ስብከት

ቅድስት ቤተክርስቲያን አምልኮቷን የምትፈጽምበት እጅግ የተደራጀ ሥርዐተ አምልኮ አላት፡፡ ከዚህ ሥርዓተ አምልኮ አንዱ ክፍል ዓመታዊ የምስጋና መርሐ ግብር እና የሥርዓተ ትምህርት ነው፡፡ ይህም በሁለት መልኩ የተደራጀ ነው፡፡

ሀ. ቀናትን መሠረት በማድረግ

በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ ጥልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ድርጊቶች እና ክንውኖች በዓመቱ ውስጥ ቀናት ተመድበውላቸው በበዓላትና በአጽዋማት መልክ ይታሰባሉ፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን እነዚህን በዓላትና አጽዋማት የምታከብርበት ዓመታዊ መርሐ ግብር እና በበዓላቱና በአጽዋማቱ የሚታሰበውን ነገር አስመልክቶ አባላቶችን የምታስተምርበት ሥርዓተ ትምህርት አላት፡፡

እንደዚህ ባለ መርሐ ግብር ከሚታሰቡት መካከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ያደረጋቸው ነገሮችና ያስተማራቸው ትምህርቶች /ፅንሰት፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሳኤ፣ ዕርገት፣ ደብረ ታቦር፣ምጽአት/፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት  /ልደቷ፣ ዕረፍቷ፣ ቤተመቅደስ መግባቷ፣ ድንቅ ተአምራት ያደረገችባቸው ዕለታት/፤፣ የቅዱሳን በዓላት /ልደታቸው፣ ዕረፍታቸው፣ ተአምራት ያደረጉባቸው. . / ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ለ. እሁዶችን /ሳምንታትን/ መሠረት በማድረግ

በዓመቱ ውስጥ ያሉት ቀናት/ከመስከረም 1 እስከ ጳጉሜን 5/ ብቻ ሳይሆኑ እሁዶቹም /ሳምንታቱም/ የተለያዩ ነገሮች ይታሰቡባቸዋል፡፡ በዓመቱ ውስጥ ባሉት እሁዶች /ሳምንታት/ በእያንዳንዳቸው የሚቀርበው ምስጋና እና የሚሰጠው ትምህርት ምን እንደሆነ የሚገልጽ መርሐ ግብር እና ሥርዓተ ትምህርት አላት፡፡ ለምሳሌ ከመስከረም 1 እስከ 7 ድረስ ያለው እሁድ /ወይም በዚህ እሁድ የሚጀምረው ሳምንት/ «ዮሐንስ አኅድአ»፣«ዮሐንስ መሰከረ ይባላል፡፡ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሕይወት እና ምስክርነት የሚታሰብበት ነው፡፡

መስከረም 8 ቀን እሁድ ቀን ቢውል ያ እሁድ «ዘካርያስ» ተብሎ ይጠራና የመጥመቁ ዮሐንስ አባት የካህኑ የዘካርያስ ነገር ይታሰብበታል፡፡

ከመስከረም 9 እስከ 17 ያለው እሁድ /እና በዚህ እሁድ የሚጀምረው ሳምንት/ «ፍሬ» ይባላል፡፡ በዚህ እሁድ እግዚአብሔር ለምድር ፍሬን እንደሚሰጥ ይታሰባል፡፡
በዚህ መልኩ በዓመቱ ውስጥ ባሉት እሑዶች በሙሉ ምን እንደሚታሰብ የሚገልጽ መርሐ ግብርና ሥርዓተ ትምህርት አለ፡፡ ይህም በተለያዩ ወቅቶች ያለውን የአየር ጠባይ እና የግብርና እንቅስቃሴ ያገናዘበ ነው፡፡

 

በእነዚህ ዕለታት ምስጋና የሚቀርብበት እና ትምህርት የሚሰጥበትን ጉዳይ /ርእስ/ መወሰን ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ነገሮችም ተዘጋጅተዋል፡፡

«ስንክሳር» የሚባለው መጽሐፍ ከመስከረም አንድ እስከ ጳጉሜን 5/6 ድረስ የሚታሰቡ ቅዱሳንን እና ክንውኖችን ዝርዝር ታሪክ ይዟል፡፡

«ግጻዌ» የሚባለው መጽሐፍ በየዕለቱ /በየእሁዱ/ ከሚታሰበው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት /ከመልእከታተ ጳዉሎስ፣ ከሰባቱ መልእክታተ ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ከመዝሙረ ዳዊት፣ ከወንጌል/ መርጦ ያቀርባል፡፡

የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍትም /ድጓ፣ ዝማሬ፣ምዕሪፍ፣ ዝማሬ መዋስዕት/ በዚህ መርሐ ግብር መሠረት የተዘጋጁ ሲሆኑ በየዕለቱ ስለሚታሰቡት ነገር ዝርዝር እና ጥልቅ የሆኑ ትምህርቶችን እና ምስጋናዎችን የያዙ ናቸው፡፡

በዚህ «ስብከት» በሚለው ዓምድ ሥር ይህንን መርሐ ግብር፣ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት አድርገን ትምህርቶችን እናቀርባለን፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ዓምድ ስር የሚቀርቡት ትምህርቶች ሦስት ዓይነት ናቸው፡፡
1. ሳምንታዊ ስብከት– በዚህ ንዑስ ዓምድ ስር በእያንዳንዱ እሁድ/ሳምንት/ የሚታሰቡትን ጉዳዮች አስመልክቶ ትምህርቶች ይቀርባሉ፡፡
2. ወቅታዊ ስብከት– በዚህ ንዑስ ዓምድ ስር ቀናትን መሠረት አድርገው ከሚከበሩት በዓላት መካከል ዋና ዋናዎቹን በተመለከተ ትምህርቶች ይቀርባሉ፡፡
3. ሌሎች– ይህ ንዑስ ዓምድ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ስብከቶች የሚቀርቡበት ነው፡፡

አዘጋጆቹን በጸሎት በማሰብ፣ በሚቀርቡ ስብከቶች ላይ አስተያየት በመስጠትና ስብከቶችን በመላክ ለዚህ ዓምድ መጠናከር ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ፡፡ እግዚአብሔር ሐሳባችንን እንድንፈጽም ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ

በዳዊት ደስታ

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ ዘመነ ማቴዎስም፣ ዘመነ ማርቆስም፣ ዘመነ ሉቃስም ሆነ ዘመነ ዮሐንስ በአራቱም ዘመናት አስቀድሞ ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ይዘከራል፡፡ ዮሐንስ የስሙ ትርጉም «ጸጋ እግዚአብሔር» ማለት ነው፡፡ ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ሰዓታት ደቂቃን ቅጽበትን /ሰኮንድን/ ሳይቀር እየሰፈሩ/እየቆጠሩ/ ዕለታት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን አሁን ላለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ዓውደ ዓመት በግእዝ ሲሆን በአማርኛ የዘመን መለወጫ/ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕንቁጣጣሽ እየተባለም ይጠራል፡፡

ቅዱስ ማርቆስ ወንጌሉን ሲጽፍ «የእግዚአብሔር ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል መጀመሪያ እነሆ መንገድህን የሚጠርግ መልእከተኛዬን በፊትህ እልካለሁ የጌታን መንገድ አዘጋጅ ጥርጊያውንም አቅኑ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ» ተብሎ በኢሳይያስ እንደ ተነገረ የነቢዩ ዘካርያስ ልጅ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዘመነ ብሉይ መጨረሻና በዘመነ ሐዲስ መጀመሪያ ላይ ተነሥቶ «መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ» እያለ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት እየመሰከረ በምድረ በዳ የንስሐን ጥምቀት እያጠመቀ ለኃጢአት ሥርየት እየሰበከ መጣ ብሎ በዘመነ ወንጌል የመጀመሪያ ምዕራፍ ገልጾታል፡፡ /ማር.1.40፤ኢሳ.40.3-4/፡፡

የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተክርስቲያን አበው የበዓላቱን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርዕሰ ዓውደ ዓመት በሚሆን መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ አባቶች ደንግገዋል፡፡ / ድርሳነ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1ጠ 3/ ይህንንም በዓል አባቶቻችን በርእሰ ዓውደ ዓመት ማክበር እንደሚገባ አስበው ያደረጉት ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ሆኖ አይደለም፡፡ ለአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዓውደ ዓመት «ቅዱስ ዮሐንስ» ይባላል፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ /መስከረምን/ ሲያትት «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው በማለት ያስረዳል፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ቀኑ እየጎደለ ይሔዳል፡፡

