የካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም
ቤተ ክርስቲያን አስተምራኛለች፡፡ ውለታዋን ከፍዬ አልጨርሰው /ብፁዕ አቡነ ናትናኤል/
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በምሥራቅ ትግራይ ክለተ አውላሎ አውራጃ አውዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ከአቶ ገብረ ሕይወት ፀዓዱ እና ከወይዘሮ ወለተ ክርስቶስ ግብረቱ ግንቦት 12 ቀን በ1923 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ወላጆቻቸው ልጆችን እየወለዱ ይሞቱባቸው ስለነበር በጭንቀት ውስጥ ሳሉ ነው ብፁዕነታቸው የተወለዱት፡፡
አባታቸው ገና በጨቅላነታቸው በመሞታቸው እናታቸው በስስት አሳደጓቸው፡፡ ባለቤታቸውንና ልጆቻቸውን ያጡት እናትም የሁሉም ምትክ የሆኑት ልጃቸውን ካሳዬ ብለው ስም አወጡላቸው፡፡ ትንሹ ካሳዬም የእናታቸውን ፍቅር ሳይወጡ፣ እናትም የልጃቸውን ስም ጠርተው፣ በዓይናቸው ዓይተው ሳይጠግቡ በልጅነታቸው በማረፋቸው ከእህታቸው ጋር መኖር ጀመሩ፡፡
የእህታቸው ፍላጎት ከብት እንዲጠብቁ፤ ዕድሜያቸው ለአቅመ አዳም ሲደርስም በሕግ በትዳር ተወስነው እያረሱ በግብርና ኑሯቸውን እንዲገፉ ነበር፡፡ የካሣዬ ሐሳብ ደግሞ ከአድማስ ማዶ ነበር፡፡ ከሊቃውንቱ እግር ሥር ቁጭ ብሎ መማር፣ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል፣ ጉባኤ አስፍቶ ወንበር ዘርግቶ ማስተማር፡፡
ትምህርት
ብፁዕነታቸው አባቴ በጣም መንፈሳዊ ሰው ነበሩ፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ አባታችን እያሉ ይጠሩኛል እኔ ግን ደስ አይለኝም ነበር፡፡ መምህሬ ስለ እኔ ትንቢት ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ትልቅ አባት ይሆናል ብለው ይናገሩ እንደነበረ ነግረውኛል፡፡ በወቅቱ እኔ ልጅ ስለነበርኩ ያንን አላስታውሰውም ሲሉ ያናገራሉ፡፡
የትምህርት ፍላጎታቸውን ለመወጣት ወደ ከኔታ ወልደ ገብርኤል ዘንድ በመሔድ ድርባ አቡነ አሳይ ቤተ ክርስቲያን ንባብና የቃል ትምህርት ጀመሩ፡፡
የኔታ ሰሎሞን የሚባሉ የአቋቋም መምህራቸው ያላቸውን የትምህርት ፍላጎት በመረዳት፣ ነገ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ሆነው ስለታዩአቸው ወደ ሌላ ሔደው እንዳይሰናከሉ በማሰብ ከእርሳቸው ዘንድ እንዲማሩ ስለሚፈልጉ ርቀው ወደ ቆሎ ትምህርት ቤት እንዳይሔዱ አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ሦስት ዋስ አስጠርተዋቸዋል፡፡
እሳቸው ግን ልባቸው ለትምህርት አድልቷልና ተጨማሪ ትምህርት ለመቅሰም ከመምህራቸውና ከቤተሰቦቻቸው ተደብቀው በጥንቱ ቆሎ ተማሪ ልማድ ስማቸውን ቀይረው ጎጃም /በጌምድር/ ትምህርትን ፍለጋ ተሰደዱ፡፡ በቆሎ ት/ቤትም መዓዛ ቅዱሳን ተብለው ተጠሩ፡፡
ወደ ጎንደር እና ጎጃም ተሻግረው ከየኔታ ኃይሉ ስሜ በየላ ኢየሱስ፣ ከየኔታ መኮንን ላስታ አመራ ማርያም ከእነዚህ ከሁለቱም ጾመ ድጓና ምዕራፍ ከተማሩ በኋላ እንደገና ወደ ቅኔ ቤት ገቡ፡፡ ክህነት የተቀበሉትም ሁለት ጊዜ ምዕራፍና ጾመ ድጓ ዘልቀው፣ ቅኔ ዘይእዜ ከቆጠሩ በኋላ ነበር፡፡
በደቡብ ጎንደር እና ወሎ ተዘዋውረውም በጉባኤ ቤቶች የዜማ፣ የአቋቋም ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ወረዳ ደረስጌ ማርያም አቅንተውም ከየኔታ መንበሩ ዘንድ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ እንዳቤት ወረዳ በሸሜ ጊዮርጊስ ደብር ከመምህር ጥበቡ ቅኔ ተመምረወዋለል፡፡
ክህነት
