የአርባ ምንጭ ማዕከል ሐዊረ ሕይወት አካሄደ

alt

በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን አርባ ምንጭ ማዕከል የተዘጋጀው ልዩ መንፈሳዊ የጉዞ መርሐ-ግብር “ሐዊረ ሕይወት” የሕይወት ጉዞ ታህሳስ 24/2008 ዓ/ም ወደ ምዕራብ አባያ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተደረገ፡፡


“በዚህ ዓመት ለ2ኛ ጊዜ የተደረገ የሕይወት ጉዞ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ እና አካባቢዋ የሚኖሩ ከ900 በላይ ማኅበረ ምእመናን ተሳትፈውበታል፡፡ ይህ ታላቅ መንፈሳዊ የሕይወት ጉዞ በወርኃ-ታኅሣሥ ጾመ ነቢያት ወቅት መደረጉ ምእመናን በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲበረቱና በገጠር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን ሁለንተናዊ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲደግፉ ለማድረግ ነው” በማለት የጉዞው አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሥራት ገዛኸኝ ገልጸዋል፡፡ alt
መርሐ-ግብሩ በሁለት ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት ተወካይ በጸሎት ተከፍቷል፡፡ በጠዋቱ ምዕራፍ የወንጌል ትምህርትን አስከትሎ ምዕመናን በታላቅ ናፍቆት የሚጠብቁት ምክረ-አበው ክፍል አንድ በጎንደር መንበረ መንግሥት መድሃኔ ዓለም ጉባኤ ቤት መምህር የሆኑት መምህር በጽሐ ዓለሙ እና ከደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት በተጋበዙ መምህር ኃይለማርያም ዘውዱ አማካኝነት ምእመኑ ማብራሪያ በሚሻባቸው ርእሶች ዙሪያ ጥልቅ የነገረ ሃይማኖት ትንተና አድርገዋል፡፡ መምህራኑ በዋናነት ለቅዱሳን፣ ጻድቃን እና ሰማዕታት የምንሰጠው ክብርና አማላጅነታቸውን፤ ስለ ጾም፣ ጸሎትና ስግደት ከቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አንጻር ቅዱሳት መጻህፍትን አጣቅሰው አመስጥረው አስተምረዋል፡፡ በምዕራፍ ሁለት የከሰዓቱ መርሐ-ግብር ደግሞ መምህራኑ በወቅታዊ የቤተክርስቲያን ፈተናዎች፣ የተሐድሶ አራማጆች ግራ በሚያጋቧቸው የኑፋቄ አስተምህሮዎች ዙሪያ፣ የጸበል ሥርዓትን በተመለከተ እና በጋብቻ ላይ ለምእመኑ የሕይወት ስንቅ ይሆን ዘንድ በስፋት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ ሥርዓት መክረዋል፤ አስተምረዋል፡፡alt በሌላ መልኩ የአርባ ምንጭ ማዕከል የበገና ተማሪዎች ነፍስን በሚያለመልም ዝማሬ እግዚአብሔርን ያመሰገኑ ሲሆን፤ በ2007 ዓ/ም በጋሞ ጎፋ ሀ/ስብከት፣ በኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነትና በማኅበረ ቅዱሳን ትብብር ተጠምቀው የመንፈስ ቅዱስን ልጅነት ያገኙት የጉኛራና ኮልሜ አዳዲስ ተጠማቂያን በተጋባዥ እንግዳነት መርሐ-ግብሩን ተሳትፈዋል፡፡ እንግዶቹም ከተቋቋመ አንድ ዓመት እንኳን ያልሞላው የሰንበት ት/ቤት በኮንስኛና በአማርኛ መዝሙር በማቅረብ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ በተያያዢነት ተጓዡ ምዕመን የደብሩን አጸደ ሕጻናት ትምህርት ቤት የመናፍቃን ጫና እና የዐቅም ውስንነት ለመቅረፍ ከ7000 ብር በላይ ሰብስቦ በዕለቱ ድጋፍ አድርጓል፡፡ በመጨረሻም ምእመኑ ይህ መሰሉ የሕይወት ጉዞ በተደጋጋሚ ወደተለያዩ ቅዱሳት መካናት መዘጋጀት እንዳለበትና ምአመኑም በሚችለው ሁሉ ከማኅበሩ ጋር አብሮ ለመሥራት ተነሳሽነቱን አሳይቷል፡፡ በመሆኑም 3ኛው ሐዊረ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በዚሁ ዓመት ወርኃ ሚያዝያ ውስጥ ወደ ዶርዜ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እንደሚደረግ የጉዞ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
ታህሳስ 25/2008 ዓ/ም