ከዚህ በመቀጠል በዓሉ በተለያየ ስያሜ ስለመጠራቱና ትርጓሜያቸውን እንመለከታለን፡፡

ዘመን መለወጫ

አስቀድመን ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ማንነትና የዘመን መለወጫ መግቢያው ላይ በስሙ ስለመጠራቱ ተመልክተናል፡፡ ዘመን መለወጫ ደግሞ ለምን እንደተባለና ለምን መስከረም ወር ላይ እንደሆነ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንዲህ በማለት ያትታሉ፡፡ ሲያትቱም ብርሃናት/ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው፡፡ ያን ጊዜ ሌሊቱም ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱንም ጠንቀቀው ቢቆጥሩት 364 ቀናት ይሆናል፡፡ ለዘመን መታወቂያ ይሆን ዘንድ ፀሐይና ጨረቃ ከዋክብትን ፈጠረ ይላልና /ሔኖክ.21.49/፡፡ በሌላ በኩልም በዘመነ ኖኅ ዓለምን ውኃ አጥለቅልቋት ከቆየ በኋላ ዳግመኛ ከነበረው ውኃ የተገለጠችበት ወር «በመጀመሪያም ወር በምድር ታየች የንፍር ውኃው ከምድር ደረቀ» የሚለውን መሠረት አድረገው የአቡሻኽር ሊቃውንት የዘመን መለወጫን ታሪካዊ አመጣጥ ያስረዳሉ፡፡/ኩፋ.7.1/
በመሠረቱ ዘመን ተለወጠ ሲባል የሚለወጡት ወራቱ ብቻ አይደሉም፡፡ በወቅቱ የሚከሰቱት/የተከሰቱት/ መልካምም ሆነ ክፉ ነገር /ገጠመኝ/ ሲሆን ወራቶቹ ግን ያው በየዓመቱ እየተፈራረቁ ይመጣሉ፡፡ ዘመን መለወጫ ላይ የሰው ልጆች ሕይወት ሊለወጥ ይገባል፡፡ ተማሪው ተምሮ ወደቀጣዩ ክፍል /ደረጃ/ የሚለወጥበት፣ ገበሬው የክረምቱን ወራት በሚገባ ተጠቅሞ የሚቀጥለውን የበጋ ወራት የሚቀበልበት፣ ሠራተኛው የክረምቱን ዝናብ ታግሶ የፀሐይን ወራት የሚቀበልበት ሌላውም እንደዚያ ሆነው ወራቶቹ በዚያ ዘመን ያለው የተፈጥሮ ክስተቶች የሚለወጥበት ዘመን ተለወጠ እየተባለ ይነገራል፡፡

እንቁጣጣሽ

ዓመታት ተፈጽመው አዲስ ዓመት ስንጀምር ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት ፣ እንቁጣጣሽ እየተባለ ይጠራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን እንደሚያስረዱት እንቁጣጣሽ የሚለው ስያሜው አመጣጥ ወይመ ጥንተ ታሪክ በመጀመሪያ ኖኅ ለሦስቱ ልጆቹ አህጉራትን በዕጣ ሲያካፍላቸው አፍሪካ ለካም ደረሰችው፡፡ በአፍሪካ ምድርም ሲገባ በመጀመሪያ ያረፈው በኢትዮጵያ ነበር፡፡ ሀገሪቱም በአደይ አበባ አሸብርቃ ነበር፡፡ ወሩ ወርኃ መስከረም በመሆኑ ደስ ብሎት «ዕንቁ ዕጣ ወጣሽልኝ» ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል፡፡ ሁለተኛው የሀገራችን ንግሥት ንግሥተ ሳባ የንጉሥ ሰሎሞንን ዜና ጥበብ እየሰማች ስታደንቅ ትኖር ነበር፡፡ በጆሮዋ የሰማችውን በዓይኗ ዓይታ ለመረዳት ስለፈለገች በግመሎች ላይ ሽቱና እጅግ ብዙ ወርቅ እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኝ በኢየሩሳሌም የማይገኝ ልዩ ልዩ ገጸ በረከት አስጭና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ገባች፡፡ ከንጉሡ ሰሎሞንም ጋር ተገናኝታ የያዘችውን ገጸ በረከት ከሰጠችው በኋላ ብዙ ነገሮችን ጠየቀችው፡፡ እርሱም አንድ ነገር ላይ ሰውሮ ሁሉንም ገለጸላት፡፡ ቤተ መንግሥቱንም በቤተ መንግሥቱ የሚገኙ እጅግ በጣም የከበሩ ዕቃዎችን ሁሉ አስጎበኛት፡፡ ሲያበቃ «ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ» ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ አበረከተላት/ሰጣት/፡፡ ወሩም ወረኃ መስከረም ነበር፡፡ ከዚህ በመነሣት እንቁጣጣሽ የሚለው መጥቷል፡፡ አሁን ከሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት ደርሶ በመፈጸም ላይ ይገኛል፡፡ የሚከበረውም መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡ አንድም «ዕንቁ ዕፅ አወጣሸ» ብሎ የአበባውን መፈንዳትን ያስረዳናል፡፡
በዚህ በአዲሱ ዓመት የሁለተኛው ሺሕ ማብቂያና የሦስተኛው ሺሕ መግቢያ ላይ እንገኛለን፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሁለት ሺሕ ዓመተ ምሕረት ያሳለፈቻቸውን መልካም ሥራዎችና የደረሰባትን መጥፎ ሥራዎችን አልፋ አሁን ላለው ትውልድ ደርሳለች፡፡ ይሕ ትውልድ ደግሞ በሦስተኛው ሺሕ ዓመት እምነቷን፣ ሥርዓቷን፣ ትውፊቷን አውቆ ለሚቀጥለው ትውልድ የማስተላለፍ አደራ አለበት፡፡
                           
ለዚህም የሚረዳውን ገዳማትና አድባራትን በማጠናከር ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ዘመናዊ አስተዳደር በመዘርጋት ከእኅት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ጥሩ ግንኙነት በማድረግ የበኩሉን ሊወጣ ይገባዋል፡፡
ሺሕ ዓመቱ ሲለወጥ በዋዜማው ላይ በምንገኘኝበት ወቅት በእነዚህ ነገሮች ላይ ተቀራርቦ በመሥራት የሰው ዘር በሙሉ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ዝግጁ እንዲሆን ማድረግን ገንዘብ ልናደርግ ይገባል፡፡

                                             

                                                          ወስብሐት ለእግዚአብሔር

KidaneMihret.JPG

ኪዳነ ምህረት

KidaneMihret.JPG

የኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያንን ለማጠናከር የልማት ሥራ ጥሪ ቀረበ

በድሬዳዋ ኈኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ሰበካ ጉባኤ ሥር የተቋቋመው የአካባቢ የልማት ኮሚቴ እያከናወነ ያለውን የልማት ሥራ ለማገዝ ሕብረተሰቡ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ የደብሩ አሰተዳዳሪ ጥሪ አቀረቡ፡፡ ልማት ኮሜቴው ከሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ ውጪ የሚጠይቅ ትምህርት ቤት ግንባታ ጀምሯል፡፡  
የደብሩ አሰተዳዳሪ መጋቢ ካህናት አባ ገብረየሱስ አሻግሬ ሰሞኑን እንደገለጹት፤ ቤተክርስቲያኒቱ ለአካባቢው ምእመናን ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሉት በተጓዳኝ በዘላቂ ልማት ራሷን እንድትችል ለተጀመረው ጥረት የልማት ኮሚቴው እንቅስቃሴ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡

በልማት ኮሚቴው አማካኝነት ቤተክርስቲያኒቱ ባላት ሰፊ ግቢ ውስጥ ከ1999 ዓ.ም አንስቶ አንድ መዋዕለ ሕፃናትና 1ኛ ደረጃ ት/ቤት አገልግሎት እየሰጠበት መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው፤ ይህንኑ ት/ቤት አስፋፍቶ እስከ 2ኛ ደረጃ ለማሳደግ ባለ 3ፎቅ ህንፃ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ልማት ኮሚቴው ከከተማው አስተዳደር አስፈቅዶ በቤተ ክርስቲያኒቱ አቅራበያ ከሐረር ቢራ አክሲዮን ማኅበር ባገኘው ሙሉ ድጋፍ የሕዝብ መናፈሻ እየሠራ እንደሚገኝ አስተዳዳሪው ገልፀው፤ ልማት ኮሚቴው እያከናወነ ያለው ተግባር ለቤተክርስቲያኒቱም ሆነ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጠቃሚ በመሆኑ ሕብረተሰቡ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡

የልማት ኮሚቴውና የትምህርት ቤቱ አመራር ቦርድ ጸሐፊ አቶ አደፍርስ ተሾመ በበኩላቸው የኮሚቴው ዋና አላማ ቤተክርስቲያኒቱ በራሷ ቋሚ ገቢ እየታገዘች መንፈ ሳዊ አገልግሎቷን በተሳካ ሁኔታ እንድታከናውን እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ልጆች የጥሩ ሥነ ምግባርና እውቀት ባለቤት የሚሆኑበትን ትምህርት ቤት ማስፋፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዐውደ ምህረት ላይ በአካባቢው ማኅበረሰብ የተቋቋመው 18 አባላት ያለው የልማት ኮሚቴ ከቤተክርስቲያኒቱ ሰበካ ጉባኤ፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከከተማው የመንግሥት ሥራ ሓላፊዎች ጋር በመቀናጀት እቅዱን በተግባር እያዋለ እንደሚገኝ የገለጹት ጸሐፊው፤ ለጥረቱ መሳካት የሕብረተሰቡ ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው ከኅብረተሰቡ፣ ከባለሀብቶች፣ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ ከልማት ኮሚቴው አባላትና ከመንግሥት ሠራተኞች ባገኘው ድጋፍ ከግማሽ ሚሊዩን ብር በላይ ውጪ አንድ የመዋዕለ ነሕፃናት እና 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ሠርቶ በማጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት ከ350 በላይ ተማሪዎችን በጥሩ አገልግሎት እያስተማረ እንደሚገኝ ጸሐፊው ገልጸው ከእነዚህ ውስጥ ከአሁን ቀደም በከተማው ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ ወላጆቻቸውን ያጡና የችግረኛ ቤተሰብ የሆኑ ሃያ ልጆች በነፃ እየተማሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የኮሚቴው ራእይ ይህንን ት/ቤት እስከ ኮሌጅ ማድረስ መሆኑን የገለጹት ጸሐፊው በአሁኑ ወቅት እስከ 10ኛ ክፍል ማስተማር የሚያስችል ባለ 3 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ ተጀምሮ መሠረት ወጥቶለት የመጀመሪያው ፎቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሜቴው ይህንን ሕንፃ ለመቀጠል ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳለበት ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ በመ ሆኑም  የአካባቢው ማኅበረሰብ፤ በሀገር ውሰጥ እና በውጭ ያሉ በጎ አድራጊዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የእርዳታ እጃቸውን መዘርጋት ለሚፈልጉ በቅድስት ማርያም መዋዕለ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ስም በተከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬደዋ ዐቢይ ቅርንጫፍ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 4076 ቢልኩ እንደሚደርስም ጠቁመዋል፡፡

 

ዘጠነኛው የአውሮ­ ማዕከል ጉባኤ ተጠናቀቀ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮ­ ማዕከል ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከሐምሌ 3 ቀን እስከ 5 ቀን 2001 ዓ.ም በኦስትሪያ ሽቬካት ከተማ ተካሔደ፡፡ በጉባኤው ላይ ከተለያዩ ቀጠና ማዕከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች የተውጣጡ ከ45 በላይ አባላት የተሳተፉ ሲሆን የማዕከሉ የ2001 ዓ.ም የአገልግሎት እንቅስቃሴና የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት በማድረግ ማጽደቁን የአውሮ­ ማዕከል የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡

በተለይ የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ጽ/ቤት ግንባታና የማዕከሉ ድርሻ፣ የአውሮ­ አኅጉረ ስብከት አጠቃላይ እንቅስቃሴና የማዕከሉ ድርሻ፣ ወቅታዊ የቤተክርስቲያን ሁኔ ታና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይቶችን አድርጎ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡

እንደዚሁም የማኅበሩን የአራት ዓመት ዕቅድ መሠረት በማድረግ ዕቅዱ ለማዕከሉ ቀርቦ ከገመገመ በኋላ ያጸደቀ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ የሚቀጥለውን ዓመት ዕቅድ ዐይቶ ማሻሻያ በማድረግ እንዳጸደቀም ይኸው መረጃ ጠቁማል፡፡

ዘጠነኛው የአውሮፖ ማዕከል ጉባኤ ሲካሔድ ለተሳታፊዎቹና ጥሪ ለተደረገላቸው ምእመናን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መሰጠቱንም ተወስቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉባኤው የተካሔደበት ከተማ ከንቲባው ለጉባኤው ለተሳታፊዎች ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉ ዘገባው አመልክቶ ስለ ኦስትሪያ አጠቃላይ ኢኮኖማያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ በሚመ ለከትገለጻ አድርገዋል ተብሏል፡፡

ከተማቸው የጥንታዊ ቤተክርስቲያን ወጣቶችን ዓመታዊ የአውሮፓ­ ማዕከል ጉባኤ በማዘጋጀቷ ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ከንቲባው ገልጸዋል ሲል የማዕከሉ መረጃ ያመለክታል፡፡

እንደዚሁም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን አማካኝነት ስለምትሠራቸው መጠነ ሰፊ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ከጉባኤው ተሳታፊዎች ለከንቲባው ገለጻ መደረጉን ተወስቷል፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ለዝግጅቱ መሰካት አስተወጽኦ ላደረጉት የቪየና ኪዳነ ምሕረት ካህናትና የሰበካ ጉባኤ ከፍ ያለ ምስጋና መቅረቡም ተገልጿል፡፡

በተለይ ለጉባኤው መሰብሰቢያ አዳራሽ በመፍቀድና ለተሳታፊዎችም ማረፊያ በመስጠት ለተባበሩት የሽ ቬካት ቅዱስ ያዕቆብ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ ለቄስ ጌራልድ ጉም ፕና ለሥራ ባልደረቦቻቸው ከምስጋና ጋር የመታሰቢያ ስጦታ ተበርክቶላ ቸዋል፡፡

በመጨረሻም ቀጣዩ የማዕከሉ 10ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ በጀርመን ሀገር እንዲዘጋጅ ተወስኖ በዚህም ከወትሮው በተለየ መልኩ የማዕከሉን የ10 ዓመት የአገልግሎት እንቅስቃሴ የሚያመለክት ዝግጅት እንዲዘጋጅ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ጉባኤው መጠናቀቁን ከዘገባው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

ለቅኔ ትምህርት ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተገለጸ

ዓውደ ርእዩ ኅብረተሰቡ ስለአብነት ትምህርት ቤቶች ግንዛቤ እንዲኖረው ረድቷል

 «ቅኔ የአብነት ትምህርቱ ፍልስፍና መሠርተ» በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በማኅበራዊ አገልገሎት ልማት ዋና ክፍል የተዘጋጀው የግማሸ ቀን ዐውደ ጥናት በስ ድስት ኪሎ ስብሰባ አዳራሽ ተካሄደ፡፡  ዐውደ ጥናቱን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም እንደገለጹት፤ ዐውደ ጥናቱ በቅኔ ትምህርት አገልግሎቱና ፍልስፍናው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
የቅኔ ትምህርት የቤተክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት፣ የሀገራችን ታሪክ እና የቀደምት አባቶችና የዛሬዎች ሊቃውንት ፍልስፍና ጥበብ እንዲሁም ማኅበራዊ ሒስ የተላለፈበት የዕውቀት ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቅኔ በሀገሪቱ ሕዝቦች የአኗኗር ሥርዓትና ባሕል ውስጥ የራሱ አሻራ ያስቀመጠ ትምህርት ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ የውጭ ሙሁራን በትምህርቱ ላይ ምርምር እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በአንጻሩ በሀገሪቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ትምህርቱን ለማሳደግ የሁሉም ርብርብ የሚያስፈልገው እንደሆነና ዐውደ ጥናቱም የጠለቀ ጥናትና ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ ምሁራንን መነሻ የሚያመላክትና የሚያነሳሳ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

«ቅኔ የግእዝ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ» በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል መምህር እና ተመራማሪ ዶ/ር ሥርግው ገላው በበኩላቸው፤ የቤተ ክርስቲያንና የሀገሪቱ ሊቃውንት የአብነት ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ የቅኔን ትምህርት ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
የቅኔን ትምህርት በማሳደግ የነገይቱን ቤተክርስቲያንና ሀገርን ወደተፈለገው እድገትና ለውጥ ለማድረስ የሚችሉትን የአብነት ትምህርት ቤት ሊቃውንት በተገቢው መንገድ ማዘጋጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የቅኔ ትምህርት እንዲስፋፋ ለማድረግ የቅኔ ትምህርት ቤቶችን ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ደረጃ በማሳደግና ሥርዓተ ትምህርት ሊቀረጽላቸው እንደሚገባም ዶ/ር ሥርግው አስተያየ ታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በዐውደ ጥናት ላይ «ቅኔ በቤተክርስቲያን አገልግሎት» ና «ቅኔ ለመጽሐፍት ትርጓሜ» በሚል ርዕስ ሌሎች ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች የማኅበረ ቅዱሳን ጥናት እና ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ በመምህር ደሴ ቀለብና በስዋሰው ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር በመጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ የቀረበ ሲሆን፤ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ከተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

