ማኅበረ ቅዱሳን በሬድዮ አገልግሎቱ የሞገድና ሰዓት ለውጥ አደረገ

 

ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን ድምጸ ተዋሕዶ የተሰኘውንና ዘወትር ዓርብ ከምሽቱ 3፡30 እስከ 4፡30 በአጭር ሞገድ 9850 kHz 19 ሜትር ባንድ ሲሰጠው በነበረው ሳምንታዊ የሬድዮ አገልግሎት ላይ የሥርጭት ሞገድና ሰዓት ለውጥ ማድረጉን አሳወቀ፡፡ ለውጡን ለማድረግ ያስፈለገበትን ምክንያት ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ የማኅበሩ ሚድያ ዋና ክፍል ሓላፊ ሲያስረዱ «ቀድሞ መርሐ ግብሩ ይተላለፍበት የነበረው ሰዓት፤ ዘወትር ዓርብ ከምሽቱ 3፡30 እስከ 4፡30፤ በንጽጽር ምሽት ስለነበር በተለይ በክልል የሚገኙ አድማጮቻችን አገልግሎቱን አለማግኘታቸውን በልዩ ልዩ መንገድ ሲገልጹልን ቆይተዋል፡፡

በዚህ መሠረት ምእመናን አገልገሎቱን በሚመቻቸው ጊዜ ማግኘት እንዲችሉ ይተላለፍበት የነበረውን አጭር ሞገድ ወደ 17.515 kHz 16 ሜትር ባንድ በመቀየር ዘወትር ዓርብ ከአመሻሹ 12፡30 እስከ 1፡30 ለማቅረብ ለውጥ አድርገናል» ብለዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኗ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ እምነትና ታሪክ በሊቃውንት ተተንትኖ የሚቀርብበት ይህ የሬድዮ መርሐ ግብር ማሠራጫ ጣቢያውን አውሮፓ ባደረገ የአሜሪካ ራድዮ ካምፓኒ አማካይነት የሚተላለፍ ነው፡፡ «እግዚአብሔር የሰጠንን መልካም አጋጣሚ ሁሉ በመጠቀም ቃሉን ለሁሉም ማድረስ ይገባናል´ ያሉት ዲ/ን ዶ/ር መርሻ «የአበው ትምህርትና ምክር በዓለም ዙሪያ ሁሉ እንዲዳረስ ምእመናን ሬድዮውን በማስተዋወቅ፣ በፕሮግራሞች ላይ የሚኖሩ አስተያየቶችንም በማድረስና በጸሎት እንዲያግዙን´ በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ አክለውም በውጭው ዓለም የሚኖሩና የኢንተርኔት አገልግሎትን በቀላሉ ማግኘት የሚችሉ ምእመናን ዝግጅቶችን www.dtradio.org ላይ ተጭነው እንደሚያገኟቸው ገልጸዋል፡፡

 

egeda 2006 2

የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት ለመልአከ መንክራት ግርማ ወንድሙ የማስተማርና የመፈወስ ፈቃድ እንዳልሰጠ አስታወቀ፡፡

 መጋቢት 11 ቀን 2006 ዓ.ም.

ከዚህ በፊት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ፈቃድ እንደተሰጠ ተደርጎ ሐምሌ 25 ቀን 2005 ዓ.ም. በቁጥር ል/ጽ/484/420/2005 የተጻፈውን ደብዳቤ ጽ/ቤቱ የማያውቀውና እውነትነት የሌለው የማጭበርበር ሥራ መሆኑን ገልጾ ምእመናን ይህንን ተገንዝበው እንዲጠነቀቁ ገልጿል፡፡

ሕገወጡንና በድጋሚ የታገዱበትን ደብዳቤ ከዚህ በታች ይመልከቱ፡፡

 egeda 2006 2egeda 2006 1

 

የባሕር ዳር ማእከል ሐዊረ ሕይወት( የሕይወት ጉዞ) ማዘጋጀቱን አስታወቀ

መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ.ም.