ቅኔ ቤት ገብተው ከየኔታ መንበሩ ደረስጌ ሰሜን ጃና አሞራ ገብተው ሲማሩ ዘመዳቸው ምሶሶ ታቃፊ ሆነህ እንዳትቀር ዲቁና አትቀበል ያላቸው ትዝ እያለቸው ዲቁና የተቀበሉት ካደጉና ከተማሩ በኋላ ነው፡፡
ከጎንደር ሸዋ/አዲስ አበባ/ ድረስ በእግራቸው ተጉዘው በመምጣት በሚያዚያ ወር በ1938 ዓ.ም በአዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ከአቡነ ይስሐቅ ዲቁና ተቀብለዋል፡፡
የቅኔ ዕውቀታቸውን ለማስፋትም ከአዲስ አበባ ስማዳ ወረዳ ደብረ ዕንቁ በማምራት ከታላቁ ሊቅ ከየኔታ ጌጡ ተሰማ ዘንድ ተምረዋል፡፡
የብሉይ ኪዳንና ዐራቱን ብሔረ ነገሥት፤ አምስቱን ብሔረ ኦሪትና ዳዊት ትርጓሜን ተምረዋል፡፡
አቡነ ባስልዮስ በጾመ ፍልሰታ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ይዘዋቸው በመሔድም ውዳሴ ማርያም እና ቅዳሴ ማርያም እየተረጐሙ እዚያው ከርመው ሦስቱን ታላላቅ ማዕርጋት ቅስና፣ ምንኩስና ቁምስና፣ በ1953 ዓ.ም ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ተቀብለዋል፡፡
በ1941 ዓ.ም ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመማር አዲስ አበባ በሚገኘው የታዕካ ነገሥት በኣታ ለማርያም ገዳም ገብተው ሐዲሳትን በመጀመሪያ ከመጋቤ ሐዲስ ወ/ሚካኤል፣ ከመ/ር ገብረ ማርያም ዓለሙ፤ ቅዳሴ ማርያምና ውዳሴ ማርያም ከመምህር ይሔይስ፣ ኪዳን፣ ትምህርተ ኅቡአት ከመምህር ከየኔታ ገ/ማርያም፣ ከመምህር ገ/ሕይወት ነገሥታቱ ፍርድ የሚሰጡበትን ፍትሐ ነገሥት ተምረዋል፡፡
ቀን እየተማሩ ከበታቻቸው ያሉትን ተማሪዎች እያስተማሩ ቆይተዋል፡፡ የመጻሐፍት ተማሪ ሆነው መጻሕፍተ ሐዲሳት፣ ኪዳን፣ ትምህርተ ኅቡአት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ቅዳሴ ማርያም፣ ቀን እየተማሩ ሌሊት ከማቴዎስ ወንጌል ጀምሮ እስከ ራእየ ዮሐንስ መጨረሻ ድረስ እንዲሁም ትርጓሜ ፍትሐ ነገሥትን በእጃቸው ጽፈዋል፡፡
መዝሙረ ዳዊት ትርጓሜን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፊት እንዲተረጉሙ ተፈቅዶላቸው በሚገባ በመወጣታቸው ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
ዓላማቸው በተመረቁበት በሐዲሱ ተማሪ አብዝተው ጉባኤ አስፍተው ማስተማር ነበር፡፡ ነገር ግን በቅድስት ሥላሴ መምህራን ማሠልጠኛ ዕድል አግኝተው ለሁለት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታትለው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡
ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ወደፊት ጵጵስና የሚሾሙ ሰዎች ውጭ አገር ሔደው የውጭውን ትምህርትና ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ያስፈልጋል በማለት ለአቡነ ባስልዮስ አሳሰቧቸው፡፡ ሰዎች ሲመረጡም በንጉሡ አማካይነት ተጠቁመው ውጪ አገር ከሚሔዱት መካከል አንዱ ሆኑ፡፡
አባ መዓዛ- ቅዱሳን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት በቂ ችሎታ አላቸው ከሚባሉ መምህራን አንዱ ናቸው፡፡ እኒህ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ዕውቀታቸቸውን በበለጠ በዓለም አቀፍ ቋንቋ ለማሻሻል ባላቸው ፍላጎት መሠረት ወደ ኢየሩሳሌም አንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ሴንት ጆርጅ ኮሌጅ ተላኩ፡፡ ወደፊት ጵጵስና የሚሾሙ ብለው ጃንሆይ በተናገሩት መሠረት የኤጲስ ቆጶስነት ትምህርት እንዲማሩና እንዲሠለጥኑ ነበር የተላኩት፡፡ ሁለት ዓመት ተኩል የቤተ ክርስቲያን ታሪክና አስተዳደር /Church History and Adminstration/ ተምረው ተመለሱ፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ወደ እንግሊዝ አገር ኦክስፎርድ ኦስሄትሮፕ የሚባል የካቶሊክ ኮሌጅ በ1961 ዓ.ም ተልከው በእንግሊዝ አገር ለዐራት ዓመታት ትምህርታውን ተከታትለው በፍልፈፍና /Bachelor of Dignity Basic Philosophy Supermental and Developmental Phsycology/ ዲግሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡
ከአገርና ከቤተ ክርስቲያን የተቀበሉትን ታላቅ አደራ አክብረው አገራቸውን ለማልማት በውጭ አገር የቀሰሙትን ሥልጣኔ እና ልምድ ለአገራቸው የሚያውሉ ምሁራን በርካታ ናቸው፡፡ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ካፈራቻቸው ሊቃውንት መካከልም አንዱ ናቸው፡፡ ብፁዕነታቸው በምዕራቡ ዓለም በትምህርት ዓለም ቆይታቸው በትምህርትና በልምድ ያካበቱትን ዕውቀት በተግባር ላይ ለማዋል የቻሉ ምሑር ናቸው፡፡
ከውጭ አገር እንደተመለሱ ከ1957-60 ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክትል አስተዳዳሪ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን በማገልገልና ምእመናንን በማስተማር ሐዋርያዊ ግዴታቸውን ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡
ከ164-1967 ዓ.ም የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመዋል፡፡
የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክልት አለቃ ሆነው እንኳን በበጎ ፈቃደኝነት ምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም እየተመላለሱ ያስተምሩ ነበር፡፡
ተምሮ ማስተማር
ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ውስጥ ጀስዊቶች /ኢየሱሳውያን/ ይኖሩ ስለነበር ብዙ ጊዜ የሃይማኖት ግጭት ይፈጠር ነበር፡፡ አንዳንዳድ ተማሪዎች በመንፈሳዊ ዕውቀታቸው ጠንካሮች ስለነበሩ በሚያቀርቡት ጥያቄ በተማሪዎቹና በመምህራን መካከልም በየጊዜው ግጨት ይፈጠራል፡፡ ዐፄ ኃይለ ሥላሴም ጉዳዩን ሲያጣሩ የግብረገብ መምህር እንደሌላቸው በተማሪዎቹ ስለተነገራቸው በአባ ሃና አቅራቢነት ብፀዕ አቡነ ናትናኤል ወደ ጃንሆይ ቀርበው እንዲቀጠሩ ስለፈቀዱ ለተፈሪ መኮንን ት/ቤት የግብረ ገብ መምህር ሆነው ተቀጠሩ፡፡ ከ1949 ዓ.ም አስከ 1954 ዓ.ም ድረስ በግብረገብ አስተማሪነታቸው ቀጥለዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት እያስተማሩ በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የአንጋፋው ተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤትን ከመሠረቱት አንዱ ናቸው፡፡
በወቅቱ ለምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሰባኬ ወንጌል በመሆንም አገልግለዋል፡፡ ልጅ ስለነበሩ፣ ሐዲሳቱንም በቃላቸው ስለሚያውቁ እንደ ብርቅ ይታዩ ነበር፡፡ ደጀ ጠኚውም በአጠቃላይ የሚመጣው ምስካዬ ኅዙናን ነበር፡፡ ብዙ ሕዝብ ስለሚመጣ ለስብከቱም የተመቸ ነበር፡፡
በትንሣኤ ዕለት ነዳያንን ማስፈሰክ የተጀመረው በእሳቸው እንደሆነም ይታወቃል፡፡
ስብከተ ወንጌል በሬዲዮ