የቅኔን ትምህርት ለማሳደግና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ቤተክርስቲያን ሰፊ ድርሻ እንዳላትና ትኩረት ልትሰጠው እንደሚገባ የዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ክቡር አምባሳደር ሙሀሙድ ድሪር እንደገለፁት፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ወገኖች ለአብነት ትምህርት ቤቶች የሰጡት ትኩረት እጅጉን እንደሚደነቅ ጠቁመው፡፡

ያብነት ትምህርት ቤቶችን በመደገፍ የቅኔን ትምህርት ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት ጥረታቸው ከዳር ይደርስ ዘንድ የባህልና የቱሪዝም ሚኒስቴር ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡
በሲምፖዝየሙ በተለያዩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅኔ የተዘረፈ ሲሆን «ቅኔ ያብነቱ ፍልስፍና» የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም ተመርቆ ለእይታ በቅቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ዋና ክፍል «በጌጠኛ ቤትህ ልማት ይሁን» በሚል መሪ ቃል ለ10 ቀናት የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ተጠናቀቀ፡፡
ከሐምሌ 18 እስከ 26 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ በዓይነቱም በይዘቱም የተለየ እንደነበረ የገለጹት የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ዋና ክፍል የቅስቀሳና ገቢ አሰባሳቢ ክፍል ሓላፊ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረት፤ ዐውደ ርእይው በፎቶ ግራፍና በተለያዩ ገላጭ መረጃዎች የተደራጀ በመሆኑ ለመእመኑ ስለ አብነት ትምህርት ቤቶች ወቅታዊ ሁኔታ ግንዛቤን እነደፈጠረ ተናግረዋል፡፡
በዐውደ ርእዩ ላይ ዋና ክፍሉ በ2002 እና 2003 ዓ.ም ገዳማትና አድባራት ላይ የሚያከናውናቸው 12 ፕሮጀክቶች ለዐውደ ርእዩ ተመልካቾች ማስተዋወቁንም ጠቁመዋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 

Kalitie.GIF

ለጥምቀት ወጥታ የቆየችው ታቦት ወደ አዲሱ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ገባች

የቃሊቲ ቁስቋም ማርያም ታቦተ ሕግ ባለፈው ጥምቀት ወጥታ ተመልሳ መግባት ፈቃዷ ባለመሆኑ የተፈጠረውን የምእመ ናንና የካህናት ጭንቅ፣ ሐዘን፣ ድንጋጤ በብዙ የሚክስ የደስታ ዕለት፡፡ ሐምሌ 25 ቀን 2001 ዓ.ም፡፡

Kalitie.GIF

 
በዚህ ዕለት ማለዳ ጀምሮ ወደ ደጇ ይጎርፍ የነበረው ምእመን አካባቢውን ጠጠር መጣያ አሳጥቶታል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ጸሎት፣ ምሕላ. . . ሲደረግ ተውሎ ከቀኑ 9፡30 ለሰባት ወራት ከርማ ከነበረችበት ድንኳን በብፁዓን አባቶች፣ በካህናትና በበርካታ ምእመናን ታጅባ የወጣችው ታቦተ ሕግ የምእመናኑን የደስታ ስሜት እጥፍ ድርብ አድርጋው ነበር፡፡

በእልልታው በዝማሬውና በምስጋና ታጅባ ከድንኳኑ አቅራቢያ ወደ ተሠራላት አዲስ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ስታመራ እርኩስ መንፈስ ያደረባቸው ብዙዎች ከተለያየ አቅጣጫ ሲጮሁ፣ ሲንፈራገጡ፣ ሰውነታቸውን ሲንጡ እና እልልታውን ለማወክ ሲጥሩ የተስተዋለበት ይህ አጋጣሚ በእርግጥም የእመቤታችን ክብር ምን ያህል እንደሆነ ለመገንዘብ የሚያስችልም ነበር፡፡
በእመቤታችን ትእዛዝ አቶ ክንፈ ሚካኤል ረታ በተባሉ ምዕመን በተሠራው አዲሱ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ዑደት አድርጋ ወደ መንበረ ክብሯ የገባችው ታቦተ ቁስቋም ማርያም ታቦተ መድኃኔዓለም እና ታቦተ ጊዮርጊስንም አስከትላ ነበር፡፡

በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ይህ ዕለት ልዩ ያደረገው ብራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዋዜማው ዓርብ ምሽት ሦስት ነጫጭ ርግቦች የእመቤታችን ታቦት በከረመበት ድንኳን ላይ ማረፋቸው እና ከዚያ ቀደም ብሎ የንብ መንጋ ድንኳን ውስጥ መክተማቸው ነው፡፡
ዕለት ተዕለት የሕንፃ ቤተክርስቲያኑን ሥራ በመከታተል እመቤታችን ያዘዘቻቸውን የፈጸሙት አቶ ክንፈ ሚካኤል ረታ በዓውደ ምሕረቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ «ታቦተ ቁስቋም ማርያም በድንኳን እያለች እኛ ቤታችን አንገባም ብላችሁ ከእርሷ ጋር የቆያችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ ካህናት፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትና ምእመናን እንኳን ደስ አላችሁ!» ብለዋል፡፡

መጋቢት 29 ቀን 2001 ዓ.ም ለዮሐንስ አጥቢያ እመቤታችን ተገልጣላቸው ከዚህ ቀደም አስተውለውት ከማያውቁት ቦታ ሕንፃ ቤተክርስቲያኑን እንዲያንጹ ባዘዘቻቸው መሠረት በሁለት ወር ከ 10 ቀናት ውስጥ ሠርተው ያጠናቀቁት እርሳቸው የማያውቋቸው እግዚአብሔር የሚያውቃቸው እየተራዷቸው መሆኑንም አቶ ክንፈ ሚካኤል ተናግረዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ ¬ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት በክብረ በዓሉ ላይ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት «እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጆቼ ሳይሰባሰቡ፣ እኔ እዚህ መሆኔን ሳያውቁ ሕሊናቸውና መንፈሳቸው ሳይደሰት አልነሳም የማለት ምልክት መስጠቷ እንጂ ድንኳን መክረም እምቢተኝነት አይደለም» ብለዋል፡፡  
«ታቦተ ቁስቋም ማርያም አልነሣም ማለቷ የተቸገሩትን ለማማለድ፣ የታመሙትን ለመፈወስና በአካባቢው የምትሠራው ብዙ ተዓምራት እንዳለ ለማሳየት ድንኳን ከርማለች፤ ዛሬ ግን ወጥታ ልጆቿን ባርካለች፤ እንኳን ደስ ያላችሁ!» ያሉት ቅዱስነታቸው፤ ዕለቱ እናታችን ቅድስት ማርያም በየጊዜው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እየተገለጸች ከልጆቿ የምትነጋገርበት ሀገራችን ሀገረ እግዚአብሔር መሆኗን የምንገነዘብበት ዕለት መሆኑን ተና ግረዋል፡፡ ይህ ሥፍራ የቃሊቲ ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም መሆኑንም አብስረዋል፡፡
በዚህ ታሪካዊ ዕለት ከተገኙት ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በሰጡት ትምህርት የቅድስት ድንግል ማርያም ድንቅ ሥራ ተነግሮ የማያልቅ ነው፡፡

«እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሀገራችንና ከሕዝባችን በተአምሯ፣ በበረከቷ ያልተለየችን የአፍ መፍቻ ቋንቋችን ናት» ያሉት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሕዝባችን «ሰአሊ ለነ ቅድስት» የሚለው አጠራሩ አማላጅነቷን የቱን ያህል እንደሚያምንበት ያሳያል ብለዋል፡፡
ታቦተ ቁስቋም በቦታው ድንቅ ተአምር እንዲሠራበት ስለመረጠች ድንኳን መቆየቷን፣ በሰው እጅ ተሠራ ለማለት የሚያዳግት ሕንፃ ቤተክርቲያን በአጭር ጊዜ ተሠርቶ መጠናቀቁ፣ እመቤታችን በተአምሯ የሠራችው መሆኑን እንደሚያሳይ የገለጹት ብፁዕ ነታቸው፤ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ያሠሩት ምእመን ዕድለኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የእመቤታችንን ተአምር በመንገር ከደጇ ጠፍተው የማያውቁት አገልጋይ አባ ገብረሥላሴ መለሰ በሰጡት አስተያየት «ጸሎተ ምህላችንን ተቀብላ እመቤታችን ፈቃዷን ስለገለጸችልን ደስታችን ወሰን የለውም. . .» ነው ያሉት፡፡
«ሰኔ 25 ቀን 2001 ዓ.ም ታቦተ ቁስቋም ባረፈችበት ድንኳን ውስጥ አንዱን ንብ ተከትለው ጥቂት ንቦች ገቡ፤ ሐምሌ 16 ቀን ጀምሮ ግን ሦስት ቀፎ የሚገመት የንብ መንጋ ወንበሯን ተረክቦ ዛሬ ድረስ ይገኛል፡፡ ይህን ስናይ እመቤታችን ልጆቿን ልትጠራ፣ በረከቷን ልታወርድ መሆኑን ተረዳን፡፡ አዲሱ ሕንፃ ቤተክርስቲያን እንደ ምትገባልንም እምነታችን ሆነ፡፡ እንዳሰብነውም ተሳካ. . .» ያሉት አባ ገብረሥላሴ «ሐምሌ 24 ምሽት ድንኳን ላይ ያረፉት ሦስት እርግቦችም ሌላው ምልክታችን ነበር» ይላሉ፡፡

