የሀገራችንን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተላለፈ የሰላም ጥሪ
‹‹ተገሐሥ እምዕኲይ ወግበር ሠናየ፤ ከክፉ ነገር ራቅ ሰላምን ፈልጋት›› (መዝ. ፴፫፥፲፪)
‹‹ተገሐሥ እምዕኲይ ወግበር ሠናየ፤ ከክፉ ነገር ራቅ ሰላምን ፈልጋት›› (መዝ. ፴፫፥፲፪)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የሥልጣኔና የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ ትምህርትና ሥልጣኔን ያስጀመረች፣ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲና የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሥርዓቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ገና ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዓትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኮትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት የጣለች፣ በውጭ ወራሪ ኃይል የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ወቅት የእምነቱ ተከታይ ምእመናኖቿና አገልጋይ ካህናቶቿ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእምነታችን መገለጫ የሆነውን የቃልኪዳኑን ታቦት ይዘው በየጦር ግንባሩ በመሰለፍና በመሰዋት እንኳንስ ሕዝቦቿ ምድሪቱም ለወራሪ ጠላት እንዳትገዛ በማውገዝ የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበረችና ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሌሎች አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ቅኝ ገዥዎች ያልደፈሯት አገር ተብላ በታሪክ ድርሳናት እንድትመዘገብ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች የሀገር ባለውለታ እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን እንኳንስ እኛ ልጆቿ ይቅርና የታሪክ ምሁራን ዘወትር በየአደባባዩ የሚመሰክሩት በብዕር ሳይሆን ለነጻነት በተከፈለ በአበው አባቶቻችን ደም የተጻፈ አኲሪ ታሪካችን ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊት ነች፡፡ አስተምህሮዋና መሠረተ እምነቷ ከአማናዊው መምህር ኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘ በመሆኑ አማናዊትና ርትዕት ናት፡፡ ከቤተክርስቲያን ታሪክ በቀጥታ መረዳት እንደሚቻለው ቤተክርስቲያኗ «ወርቃማ» ተብለው የሚጠሩ ዘመናትን ያሳለፈች ስትሆን በዚያው መጠን እጅግ ፈታኝ የሆኑ የመከራ ጊዜያትንም አሳልፋለች፤አሁንም እያሳለፈች ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም የራሱን እምነት በሰላም ማራመድ ሲገባው በተቃራኒው ፀረ ኦርቶዶክስ ዘመቻ በሁለት ግንባር በመካሔድ ላይ ይገኛል፡፡
የፀረ ክርስትናው ቡድን ውድመትና የሐሳውያን መናፍስት የቅሠጣ ዘመቻ፤በሰባክያነ ወንጌል እጥረትና በአባቶች ቸልተኝነት አብያተ ክርስቲያን እየተዘጉ ናቸው፤ምእመናንንም በነጣቂ ተኲላዎች እየተበሉ ነው፡፡ ለውጡን ተከትሎ የሚነሣ ፀረ ክርስትና ቡድን በሚወስደው ኢ-ክርስቲያናዊ እርምጃ ምክንያት የአምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ የሆኑት አብያተ ክርስቲያን ሲደፈሩና ሲወድሙ፤ በአገልጋዮቿ ካህናትና በተከታዮቿ ምእመናንም ላይ እስከ ኅልፈተ ሕይወት ጉዳት ሲደርስ፤ሌላ አቅም ባይኖራትም የተከታይ አቅም እያላት «ዝም በሉ የእኔን እግር ነው የሚበላው» እንደተባለው ዐይነት ነገር የደረሰባትን ጉዳትና ችግር ሁሉ በትዕግሥት፤በአርምሞና በጽሞና ማሳለፍ ይቻላል (ዜና ቤተክርስቲያን ርእሰ አንቀጽ፤ ጥቅምት እና ኅዳር ፳፻፲፩ ዓ.ም.)
እነዚህ ፈታኝ ወቅቶች ኢትዮጵያዊያን ሕዝባዊ ጠባይን የተላበሰ የአኗኗር ዘይቤ እንዲከተሉ ከማድረጉም በላይ የተለያዩ እምነቶች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ መንገድን አመቻችተዋል፡፡ ቤተክርስቲያኗም ከውስጥና ከውጭ በተነሱባት ፈተናዎች ምክንያት «ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው» (ማቴ.፳፥፲፱ ) «ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ» (ማር.፲፮፥፲፭) «አባቴ እንደላከኝ እናንተንም እልካችኋለሁ» (ዮሐ.፳፥፳፩) ተብሎ በወንጌል የታዘዘውን ለዓለም ለማዳረስ በምታደርገው አገልግሎት ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንቅፋት ሆነውባት አገልግሎቷን በሚፈለገው መጠን መፈጸም እንዳትችል አድርጓታል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የኅብረተሰቡን ችግር ምክንያት በማድረግ የተለያዩ እምነቶች አብዛኛውን የገጠርና ጠረፋማ ኀብረተሰብ የተሳሳተ አስተምህሮን በማስተማርና በጥቅም በመደለል ፍጹም ከቤተክርስቲያኗ ሲያርቁት መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ለዚህም በቂ ማስረጃ የሚሆኑን ለሦስት ተከታታይ ጊዜያት የተካሄዱት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤቶች ምስክሮች ናቸው፡፡
ይህ የሌሎች ቤተ እምነት ተጽኖ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በቂ አለመሆንና የምእመናን የግንዛቤ ማነስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ለሦስት ተከታታይ ወቅቶች በተካሄደው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት ቊጥራቸው እየቀነስ መጥቷል፡፡ ይህም በአኃዝ ሲሰላ (በ፲፱፻፸፮ ዓ.ም፤60.02% በ፲፱፻፹፮ ዓ.ም፤ 50.6% እና በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም፤43.5%) ይሆናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የአጽራረ ቤተክርስቲያን እንቅስቃሴ የሚገታና ምእመናንን በቤተክርስቲያን እንዲጸኑ ሊያደርግ የሚችል ሥራ መሥራት ካልተቻለ አሁንም ብዙ ምእመናንን ከቤተክርስቲያን በረት ይልቅ ወደ ሌሎች ቤተ እምነቶች የመኮብለል እድላቸውን ሊያሰፋው እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡ ስብከተ ወንጌል የቤተክርስቲያናችን የጀርባ አጥንት ነውና የግራኝ አሕመድ ጊዜ እንደገና እንዳያገረሽ፤ቤተክርስቲያናችን ዘመቻ ፊልጶስን ልታውጅ ይገባታል፡፡
ምንጭ፡ዐውደ ርእይ፤ ስለ ወንጌል እተጋለሁ! መጽሔት ከሰኔ ፲፬ እስከ ፲፮/፳፻፲፩ ዓ.ም.
