‹‹እናንተ የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ናችሁ›› – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ባስመረቀበት ዕለት ተገኝተው በሰጡት ቃለ ምዕዳን ‹‹እናንተ የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ናችሁ›› በማለት ተመራቂዎቹ ወንጌልን ከዳር እስከ ዳር የማዳረስ አደራ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

‹‹እናንተ ከመልካም ዛፍ የተገኛችሁ መልካም ፍሬዎች እንደ መኾናችሁ ይህን ፍሬያችሁን እንድታካፍሉ ቤተ ክርስቲያን አደራ ትላችኋለች›› ያሉት ቅዱስነታቸው ‹‹መብራታችሁ በሰዉ ዅሉ ፊት ይብራ›› የሚለውን የወንጌል ቃል መነሻ አድርገው በከተማ ብቻ ሳይወሰኑ በየገጠሩ በመዘዋወር በአታላዮች የሚወሰዱ ወገኖችን እንዲጠብቁ እና እንዲያስተምሩ ተመራቂዎቹን አሳስበዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በየገጠሩ አንድ ሰባኬ ወንጌል ጠፍቶ በየከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ በአንድ አጥቢያ ከሁለት በላይ መምህራን መመደባቸውን ተችተዋል፡፡

ሴቶች በመንፈሳዊ ኮሌጁ ተምረው በመመረቃቸውና ከፊሎቹም ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው መደሰታቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ፈለግ ተከትለው በየኮሌጆቹ የሚሰጠውን ትምህርተ ሃይማኖት እንዲከታተሉና ራሳቸውን በቃለ እግዚአብሔር እንዲያጎለብቱ እናቶችና እኅቶችን መክረዋል፡፡

በመጨረሻም ተመራቂዎቹ በሚሠማሩበት ቦታ ዅሉ በስብከተ ወንጌል ተግተው በማገልገል፤ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ደግሞ የሰባክያነ ወንጌልን አገልግሎት በመቈጣጠር፤ ምእመናኑም ከትክክለኞች መምህራን ትክክለኛውን ቃለ ወንጌል በመማር መንፈሳዊ ሓላፊነታቸውን እንዲወጡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርቱን ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያኩ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ አባቶች ካህናት፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የተመራቂ ቤተሰቦች በተገኙበት ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ አስመርቋል፡፡

ኮሌጁ ደቀ መዛሙርቱን ያስመረቀው በቀን፣ በማታ በተመላላሽ እና በርቀት መርሐ ግብር፤ በልዩ ልዩ የትምህርት ክፍል፤ በማስተርስ፣ በዲግሪ እና በዲፕሎማ ማዕረግ ነው፡፡ በዕለቱ ተመራቂዎቹ ባለ አምስት አንቀጽ የአገልግሎት ቃል ኪዳናቸውን በተወካያቸው አማካይነት አቅርበዋል፡፡ ሴቶች እኅቶቻችንም በልዩ ልዩ ማዕረግ የተመረቁ ሲኾን ከእነርሱ መካከል ጥቂቶቹ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ መሸለማቸው ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብዙዎችን አስገርሟል፡፡

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ እስከ አሁን ድረስ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያፈራ የኖረና በማፍራት ላይ የሚገኝ አንጋፋ የትምህርት ማእከል ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያን ባለ አደራዎች ሰባክያነ ወንጌል መፍለቂያ የኾነው ኮሌጁ ከኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ያፈነገጠ የኑፋቄ ትምህርት ሲያዛምቱ የተገኙ ሰርጎ ገብ ተማሪዎችን ከአሁን በፊት አውግዞ እንደ ለየ፤ ለወደፊትም ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ሳይፋለስ ለትውልድ ይተላለፍ ዘንድ ሥርዓቱን የጠበቀ ትምህርት የመስጠት ተልእኮዉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በኮሌጁ የቦርድ ሥራ አመራር ሪፖርት ተገልጿል፡፡

‹‹ከእናንተ ብዙ ይጠበቃል›› ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፲፱ ቀን ፳፻፱ .

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የዕለቱን ወንጌል ሲያነቡ (ሉቃ. ፲፥፩-፲፮)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በልዩ ልዩ ትምህርት ክፍል ያስተማራቸውን ደቀ መዛሙርት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች በተገኙበት ሰኔ ፲፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ አስመርቋል፡፡ ተመራቂዎቹም የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በሚመለከት ያዘጋጁትን የአቋም መግለጫ በተወካያቸው አማካይነት አቅርበዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በሰጡት ቃለ ምዕዳን ‹‹ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ጠብቃ ያቆየችው ትክክለኛ የኾነ አስተምህሮዋ፣ ባህል እና ትውፊቷ ሳይበረዝና ሳይፋለስ ለትውልደ ትውልድ መሸጋገር ይችል ዘንድ ከእናንተ ብዙ ይጠበቃል›› ሲሉ ተመራቂዎቹን አሳስበዋል፡፡

ዕለቱ፣ ተመራቂዎቹ የቤተ ክርስቲያንን አደራ ተቀብለው በየተሠማሩበት የሥራ መስክ ዅሉ እስከ መጨረሻው በታማኝነት ቃል የሚገቡበት ቀን መኾኑን ያስገነዘቡት ቅዱስነታቸው ‹‹የመንግሥተ እግዚአብሔር መልእክተኛ የኾነ ዅሉ መስቀሉን ተሸክሞ ለማገልገል የተመረጠ ስለ ኾነ በሚያጋጥመው የጕዞ ዐቀበት እና ቍልቍለት ሊቸገር አይገባውም፤ በማን እንደ ተመረጠ ያውቃልና ነው›› በማለት ተመራቂዎቹ ብዙ ፈተና እንደሚጠብቃቸው አውቀው ዅሉንም በትዕግሥት በማሸነፍ የሕይወት አክሊል ባለቤቶች ለመኾን ከወዲሁ እንዲዘጋጁ መክረዋል፡፡

ተመራቂዎቹ በሚላኩበት ቦታ ዅሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለትውልድ የሚጠቅም አርአያነት ያለው ሥራ ለመሥራት እንዲችሉ ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ዘወትር እንደምትጸልይም ተናግረዋል፡፡ በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያም መንፈሳዊ ኮሌጁ በየጊዜው ተተኪ መምህራንን ለማፍራት እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ‹‹ዘመኑ የዕውቀት ነውና የመማር ማስተማር ዘዴው ዘመኑን የዋጀ እንዲኾን ከበፊቱ በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ በቤተ ክርስቲያናችን ስም አደራ እንላለን›› በማለት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የከፋ ሸካ ቤንጂ ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ በበኩላቸው ‹‹በቆያችሁበት የትምህርት ዘመን ከመምህሮቻችሁ ያገኛችሁትን መንፈሳዊ ዕውቀት እግዚአብሔር ሒዱ ብሎ ወደሚልካችሁ ዓለም በመሔድ ሕዝባችሁንና ሃይማኖታችሁን ጠብቃችሁ ሳትታክቱ እንድታገለግሉ ስትል ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊ መልእክቷን ታስተላልፋለች›› የሚል ቃለ በረከት ለተመራቂዎቹ ሰጥተዋል፡፡

