ማኅበረ ቅዱሳን በሰሜን አሜሪካ ሜኖሶታ ሁለት ከተሞች የኦሮምኛ ቴሌቪዥን ሥርጭት ጀመረ

ሚያዚያ 11 ቀን 2008 ዓ.ም

ከአሜሪካ ማእከል

ማኅበረ ቅዱሳን በሰሜን አሜሪካ ሜኖሶታ ውስጥ በሚገኙ በሚኖፖሊስ እና በቅዱስ ጳውሎስ /Minneapolis & Saint Paul/ ሁለት ከተሞች ከሚያዚያ 9 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ሥርጭቱን ማስተላለፍ መጀመሩን የአሜሪካ ማእከል ገለጸ፡፡

የቴሌቪዥን ሥርጭቱ በየሳምንቱ እሑድ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት /Sunday at 4:00 PM USA Central time/ በቻናል 75 የሚተላለፍ ሲሆን ምእመናን መርሐ ግብሩን እንዲከታተሉ ማእከሉ አስታውቋል፡፡

በተያያዘ ዜና በአሜሪካ የሜኖፖሊስ ማእከል ሚያዚያ 8 እና 9 ቀን 2008 ዓ.ም ጉባኤ ማካሔዱን የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

01admaa

አዳማ ማእከል የሐዊረ ሕይወት አካሔደ

መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም

ከአዳማ ማእከል

01admaaበማኅበረ ቅዱሳን የአዳማ ማእከል ለ4ኛ ጊዜ ያዘጋጀውን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በመቂ ግራዋ ጃዌ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም አካሔደ፡፡

መርሐ ግብሩ በደብሩ ሊቀውንተ ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን በማእከሉ መዝምራንና በቀሲስ ምንዳየ ብርሃኑ መዝሙር ቀርቦ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት ዓላማ(ተልዕኮ) ያለው ክርስቲያን€ በሚል ርዕስ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

በምክረ አበው መርሐ ግብር ከምእመናን የተሰበሰቡ ጥያቄዎችን መሠረት አድርጎ በተሐድሶ እንቅስቃሴ ላይ የምእመናንና የሊቃውንት ድርሻ፤ ገድላትና ድርሳናት ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ያላቸው አገልግሎት፤ ሉላዊነትን እንዴት መቋቋም ይቻላል፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን ያደረገችው አስተዋጽኦ፣ . . . አስመለክቶ በዲ/ን ዳንኤል ክብረት እና ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ መልስ ተሰጥቶባቸው የጠዋት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

ከሰዓት በኋላ በተከናወነው ቀጣይ መርሐ ግብር በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ጌታ ሆይ አድነኝ ብሎ ጮኸ€ በሚል ርዕስ የወንጌል ትምህርት፣ በመቂ ግራዋ ጃዌ አቡነ ገብረ መንፈስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በተከታታይ ቀርበዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ በግንባታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከምእመናን የ27 ሺሕ(27000) ብር ድጋፍ ተደርጓል፡፡

01ejersa

ማኅበረ ቅዱሳን የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በኤጄርሳ ለፎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ያካሒዳል

መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

01ejersaማኅበረ ቅዱሳን መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በደንዲ ወረዳ በሚገኘው ኤጀርሳ ለፎ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚያካሒደው 10ኛው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ከዚህ በፊት ከተካሔዱት በተሻለ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡

የማኅበሩ ሐዊረ ሕይወት አዘጋጅ ኮሚቴ ከሀገረ ስብከቱና ከሚመለከተው የቤተ ክርስቲያኑ ሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊውን ቅደመ ዝግጅት  ሲሆን ትኬቱን በብር 200.00 በማሠራጨት ላይ ይገኛል፡፡

የትኬት ሽያጩም መጋቢት 7 ቀን 2008 ዓ.ም የሚጠናቀቅ በመሆኑ ከተጠቀሰው ቀን በኋላ ማስተናገድ እንደማይቻል የገለጸው ኮሚቴው ምእመናን 5 ኪሎ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አጠገብ በሚገኘው በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ትኬቱን ቀደም ብለው መግዛት እንደሚችሉ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

የኤጄርሳ ለፎ ደብረ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አቅጣጫ የአዲስ ዓለም ማርያም ገዳምን አልፎ እሑድ ገበያ ከተባለው የገጠር ከተማ ወደ ውስጥ ሦስት ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ በግምት ከአዲስ አበባ በ65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

ኤጄርሳ ለፎ በደብርነት የተተከለው በ1830 ዓ.ም ቢሆንም ታቦቱ ግን ከዚያ ቀደም ብሎ ከምንጃር እንደመጣ ይነገራል፡፡ ኤጄርሳ ለፎ የኦሮምኛ ቃል ሲሆን ትርጉሙም የመንገደኞች/እግረኛች/ ወይራ ማለት ነው፡፡ ከአዲስ አበባ ወለጋ፣ ከወለጋ አዲስ አበባ ለሚመላለሱ መንገደኞች እንደ ማረፊያ የሚያገለግሉ በርካታ የወይራ ዛፎች የሚገኙበት ቦታ ስለነበር ስያሜውን እንዳገኘ የአካባቢው ተወላጆች ይገልጻሉ፡፡

በ1931 ዓ.ም ከማዕጠንት በወደቀ ፍም የሣሩ ጉዝጓዝ ተያይዞ ቤተ ክርስቲያኑ የተቃጠለ ሲሆን፣ በቃጠሎው ከላይ ያለው ጉልላት ሲወድቅ ታቦቱ ላይ አርፏል፡፡ ነገር ግን ታቦቱ ከቃጠሎው በእግዚአብሔር ቸርነት ተርፏል፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ በርካታ ንዋያተ ቅድሳትና የብራና መጻሕፍት ያሉት ሲሆን የሚቀመጡበት ቤት በመፍረሱ በአደጋ ላይ ይገኛል፡፡

02afarr

የአፋር ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ጽሕፈት ቤትና የእንግዳ ማረፊያ ተመረቀ