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿን የምታስተምርበት ዘርፈ ብዙ መንገድ አላት፡፡ በቃል፣ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት፣ በሰንበቴና በተለያዩ ክብረ በዓላት መንፈሳዊ ዕውቀት፣ ሥነ ምግባርን፣ ማኅብራዊ ኑሮን ከምታስተምርባቸው መንገዶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያን የሬዲዮ ፕሮግራም ተሰጥቷት በሬዲዮ ታስተምር ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የቀድሞው አባ መዓዛ ቅዱሳን የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል በርቱዕ አንደበታቸው በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ ማኅበራዊ ኑሮ በቤተ ክርስቲያን እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትትምህርት ይሰጡ ነበር፡፡
ብፁዕነታቸው በሕይወት ዘመናቸው ካከናወኗቸው ተግባራት ለምእመናን በሬዲዮ ስብከተ ወንጌልን በማስተላለፍ የሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ደሰታ እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡
በዘመነ ደርግ
የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳደሪ፣ የሰበታ ቤተ ደናግል የበላይ ሓላፊና የቦርድ አባል ሆነው አገልግለዋል፡፡
ደርግ አረማዊ ነው ብለህ አስተምረሃል በማለት ተከሰው ከፍተኛ እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ ሐዋርያት ከደረሳቸው ጽዋ እካፈል ዘንድ ስለፈቀደልኝ እንደ ፈተና አላየውም፡፡ ሐዋርያዊ ግዴታዬ ነው ይሉ ነበር፡፡
ከ168-1971 ዓ.ም በባህል ሚኒስቴርም በቋንቋ ጥናት አካዳሚ ውስጥ መርሐ ልሳን ተብሎ በሚታወቀው ክፍል በመምህርነት ሠርተዋል፡፡
ጵጵስና
ጥር 13 ቀን 1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ለኤጲስ ቆጶስነት ከተመረጡት 13 አባቶች መካከል አንዱ ሲሆኑ የትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ በትግራይ ሀገረ ስብከትም እስከ 1975 ዓ.ም አገልግለዋል፡፡
ትግራይ ሀገረ ስብከት
ብፁዕነታቸው ከትግራይ የወጡት ገና በ13 ዓመታቸው በመሆኑ ስለ ትግራይ ሀገረ ስብከት ብዙ ለማወቅ ተቸገሩ፡፡ የትግራይ አብያት ክርስቲያናት ገዳማት ሲሆኑ አተካከላቸውም ተራራማ ቦታ ላይ ነው፡፡ መተዳደሪያቸው የሆነው መሬትም በደርግ ተነጥቀው ነው ያገኙዋቸው፡፡ ጥንታውያን ገደማት እንዳይጠፉ ከክርስቲያን ልማትና ተራድኦ ድርጅት ርዳታ ተቀብለው ለማቋቋም ጥረት አድርገዋል፡፡ ሰበካ ጉባኤ የሌላቸውን አብያተ ክርስቲያናትን በመለየት ሰበካ ጉባኤ አቋቁመዋል፡፡ የሀገረ ስብከቱን የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለማጠናከር ቀን ከሌት ለፍተዋል፡፡ በሀገረ ስብከቱ ያቀዷቸውን ሥራዎች በርካታ ቢሆኑም ወቅቱ ከፍተኛ ጦርነት የሚካሔድበት አካባቢ ስለነበር አገልግሎታቸውን እንዳሰቡት መፈጸም አላስቻላቸውም፡፡ ከ6 ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አርሲ ሀገረ ስብከት ተዛውረዋል፡፡
አርሲ ሀገረ ስብከት
በአርሲ ሀገረ ስብከት ከ1975 ጀምሮ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በመሆን ለ33 ዓመታት ከፍተኛ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ በአርሲ ሀገረ ስብከት ቆይታቸውም በምእመናን የሚወደዱና የሚከበሩ ታላቅ አባት ናቸው፡፡
ወቅቱ የደርግ ዘመን በመሆኑ የዘመኑ ሰዎች ብፁዕነታው ከወጣቶች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አበላት ሳይቀር አብረው የታሰሩበት ጊዜ ነበር፡፡ መታወቂያህ የቀበሌ አይደለም የቤተ ክህነት ነው እያሉ ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል፡፡ ለቁም እሥር የተዳረጉበትም ጊዜ ነበር፡፡