የተከበራችሁ አንባብያን በዘመናችን ቤተ ክርስቲያን ያለችበትን ሁኔታና በየአካባቢው እና በየክልሉ በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት አስመልክቶ ክፍል አንድን ማቅረባችን ይታወቃል ክፍል ሁለትን እነሆ ብለናል፡፡
ምዕራባውያንና የእነሱ ጉዳይ አስፈጻሚዎች ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ይጠቅመናል ብለው ያሰቡትን ሁሉ ፈጽመዋል፡፡ የአሳባቸው አቀንቃኝ ኢትዮጵያዊ “ፈረንጆችንም” አግኝተዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም ሊቃውንቷንም ለመተቸት ያለ ስማቸው ስም ያለ ግብራቸው ግብር በመስጠት ጥላቻውን በመግለጽ አልሜዳ የተባለ ሚሲዮናዊ የፈጠራ ታሪክ ጽፏል፡፡ የእሱን ጥላቻ እየጠቀሱ ቤተ ክርስቲያንን የሚተቹት የግብር ልጆቹ ናቸው፡፡ የእሱን ጥፋት ዳንኤል ክብረት «አልሜዳ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን አምርሮ የሚጠላ ኋላ ቀርና በኑፋቄ የተሞላች አድርጎ የሚፈርጅ ኢየሱሳዊ /ሚስዮናዊ/ ነበር፡፡ በጽሑፎቹ ላይ ይህን ነው ሲያንጸባርቅ የኖረው፡፡ ከዚህ ጠባዩ አንጻርም አቡነ ተክለ ሃይማኖትን ቢተች የሚጠበቅ እንጂ የሚገርም አይደለም» (ዳንኤል፣ ፳፻፲፩፣፫‐፬) በማለት ገልጦታል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም ሆነ ተሐድሶአውያን አቡነ ተክለ ሃይማኖትን የሚተቹት የእሱን አሳብ እየጠቀሱ ነው፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን መንቀፍና ያለ ግብራቸው ግብር መስጠት ቤተ ክርስቲያንን ለማዳከም ይጠቅመናል ብለው ያስባሉ፡፡ ለኋለኞቹ የቤተ ክርስቲያን ተችዎች ጀማሪና ፊታውራሪያቸው አልሜዳ ነው፡፡ የውጭ ጸሐፊዎች የኢትዮጵያውያንን አእምሮ በመበረዝ ቤተ ክርስቲያን ላይ ትችት እንዲያዘንቡ ምክንያት መሆናቸውን ከአልሜዳ ጽሑፍ መረዳት ይቻላል፡፡ ለመነሻ ያህል ይህን ካቀረብን በየዘርፉ የደረሱትን ችግሮች እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡
ሀ. የቤተ ክርስቲያን መቃጠል፡- በየዘመናቱ፣ በየቦታው አብያተ ክርስቲያናት በአክራሪ ሙስሊሞች፣ በግለኝነት በታወሩ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮችና በአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ሲቃጠሉ ቆይተዋል፡፡ ይህን የሚያደርጉት የግል ጥላቻና የተለየ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖች እንጂ ሁሉም የሌሎች እምነቶች ተከታዮች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስትቃጠል አብረው የሚያዝኑና የሚያለቅሱ፣ ክርስቲያኖች ሲሳደዱና መከራ ሲደርስባቸው በቤታቸው የሚሸሽጉ ብሎም አብረው መከራ የሚቀበሉ፣ ክርስቲያኖች ኃይላቸውን እያሰባሰቡ አቅማቸውን እያጠናከሩ መልሰው ለመገንባት ሲደክሙ ከገንዘብ እስከ አሳብ ድጋፍ የሚያደርጉ የሌላ እምነት ተከታዮች አሁንም በየቦታው መኖራቸው የሚካድ አይደለም፡፡ በዘመናችንም ክርስቲያኖች በጥብዐት መከራውን ተቋቁመው ክርስትና በሞት፣ በስድት፣ በእሳትና በመከራ የማይፈታ መሆኑን አስመስክረዋል፡፡ በዚሁ አንጻር ግን በመገናኛ ብዙኃን በተለያዩ ቦታዎች የሚቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያናት ያልታወቁ ግለሰቦች ያቃጠሏቸው እንደሆነ ቢነገርም ታስቦበት፣ ተጠንቶ፣ ምን ለማግኘትና ምን መልስ ለመስጠት አስቀድሞ እየታሰበ ቃጠሎው መፈጸሙን የሚጠቁሙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ፲፱፻፺፫ዓ.ም ሚያዝያ ፲፪ ቀን በአርሲ ሀገረ ስብከት ኮፈሌ ወረዳ ጉች ቀበሌ ገበሬ ማኅበር የሚገኘው የመድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በአክራሪ እስላሞች ለመቃጠል የቻለው ከተማ ላይ ሊያደርሱት የነበረው አደጋ በመከላከያ ሠሪዊትና በፖሊስ ስለተደናቀፈባቸው ነው፡፡ ገጠር በመግባት የክርስቲያኖችን ቤት እየመረጡ ማቃጠላቸው የታቀደና የተደራጀ ጥቃት መሆኑን ለመረዳት ይቻላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሃይማኖታዊ ትንኮሳ ከትላንት እስከ ዛሬ መቀጠሉ ታስቦበት እየተሠራ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በአንድ በኩል አጥፊዎች ልብ እንዲገዙ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ከትላንት እስከ ዛሬ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በመረዳት ለእምነት ቤቶችና ለክርስቲያኖች ልዩ ጥበቃ እንዲያደርግ ሊያነቁ፣ ምእመናንም ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ እንዲደራጁና አዲስ ነገር ሲገጥማቸው ለፍትሕ አካላት እንዲያቀርቡ ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡ ክርስቲያኖች የሚማሩት ከመከራ፣ ቅድስናቸው የሚገለጠው በፈተና መሆኑ የተጻፈ፣ ክርስቲያኖች በተግባር ፈጽመው ያሳዩት ሕይወት ነው፡፡
በጅማ ሀገረ ስብከት ከመስከረም ፲፮ እስከ ጥቅምት ፬ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም ጨጉ ቅዱስ ገብርኤል፣ ቦሬ ቅዱስ ገብርኤልና በሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናት በአክራሪ እስላሞች ተቃጥለዋል፡፡ ንዋያተ ቅድሳት ተዘርፈዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በጅማ፣ በምዕራብ በወለጋና በኢሉባቡር ከ፲፫ በላይ አብያተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ተዘርፈዋል፡፡ ኅዳር ፮ ቀን ፲፱፻፺፰ዓ.ም በአርሲ ሀገረ ስብከት በኮፈሌ ወረዳ የምትገኘው የአይሻ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፀረ ክርስትና አቋም ባለው ቡድን ተቃጥላለች፡፡ አገልጋይ ካህናት በቤተ መቅደስ ውስጥ ታርደዋል፣ አሥር ክርስቲያኖች በገጀራ ተገድለው፣ አብያተ ክርስቲያናትና የክርስቲያኖች መኖሪያ ቤቶች ተቃጥለዋል፡፡ ብዙ ንብረት ወድሟል፤ ነዋሪዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው በሀገራችን ሰላም እንዳይሰፍን ሆን ብለው ግጭት የሚፈጥሩ አካላት መኖራቸውን ነው፡፡
