የሩቅ ምሥራቅ ግንኙነት ጣቢያ ሐዊረ ሕይወት አካሄደ !

6

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን የሩቅ ምስራቅ ግንኙነት ጣቢያ ከዐስራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ወደ አስተማረበት ደቡባዊ ሕንድ ኬረላ ግዛት ከታህሣሥ 17 እስከ 25 ቀን 2008 ዓ.ም የሐዊረ ሕይወት ጉዞ አካሂዷል፡፡

በዚህ መንፈሳዊ ጉዞ በሕንድ የተለያዩ ግዛቶች ከኒው ደሊህ፣ሮርኪ፣ ፐንጃቢ፣ ፑኔ ፣ ሙምባይ ፣አንድራ እና ባንግሎር የሚማሩ እና የሚኖሩ ምእመናን በባቡር ከ 10 እስከ 48 ሰዓት ተጉዘው ተሳታፊ ሆነዋል ፡፡በጉዞው ላይ ኤርትራውያንም ተሳትፈዋል።

የሐዊረ ሕይወት ተሳታፊዎችም ቅዱስ ቶማስ በመጀመርያ መቶ ክፍለ ዘመን የሥራቸዉን አብያተክርስቲያናት የአጽሙ ክፍል ያለበትን ቤተክርስቲያን ፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የልብሷ ክፋይ ያለበትን ቤተክርስቲያን ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የአጽሙ ክፋይ ያለበት ቤተክርስቲያንን ፣ ቅዱሳን አባቶች እና እናቶች የጸለዩባቸዉን ገዳማትና አድባራት፣ የህፃናት ማሳደጊያ ማዕከላትን፣ በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱ ሰዎች ማገገሚያ ማዕከልን፣ 200 ዓመት ያስቆጠረዉን ሴሚናሪ(Seminary) መንፈሳዊ ኮሌጅ እና የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክን ƒƒƒ‚በመጎብኘት የበረከቱ ተሳታፊ መሆናቸውን የሩቅ ምሥራቅ ግንኙነት ጣቢያ ያደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}../ruqemeseraqe{/gallery}

በሐዊረ ሕይወት ጉዞም የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የማር ጎርጎርዮስ የተማሪዎች ማኅበር ፕረዘዳንት እና የቦምቤ ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ አባ ቄርሎስ (His Grace Geevarghese Mar Coorilos Metropolitan of Bombay Diocese and Presedant of Mar Gregorios Orthodox Christian Student Movement) ከመጀመሪያ አንስቶ ጉዞው እንዲሳካ በመጸለይና በሀሳብ በመርዳት በመጨረሻም ሀገረ ስብከታቸው ከሚገኝበት ማራሽትራ ግዛት ከሙምባይ ከተማ ተነስተው 1600 ኪ.ሜ በመጓዝ መንበረ ፕትርክናው ከሚገኝበት ኬረላ ግዛት ኮታይም ከተማ ከታህሣሥ 19 እስከ 22 2008 ዓ.ም ድረስ በቦታው በመገኘት ለጉዞው መሳካት ሁኔታዎችን በማመቻቸት እና ከተጓዦች ጋር በየዕለቱ በመገኘት በአባታዊ ምክር እንዲሁም ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት እና የህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተሐድሶ መናፍቃን ስለደረሰባት ከፍተኛ ፈተና ገላጻ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በጉባኤው ላይ መዝሙር እና ወረብ በየአብያተክርስቲያናቱ ገዳማት እና መንፈሳው ኮሌጆችተማሪዎች የቀረበ ሲሆን የተጓዦችን ሕይወት የሚያንጹ ትምህርቶች በተለይም ስለመንፈሳዊነት እና ወጣትነት ውይይት ስለቤተክርስቲያን ወቅታዊ ፈተናዎችና መፍትሔዎቻቸው እንዲሁም ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ገለጻና ውይይት ተደርጓል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሁለቱ አብያተክርስቲያናት የወጣት ተማሪዎች ኅብረትን ለማጠናከር ሲባል በሊቀ ጳጳስ አባ ቄርሎስ በተደረገ ግብዣ ከታህሣሥ 15 እስከ 16 ቀን 2008 ዓ.ም ከማኅበረ ቅዱሳን የሩቅ ምሥራቅ ግንኙነት ጣቢያ የተወከሉ አባላት በ107 ኛው የማር ጎርጎርዮስ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ወጣቶች ሀገር አቀፍ ስብሰባ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በመጨረሻም የሕንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ባስልዮስ ማርቶማ ጳዉሎስ ዳግማዊ (Baselios Marthoma Paulose II Catholicos of the East and Malankara Metropolitan Malankara Orthodox Syrian Church) ለተጓዦች ባደረጉት ግብዣ በመንበረ ፓትርያርክ በመገኘት ለቅዱስነታቸው የኢትዮጵያዊዉን የዜማ ሊቅ የቅዱስ ያሬድ ሥዕል እና ታሪኩን የያዘ ጥራዝ የተበረከተላቸው ሲሆን ተሳታፊዎች በቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርጎ ስለሕንድ ቤተክርስቲያን ሰፊ ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን ቅዱስነታቸውም ስለ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን እና ስለ ሕንድ ቤተክርስቲያን ገለጻ በማድረግ ለተጓዦች ጸሎትና ቡራኬ በመስጠት የዕለቱ መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡ በእግዚአብሔር መልካም ፍቃድ ተሳታፊዎችወደ መጡበት ቦታ ከታህሳስ 23 እስከ ታህሳስ 25 2008 ዓ.ምባሉት ጊዚያት በመኪና፣በባቡር እና በአውሮፕላን በመጓዝ በሠላም ተመልሰዋል፡፡