አርሲ ተመድበው ሲመጡም 117 አብያተ ክርስቲያናት ብቻ የነበሩ ሲሆን ከ300 በላይ አዳዲስ አብያተ ክርስቲናትን በማስተከል ምእመናን በርቀት ምክንያት ሳይንገላቱ በአቅራቢያቸው ቤተ ክርስቲያን እንዲኖራቸው አድርገዋል፡፡ ሁሉም አብያተ ከርስቲያናት የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡
ብፁዕ አባታችን አቡነ ናትናኤል በዝዋይ ሐይቅ በሚገኙ ደሴቶች ላይ በታሪክ የሚዘከር ሥራም ሠርተዋል፡፡
አርሲ ሃገረ ስብከትን በሊቀ ጳጳስነት ከተረከቡ በኋላ ከእሳቸው በፊት በነበሩ አባቶች ጥረት ተደርጐ ፍጻሜ ያላገኘውን የደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በ1978 ዓ.ም ተጀምሮ በ1986 ዓ.ም ሥራው ተጠናቆ ቅዱስ ፓትርያርኩ አቡነ ጳውሎስ መርቀውታል፡፡
የአብርሃም ቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ በአንድ የመንገድ ሥራ ተቋራጭ ድርጅት ርዳታ ተገንብቷል፣ እንዲሁም የአርባዕቱ እንስሳን ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ የሚኖሩ በጐ አድራጊ ምእመናን ቤተልሔሙን ሠርተው ዋናውን ቤተ ክርስቲያን ተሠርቷል፡፡
ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም
በአሰላ ምእመናን ኅሊና ዘወትር እንዲዘከሩ የሚያደርግ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ካከናወኗቸው ተግባራት ውስጥ ከአሰላ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኘውን የዐፄ ኃ/ሥላሴ ሹማምንት ቤተ መንግሠት የነበረውን ቦታ ተከራክረው በማስመለስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ቦታውንም ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም እና የሕፃናት ማሳደጊያ ብለው ሰይመው ልጆችን ሰብስበው በማስተማር አባታዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡ የካህናት ማሰልጠኛም በግቢው ውሰጥ አቋቁመዋል፡፡
መነኮሳትንም በአባታዊ ጥሪያቸው ሰብስበው ለመነኮሳቱ ማደሪያ አሠርተው ሥርዓተ ገዳምን አስፈጽመዋል፡፡
በውስጡ ከ120 በላይ እናት አባት የሞቱባቸው ልጆችን የሐይማኖት ልዩነት ሳይፈጥሩ አሳድገውበታል፣ አሁንም በማሳደግ ላይ ነበሩ፡፡ እነዚህ ልጆች አብዛኛዎቹ ኢንጅነሮች፣ ሚዲካል ዶክተሮች ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ታላላቅ ባለሙያዎች የሆኑ አድገውበታል፣ አሁንም እያደጉበት ይገኛል፡፡
ከአውሮፓ ኅብረት እርዳታ ጠይቀው በጤና ጥበቃ ደረጃ በገዳሙ ለሚያደጉት ለልጆቹም ሆነ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚያገለግል ጤና ጣቢያ /ክሊኒክ/ አቋቁመው ከ25,000 ሕዝብ በላይ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ሕግ ታራሚዎች ወንጌል እንዲማሩ፣ ንስሐ እንዲገቡ ቤተ ክርስቲያን አሠርተዋል፡፡
የደን ባለአደራ ቤተ ክርስቲያን ስለሆነች ደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ ገዳም ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን በተከሉበት ቦታ ላይ ደኑ ሳይመነጠር ቦታው ጠፍ ሳይሆን እንዲዘልቅ በማሰብ ቤተ ክርስቲያን የሰጡአትን አደራ ጠባቂ ስለሆነች ደኑ ተጠብቆ እንዲኖር ለትውልድ እንዲሻገር አድርገዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ወላጆቻቸውን በሞት ተነጥቀው አሳዳጊ ለሌላቸው ሕፃናት የሚሆን የመመገቢያና የማደሪያ ሕንፃ ካስገነቡ በኋላ ሕፃናት በመንፈሳዊ ሕይወትና ዕውቀት ተኮትኩተው እንዲያድጉ የጻድቁን የአቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አሳንፀዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ለዐሥራ ሁለት መናኞች የሚሆን ቤትም አሠርተዋል፡፡