በወቅቱ አጥፊዎችን ሊያስተምር የሚችል እርምጃ መወሰድ ሲገባ ጉዳዩ ለሕዝብ ይፋ እንዳይሆን ከመንግሥት አካላት ተጽዕኖ ይደረግ ነበር፡፡ አጥፊዎችን ማስታገስ ሲገባ ጉዳት የደረሰባቸው ክርስቲያኖች ጉዳታቸውን እንዳይናገሩ መከልከል ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ ሲፈጸም መፈጸም በሕግም በሞራልም የሚያስወቅስ ነው፡፡ ይህ በምንም ዓይነት መንገድ ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ለአጥፊዎች ከለላ መስጠትን እንጂ ለፍትሕ መቆምን አያሳይም፡፡ አጥፊዎች ሲያጠፋና ክርስቲያኖችና አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ ዝም ብሎ ማየት ትዕግሥትን ሳይሆን የጥፋት ተባባሪ መሆንን የሚያሳይ ነው፡፡
በወቅቱ የመንግሥት አካላትን ያሳስብ የነበረው የገደሉትንና አደጋ ያደረሱትን አካላት ለመያዝ ሳይሆን አደጋው በተፈጸመበት ወቅት ከቦታው ተገኝተው የዘገቡትን አካላት ለመያዝ ነበር፡፡ ይህ ተግባር አሁንም ስለቀጠለ ቤተ ክስስቲያን እየተገፋች ድምፅ የሚያሰማላት አካል እያጣች ነው፡፡ አጥፊዎች ለስንት ሺህ ዘመናት የኖረ የሀገር ሀብት ሲያወድሙ እንደ ቀልድ እየታለፈ መሆኑ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በየካቲት ወር መጨረሻና በመጋቢት ወር መጀመሪያ በድሬደዋ ከተማ አጠገብ የሚገኘውን ደን በመመንጠር የቤተ ክርስቲያንን መሬት በመከፋፈል ላይ ሳሉ ሕግ አስከባሪ አካላት ቢደርሱም አልታዘዝንም በማለት ቆመው ሲመለከቱ አጥፊዎች ከቦታው እንዲሸሹ ሲያደርጉ እንደነበር የዐይን እማኞች ገልጠዋል፡፡ በሊሙ ኮሳ ወረዳ በያዝነው ዓመት በተፈጸመው ጥፋት ከወረዳ አመራር ጀምሮ ሥልጣን ላይ የሚገኙ ወገኖች ጥፋቱን ያደረሱት አካላት በእምነት ስለሚመስሏቸው ወደ ሕግ ለማቅረብ አለመቻላቸውን ወረዳ ቤተ ክህነቱ ለሀገረ ስብከቱ የጻፈው የድረሱልኝ ደብዳቤ ያስረዳል፡፡ ምክንያት ተፈልጐ የሚያዙትና ካለ ፍርድ እስር ቤት እንዲቆዩ የሚደረጉትም ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ይህም ክርስቲያኖች እንዲሞቱ የተፈረደባቸው፣ ለሚደረስባቸው አደጋ ሁሉ ከለላ የሌላቸው መሆኑን ሲያመለክት አጥፊዎች ደግሞ ሽፋን የሚሰጣቸው ይመስላል፡፡ ይህንም በሐረር ከተማ ጥር ፲፩ ቀን ፲፱፻፺፫ ዓ.ም ለጥምቀት በዓል በወጡ ምእመናን ላይ ለጁምአ ስግደት በአንድ መስጊድ ተሰብስበው የነበሩ ሙስሊሞች በፈጸሙት ትንኮሳ ግጭት ተፈጥሮ የአራት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በፖሊስ ቊጥጥር ሥር የዋሉት ፲፮ ምእመናን ያለ ምንም ውሳኔ ከስድስት ወራት በላይ መቆየታቸው ማሳያ ነው፡፡ ግጭቱን ማን እንደጀመረው? ዓላማው ምን እንደነበር? አጣርቶ አስቸኳይ ውሳኔ መስጠት፣ አጥፊም በጥፋቱ እንዳይቀጥል ማስተማር ሲገባ ክርስቲያኖችን መርጦ ማሰር መፍትሔ አይሆንም፡፡ ወንጀል የፈጸመ ሰው አይያዝ ባይባልም ክርስቲያኖች ብቻ ተይዘው የሚታሰሩበት፣ ቢታሰሩም ቶሎ ለፍርድ የማይቀርቡበት ምክንያት ሌላ ዓላማ ያለ ያስመስላል፡፡
በአጥፊዎች ላይ ውሳኔ ቢሰጥበትም ቤተ ክርስቲያንን ላቃጠሉ፣ ንዋያተ ቅድሳትን ለዘረፉ አካላት የሚሰጠው ፍርድ አንድ በግ ከሰረቀ ሌባ ጋር ልዩነት የሌለው በነፃ ከማሰናበት ያልተሻለ መሆኑ ለክርስቲያኖችና ለቤተ ክርስቲያን ትኩረት መነፈጉን የሚያሳይ ነው፡፡ መረዳት የሚገባው ቤተ ክርስቲያንን አቃጥለው፣ ቅርሱን አውድመው እስከሚጨርሱ ዝም ከተባለ “ኢትዮጵያን የጎብኝዎች መዳረሻ እናደርጋለን” የሚለው አሳብ የሕልም እንጀራ መሆኑን ነው፡፡ የሚነገረው ቃልም ተፈጻሚነት ሳይኖረው ክርስቲያኖችን በማይሆን ነገር ለማዘናጋት የሚፈጸም መሆኑን የሚያሰገነዝብ ነው፡፡ ይህም በቤተ ክርስቲያን ላይ የተነሡት አፅራረ ቤተ ክርስቲያን ብቻቸውን ሳይሆኑ በጀርባቸው ሌላ አይዞህ ባይ እንዳላቸው የሚያመለክት ነው፡፡ የክርስቲያኖችና የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ትኩረት እንዳይሰጠው፣ በመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዳያገኝና ሽፋን የሚያገኘውም ዘግይቶ መሆኑ ሌላ ችግር ይዞ እንዳይመጣ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ የሚሰጠው አስተያየት እውነት የሚመስለው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የሚፈጽሙት እንዲሸፈን መደረጉ ነው፡፡
በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሜኤሶን ወረዳ በሚገኘው የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አቡነ ሳሙኤል ገዳም የካቲት ፳ ቀን ፳፻፬ ዓ.ም ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ለከብት ዘረፋ ወደ ገዳሙ ክልል የገቡ የኢሳ ጎሳ አባላትን ለመከላከል የተደረገውን የተኩስ ልውውጥ ተከትሎ ሰደድ እሳት ተቀሰቀሰ፡፡ በወቀቱ የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ከ፳፻፩ ዓ.ም በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ነበር፡፡ ከአሥራ አምስት ዓመት በፊት ተቀስቅሶ ለ፲፭ ቀናት የቆየው ሰደድ እሳት ከ፲፩ ሺህ ሄክታር በላይ ደን አውድሟል፡፡ እሳቱ በቊጥጥር ሥር የዋለው ከዋናው የገዳሙ ግቢ ለመድረስ ፭፻ ሜትር ያህል ሲቀረው ነበር፡፡ በወቅቱ ከ፴፰ ያላነሱ ከሰል አክሳዮች ለሰደድ እሳቱ መነሣት ምክንያት ናቸው በሚል ተጠርጥረው በቊጥጥር ሥር ቢውሉም ወዲያው በዋስ ተለቀዋል፡፡ ክስ ይመሥረትባቸው አይመሥረትባቸውም የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው በቤተ ክርስቲያንና በክርስቲያኖች ላይ ለሚደርሰው ጥፋት ማስተካከያ የሚሰጥ አለመኖሩን ያሳያል፡፡
ይቆየን!
ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከግንቦት ፲፮-፴ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም
በተለያዩ መድረኮች ቤተ ክርስቲያን ከእምነት ውጭ የሆኑትን ለማሰቃየት የክፉ አድራጊዎች ጠበቃ የሆነች የሚያስመስሉ ጽሑፎች ይቀርባሉ፡፡ ድብቅ ዓላማ ያላቸው ወገኖች ቤተ ክርስቲያንንና ክርስቲያኖችን ለማጥፋት ሰበብ በመፈለግ ጥፋተኛ እያስመሰሉ ያቀርባሉ፡፡ በመሠረቱ ይህ አስተሳሰብ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉበት፡፡ የመጀመሪያው ታሪክ በመሰነድ፣ ትውልድ በምግባር ኮትኩታ ያቆየች ባለውለታ፣ ቅርሶቿ ለሀገር ልዩ መታወቂያ ጐብኝዎችን ማርኮ የሚያመጣ ሆኖ ሳለ ያለ ስሟ ስም መስጠቱ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከእውነት የራቀ ሐሳብ ይዘው ጥፋተኛ ሳትሆን፤ ጥፋተኛ ስለሆነችና ከአጥፊዎች ስለተባበረች መጥፋት ይገባታል እንበቀላት የሚለው ነው፡፡ እነዚህ ለማጥፋት ምክንያት ፈላጊ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን እያቃጠሉና ምእመናንን እየገደሉ ለምን ሲባሉ ጥፋተኛ ስለሆነች ይላሉ፡፡ መቼ፣ የት፣ በማን፣ እነማንን ተብለው ሲየጠቁ መልስ የላቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማቃጠልና ምእመናንን መግደል የእምነቱ ተከታዮች ራሳቸውን ወደ መከላከል ከዚያም ወደ መጉዳት ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ መረዳት ይገባል፡፡ ለተፈጸመው ጥፋት አጸፋውን ቤተ ክርስቲያን ብትመልስ በሀገር ላይ ሊከሠት የሚችለውን ጥፋት አስቀድሞ መረዳትም ይጠቅማል፡፡ ጥናትን ሽፋን አድርጎ ለአጥፊዎች ዱላ የሚያቀብሉ አካላትም ከድርጊታቸው መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት አጥፊዎችን ለሕግ ከማቅረብ በተጨማሪ ለክርስቲያኖችና ለቤተ ክርስቲያን ከለላ መስጠት ይኖርበታል፡፡ አጥፊዎችም ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የመዘዙት ሰይፍ ወደ ራሳቸው እንዳይዞር እና የእርስ በእርስ መጠፋፋት ሊያስከትል እንደሚችል ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በሃይማኖትና በዘር ምክንያት የተቀሰቀሰ ግጭት መብረጃ እንደሌለው በየሀገራቱ የተፈጸሙትን ጥፋቶች ማየት ይገባል፡፡ ታሪክ መጥቀስ ብቻውን የዕውቀት ባለቤት አያደርግም ከታሪክ መማር እንጂ፡፡
ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ወዲህ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውንና ከዛሬ ነገ እርምት ይወስድበታል በማለት በትዕግሥት ስትጠብቅ መኖሯን ከመግለጻችን በፊት ቤተ ክርስቲያን ለሀገር ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በመጠኑ ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማያት ስታዘጋጅ፣ በፍቅር ስባ፣ በትምህርት አለዝባ በእምነትም በምግባርም እንዲስተካከሉ በማድረግ ነው፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት መካከል ሀገራችን ብቸኛ የራሷ ፊደል ያላት፣ ዘመን ተሻግሮ ከዘመናችን የደረሰ ቅርስ አበርክታ ሀገራችን በመላው ዓለም እንድትታወቅ ያደረች ባለውለታ ናት፡፡ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ኢትዮጵያውያን የቅኝ ግዛት ቀንበርን ሰብረው ጥለው፣ የነጭን ትምክተኛነት አስተንፍሰው ልጆቻቸው ቀና ብለን እንድንሔድ የመሪነቱን ሚና የተጫወተች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በውጭ ሀገራት በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተጽፈው እምነት፣ ዕውቀት፣ ሥነ ምግባር የሚያስተምሩ መጻሕፍት ኢትዮጵያዊ በሆነ ብሂል ተተርጒመው ትውልድ እንዲማርባቸው፣ ሊቃውንቶቿ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በአውሮፓ የኢትዮጵያን ባህል፣ ሃይማኖት፣ ታሪክ በማስተዋወቅ የአምባሳደርነት ሚና እንዲጫወቱ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህን የቤተ ክርስቲያን አስተዋጽኦ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ‹‹የኢትዮጵያ ምሁራን መነኮሳት በኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ክልል ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ውጭ በመሔድ በታሪክ ሊታወስና ሊጠና የሚገባ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ አካባቢ በሱዳንና በግብፅ፣ በየመንና በኢየሩሳሌም፣ በአውሮፓ በመሔድ እነሱም እየተማሩ፣ የውጭውንም ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋና ታሪክ፣ ሃይማኖትና ባህል እንዲያውቅና እንዲፅፍ አድርገዋል›› (አክሊሉ፤፹፩) በማለት ገልጠውታል፡፡
እውነተኞቹ ተመራማሪዎች ያለ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን ማሰብ እንደሚከብድ በምርምራቸው አረጋግጠው እውነቱን ከሐሰት፣ ብስሉን ከጥሬ፣ የሚጠቅመውን ከሚጐዳው፣ የተፈጸመውን ካልተፈጸመው ለይተው ከጥንካሬያችን እንድንማር ከስሕተታችን እንድንጠበቅ ያደረጋሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማዳከም ዓላማችንን ያሳካልናል ብለው የሚያስቡ ወገኖች ደግሞ ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ፈልገው ቅስማቸው ተሰብሮ እንዲመለስ ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ስለተረዱ ስሟን ለማጥፋት፣ ታሪኳን ለመበከል የጻፉትን አሉባልታ እውነት አድርገው በመውሰድ ታሪክ ሲያበላሹ፣ በተቀመጡበት የኃላፊነት ቦታ ጥፋት ሲፈጽሙ ይታያሉ፡፡ ሰውን በሰውነቱ እኩል ማገልገል ሲገባቸው በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በጎጥ፣ በቡድንና በባህል በመከፋፈል ሥልጣንን ለክፉ ተግባር ይጠቀማሉ፡፡ ሕዝብን ለማገልገል የተሰጣቸውን ሥልጣን ተጠቅመው ቤተ ክርስቲያንንና ምእመናንን የማሳደድ ተልእኮ ይፈጽማሉ፡፡ ሀገር ሰላም ካልሆነችና ዜጎቿ በሰላም ወጥተው ካለገቡ አጥፊዎችም ችግር እንደሚገጥማቸው አልተረዱትም፡፡