ሊቀ ኅሩያን መሐሪ አስረስ

መምህር ማሞ ከበደ

በኮሌጁ ተምረው የሚመረቁ መምህራን በልዩ ልዩ የዕውቀት ዓይነት የበለጸጉ ሊቃውንት መኾናቸውን በማውሳት ‹‹ከአሁን በኋላ ዝናብ ዘንቦ መሬትን እንደሚያርሰው ዅሉ ከሞላው የዕውቀት ባሕራችሁ እየቀዳችሁ የምእመናንን አእምሮ እንደምታረሰርሱት ትጠበቃላችሁ›› ያሉት ደግሞ የኮሌጁ ዋና ዲን ሊቀ ኅሩያን መሐሪ አስረስ ናቸው፡፡

‹‹በኮሌጃችን ተምረው የሚመረቁ መምህራን የአብነቱን ትምህርት ከዘመናዊው ጋር አጣጥመው በዕውቀት ላይ ዕውቀት ጨምረው የሚወጡ መንፈሳውያን ሐኪሞች ናቸው፡፡ ትምህርታቸውም ደዌ ሥጋን ብቻ ሳይኾን ደዌ ነፍስንም ይፈውሳል›› ያሉት መምህር ማሞ ከበደ የመንፈሳዊ ኮሌጁ አስተዳደር ምክትል ዲን እና የኮሌጁ መምህርም ኮሌጁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ጨምሮ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ሲያፈራ እንደ ቆየ አሁንም በማፍራት ላይ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

የኮሌጁ ተመራቂዎች በከፊል

በዚህ ዓመትም በብሉይ ኪዳን አንድ፤ በሐዲስ ኪዳን አንድ፤ በቀን አዳሪ ሲሚናር ዐሥራ አንድ፤ በቀን ተመላላሽ ሃያ ሦስት፤ በማታው መርሐ ግብር ሁለት መቶ ዐርባ አምስት በድምሩ ሁለት መቶ ሰማንያ አንድ ደቀ መዛሙርትን ማስመረቁን፤ ከተመራቂዎች መካከልም አካል ጉዳተኞች እና ሴቶች እንደሚገኙ መምህር ማሞ ከበደ አስታውቀዋል፡፡ አራቱን ጉባኤያት ማስተማር፤ በዲግሪ መርሐ ግብር ማስመረቅ እና የርቀት ትምህርት መጀመር ከኮሌጁ የወደፊት ዕቅዶች መካከል የሚጠቀሱ ተግባራት መኾናቸውንም አስረድተዋል፡፡

የኮሌጁ ተመራቂዎች በከፊል

አጠቃላይ የኮሌጁን የማስተማር ተልእኮ በሚመለከት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ ምክትል ዲኑ እንዳብራሩት ኮሌጁ ከኅዳር ወር ፳፻፰ ዓ.ም ጀምሮ ሰርጎ ገብ መናፍቃንን የሚከታተል ኰሚቴ አቋቁሞ ከኦርቶዶክሳዊው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ያፈነገጠ ባዕድ ትምህርት የሚያስተምሩ ደቀ መዛሙርትን በማጣራት በየጊዜው እንዲወገዙና ከትምህርት እንዲታገዱ ሲያደርግ የቆየ ሲኾን፣ በዘንድሮው ዓመትም እምነቱ ተጣርቶ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ የሃይማኖት ሕጸጽ የተገኘበት አንድ ደቀ መዝሙር እንዳይመረቅ እገዳ ተጥሎበታል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ፡- ዲያቆን ዳንኤል ታደሰ እና ቀሲስ አድማሱ ሰንበታ

ከዚሁ ዅሉ ጋርም የካህናትና ሰባክያነ ወንጌል እጥረት ካሉባቸው አህጉረ ስብከት መሥፈርቱን የሚያሟሉ ሰባት ደቀ መዛሙርትን በመምረጥ ማኅበረ ቅዱሳን ሙሉ ወጫቸውን ሸፍኖ በመንፈሳዊ ኮሌጁ እያስተማረ መኾኑን፤ ከእነዚህ መካከልም ከምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት የመጡት ሁለቱ ሰባክያነ ወንጌል ቀሲስ አድማሱ ሰንበታ እና ዲያቆን ዳንኤል ታደሰ ለሦስት ዓመታት ተምረው በዘንድሮው ዓመት መመረቃቸውን ከቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡

ዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ሁለቱ ተመራቂዎችም ማኅበሩ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን በእግዚአብሔር ስም አቅርበዋል፡፡ ለወደፊቱም በየቦታው እየተዘዋወሩ ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ተቋቁመው በክህነት እና በስብከተ ወንጌል ሰፊ አገልግሎት በመስጠት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰጣቻቸውን መንፈሳዊ ሓላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዐውደ ርእዩ በአሜሪካ ቀረበ

በዝግጅት ክፍሉ

ሰኔ ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ›› በሚል ርእስ የተዘጋጀው ፭ኛው ዙር የማኅበረ ቅዱሳን ዐውደ ርእይ ከሰኔ ፲ – ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በአሜሪካ አገር መቅረቡን የአሜሪካ ማእከል አስታወቀ፡፡

ዐውደ ርእዩ በጸሎተ ወንጌል ሲከፈት

በአትላንታ ንዑስ ማእከል አዘጋጅነት በአትላንታ ከተማ በደብል ትሪ ሆቴል በቀረበው በዚህ ልዩ ዐውደ ርእይ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የየአጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች እና የመንፈሳውያን ማኅበራት አባላት፣ ታዳጊ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ የአሜሪካ ምእመናን መታደማቸውን የንዑስ ማእከሉንና የዝግጅት ኰሚቴውን ሪፖርት ጠቅሶ ማእከሉ ዘግቧል፡፡

ዐውደ ርእዩ በአባቶች ቡራኬ ሲጀመር

በመኪና ከአራት እስከ ዐሥር ሰዓታት ከሚወስዱ ክፍለ ግዛቶች (ስቴቶች) ጭምር ዐውደ ርእዩን ለመመልከት በአትላንታ ከተማ የተገኙ ምእመናን እንደ ነበሩም ከዝግጅት ኰሚቴው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡ የተመልካቾች ቍጥር ከመብዛቱ የተነሣ ዐውደ ርእዩ በሁለት ክፍሎች የቀረበ ሲኾን፣ ትዕይንቶቹም በእንግሊዝኛ ቋንቋ እየተተረጐሙ ተመልካቾች በሚረዱት መልኩ ተብራርተዋል፡፡

የብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መልእክትና ቃለ ምዕዳን በመጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት ሲቀርብ

ዐውደ ርእዩ በጸሎተ ወንጌል በተከፈተበት ዕለት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መልእክትና ቃለ ምዕዳን በመጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት የአትላንታ ዳግማዊ ቁልቢ ደብረ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ሃይማኖት አብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ ቀርቧል፡፡

በመልእክታቸው እንደ ተጠቀሰው የዐውደ ርእዩ ትዕይንቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጕመው እንዲቀርቡ መደረጋቸው ይበል የሚያሰኝ ተግባር መኾኑን ብፁዕነታቸው አድንቀዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለሕዝበ ክርስቲያኑ በስፋት ለማዳረስ ይቻል ዘንድ ይህ መንፈሳዊ አገልግሎት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በሌሎች ከተሞችም እንዲከናወን ያሳሰቡት ብፁዕነታቸው አገልግሎቱን ሀገረ ስብከታቸው እንደሚደግፍም ቃል ገብተዋል፡፡