መጋቢት 2 ቀን 2008 ዓ.ም

ከሎጊያ ማእከል

02afarr

በአፋር ሀገረ ስብከት በሠመራ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኘው የመንበረ ጵጵስና ጽሕፈት ቤትና የእንግዳ ማረፊያ በብፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የካቲት 6 ቀን 2008 ዓ.ም ተመረቀ፡፡

01aafarr

የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የሀገረ ስብከቱ ዓመታዊ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከየካቲት 5-6 ቀን 2008 ዓ.ም በሎጊያ ደብረ ማኅቶት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በሐመረ ኖኅ ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ በመከናወን ላይ እያለ ሲሆን የመንበረ ጵጵስናውን የግንባታ ሥራ ክንውን አስመልከቶ ገለጻ ተደርጓል፡፡

03afarr

ብፁዕነታቸውም በሥራው ላይ ለተሳተፉ ባለሙያዎች፣ የሀገረ ስብከቱ ልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎችና ሠራተኞችን፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሓላፊዎችንና ሠራተኞችን እንዲሁም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማበርከት ላይ ለሚገኙ ማኅበራትና ምእመናን ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው የካቲት 5 ቀን 2008 ዓ.ም ጠዋት በ2፡30 በብፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጉባኤው በጸሎተ ቡራኬ ተከፍቷል፡፡ ጉባኤው በሁለት ቀናት ውሎው የሚነጋገርባቸውን አጀንዳዎች እና የሀገረ ስብከቱ የ2007 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ዘገባ በመጋቤ ሥርዓት መሠረት ስዩም የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸው ጸድቀዋል፡፡ ቀጥሎም በሀገረ ስብከቱ ውስጥ የሚገኙት የአምስቱ ወረዳ ቤተ ክህነቶች የ2007 ዓ.ም የዕቅድ አፈጻጸም ዘገባ በተወካዮቻቸው አማካይነት አቅርበው ጉባኤው ተወያይቶባቸዋል፡፡

04afarrከመንበረ ጵጵስና ጽሕፈት ቤትና የእንግዳ ማረፊያው ምረቃ ቀጥሎም የማኅበረ ቅዱሳን ሎጊያ ማእከል የ2007 ዓ.ም የዕቅድ ክንውን፣ እንዲሁም ማእከሉ ያዘጋጀውን የሀገረ ስብከቱ የ20 ዓመት ሐዋርያዊ ጉዞ ረቂቅ ጽሑፍ ሰነድ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፣ የ20 ዓመት ሐዋርያዊ ጉዞውን በማስመልከት ዐውደ ርእይ ቀርቦ ለጽሑፉ ግብዐት የሚሆኑ ውይይቶች ተካሒደዋል፡፡

በዐውደ ርእዩ ከዚህ ቀደም የአፋር ሀገረ ስብከትን በመምራትና በማስተዳደር የሚታወቁት ሊቃነ ጳጳሳት፣ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ዮናስ ወደ ሀገረ ስብከቱ ከመጡ በኋላ ያከናወኗቸውን መንፈሳዊ አገልግሎት እና ልማት ተዳስሰዋል፡ በዓመቱም ጥሩ ውጤት ላስመዘገቡ ወረዳ ቤተ ክህነቶች፣ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ ለሎጊያ ማእከልና ሰንበት ትምህርት ቤቶች የምሰክር ወረቀት ተሰጥቶ የጉባኤው የአቋም መግለጫ ከተነበበ በኋላ በብፁዕነታቸው ቡራኬና ጸሎት ተጠናቋል፡፡

በጉባኤው ላይ የሀገረ ስብከቱ የሥራ ሓላፊዎች፣ የወረዳ ቤተ ክህነት ሊቃነ ካህናት፣ የየአጥቢያው ተወካዮች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች፣ የሎጊያ ማእከል ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

01aba natn

የብፁዕ አቡነ ናትናኤል የሕይወት ታሪክ

የካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም

€œቤተ ክርስቲያን አስተምራኛለች፡፡ ውለታዋን ከፍዬ አልጨርሰው /ብፁዕ አቡነ ናትናኤል/

01aba natnብፁዕ አቡነ ናትናኤል በምሥራቅ ትግራይ ክለተ አውላሎ አውራጃ አውዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ከአቶ ገብረ ሕይወት ፀዓዱ እና ከወይዘሮ ወለተ ክርስቶስ ግብረቱ ግንቦት 12 ቀን በ1923 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ወላጆቻቸው ልጆችን እየወለዱ ይሞቱባቸው ስለነበር በጭንቀት ውስጥ ሳሉ ነው ብፁዕነታቸው የተወለዱት፡፡

አባታቸው ገና በጨቅላነታቸው በመሞታቸው እናታቸው በስስት አሳደጓቸው፡፡ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ያጡት እናትም የሁሉም ምትክ የሆኑት ልጃቸውን ካሳዬ ብለው ስም አወጡላቸው፡፡ ትንሹ ካሳዬም የእናታቸውን ፍቅር ሳይወጡ፣ እናትም የልጃቸውን ስም ጠርተው፣ በዓይናቸው ዓይተው ሳይጠግቡ በልጅነታቸው በማረፋቸው ከእህታቸው ጋር መኖር ጀመሩ፡፡

የእህታቸው ፍላጎት ከብት እንዲጠብቁ፤ ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳም ሲደርስም በሕግ በትዳር ተወስነው እያረሱ በግብርና ኑሯቸውን እንዲገፉ ነበር፡፡ የካሣዬ ሐሳብ ደግሞ ከአድማስ ማዶ ነበር፡፡ ከሊቃውንቱ እግር ሥር ቁጭ ብሎ መማር፣ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል፣ ጉባኤ አስፍቶ ወንበር ዘርግቶ ማስተማር፡፡

ትምህርት

ብፁዕነታቸው አባቴ በጣም መንፈሳዊ ሰው ነበሩ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ አባታችን እያሉ ይጠሩኛል እኔ ግን ደስ አይለኝም ነበር፡፡ መምህሬ ስለ እኔ ትንቢት ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ትልቅ አባት ይሆናል ብለው ይናገሩ እንደነበረ ነግረውኛል፡፡ በወቅቱ እኔ ልጅ ስለነበርኩ ያንን አላስታውሰውም€ ሲሉ ያናገራሉ፡፡