በካናዳ፣ በቫቲካን፣ በጀርመንና በሌሎችም ሀገሮች የኢትዮጵያ ጥናት ተቋማት እንዲከፈቱ፣ ተመርምሮ የማያልቅ ዕውቀት የያዙት የብራና መጻሕፍት ለዓለም እንዲተዋወቁ ያደረጉት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምራ «ሑሩ ወመሀሩ» ብላ ያሰማራቻቸው ሊቃውንት ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም ሀገራችን እንግዳ ተቀባይ የሆነችውና ዓለም ፊቱን ያዞረባቸውን የመሐመድ ተከታዮች ሳይቀር መጠጊያ እንድትሆን ያደረጋት ቤተ ክርስቲያን በእምነት ኮትኩታ፣ በምግባር አንፃ ያስተማረቻቸው እነ ንጉሥ አርማህ ርኅሩኆች ብቻ ሳይሆኑ አስጠጉኝ ብሎ የመጣባቸውን አሳልፈው ለመስጠት ሰብአዊነት የተለያቸው ስላልነበሩ ጭምር ነው፡፡
ወርቅ ላበደረ ጠጠር፣ እህል ላበደረ አፈር እንዲሉ ይህን ውሉ ውለታ ለዋለች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰጠው መልስ ነው፡፡ የደረሱበት መረጃ ካለ ማስረጃን መሠረት አድርጎ እውነት ማሳወቅ አንድ ነገር ነው፣ ሐሰትን እውነት እያስመሰሉ ማቅረብና ሰውን ለብጥብጥ መጋበዝ ግን ጤነኛ አእምሮ ያለው፣ በእግዚአብሔር የሚያምን ሰው የሚፈጽመው አይደለም፡፡ በየጊዜው ቤተ ክርስቲያንን የሚያቃጥሉት፣ ክርስቲያኖችን የሚገድሉት፣ ንብረታቸውን የሚቀሙትና የሚያሳድዱት ከመጥፎ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ መንግሥት እርምት ይወስዳል ቢባልም ምንም ነገር እንዳልተፈጸመ እየታለፈ፣ የማዘናጊያና የማረሳሻ ተግባር እየተፈጸመ ነው፡፡
ከምዕራባውያን የተኮረጀው ሥርዐተ ትምህርት ባልነበረበት ዘመን የሀገራቸው አምባሳደር የነበሩ፣ የውጭ ዲፕሎማት ሲመጣ አስተርጓሚ ሆነው ሲያገለግሉ የኖሩ ሊቃውንትን ያፈራችን ቤተ ክርስቲያን ከዋለችበት ላለማሳደር፣ ካደረችበት ላለማዋል እየተፈጸመ ያለው ግፍ መቆም አለበት፡፡ የሊቃውንቱን አስተዋጽኦ አክሊሉ ሀብቴ ‹‹ሆኖም እዚያ (ኢየሩሳሌም) የተደራጀው የመነኮሳት ማኅበር ኢትዮጵያን በመወከል ወደ ኢጣሊያም፣ ወደ አርመንም፣ ወደ ቊስጥንጥንያም፣ በመሔድ ግንኙነት ፈጥሮ እንደነበርና ምን አልባትም ከአርመኖች ጋር በነበረው የቅርብ ግንኙነት አርመኖች ፊደላቸውን ሊቀረፁ የቻሉት ከኢትዮጵያ ፊደል እንደሆነም ይነገራል፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም በሚመላለሱበት ዘመን እግረ መንገዳቸውንም ከሱዳንና ከግብፅ ክርስቲያኖች ጋር የቅርብ ግንኙነት መፍጠራቸው ይታመናል፡፡ የቀድሞዎቹ የኢትዮጵያ ምሁራን መነኮሳት ፈር ቀዳጅ አስተዋጽኦ እንዲሁ መጠናት የሚገባው ነው›› (አክሊሉ፣ ፷፪) በማለት ገልጠውታል፡፡
ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ሰው አክባሪ፣ ሀገር ወዳድ፣ የሥራ ፍቅር ያላቸው፣ የራሳቸውን የማያስነኩ፣ የሌላውን የማይፈልጉ አድርጋ ስታሳድጋቸው ጠብ አጫሪነትን፣ በጉልበታቸው የሚመኩ መሆንን እንዲጸየፉ በማድረግ ነው፡፡ ጠላታቸውን በጽናትና በትዕግሥት እንዲቋቋሙ፣ ሀገርና ሃይማኖት ሊያጠፋ የመጣውን የጥፋት ኃይል እንዳያሸንፍ ያደረገች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይህ ድርጊቷ ያበሳጫቸው ምዕራባውያን በዘመናዊ ትምህርት ሰበብ በየሴሚናሪዎቻቸውና ኮሌጆቻቸው አስተምረው የላኳቸው ወገኖቻችን ነባሩን የኢትዮጵያ ሃይማኖትና፣ የክርስቲያኖች ተጋድሎ የሚያናንቅ፣ መልኩ የእኛ ቢሆንም የነጭ ጉዳይ አስፈጻሚ ሀገሪቱን ለባዕድ አሳልፎ ለመስጠት የባለቤትነት ስሜት የሚያድርበት እንዳይሆን አእምሮውን ለውጠው ሲልኩት ኖረዋል፡፡ በመመረቂያ ጽሑፍ ሰበብ ቤተ ክርስቲያንን ያለ ስሟ ስም፣ ያለ ግብሯ ግብር እየሰጡ የዘመናችን ተመራማሪ ነን ባዮች የግብር አባት ሆኑ፡፡ በዚህ ተግባራቸውም ትውልዱ በሰላም ውሎ እንዳይገባ እንቅልፍ ላጡ ወገኖች መንገድ መሪ የጥፋት ተባባሪ ሆነው አልፈዋል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሠየሙ አካላት በተለያዩ የኅትመትና የብሮድካስት ሚዲያዎች በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያወርዱትን የስድብ ዶፍ መመልከት ይቻላል፡፡ በአካል መግዛት ያልተቻላቸውን ኢትዮጵያውያንን በአእምሮ ለመግዛት መሰሎቻችንንና በሥጋ የሚዛመዱንን አእምሮ እየለወጡ የሚልኩልንንና እነሱም አልፎ ሒያጅ መንገደኞችና ለቤተ ክርስቲያን ጥላቻ ያደረባቸውን ወገኖች እየጠየቁ የጻፉትን አሉባልታ በትክክለኛ ማስረጃ በመሞገት፣ የዕውቀታቸውን ግልብነት፣ የመረጃቸውን ተራነት፣ የትነታኔያቸውን አመክንዮ አልባነት ማሳየት ይኖርብናል፡፡ አጥፊዎች ታጥቀው ሲዘምቱብን ዝም ብሎ ማየት እሳት መቃጠሉን የሰማ የዋህ እኔስ ሣር ውስጥ ተደብቄያለሁ በማለት የመለሰውን የሚያስታውስ ይሆናል፡፡
ቱሪስቶች ሊጐበኙ የሚመጡት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ገዳማት፣ አድባራት፣ ሥዕላት፣ የብራና መጻሕፍትና ንዋያተ ቅድሳት እንዲሁም ክርስቲያን ነገሥታት የገነቧቸውን አብያተ ክርስቲያናት፣ ሐውልቶችና አብያተ መንግሥታት ለመጎብኘት ነው፡፡ ይህን አስተዋጽኦ ያደረገችልን ቤተ ክርስቲያን መደገፍና መጠበቅ ሲገባ ስትጠቃ ዝም ብሎ ማየት ማሯን እንጂ ንቧን አልፈልግም እንደ ማለት ይቈጠራል፡፡ ለጥፋት የተሰለፉ ወገኖች በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን ላይ አደጋ ሲያደርሱ የግለሰቦች ጉዳይ እየመሰለ ይቀርባል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ይነገራል፡፡ በሌሎች እምነቶች ላይ የሚፈጸመው ወይም ራሳቸው ፈጽመው ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል የተባለውን ለሚፈጽሙት ግን ከመገናኛ ብዙኃን ጀምሮ የሚሰጠው ሽፋን የሚገርም ነው፡፡ ይህም ክርስቲያኖች ሲገደሉ፣ አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ መረጃው በቶሎ እንዳይነገር ከተቻለም ተዳፍኖ እንዲቀር ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን እንድንጠረጥር የሚያደርግ ነው፡፡ ለምሳሌ በቡኖ በደሌ የተፈጸመውን ሰቆቃ በሥልጣን ላይ የተቀመጡ አካላት ወንጀሉን የፈጸሙት አካላት በእምነት ስለሚመስሏቸው ለማዳፈን ሞክረዋል፡፡ በሰሜን ሸዋና በኬሚሴ በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያን ላይ የደረሰው ጥፋት በመገናኛ ብዙኃን የተነገረው ጥፋቱ ከተፈጸመ ከአራት ቀናት በኋላ መሆኑን ኢትዮጲስ ጋዜጣ በሚያዝያ ፮ ዕትሙ አስነብቧል፡፡ በበሻሻ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና አካባቢው አብያተ ክርስቲያን ተቃጥለውና ምእመናን ተገድለው አጥፊዎችን መያዝ ሲገባ መረጃው ያላቸውን ክርስቲያኖች ለመያዝ ይደረግ የነበረው ወከባ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