የዐውደ ርእዩ ታዳሚ አባቶች እና ምእመናን በከፊል

በዐውደ ርእዩ ከተሰሙ መልካም ዜናዎች አንዱ አንድ መቶ ሦስት የአብነት ተማሪዎችን በአንድ ለአንድ የድጋፍ ዘዴ ለመርዳትና ለማስተማር የሚያስችል ቃል መገባቱ ሲኾን፣ በቍጥር ከአራት እስከ ዐሥር የሚደርሱ የአብነት ተማሪዎችን በግል ወጫቸው ለማስተማር አንዳንድ ምእመናን ቃል ገብተዋል፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም ለጎንደር በአታ የቅኔ ጉባኤ ቤት ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል $2,628 (ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ሃያ ስምንት ዶላር) ምእመናን ለግሰዋል፡፡

የዐውደ ርእዩ ተሳታፊ ምእመናን በከፊል

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ዕለት መልእክት ያስተላለፉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ዐውደ ርእዩ አስተማሪ እንደ ነበር አስታውሰው በዚህም ይህን ሠራን ብሎ መታበይ እንደማያስፈልግ እና ስለ ሥራው ዅሉ እግዚአብሔርን ማመስገን ተገቢ እንደ ኾነ አስተምረዋል፡፡

የአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ ማንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ዕርገተ ቃል ‹‹አሁን ታሪክ ተቀይሯል፡፡ የአገልግሎቱ በር ተከፍቷል፡፡ ስለኾነም ማኅበሩ በአትላንታ ሰፋፊ ራዎችን መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ከሕዝቡ ጥያቄና አስተያየት የተረዳነውም ይህንኑ ነው፡፡ ስለዚህ በርቱ›› በማለት አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

‹‹ለዚህ ዅሉ ሥራ መሳካት ምክንያቱ እግዚአብሔር ከኛ ጋር ስለ ኾነ ነው›› ያሉት የአትላንታ መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ቀሲስ ያዕቆብ በበኩላቸው፣ ንዑስ ማእከሉ በዚህ ሥራ ብቻ ሳይወሰን ሌሎች መንፈሳውያን ተግባራትንም አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡

ምእመናን የዐውደ ርእዩን ትዕይንቶች ሲከታተሉ (በከፊል)

በዝግጅቱ የቤተ ክርስቲያንን አስተዋጽዖ፣ ፈተናዎችንና የምእመናንን ድርሻ በስፋት እንደ ተረዱበት እና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የዅሉም ምእመናን ጉዳይ መኾኑን እንደ ተገነዘቡበት የዐውደ ርእዩ ጐብኝዎች በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

ምእመናን የዐውደ ርእዩን ትዕይንቶች ሲከታተሉ (በከፊል)

በመጨረሻም ለዚህ መርሐ ግብር መሳካት ትብብርና እገዛ ላደረጉ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች፣ ለሰበካ ጉባኤ አባላትና ማኅበረ ካህናት፤ ለየሰንበት ት/ቤቶች አባላት፤ ድጋፍ በመስጠት (ስፖንሰር በማድረግ) ለተባበሩ የግል ድርጅቶች እና ለልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን (ሚዲያ) አካላት የዐውደ ርእዩ አዘጋጅ ኰሚቴ ላቅ ያለ ምስጋናውን በማኅበረ ቅዱሳን ስም አቅርቧል፡፡

ከዐውደ ርእዩ ትዕይንቶች ከፊሉ

ዐውደ ርእዩ በሚቀጥለው ቅዳሜና እሑድ (ሰኔ ፲፯ እና ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም) በዋሽንግተን ስቴት ሲያትል ከተማ እንደሚቀርብ የአሜሪካ ማእከል አስታውቋል፡፡

ከዐውደ ርእዩ ክውን ትዕይንቶች አንዱ (የአብነት ተማሪዎች በትምህርት ላይ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ‹‹የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ›› በሚል ርእስ ያዘጋጀው ፭ኛ ዙር ዐውደ ርእይ ከግንቦት ፲፯ – ፳፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማእከል ቀርቦ በብዙ ሺሕ ሕዝብ እንደ ተጐበኘ የሚታወስ ነው፡፡

ይህን ዐውደ ርእይ በርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ማእከላት በየጊዜው እያዘጋጁ ትምህርቱ ለምእመናን እንዲዳረስ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

በቅርቡም ከአገር ውስጥ ማእከላት መካከል ባሕር ዳር ማእከል ከግንቦት ፬ – ፲፫፤ ፍኖተ ሰላም ማእከል ከሰኔ ፰ – ፲፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በቅደም ተከተል ዐውደ ርእዩን አዘጋጅተው ለብዙ ሺሕ ሕዝብ እንዳስጐበኙ ከማእከላቱ የደረሰን መረጃ ያመላክታል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የኖላዊነት ተልእኮው ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳሰቡ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

የኢትዮጵያ ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰባክያነ ወንጌል፤ በተለይ ምእመናንን በቅርበት የመከታተል ሓላፊነት ያለባቸው የእግዚአብሔር እንደራሴዎች፣ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃዎች የኾኑ ካህናት የነፍስ ልጆቻቸውን ተግተው በማስተማር የኖላዊነት ተልእኮአቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አሳሰቡ፡፡

ብፁዕነታቸው ሰኔ ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከማኅበረ ቅዱሳን ጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ በ፳፻፱ ዓ.ም ርክበ ካህናት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችን መሠረት በማድረግ በተለይ የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴዎችን፣ ዐቂበ ምእመናንን፣ የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ አገልግሎትና የልማት ሥራዎችን በሚመለከት ሰፋ ያለ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ቅዱስ ሲኖዶስን የሚመራውና ሥራውን የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ሰው ምክንያት ነው›› ያሉት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ የመጨረሻው ወሳኝ አካል የኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት፣ ለምእመናን ሕይወት የሚጠቅሙ መመርያዎችን በየጊዜው ሲያወጣ እና ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ አክብሮ መቀበል ክርስቲያናዊ ግዴታ መኾኑን አስረድተዋል፡፡ መመርያዎቹና ውሳኔዎቹ በተግባር ላይ እንዲውሉም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ሕዝበ ክርስቲያኑ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው ተወግዘው ከተለዩ መናፍቃን በተጨማሪ በብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከት ደቡብ ምዕራብ ሸዋም ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጪ የኾኑ ትምህርቶችንና መዝሙሮችንም በስውር ሲያስተምሩ፤ ሲዘምሩ የነበሩ ዘጠኝ የተሐድሶ ኑፋቄ አራማጆችን አውግዘው መለየታቸውን ብፁዕነታቸው አውስተው፣ በሦስት መንገዶች ማለትም አውግዞ በመለየት፤ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በማገድ እና ማስጠንቀቂያ በመስጠት ሀገረ ስብከታቸው በመናፍቃኑ ላይ ርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል፡፡

የኑፋቄ ትምህርት እንደሚሰጡ ሕጋዊ ማስረጃ ቀርቦባቸው ከአሁን በፊትም ኾነ በዘንድሮው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተወግዘው ከቤተ ክርስቲያን አንድነት የተለዩ መናፍቃን ጥፋታቸውን አምነው፣ ስሕተታቸውን አርመው በንስሐ ለመመለስ ዝግጁ ከኾኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በይቅርታ እንደምትቀበላቸው፤ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ በመተላለፍ ምእመናንን ማሰናከላቸውን ከቀጠሉ ግን በሕግ እንደምትጠይቃቸው አስረድተዋል፡፡