የትምህርት ፍላጎታቸውን ለመወጣት ወደ ከኔታ ወልደ ገብርኤል ዘንድ በመሔድ ድርባ አቡነ አሳይ ቤተ ክርስቲያን ንባብና የቃል ትምህርት ጀመሩ፡፡

የኔታ ሰሎሞን የሚባሉ የአቋቋም መምህራቸው ያላቸውን የትምህርት ፍላጎት በመረዳት፣ ነገ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ሆነው ስለታዩአቸው ወደ ሌላ ሔደው እንዳይሰናከሉ በማሰብ ከእርሳቸው ዘንድ እንዲማሩ ስለሚፈልጉ ርቀው ወደ ቆሎ ትምህርት ቤት እንዳይሔዱ አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ሦስት ዋስ አስጠርተዋቸዋል፡፡

እሳቸው ግን ልባቸው ለትምህርት አድልቷልና ተጨማሪ ትምህርት ለመቅሰም ከመምህራቸውና ከቤተሰቦቻቸው ተደብቀው በጥንቱ ቆሎ ተማሪ ልማድ ስማቸውን ቀይረው ጎጃም /በጌምድር/ ትምህርትን ፍለጋ ተሰደዱ፡፡ በቆሎ ት/ቤትም €œመዓዛ ቅዱሳን€ ተብለው ተጠሩ፡፡

ወደ ጎንደር እና ጎጃም ተሻግረው ከየኔታ ኃይሉ ስሜ በየላ ኢየሱስ፣ ከየኔታ መኮንን ላስታ አመራ ማርያም ከእነዚህ ከሁለቱም ጾመ ድጓና ምዕራፍ ከተማሩ በኋላ እንደገና ወደ ቅኔ ቤት ገቡ፡፡ ክህነት የተቀበሉትም ሁለት ጊዜ ምዕራፍና ጾመ ድጓ ዘልቀው፣ ቅኔ ዘይእዜ ከቆጠሩ በኋላ ነበር፡፡

በደቡብ ጎንደር እና ወሎ ተዘዋውረውም በጉባኤ ቤቶች የዜማ፣ የአቋቋም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ወረዳ ደረስጌ ማርያም አቅንተውም ከየኔታ መንበሩ ዘንድ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ እንዳቤት ወረዳ በሸሜ ጊዮርጊስ ደብር ከመምህር ጥበቡ ቅኔ ተመምረወዋለል፡፡

ክህነት

02aba natnቅኔ ቤት ገብተው ከየኔታ መንበሩ ደረስጌ ሰሜን ጃና አሞራ ገብተው ሲማሩ ዘመዳቸው ምሶሶ ታቃፊ ሆነህ እንዳትቀር ዲቁና አትቀበል€ ያላቸው ትዝ እያለቸው ዲቁና የተቀበሉት ካደጉና ከተማሩ በኋላ ነው፡፡

ከጎንደር ሸዋ/አዲስ አበባ/ ድረስ በእግራቸው ተጉዘው በመምጣት በሚያዚያ ወር በ1938 ዓ.ም በአዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ከአቡነ ይስሐቅ ዲቁና ተቀብለዋል፡፡

የቅኔ ዕውቀታቸውን ለማስፋትም ከአዲስ አበባ ስማዳ ወረዳ ደብረ ዕንቁ በማምራት ከታላቁ ሊቅ ከየኔታ ጌጡ ተሰማ ዘንድ ተምረዋል፡፡

የብሉይ ኪዳንና ዐራቱን ብሔረ ነገሥት፤ አምስቱን ብሔረ ኦሪትና ዳዊት ትርጓሜን ተምረዋል፡፡

አቡነ ባስልዮስ በጾመ ፍልሰታ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይዘዋቸው በመሔድም ውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም እየተረጐሙ እዚያው ከርመው ሦስቱን ታላላቅ ማዕርጋት ቅስና፣ ምንኩስና ቁምስና፣ በ1953 ዓ.ም ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ተቀብለዋል፡፡

በ1941 ዓ.ም ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመማር አዲስ አበባ በሚገኘው የታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ገብተው ሐዲሳትን በመጀመሪያ ከመጋቤ ሐዲስ ወ/ሚካኤል፣ ከመ/ር ገብረ ማርያም ዓለሙ፤ ቅዳሴ ማርያምና ውዳሴ ማርያም ከመምህር ይሔይስ፣ ኪዳን፣ ትምህርተ ኅቡአት ከመምህር ከየኔታ ገ/ማርያም፣ ከመምህር ገ/ሕይወት ነገሥታቱ ፍርድ የሚሰጡበትን ፍትሐ ነገሥት ተምረዋል፡፡

ቀን እየተማሩ ከበታቻቸው ያሉትን ተማሪዎች እያስተማሩ ቆይተዋል፡፡ የመጻሐፍት ተማሪ ሆነው መጻሕፍተ ሐዲሳት፣ ኪዳን፣ ትምህርተ ኅቡአት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ ማርያም፣ ቀን እየተማሩ ሌሊት ከማቴዎስ ወንጌል ጀምሮ እስከ ራእየ ዮሐንስ መጨረሻ ድረስ እንዲሁም ትርጓሜ ፍትሐ ነገሥትን በእጃቸው ጽፈዋል፡፡

መዝሙረ ዳዊት ትርጓሜን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፊት እንዲተረጉሙ ተፈቅዶላቸው በሚገባ በመወጣታቸው ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡

ዓላማቸው በተመረቁበት በሐዲሱ ተማሪ አብዝተው ጉባኤ አስፍተው ማስተማር ነበር፡፡ ነገር ግን በቅድስት ሥላሴ መምህራን ማሠልጠኛ ዕድል አግኝተው ለሁለት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡


ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ወደፊት ጵጵስና የሚሾሙ ሰዎች ውጭ አገር ሔደው የውጭውን ትምህርትና ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ለአቡነ ባስልዮስ አሳሰቧቸው፡፡ ሰዎች ሲመረጡም በንጉሡ አማካይነት ተጠቁመው ውጪ አገር ከሚሔዱት መካከል አንዱ ሆኑ፡፡