ይቆየን!
ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከግንቦት ፲፮-፴ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም
ዲያቆን ዘአማኑዔል አንተነህ
ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በቀድሞው አጠራር በሰሜንና በጌምድር ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ ደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር በደራ ወረዳ አፈሯ እናት በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዴዎስ ደብር ልዩ ስሙ አባ ጉንቸ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከአባታቸው ከአቶ ፈንታ ወልድዬ ከእናታቸው ከእሙሐይ ጥዑምነሽ አብተው በ፲፱፻፳፯ ዓ/ም ግንቦት ፳፱ ቀን ተወለዱ፡፡ብፁዕነታቸው በአባታቸውና በእናታቸው በሥርዓትና እንክብካቤ ካደጉ በኋላ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በወላጆቻቸው መልካም ፈቃድ በተወለዱበት በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዴዎስ ቤተ ክርስቲያን ከታዋቂው የድጓ መምህር ከየኔታ ኃይሉ ፊደል ቆጥረው ዳዊት ከደገሙ በኋላ ጾመ ድጓ፤ ውዳሴ ማርያም ዜማ እስከ አርያም ክስተት አጠናቀው ተመርዋል፡፡
የቁም ጽሑፍ ከአጎታቸው ከቀኝ ጌታ ዓለሙ ወልድዬ ተምረው ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ፀጋ የዲቁና ማዕረግ ከብጹዕ አቡነ ሚካኤል ደብረ ታቦር ከተማ ተቀብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ባላቸው የትምህርት ፍላጎት መሠረት ትምህርታቸውን በመቀጠል ቅኔ ጎጃም ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከመምህር ፀሐይ ተምረዋል፡፡ በተጨማሪም የቅኔ ትምህርታቸውን ለማጠናከር ወደ ሰሜን ሽዋ በመሄድ ምንታምር ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከየኔታ ኃይለ ጊዮርጊስ በመግባት ቅኔ በመማር ተቀኝተዋል፡፡ ዝማሬ መዋሥዕት ለመማር ወደ ደቡብ ጎንደር ተመልሰው ከየኔታ መርዓዊ ዙርአባ በመግባት የዝማሬ መዋሥዕት ትምህርታቸውን አጠናቀው በመምህርነትም ተመርቀዋል፡፡ ከዛም ወደ ደብረ ፅጌ ተመልሰው በመሄድ ከየኔታ ገብረ እግዚአብሔር ደብረ አባይ ቅዳሴ ተማሩ፡፡ ከመምህር ገብረ ሕይወት ሐዲሳት፤ ፍትሐ ነገስት አንድምታ ትርጓሜ፤ ዳዊት አንድምታ ትርጓሜ፤ ውዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ፤ ባሕረ ሐሳብ የኪዳንና ትምህርተ ኅቡአት አንድምታ ትርጓሜም ተምርዋል፡፡
በደብረ ፅጌ በነበሩበት ወቅት ትንቢተ ኢሳይያስና ትንቢተ ዳንኤል አንድምታ ትርጓሜና የቀሩትን መጻሕፍተ ብሉያት ተምረዋል፡፡ በደብረ ፅጌ ከመምህር ቀለመወርቅ አቋቋምም ለመማር ችለዋል፡፡ በወቅቱ ዘመናዊ ትምህርት ለመማር በነበራቸው ፍላጎት ኃይሌ ደጋጋ ከሚባል ትምህርት ቤት ገብተው ከ፩ኛ እስከ ፰ኛ ክፍል በደብረ ጽጌ ተምረዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት እያሉ ከአጎታቸው በተማሩት ቁም ጽሑፍ ተአምረ ማርያም ፤ ፍትሐ ነገስት፤ ፬ቱ ወንጌላትና መልእክተ ጳውሎስ እስከ ዮሐንስ ራእይ እንዲሁም ዚቅ በእጃቸው ጽፈዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን በመንፈሳዊ አባትነት ለማገልገል መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በማጠናከር ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገቡ፡፡ አገልግሎታቸውንም በቅንነት፤ በታማኝነትና በትሕትና እየፈጸሙ ከገዳሙ ከቆዩ በኋላ በዛው ገዳም መንኩሰዋል፡፡ ስማቸውም መምህር አባ ኅሩይ ፈንታ እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡ ከዚያም በመቀጠል ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ኤርትራዊ የቅስና ማዕርግ ተቀበሉ፡፡ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያኗን ለማገልገል ጽኑ ፍላጎት ስለነበራቸው ወደ አርባ ምንጭ በመሄድ የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሆነው በሀገረ ስብከቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የካህናት ማሰልጠኛ እንዲከፈት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ከነበሩት ሊቀ ጳጳስ መመሪያ እየተቀበሉ ማሰልጠኛው እንዲከፈትም ሆኗል፡፡ በዚሁ በአርባ ምንጭ ቆይታቸውም ከብፁዕ አቡነ ሰላማ የቁምስና ማዕርግ ተቀብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ለመኖር ባላቸው ፍላጎት መሠረት ከአርባ ምንጭ ተመልሰው የደብረ ሊባኖስ ገዳም አንዱ አካል በሆነው በደብረ ጽጌ አገልግሎት እየሰጡ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አባት በመሆን ስብከተ ወንጌል እያጠናከሩ ለብዙ ዓመታት ቆይተዋል፡፡