ሐዋርያዊ ተልእኮን በሚመለከትም ማኅበረ ቅዱሳን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በማዘጋጀት በአማርኛ ቋንቋ እና አፋን ኦሮሞ ትምህርተ ወንጌል ከመስጠቱ ባሻገር ምእመናንን በማስተባበር ለተቸገሩ አብያተ ክርስቲያናት የገንዘብ ድጋፍ በማድረጉ የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን መደሰታቸውን ብፁዕነታቸው ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ይበልጥ ለማፋጠን ይቻል ዘንድ ማኅበሩ ቅዱሳት መጻሕፍትንና መንፈሳውያን መዝሙራትን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች በማሠራጨት አገልግሎቱን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡

የስብከተ ወንጌል አገልግሎቱን በስፋት ማዳረስ፣ የአብነት ት/ቤቶችን ማስፋፋት፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እና ገቢ የሚያስገኙ ፕሮጀክቶችን መተግበር ወደፊት ሊከናወኑ የታቃዱ ተግባራት መኾናቸውን ያስታወቁት ብፁዕነታቸው፣ በሀገረ ስብከቱ ሥር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን በዘላቂነት ለመደገፍ ሲባል በወሊሶ ከተማ ለሚገነባው ባለ አራት ፎቅ ዅለገብ ሕንጻ ግንባታም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍ እንዲያደርግ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ‹‹ዘመኑ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ፈተና የበዛበት፤ ከውስጥም ከውጪም ጠላቶች የበረከቱበት ወቅት ነው፡፡ በተለይ ትክክለኛ ሰባኪ እና የቤተ ክርስቲያን ልጅ መስለው በቅዱሳን ስም የሚሰበሰበውን ገንዘቧን እየበሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እየጎዱ ያሉ አፅራረ ቤተ ክርስቲያንም እየበዙ ነው፡፡ ስለኾነም ሰባክያነ ወንጌል፣ ቀሳውስት እና ዲያቆናት፣ እንደዚሁም የሰንበት /ቤት ወጣቶች ምእመናኑን በሥርዓት ሊያስተምሩ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም ከኑፋቄ ትምህርት አራማጆች ሊጠነቀቅ፤ በቃለ እግዚአብሔር በመጎልበትም ራሱን ከስሕተት ሊጠብቅ ይገባል›› በማለት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ስዊድናዊው ፕሮፌሰር አምሳ ሁለት መጻሕፍትን አበረከቱ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በስዊድን አገር የሉንድ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የኾኑት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሮቢንሰን በልዩ ልዩ ባለሙያዎችና በተለያዩ አርእስት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተዘጋጁ አምሳ ሁለት መጻሕፍትን ለማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል በስጦታ መልክ አበረከቱ፡፡

ፕ/ር ሳሙኤል ሮቢንሰን መጻሕፍታቸውን ሲያስረክቡ

‹TAITU Empress of Ethiopia; Lake Tana and The Blue Nile an Abyssinian Quest; Education in Ethiopia Prospect and Retrospect; The Abyssinian Difficulty the Emperor Tewodross and the Magdala Campaign 1867-68; Slavery, Slave Trade and Abolition Attempts in Egypt and Sudan› የሚሉት ከአምሳ ሁለቱ መጻሕፍት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ መጻሕፍቱን ሲረከቡ

ወላጅ አባታቸው ፕሮፌሰር ሮቢንሰን፣ ከሌላ እምነት ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት የተመለሱ የቤተ ክርስቲያን ልጅ እንደ ነበሩና በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ለበርካታ ዓመታት በመምህርነት አገልግሎት እንደ ሰጡ ያስታወሱት ፕሮፌሰር ሳሙኤል፣ ማኅበሩ የሚያከናውነውን የጥናትና ምርምር ተግባር ለመደገፍና ለማበረታታት በውድ ገንዘብ የገዟቸውን እነዚህን መጻሕፍት በወላጅ አባታቸው ስም ለማእከሉ ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡

በምጣኔ ሀብት፣ በታሪክ፣ በኅብረተሰብና አካባቢ ሳይንስ፣ በፖለቲካ እና ሌላም የትምህርት መስክ የተዘጋጁት መጻሕፍቱ በተለይ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን፣ ተመራማሪዎችና ተማሪዎች የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ መጻሕፍቶቻቸውን ለማኅበሩ ያበረከቱት በስዊድን አገር የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ በሚገኙት የቀድሞው የጥናትና ምርምር ማእከሉ ዳይሬክተር ቀሲስ መንግሥቱ ጎበዜ አስተባባሪነት መኾኑን የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ሞላ ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጌታቸው እንዳስታወቁት መጻሕፍቱ በተበረከቱበት ሚያዝያ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከልዩ ልዩ ዓለማቀፍ የትምህርት ተቋማት የመጡ የውጭ አገር ዜጎች ከፕሮፌሰር ሳሙኤል ጋር በማኅበሩ ሕንጻ ተገኝተዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች በከፊል

በዕለቱ በነበረው መርሐ ግብር፣ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ (ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ዶክተር ዮሐንስ አድገህ (የጥናትና ምርምር ማእከሉ ዋና ዳይሬክተር) የማኅበረ ቅዱሳንን አመሠራረትና የማእከሉን ተግባር በአጭሩ ለእንግዶቹ አቅርበዋል፡፡ ቀሲስ መንግሥቱ ጎበዜም ማኅበሩ በጥናትና ምርምር ማእከሉ አማካይነት ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን አገልግሎት አስረድተዋል፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ፡- ቀሲስ መንግሥቱ ጎበዜ፣ ፕ/ር ሽፈራው በቀለ እና ፕ/ር ሳሙኤል ሮቢንሰን

መጻሕፍቱ አንባብያን ይጠቀሙባቸው ዘንድ በሕጋዊ ደረሰኝ ወደ ማኅበሩ ቤተ መጻሕፍት ገቢ መደረጋቸውን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው ሞላ፣ ማኅበረ ቅዱሳን ምሁራንን በማሳተፍ የሚያከናውነውን የጥናትና ምርምር ሥራ የውጭ አገር ዜጎች ለመደገፍ መነሣሣታቸው ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በውጩ ዓለም ዘንድ ያላትን ልዩ ቦታ ያመላክታል፡፡ መጻሕፍት ልገሳውም የጥናትና ምርምር ማእከሉን ወደ ተቋም ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ከግብ ለማድረስ ያግዛል›› ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ሞላ የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር

በመጨረሻም ፕሮፌሰር ሳሙኤልንና ሌሎች የትምህርት ባልንጀሮቻቸውን በማስተባበር መጻሕፍቱ ለማኅበሩ ቤተ መጻሕፍት ገቢ እንዲኾኑ ያደረጉትን ቀሲስ መንግሥቱ ጎበዜን የማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር በቤተ ክርስቲያን ስም አመስግነው ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን የሚሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለመደገፍ ፈቃደኛ የኾናችሁ አጋሮቻችን! እንደ ፕሮፌሰር ሳሙኤል ሮቢንሰን ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ለቤተ መጻሕፍታችን በማበርከት መንፈሳዊ ድርሻችሁን እንድትወጡ ይኹን›› ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጥናትና ምርምር ማእከሉ ሥር የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ቤተ መጻሕፍት ቅዱሳት መጻሕፍትን ብቻ ሳይኾን በልዩ ልዩ የትምህርት መስክና ቋንቋ የተዘጋጁ በርካታ ዓለማቀፍ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን ለንባብ እንደሚያቀርብ፤ ዘወትር ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ከጠዋቱ 2፡3 – ምሽቱ 1፡00 ሰዓት (የምሳ ሰዓትን ጨምሮ) አገልግሎት እንደሚሰጥ ያስረዱት የማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር፣ ‹‹መንፈሳዊም ኾነ ዘመናዊ ዕውቀታችሁን ለማዳበር የምትፈልጉ ዅሉ ከማኅበሩ ሕንጻ ስድስተኛ ፎቅ ድረስ በመምጣት በአገልግሎቱ ተጠቃሚ ኹኑ›› ሲሉ መንፈሳዊ ጥሪአቸውን አቅርበዋል፡፡