አባ መዓዛ- ቅዱሳን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት በቂ ችሎታ አላቸው ከሚባሉ መምህራን አንዱ ናቸው፡፡ እኒህ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ዕውቀታቸቸውን በበለጠ በዓለም አቀፍ ቋንቋ ለማሻሻል ባላቸው ፍላጎት መሠረት ወደ ኢየሩሳሌም አንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ሴንት ጆርጅ ኮሌጅ ተላኩ፡፡ ወደፊት ጵጵስና የሚሾሙ ብለው ጃንሆይ በተናገሩት መሠረት የኤጲስ ቆጶስነት ትምህርት እንዲማሩና እንዲሠለጥኑ ነበር የተላኩት፡፡ ሁለት ዓመት ተኩል የቤተ ክርስቲያን ታሪክና አስተዳደር /Church History and Adminstration/ ተምረው ተመለሱ፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ወደ እንግሊዝ አገር ኦክስፎርድ ኦስሄትሮፕ የሚባል የካቶሊክ ኮሌጅ በ1961 ዓ.ም ተልከው በእንግሊዝ አገር ለዐራት ዓመታት ትምህርታውን ተከታትለው በፍልፈፍና /Bachelor of Dignity Basic Philosophy Supermental and Developmental Phsycology/ ዲግሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡

ከአገርና ከቤተ ክርስቲያን የተቀበሉትን ታላቅ አደራ አክብረው አገራቸውን ለማልማት በውጭ አገር የቀሰሙትን ሥልጣኔ እና ልምድ ለአገራቸው የሚያውሉ ምሁራን በርካታ ናቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ሊቃውንት መካከልም አንዱ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው በምዕራቡ ዓለም በትምህርት ዓለም ቆይታቸው በትምህርትና በልምድ ያካበቱትን ዕውቀት በተግባር ላይ ለማዋል የቻሉ ምሑር ናቸው፡፡

ከውጭ አገር እንደተመለሱ ከ1957-60 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን በማገልገልና ምእመናንን በማስተማር ሐዋርያዊ ግዴታቸውን ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡

ከ164-1967 ዓ.ም የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክልት አለቃ ሆነው እንኳን በበጎ ፈቃደኝነት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም እየተመላለሱ ያስተምሩ ነበር፡፡

ተምሮ ማስተማር

ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ውስጥ ጀስዊቶች /ኢየሱሳውያን/ ይኖሩ ስለነበር ብዙ ጊዜ የሃይማኖት ግጭት ይፈጠር ነበር፡፡ አንዳንዳድ ተማሪዎች በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው ጠንካሮች ስለነበሩ በሚያቀርቡት ጥያቄ በተማሪዎቹና በመምህራን መካከልም በየጊዜው ግጨት ይፈጠራል፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴም ጉዳዩን ሲያጣሩ የግብረገብ መምህር እንደሌላቸው በተማሪዎቹ ስለተነገራቸው በአባ ሃና አቅራቢነት ብፀዕ አቡነ ናትናኤል ወደ ጃንሆይ ቀርበው እንዲቀጠሩ ስለፈቀዱ ለተፈሪ መኮንን ት/ቤት የግብረ ገብ መምህር ሆነው ተቀጠሩ፡፡ ከ1949 ዓ.ም አስከ 1954 ዓ.ም ድረስ በግብረገብ አስተማሪነታቸው ቀጥለዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እያስተማሩ በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የአንጋፋው ተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤትን ከመሠረቱት አንዱ ናቸው፡፡

በወቅቱ ለምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሰባኬ ወንጌል በመሆንም አገልግለዋል፡፡ ልጅ ስለነበሩ፣ ሐዲሳቱንም በቃላቸው ስለሚያውቁ እንደ ብርቅ ይታዩ ነበር፡፡ ደጀ ጠኚውም በአጠቃላይ የሚመጣው ምስካዬ ኅዙናን ነበር፡፡ ብዙ ሕዝብ ስለሚመጣ ለስብከቱም የተመቸ ነበር፡፡

በትንሣኤ ዕለት ነዳያንን ማስፈሰክ የተጀመረው በእሳቸው እንደሆነም ይታወቃል፡፡

ስብከተ ወንጌል በሬዲዮ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿን የምታስተምርበት ዘርፈ ብዙ መንገድ አላት፡፡ በቃል፣ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት፣ በሰንበቴና በተለያዩ ክብረ በዓላት መንፈሳዊ ዕውቀት፣ ሥነ ምግባርን፣ ማኅብራዊ ኑሮን ከምታስተምርባቸው መንገዶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያን የሬዲዮ ፕሮግራም ተሰጥቷት በሬዲዮ ታስተምር ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የቀድሞው አባ መዓዛ ቅዱሳን የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በርቱዕ አንደበታቸው በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ማኅበራዊ ኑሮ በቤተ ክርስቲያን እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትትምህርት ይሰጡ ነበር፡፡

ብፁዕነታቸው በሕይወት ዘመናቸው ካከናወኗቸው ተግባራት ለምእመናን በሬዲዮ ስብከተ ወንጌልን በማስተላለፍ የሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ደሰታ እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡

በዘመነ ደርግ

የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳደሪ፣ የሰበታ ቤተ ደናግል የበላይ ሓላፊና የቦርድ አባል ሆነው አገልግለዋል፡፡

ደርግ አረማዊ ነው ብለህ አስተምረሃል በማለት ተከሰው ከፍተኛ እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ ሐዋርያት ከደረሳቸው ጽዋ እካፈል ዘንድ ስለፈቀደልኝ እንደ ፈተና አላየውም፡፡ ሐዋርያዊ ግዴታዬ ነው€ ይሉ ነበር፡፡

ከ168-1971 ዓ.ም በባህል ሚኒስቴርም በቋንቋ ጥናት አካዳሚ ውስጥ መርሐ ልሳን ተብሎ በሚታወቀው ክፍል በመምህርነት ሠርተዋል፡፡

ጵጵስና

ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኤጲስ ቆጶስነት ከተመረጡት 13 አባቶች መካከል አንዱ ሲሆኑ የትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ በትግራይ ሀገረ ስብከትም እስከ 1975 ዓ.ም አገልግለዋል፡፡

ትግራይ ሀገረ ስብከት

ብፁዕነታቸው ከትግራይ የወጡት ገና በ13 ዓመታቸው በመሆኑ ስለ ትግራይ ሀገረ ስብከት ብዙ ለማወቅ ተቸገሩ፡፡ የትግራይ አብያት ክርስቲያናት ገዳማት ሲሆኑ አተካከላቸውም ተራራማ ቦታ ላይ ነው፡፡ መተዳደሪያቸው የሆነው መሬትም በደርግ ተነጥቀው ነው ያገኙዋቸው፡፡ ጥንታውያን ገደማት እንዳይጠፉ ከክርስቲያን ልማትና ተራድኦ ድርጅት ርዳታ ተቀብለው ለማቋቋም ጥረት አድርገዋል፡፡ ሰበካ ጉባኤ የሌላቸውን አብያተ ክርስቲያናትን በመለየት ሰበካ ጉባኤ አቋቁመዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለማጠናከር ቀን ከሌት ለፍተዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ያቀዷቸውን ሥራዎች በርካታ ቢሆኑም ወቅቱ ከፍተኛ ጦርነት የሚካሔድበት አካባቢ ስለነበር አገልግሎታቸውን እንዳሰቡት መፈጸም አላስቻላቸውም፡፡ ከ6 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አርሲ ሀገረ ስብከት ተዛውረዋል፡፡

አርሲ ሀገረ ስብከት

በአርሲ ሀገረ ስብከት ከ1975 ጀምሮ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በመሆን ለ33 ዓመታት ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በአርሲ ሀገረ ስብከት ቆይታቸውም በምእመናን የሚወደዱና የሚከበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡

ወቅቱ የደርግ ዘመን በመሆኑ የዘመኑ ሰዎች ብፁዕነታው ከወጣቶች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አበላት ሳይቀር አብረው የታሰሩበት ጊዜ ነበር፡፡ መታወቂያህ የቀበሌ አይደለም የቤተ ክህነት ነው እያሉ ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ ለቁም እሥር የተዳረጉበትም ጊዜ ነበር፡፡

አርሲ ተመድበው ሲመጡም 117 አብያተ ክርስቲያናት ብቻ የነበሩ ሲሆን ከ300 በላይ አዳዲስ አብያተ ክርስቲናትን በማስተከል ምእመናን በርቀት ምክንያት ሳይንገላቱ በአቅራቢያቸው ቤተ ክርስቲያን እንዲኖራቸው አድርገዋል፡፡ ሁሉም አብያተ ከርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡

ብፁዕ አባታችን አቡነ ናትናኤል በዝዋይ ሐይቅ በሚገኙ ደሴቶች ላይ በታሪክ የሚዘከር ሥራም ሠርተዋል፡፡

አርሲ ሃገረ ስብከትን በሊቀ ጳጳስነት ከተረከቡ በኋላ ከእሳቸው በፊት በነበሩ አባቶች ጥረት ተደርጐ ፍጻሜ ያላገኘውን የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ1978 ዓ.ም ተጀምሮ በ1986 ዓ.ም ሥራው ተጠናቆ ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ መርቀውታል፡፡

የአብርሃም ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ በአንድ የመንገድ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ርዳታ ተገንብቷል፣ እንዲሁም የአርባዕቱ እንስሳን ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ የሚኖሩ በጐ አድራጊ ምእመናን ቤተልሔሙን ሠርተው ዋናውን ቤተ ክርስቲያን ተሠርቷል፡፡

ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም

abune natnበአሰላ ምእመናን ኅሊና ዘወትር እንዲዘከሩ የሚያደርግ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ካከናወኗቸው ተግባራት ውስጥ ከአሰላ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘውን የዐፄ ኃ/ሥላሴ ሹማምንት ቤተ መንግሠት የነበረውን ቦታ ተከራክረው በማስመለስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ቦታውንም ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም እና የሕፃናት ማሳደጊያ ብለው ሰይመው ልጆችን ሰብስበው በማስተማር አባታዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ የካህናት ማሰልጠኛም በግቢው ውሰጥ አቋቁመዋል፡፡

መነኮሳትንም በአባታዊ ጥሪያቸው ሰብስበው ለመነኮሳቱ ማደሪያ አሠርተው ሥርዓተ ገዳምን አስፈጽመዋል፡፡

በውስጡ ከ120 በላይ እናት አባት የሞቱባቸው ልጆችን የሐይማኖት ልዩነት ሳይፈጥሩ አሳድገውበታል፣ አሁንም በማሳደግ ላይ ነበሩ፡፡ እነዚህ ልጆች አብዛኛዎቹ ኢንጅነሮች፣ ሚዲካል ዶክተሮች ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ታላላቅ ባለሙያዎች የሆኑ አድገውበታል፣ አሁንም እያደጉበት ይገኛል፡፡

ከአውሮፓ ኅብረት እርዳታ ጠይቀው በጤና ጥበቃ ደረጃ በገዳሙ ለሚያደጉት ለልጆቹም ሆነ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚያገለግል ጤና ጣቢያ /ክሊኒክ/ አቋቁመው ከ25,000 ሕዝብ በላይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡

ሕግ ታራሚዎች ወንጌል እንዲማሩ፣ ንስሐ እንዲገቡ ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡

የደን ባለአደራ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ ገዳም ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን በተከሉበት ቦታ ላይ ደኑ ሳይመነጠር ቦታው ጠፍ ሳይሆን እንዲዘልቅ በማሰብ ቤተ ክርስቲያን የሰጡአትን አደራ ጠባቂ ስለሆነች ደኑ ተጠብቆ እንዲኖር ለትውልድ እንዲሻገር አድርገዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ወላጆቻቸውን በሞት ተነጥቀው አሳዳጊ ለሌላቸው ሕፃናት የሚሆን የመመገቢያና የማደሪያ ሕንፃ ካስገነቡ በኋላ ሕፃናት በመንፈሳዊ ሕይወትና ዕውቀት ተኮትኩተው እንዲያድጉ የጻድቁን የአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አሳንፀዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ለዐሥራ ሁለት መናኞች የሚሆን ቤትም አሠርተዋል፡፡

