ጉድለት፥ ሕመም፥ የገንዘብ እጦት፥ ትዳር ወ.ዘ.ተ. የመሳሰሉትን መጠቀም ዋናው ነው፡፡ እርስ በርስ በመረዳዳት በኩል ደግሞ በእኛ ምእመናን ዘንድ ድካም ይታያል፡፡
ሐ. ወቅታዊው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ
ምእመኑ በወቅቱ ፖለቲካ ክፉኛ በመናወጡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን በአንድም በሌላ መንገድ በወቅቱ ፖለቲካ እጇ እንዳለባት በመቁጠር ምእመኑ አባቶቹን እንዲርቅና እንዲያወግዝ፥ አባቶችም የምእመኑን ጥያቄ በወግ እንዳይሰሙ አድርጓቸዋል፡፡
መ. የባሕል ተፅዕኖ
በአካባቢው ላለችዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንቅስቃሴ ዕንቅፋት የሆነው ምእመናኑ በሚኖሩበት ሀገር ባሕልና ልማድ ተፅዕኖ ሥር መውደቃቸው ነው፡፡ ይህ ተፅዕኖ ደግሞ በምእመናኑ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን በካህናቱም አካባቢ ይታያል፡፡
IV. መፍትሔዎች
የዚህ ጥናት ዓላማ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያሉባትን ችግሮች ዘርዝሮ የሚፈቱባቸውን የመፍትሔ አሳቦች ማቅረብ ነው፡፡ ለችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ የሚባሉ ነጥቦች በዝርዝር ይቀርባሉ፡፡ አንዳንዶቹ የመፍትሔ ሐሳቦች የራሳቸው የሆኑ ዝርዝር የስልት ጥናቶች የሚያስፈልጋቸው ይመስላሉ፡፡
ሀ. በአኅጉሩ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኗ ምልዓተ ጉባኤ /ካህናትና ምእመናን/ ተወያይተው የሚያስቀምጧቸው ዓላማዎችና ግቦች ማዘጋጀት
በዚህ ጥናት ሒደት እንደታየው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ አካባቢ ልታከናውናቸው የሚችሉ በርካታ ተግባራት አሉ፡፡ ተግባራቱን ለማከናወንም የተለያዩ አካላት ትምህርተ ሃይማ ኖቷን፣ ሥርዓተ እምነቷንና ትውፊቷን አክብረው አብረዋት ሊሠሩ እንደሚፈልጉ ታይቷል፡፡ በመሆኑም በአኅጉሩ ያለችዋ ቤተ ክርስቲያን አካባቢው የሚጠይቀውን አገልግሎት በስደት ላለው ምእመንም ሆነ በትክክለኛው ትምህርቷና ሰማያዊ ሥርዓቷ ተማርኮ ወደ ዕቅፏ ለመግባት በደጅ ቆሞ ለሚጠባበቀው መንፈሳዊ ድጋፍ መስጠት እንድትችል በመሪ አሳብነት የሚያገለግሉ ዓላማዎችና ግቦች በአስቸኳይ ልታስቀምጥ ይገባል፡፡ ለዚህም አኅጉሩ ውስጥ ያሉትን ካህናትና ምእመናን ያሳተፈ አንድ አጠቃላይ ጉባኤ ማድረግ ይገባል፡፡
ለ. የአካባቢውን ሁሉን ዐቀፍ ሁኔታ ያገናዘበ ዝርዝር መመሪያ ማዘጋጀት
ዓለም አቀፋዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራቡ ዓለም በስደት ያሉ ልጆቿንና የሚፈልጓትን ለማገልገል በሐዋርያዊ እግሮቿ ገስግሳ ከተሻገረች በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ማዕከላዊው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የቤተ ክርስቲያኗን በምዕራቡ ዓለም መስፋፋት አስፈላጊነት አምኖ ለተግባራዊነቱ ቢንቀሳቀስም እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ይተዳደሩባቸው ዘንድ የውጭውን ዓለም ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ልዩ ልዩ መመሪያዎችን አውጥቶ አልሰጠም፡፡ በሀገር ቤቱ የቤተ ክርስቲያን ይዞታ መሠረት የተዘጋጁ መመሪያዎች ባሕር ተሻግረው እንዲያገለግሉ ይጠብቃል፡፡ ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ የሕግና ሥርዓት ምንጭ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን ከሚመራ አካል የሚጠበቅ አይደለም፡፡ በመሆኑም