ጥር 16 ቀን 2001 ዓ.ም ታቦቷን አንግሠው ዳግም ወደ ቤተመቅደስ እንድትገባ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው የቀረው ዛሬ ግን የእመቤታችን ፈቃድ እጅግ ያስደሰታቸው መሪጌታ ቤዛ የሻው «ሐዘናችን በደስታ ተለውጧል፡፡ ይህን ተዓምር ማየቴ ዕድለኛ ነኝ፡፡ ለእመቤታችን ክብር ምስጋና ይግባት» ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ ዕለት በእርግጥም የደስታ ዕለት ነው፡፡ ብዙዎች የሚሰጡት አስተያየት ከደስታ እንባ ጋር ነው፡፡ በዕለቱ እየተጨባበጡ፣ እየተቃቀፉ ደስታቸውን የሚገልጹ በዓውደ ምሕረቱ በእመቤታችን የተደረገላቸውን ተአምር የሚመሰክሩ ብዙዎች ነበሩ፡፡

እሑድ ሐምሌ 26 ቀን 2001 ዓ.ም የቃሊቲ ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ሕንፃ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ሲከበር እጅግ ከፍተኛ ሕዝብ እንደተገኘም ታውቋል፡፡

ከአዘጋጁ- ባለፈው የጥምቀት በዓል ከቅዱስ ሚካኤል ታቦት ጋር ወደ ጥምቀተ ባሕር ሥፍራ ወጥታ ተመልሳ ወደ ቤተመቅደሷ ሳትገባ በራሷ ፈቃድ ድንኳን ስለከረመችው የቁስቋም ማርያም ታቦት ታሪክ በተከታታይ ስንዘግብ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ወደፊትም በዚሁ ሥፍራ ስለተከናወኑ ገቢረ ተዓምራት የምንገልጽ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 
 

የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ ተጠናቀቀ

በግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የቤተክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊና የልማት ሥራዎች እንዲያከናውን የተመረጠውንና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብ ከት የተነሳውን ችግር ለመፍታት የተጠራው አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ተጠናቀቀ፡፡

ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በተሰጠውና ቅዱስ ፓትርያርኩ ባነበቡት መግለጫ እንደተመለከተው፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚታየውን የአፈጻጸም ችግር እንዲከታተል በግንቦቱ የርከበ ካህናት ጉባኤ የተሰየመው የሥራ አስ ፈጻሚ ኮሚቴ ከተሰየመበት መደበኛ ተግባሩ ጋር በቤተክርስቲያኒቱ የልማት ዘርፍ ላይ ውጤቶች ለማጠናከር የገቢ ምንጭ የሚያስገኙትን ፕሮጀክቶች ለመፍጠር የሚያስችለውን ረቂቅ አላዘጋጀም ይላል፡፡
ውስጥ ደንቡን አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በተፈጠረው ሰው ሠራሽ ችግር ምክንያት የቤተክርስቲያኒቱን ማዕከላዊ አስተዳደር ለትችት የዳረገ ውዘግብ ተፈጠሮ እንደነበር ቅዱስ ፓትርያርኩ ያነበቡት መግለጫ አስታውሶ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የችግሩን መነሻ ከምንጩ በመመርመር ሁሉ ንም በየሥራ ዘርፉ ማስተናገድ የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፉንም መግለጫው አመልክቷል፡፡
በቅዱስ ¬ትርያርኩ የተነበበው መግለጫ እንደሚያመለክተው፤ በአም ስተኛው ¬ትርያርክ አሥራ ሰባተኛ ዓመት በዓለ ሲመት አከባበር ማግስት ጀምሮ በተካሄደው ስብሰባ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ማሳለፉን አስተውቋል፡፡

አንደኛ ታግዶ የነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እግዱ ተነስቶ ሊመራበት የሚያስችለውን ውስጠ ደንብ ከሚመድቡለት ባለሙ ያዎች ጋር በመሆን አዘጋጅቶ እን ዲያቀርብ፤ የሚያዘጋጀውን የመተዳ ደርያ ደንብ እስከሚያቀርብ ድረስም ከቤተክርስቲያኒቱ የአመራር አካላት ጋር እየተመካከረ እንዲሠራ መወሰኑን በቅዱስነታቸው የተነበበው መግለጫ ያመለክታል፡፡
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተ ዳደር ችግር በተመለከተ ምልዓተ ጉባኤው በረጋ መንፈስ በነቃ አእ ምሮ ሊተኮርበት የሚገባ ታላቅ ሀገረ ስብከት መሆኑን በመገንዘብ ለውዝግቡ መነሻ የሆነውን የፋይናንስና የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር አጣርቶ ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚያቀርብ ገለልተኛ ኮሚቴ እንዲቋቋም ጉባኤው መስማመቱንም መግለጫው ጠቁሟል፡፡

ቀደም ሲል በቅዱስ ¬ትርያርኩ እገዳ ተጥሎባቸው የነበሩት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የብፁዕ ወቅዱስ ¬ትርያርኩ ረዳት ጳጳስ አቡነ ሳሙኤል እገዳ እስከ ጥቅምት 2002 ሲኖዶስ ስብሰባ እን ዲቆይና እንዲታይ፤ እስከዚያው ድረ ስም ሀገረ ስብከቱ ቅዱስ ሲኖዶስ በሾመው ሥራ አስኪያጅ እየተመ ራና እየተዳደረ እንዲቆይ መወሰኑን ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል፡፡
በመግለጫው ላይ እንደተመለከተው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስተያኒቱን አጣዳፊ ተግባር ለማከናወን ከተሰየመ በት ሐምሌ 6 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ አህጉር እንዲሁም በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሲነገር የሰነበተው፤ ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው፤ ከእውነት የራቀ ዘይቤ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ሲልም መግለጫው አስረድቷል፡፡

በቅዱስ ¬ትርያርኩ የተነበበው መግለጫ በመጨረሻ እንዳመለከተው፤ ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዘው ከሚያስተላልፋቸው መልእክቶች መካከል ሰላምና መረጋ ጋት የመጀመሪያውን አጀንዳ ይዘው ይገኛሉ በማለት ጠቁሞ፤ እግዚአብሔርን ማመስገን፣ ቤተክርስቲያንና ወገንን ማገልገል፣ ሀገርን ማልማት የሚቻለው ፍቅር፣ አንድነትና ሰላም ሲኖር ብቻ ነው ይላል፡፡

በመሆኑም ከራሳችን ከእያንዳን ዳችን ከቤተሰባችን ቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ሁሉም ኅብረተሰብ በሰላም የተመሠረተ ሕልውና እንዲኖረው በቅዱስ ¬ትርያርኩ የተነበበው መግለጫ ያመለክታል፡፡

በሌላ ዜና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ብፁዓን አባቶች ማንነታቸው ባልታ ወቁ ግለሰቦች ሐምሌ 8 ቀን 2001 ዓ.ም ምሽት በመንበረ ¬ትርያርክ ጽ/ቤት ግቢ በሚገኘው መኖሪያቸው የመደብደብ ሙከራ እንደደረሰባቸው ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል፣ ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገልጸዋል፡፡

እንደ ብፁዓን አባቶች ገለጻ ማግሥቱ ለመሰብሰብ እየተዘጋጁ፣ ጸሎት እያደረሱ ሳለ ሌሊት ማንነታ ቸው ያልታወቁ ሰዎች ቤታቸውን በኃይል በመደብደብ በር እንዲከፍቱ ላቸውና የሚያወያዩአቸው ነገር እንዳለ ሲገልጹላቸው ማንነታቸውን ስለማያውቁ እንደማይከፍቱ ምሽትም በመሆኑ ማንነታቸውን የማያውቋቸውን ሰዎች ለማነጋገር ፈቃደኛ እንዳልሆኑ በመግለጽ እንደመለሷቸው አስተያየታቸውን የሰጡን አባቶች አስረድተዋል፡፡

