“በመካከላችንም ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን፤ በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛም ወደ ገነት መለሰው” (ቅዱስ ኤፍሬም)
አፈ በረከት ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ለማመስገን አጅግ አብዝቶ ይለምን የነበረ፤ በእመቤታችን ጥሪም “አመስግነኝ” የተባለ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ በድርሰቱ ምሥጢረ ሥላሴን፣ ምሥጢረ ሥጋዌን፣ ምሥጢረ ጥምቀትን፣ ምሥጢረ ቊርባንን፣ ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን፣ በአጠቃላይ ሃይማኖትን ከምግባር፣ ነገረ ድኅነትን ከነገረ ቅዱሳን ጋር አስማምቶ የደረሰና ያስተማረ ታላቅ አባት ነው፡፡ በአባቶች የተመሰለውን ምሳሌና በነቢያት የተነገረውን ትንቢት አመሥጥሮና አራቅቆ የተረጎመ ሊቅም ነው፡፡ በመሆኑ ነገረ ድኅነትን በተናገረበት ምስጋናው “በመካከላችን ሆኖ በመስቀሉ አስታረቀን፤በልዩ ትንሣኤውም ሰውን ዳግመኛ ወደ ገነት መለሰው” የሚለውን ኃይለ ቃል እናገኛለን፡፡