ይህ አስፈላጊ ግን የተረሳ ሳይሆን ጨርሶ ያልታሰበ ጉዳይ በአስቸኳይ ትኩረት ተሰጥቶት በውጭው ዓለም ያለች ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን የምትፈጽምባቸው ዐቢይም ይሁን ዝርዝር መመሪያዎች ሊዘጋጁና በተግባር ሊውሉ ይገባል፡፡ ለዚህም የአኅጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች በአስቸኳይ በአካባቢው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ አጠቃላይ የአሠራር መመሪያ አርቅቆ ለውሳኔ የሚያቀርብ አንድ ኃይለ ግብር /Task Force/ ሊሰይሙ ያስፈልጋል፡፡ የዚህ መፍትሔ አሳብ ተግባራዊ መሆን ከታች ለሚዘረዘሩ አስተዳደራዊ የመፍትሔ አሳቦች እንደ መሠረት ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡
ሐ. አስተዳደራዊ አንድነትን መፍጠር
ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አሐቲ ከሚያሰኟት ነገሮች አንዱ ማዕከላዊ በሆነ አንድ መንፈሳዊ አስተዳደር መመራቷ ነው፡፡ በመሆኑም በማዕከላዊው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደርና በአውሮፓ ባለችው ቤተ ክርስቲያን መካከል የጸና ግንኙነት እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድም ከሁለቱም አካላት ከፍተኛ ተግባር ይጠበቃል፡፡ ማዕከላዊው አስተዳደር በውጪው ዓለም ያለችዋን ቤተ ክርስቲያን መምራት እንዳለበት ተገንዝቦ ሊንከባከባት የአገልግሎት መመሪያም ሊሰጣት ይገባል፡፡ በየወቅቱ በሚያደርጋቸው ልዩ ልዩ ጉባኤያት ጠንካራ ውክልና ኖሯት እንቅስቃሴዎቿ ሁሉ እየተገመገሙ የደከመውን በማጠናከር የጎደለውን በመሙላት አገልግሎቷን በተጠናከረ መልኩ እንድትቀጥል ማድረግ ይገባዋል፡፡ አልፎ አልፎ በሚያደርጋቸው አስተዳደራዊ እንቅስቃሴዎችም በዝርወት ያለችዋን ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉና የሚመሩ አባቶችን እና ምእመናንን ቅር የሚያሰኙ ተግባራት መፈጸም የለበትም፡፡ የሚወስዳቸውን አስተዳደራዊ እርምጃዎች ሁሉ በውጪው ካሉ አባቶች ጋር እየተመካከረ ሊሆን ይገባል፡፡
በውጪ ያሉ አባቶችና ምእመናንም አሐቲ በምትሆን ቤተ ክርስቲያን ከማዕከላዊው አስተዳደር ጋር አንድ መሆናቸውን ከልባቸው ሊያውቁት ይገባል፡፡ በመሆኑም ከላይ ለሚመጡ ትእዛዞችና የማስተካከያ አሳቦች ተገዥዎች መሆን አለባቸው፡፡ እነሱም አንዳንድ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች ወደ ላይ እየላኩ የማስወሰን ልምድ ሊያዳብሩ ይገባል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደየ ደረጃው ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን አበው ወደ አኅጉሩ እየሔዱ ምእመናንን እንዲባርኩና በመንፈሳዊ አባትነታቸው የምእመኑን ችግር በቅርብ እንዲያዩ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከላይ ለተባሉትም ሆነ ላልተባሉት ጉዳዮች ተግባራዊነት እያንዳንዱን የግንኙነት እንቅስቃሴ በግልጽ የሚያመላክት አጠቃላይና ዝርዝር መመሪያ ሊዘጋጅ ያስፈልጋል፡፡ ይኽ ዐቢይ ጉዳይ በሁለቱም አካላት ትኩረት ተሰጥቶት በአስቸኳይ ካልተተገበረ በትንሹም ቢሆን ብቅ እያለ የሚመስለውና በአሜሪካ የሚሰማው የቤተ ክርስቲያን ፈተና በዚህም መምጣቱ የሚቀር አይኾንም፡፡
መ. የዕቅድንና ሪፖርትን ጥቅም አስመልክቶ የተለየ ግንዛቤ መፍጠር
እንኳን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትን ያህል የተቀደሰ ተግባር የትኛውም ቀላል እንቅስቃሴ በዕቅድና በሪፖርት በሚመራበት በዚህ ዘመን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ ተልእኮዋን ለማስፈጸም የሚረዷት ሁነኛ የሥራ ዕቅዶች አውጥታ የዕቅዶቹንም ተፈጻሚነት በየጊዜው ሪፖርት እያቀረበች አለመወያየቷ አሳፋሪ ነው፡፡ በጀርመን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርሰቲያን በዓመት አንድ ጊዜ በምታደርገው ጉባኤ ዕቅዶችና ሪፖርቶች ሲቀርቡ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን የሚቀርቡት ዕቅዶችም ይሁኑ ሪፖርቶች ቤተ ክርስቲያኗ በዝርወት ላለው ሕዝብ ማድረግ የሚገባትን ያገናዘቡ ሳይሆኑ በቢሮ ሥራ የሚያልቁ በአመዛኙ ገንዘብ ነክ የሆኑ ጉዳዮች ናቸው፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኗ ልትንቀሳቀስባቸው የሚገቧትን ጉዳዮች በየጊዜው እያገናዘቡ የሚቀርቡ የአገልግሎት ዕቅዶች እየነደፈች ያንንም ለምእመናኗ በግልጽ እያሳወቀች ልትንቀሳቀስ ይገባል፡፡ የሚፈለጉት አገልግሎቶች በዕቅድነት እየተያዙ እንዲፈጸሙ አባቶችንም ሆነ ምእመናኑን የማንቃትና የማደራጀት ሥራ ሊሠራ ይገባል፡፡
ሠ. ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ነጻ የሆኑ ጉባኤያትን በማዘጋጀት አባቶች ስለሚሰጡት አገልግሎት እንዲወያዩና ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ
በጀርመን የሚያገለግሉ ካህናት ልዩ ልዩ ዓመታዊ በዓላትን መሠረት እያደረጉ በዓሉን በሚያደርገው አጥቢያ እየተገናኙ ይወያያሉ፡፡ ነገር ግን በጥናቱ ሒደት እንደታየው ብዙ ጊዜ የሚወያዩት በጥቃቅን አስተዳደራዊ ጉዳዮች እንጂ ስለ አገልግሎታቸውና የመሳሰሉት ላይ አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም ካህናት የሚንቀሳቀሱት የሳምንቱን መጨረሻ የትራንስፖርት ቲኬት በመግዛት ስለሆነ በዓሉ ካለቀ በኋላ በሩጫ ወደየመጡበት ይመለሳሉ፡፡ በመሆኑም ካህናቱ ስለ አገልግሎታቸው የሚወያዩባቸውና አዳዲስ ሥልቶች የሚቀ ይሱባቸው ራሳቸውን የቻሉ ጉባኤያት ማዕከላዊ በሆኑ ቦታዎች ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ጉባኤያት አማካይነት በአገልግሎት ጉዟቸው ስላጋጠሟቸው ችግሮች ይወያያሉ፤ ምእመናኑን የበለጠ የሚያገለግሉባቸውን መንገዶች ይተልማሉ ወ.ዘ.ተ.
ረ. አካባቢ ተኮር የሆኑ ትምህርቶችን መስጠት
ሰዎች በምግባራቸው ጎልብተው በእምነታቸው እንዳይጸኑ ከሚያደርጓቸው ነገሮች አንዱ አካባቢያዊ ተጽእኖ ነው፡፡ ይህ እውነታ በአውሮፓ በሚኖሩ ምእመናን ሕይወት ላይ በግልጽ ይታያል፡፡ በመሆኑም ወጣቶችም ይሁኑ ታላላቆቹ ምእመናን በእምነታቸው እንዲጸኑ ችግራቸውን ያገናዘቡ ትምህርቶች በልዩ ልዩ መንገድ ሊሰጣቸው ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ በዚሁ ተወልደው ለሚያድጉ ሕፃናት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡
ሰ. ከተለያዩ የእምነት ድርጅቶችና የመንግሥት አካላት ጋር በመነጋገር ቦታዎች የሚገኙበትን መንገድ መፈለግ
በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደተሰማው አውሮፓና አውሮፓውያን ብዙ ገንዘብ አፍስሰው የገነቧቸው የጸሎት ቤቶች የቀደመ አገልግሎት ተቀይሮ የልዩ ልዩ ሥጋዊ ተግባራት ማከናወኛዎች ሆነዋል፡፡ ያ ዕጣና ፈንታ ያልደረሳቸውም ተዘግተው ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሀገሩን ሕጋዊ ሒደት ጠብቃ እነዚህን ቦታዎች ማግኘት እንድትችል መንቀሳቀስ ይገባታል፡፡
ቀ. ስለ መናፍቃን እንቅስቃሴ መግለጽ