በጠንቋይና ቃልቻ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን በማስለቀቅ ለምእመናን ቤተ ክርስቲያን በማሰራት ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡

ብፁዕነታቸው በሀገረ ስብከታቸው የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታትም ይታወቃሉ፡፡

በ1977 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ድርቅ የዕርዳታ ድርጅቶችን በመጠየቅ፣ ከበጎ አድራጊዎች በማሰባሰብ ስንዴ በማስመጣትና በማከፋፈል ወገኖቻቸውን ታድገዋል፡፡

ከእኔ በኋላ የሚመጣው ሰ ከዚህ አስፋፍቶ የተሻለ ሥራ ይሠራል የሚል እምነት አለኝ በሞት እስከምወሰድ የድርሻዬን ልወጣ€ በማለት ሲደክሙ እሰከ ዕለተ ዕረፍታቸው ያለ እረፍት ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ሓላፊነት ተወጥተዋል፡፡

€œቤተ ክርስቲያን አስተምራኛለች፡፡ ውለታዋን ከፍዬ አልጨርሰውም€ በማለት ይናገሩ እንደነበር በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡

ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት እንዲጀመር፣ ወጣቱና የተማረው ክፍል ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲቀርብ፣ ማኅበሩም ተጠናክሮ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ካስቻሉ ታላላቅ አባቶች መካከል አንዱ ናቸው፡፡

ብፁዕነታቸው ታላቅ የወንጌል አርበኛ፣ አስተውለው የሚናገሩ፣ ምእመናን እንዳይበደሉ ጥብቅና የሚቆሙ፣ ከሁሉም ጋር ሰላማዊ፣ ታጋሽ አባት ነበሩ፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ነሐሴ አጋማሽ 2004 ዓ.ም እንዳረፉም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተመርጠው እስከ የካቲት 2005 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትያርክ ሆነው እስከ ተመረጡበት ዕለት በዐቃቤ መንበርነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በመምራት አባታዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡

ሥርዓተ ቀብራቸውም፤ በርካታ አገልገሎት ሲፈጽሙበት በነበረው በደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ኀሙስ የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውነተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን በተገኙበት ይፈጸማል፡፡

የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይደርብን፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ፡- የጥቅምት ወር 1961 ዓ.ም €œድምጸ ተዋሕዶ፣

ዜና ቤተ ክርስቲያን ጥር 4 ቀን 1971 ዓ.ም፣

ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ሚያዚያ 1998 ዓ.ም፣

በብፁዕነታቸው የሕይወት ዙሪያ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም ያልታተመ፡፡

01awde r 01

የ5ኛው ዙር ዐውደ ርእይ ዝግጅት በመጠናቀቅ ላይ መሆኑ ተገለጸ

የካቲት 19 ቀን 2008 ዓ.ም

01awde r 01ማኅበረ ቅዱሳን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፣ ድርሻችንን እንወቅ በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 15-21 ቀን 2008 ዓ.ም በኤግዚቢሽን ማእከል የሚያቀርበው ዐውደ ርእይ ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የዐውደ ርእዩ ዐቢይ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

01awde r 02ዐውደ ርእዩን ለማዘጋጀት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ፈቃድ ከማግኘት ጀምሮ፣ ኤግዚቢሽን ማእከሉን በመከራየትና ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር ዐወደ ርእዩ ተጀምሮ እስኪፈጸም ድረስ በተሳካ ሁኔታ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ገልጸው፣ ያሰብነውን በትክክል እንድናሳካ ጸሎት አስፈላጊ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በጸሎት ኃይል ነው የሚከናወነው፤ የሚያጋጥመንን ፈተና ሁሉ እንድናልፍ በጸሎት እንድታሰቡን ይገባል ብለዋል፡፡ በዐውደ ርእዩም ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ምእመናን ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዋና ጸሓፊው ሰፊ ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበትና የቤተ ክርስቲያንን ዓለም አቀፋዊነት የሚያሳይ፤ እንዲሁም በይበልጥ ቤተ ክርስቲያያንን እንድናውቃት የሚያደረገን ስለሆነ ምእመናን ዐውደ ርእዩን እንዲመለከቱ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዐውደ ርእዩ ዐቢይ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ተሾመ በበኩላቸው ቅድመ ዝግጅቱን በሰው ኃይልና አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በማሟላት ምእመናን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት፣ ከእነሱም የሚጠበቀውን ማበርከት እንዲችሉ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ በማጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የዐውደ ርእዩ ዓርማ እና መሪ ቃል በአባቶች ቡራኬ የተመረቀ ሲሆን፤ በዓርማው የተካተቱና ማስተላለፍ የተፈለገውን መልእክት አስመልክቶ በዲ/ን ዋሲሁን በላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

01awde r 03የዐውደ ርእዩ ይዘት በዐራት አበይት ትእይንቶች የተከፈለ ሲሆን፤ በእያንዳንዱ ትእይንት ውስጥ በርካታ ንዑሳን ክፍሎች ተካትተዋል፡፡ ዐራቱ ዐበይት ትእይንቶች፡-

1.የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት እና ቤተ ክርስቲያን ማን ናት?

2.የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ

3.የቤተ ክርስቲያን ተጋድሎ

4.ምን እናድርግ? በሚል ተከፋፍለው ይቀርባሉ፡፡

በተጨማሪም ኦርቶዶክሳውያን ክውን ጥበባት የሚቀርቡበት ዝግጅትም በስፋት ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በከውን ጥበባት ልዩ ዝግጅት የአብነት ትምህርት ቤቶችና የትምህርት አሰጣጣቸው፣ ሊቃውንቱ ከነደቀመዛሙርቶቻቸው ተገኝተው የሚያቀርቡ ሲሆን በሰባቱም ቀናት በተለያዩ ርእሶች የአደባባይ ተዋስኦ/Public Lecture Speeches/ ይቀርባል፡፡

በዐውደ ርእዩ ላይ ገለጻውን ለሚያካሄዱ የማኅበሩ አባላት፣ ለሰንበት ትምህርት ቤቶች እና ግቢ ጉበኤያት ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑን የተናገሩት የዐቢይ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ ዐውደ ርእዩ ለአንድ ሳምንት ብቻ የሚቆይ በመሆኑ በመዝጊያው ቀን ሊከሰት የሚችለውን መጨናነቅ ለመቀነስ ከተከፈተበት ቀንና ስዓት ጀምሮ ምእመናን ተገኝተው እንዲመለከቱ አሳስበዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ ቀደም በ1988፣ በ1992፣ በ1994፣ በ2000 ዓ.ም ለዐራት ጊዜያት በተለያየ ይዘት ላይ ያተኮረ ዐውደ ርእይ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ከመጋቢት 15-21 ቀን 2008 ዓ.ም የሚካሔደው ለአምስተኛ ጊዜ ነው፡፡

01dilla

በዲላ ማረሚያ ቤት አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን አገኙ

የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም

ከዲላ ወረዳ ማእከል

01dillaየዲላ ወረዳ ማእከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር በዲላ ማረሚያ ቤት ያስተማሯቸውን 48 ኢ አማንያን የነበሩ የሕግ ታራሚዎች ተጠምቀው የሥላሴ ልጅነትን አገኙ፡፡

የዲላ፣ ወናጎና ቡሌ ወረዳዎች ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ተክለ ዮሐንስ በላቸው የሕግ ታራሚዎቹ በዲላ ማረሚያ ተቋም ውስጥ በማኅበረ ቅዱሳንና በሰንበት ትምህርት ቤቶች እገዛ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምረው ለዚህ ታላቅ ክብር በመብቃታቸው ሁላችንም ልንደሰት ይገባል ብለዋል፡፡

01dilla hawaየሕግ ታራሚዎች ባሉበት ሆነው ንስሐ መግባት እንዲችሉ፣ እንዲማሩና ኪዳን እንዲያደርሱ በሀገረ ስብከቱ መልካም ፈቃድ አንድ ካህን መቀጠራቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ወደፊትም ባሉበት ሆነው ሥጋ ወደሙን መቀበልና መጠመቅ እንዲችሉ፣ በማረሚያ ቤት ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ እንደሆነና ለዚህም ከፍተኛ እገዛ ያረገላቸውን የዲላ ማረሚያ ቤት አስተዳደርን አመስግነዋል፡፡

የማስተማርና የማጥመቅ አገልግሎቱን በተመለከተም ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ከማሰጠት በተጨማሪ አዳዲስ አማንያን በእምነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ የማድረጉ አገልግሎት አነስተኛ በመሆኑ የክትትሉ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡

የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን አልዓዛር ለማ ባስተላለፉት መልእክት ትምህርት በማስተማርና የቅርብ ክትትል በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገውን ማኅበረ ቅዱሳን የዲላ ወረዳ ማእከልን አመስግነው፤ የዲላ ከተማና የአካባቢው ሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ምእመናን የሕግ ታራሚዎችን በመጠየቅና በማጽናናት ይህን መልካም ፍሬ ማየት በመቻሉ ደስታው የሁሉም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ከአሁን በፊት የተጠመቁትንና አዲስ ተጠማቂያንን እንዲበረቱ ትክክለኛውን መንገድ በመምረጥ ተጠምቃችኋልና የያዛችሁትን እምነት አጽንታችሁ ልትጠብቁና ለሌሎች የሕግ ታራሚዎችም ምሣሌ በመሆን ልትኖሩ ይገባል በማለትም አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ለተገኙት ምእመናንም የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ወገኖቻችን ወደዚህች ሃይማኖት ሊመጡ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በደስታ ልንቀበላቸው፣ ልንከባከባቸውና ልንደግፋቸው ይገባል€ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ከተጠማቂዎቹ መካከል የሆነው ትግሉ ብሩ ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት እንዴት ሊመጣ እንደቻለ ለቀረበለት ጥቄ ሲመልስ €œከልጅነቴ ጀምሮ ያደግሁት በሌላ ሃይማኖት ውስጥ ነበር፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት ማረሚያ ቤት ከገባሁ በኋላ መንፈሳዊ የሆኑ ጓደኞችን በማግኘቴ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት እንድማር ተነሳሳሁ፡፡ የዘላለም ሕይወት የማገኘው በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት እንደሆነና ቀዳማዊት እምነት መሆንዋን በመረዳት ለመጠመቅ ችያለሁ፡፡ ወደፊትም በተማርኩት ትምህርት ያላመኑትን በማስተማርና በተሰጠኝ ጸጋ እግዚአብሔርን አገለግላለሁ ብሏል::

በማኅበረ ቅዱሳን ሐዋሳ ማእከል የዲላ ወረዳ ማእከል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አራርሳ ቦኪ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት በማረሚያ ተቋሙ የተደረገው የማስተማርና የማጥመቅ አገልግሎት 3ኛ ዙር መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ በፊት በመጀመሪያው ዙር 27፣ በ2ኛው ዙር 24፣ እንዲሁም አሁን ደግሞ 48 በአጠቃላይ 97 የሕግ ታራሚዎች ከተለያዩ እምነቶች ወደ ጥንታዊት፣ ዘላለማዊት፣ ኵላዊት፣ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት መምጣታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በእምነታቸው እንዲጸኑም ወረዳ ቤተ ክህነቱ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የዲላና አካባቢው ምእመናንም እገዛቸው እንዳይለያቸው አሳስበዋል፡፡

ከተጠማቂዎቹ መካከል 46ቱ በዲላ ጌዴኦ ዞን ዲላ ማረሚያ ተቋም ውስጥ የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ሲሆኑ ሁለቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው፡፡