ከዚያም ለከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ማዕርግና አገልግሎት ታጭተው ወደ አዲስ አበባ ሄዱ፡፡ ጥር ፲፫ ቀን በ፲፱፻፸፩ ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፓትርያርክ ሊቀ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ከተሸሙት ከ፲፫ቱ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል አንዱ በመሆንም ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ተብለው በአንብሮተ ዕድ ቆጶስነት ማዕርግ ተቀብለዋል፡፡
የብፁዕነታቸው የ፵ ዓመታት የሥራ ዘመን
ከ፲፱፻፸፩ አዲስ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፸፮ ዓ.ም ድረስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ የጀመሩበት ሀገረ ስብከትም ነበር፡፡ በዚሁ ሀገረ ስብከት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ በጅማ ሀገረ ስብከት ብፁዕነታቸው ተመድበው ሲሄዱ የካህናት ማሰልጠኛ የሌለ በመሆኑ ዲያቆናት፤ካህናት፤መምህራን ካላቸው እውቀት በተጨማሪ በሥልጠና ከዘመኑ ጋር ተዋሕደው ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያገለግሉ ለማድረግ የካህናት ማሰልጠኛ ከፍተዋል፡፡ ከነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ ፶ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት በመትከል ሕዝቡን በማስተማርና በመምከር ቅዳሴ ቤታቸውን አክብረው ቤተ ክርስቲያን እንድትስፋፋ አድርገዋል፡፡
ከ፲፱፻፸፮ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፸፰ ዓ.ም ድረስ የከፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመድበው ሲሄዱም ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር ተዋሕዶ ሃይማኖት እንዲስፋፋ ባላቸው ጠንካራ አቋም ፳፮ አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል ቅዳሴ ቤታቸውንም አክብረዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ከ፲፱፻፸፰ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ድረስ ለ፬ ዓመታት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ፍትሕ መንፈሳዊ የበላይ ጠባቂ ሆነው በተመደቡበት ወቅት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎት እንዲጠናከርና እንዲስፋፋ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊነት ለ፬ ዓመታት ቤተ ክርስቲያኗን እያገለገሉ በቆዩበት ወቅት የጽሕፈት ቤቱን አደረጃጀት በሚገባ በመምራት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በአግባቡ እንዲፈጸም በማድረግ ከብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ የሚሰጡ መመሪያዎችን በመተግበርና በማስተግበር ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ሥራ ሰርተዋል፡፡
ከ፲፱፻፹፩ ዓ.ም እስከ ፳፻፩ ዓ.ም ድረስ ለ፳ ዓመታት የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲመደቡ ሀገረ ስብከቱ አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ለሊቀ ጳጳስ ማረፊያ (መንበረ ጵጵስና) የሌለው ከመሆኑም በላይ የሀገረ ስብከቱ አደረጃጀትም ገና ብዙ ሥራ ይጠይቅ ነበረ፡፡ በአዲስ መልክ ለማደራጀት ብዙ ድካም የሚጠይቅም ስለነበረ ብፁዕነታቸው ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ፀጋ ራሳቸው አቅደው ሀገረ ስብከቱ ምንም ገንዘብ ባይኖረውም መጀመሪያ መንበረ ጵጵስና መሠረት እንዳለበት ወሰኑ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር አብያተ ክርስቲያናቱም የተቻላቸውን እንዲያወጡና ሀገረ ስብከቱን እንዲያጠናክሩ በማስተማር ከአዲስ አበባና ከውጪ ሀገራት ገንዘብ በማሰባሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ፲ ክፍል ያለው መንበረ ጵጵስና፤ ፳፩ ክፍል ያለው የሀገረ ስብከት ቢሮ ፤ ፩ ንብረት ክፍል፤ ፩ አዳራሽ እና ፩ መጋዝን በማሠራት ሀገረ ስብከቱ እንዲጠናከር በማድረግ ሠራተኞችን አደራጀተው የተሠራውን መንበረ ጵጵስና ከተለያዩ ቦታ የተጠሩ እንግዶች በተገኙበት መርቀው ሀገረ ስብከቱ በይፋ የመንበረ ጵጵስና ቢሮ አንዲኖረው አድርገዋል፡፡
ብፁዕነታቸው ወደ ደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተመድበው ሲሄዱ ጥንታዊና ታሪካዊ የሆነው የተክሌ ምስክር አቋቋም ጉባኤ ቤት ተዳክሞ ስለነበረ የምስክር አቋቋም ጉባኤ ቤቱን ከአካባቢው ተወላጆች ጋር በመመካከር በአዲስ መልክ በማቋቋም ጉባኤ ቤቱ እንዲጠናከር በማድርግና ዘመናዊ ጉባኤ ቤት በማሠራት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ (ዶክተር) አስመርቀው ለጉባኤ ቤቱ አድራሾች በጀት አስበጅተው እንዲጠናከር አድርገዋል፡፡ በ፳ ዓመታት የደቡብ ጎንደር ሊቀ ጵጵስና አገልግሎታቸው ውስጥ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር ቦታ ከመንግሥት በማስፈቀድ ፮፻፹፭ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት በሀገረ ስብከቱ እንዲተከሉ በማድረግ የቤተ ክርስቲያን ማስፋፋት ሥራ ሠርተዋል፡፡ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተተክለው ከቆዩት አብያተ ክርስቲያናት መካከል በደብርነት ያሳደጓቸው ከ፭፻ በላይ ሲሆኑ ወደ አንድነታቸው እንዲመለሱ ያደረጓቸው ገዳማትም ፲፪ ናቸው፡፡ ከእነዚህም በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል ጣና ቂርቆስ፤ጣራ ገዳም እና ምጽሌ ፋሲለደስ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡
ወደ ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ሲመደቡ የመጀመሪያ ሥራቸው የሀገረ ስብከቱን ሰላም ማስጠበቅ ነበር፡፡ ሠራተኛው ተግባብቶ ሥራውን እንዲሠራ የተለያዩ ሥራዎችንም ሠርተዋል፡፡ በዚህም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ «የሰላም አባት» የሚል የክብር ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱ በልማት ጠንክሮ አብያተ ክርስቲያናት ተስፋፍተው ማየት የሁልጊዜ ሕልማቸው ነው፡፡ሀገረ ስብከቱ የራሱ የሆነ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ኖሮት፤ ማኀበረ ካህናትንና ምእመናንን አሰባስቦ፤ ስለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን ልማት፤ ስለመልካም አስተዳደርና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ተሰባስቦ ለመወያየት የራሱ የሆነ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አልነበረውም፡፡ ለዚህም በመንበረ ጵጵስናው ግቢ ከሚገኘው ቦታ በስተደቡብ በኩል ዘመናዊ ቢሮ ያለው ሁለገብ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለመሥራት ራሳቸው አቅደው ሥራው እንዲጀመር በማድረግ የሕንፃ ማሰሪያ ገንዘቡን በተለያዩ ወረዳዎች ቆላ ደጋ ሳይሉ፤ አቀበት ቁልቁለት ሳይበግራቸው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር ገንዘብ በማሰባሰብ በተጨማሪም ከክህነትና ከንዋየ ቅድሳት መባረኪያ የሚገኘውን ገቢ በሙሉ ለሕንፃ ግንባታው ሥራ እንዲውል በመፍቀድ ከስድስት መቶ ሽህ ብር በላይ በብፁዕነታቸው ስም ተበርክቷል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ንብረት በሆነው በሐዋርያው ጳውሎስ ግቢ ባለ ፬ ፎቅ የገቢ ማስገኛ ሕንፃ ለመገንባትና ሌሎችንም ሥራዎች በግቢው ለመሥራት ዕቅድ አውጥተው የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ በድርቡሽ ወቅት ከጠፉት ከ፵፬ቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ፫ቱ ምዕት ቤተ ክርስቲያን በቦታው ለመመለስ ብፁዕነታቸው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው አዲስ ኮሚቴ በማቋቋም በከፍተኛ ጥረት ቀደም ሲል ከነበረበት ቦታ ላይ የ፫ቱ ምዕት ቤተ ክርስቲያን መቃረቢያ እንዲሠራ በማድረግ ታቦተ ሕጉ እንዲገባና ቀድሰው ቅዳሴ ቤቱን አክብረው ታሪክ እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ከ፭፻ በላይ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተክሉ በማድረግ ምእመናን እንዲበዙና ቤተ ክርስቲያን እንድትስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርከተዋል፡፡ በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ ገዳም በበቅሎ በመሄድም አዲስ ገዳም እንዲመሠረት አድርገዋል፡፡ በተለይ ለሀገረ ስብከቱ ካቀዷቸው እቅዶች መካከል፤ በመንበረ ጵጵስናው ግቢ በስተምስራቅ በኩል የሀገረ ስብከቱ ንብረት የሆነ ፬ ክፍል ቤት ተሠርቶበት ከሚገኘው ቦታ ላይ ባለ ፬ ፎቅ ሕንፃ በመሥራት ለገቢ ማስገኛ አገልግሎት እንዲውል አቅደዋል፡፡ ይህን ሥራና ሌሎችንም ባቀዱት መሠረት ለማስፈጸም ደፋ ቀና ሲሉ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት የግልና የጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ሕመሙ ሊሻላቸው ባለመቻሉ በተወለዱ በ፹፬ ዓመታቸው ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. ዐርፈዋል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የመንግሥት ተወካዮች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያኑ በተገኙበት በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዲዎስ ቤተ ክርስቲያን ግንቦት ፳ ይፈጸማል፡፡
ጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው ከጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የመንበረ ፓትርያርኩን አጠቃላይ ሰበካ መንሳዊ ጉባኤና ዓመታዊውን የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ለ15 ቀናት ሲያካሒድ ሰንብቷል፡፡
በዚሁ መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻውን ሥርዓተ ጸሎት ካደረሰ በኋላ ወሳኝ በሆኑ የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡
ስለዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉር የነፃነት ምልክት እንደሆነች ሁሉ የሰላምና የጸጥታም ምልክት መሆን አለባት፤ ከዚህ አንፃር ሰሞኑን በተለያየ ምክንያት በወገኖቻችን መካከል የተከሰተው ግጭት ተወግዶ ሙሉ ሰላምን የማስፈኑ ሥርዓት ተፋጥኖ እንዲረጋገጥ፣ ከዚህም ጋር በግጭቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖቻችን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ባለው መዋቅር ብር 6,000,000 (ስድስት ሚሊዮን) የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ፡፡ እንዲሁም ከጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ አገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት ለሁለት ሱባዔ ማለትም ለ14 ቀናት ያህል ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
ምልዓተ ጉባኤው ከዚህ በላይ በተገለፁትና በሌሎችም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አስፈላጊውን መመሪያ ከሰጠ በኋላ ስበስባውን በጸሎት አጠናቆአል፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣
ለሕዝባችን ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 21 ቀን 2010 ዓ.ም.
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