በጠንቋይና ቃልቻ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን በማስለቀቅ ለምእመናን ቤተ ክርስቲያን በማሰራት ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ አድርገዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በሀገረ ስብከታቸው የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታትም ይታወቃሉ፡፡
በ1977 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው ድርቅ የዕርዳታ ድርጅቶችን በመጠየቅ፣ ከበጎ አድራጊዎች በማሰባሰብ ስንዴ በማስመጣትና በማከፋፈል ወገኖቻቸውን ታድገዋል፡፡
ከእኔ በኋላ የሚመጣው ሰው ከዚህ አስፋፍቶ የተሻለ ሥራ ይሠራል የሚል እምነት አለኝ በሞት እስከምወሰድ የድርሻዬን ልወጣ በማለት ሲደክሙ እሰከ ዕለተ ዕረፍታቸው ያለ እረፍት ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ሓላፊነት ተወጥተዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን አስተምራኛለች፡፡ ውለታዋን ከፍዬ አልጨርሰውም በማለት ይናገሩ እንደነበር በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ፡
ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት እንዲጀመር፣ ወጣቱና የተማረው ክፍል ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲቀርብ፣ ማኅበሩም ተጠናክሮ እዚህ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ካስቻሉ ታላላቅ አባቶች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ብፁዕነታቸው ታላቅ የወንጌል አርበኛ፣ አስተውለው የሚናገሩ፣ ምእመናን እንዳይበደሉ ጥብቅና የሚቆሙ፣ ከሁሉም ጋር ሰላማዊ፣ ታጋሽ አባት ነበሩ፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ነሐሴ አጋማሽ 2004 ዓ.ም እንዳረፉም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተመርጠው እስከ የካቲት 2005 ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትያርክ ሆነው እስከ ተመረጡበት ዕለት በዐቃቤ መንበርነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በመምራት አባታዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸውም፤ በርካታ አገልገሎት ሲፈጽሙበት በነበረው በደብር ቅዱስ ደብረ መዓዛ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ኀሙስ የካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውነተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን በተገኙበት ይፈጸማል፡፡
የብፁዕ አባታችን በረከታቸው ይደርብን፡፡ አሜን፡፡
ምንጭ፡- የጥቅምት ወር 1961 ዓ.ም ድምጸ ተዋሕዶ፣
ዜና ቤተ ክርስቲያን ጥር 4 ቀን 1971 ዓ.ም፣
ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ሚያዚያ 1998 ዓ.ም፣
በብፁዕነታቸው የሕይወት ዙሪያ የተዘጋጀ ዘጋቢ ፊልም ያልታተመ፡፡