ዓላማቸው ያልተሳካላቸው ማንነታቸው ያልታወቁት ግለሰቦች ቅዱስ ¬ትርያርኩ ባልተገኙበት ወቅት ቅዱስ ሲኖዶሱን በሰብሳቢነት ይመሩ የነበሩትን የብፁዕ አቡነ ቄርሎስን በር ሰብረው በመግባት ጭምር ጉዳት ለማድረስ እንደሞከሩ ብፁዓን አባ ቶች ጠቁመው፤ የአንዳንዶቹን በር በኃይል በመምታትና በማስጠንቀቅ «ጠብቅ እናሳይሐለን» የሚሉ ዛቻዎች በመሰንዘር ያስፈራሩ እንደነበረም ገልጸዋል፡፡

ጉዳት ለማድረስ የመጡት ግለሰ ቦች በመጀመሪያ የብፁዓን አባቶችን በር ሲያንኳኩ «ፖሊሶች ነን ክፈቱ» ይሉ እንደነበርና የብፁዓን አባቶቹ ቤት የደበደቡበት ሰዓት ተመሳሳይ እንደነበር አስተያየት ከሰጡን አባቶች ለመረዳት ችለናል፡፡

ምዕመናን በተከሰተው ነገር ሳይደና ገጡ ሁሉን ማድረግ ወደሚችለው አምላክ ይጸልዩ ያሉት ብፁዓን አባ ቶች፤ መንግሥት ጉዳዩን በጥልቅና በትኩረት በመከታተል ጥበቃ እንዲ ያደርግና የቤተክርስቲያንን ችግር እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በጠቅላይ ቤተክህነት የጥበቃ ሓላፊውን በአባቶች ላይ የደረሰውን የድበደባ ሙከራ አስመልክተን ያደረግነው ሙከራ አጥጋቢ ምላሽ ባለመገኘቱ አልተሳካም፡፡

በጉዳዩ ላይ ቤታቸው የተደበደበ ባቸውን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ቤተሰቦቻውን አነጋግረናል ከዚህ እን ደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ ብፁዕ ነታቸው ሌሊት በቅጽረ ቤተ ክህነት ስለተፈጠረው ጉዳይ ጠይቀናቸው ምላሻቸው የሚከተለው ነበር፡፡

ሐምሌ 8 ቀን የነበረው ስብሰባ በጣም ጥሩ ስብሰባ ነበር፡፡ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት በተገኙበት እየተነጋገርን አንድ ሁለቱ ችግር ተቃሎ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን ጉዳይ ለማነጋገር እሳቸው ስላልነበሩ ነገ እሳቸው ባሉበት እንነጋገራለን፡፡ ብለን ነው በሰላም የወጣነው፡፡ ከዚያ በኋላ በሰላም ወደ ቤታችን ገባን፡፡

ሌሊት የአባቶች ቤት ተመቷል፤ የአቡነ ቄርሎስ ግን በጣም የበዛ ነበር መዝጊያውም ተሰብሯል፡፡ ይህን ዐይቻለሁ፤ በውስጡም በውጭውም «የ¬ሊስ ያለህ፣ የመንግሥት ያለህ» ድረሱልኝ በእንደዚህ ቁጥር ቤት ያለን እየተደበደብን ነው ብዬ ስጮህ ገለል ብለው ሔዱ፤ እንጂ ወደ መኝታ ቤቱ ሊገቡ ትንሽ ነበር የቀረው ብለው ነግረውኛል፡፡ በማለት የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

ዲ/ን ተክለ ወልድ የብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ረዳት ነው፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ የሚለው አለ፡፡ «ዋናውን በር ገንጥለው ገብተዋል፡፡ ቀጥለው የመኝታ ክፍሉን በር ለመስበር ሲታገሉ ብፁዕ ነታቸው ውስጥ ሆነው ስልክ መደወላቸውን ሲሰሙ ትተው ሔዱ፡፡ ማዕድ ቤት ገብተው ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ ፈትሸዋል፣ መሳቢያዎች ሁሉ ተከፋፍ ተው ተበርብረዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አሁን ደህና ናቸው፡፡ አጋጣሚ አንዲት ነርስ እኅታችን ጤንነታቸውን እየተከተለች የሕክምና ርዳታ ታደርግላቸው ትከታተላቸው ስለነበር እሷ የሳሎኑ በር ሲሰበር መኝታ ቤቱን ቆልፋ ለሕይወታቸው መትረፍ ምክንያት እንደሆነችም ይገልጻል፡፡

የጉራጌ ከንባታና ሀዲያ እና ሲልጤ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መልከጼዴቅ ምን ይላሉ?

«ነገሩ ያሳዝናል ግን እግዚአብሔር ይመስገን ደህና ነን፡፡ ለሁሉም የኛ አለቃ፣ ንጉሥ፣ ባለሥልጣን፣ እግዚአብሔር ነው፡፡ ስለዚህ ለእግዚአብሔር ከመንገርና ከመስጠት ሌላ የምንለው የለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ሕገ ቅዱስ ሲኖዶስ ይከበር ነው ያልነው፡፡ ሌላ ያልነው ነገር የለም፡፡

በአሁኑ ሰዓት በእውነቱ ቤተክርስቲያን የጠበቀችውን ያህል አልተጓዘችም ብለናል፡፡ አባቶችም ሲታገዱ በሲኖዶሱ ሕግ፣ ሲኖዶሱ ያግድ፣ ከሲኖዶሱ ጋር ይሥሩ፣ እንርዳዎት፣ እናገልግልዎት፣ እናግዝዎት ነው ያልነው እኛ ሌላ ነገር ያልነው ነገር የለም፡፡ እኛ በየሀገረ ስብከታችን እያገለገልን እየተሯሯጥን ነው፡፡
ባለሥልጣናት ባለፈው ዓርብ መጥተው የቅዱስ ሲኖዶስን፣ የቤተክርስቲያንን ቃለ አዋዲ አክብራችሁ፣ ተደማመጡ፣ ቤተክርስቲያኒቱ እንኳን ለራሷ ለአፍሪካም መሆን የም ችል ናት አሉን፡፡

ሕዝቡም ተበጥብጧል፣ ተጨንቋል እባካችሁ ሰላም አውርዱ፣ መንግሥት ሓላፊነት አለበት፡፡ አመራርና አካሔድ ልንነግራችሁ ነው የመጣነው፡፡ ከተበጣበጠ መንግሥት ጣልቃ ይገባል፣ ሓላፊነት አለበት፡፡ እናንተ አባቶች ናችሁ፤ የምትመክሩንና የምትረዱን እንጂ እኛ እናንተ ውስጥ ጣልቃ መግባት አንችልም፡፡ የራሳችሁን ችግር በራሳችሁ አክብሩ፤ የሐምሌ 5 ቀን በዓልን በሰላም አክብሩ፤ የራሳችሁ በዓል ነው ብለው ጥሩ መመሪያ ሰጡን ተወያዩ አሉን፡፡ እንደገና ተሰባሰብን ሐምሌ 7 ቀን ሰላም ይኖራል ብለን፡፡ ነገር ግን የባሰ ነበር ጉዳዩ፡፡

አሁን ደግሞ እየታየ ያለው ደስ የማይል ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አምላክ ይፍረደን፤ እሱ እንደፈቀደ ይሁን፣ ቅዱስ አባታችንን ለመንቀፍ አይደለም፣ እሳቸውን ለማዋረድ አይደለም እናከብራቸዋለን፡፡ እኛ ያልነው ሕግ አክብረው ያስከብሩን፣ በሕግ ይምሩን ነው የምንለው፡፡

እኛ መሠረታችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ጠባቂያችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ቀጥሎ ደግሞ መንግሥት ነው፡፡ በመንግሥት ተስፋ አንቆርጥም፡፡ የማጣራት ሥራ ሠርቶ መግለጥ አለበት፡፡

ሁሉንም የሚያውቀው ጌታ እግዚአብሔር ነው፡፡ ለሁሉም ጽዋው ይሞላል፤ ዋጋውን ይከፍላልና ብዙ ችግሮች ደርሰዋል፣ እየደረሱም ናቸው፡፡ ግን አባቶች ለሞትም ቢሆን የተዘጋጀን ነን፡፡

የበር መስበር አይደለም፣ ማስፈራራት አይደለም ለቤተ ክርስቲያን ካስፈለገ እንሞታለን፤ የቀደሙትም ሞተውላታል፡፡ አሁንም ቢሆን አባቶች ወደ ኋላ አንልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ በፈተና እየተፈተነች ነው ዘመናትን የተሻገረችው ከፈተና ወጥታ አታውቅም፡፡