በግብጽ አብያተ ክርስቲያናት በደረሰ የቦምብ ጥቃት ከዐርባ አራት በላይ ክርስቲያኖች ዐረፉ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሚያዝያ ቀን ፳፻፱ .

egypt10

በግብጽ አገር የቅዱስ ማርቆስ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ አብያተ ክርስቲያናት

በግብጽ አገር በአሌክሳንደርያ እና ታንታ ከተሞች በቅዱስ ማርቆስ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብጽ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ሚያዝያ ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በደረሰ ከፍተኛ የቦምብ ጥቃት ከዐርባ አራት በላይ ክርስቲያኖች ሲያርፉ፣  ከአንድ መቶ በላይ የሚኾኑት ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳረጉ፡፡

egypt11

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው አብያተ ክርስቲያናት ውስጣዊ ክፍል እና ጥቃቱ በሕንጻዎቹ ላይ ያደረሰው ጉዳት በከፊል

ጥቃቱ የደረሰው በርካታ የግብጽ ምእመናን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው በዓለ ሆሣዕናን ሲያከብሩ በነበሩበት በዕለተ ሰንበት ረፋድ ላይ ሲኾን፣ በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት በምእመናን በምእመናን ላይ ለደረሰው አሰቃቂ ጥቃትም ‹አይ ኤስ አይ ኤስ› ተብሎ የሚጠራው የጥፋት ቡድን ‹‹ሓላፊነቱን እወስዳለሁ›› ማለቱን፤ የሟቾች ቍጥርም ከተጠቀሰው አኃዝ በላይ እየጨመረ መምጣቱን ልዩ ልዩ የብዙኃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡

bishop-angaelos

ብፁዕ አቡነ አንጌሎስ – በእንግሊዝ አገር የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ

በእንግሊዝ አገር የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አንጌሎስ የደረሰውን ጥቃት በማስመልከት በሰጡት ቃለ ምዕዳን፡- ‹‹… በዛሬው ዕለት በዓለ ሆሣዕናን እና የክርስቶስን ወደ ኢየሩሳሌም መግባት እንዳከበርን ዅሉ፣ በዚህች ዕለት ያለፉ ወገኖቻችንም ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም መግባታቸውን እናጠይቃለን፡፡ የመድኃኒታችንን ቅዱስ ሳምንት (ሰሙነ ሕማማት) ስናከብርም የቤተሰቦቻቸውን ሐዘን እና በዚህ ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን  ወገኖቻችንን ሕመም እንጋራለን፡፡ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ታላቁን በዓለ ትንሣኤ በምናከብርበት ወቀትም ምድራዊ ሕይወታችን ብዙ ጊዜ በመከራ የተመላ የሕይወት ጉዞ እንደ ኾነና ይህ መከራም በመጨረሻው ዘመን ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔር መንግሥት ለመውረስ እንደሚያበቃን እናስተውላለን›› የሚል መልእክት አስተላፈልዋል፡፡

egypt12

‹‹ስለ እርሱ ዅልጊዜ ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎች ኾነናል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች በተለይ ግብጻውያን በተደጋጋሚ በአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ጥቃት እየደረሰባቸው ነው፡፡ በዚህ ዓመት በግብጽ ከደረሱ አሰቃቂ ጥቃቶች መካከል ታኅሣሥ ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በካይሮ ከተማ የደረሰው የቦምብ ፍንዳታ ከሃያ አምስት በላይ ግብጻውያን ክርስቲያኖችን መቅሠፉና ከአምሳ በላይ የሚኾኑትን ማቍሰሉ የሚታወስ ነው፡፡ በትናንትናው ዕለት የደረሰው ከፍተኛ ጥቃትም መላው የግብጽ ሕዝብን አስጨንቋል፡፡ የግብጽ መንግሥትም ለሦስት ወራት የሚቆይ የአስኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቷል፡፡

ምንጮች፡

  • Alahram /Daily News Egypt
  • Aljazeera
  • BBC
  • Christian Today
  • CNN
  • Orthodoxy Cognate Page
  • Reuters

የ፲፪ኛው ሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በፎቶ

መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን ለ፲፪ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በቾ ወረዳ ቤተ ክህነት ከአዲስ አበባ ከተማ በሰባ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቱሉ ጉጂ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዛሬው ዕለት ተካሒዷል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይም ከዐሥራ ሦስት ሺሕ ሁለት መቶ አምሳ በላይ ምእመናን መሳተፋቸው ታውቋል፡፡ መርሐ ግብሩ ከሰዓታት በፊት በጸሎት የተፈጸመ ሲኾን፣ የጉባኤውን አጠቃላይ ኹኔታም በሚከተሉት ፎቶዎች ትመለከቱ ዘንድ ጋበዝናችሁ፤

img_0137

ቱሉ ጉጂ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን

img_0275

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል

img_0348

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ

img_0317

ብፁዕ አቡነ ዳንኤል ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ

img_0092

img_0097

መርሐ ግብሩ በጸሎተ ወንጌል ሲከፈት

img_0103

img_0098

የጉባኤው ተሳታፊዎች ቆመው ጸሎተ ወንጌል ሲያስደርሱ

img_0290

የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል

img_0237

ምክረ አበው አቅራቢ መምህራን

img_0243

img_0227

img_0271

የማኅበረ ቅዱሳን ዘማርያን የበገና ዝማሬ ሲያቀርቡ

img_0113

የመርካቶ ደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ሰ/ት/ቤት የጎልማሶች መዘምራን መዝሙር ሲያቀርቡ

img_0213

መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ የበገና ዝማሬ ሲያቀርቡ

img_0121

የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል

img_0110

img_0160

img_0326

img_0329

img_0153

img_0180

img_0169

የጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል

img_0216

በጉባኤው የተገኙ የቱሉ ጉጂና የአካባቢው ምእመናን በከፊል

img_0005

የጉዞው ቅድመ ዝግጅት

img_0018

img_0021

img_0012

img_0047

ጉዞ ወደ ቱሉ ጉጂ

img_0076

የቱሉ ጉጂ አካባቢ ወጣቶች መንገድ ሲያስተካክሉ

img_0078

img_0081

የመኪኖች መቆሚያ እና የጉባኤው ቦታ በከፊል ከርቀት ሲታይ

img_0122

img_0087

ምእመናን ከመኪና ወርደው ወደ ጉባኤው ሲያመሩ

img_0083

img_0132

የጉባኤው ሥፍራ በከፊል

img_0350

ጉባኤው በጸሎት ከተፈጸመ በኋላ ምእመናን ወደ ተዘጋጁላቸው መኪኖች ሲመለሱ

img_0355

img_0352

img_0353

img_0360

በበልበሊት ኢየሱስ ገዳም ዙርያ የተነሣው የእሳት ቃጠሎ ጠፋ

የምዕራፈ ቅዱሳን በልበሊት ኢየሱስ ገዳም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን

በዝግጅት ክፍሉ

መጋቢት ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት በእንሳሮ ወረዳ ቤተ ክህነት በምዕራፈ ቅዱሳን በልበሊት ኢየሱስ አንድነት ገዳም ዙርያ የተነሣው የእሳት ቃጠሎ መጥፋቱን የገዳሙ አበምኔት ገለጹ፡፡

መጋቢት ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከምሽቱ ፲፩ ሰዓት ገደማ በግልጽ ባልታወቀ ምክንያት የተነሣው ይህ የእሳት ቃጠሎ በገዳሙ መነኮሳት፣ በአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን እና በወረዳው የመንግሥት አካላት ጥረት ከሌሊቱ ፭ ሰዓት ገደማ ጠፍቷል፡፡

01

የአካባቢው መልክዐ ምድር

ቃጠሎው በቤተ ክርስቲያኑ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት ባያደርስም በግምት አምስት ሄክታር የደን ሽፋንና ሦስት ሄክታር የአትክልት ቦታ በድምሩ ስምንት ሄክታር የሚኾነውን የገዳሙ መነኮሳት ያለሙትን የገዳሙን ይዞታ ማውደሙን የገዳሙ አበምኔት በኵረ ትጉሃን ቆሞስ አባ ሐረገ ወይን አድማሱ አስታውቀዋል፡፡

ከሥፍራው ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አገልጋዮች መጋቢት ፲፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በገዳሙ ተገኝተው ማኅበረ መነኮሳቱን ያጽናኑ ሲኾን፣ ማኅበረ መነኮሳቱም ተረጋግተው ወደ ቀደመ የጸሎት ተግባራቸው ተመልሰዋል፡፡

?

ገዳሙ ከሁለት መቶ አምሳ በላይ መነኮሳት እና መነኮሳይያት፤ እንደዚሁም ወደ ሁለት መቶ የሚደርሱ የቅኔ፣ የድጓ እና የቅዳሴ ደቀ መዛሙርት የሚገኙበት ሲኾን፣ ገዳሙ የሚተዳደርበት በቂ ገቢ የሌለው ከመኾኑ ባሻገር የአብነት ተማሪዎቹም በመጠለያ እና በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል ተቸግረዋል፡፡ ‹‹ስለዚህም የገዳሙን ህልውና ለመጠበቅ እና የአብነት ተማሪዎችን ከስደት ለመታደግ መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፋችሁ አይለየን›› ሲሉ የገዳሙ አበምኔት በገዳሙና በማኅበረ መነኮሳቱ ስም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

02

ቃጠሎው ያደረሰው ጉዳት በከፊል

ምዕራፈ ቅዱሳን በልበሊት ኢየሱስ አንድነት ገዳም መልክዐ ምድራዊ አቀማመጡ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በመኾኑ በየጊዜው በግምት ስድሳ ሄክታር የሚደርስ የገዳሙ ይዞታ በጎርፍ መወሰዱን፤ በአሁኑ ሰዓትም በክልሉ መንግሥት በጀት በገዳሙ ዙርያ የአፈር ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ከገዳሙ ጽ/ቤት ለመረዳት ተችሏል፡፡

መረጃውን ያደረሰን በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ነው፡፡

የተወደዳችሁ ምእመናን! በየጊዜው በገዳሞቻችን ላይ የሚደርሰውን የእሳት ቃጠሎ እና መሰል አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ዅላችንም ተግተን፣ ነቅተን ቤተ ክርስቲያናችንን እንጠብቅ ስንል መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እርማት

በዚህ ዜና ሦስተኛው አንቀጽ ላይ ‹… ስምንት ሺሕ ሄክታር …› በሚል የተገለጸው በስሕተት ስለ ኾነ ስምንት ሄክታር› ተብሎ መስተካከሉን ከይቅርታ ጋር ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

‹‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ ታማኝ አገልጋይ ማነው?››

በመ/ ምስጢረ ሥላሴ ማናየ

መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስያሜ የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ‹ገብር ኄር› ይባላል፡፡ ሰያሜውን የሰጠውም ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ከአምስቱ መጻሕፍቶቹ አንዱ በኾነው ጾመ ድጓ መጽሐፍ ሳምንቱን የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዓተ ማኅሌቱ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ በስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብር ኄርን የሚያወሳ ነው ማለት ስለ ታማኝ አገልጋይ የሚያስረዳ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ፳፭፥፲፬-፳፭ የተገለጸውና በዕለቱ የሚነበበው ወንጌል የሚነግረንም ይህንኑ ትምህርት ነው፡፡

አንድ ባዕለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሔደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ ዐሥር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ‹‹ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አምስት አተረፍኩ›› አለው፡፡ ‹‹ገብር ኄር ወምዕመን ዘበውሁድ ምእምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፤ አንተ ታማኝ ባሪያ! በጥቂቱ ታምነሃልበብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ‹‹ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፤›› ብሎ መክሊቱን አቀረበ፡፡ ጌታውም፡- ‹‹አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልበብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡

አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ‹‹ጌታዬ፣ አንተ ክፉና ጨካኝ፤ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ፤ እንደ ኾንክ ስለ አወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ›› አለው፡፡ ‹‹አንተ ሰነፍ ባሪያ! መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር፡፡ እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር፤›› አለና ‹‹ኑ፤ የዚህን ሐኬተኛ መክሊት ውሰዱና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል›፡፡ ንዑ ይህን ሰነፍና ሐኬተኛ ባርያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑ ጨለማ ወደ አለበት ውሰዱት! ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨምሩት!›› የሚል ፍርድ ወሰነበት፡፡

ባዕለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት ጌታችን በዕለተ ምጽአት ለዅሉም በሠራው ምግባር መጠን ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡ ያገለገሉትን ‹‹ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፉ አገልጋይ ወደ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ቦታ መወርወሩም ኀጥአን ወደ ሲኦል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ከላይ ያነሳነው የቅዱስ ወንጌል ቃል፡- ‹‹ታማኝ አገልጋይ ማነው?›› ይላል፡፡ ይህ እያንዳንዱ በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ የሰው ልጅ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ አምላካዊ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀጥለን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው ከተመዘገበላቸው ታማኝ አገልጋዮች መካከል ሦስቱን ጠቅሰን ከእነርሱ ሕይወት እንድንማር የሚያነሣሣ መጠነኛ ትምህርት እናቀርባለን፤

ሙሴ

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ታማኝ አገልጋይ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ ‹‹በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በሕልም አናግረዋለሁ፡፡ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ዅሉ የታመነ ነው፤›› እንዲል (ዘኍ.፲፪፥፮)፡፡ ይህ የፍጡር ቃል ሳይኾን በፈጣሪው የተሰጠ ምስክርነት ነው፡፡ በውኑ በዘመናችን እንኳን ፈጣሪ ፍጡራን ታማኝነቱን የሚመሰክሩለት አጋልጋይ ይኖር ይኾን? እንጃ! የሙሴን ታማኝ አገልጋይነት በረኃ፣ ስደት፣ መከራ፣ የፈርዖን ግርማ እና ቁጣ አልበገረውም፡፡ ዐርባ ዓመት ስለ ወንድሞቹ በመሰደድ ዐርባ ዓመት ደግሞ የተሰደደላቸው ወንድሞቹን በመምራት፣ ባሕር በመክፈል፣ ጠላት በመግደል፣ መና በማውረድ፣ ደመና በመጋረድ ውኃ ከዓለት አፍልቆ በማጠጣት መከራውን ከወገኖቹ ጋር በመቀበል የቀኑን ኃሩር፣ የሌሊቱን ቁር (ብርድ) ታግሦ በታማኝነት አገልግሏል፡፡ ታማኝነቱም እስከ ሞት ድረስ ነበር፡፡

‹‹ሙሴም ወደ እግዚብሔር ተመልሶወዮ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፡፡ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ? ከባለሟልነትህ አውጣኝ?›› ተብሎ ተጽፏል (ዘፀ.፴፪፥፴፩)፡፡ ታማኝ አገልጋይ የሚባለው እንደ ሙሴ ‹‹እኔ ልሙት ሌሎች ይዳኑ›› የሚል ሰው ነው፡፡ አሁን የምናየው ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ‹‹ሰዎች ይሙቱ፤ እኔ ልኑር፡፡ ሰዎች ጦም ይደሩ፤ እኔ ልብላ፡፡ ሰዎች ይራቆቱ፤ እኔ ልልበስ፡፡ ሰዎች ይዘኑ፤ እኔ ልደሰት›› ነው፡፡ ይህም ታማኝ አገልጋይ ያለ መኾን መገለጫ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ እንጂ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም አይደለም፡፡

ዛሬ በዓለማችን የምንመለከተው ድርጊት ግን ‹‹ጩኸት ለአሞራ መብል ለጅግራ›› የሚባለውን ዓይነት ነው፡፡ በታማኝ አገልጋዮች ድካም የሚሸለሙ፤ ታማኝ አገልጋዮች በሠሩት ሪፖርት የሚያቀርቡ፤ ባልሠሩት ሥራ የሚወደሱ፤ ከጥቅሙ እንጂ ከድካሙ መካፈል የማይሹ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንቅፋት የሚመታው እግርን ነው፡፡ አክሊል የሚቀዳጀው ግን ራስ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ማለት እንደራስ አክሊል ዘውድ የሚጸፋ ብቻ ሳይኾን እንደ እግር እንቅፋቱን፣ እሾኹን፣ ውጣ ውረዱን፣ መከራውንና ድካሙን የሚቀበል ነው፡፡ በጥቅም ጊዜ ለራሱ በአካፋ የሚዝቅ፤ ሌሎች በጭልፋ የሚቆነጥር አይደለም፡፡ ሙሴ ባሕር የከፈለው፣ መና ያወረደው ደመና የጋረደው ውኃ ያፈለቀው ለራሱ አልነበረም፤ ለሚመራቸው ሕዝብ ነበር እንጂ፡፡ ታማኝ አገልጋይ ያሰኘውም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ከብሮበታል፤ ተመስግኖበታልም፡፡

ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ዘመነ መሳፍንት አልፎ ዘመነ ነገሥት ሲተካ እስራኤልን በንጉሥነት እንዲመራ እግዚአብሔር ከበግ ጥበቃ የመረጠው ንጉሥ ነው፡፡ እርሱም በተሰጠው ሥልጣን ሳይታበይ በታማኝነት ሕዝበ እስራኤልን መርቷል፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ መሰከረው ዅሉ ስለ ለዳዊትም መስክሮለታል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር እንደ ልቡ የኾነ ሰው መርጧልናየዘይቱን ቀንድ ሞልተህ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (፩ሳሙ. ፲፫፥፲፫፤ ፲፮፥፪)፡፡

በመዝሙረ ዳዊትም ‹‹ወረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ወቀባዕክዎ ቅብዐ ቅዱስ፤ ባሪያዬ ዳዊትን አገኘሁት የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት›› ተብሎ ተነግሮለታል (መዝ. ፹፰፥፳)፡፡ ይህንንም አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ሰዓታት ድርሰቱ፡- ‹‹ረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ብእሴ ምእመነ ዘከመ ልብየ፤ አገልጋዬ ዳዊትን እንደ ልቤ የታመነ ሰውን አገኘሁት›› ሲል ተርጕሞታል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ከመንገሡ በፊት የተገኘው በታማኝነት ነበር፡፡ ከነገሠ በኋላም ታማኝ ነበር፡፡ አሁን በዚህ ዓለም የምንኖር እኛ ግን በድኅነት ታማኝ እንኾንና ሀብት፣ ሹመት፣ ሥልጣን ሲመጣ ታማኝነትን እናጣለን፤ እንዲያውም ታማኝነትን እንንቀዋለን፡፡ መስረቅ ጀግንነት ይመስለናል፡፡ መዋሸት ሥልጣኔ ይኾንልናል፡፡

ዳዊት ሳይሾም በጎቹን በመጠበቅ ታማኝ ነበር፡፡ በጎቹን የሚነጥቅ ተኩላ አንበሳ ቢመጣ በኋላው ተከትሎ ነብሩን በጡጫ፣ አንበሳውን በእርግጫ ብሎ በጎቹን ያስጥል ነበር፡፡ ‹‹እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፡፡ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር፡፡ በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፤ ከአፉም አስጥለው ነበር፡፡ በተነሣብኝም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር፡፡ ይህም ፍልስጥኤማዊ ከነዚያ እንደ አንዱ ይኾናል፤ እንግዲህ እገድለው ዘንድ፤ ከእስራኤል ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሔድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቆላፍ ምንድን ነው? ከአንበሳና ከድብ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል!›› በማለት እርሱ እንደ ተናገረው (፩ኛሳሙ.፲፯፥፴፬)፡፡

ዛሬም ቢኾን በእስራኤል ዘነፍስ በምእመናን ላይ የሚገዳደሩ ብዙ ፍልስኤማውያን ተሰልፈዋል፡፡ እነዚህን ድል የሚነሣ፤ በጎቹን ምእመናን ከተኩላ፣ ከአንበሳና፣ ከድብ አፍ የሚታደግ ታማኝ አገልጋይ ማነው? ከምእመናን ተግዳሮት የሚያርቅ ፈጣሪዬ ከመከራ ያድነኛል ብሎ የሚታመን የኢ አማንያን ብዛት የማያስፈራው ማን ነው? ከትንሽነቱ እስከ ታላቅነቱ የታመነ አገልጋይ ማነው? ለተሾመበት ሓላፊነት ታማኝ ማነው? አሁንም ዓለማችን ከሥጋውያን ባለ ሥልጣናትም ኾነ ከመንፈሳውያን መሪዎች የምትሻው ታማኝ ሰው ነው፡፡ በሙስና ያልተዘፈቀ፤ ጉቦ አይኑን ያላጨለመበት፤ ለመንጋው አርአያና ምሳሌ የሚኾን ሰው፤ ታማኝ አገልጋይ ማለት እርሱ ነው፡፡ በመሐላ የተቀበለውን የአገልግሎት ሓላፊነት የማይዘነጋ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ መምህር፣ ሐኪም፣ ዳኛ፣ ነጋዴ፣ ተማሪ፣ ወታደር፣ የቤት ሠራተኛ፣ የቢሮ ሠራተኛ ታማኝ መኾን አለበት፡፡

መንጋው በክህደት ሲጠፋ ዝም ብሎ የሚያይ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ ታማኝ አይደለም፡፡ ታማሚው እየተሰቃየ የሚዝናና ሐኪም ታማኝ አይደለም፡፡ ፍርድ የሚያጎድል፤ ድሆችን የሚበድል፤ ለደሃ አደጎች የማይፈርድ ዳኛ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ ቅቤ በሙዝ እና በድንች ቀላቅሎ፣ በርበሬ በሸክላ አፈር ጨምሮ፣ ሌሎችን አጭበርብሮ የሚሸጥ ነጋዴ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ እየነገደ ያለው በሰው ሕይወት መኾኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ዅሉም እንደየአቅሙ በተሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ ታማኝ መኾን አለበት፡፡

ዮሴፍ

ዮሴፍ ለወንድሞቹ ምግባቸውን ተሸክሞ የእርሱ ስንቅ ቢያልቅ የወንድሞቹን ስንቅ ያልበላ በትንሹ የታመነ ሰው ነበር፡፡ ወንድሞቹ ሸጠውት በቤተ ጲጥፋራ በሚያገለግልበት ጊዜም ታማኝ ነበር፡፡ ታማኝነቱ በጲጥፋራ ቤት ጌታ አድርጎታል፡፡ ‹‹ዮሴፍ ተሸጠአገልጋይም ኾነ፡፡ እግሮቹ በእግር ብረት ሰለሰሉ፡፡ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች፡፡ ቃሉ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው፡፡ ንጉሥ ላከ፤ ፈታውም የሕዝብ አለቃ አድርጎ ሾመው፡፡ የቤቱም ጌታ አደረገው፡፡ በገንዘቡ ዅሉ ላይ ገዢ አደረገው፡፡ አለቆቹን እንደ እርሱ ይገሥፅ ዘንድ፤ ሽማግሌዎችን እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ፤›› ተብሎ እንደ ተነገረለት (መዝ.፻፬፥፲፯)፡፡

በዚህ ኹኔታ የነበረው ዮሴፍ የጌታው ሚስት ሲወጣ ባቱን፣ ሲገባ ደረቱን እያየች ዐይኗን ጣለችበት፤ በዝሙት አይን ተመለከተችው፡፡ ‹‹ከእኔ ጋር ተኛ›› እያለችም በየቀኑ አስቸገረችው፡፡ እርሱ ግን ‹‹እምቢ›› አላት፡፡ ለጌታው ሚስትም፡- ‹‹እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ዅሉ ለእኔ በእጄ አስረክቦኛል፡፡ በቤቱ ያለውን ምንም የሚያውቀው የለም፡፡ በዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፡፡ ሚስቱ ስለ ኾንሽ ከአንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፡፡ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? እንዴትስ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአትን እሠራለሁ?›› በማለት የዝሙት ጥያቄዋን ውድቅ አደረገባት (ዘፍ.፴፱፥፯)፡፡

በዮሴፍ ታማኝነት የጌታው ቤት ተባርኳል፡፡ ሀብቱ በዝቷል፡፡ በታማኝነቱ በቤቱ ያለውን ዅሉ ተረክቦ ነበር፡፡ የቀረበለት ፈተና ግን ከባድ ነበር፤ ኾኖም ግን በታማኝነቱ ለማለፍ ችሏል፡፡ ዮሴፍ በታማኝ አገልጋይነቱ በመጣበት መከራ ቢታሰርም እንኳን ያለ ሹመት አላደረም፤ የእስረኞች አለቃ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ሲወጣም ግብጽን በሙሉ መርቷል፡፡ በግብጻውያን ላይ ተሾሟል፤ በጥቂቱ ታምኗልና፡፡ ‹‹በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል›› እንዲል (ማቴ.፳፭፥፳፬)፡፡ዛሬ በእየአንዳንዱ ጓዳ እንደ እሳት የሚያቃጥሉ አገልጋዮች ናቸው ያሉት፡፡ ልጅ በፈላ ውኃ የሚቀቅሉ ናቸው የሚበዙት፡፡ እንኳን በዅሉ ገንዘብ ለመሾም በጥቃቅን ዕቃዎች እንኳን የሚታመን ሰው ጠፍቷል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- ‹‹አቤቱ አድነኝ፤ ደግ ሰው አልቋልና፡፡ ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና፤›› በማለት እንደ ተናገረው በመካከላችን መተማመን የለም (መዝ.፲፩፥፩)፡፡

እናም ከእነዚህ ሦስት ታማኝ አገልጋዮች (ሙሴ፣ ዳዊት እና ዮሴፍ) ሕይወት ዅሉም የሰው ልጅ ታማኝ አገልጋይነት የሚያሰጠውን ክብርና ጸጋ ተመልክቶ በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል፡፡ ታማኝ መኾን መጀመሪያ የሚጠቅመው ራስን ነው፤ ከዚያ በኋላ ለአገር፣ ለወገን፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ላመኑትም ላላመኑትም ዅሉ ጠቃሚ ይኾናል፡፡ በመጨረሻም የጽድቅ አክሊልን ይቀዳጃል፤ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳል፡፡ ታማኝነት በሰውም፣ በእግዚአብሔርም ፊት ያስከብራልና፡፡ ጻድቃን፣ ሰማዕታት ቅዱሳን በታማኝነት በማገልገላቸው ፈጣሪአቸውን ደስ አሰኝተው ከብረዋል፡፡

በሓላፊው ገንዘብ ያልታመኑት እነይሁዳ፣ ሐናንያ እና ሰጲራ የደረሰባቸውን ጉዳት አይተናል፡፡ አካን ወልደ ከርሚንም ተመሳሳይ ቅጣት ደርሶበታል (ሐዋ.፭፥፩-፳፭)፡፡ ስለ ኾነም ዅሉም በተሰማራበት የአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ኾኖ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሀለሁ፤›› የሚለውን የጌታውን የምስጋና ቃል ለመስማት ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ መልካም አገልግሎት አገልግለን፣ በእግዚአብሔር ‹አግብርት ኄራን፤ ታማኝ አገልጋዮች› እንድንባል፤ መንግሥቱንም እንድንወርስ አምላካችን ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ አዘንተኞቹን አጽናኑ

6w5a3729

ቅዱስ ፓትርያኩ ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ከሌሎችም የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ጋር ወደ አዘንተኞቹ ድንኳን ሲገቡ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በአዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ‹‹ቆሼ›› እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ መጋቢት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በድንገተኛ አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ምእመናን ቤተሰቦችን በትናንትናው ዕለት መጋቢት ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በሥፍራው ተገኝተው አጽናኑ፡፡

በደረሰው ድንገተኛ አደጋ ላለፉና ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የተሰማቸውን ኀዘን ቅዱስነታቸው ገልጸው በቃለ እግዚአብሔርና በአባታዊ ምክራቸውም አዘንተኞቹን አጽናንተዋል፡፡

ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በሥፍራው የተገኙት ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው፣ ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይና ምሥራቃዊ ዞን አዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስም እንደዚሁ ለአዘንተኞቹ የማጽናኛ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

ቆሼ ሠፈር

አደጋው የደረሰበት ቦታና አስከሬን የማውጣቱ ሥራ በከፊል

ቋሚ ሲኖዶሱ ከወሰነው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትም በአደጋው ምክንያት በጊዜአዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖች የአንድ መቶ ሺሕ ብር ድጋፍ ማድረጉን ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ መንበረ ፓትርያርካቸው ተመልሰዋል፡፡

መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ቋሚ ሲኖዶስ በአደጋው ላለፉ ምእመናን የተሰማውን ኀዘን መግለጹና ቤታቸው በአደጋው በመፍረሱ ምክንያት በጊዜአዊ መጠለያ ለሚገኙ ወገኖችም ከቤተ ክርስቲያኒቷ የሁለት መቶ ሺሕ ብር ርዳታ እንዲሰጥ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