የሕግ ታራሚዎቹ በሚጠመቁበት ዕለት ካህናት አባቶች፣ መምህራነ ወንጌል፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ሌሎችም ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

mk logo1

ቅዱስ ፓትርያርኩ ለጻፉት ደብዳቤ ማኅበረ ቅዱሳን መልስ ሰጠ

mk logo1

ጥር 25 ቀን 2008 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማጠናከር በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታን አግኝቶ የተቋቋመው ማኅበረ ቅዱሳን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በተለያየ መልኩ ሲፈተን ኖሯል፡፡ ይሁን እንጂ ፈተናውን በምድራዊ ኃይል ሳይሆን በኃይለ እግዚአብሔር በብፁዓን አበው ጸሎትና በእውነተኞቹ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ምክርና ተግሣፅ ሲቋቋመው ቆይቷል፡፡

ነገር ግን አንዱ ፈተና ሲያልፍ ሌላው ከመተካቱ ውጭ አንድም ጊዜ ማኅበረ ቅዱሳን ያለፈተና አገልግሎቱን ያከናወነበት ጊዜ የለም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነን ሰሞኑን የተከሠተው ጉዳይ ነው፡፡ ሰሞኑን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አንድ የመመሪያ ደብዳቤ ለተለያዩ አካላት መጻፉ ይታወቃል፡፡ ይህ ደብዳቤ ብዙ ምእመናንንና አገልጋዮችን ያሳዘነ፣ ለአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ደስታን የፈጠረ ሆኗል፡፡ የቅዱስ ፓትርያርኩን ደብዳቤ መነሻ በማድረግም ማኅበረ ቅዱሳን እውነታውን ሁሉም አካላት ይረዱት ዘንድ መልስ ጽፏል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያሰተላለፉት የመመሪያ ደብዳቤና ማኅበረ ቅዱሳን የሰጠው እውነታውን የሚያስገነዝብ የመልስ ደብዳቤ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ ጻፉት ደብዳቤpdf button ማኅበረ ቅዱሳን መልስpdf button

DSC04666

በኮንሶ ወረዳ ከ540 በላይ ሰዎች ተጠመቁ

አርባ ምንጭ ማእከል

ጥር 23 ቀን 2008 ዓ.ም

DSC04666

በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በኮንሶ ወረዳ ኮልሜ፣ አባሮባ እና ዱሮ (አርፋይዴ፣ኦካይሌ፣ ጉላይዴ፣ ቦይዴ፣ ማደሪያ እና ካሻሌ) ቀበሌያት ከ540 በላይ ሰዎች ጥር 11 ቀን 2008 ዓ.ም ተጠመቁ፡፡የጋሞ ጎፋ ሀገረስ ስብከት በዕለቱ የማጥመቅ ሥነ-ስርዓቱን እንዲፈጽሙ ወደስፍራው ያቀኑትን ሁለት ካህናት የመደበ ሲሆን የኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነት፣ ማኅበረ ቅዱሳን አርባ ምንጭ ማእከል የስብከተ ወንጌል ክፍል፣ ሰባት የግቢ ጉባኤያት ዲያቆናት እና የካራት ወረዳ ማእከል በቦታው በመገኘት ጥምቀቱን አስተባብረዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ እና የኮንሶ ወረዳ ቤተ ክህነት ወንጌል ወዳልተዳረሰባቸው የገጠር መንደሮች የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በማስተማር ኢ-አማንያን እንዲጠመቁ ጥረት እያደረገ ሲሆን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከልና የአርባ ምንጭ ማእከልም ለስኬቱ እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከድጋፎቹም ውስት የ2007 ዓ/ም አዲስ ተጠማቂያንን ለሚያስተምር አንድ ቋሚ የድጎማ መምህር ዋናው ማዕከል የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፤ የአርባ ምንጭ ማእከልም በዱሮ እና ጉኛራ ቀበሌዎች አዳዲስ ሰንበት ት/ቤቶች እንዲደራጁ እና ሁለት የሰንበት ት/ቤቶች ተተኪ መምህራን እና አንድ ካህን በአካባቢ ቋንቋ ወንጌልን እንዲያስተምሩ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች እየተጠመቁ መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚሁ እለት በዋናው ማእከል የተዘጋጀ ነጠላና የአንገት መስቀል ለሁሉም ተጠማቂያን የተሰጠ ሲሆን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል እጣን፣ ጧፍና ዘቢብም ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በወረዳው በ2007 ዓ/ም በሁለት ዙር ከ980 በላይ ኢ-አማንያን ተጠምቀው የመንፈስ ቅዱስን ልጅነት ማግኘታቸው የሚታወስ ሲሆን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናው አገልግሎት እየተሳተፉ እንደሚገኙ የወረዳው ቤተ ክህነትና የማእከሉ ስብከተ ወንጌል ክፍል አሳውቀዋል፡፡

{gallery count=1 width=350 height=300 counter=1 links=0 alignment=center animation=3000}../temeket{/gallery}

To media kifil

በተለያዩ ጊዜያት ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ለተመረቃችሁ እህቶችና ወንድሞች በሙሉ

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ኮርስና ልዩ ልዩ መርሐ ግብራትን የሚያከናውንበት የመማሪያ አዳራሽ እያሰራ ይገኛል። ነገር ግን ይህን አዳራሽ በራሱ ሰርቶ ለማጠናቀቅ የሚያስችል አቅም የለውም።

ስለሆነም ይህን አዳራሽ ለማጠናቀቅ የሁላችንም ኦርቶዶክሳዊያን ሐላፊነት ነውና በተለያዩ ጊዜያት የተመረቃችሁ የቀድሞው የግቢ ጉባኤው አባላት እንዲሁም ሌሎች በአዳራሽ ሥራው መሳተፍ የምትፈልጉ ኦርቶዶክሳዊያን በሙሉ በሚከተለው የግቢ ጉባኤው የሒሳብ ቁጥር የምትችሉትን ገንዘብ በማስገባት ድጋፋችሁንና እርዳታችሁን ታደርጉ ዘንድ ግቢ ጉባኤው ጥሪውን ያስተላልፋል። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ 1000139923058 (የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አክሱም ቅርንጫፍ) ለተጨማሪ መረጃ፡ 0918052641 (በላቸው መስፍን – የግቢ ጉባኤው አዳራሽ አሰሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ)

To media kifil