ግዛቸው መንግስቱ ከባሕር ዳር ማእከል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማእከል ምእመናን በጾሙ ወቅት መንፈሳዊ በረከትና ዕውቀት እንዲያገኙ በማሰብ መጋቢት 21/2006 ዓ.ም ወደ ጥንታዊቷና ታሪካዊቷ አብችክሊ ጽርሐ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሐዊረ ሕይወት ቁጥር ፪ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ እንደ ማእከሉ ገለጻ የዚህ የሐዊረ ሕይወት መዘጋጀት ዋና ዓለማው ሕዝበ ክርስቲያኑ በመንፈሳዊ ሕይወቱ እንዲበረታና መንፈሳዊ እድገት እንዲያመጣ ማድረግ ነው፡፡ ዓላማውን ውጤታማ ለማድረግ በዕለቱ ጸሎተ ወንጌል በካህናት ይደረሳል፣ ምክረ አበውና ቡራኬ በሊቃነ ጳጳሳትና ገዳማውያን አባቶች ይሰጣል፣ የተጠየቁ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች በሊቃውንቱ ምላሽ ያገኛሉ፣ ትምርህርተ ወንጌል፣ መዝሙር፣ መነባንቦችና ሌሎችም መንሳፈዊ መርሐ ግብራት በተያዘላቸው መርሐ ግብራት ይቀርባሉ፡፡

ጉዞው የሚደረግባት ጥንታዊና ታሪካዊት አብችክሊ ጽርሐ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን የምትገኘው በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ደቡብ አቸፈር ወረዳ ዱርቤቴ ከተማ ሲሆን ለጉዞ የተመረጠችው ቤተ ክርስቲያኗ ጥንታዊና ታሪካዊ በመሆኗ፣የእግር መንገድ ስለሌለው ለጉዞው ተሳታፊዎች ምቹ ስለሆነች፣ ለሐዊረ ሕይወት ጉዞ ማራኪ ቦታ ስለሆነች እንደሆነ አዘጋጅ ኮሚቴው አስታወቋል፡፡

 

ለጉዞው አብይና ንዑስ ኮሚቴዎች አቋቋሞ ሰፊ ዝግጅት ማድረጉን ያስተወቀው ማዕከሉ በዚህ የሕይወት ጉዞ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ገዳማውያን አባቶች፣ ሰባኪያነ ወንጌል፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ዘማርያንና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች እንደሚገኙ ገልጿል፡፡

 

የሐዊረ ሕይወት አዘጋጅ ኮሚቴው እንደገለጸው 1500 የጉዞ ትኬቶች ብቻ የተዘጋጁ ስለሆነ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ምእመናን ትኬቶቹ በባሕር ዳር ከተማ ታዬ ሞላ ስቴሽነሪ፣ ከራድዮን ካፌ ቁጥር 1ና 2፣ በማኅበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅዱሳት መሸጫ ሱቅ፣ ባ/ዳር ማዕከል ጽ/ቤት፣ ከቅድስት ኪዳነ-ምሕረት ሰ/ት/ቤት ንዋያተ ቅዱሳት መሸጫ ሱቅ እና ከሰላም አድርጊው ማርያም ሰ/ት/ቤት/ንዋያተ ቅዱሳት መሸጫ ሱቅ፣ በዓታ ለማርያም ሰ/ት/ቤት ሱቅ፣ ከማኅበሩ አባላትና ከግቢ ጉባኤያት ማግኘትና ፈጥነው መግዛት እንደሚችሉ ጠቁሟል፡፡

 

የደርሶ መልስ ዋጋ 100 ብር ብቻ ሲሆን ለጉዞው የሚስፈልጉ ልዩ ልዩ ወጪዎችንና ሙሉ መስተንግዶን የሚጨምር ሲሆን ኮሚቴው በጉዞው የሚሳተፉ ምእመናን ተገቢውን ክርስቲያናዊ አለባበስ መልበስና ማስታወሻ መያዣዎን እንዳይዘንጉ፣ ሊጠይቁት የሚፈልጉት ማንኛውም ጥያቄ ካለ ከታች በተገለፁት አድራሻዎች አስቀድመው መጠየቅ እንደሚችሉና በቂ ምላሽ እንደሚያገኙ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

  • በጽሑፍ በፖስታ አድርገው ከራድዮን ካፌ ቁጥር 1 እና 2 እና ከማኅበሩ ጽ/ቤት

  • በኢሜል፡- yemabu@gmail.comtsebank@gmail.com,bt.2005@yahoo.com

  • በስልክ በመልክት ወይም በመደወል 0913778229 /18020509/ 18728098/

 

dubai

የዱባይ ሻርጃ አጅማን ሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ተከበረ፡፡

 

መጋቢት 10 ቀን 2006 ዓ.ም.

እርቅይሁን በላይነህ

በሊባኖስ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትና አካባቢው ክብረ በዓሉ የተካሄደው በዱባይ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ላይ በተጣለ ድንኳን ሲሆን የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ በበዓሉ ታድመዋል፡፡

dubai

ከ20 ዓመት በፊት የተመሠረተችው የሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረቷ ምክንያት ከሆኑት ምእመናን በተጨማሪ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የአኀት አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች ከአዲስ አበባ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተጋብዘው የሄዱ መምህራን ክብረ በዓሏን ለማድመቅ በቦታው ተገኝተዋል፡፡

ይህ 20ኛ የምሥረታ በዓል የቤተ ክርስቲያናችንን ታሪክ የሚያሳይ ዐውደ ርዕይ፣ መንፈሳዊ ይዘት ያላቸው መነባነብና ግጥሞች፣ የሕፃናት ዝማሬዎች፣ በትዳር ሕይወት ውስጥ ያሉ እኅት ወንድሞች መዝሙራት፣ የቤዛ ብዙሃን የሰንበት ትምህርት ቤቱ መዘምራንና የቤተ ክርስቲያኒቱ ዲያቆናት መዝሙራትን አካቶ በዓሉ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በክብረ በዓሉ ላይ 10 ዕድለኞችን አሸናፊ ያደረገ ዕጣ የወጣ ሲሆን የ1ኛ ደረጃ ባለዕጣ የመኪና ባለዕድል ሆኗል፡፡ በክብረ በዓሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ መመሥረትና 20 ዓመታትን በገንዘብ በዕውቀትና በጉልበት እየረዱ ላሉ አገልጋዮች ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ አይከልና በትረ ሙሴ የተሸለሙትና ከተሸላሚዎች ቀዳሚው የሆኑት ብፁዕ አቡነ ድሜጥሮስ መርሐ ግብሩን በጸሎት ከመዝጋታቸው በፊት ባደረጉት ንግግር “እናንተ የእኛ ሽልማቶች ጌጦቻችን ናችሁ” ብለዋል፡፡

 

01 hawire

ሐዊረ ሕይወት

01 hawire

metshate 01

ሦስተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጥናት መጽሔት ለኅትመት በቃ

መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

metshate 01የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል በተለያዩ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን በማካሄድ ያሳተመውን ሦስተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምርምር መጽሔት /Journal/ ለኅትመት በቃ፡፡

የምርምር መጽሔቱ ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ስይፈ አበበ “ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለውሳኔ ሰጪዎች ግብአት ይሆናል፤ቤተ ክርስቲያን በጥናት እና ምርምር የተደገፈ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት እንድታበረክት ያግዛታል፤ለተለያዩ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ ይሰጣል፤ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት እና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚገኙ ምሁራን ልጆቿን ለቀጣይ ጥናት ያነሳሳል፣ ያበረታታል” ብለዋል፡፡

የምርምር መጽሔቱ ሰባት ጥናታዊ ጽሑፎችን በማካተት የቀረበ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ፡-

  • የቅዱስ ያሬድ የሕይውት ታሪክና የሥራዎቹ አጭር ዳሰሳ ታሪክ /History/

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሻራ በሸካቾ ብሔር ፤ማኅበራዊ እና ቅርስ /Social Heritage /

  • የደንና ብዝኀ ሕይወት ጥበቃ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን /Forestry & Biodiversity/

  • The Ethiopian Religious Community and Its Ancient Monastery, Deires-Sultan, in Jerusalem from Foundation to 1850s ታሪክ /History/ Treasures of the Lake Zway Churches and Monastery, South Central Ethiopia ቅርስ /Heritage/

  • Woody, Species Diversity, Floristic Composition and Structure of DebreLibanose Forests. Biodiversity

  • Oromo Language use in Wellega Dioceses: opportunities and Challenges በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር/Teaching with Mother toungs/ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ተዘጋጅቷል፡፡

የምርምር ማዕከሉ በምርምር ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ አጥኚዎችን ያበረታታል፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የማማከር አገልግሎት ይሰጣል፤ የውይይት መድረኮችን እና ዐውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት ያወያያል፡፡

ጥንታዊቷ የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተመዘበረች

 መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም.

ሹመት ገ/እግዚአብሔር

በደሴ ማእከል ከወረኢሉ ወረዳ ማእከል

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በወረኢሉ ወረዳ የምትገኘው የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ማንነታቸው ባልታወቁ ዘራፊዎች ተመዘበረች፡፡

የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከወረኢሉ ከተማ 24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም በግምት ከጧቱ 4፡00 ሰዓት ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ንዋየ ቅድሳቷ የመዘረፍና የመውደም አደጋ ደርሶባታል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው የቤተ ክርስቲያኒቱን በርና መስኮት ሰብሮ በመግባት ሲሆን፤ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የቅዳሴ መጽሐፍ ባለምልክቱ፣ ሰባት የቤተ ክርስቲያን መጋረጃ፣ ሰባት መቋሚያ፣ ሦስት ምንጣፍ እና አምስት መሶበ ወርቅ ተሰርቋል፡፡ ትልቅ የመፆር መስቀል እና የእጅ መስቀሎች የተፈላለጡ ሲሆን መንበሩ ተገነጣጥሏል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗንና መንበሩን ሳርና ስዕለ አድህኖ በመሰብሰብ ለማቃጠል የተደረገው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

መጽሐፈ ክርስትና፣ ሥርዓተ ተክሊልና መጽሐፈ ግፃዌ ሙሉ በሙሉ ተቀዳደው፤ ሻኩራ፣ ፃህል፣ እርፈ መስቀል፤ ሻማዎች፣ የተቀጠቀጡ አንድ ሺህ ጧፎች፤ አስር ኪሎ እጣን፤ ጥላዎች ተቀዳደው፤ 15 ባለ መስታወት ፍሬም ስዕለ አድህኖዎች ተሰባብረው፤ ከፍሬም ውጭ የሆኑ 88 ስዕለ አድኅኖዎች ተቀዳደው ጫካ ውስጥ የተጣሉ ሲሆን፤ መቋሚያዎችና አምፖሎች ከነማቀፊያቸው ተሰባብረው ገደል ውስጥ ተጥለዋል፡፡ 6 ትላልቅ ሥዕለ አድኅኖዎችም ተቃጥለዋል፡፡

ይህንን ልብ የሚያደማና የሚያሳዝን ድርጊት የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች እና የፀጥታ ኃይሎች ቦታው ድረስ በመሄድ የተመለከቱ ሲሆን፤ ድርጊቱን የፈፀሙትን ወንጀለኞች ለመያዝ የወረዳው ፖሊስ አስፈላጊውን ክትትልና ምርመራ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በግራኝ አህመድ ከመቃጠሏና ከመውደሟ በፊት “ቀርቀሬ ማርያም” በሚል ስያሜ ትጠራ የነበረ ሲሆን፤ የአካባቢው ተወላጆች ወደ ጦር ሜዳ በሔዱ ጊዜ “ያገሬ ታቦት ወይ በይኝ፣ ከዚህ ጦርነት በሰላም ከመለሺኝ ስመለስ ስዕለቴን አገባለሁ” ብለው በመሳላቸውና ሥዕለታቸውም በመድረሱ ሲመለሱ “ወይብላ ማርያም” በሚል ስያሜ እንደተጠራች ይነገራል፡፡ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኗ እንደገና ታንፆ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ መልክ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነበረች፡፡

 

የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ሥርጭት አንደኛ ዓመት ተከበረ

 

መጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ሥርጭት አንደኛ ዓመት በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ አርቲስቶች የማኅበሩ ደጋፊዎችና የማኅበሩ የሥራ አመራር አባላት በተገኙበት ተከበረ፡፡

በዕለቱ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን አንደኛ ዓመት ለማክበር የተገኙትን ባለድርሻ አካላት “እንኳን ደኅና መጣችሁ” ያሉት የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ እንደገለጹት “ማኅበረ ቅዱሳን ወንጌለ መንግሥትን ለዓለም ለማዳረስ በሚደረገው መንፈሳዊ አገልግሎት የኅትመት ውጤቶች ሲጠቀም መቆየቱን ገልጸው አሁንም በቴክኖሎጂው በመታገዝ በዓለም ሁሉ ከምንደርስበት መንገዶች አንዱ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሩ መጀመር የምሥራች ሲሆን በእውቀት፣ በገንዘብ፣ በጉልበት ድጋፋችሁ ሁል ጊዜ የማይለየን ክቡራን እንግዶቻችን አሁንም ድጋፋችሁ እንዳይለየን በሚል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ቃለ እግዚአብሔርን ለመመገብ የተገኙት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ እንዳስተማሩትም “ስብከት የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ነው፡፡ የጠፋው በኃጢአት ምክንያት የኮበለለ የሰው ልጅ ሲሆን የሚጠራው፣ የሚያፈላልገው እግዚአብሔር ነው፡፡ ከማፈላለጊያ መንገዶች አንዱ ደግሞ ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት በመሆኑ አገልግሎቱን ልንረዳ ይገባል፡፡ በማለት አስተምረዋል፡፡

በዕለቱ መርሐ ግብር መሠረት የበገና መዝሙር በመ/ር አቤል ሙሉጌታ፣ መነባንብ በአርቲስት ንብረት ገላው፣ በቴሌቪዥን ክፍል ዘጋቢ ፊልም ቀርቦ በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ሓላፊ በዶ/ር መርሻ አለኸኝ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ለታዳሚው ቁጭትን የፈጠረና በተለይ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ቃለ እግዚአብሔርን በተለያዩ ቋንቋዎች ማዳረስ ሲቻል አለማዳረሳችን ግንዛቤ አግኝቷል፡፡

ከጥናታዊ ጽሑፉ በመነሣት የአኀት አብያተ ክርስቲያናት (ኮፕት) ጥቂት ምእመናን ይዘው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሲኖራቸው፤ የኛ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ምእመናን እያለን ይበልጥ መሥራት ሲገባን አለመሥራታችን፣ በሀገራችን የሌላ እምነት ተከታዮች የ24 ሰዓት ሬድዮና ቴሌቪዥን ሲኖራቸው እኛ ግን በሳምንት ከሦስት ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ መኖሩ በንጽጽር ቀርቦ የጉባኤው ተሳተፊ ለቀጣዩ ከማኅበሩ ጋር በመተባበር የበኩላቸውን እንደሚያበረከረቱ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የማኅበሩ በሳምንት የአንድ ሰዓት የቴሌቪዥን ሥርጭት ወደ 24 ሰዓት እንዲያድግ በቅርቡ የገቢ ማሰባሰቢያ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተጋባዥ እንግዶች አበክረው አሳስበዋል፡፡ የማኅበሩን የቴሌቪዥን መርሐ ግብር በ EBS TV እሑድ ከ5፡00-600 ሰዓት የሚተላለፍ ሲሆን በድጋሚ ሐሙስ ጠዋት 1፡00-2፡00 ሰዓት ይተላለፋል፡፡ በተጨማሪም www.eotc.tv ይከታተሉ፡፡

 

desa 2006 01

የደሴ ማእከል ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ስለቤተክርስቲያን ዘላቂ ልማት ከበጎ አድራጊዎች ጋር ውይይት አደረገ፡፡

የካቲት 28 ቀን 2006 ዓ.ም. 

ወርቁ በላይሁን ደሴ ማእከል

የደሴ ማእከል ቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል “ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት በጋራ እንሥራ” በሚል መርህ ለሁለተኛ ጊዜ ከደሴ ከተማ በጎ አድራጊዎች ጋር የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም ውይይት አደረገ፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ desa 2006 01ጥሪ የተደረገላቸው በጎ አድራጊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ለዘላቂ የቤተ ክርስቲያን ልማት መሠራት ስለሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱም በስብከተ ወንጌል፣ በቅዱሳት መካናትና በአብነት ት/ቤቶች ዙሪያ ድጋፍ በማድረግ ረገድ ወጥነት ባለው መልኩ የልማት ፕሮጀክቶችን መሥራት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት በማእከሉ ተቀርጸው የቀረቡ ፕሮጀክቶችንና ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችንም ለመሥራት የምዕመናንን ተሳትፎ ለማጠናከር ስድስት ኣባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴ በዕለቱ ተመርጧል፡፡

ኮሚቴውም ለቀረቡት ፕሮጀክቶች የአካውንት መክፈቻ የሚሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥረት ያደረገ ሲሆን፤ አስተዋጽዖን በተመለከተ እያንዳንዱ ተሳታፊ በተሰጠው የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ሞልተዋል፡፡ በየወሩ ድጋፍ ለሚያደርጉ በጎ አድራጊዎችም የተባባሪ አባልነት መታወቂያ እንዲዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር ዮሐንስ ደምሴ በዕለቱ የተገኙት ተሳታፊዎች በሥራ ቦታና በመኖሪያ አካባቢ የሚያውቋቸውን በውይይቱ ያልተገኙ ምዕመናንን በዚህ በጎ አገልግሎት እንዲሳተፉ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ለመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ማእከሉ ያዘጋጀውን ዶክመንተሪ ፊልም የቀረበ ሲሆን፤ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

 

ምኲራብ

 የካቲት 27 ቀን 2006 ዓ.ም. 

ታመነ ተ/ዮሐንስ

 

“ዘወትርም በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር” ሉቃ.19፥47

ምኲራብ የአይሁድ የጸሎት ቤት ሲሆን በብሉይ ኪዳን ዘመን የአይሁድ አምልኮ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስና በሥርዓቱ የተመሠረተ ነበር፡፡ ናቡከደነጾር ግን ቤተ መቅደሱን አፈረሰ ሕዝቡንም ወደባቢሎን አፈለሰ፡፡ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎትና ለማኅበረተኛነት ልዩ ቤት ሊሠሩ እንደጀመሩ ይታሰባል፡፡ /የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት/

አይሁድ በምኲራቦቻቸው የሕግንና የነቢያትን መጻሕፍት /የብራና ጥቅሎች/ በአንድ ሣጥን ውስጥ ያስቀምጣሉ በመሆኑ እኒህን የጸሎት ሥፍራዎቻቸውን ለትምህርትና ለአምልኮ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በሕገ ኦሪት የአይሁዳውያን ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ ሕግና ልማዳቸው ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ተግባራት ከሚሄዱበትም ይልቅ በዓመት አንዴ የሚቀርበውን መሥዋዕትና መባዕ ለመስጠት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር ከሕግ ጸባያዊ /ከተፈጥሮ ሕግ/ እኩል ሕግ መጽሐፋዊንም /የመጽሐፍት ሕግን/ ሲፈጽም ስለኖረ እንደ ሕጉ ወደ ቤተ መቅደስ በመሄድ ሥርዓት ይፈጽም ነበር፡፡

“ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሞላው ጊዜ እንደአስለመዱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ” እንዲል /ሉቃ.2፥42/ አምላካችንና መድኃኒትችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሥርዓት የሐዲስ ኪዳን አስተምህሮውን /ወንጌልን/ መስበክ ከጀመረም በኋላ አጽንቶ ይፈጽም ነበር፡፡ መጽሐፍም ይህን ሲያጸናልን፡- “ዕለት ዕለትም በቤተ መቅደስ /ምኩራብ/ ያስተምር ነበር፡፡” /ሉቃ.19፥47/ ይለናል፡፡

ጌታችን በምኩራብ እየተገኘ ሲያስተምር ትምህርቱን ሕግን አውቆ እንደሚያሳውቅ ሠራዔ ሕግ ስለሆነ በሙሉ ሥልጣንና ኃይል ያስተምር ነበር፡፡ “በሰንበት በምኩራብ ገብቶ ያስተምራቸው ጀመረ፡፡ ትምህርቱንም አደነቁ፤ እንደጻፎቻቸው ያይደለ እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና” እንዲል /ማር.1፥21/፡፡

ይህም ስለምን ነው ቢሉ ባያውቁትም ቅሉ ከርሱ ባገኙት ሥልጣንና ከመምህራኖቻው በተማሩት እውቀት ተመርተው ያስተምሩ ነበር፤ እርሱ ግን ዓለምን በመዳፉ የያዘ ለእነርሱም በሕገ ኦሪት አማካኝነት እውቀት ዘበፀጋን ከፍሎ የሰጠ ነውና ከራሱ አንቅቶ ያስተምር ነበርና ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መሠረትና መንገድ በምኩራብ እየተገኘ በግልጥ ያስተምርና ይፈውስ ነፍሳትንም ወደመንጋው ይጨምር ነበር፡፡ አስተምህሮውን ለምን በግልጥ አደረገ ቢባል አንደኛው ምክንያት አይሁድ ለመማርና ለመለወጥ ያይደል እንከን ያገኙበት ዘንድ ዕለት ዕለት ከትምህርት ገበታው ላይ ይገኙ ለነበሩት ለፈሪሳውያንና ለጸሐፍት ምክንያትን ያሳጣ ዘንድ ነበር፤ ይኸውም በሥውር ፈጽሞት ቢሆን ኖሮ ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በመላው ይሁዳ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል ብለው ለከሰሱት ምክንያት ማሳመኛ አይደለም በሆነ ነበርና ነው፡፡

እንዲሁም ሕዝብን በእርሱ ላይ በማነሳሳት ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩ የካህናት አለቆችና ጸሐፍትን መጽሐፍ እንዲህ ይላል “የካህናት አለቆችና ጻፎችም ቆመው በብዙ ያሳጡት ነበር፡፡” /ሉቃ.23፥5-10/ ስለሆነም አይሁድ እንኳን በምክንያት ተደግፎላቸው ቀርቶ ነቁጥ ከማይገኝበት ከጌታችን በሆነው ባልሆነው ምክንያት ይፈልጉ ነበርና ለዚህ የተመቸ እንዳይሆን /ለእነርሱም የመሰናከያ ምክንያት እንዳይሆን/ ይህን አድርጓል፡፡

ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “በአባቱ እቅፍ ያለ ልጁ እርሱ ገለጠልን” /ዮሐ.1፥18/ እንዲል ትንቢታትንና ምሳሌያትን እያፍታታ፣ የተሰወረውን እየገለጠ ሊያስተምር ወደዚህ ዓለም መጥቷልና ማስተማሩን በግልጥ አደረገ፡፡ እርሱም ቢሆን አንዳች ነገርን እንዳልሰወረ በሊቀካህናቱ ፊት ባቆሙት ጊዜና ስለትምህርቱ በጠየቁት ጊዜ እንዲህ በማለት መስክሯል፡- “እኔ ለዓለም በግልጥ ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብም በቤተ መቅደስም ሁል ጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም የተናገርሁት አንዳች ነገር የለም፡፡” /ዮሐ.18፥20/

በሌላ መልኩ ይህ ቤተ መቅደስ /የጸሎት ሥፍራ/ በኦሪት የሚፈጸሙ ሥርዓቶችን /መሥዋዕትንና መብዓ ማቅረብን የመሳሰሉትን/ የሚያከናውኑበት ሥፍራ የነበረ እንደመሆኑ መጠን በሥፍራው የመሥዋዕት እንስሳት፣ የመሥዋዕት ማቅረቢያና ማሟያ ግብአቶች ለሽያጭ ይቀርቡ ነበር፤ አይሁድ አምልኳቸውን ከመፈጸም ይልቅ ቅሚያ፣ ዝርፊያ፣ ማታለል ይፈጽሙበት ነበር፡፡ ጌታችን “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” /ማቴ.21፥13/ በማለት ተቃውሟቸዋል ሻጮችንም ሆነ ገዢዎች የነበሩትን ሁሉ በጅራፍ ገርፎ አባሯል፡፡ ሻጮችንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ…..” /ማቴ.21፥12/ እና “ማንም ዕቃ ተሸክሞ በመቅደስ እንዲያልፍ አልፈቀደም” /ማር.11፥16/ የሚሉት ኃይለ ቃላት ይህንኑ ድርጊቱን የሚያስረዱን ናቸው፡፡

እንዲሁም ቤተ መቅደስን የመንጻት ሥርዓት በፈጸመበት ወቅት ካስተላለፋቸው መልእክታት አንዱ የጥንቱ የመስዋዕት አቀራረብ ሥርዓት ማክተሙን ማወጅ ነበር ስለዚህም ለመሥዋዕት የቀረቡ በጎችንም እንዲያወጡ አዘዘ፡፡ እውነተኛው የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕትም እርሱ መሆኑንና ጊዜው መድረሱን አጠየቀ ከፊቱ መንገዱን ሊያዘጋጅ በኤልያስ መንፈስ ይመጣል የተባለው መጥምቁ ዮሐንስም “እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት በተደጋጋሚ ያወሳው ስለዚህ ነበር /ዮሐ.1፥29 እና 36/፡፡

ጌታችንም ቢሆን በመዋዕለ ሥጋዌው ስለ ኦሪት አንዳንድ ሥርዓቶችን ማለፍ ለሐዋርያትና ለሚከተሉት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር “ኦሪትም ነቢያትም ከጥንት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ድረስ ነበሩ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርስዋ ይጋፋል፡፡” /ሉቃ.16፥16 “ከኦሪት አንዲት ቃል ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል” እንዳለ ጌታችን በቃሉ፡፡ ምክንያቱም እርሱ ያስተማረው ወንጌል ጥንት በመጻሕፍተ ነቢያት የተገኘ ስለነበረ ነው፡፡

እንግዲህ ቅዱስ ያሬድ ከደረሳቸው የዜማ ድርሳናት ውስጥ በዐብይ ጾም የሚዜመው ጾመ ድጓ የዓብይ ጾም ሳምንታትን በ9 ከፋፍሎ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ጽሑፋችን ምኩራብ ስለተሰኘው ሳምንትና ጌታችን በቤተ መቅደስና በምኩራብ እየተገኘ ስላስተማረባቸው ጊዜያት የምናስብበትን ጾሙን በቃለ እግዚአብሔር አስረጅነትና ሕይወትነት የሥርዐቱን ፍጹም መንፈሳዊነት ተረድተን የምንጾመው ነው፡፡ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለት ዕለት በቤቱ የሚነገረውን ቃሉን ለመስማትና ለመተግበር ያበቃን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን፡፡