አሁንም ቢሆን ሲኖዶሱ የተወያየው፣ እርሳቸው ስብሰባውን እንዲመሩ፣ አስተዳደራዊ ሥራውን ሌሎች እንዲሠሩ ሁልጊዜ የምንነጋገረው፣ ለመንግሥትም እያሳሰብን ያለነው ይሄን ነው፡፡

እሳቸው በአባትነታቸው፣ በሊቀ መንበርነታቸው ጉባኤውን ይምሩ፤ ሲኖዶሱ ግን በሲኖዶሱ ሕግ መሠረት ተወያይቶ ይወስን የሚል ሐሳብ ለብዙ ዓመታት ስናነሣ ቆይተናል፡፡ ስለልማት፣ ስለ ሃይማኖት ተጨቃጭቀን አናውቅም፡፡ አሁን ሰለቸን ብዙዎች አባቶች፣ ደከማቸው፤ በጣም ያሳዝናል፡፡

በዋናነት ኃይለኛ ክርክርና ጭቅጭቁ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይከበር ነው፡፡ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን ነው፣ በጀት በሥነ ሥርዓት እንዲመራ ነው፡፡ ሥራ አስፈጻሚውንም ቅዱስ ሲኖዶስ ሲመድበው ሥራ እንዲሠራ ነው፡፡ ኮሚቴው ቅዱስነትዎ በጥርጣሬ ሊያዩት አይገባም፡፡ ኮሚቴው እርስዎን የሚረዳና የሚያግዝ ነው ያልነው፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ በአብዛኛው አባቶች አንድን ዓይነት መንፈስ ነበራቸው፡፡ የሃሳብ ግጭቶች ይኖራሉ፣ እያንዳንዱ የራሱ የሆነ አመለካከት ይኖረዋል ግን በአብዛኛው ሲኖዶሱ ደግሞ አንድ ዐይነት መንፈስ የሚታይበት ነው፡፡

በመጨረሻ የማስተላልፈው ቤተ ክርስቲያን በመርከብ ትመሰላለች፡፡ በባሕር ላይ ያለች መርከብ አውሎ ንፋስ ሊያንገላታት ይችላል፡፡ ስለዚህ ሐዋርያትን እናስታውስ፡፡ አውሎ ንፋስ የተሳፈሩበትን መርከብ ሲያናውጠው ክርስቶስም አብሮ ነበር፡፡ ክርስቶስ ያለባት መርከብ ዐውሎ እንደተነሣባት ነው፤ ሁሉም ሐዋርያት «አድነን» ነው ያሉት፤ ወደ እሱ ነው የጮሁት መጨረሻ ላይ ነፋሱን የገሰጸው እሱ ነው፡፡ አሁንም የቤተ ክር ስቲያን አምላክ ይህንን ማዕበል ፀጥ ያደርገዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጾም ጸሎት ያስፈልጋልና፡፡ ምእመናን ወደ እግዚ አብሔር እንዲጮሁ ነው የማሳስበው፡፡ በዚህ ምክንያት እንዳይሸማቀቁ እንዳ ይደናገጡ ሃይማኖታቸውን ብቻ ይጠብቁ፡፡ በማለት አባታዊ ጥሪያቸውን በእንባም ጭምር አስተላልፈዋል፡፡

አቡነ ፋኑኤል የሲዳማ፣ የጌድዮ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳ ዎች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ናቸው፡፡ ጥቃት ባይደርስባቸውም ሙከራ ተደርጎባቸው እንደ ነበር ሰማንና የደረሰባቸውን እንዲያብራሩልን ጠየቅናቸው ቃላቸውን እነሆ «እኔ ዘንድ የተፈጠረው ችግር ሐምሌ 9 ቀን ከምሽቱ 4፡30 ላይ ነው፡፡ ማንነታቸውን የማላውቅ ሰዎች ወደ መኖሪያዬ በመኪና መጡ፡፡ በኃይል የቤቴን መዝጊያ ደበደቡ፡፡ ጠባቂዎችን ተጠንቀቁ፤ በር አትክፈቱ አልኩ በዚያ ሰዓት እንግዳ እንደማይመጣ አውቃለሁ፡፡

ውጭም ያሉ ልጆችም በመስኮት አንኳኩተው ምንድን ነው አሉኝ፤ ዝም በሉ አልኳቸው፡፡ በጣም አንኳኩ በጣም ጠንከር አለ፡፡ በዚህ መሐከል ለቤተ ሰብና ለፖሊስ እንዲደወል አደረግሁ፡፡ 10 ደቂቃ ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተመልሰው በመኪናቸው ሄዱ ወዲያው ቤተሰብም ፖሊስም መጣ፡፡ ነዕለታዊ ሪፖርት ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ አስመዘገብኩ፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው እኔ ላይ ብቻ መስሎኝ ነበር፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሌሊት ስደውል እዚያም የባሰ እንደነበር ሰማሁ፡፡ እኔ የምኖረው ቃሊቲ ገብርኤል አካባቢ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የመጣው በቅዱስ ሲኖዶሱ ሽኩቻ ነው፡፡

መቼም እኛ ሌላ ተቃዋሚ ወይም ጠላት የለንም፡፡ ምን ተፈልጐ ለምን እንደተፈጸመ አይገባኝም፡፡ በወቅቱ ስብሰባው የተካሄደው ለግማሽ ቀን ነው፡፡ ለሥራ አስፈጻሚ ተብሎ የተመረጠው ኮሚቴ እገዳው ተነሥቶለታል፡፡ ሌላው የብፁዕ አቡነ ሳሙኤል ጉዳይ ነው እሱን ነገ እናየዋለን ነበር ያልነው፡፡ ስብሰባ ውም ቁጣ የተሞላበት አልነበረም፡፡ የተረጋጋና በሰከነ መንፈስ የተካሄደ ነበር፡፡ በማለት ጥቃቱ በተፈጸመበት ዋዜማም ቢሆን ለዚህ ድርጊት የሚያ ነሣሣ ምንም ዓይነት ምክንያት እንዳ ልነበር ገልጸዋል፡፡

ሕገ ሲኖዶስን አስመልክተው በርግጥ ቅዱስነታቸው ተቀባይነት የሌለው ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ መሻሻል አለበት፣ ብዙ ነገር ጐድሎታል ይሉም ነበር ምን እንደሚጨምሩ፣ የትኛው አንቀጽ እንደሆነ የሚሻሻለው ባይገልጹም በድፍኑ ግን ቅሬታ እንዳላቸው ይገልጹ ነበር፡፡

በስብሰባው ወደ 6 አጀንዳ ቀርቧል እስካሁን የታየው ገና አንዷ ብቻ ነው፡፡ አሁን የተፈለገው ጠቅላላ ነገሮቹ እንዳይታዩ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡

በመጨረሻ የማስተላልፈው መልእክት ይሄ ፈተና ነው፤ በእኛ ላይ የመጣ ማዕበል ፈተና ነው ሁሉም በሃይማኖቱ ጸንቶ ቤተ ክርስቲያኒቱንም እኛንም ያስበን ሁላችንም በያለንበት እንጸልይ በሃይማኖት እንጽና ነው የምለው፡፡ እኛ ሁል ጊዜ ሕይወታችን ከወንጌል አገልግሎት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አሁንም የምናደርገው ይህንኑ ነው፡፡ ቀጣዩም ሕይወታችን በወንጌል ማገልገል ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ጉዳይ በተመለከተ ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ለውጥም ስለሚያስፈልግ ነው ይሄ ሁሉ የተከሰተው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በሁለንተናዋ በልማቱም በወንጌል አገልግሎቱም ወደኋላ ቀርተናል ማለት ይቻላል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ችግር ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተሰወረ አይደለም፡፡ አሁን በሲኖዶስ ደረጃ ጐልቶ ወጣ፤ እንጂ ሕዝብ ተነጋግሮበት ያበቃለት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በሃይማኖት በጸሎት ጸንተን መኖር ይገባ ናል፡፡ በተፈጠረው ሁኔታም ሳንደናገጥ ሳንሸበር ባለንበት ጸንተን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕልውና የሚቀጥልበትን መንገድ ማሰብ ያስፈልገናል በማለት መልእክታቸውን ያጠቃልላሉ፡፡

ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊና የዋግ ህምራ ሊቀ ጳጳስ ስለጉዳዩ በጥልቅ ሐዘን ይናገራሉ፡፡ይህ ነገር ይበጃል) ምእመኑ በጭን ቀት ላይ ነው ያለው የኛን ድምፅ መስማት ይፈልጋል፡፡ እኔ በሁኔታው ተረብሼ ሳልተኛ ነው ያደርኩት በቃ አሞኛል፡፡ አሁን ይህን የማስብበት የተረጋጋ አእምሮ የለኝም፤ ብለዋል፡፡
የቦረናና ጉጂ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስም ከዛቻና ስድብ ባያልፍም የጥቃቱ ሰለባ ነበሩና የሚናገሩት አላቸው፡፡«እግዚአብሔር በቸርነቱ በደላችንን ሳይመለከት አትርፎናል፡፡ ቤታችን በምሽት ባልታወቁ ግለሰቦች ተደበደበ በግምት ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡ የመጡት ሰዎች በሩን በኃይል ደበደቡ ክፈት አሉኝ፡፡ አልከፍትም አልኳቸው «አይ ልናማክሮት ነው አንዳንድ ነገሮችን ልናዋዮት ነው በሩን ክፈቱ አሉኝ» ሰዓቱ አልፏል እኔ አልከፍትም አልኳቸው «¬ሊሶች ነን» አሉኝ ፖሊሶችም ብትሆኑ በዚህ ሰዓት ሕጉ አይደለም፤ የሰውን በር ማስከፈት ስለዚህ አልከፍትም አልኳቸው፡፡ ክፈት እያሉ በሩን በኃይል መደብደብ ጀመሩ፡፡ እኔም በውሳኔዬ ጸናሁ፤ እነሱም ድብደባውን አጠነከሩ፣ በኋላ የውስጥ በር ዘግቼ ስልክ ወደ ፖሊስና ቤተሰብ ደወልኩ፡፡ ከዛም በኋላ ብዙ ሰዓት ይሆናል በሩን የቀጠቀጡት እኔ እንደውም ሰብረው የገቡ መስለውኝ ነበር፡፡ ሌላ ክፍል ውስጥ ቆልፌ ተቀምጬ ሳለ እግዚአብሔር መለሳቸው፡፡ የሔዱ ሲመስለኝ ቀጥሎ የሌላ አባት ቤት ሲደበደብ ሰማሁኝ፤ የማንን ቤት ነው የደበደቡት እያልኩ ነበር፡፡

ከኔ ቤት ቀጥሎ ያለውን ቢመስለ ኝም የሳቸው ቤት አልተነካም፣ ነገር ግን ብዙ ቤት ነው የተደበደበው በአጠቃላይ የጳጳሳቱ ቤት ነው የተደበደበው ግን እኛ በቸርነቱ ተርፈናል፡፡

ምክንያት ይሆናል የምለው ምናልባት በሲኖዶስ ስብሰባ ላይ በሰጠነው ሐሳብ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንግዲህ ከዚህ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል ሌላ የተጣላነው ሰው የለንም ያው መነሻው በስብሰባው ላይ ሕገ ሲኖዶስ ይከበር ማለታችን ይመስለኛል፡፡

የቤተ ክህነት ግቢ ጥበቃ አለው፡፡ ድርጊቱ ሲፈጸም ለዘበኞች ደወልኩ እንመጣለን ይላሉ እንጂ አንዳች እርዳታ አላገኘሁም፡፡ ለወደፊቱ መንግሥት ጥበቃ ካላደረገልን እንግዲህ ለሕይወታችን በጣም የሚያሰጋ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ጥረው መጨረሻ ሳይሳካ በመቅረቱ ነው እየተሳደቡ የሔዱት፡፡ ታገኛታለህ ቆይ እያሉ ነው ሲዝቱብኝ የነበረው፡፡

ማንም የደረሰልን የለም፣ እግዚአብሔር ግን ረድቶናል፡፡ ፖሊሱ መጣ ተባለ ነገር ግን ወደ ውስጥ መግባት የቻለ አይመስለኝም፤ መብራትም አልነበረም፡፡ በወቅቱ ያው ጨለማን ተገን አድርገው ነው፤ ለድብደባ የተሰማሩት አጥቂዎቹ፤ እንግዲህ የነገን ባናውቅም ለአሁን ተርፈናል፡፡

እኛ ለእግዚአብሔር አመልክተናል፡፡ መንግሥትም ጥበቃ እንዲያደርግልን ነው ጥሪያችንን አቅርበናል፡፡ ይህ ችግር በስብሰባው ላይ በተፈጠረ ያለመግባባት የመጣ ነው፡፡ ምክንያቱም በአቋማችን በጸናነው አባቶች ላይ ብቻ ተለይቶ ነው ድብደባው የተፈጸመው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ትከበር፣ አስተዳደሯ ይከበር፣ ሙስና ይጥፋ ሁሉም ነገር በቤተ ክርስቲያን ሕግ ይሁን በማለታችን ዛቻና የበር ድብደባ ተፈጽሞብናል፡፡

የትናንት /ሐምሌ 8 ቀን 2001 ዓ.ም/ የስብሰባ ውሏ ችን የሰባቱን ሊቃነ ጳጳሳት እግድን ስለማንሣት ነበር የተወያየነው፡፡ ከዛ በኋላ በሌላ አጀንዳ ለዛሬ /ለሐምሌ 9/ ልነነጋገርና የመንግሥት አካላት እንዲገኙ ልን ተነጋግረን ነው የተለያየነው፡፡
የቤተ ክርስቲያን መዋቅርና አስተዳደራዊ መሠረቷ ሕገ ሲኖዶስ ነው፡፡

ያባቶች ሐሳብ አንድ ነው፡፡ ሁኔታዎች ላይ መስማማት እንጂ የመለያየት ነገር የለም፤ የሁሉም ዓላማና ራእይ አንድ ነው፡፡ ሐሳባቸው ዓላማቸው አስተዳደር ይስተካከል ሕገ ቤተ ክርስ ቲያኑ ይከበር ነው የተለያየ አይደለም፡፡ በመሠረታዊ ጉዳዩ የሁሉም አባቶች አቋም አንድ ዓይነት ነው፡፡ ለምሳሌ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ቤት እንደገናም በ¬ትርያርኩ መሪነት የተሰበሰቡ አሉ ይባላል፡፡ እንግዲህ ¬ትርያርኩም ጋር ሄደው ቢሰበሰቡ ሐሳባቸው አንድ ነው፡፡ እርስዎ ፊት የተወያየነውን ነገር በሲኖዶሱ ፊት እንስማማበታለን /እንፈራረምበታለን/ ነው ያሉት እንጂ በሐሳብ መከፋፈል የለም፡፡

በተፈጠረው ነገር ምእመናን እን ደተረበሹ እናውቃለን፡፡ ምእመናን የተበላሸ ነገር በአንዴ ሊስተካከል አይችልም፤ ያለ እምነት ውጤት አይ ገኝምና አሁንም በትዕግሥት እግዚኦታቸውን ይቀጥሉ፡፡ ምእመናንን የሚረብሽ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ምእ መን በጸሎት ሆኖ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ከፈተና እንዲታደ ጋት በጸሎት እንዲጠይቅ ነው፡፡ በጸሎት እንዲያስቡን ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርን በጸሎታቸው እንዲ ጠይቁልን ነው የሚያስፈልገው፡፡» በማለት ነበር ስለሁኔታው የገለጹት፡፡
ጥቃቱን የፈጸመው ቡድን ሆን ብሎ ብፁዓን አበውን የሚያሳድድ በመሆኑ ለብፁዓን አበው ጥበቃ እንዲ ደረግላቸውና ወንጀለኞቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ ምእመናን እየጠየቁ ነው፡፡
ብፁዓን አበው ምእመናን በጾምና በጸሎት እንዲተጉ ደጋግመው የጠየቁት ሲሆን በሃይማኖት ጸንተው የእግዚአብሔርን ፍርድ እንዲጠጣበቁ አሳስበዋል፡፡

 
 
 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ማኅበረ ቅዱሳን «ደጀ ሰላም»ብሎግ ልሣኑ አለመሆኑን አስታወቀ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ፣ «ደጀ ሰላም» በሚሰኝ ብሎግ ላይ የሚለቀቀው መግለጫ እንደማይመለከተው አስታወቀ፡፡

የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ዳንኤል ተስፋዬ ብሎጉ «የማኅበረ ቅዱሳን ልሳን ነው» የሚል መረጃ ባልታወቁ አካላት መሰራጨቱንና በዚህም ምክኒያት ጉዳዩን አስመልክቶ ተደጋጋሚ ጥያቄ በስልክና በኢሜል እንደቀረበላቸው ገልጸዋል፡፡

ዋና ጸሐፊው ብሎጉ የማኅበረ ቅዱሳን እንዳልሆነና ማኅበሩ በዚህ ብሎግ መረጃ እንደማያስተላልፍ ምዕመናን እና የቤተ ክርስቲያን አካላት ሁሉ እንዲያውቁ አሳስበዋል፡፡

 
 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

intro

intro page