ምእመናኑ ከመናፍቃኑ ቅሰጣ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲጠብቁ በልዩ ልዩ መንገዶች መናፍቃን የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች በመግለጽ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይም መናፍቃኑ ምእመናንን ለመንጠቅ የሚጠቀሙባቸውን እርዳታ መሰል ዘዴዎች በማጥናት በቤተ ክርስቲያን በኩል አገልግሎቱ እንዲሰጥ ማድረግ ይገባል፡፡
በ. የፖለቲካ አመለካከቶች ከቤተ ክርስቲያንና አካባቢዋ እንዲጠፉ ማድረግ
በምዕራቡ ዓለም ቤተ ክርስቲያናችን ካሉባት ችግሮች አንዱ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው ግለሰቦች ምእመንነታቸውን ተገን በማድረግ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ መዋቅሮች በመግባት ቤተ ክርስቲያኗን የግል ዓላማቸው ማራመጃ ማድረጋቸው ነው፡፡ ይህ ድርጊት ምእመኑን ከእናት ቤተ ክርስቲያኑ ይለያል፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያኗ በልዩ ልዩ መዋቅር ያሉትን ፖለቲካዊ አመለካከቶች ከቤተ ክርስቲያኗ እየነቀሉ የማውጣት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ይህንንም ለማድረግ ምእመናንን በግልጽ ስለጉዳዩ እያነሡ ማስተማር፣ አመለካከቱ ያላቸውን አባቶችም ይሁን ግለሰቦች መምከርና ማስመከር እንቢ ያሉትንም በምእመናን ትብብር ከቤተ ክርስቲያኗ ማኅበር እንዲለዩ ማድረግ መቻል ይኖርበታል፡፡
ተ. የገጽታ ግንባታ ሥራ መሥራት
ከላይ እንደቀረበው በአውሮፓ ያለው ምእመን በብዛት ለአባቶች ክብር አይሰጥም፡፡ ይህም ከቤተ ክርስቲያን ምስጢራት ሱታፌ እንዲርቅ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም ምእመኑ ለአባቶቹ ፍቅር ባጣበት በዚህ ዘመን የአባቶችን ገጽታ የማድመቁና ጥብቅና የመቆሙ ሥራ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ሰባክያንም ሆኑ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት በአገልግሎታቸው ሒደት ከምእመናን ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሁሉ ስለ ካህናት ማንነትና ስለ አገልግሎታቸው አስፈላጊነት መልካሙን በመግለጽ የሕዝብ ግንኙነት ሥራቸውን ሊሠሩ ግድ ይላል፡፡
ቸ. አካባቢውን ያገናዘቡ የቃለ እግዚአብሔር ማስተላለፊያ መንገዶችን መጠቀም
ዛሬ ዓለም በደረሰበት የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ ዕውቀትን በቀላል ወጪና የሰው ኃይል ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው ለማስተላለፍ የሚያስችሉ መንገዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ መረጃ መረብ፣ የርቀት ትምህርት፣ ፓልቶክ፣ የቴሌፎን ጉባኤ፣ ሬድዮና ቴሌቪዥን በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉት ናቸው፡፡ እነዚህ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት አገልግሎት ላይ በሚውሉባቸው ሀገራት አገልግሎት የምትሰጥ ቤተ ክርስቲያናን ለዓላማዋ ማስፈጸሚያ መጠቀም የውዴታ ግዴታዋ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በየዘርፉ የሠለጠኑ ምእመናንን መመልመልና ወደ አገልግሎቱ ማሰማራት ይጠበቅባታል፡፡
ነ. ራሷን የምታስተዋውቅባቸው ልዩ ልዩ መንገዶችን መቀየስ
በአካባቢው ቤተ ክርስቲያኗ ራሷን ለማስተዋወቅ ከላይ የተዘረዘሩትን መንገዶች ከመጠቀም በተጨማሪ ልዩ ልዩ ዐውደ ርእያትን፣ ሲምፖዝየሞችን፣ የባሕል ማስተዋወቂያ ዝግጅቶችን ወዘተ. ማዘጋጀት ትችላለች፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር