ታኅሣሥ 21 ቀን 2007 ዓ.ም.
ዲ/ን ታደለ ፈንታው
ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ እነሆ ድንግል በድንግልና ትጸንሳለች ወንድ ልጅንም ትወልዳለች ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፡፡/ኢሳ፯፥፲፬/ የሚለው የነቢያት ቃል ፍጻሜውን አገኘ፡፡ይህ ትንቢት የይሁዳ መንግሥት በጦርነት ከበባ ላይ በነበረበት ጊዜ ሁለቱ የሦርያና የእስራኤል ነገሥታት የኢየሩሳሌም ቅጥር ሊያፈርሱ በተነሡበት ጊዜ የተነገረ ትንቢት ነው፡፡
ንጉሡ አካዝ በታላቅ ጭንቀት ላይ ነበር፡፡ ከተማዋን ለማዳን ያለ የሌለ ጥበቡን ሊጠቀም አሰበ፡፡ የከበቡትን ወገኖች በውኃ ጥም ያሸንፍ ዘንድ ዋናውን ምንጭ መቆጣጠር ዓይነተኛ መፍትሔ እንደሆነ እቅድ አወጣ፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ እግዚአብሔር ሁለቱንም ነገሥታት ያጠፋቸዋልና አትፍራ አለው፡፡ አግዚአብሔር ከሰማይ ሠረገላና ሠራዊት ቢልክ እንኳን ይህ ይፈጸማልን) አለው፡፡
እግዚአብሔር የንጉሡን እምነት ማነሥ ተመልክቶ ምልክትን እንዲለምን ነገረው፡፡ ከጥልቁ ወይም ከከፍታውም ቢሆን ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ምልክትን ለምን አለው፡፡ ፀሐይን ዐሥር ዲግሪ ወደኋላ መመለስ፣ ጨረቃም በመንፈቀ ሌሊት እንዳያበራ ከዋክብትም መንገዳቸውን ይቀይሩ ዘንድ መለመን ይቻላል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ግን እግዚአብሔር ከሰማይ ከወረደበትና በሰው ልጆች መካከል ከተመላለሰበት ምስጢር ጋር ቢነጻጸር እዚህ ግባ የሚሉት አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አካዝን ያስደሰተህን ሁሉ ጠይቅ አለው፡፡ ጠይቅ የተባለው ምልክት ብቻ ቢሆን ቀላል ነበር፤ ነገር ግን ከዚህ በላይ የሆነ ስለሆነ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል ተባለ፡፡ ይህ ምልክት ድንግል በድንግልና የወለደችው በቤተ ልሔም ይሁዳ የተወለደ መድኅን ክርስቶስ ጌታ መድኃኒት ነው፡፡
ጌታ መድኃኒት/ሉቃ 2፥፲፩/
ስለመድኅን ክርስቶስ በመላእክት የተነገረው ነገር እጅግ ያስደንቃል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንደሚከተለው ተርኮታል፡፡ « በዚያም ሌሊት መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡ እነሆም የጌታ መልአክ ወደእነርሱ ቀረበ፤ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትንም ፈሩ፡፡ መልአኩም አላቸው እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ሆነ ተወልዶላችኋልና፡፡ ይህም ምልክት ይሆንላችኋል ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ፡፡ ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡´/ሉቃ 2፥፰-፲4/
ለስም አጠራሩ ምስጋና ይግባውና ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ጌታ መድኃኒት ያለውን ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ ኢየሱስ በማለት ጠርቶታል፡፡ ሁለቱም ከመላእክት ሰምተው ነው በዚህ ስም የጠሩት፡፡ ኢየሱስ ማለት ጌታ መድኃኒት እንደሆነ የአዲስ ኪዳን ቤተክርስቲያን ብቻ ሳትሆን በብሉይ ኪዳን ቤተክርስቲያንም ዘንድ ይህ ስም የታወቀ ነበር፡፡ ኢየሱስ የሚለው ስም በብሉይ ኪዳን ቤተክርስቲያን ዘንድ የታወቀ በአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን የተለየ ስም ነው፡፡
ኢየሱስ የሚለው ስም በአይሁድ ዘንድ የታወቀ እንደነበረ ታሪክ ጸሐፊው ዮሴፍ ወልደ ኮርዮን ይናገራል፡፡ በዚህ ስም የሚታወቁ ዐሥራ ሁለት ስሞችን ዘርዝሯል፡፡ አይሁድ ድኅነት ይፈልጉ ጠብቀውም ይሹት እንደነበረ ከስም አወጣጣቸው ይታወቃል፡፡ ልጆቻቸውን መድኃኒት በማለት ጠርተዋቸዋል፡፡ ምንም እንኳን የመሲሑን መምጣት ትንቢት የተናገሩ ከወገኖቻቸው ከአይሁድ ብዙዎችን ያለፉ ቢሆኑም እውነተኛ መድኃኒት ግን አልነበሩም፡፡ እውነተኛው መድኃኒት « በሥጋ ከዳዊት ዘር ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደው እንደ ቅድስና መንፈስ በኃይል የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ሆኖ የተገለጠው/ሮሜ 1፥4/´ መድኅን ክርስቶስ ጌታ ኢየሱስ ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን ዘመን ለምሳሌ ኢያሱ ማለት መድኃኒት ማለት ነበር፡፡ በዚህ ስም የተጠሩ ሁሉ ስሙ እንጂ አማናዊ የሆነው ኃይሉ በእነርሱ ዘንድ አልነበረም፡፡ አማናዊ ኃይል ያለው እውነተኛው መድኃኒት በተገለጠ ጊዜ ይህን ስም ብቻውን ይጠራበታል፡፡ የነገር ጥላው አማናዊ በሆነው ነገር ተተክቷልና «እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ይገባል´/ዮሐ፫፥፴/ የሚለውን የመጥምቁን ቃል ልብ ይሏል፡፡ እርሱ ብቻ ልዑል፥ መድኃኒት ነው፤ ሕዝቡንም ከኃጢአታቸው ፈጽሞ የሚያድናቸው ነው፡፡/ማቴ ፩፥፳፩/
ሌሎች መድኃኒት ተብለው ቢጠሩ የሰው ልጆችን ከዘላለማዊ ሞት መታደግ አልተቻላቸውም፡፡ ስለኃጢአታቸውም ተገብተው ደማቸውን አላፈሱላቸውም፡፡ እርግጥ ነው በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ ብዙ ቅዱሳን አጥንታቸውን ከስክሰዋል ደማቸውን አፍስሰዋል ለሕዝቡ ግን እውነተኛ ድኅነትን ማምጣት አልተቻላቸውም፡፡ እርሱ ግን እውነተኛ መድኃነት ጌታም ነው፡፡
ኢየሱስ የሚለው ስም ሊሠራ ያለውን የጽድቅ ሥራ ፈጽሞ ያሣየ ነው፡፡
ስም ግብርን ይገልጣልና መልአኩ « እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ´/ማቴ ፩፥፳፩/ በማለት እንደተናገረው ስሙ እንዲሁ ሆነ፡፡ እንደገናም ስሙ ክርስቶስ ነው፡፡ መሲሕ ማለት ነው፡፡ አዳኝ መድኃኒት የሚለው ስሙ ግብሩን ሰው የሆነበትን ፣በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የታየበትንም ምስጢር ይገልጣል፡፡ ለሰው ልጆች ድኅነት ያስፈለጋቸው ከኃጢአታቸው የተነሣ ነው፡፡ ኃጢአትን ባይሠሩ መድኃኒት ባላስፈለጋቸው ነበር፡፡ ኢየሱስ የሚለው የአምላካችንም ስም በምድር ላይ የታወቀ ባልሆነ ነበር፡፡ እንዲህ የሚለው የወንጌል ቃል የታመነ ነው፡-« ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደአባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ´/ገላ ፩/ ከዚህ ክፉ ዓለም ከኃጢአት ነፃ ያወጣን ዘንድ መሞት ነበረበት ለመሞት ደግሞ መወለዱ የግድ ነው፡፡ እኛን ሊያክል እኛን ሊመስል በእኛ ጎስቋላ ሥጋ ይገለጥ ዘንድ ይገባው ነበርና፡፡ኃጢአት ገዳይ መርዝ ነው፤ ነገር ግን መድኅን ክርስቶስ አሸንፎታል፡፡
ስለዚህ ከመድኅን ክርስቶስ ጋር ላለን ግንኙነት መሠረቱ ጽድቃችን ሳይሆን መርገማችን፥ መልካምነታችን ሳይሆን ክፋታችን ፥ መቆማችን ሳይሆን ውድቀታችን ነው፡፡ በተጎበኘንም ጊዜ በእኛ ዘንድ የተገኘው በጎነት ሳይሆን ክፋት ጽድቅ ሳይሆን ኃጢአት፥ ጸጋ ሳይሆን ከንቱነት ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደዚህ ዓለም መጣ የሚለው ቃል የታመነ ነው ይላል፡፡ ሐዋርያው ይሄን ሲል ከኃጢአት ቅጣት ሊታደገን እንደመጣ ያመለክታል፡፡ምንም እንኳን አእምሮአችን በኃጢአት ምክንያት ቢበላሽም ልቡናችን ቢጨልምም በኃጢአት ምክንያት ምውት ብንሆንም ክፋትን አስወግዶ በጎነትን ይሰጠን ዘንድ፥ ኃጢአትን አስወግዶ ጽድቅን ያለብሰን ዘንድ፥ የጨለመውን ልባችን በፍቅሩ ብርሃን ያበራልን ዘንድ፥ የሕያው የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ በእርግጥ ሰው ሆነ፡፡ በበረት ተወለደ፥ አድግና ላህም ትንፋሻቸውን ገበሩለት፥ የዐሥራ ዐምስት ዓመት ብላቴና ወሰነችው፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት በእርግጥም ያስደንቃል፡፡
የጌታ ሰው መሆን በጊዜው ጊዜ የተፈጸመ ነው
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይሄንን የክርስቶስን የቸርነት ሥራ እንዲህ በማለት በማያሻማ ቃል የገለጠው ነው፡- «ወአመ በጽሐ ጊዜሁ ፈነወ እግዚአብሔር ወልዶ ዘተወልደ እምብእሲት የዘመኑ መጨረሻ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ልጁን ወደ ዓለም ላከ´/ገላ ፬፥4/ በእርግጥም አበው ሰማያትን ቀድደህ ምነው ብትወርድ ፥ ተራሮች ምነው ቢናወጡ፤እሳት ጭራሮውን እንደሚያቃጥል፥ እሳትም ውኃውን እንደሚያፈላ፥ ስምህ ለጠላቶችህ ይገለጥ ዘንድ፥ አሕዛብም በፊትህ ይንቀጠቀጡ ዘንድ፡፡ ያልተጠባበቅነውን የጽድቅ ሥራህን በገለጥህ ጊዜ ወረድህ፥ ተራሮችም በፊትህ ተንቀጠቀጡ፡፡ሰዎች ከጥንት ጀምሮ ለሚጠብቁህ ከምትሠራላቸው ከአንተ በቀር ሌላ አምላክን አልሰሙም በጆሮአቸውም አልተቀበሉም፤ ዓይንም አላየችም፡፡/ኢሳ ፶፫፥፩-፬/ በማለት የመሰከሩለት በተስፋ የጠበቁት ትንቢት የተናገሩለት ሱባኤ የቆጠሩለት አምላክ የዘመኑ መጨረሻ በደረሰ ጊዜ ተገለጠ፡፡
ዓለሙ ያለ እርሱ ጨለማ ነበረ፡፡ በኃጢአትም የተያዘ፤ በኃጢአት ፈጽመን የተያዝን ከሆንን እምነት አይገኝብንም፡፡ የብሉይ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ስለዚህ ቀን ብዙ ጮኸች፡፡ ስለዚህ ቀን ደስታ ብዙ መከራን ተቀበለች፤ ትንቢት አናገረች፤ ሱባኤ አስቆጠረች፡፡ መድኀኒታችን ግን በጊዜው እንጂ ያለጊዜው አልመጣም፡፡ «ሳሕሉ ለእግዚአብሔር በጊዜሁ´ በማለት ነቢዩ ዳዊት እንደተናገረ፡፡ በእኛም ሕይወት እንዲሁ ነው፡፡ እግዚአብሔር የቸርነት፣ የምሕረት ሥራውን የሚሠራው በጊዜው እንጂ ያለጊዜው አይደለም፡፡ ስለዚህ ነው ቅድስት ቤተክርስቲያን ይህንን ጊዜ በቅዳሴው በሰዓታቱ በኪዳን ጸሎቱ፣ በጸበሉ፣በጾሙ እያራራች ወደ አምላካችን እንድንቀርብ እያበረታታች ጊዜውን እንድንጠብቅ የምታደርገን፡፡ ጌታችን ከጊዜው ቀድሞ ከጊዜውም ዘግይቶ አይመጣም፤ በጊዜው ጊዜ እንጂ፡፡ እርሱ ፈጽሞ ቀጠሮ አክባሪ ነው፡፡ ሰው የሆነው በፍጹም ቀጠሮው ጊዜ ነው፡፡ ጊዜው ረዘመ ብሎ አይዘነጋም፡፡
የጌታ ሰው መሆን ትንቢት የተነገረለት ሱባኤ የተቆጠረለት እንጂ እንዲሁ በድንገት የተከናወነ እንዳልሆነ እንመለከታለን፡፡ ብሉይ ኪዳን ይሄንን የሚመለከቱ ትንቢታትን የተመላ ነው፡፡ የሚወለድበት ሥፍራ፣ የሚወለድበት ጊዜ ፣የአወላለዱ ጠባይ አስቀድሞ የተነገረ ነው፡፡ ክርስቶስ በወሰነው ጊዜ በዚህ ዓለም ተገለጠ፤ የሆነው በእርሱ ፈቃድ በአባቱ ፈቃድ በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሆነ ነው፡፡ ሁሉን የሚያውቅ ጌታ የማንኛውንም ድርጊት ጌዜ እርሱ ወስኖታል፡፤ በሕይወታችን የሚከሰተው ማንኛውም ነገር በእርሱ ፈቃድ የሚከናወን በእርሱ ዘንድ ጊዜውም አስቀድሞ የታወቀ ነው፡፡ አንድም ነገር ያለጊዜው አይሆንም ከጊዜውም አንዲት ሴኮንድ እንኳን አይዘገይም፡፡ ፈቃዱ በተወሰነለት ጊዜ ይከናወናል ሊያፈጥነውም ሊያዘገየውም የሚቻለው ወገን የለም፡፡
የክርስቶስ ሰው መሆን ፍርሐትን ያራቀ ነው፡፡
የጌታ መልአክ ለእረኞች እንዲህ አላቸው፡-« እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ ሆነ ተወልዶላችኋልና´/ሉቃ 2፥፲/ መልአኩ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ምስራች አለ እንጂ ወንድ ሴት፣ ጥቁር ነጭ፣ ባሪያ ጨዋ አይሁዳዊ የግሪክ ሰው አላለም ፡፡ ዘር ነገድ ጎሳ አልተመረጠበትም፤ ጥሪው የተላለፈው ለሁሉም ነው፡፡ ምስራች ዜናው ለሕዝብም ለአሕዛብም ነው ለተቀበሉት ሁሉ የተደረገ ነው፡፡ መልአኩ እረኞችን አትፍሩ አላቸው፡፡እረኞች ወገን ከሆንን ያስፈራን ምንድነው) በኃጢአት መያዛችን አይደለምን፡፡ ስለዚህ ኃጢአታችን ያስወግድልን ዘንድ በርግጥ ሰው ሆነ፡፡ ስለዚህ ምን ያስፈራናል አምላካችን በመካከላችን ሳለ፡፡ አሁን ጌታ ተወልዶአልና ደስታችን እጥፍ ድርብ ነው፡፡
አማኑኤል በመካከላችን የሆነ ብቻ አይደለም ሰውን ወደ ቀደመ ክብሩ ይመልሰው ዘንድ የሰውን ባሕርይ ባሕርዩ ያደረገ ጭምር ነው እንጂ፡፡ አሁን አንድ ነገር እናውቃለን እግዚአብሔርን የሚያስቸግረው የኃጢአታችን ብዛት አይደለም ወደእርሱ ለመቅረብ የተከፈለልን ዋጋ ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናችን እንጂ፡፡ የተወለደው ሁሉን የሚችለው አምላክ ነው፡፡ ለዘላለም በሕይወት እንኖር ዘንድ አንድም እኛ ወደሰማይ መውጣት አለዚያም እግዚአብሔር እኛ ወደአለንበት ስፍራ መውረድ ነበረበት፡፡ ከዚህ ውጪ ከእግዚአብሔር ጋር የምንሆንበት ዕድል የለም፡፡ እኛ ወደ እርሱ ዘንድ መውጣት እንዳልተቻልን በተመለከተ ጊዜ እግዚአብሔር ይፈልገን ዘንድ እኛ ወደ አለንበት ስፍራ መጣ፡፡ በእርግጥም የእግዚአብሔር የቸርነት ሥራ ያስደንቃል፡፡
መላእክት ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን የምስራች ያሉት ቅዱስ ወንጌልን ነው፡፡ ክርስቶስ እግዚአብሔር ባይሆን ኖሮ ወንጌል የሚባል ነገር አይኖርም ነበር፡፡ ከጌታ ልደት አስቀድሞ ነቢያት ነበሩ፤ ነገር ግን እነዚህ ነቢያት እውነትን መመስከራቸው ብቻ ዓለም ከኃጢአት እስራት እንዲፈታ አላስቻለውም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለዓለሙ የሆነውን የምስራች እንዲያበስሩ የላካቸው ቅዱሳን መላእክት ጦር የታጠቁ ደገር የነቀነቁ አልነበሩም፡፡ ነገር ግን የሰላም ምልክት በሕፃኑ እጅ በበረት/በከብቶች ግርግም/ የተያዘ ነበር፡፡ ሰዎች እንደጠበቁት በነገሥታት እልፍኝ የተከናወነ አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ ራሱን ዝቅ አድርጎ ትሑት ሆኖ መጣ፡፡
አስቀድመን እንደተናገርነው ወደ ምስራቹ ቃል የቀረቡ ትጉ፣ ያላንቀላፉ፣ መንጋቸውን በጥንቃቄ ሲጠብቁ የነበሩ እረኞች መድኅን ክርስቶስን ያገኙት በበረት ነው፡፡ የተጠቀለለው በሐር ጨርቅ አልነበረም፡፡ ምድራውያን ነገሥታት ከሚደፉት ዘውድ አንዱን እንኳን አልደፋም የሰማይና የምድር ንጉሥ ሆኖ ሳለ፡፡ እንደ ድኃ የተጠቀለለው በጨርቅ ነው፡፡ የእናቱ ትሕትና ያስደንቃል፡፡ እናንተ ድኆች ሆይ ደስ ይበላችሁ ሀብታም ሳለ ክርስቶስ ስለእናንተ ደኃ ሆኗልና፡፡ እናንተ መሳፍንቶች የምድር ነገሥታት ሆይ ትውልዱ ሰማያዊ የሆነውን ተመልከቱት! በእንግዶች ማረፊያ እንዳልተገኘለት ተመልከቱ! የሰው ልጆች ሆይ እነሆ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ /ወልደ አብ ወልደ ማርያም/ አጥንቱ ከአጥንታችሁ ስጋው ከስጋችሁ የሆነ ዝቅ ዝቅ ያለበትን መጠን ተመልከቱ! ክርስቶስ የድኆች፣ የማይጠቅሙ የተናቁ ወገኖች ባልንጀራ ሆነ፤ ከቀራጮች ጋር ተመገበ፡፡
የክርስቶስ ልደት የደስታ ምንጭ ነው፡፡
የጌታ መልአክ ለእረኞቹ አላቸው« እነሆ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች እነግራችኋለሁና፡፡/ሉቃ 2፥፲/ በርግጥም የጌታ መልአክ ቃል ለሕዝቡ ሁሉ የደስታ ምንጭ እንደሆነ መመልከት ይቻላል፡፡ መድኃኒት ተወልዶላችኋልና፡፡ ምድራዊ ያይደለ ሰማያዊ የሆነ መድኃኒትን፡፡ በርግጥ የነፍሱን ሐኪም ሲያገኝ ደስታው ፍጹም የማይሆንለት ማነው) በኃጢአት እስር ቤት ያላችሁ ነፃ ሊያወጣችሁ መጥቷል፡፡ ቤተ ልሔም እውነተኛ የእንጀራ ቤት ሆነች፡፡ ቅዱሳኑ ሁሉ ደስ ይበላችሁ ስትጠብቁት የነበረ ተስፋ በእርግጥ እውን ሆኗልና፡፡ ደስታው በእረኞች ዘንድ ተጀመረ፤ ሕዝብና አሕዛብን አዳረሰ፡፡
የክርስቶስ መወለድ መላእክትን ያስደነቀ ነው፡፡
መላእክት በታች/በምድር/ በበረት በላይ/በሰማያት/ በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ቢመለከቱት አደነቁ፡፡ « እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡´/ሉቃ 2፥፲፬/ መላእክት የጌታን ልደት እንዴት አስቀድመው እንደሰሙ አናውቅም፤ ነገር ግን የጌታ መወለድ ዜና በሰማያውያን ዘንድ በደረሰ ጊዜ ምን ዓይነት መደነቅ እንደሚፈጠር መገመት እንችላለን፡፡
በርግጥም የማይወሰነው ተወስኖ መላእክት ሊያዩት የሚመኙት አምላክ የትሕትናን ሸማ ተጎናጽፎ በበረት መገኘት እጅግ ያስደንቃል፡፡ የጌታ ሕይወቱን ግርፋቱን ሞቱን ሲመለከቱ ምን ያህል ይደነቁ! በርግጥም ለዘመናት ተሰውሮ የነበረውን ይሔንን ታላቅ ምስጢር ተመልክቶ ሊደነቅ የማይችል ማን ይኖራል) ወደ ምድር በመጡና ወደ ቤተልሔም በቀረቡ ጊዜ ከሰው ልጆች ጋር በአንድነት ዘመሩ፡፡ ዘላለማዊው ሕፃን ሆኖ ዘመን ሲቆጠርለት አደነቁ፤ ፍጥረታትን የተሸከመ እርሱ በእናቱ ጀርባ ታዝለ ፡፡
ፍጥረታትን የሚመግብ እርሱ የእናቱን ጡት ተመገበ፡፡ ሁሉን በቃሉ የፈጠረ እርሱ ፍጥረታትንም የተሸከመ ደካማ ስጋን ባሕርዩ አድርጎ እናቱ ተሸከመችው፡፡ በሕፃን መጠንም ተወለደ፡፡ የነገሥታት ንጉሥ መሆኑን የምትገነዘቡ ወገኖች አድንቁ! ደኃ ሆኖ ትመለከቱታላችሁ፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዲህ በማለት ያደንቃል፡- « የዕብራውያን ጌታ ከዕብራዊት ድንግል ተወለደ፥ ሐዋርያቱን በሰባ ሁለት ቋንቋ ያናገረ፥በሰናዖር የአሕዛብን ቋንቋ የተበተነ ቋንቋ እንደማያውቅ ሰው እናቱ በምትናገርበት ልሳን የዕብራውያንን ቋንቋ አፉን ፈታ፤ ይህንንም ቋንቋ እየተናገረ አደገ´፡፡
አዲስ የተወለደው ንጉሥ ወዴት ተኛ) የወርቅ ፍራሽ ከዝሆን ጥርስ የተሠራ አልጋ ተዘጋጀለትን) በቄሣሮች ቤተ መንግሥት የተሻለ ክፍል ሰጡትን) አይደለም፡፡ መድኅን ክርስቶስ የተኛው በከብቶች ግርግም ነው፡፡ ከብቶች በሚመገቡት በረት ንጉሡ ክርስቶስ ተኛ፡፡ ክፉ ሰዎች በረትም ማደሪያ ሆኖ ረጅም ጊዜ በዚያ ይቀመጥ ዘንድ አልፈቀዱለትም፡፡ ክፉ ሰዎች እነርሱ ባማረ ቤት ባማረ ኑሮ እየኖሩ ዕረፍት የሚነሣቸው የድሆች ተረጋግቶ መቀመጥ ነው፤ እነርሱን ሳያሳድዱ ወይም ጨርሰው ሳያጠፉ እንቅልፍ የላቸውም፡፡ አይሁድ በጌታ ላይ የፈጸሙት ተመሣሣይ ነገርን ነው፡፡ እናቱ ሕፃኑን ይዛ ወደ ግብፅ ተሰደደች፡፡ በእንግድነት አገር እንግዳ ሆነ፡፡ ከስደት ከተመለሰ በኋላ በናዝሬት አደገ፡፡ መላእክት በዚህ ሁሉ ነገር የሚደነቁ አይመስላችሁም አሳዳጁ ሲሳደድ የትሕትናውን ወሰን ተመልከቱ!
የክርስቶስ መወለድ የሰው ልጆች ሁሉ አድናቆት ነው፡፡
መላእክት በጌታ ልደት ከተደነቁ የሰው ልጆችማ በዚህ ታላቅ ምስጢር ምን ያህል እጹብ እጹብ ማለት ይገባቸው ይሆን) እግዚአብሔር የበደሉ የሰው ልጆች ቃሌን ተላልፈዋልና እንደወጡ ይቅሩ ይጥፉ አላለም፡፡ ለድኅነታቸው የሚሆን አስደናቂ የድኅነት መንገድን አዘጋጀ፡፡ የማዳን ሥራውን እርሱ የሚፈጽመው እንጂ ለፍጡር የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ፍጡር ይህን ማድረግ የሚቻለው አይደለምና፡፡ ስለዚህም ነው የሰው ልጅ አምላክ በሆነ በክርስቶስ ደም እንጂ በፍጡር ደም ሊድን ያልተቻለው፡፡ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ቄርሎስ፡፡ «እኛ በጸጋ አማልክት ነን ክርስቶስን ከባሕርይ አምላክነት የሚያሳንስ አንዳችም ነገር አውርዶ ከእኛ ጋር ስለሚያስተካክለው አዳኛችን መሆን አይቻለውም´ ይላል፡፡
ስለዚህ ጌታና መድኃኒት ንጉሥም የሆነ እርሱ ተበድሎ እርሱ የሚክስ ሆነ፡፡ ይኼንን ማድረግ የሚቻለው ከእርሱ በቀር ሌላ ስለሌለ አምላክ ስጋን ተዋሓደ፡፡ በርግጥ ራሳችንን ብንመረምር እግዚአብሔር ይሄንን ያህል ይወድደን ዘንድ ራሱንም ለመስቀል ላይ ሞት አሳልፎ ይሰጥልን ዘንድ የሚያደርግ አንዳች ነገር በእኛ ላይ እንደሌለ ትገነዘባላችሁ፡፡ እግዚአብሔር አብዝቶ ቢጠራን አጥብቀን ከፊቱ የሸሸን ወገኖች ነን፡፡/ሆሴ፲፩፥፩/
የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን!