ተረት…………ተረት (ለህጻናት)

      ልጆች ዛሬ አንድ ተረት ይዤላችሁ ቀርቤአለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ ፀሐይና ነፋስ ረጅም መንገድ አብረው ጉዞ ጀመሩ፡፡ እነዚህ ጓደኛሞች አብረው እየሔዱ ጨዋታ አንስተው ሲያወሩ ነፋስ ፀሐይን አንድ ጥያቄ ጠየቃት «ሰዎች የምትፈልጊውን ነገር እንዲያደርጉልሽ የምታደርጊያቸው በምንድን ነው?» ሲል ነፋስ ጠየቃት ፀሐይም የነፋስን ጥያቄ ሰማችና «እኔማ ከሰዎች የምፈልገውን መጠየቅ ብፈልግ በጣም ቢቆጡ፣ ቢሳደቡ እንኳን ቀስ አድርጌ በትህትና በፍቅር ረጋ ብዬ እጠብቃቸውና የምፈልገውን እንዲሰጡኝ /እንዲያደርጉልኝ/ አደርጋለሁ» አለችው፡፡ ነፋስ ወዲያውኑ ቀበል አደረገና «በጣም ተሳሳትሽ የምን መለማመጥ? የምትፈልጊውን ለማግኘት በጉልበት መጠቀም ነው እንጂ» አለ፡፡ «ፀሐይ እንደሱማ አይቻልም» አለች፡፡

                    

      ነፋስም እኔ እችላለሁ ተመልከች «ያ» መንገድ ላይ የሚጓዘውን ሰውዬ በደቂቃ ውስጥ ልብሱን በየተራ ብትንትን አድርጌ አስወልቀዋለሁ» ሲል ፎከረ፡፡ ነፋስም በአንዴ ኃይሉን አነሣና የሰውየውን ልብስ ለማስወለቅ መታገል ጀመረ፡፡ ይኼኔ ሰውየው ልብሱን እንዳይወስድበት በኃይል ልብሱን ጭብጥ አድርጎ አስጣለ /አዳነ/፡፡ ነፋስም ሰውየው ስላሸነፈው ተናደደና አዋራ አስነሥቶ ሰውየው ዐይን ላይ በትኖበት ጥሎት ሔደ፡፡ ፀሐይም በመገረም እየተመለተችው እሺ አያ ንፋስ አሸንፈህ የፈለከውን አገኘህ)» ብላ ጠየቀችው ነፋስም «ይገርምሻል ልብሱን አልለቅም ሲለኝ አዋራ አንሥቼ ዐይኑ ላይ ጨመርኩበት» አላት፡፡

      ፀሐይ ሳቅ እያለች «አይ አያ ነፋስ፡፡ በትግል አልሆን ሲልህ በጉልበት ለመጠቀም ሞከርክ? ግን እንደዚህ አይደለም እኔን አስተውለህ ተመልከተኝ» አለችውና ልታሳየው ወደ ሰውየው ሔደች፡፡

      ሰፊ ከሆነው ከሰማይ መቀመጫዋ ብድግ አለችና ሰውየውን ገና ጠዋት ከሚመጣው ሙቀቷ ሰላምታ አቀረበችለት ሰውየውም የፀሐይን ሙሉ ፈገግታና ትህትና በጣም ደስ አሰኝቶት ከሙቀቷ ስር ቁጭ አለ፡፡ እንደገና ከሰዓት በኋላ መንገድ ሲሔድ ሰላም አለችውና ከሙቀቱ ጭምር አደረገች፡፡ «በጣም ስለሞቀህ ለምን ኮትህን አታወልቅም?» ስትል ጠየቀችው ደስ ብሎት ምንም ሳይከፋው ፈጠን ብሎ «እሺ» አለና ውልቅ አድርጎ ያዘው፣ አሁንም ሙቀቷን ጨመረችና «ሸሚዙን ብታወልቀው» አለችው አወለቀው ሙቀቷ በጣም እየጨመረ መጣ፡፡ «ለምን በቀዝቃዛ ውኃ አትታጠብም ስትል ቀስ አድርጋ ጠየቀችው በጣም ደስ ይለኛል አለና ሰውነቱን በቀዝቃዛ ውኃ አስነከረችው፡፡»

      ይሔኔ ነፋስ በጣም ደነቀው፡፡ በራሱ ኃይለኝነት በጣም አፈረ፡፡ ሰዎች ነፋስን ብርድ በመጣ ቁጥር የበለጠ እየፈሩት ወደ ሙቀት እንደሚሸሹት አወቀ፡፡ ፀሐይ ግን በትህትና በፍቅር ሰዎችን ስለምትቀርብ ወደ ቅዝቃዜ ብትወስዳቸው እንኳን ቅር አይላቸውም፡፡ በደስታ እንደሚከተሏት ተመለከተ፡፡ የፀሐይን ጥሩ ፀባይ በጣም አደነቀ፡፡

       አዎን ልጆች ከሰፈር አብሮ አደጎቻችሁ ከትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ እንዲሁም ከወላጆቻችሁ ጋር አብራችሁ ስትኖሩ የምትፈልጉትን ለማግኘት በመሳደብ፣ በኃይል፣ በመማታት አይደለም፡፡ ነፋስን አይታችኋል አይደል? ክፉና ኃይለኛ መሆን ሰዎች እንዲርቁን እንዲጠሉን አዋቂዎችም እንዲረግሙን ያደርገናል፡፡ እና ልጆች ልክ እንደ ፀሐይ ጥሩና ደግ ትሁትና ታዛዥ ሆናችሁ ሰዎትን ብትቀርቡ ሁሉም ይወዳችኋል፣ ይመርቃችኋል፡፡ እሺ ልጆች? ደኅና ሁኑ ልጆች ደኅና ሁኑ፡፡

የቤተልሔም እንስሳት(ለህጻናት)

        ልጆች ዛሬ ስለቤተልሔም እንስሳት ነው የምንጽፍላችሁ፡፡ ቤተልሔምን ታውቃላችሁ? ቤተልሔም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት ከተማ ናት፡፡ እና ልጆች የቤተልሔም እንስሳት የጌታችን መወለዱን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተደስተው «ምን ይዘን እንሒድ? ምንስ እናበርክት?» በማለት በሬዎች፣ በጎች፣ ጥጃዎች፣ አህያዎች ሌሎች እንስሳትም ተሰብስበው «ምን እናድርግ» እያሉ መወያየት ጀመሩ፡፡

ፀሐይ ልጆቿን ጨረቃንና ከዋክብትን ጠራቻቸውና

«ልጆቼ ሆይ ዛሬ ታላቅ ደስታ በኢየሩሳሌም ሀገር በቤተልሔም ከተማ ተፈጽሟል የዓለም ፈጣሪ ጌታችን ተወልዷልና ፍጥረታት ሁሉ በደስታ የምንሆንበት ቀን ነው፡፡ እና ልጆች የጥበብ ሰዎች /ሰብዓ ሰገል/ ጌታችን መወለዱን ሰምተው ከሩቅ ሀገር ተነሥተው መምጣት ፈልገዋልና ከእናንተ መሐከል ማነው ጎብዝ? እነዚያን የክብር እንግዶች ፈጥኖ ይዟቸው የሚመጣው?» ስትል ጠየቀቻቸው፡፡ ሁሉም «እኔ እኔ ካልተላኩ» ብለው ሲያስቸግሯት እናታቸው ፀሐይ ዕጣ አወጣች፡፡ ለአንዷ ኮከብ ወጣላት፣ ከደስታዋ ብዛት በሰፊው ሰማይ ላይ ክብልል ክብልል እያለች እየበረረች እንግዶች ዘንድ ደረሰች፡፡ እንግዶቹም ለታላቁ ጌታችን የምናበረክተው ብለው ዕጣን፣ወርቅ፣ከርቤ ይዘውለት ሲመጡ አገኘቻቸው፡፡ ኮከቧም በጣም ደስ አላትና ቦግ ብላ በራች፡፡ ወደ ቤተልሔም እየመራቻቸውም ሔደች፡፡

ጌታችን በተወለደባት ሌሊት በቤተልሔም ከተማ አካባቢ ከብቶቻቸውን ሲጠብቁ ያደሩ እረኞች ነበሩ፡፡ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፡፡ ወዲያውም ያሉበት ቦታ በብርሃን ተጥለቀለቀ በዚህ ጨለማ ምን ብርሃን ነው የምናየው ብለው ፈርተው ሊሸሹ ሲሉ የእግዚአብሔር መልአክ «አይዞአችሁ ልጆች እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁ፤አትፍሩ፡፡ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱ ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋል ይህም ምልክት ይሆንላችኋል ሕፃን ተጠቅልሎ ተኝቶ ታገኛላችሁ አላቸው፡፡ ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡ /ሉቃ.2፥8-20/፡፡ ልጆች ይገርማችኋል የዚያን ዕለት አበባዎች በደስታ አበቡ፣ ሣር ቅጠሎችም ለመለሙ፣ ንቦች ማራቸውን አበረከቱ፣ ላሞችም ወተታቸውን ሰጡ ሁሉም ያለውን ሰጠ፡፡ የቤተልሔም እንስሳት «እኛስ ምን እንስጥ?» እያሉ ግራ ገባቸው በመጨረሻም አህያ ከሁሉም የበለጠ ሐሳብ አመጣች «ግን ጌታችን በበረት ነው የተወለደው አይደል?» ስትል ጠየቀቻቸው «አዎን» አሏት «ታዲያ እኮ ልብስ የለውም ደግሞም እንደምታዩት ጊዜው ብርድ የበዛበት ነው፡፡» አለች፡፡

«እና አህያ ምናችን ልብስ ይሆነዋል ብለሽ አሰብሽ?» አለች በግ፡፡ «ለምን ትንፋሻችንን አንሰጥም» አለች፡፡ ሁሉም በጣም ደስ አላቸው፡፡ ትንፋሻቸውን ሊያበረክቱለት ጌታችን ወደ ተወለደበት በረት እየሮጡ ሔዱ፡፡

ልጆች እናንተስ ለጌታችን ልደት ወደ ቤተክርስቲያን ምን ይዛችሁ ልትሔዱ አሰባችሁ? ሻማ፣ ጧፍ ልትሰጡ አሰባችሁ? ጎበዞች! ልጆች እናንተም መባ ሰጥቶ መመለስ ብቻ ሳይሆን ቅዱስ ቁርባንን ተቀብላችሁ መምጣት አለባችሁ፡፡ እንደ ቤቴልሔም ልጆች /እረኞች/ እየዘመራችሁ የጌታችንን ልደት አክብሩ እሺ? በሉ፤ ደኅና ሁኑ ልጆች፡፡

ብስራት

እመቤት ፈለገ

በመጋቢት 29 ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተመቅደስ ውስጥ ሆና ስትጸልይ በጣም የሚንፀባርቅ ታላቅ ብርሃን ሆነ፤ ወዲያው እጅግ የሚያምር ስሙም ገብርኤል የተባለ መልአክ አየች፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም በማመስገን ሰላምታ አቀረበላትና ‹‹ከሴቶች የተለየሽ ጸጋን የተመላሽ ደስተኛይቱ ሆይ እግዚአብሔር ካንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ›› አላት፡፡

 

እመቤታችን ድንግል ማርያምም ከንግግሩ የተነሳ ደነገጠችና ‹‹እንዴት እንዲህ ባለ ቃል ታመሰግነኛለህ›› አለችው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ደስ በሚያሰኝ ቃል እመቤታችንን አረጋጋትና ‹‹እነሆ ታላቅ ልጅ ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹ይህ ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል›› አለችው፡፡ መልአኩም ‹‹እግዚአብሔር ማድረግ የማይችለው ምንም ነገር የለም፤ ዘመድሽ ኤልሳቤጥ እንኳን ካረጀች የመውለጃዋ ጊዜ ካለፈ በኋላ ጸነሰች፤ እንዲያውም ከጸነሰች ስድስት ወር ሆኖቷል፤ ስለዚህ አንቺም በድንግልና ትጸንሻለሽ፡፡›› አላት፡፡ እመቤታችንም ‹‹እኔ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነኝ ፤ እግዚአብሔር ያዘዘኝን ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ እንደ ቃልህ ይደረግልኝ›› አለችው ስለዚህም እመቤታችን የአምላክ እናት ሆነች፡፡

 

ልደተ ክርስቶስ /የገና በዐል/

በአዜብ ገብሩ

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ? ዛሬ ስለጌታችን አምላካችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት /ገና በዓል/ እንነግራችኋለን፡፡ በደንብ ተከታተሉን፡፡ እሺ?

 

ልጆች በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፡፡ አውግስጦስ ቄሳር የተባለ ንጉሥ ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ አዘዘ፡፡ በትእዛዙ መሠረትም ሰው ሁሉ ሊቆጠር ወደየትውልድ ከተማው ሄደ፡፡ ዮሴፍና እመቤታችንም ሊቆጠሩ ከናዝሬት ወደ ትውልድ ሥፍራቸው ወደ ቤተልሔም ሄዱ፡፡ በቤተልሔም ሳሉም እመቤታችን የምትወልድበት ቀን ደረሰ፡፡ በዚያ ሥፍራም ብዙ እንግዳ ስለነበር እነ ዮሴፍ የሚያርፉበት ቦታ አላገኙም ነበር፡፡ ማደርያም ስላልነበራቸው በከብቶች ማደርያ በበረት ውስጥ እመቤታችን ልጅዋን ወለደችው፡፡
 
በጨርቅ ጠቅልላ እዛው በበረት ውስጥ አስተኛችው፤ በዚያ ሀገር ይኖሩ የነበሩ እረኞችም ሌሊት ከብቶቻቸውን ይጠብቁ ነበር፤ የእግዚአብሔር መልአክም በእረኞቹ አጠገብ ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው በራ፤ በጣምም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው ‹‹እነሆ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምስራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ ‹‹እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት የሆነ ተወልዶላችኋል፡፡ ይኸውም ጌታ እና እግዚአብሔር የሆነ መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እናንተም ባገኛችሁት ጊዜ ምልክቱ እንዲህ ነው፡፡ ሕፃን በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ መላእክት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚህ እረኞች እርስ በርሳቸው ‹እስከ ቤተልሔም እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ አሉ፡፡ ፈጥነውም ሄዱ፡፡ ማርያምንና ዮሴፍን አገኙአቸው፡፡ ሕፃኑንም በበረት ውስጥ አገኙት፡፡ በአዩትም ጊዜ የነገሩአቸውን ሰምተው በጣም ተደነቁ፡፡ እረኞቹም እንደነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድርም ለሰው ልጆች በጎፈቃድ ሆነ›› ብለው እያመሰገኑና እያከበሩ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡ አያችሁ ልጆች እነዚህ ክርስቶስን ሊያዩ የመጡ ሰዎች ደስተኞች ነበሩ፤ ስለዚህ ልጆች እኛም በቤተ ክርስቲያን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት በደስታ ልናከብር ይገባናል፡፡ ከመላእክት ጋር ሆነንም ‹‹በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን›› እያልን እንዘምር፡፡ እንግዲህ ልጆች መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ እሺ፡፡

አሥሩ ትእዛዛት

  እመቤት ፈለገ
እግዚአብሔር አምላካችን እጅግ በጣም የሚወደን እና የሚያስብልን አባታችን ነው፡፡ እርሱ ደግሞ ሁሉንም የሚያውቅ ስለሆነ ለእኛ ምን እንደሚጠቅመን፤ምን እንደሚያስፈልገን፤ምን እንደሚጎዳን ሰለሚያውቅ አሥሩን ትእዛዛት ሰጠን፡፡

 እነዚህም፡-
          1.ከኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ
          2.የእግዚአብሔር አምላክህን ስም በከንቱ አትጥራ
          3.የሰንበትን ቀን አክብር
          4.አባትና እናትህን አክብር
          5.አትግደል
          6.አታመንዝር
          7.አትስረቅ
          8.በሐሰት አትመስክር
          9.የባልንጀራህን ቤት አትመኝ
         10.ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚሉት ናቸው፡፡

 

እነዚህ ትዕዛዞች ሁሉም ሰው እንዲያደርጋቸው ርህሩህ አባታችን እግዚአብሔር አዞናል፡፡ እነዚህ ትዕዛዞችን ከፈጸምን እግዚአብሔር ይወደናል፤በረከትም ይሰጠናል፡፡
ልጆች እግዚአብሄርን እንወደዋለን አይደል? እግዚአብሄርን መውደዳችን የሚታወቀው ደግሞ አድርጉ ያለንን ስናደርግ፤ አታድርጉ ያለንን ደግሞ የማናደርግ ከሆነ ነው፡፡ይህን ካደረግን እግዚአብሔር በእኛ ደስ ይለዋል፤ ይባርከናል፤የሚያስፈልገንን ሁሉ ይሰጠናል፡፡ እነዚህ ትዕዛዛት ካልፈጸምን  ግን እግዚአብሔር ያዝንብናል፤ ከደጉ አምላካችንም እንለያያለን፡፡ ከአምላካችን ከተለየን ደግሞ ጥሩ ነገር አይኖረንም፡፡ ስለዚህ ልጆች እነዚህን ትእዛዛት ልንፈጽማቸው ስለሚገባ እያንዳዳቸውን በዝርዝር በሌላ ቀን እናያቸዋለን፡፡

በሌላ ቀን አሥሩን ትዛዛት በዝርዝር እስከምናያቸው ድረስ እናንተ በቃላችሁ ይዛችሁ ለእማማ፤ ለአባባ እና ለጓደኞቻችሁ ንገሯቸው፡፡
                                                                                  

Silestu Dekik.jpg

ሠለስቱ ደቂቅ

በአዜብ ገብሩ
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች?ደህና ናችሁ ልጆች? ዛሬ ስለ ሦስቱ ህጻናት ታሪክ እንነግራችኋለሁን በደንብ ተከታተሉን እሺ፡፡
 

በአንድ ወቅት በባቢሎን ከተማ የሚኖር ናቡከደነፆር የሚባል ንጉሥ ነበር፡፡ይህም ንጉሥ ከወርቅ የተሰራ ትልቅ ጣኦት አሠርቶ አቆመ፡፡ ሕዝቡንም ሁሉ ሰበሰበና ለጣኦቱ እንዲሰግዱ አዘዘ፡፡ ለጣኦት ያልሰገደ ግን በእሳት ውስጥ ይጣላል ብሎ አዋጅ አስነገረ፡፡

Silestu Dekik.jpg
 
ከሕዝቡም መካከል ሚሳቅ፤ሲድራቅ እና አብደናጎም የተባሉት ህፃናት ግን ለጣኦቱ አንሰግድም አሉ፡፡ምክንያቱም እግዚአብሔርን ስለሚወዱ ለእርሱ ስለሚገዙ ነው፡፡ንጉሡ እነዚህን ህጻናት ለጣኦቱ አንሰግድም በማለታቸው በጣም ተቆጣ፡፡ካልሰገዱም ወደ እሳት እንደሚጣሉ ነገራቸው፡፡ህጻናቱም የሚያመልኩት አምላክ በሰማይ እንዳለና እርሱም ከእሳቱ እንደሚያድናቸው ነገሩት፡፡እንዲህም ሲሉ ወደ እግዚአብሔር ጸለዩ ‹‹አንተ ከእኛ ጋር ነህና ክፉውን አንፈራም››። ንጉሡም በመለሱለት መልስ ይበልጥ ተቆጣ፡፡ እሳቱንም ይነድ ከነበርው ሰባት እጥፍ እንዲያነዱትና ወደ እሳቱ ውስጥ እንዲጥሏቸው አዘዘ፡፡
ሲድራቅ ሚሳቅና አብደናጎም ግን እሳቱ አላቃጠላቸውም ነበር፡፡ በእሳት ውስጥ ሆነው እግዚአሔርን በመዝሙር እያመሰግኑ ነበር፡፡ከእነርሱም ጋር ሌላ አራተኛ ሰው ይታይ ነበር፡፡ እርሱም ከእሳቱ ሊያድናቸው  ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከው መልአክ  ቅዱስ ገብርኤል ነበር፡፡ በእሳቱ ውስጥ ሆነው መዝሙር ሲዘምሩ ንጉሡ በጣም ተገረመ ከእሳቱ እንዲያወጧቸው አዘዘ። ከፀጉራቸው አንዲቷ እንኳን ሳትቃጠል በሰላም ከእሳቱ ወጡ፡፡ንጉሡም ባየው ተዓምር ተደንቆ የእነርሱን አምላክ አመለከ በፊታቸውም ለእግዚአብሔር ሰገደ።
አያችሁ ልጆች እነዚህ ሦስቱ ህጻናት  ጎበዞች ናቸው፤ አምላካቸው እንደሚያድናቸው በሁሉም ቦታ ቢሄዱ ከእነርሱ ጋር እንደሆነ ስለሚያምኑ እሳቱን አልፈሩም፡፡እግዚአባሔርም ስለእምነታቸው እሳቱን አቀዘቀዘው፡፡በሰላም ከእሳቱም አወጣቸው፡፡

ክፉ ለሚያደርጉባችሁ ሰዎች መልካምን አድርጉ::

በአዜብ ገብሩ

በአንድ ወቅት ሳኦል የሚባል የእስራኤላውያን ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ንጉስ በዳዊት ላይ እጅግ ይቀናበት ነበር፡፡ ምክንያቱም ዳዊት ፍልስጤማዊው ጎልያድን ስላሸነፈ እስራኤላውያን በጣም ወደውት ነበር፡፡ ታዋቂም ሆኖ ነበር፡፡ ሳኦልም እግዚአብሔር እርሱን ትቶ ከዳዊት ጋር እንደሆነ ማሰብ ጀመረ፡፡ ስለዚህ በተለያየ ጊዜ ዳዊትን ለመግደል ሙከራ ያደርግ ነበር፡፡

 

አንድ ጊዜ ሳኦል የጦር ሰራዊቱን አስከትሎ ዳዊትን ለመግደል ፍለጋ ጀመረ ሳኦል ሳያውቅ ዳዊት ከሰራዊቶቹ ጋር የሚተኛበትና የሚሸሸግበት ዋሻ ስር ተኛ፡፡ ዳዊት ግን በዋሻው ውስጥ ተደብቆ ነበር፡፡ ሳኦልንም አየው፤ ልጆች እናንተ ዳዊትን ብትሆኑ ምን ታደርጉ ነበር? ዳዊት ግን ሳኦልን ሳይገድለው በተኛበት የልብሱን ጫፍ ቆርጦ ወሰደ፡፡ ሳኦልም ከእንቅልፉ ሲነቃ በተኛበት ጊዜ የተፈጠረውን ነገር ምንም አላወቀም፡፡ ዳዊትም ከኋላው ልብሱን እንደቆረጠበት ነገረው፡፡ ሳኦልም አለቀሰ፤ እጅግም አዘነ፡፡ ምክንያቱም ዳዊት እርሱን መግደል ሲችል ስላልገደለው ነው፡፡ ለዳዊትም እንዲህ አለው ‹‹ከእኔ ይልቅ አንተ ፃድቅ ነህ፤ እኔ ክፉ ሳደርግብህ አንተ ግን ክፉ አላደረግህብኝም፤ ስለዚህ ለእኔ ስላደረግኸው ቸርነት እግዚአብሔር መልካሙን ይመልስልህ’’ አለው:: ከዚህም በኋላ ሳኦልና ዳዊት ይቅር ተባባሉ፡፡

አያችሁ ልጆች እኛም ልክ እንደ ዳዊት የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን ሁሉንም ሰው መውደድ አለብን፡፡ ክፉ ያደረጉብንን፣ የማይወዱንንና ሊጎዱን ያሰቡ ሰዎች ይቅር ማለት አለብን አንድ ሰው ክፉ ሲያደርግብንም እኛ ግን ያንን ሰው ይቅር ልንለውና ልንወደው ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን ሰዎችን የምንወድና ለሰዎች የምንራራ መሆን አለብን፡፡

ለቅዱስ ቁርባን ስለ መዘጋጀት

                                                                                   በአዜብ ገብሩ
ልጆች ዛሬ ቅዳሴ ስናስቀድስ ወደ ቤተክርስቲያን ስንመጣ ምን ማድረግ እንዳለብን እነግራችኋለሁ፡፡
በቤተክርስቲያን ጸሎት እናደርጋለን፣ እንቆርባለን፣ ትምህርት እንማራለን፡ስናስቀድስ ከእግዚአብሔር፣ከመላእክት እና ከቅዱሳን ጋር ሰለምንገናኝ ማስቀደስ በጣም ደስ ይላል፡፡

ልጆች ልንቆርብ ስንል ምን ማድረግ እንዳለብን ታውቃላችሁ? የሠራነው ኃጢአት ካለ ለእግዚአብሔር እና ለንስሐ አባታችን መናገር አለብን፡፡ የተጣላነው ሰው ካለ ይቅርታ መጠየቅ፣ ውሸት አለመዋሸት አለብን፡፡ ሌላው ልጆች ገላችንን መታጠብና ንጹሕ የሆነ ልብስ መልበስ አለብን፡፡

ምክንያቱም ከሁሉም በላይ የሆነውን የአምላክ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ልንቀበል ስለሆነ ነው፡፡ ንጹሕ የሆነውን ልብሳችሁን ከለበሳችሁ በኋላ ቅዳሴ ከመጀመሩ በፊት በቤተክርስቲያን መገኘት አለባችሁ፡፡ ይህንንም ለወላጆቻችሁ ነግራችሁ በጊዜ ይዘዋችሁ እንዲመጡ አድርጉ፡፡ በቅዳሴ ጊዜም እግዚአብሔር የማይወደውን ወሬ ማውራት ስለማይፈቀድ ይህን ማድረግ የለባችሁም ዝም ብላችሁ ቅዳሴውን መከታተል አለባችሁ፡፡ ከጎናችሁ የቆሙ ሕፃናትም ሲያወሩ ካያችሁ ክቡር በሆነው በእግዚአብሔር ቤት እንዳሉ ልትነግሯቸው ይገባል፡፡

የቅዳሴ ሥርዓት እና ምንባብ ያለበት መጽሐፍ ይዛችሁ ጸሎቱን በደንብ መከታተል አለባችሁ፡፡ልትቆርቡም ስትሉ ከጎናችሁ ካለው ልጅ ጋር መጋፋት መሰዳደብና መጣላት አይገባም፤ ተራችሁን በትህትና ቆማችሁ መጠበቅ አለባችሁ፡፡ ከቆረባችሁ በኋላ የቅዳሴ ጸበል ጠጡ፡፡ ቆሻሻ የሆነ ነገር ወደ አፋችሁ እንዳይገባ፣ከአፋችሁ እና ከአፍንጫችሁም ምንም ዓይነት ነገር እንዳይወጣ አፋችሁን በነጠላችሁ ሸፍኑ፡፡ ቅዳሴው አልቆ ዲያቆኑ በሰላም ወደየቤታችሁ ግቡ ብሎ እስኪያሰናብት ድረስ በቤተክርስቲያን ቆዩ፤ቅዳሴው ሲጠናቀቅም እግዚአብሔርን አመስግናችሁ በመንገድ እንቅፋት እንዳይመታችሁ እየተጠነቀቃችሁ ከወላጆቻችሁ ጋር ወደየቤታችሁ ሂዱ፡፡

እኛ ቤተ ክርስቲያን ሄደን ስንቆርብ ጌታችንም ከእኛ ጋር ወደ ቤታችን ይመጣል፤በዚህም ምክንያት ቤታችን ይገባል፤ቤታችንንም ይባርክልናል፡፡

ስለ እመቤታችን ቤተመቅደስ መግባት

እህተ ፍሬስብሃት

 

ኢያቄምና ሐና የሚባሉ በተቀደሰ ትዳር የሚኖሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ነበሩ፡፡ ሁለቱም እግዚአብሔርን የሚወዱ ደግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሐና ልጅ መውለድ አትችልም ነበር፡፡ ልጅም ስለሌላቸው በጣም አዝነው ይኖሩ ነበር፡፡ ሁልጊዜ ወደ ቤተ እግዚአብሔር እየሄዱ ልጅ እንዲሰጣቸው ልመና ያቀርቡ ነበር፡፡ ለእግዚአብሔርም ልጅ ከሰጠኸን ለአንተ ብጽአት (ስጦታ) አድርገን እንሰጣለን ብለው ተሳሉ፡፡

 

እግዚአብሔርም ልጅ ሰጣቸው፡፡ ሐናም በግንቦት አንድ ቀን ከፀሐይ የምታበራ ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ሕፃኗንም ማርያም ብለው ስም አወጡላት፡፡ ልጃቸው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በንጽህና ሲያሳድጉ 3 ዓመት ከሆናት በኋላ በተሳሉት ስእለት መሠረት ወደ ቤተ እግዚአብሔር መውሰድ እንዳለባቸው ተነጋገሩ፡፡ ለመንገድ የሚሆን ስንቅና ለቤተ እግዚአብሔር የሚሆን ስጦታ ሁሉ አዘጋጁ፡፡ 
 

ከዚያም ልጃቸውን ድንግል ማርያምን ይዘው ወደ ቤተመቅደስ ሄዱ፡፡በቤተ መቅደስ የካህናት አለቃ የነበረው ካህኑ ዘካርያስ ተቀበላቸው፡፡ሐና እና ኢያቄም ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል የተደረገላቸውንም ድንቅ ተአምር ነገሩት፡፡
 
ካህኑ ዘካርያስም ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል ባለመርሳታቸው እጅግ ተደሰተ፡፡ ነገር ግን ወዲያው አንድ ነገር አሳሰበው፡፡ምን መሰላችሁ ልጆች እመቤታችንን በዚያ በቤተመቅደስ ስትኖር ማን ይመግባታል ብሎ ነበር የተጨነቀው፡፡ 
 
ወዲያው ከሰማይ ቅዱስ ፋኑኤለ የተባለው መልአክ መጣ መልአኩ እመቤታችን አቅፎ በአንድ ክንፉ ከልሎአት ከሰማይ ያመጣውን ኅብስት እና መጠጥ መግቦአት እንደመጣው ሁሉ ወደ ሰማይ አረገ፡፡ካህኑ ዘካርያስና ህዝቡም እግዚአብሔር ምግቧን እና መጠጧን እንዳዘጋጀላት ተመለከቱ፡፡ካህኑ ዘካርያስ በፍፁም ደስታ እመቤታችንን ተቀብሎ ወደ ቤተ መቅደስ አሥገባት ይህ ዕለት ታኅሳስ 3 ቀን ሲሆን በዓታ ለማርያም ተብሎ በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡

 

ልጆች እኛም በዓሉን በማክበር ከእመቤታችን በረከትን ማግኘት አለብን፡፡

ታቦት

እህተ ፍሬስብሐት

 ልጆች ታቦት ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?

ልጆች ታቦት ማለት የእግዚአብሔር ትዕዛዝ የተፃፈበት ቅዱስ ሰሌዳ ማለት ነው፡፡ በመጀመሪያ ታቦትን ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበለው ሙሴ ነበር።

እስራኤላውያን በግብፅ በስደት ከኖሩ በኋላ በሙሴ መሪነት ወደ ሀገራቸው ወደ እስራኤል ጉዞ ጀመሩ፡፡ ብዙ ቀናቶችን ከተጓዙ በኋላ እረፍት አድርገው እግዚአብሔር ሙሴን ሲና  ወደተባለው ተራራ እንዲወጣ አዘው፡፡ ሙሴም ወንድሙ አሮን ህዝቡን እንዲጠብቅ አድርጎ ወደ ተራራው ወጣ፡፡ በተራራውም ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት ከፆመ በኋላ ከእግዚአብሔር እጅ ሁለቱን ታቦቶች ተቀበለ፡፡ በታቦቱ ላይም አስር የእግዚአብሔር ትዕዛዞች ተፅፈውበታል፡፡ እግዚአብሔር ታቦትን የሰጠበት ምክንያት ሌሎች ህዝቦች ጣኦትን ያመልኩ ስለነበር እስራኤላውያን ግን እግዚአብሔርን ስለሚያምኑ ሌሎች ህዝቦችን አይተው ጣኦት እንዳያመልኩ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን ታቦት እንዲያመልኩ ታቦትን ለሙሴ ሰጠው፡፡

ሙሴ ከሲና ተራራ ታቦታቱን ይዞ እስከሚመለስ እስራኤላውያኑ 40 ቀን መታገስ አቅቷቸው አሮንን አስገድደው ጣዖት ሠርተው ሲሰግዱ አገኛቸው። በዚህ ጊዜ ሙሴ ህዝቡ እግዚአብሔርን ትተው ጣኦትን በማምለካቸው በጣም ስለተናደደ ታቦቶቹን በጣኦቱ ላይ ጣላቸው እና ታቦቱም ጣኦቱም ተሰባበሩ፡፡ ሙሴ ታቦቶች በመሰባበራቸው በጣም አዘነ፡፡ እግዚአብሔርም የሙሴን ማዘን ተመልክቶ “የሰበርካቸውን አስመስለህ አንተ ራስህ ስራ እኔም እባርክልሃሁ” አለው፡፡ ሙሴም እንደታዘዘው ቅርፁን ከሰራ በኋላ እግዚአብሔርም እንደገና አስሩ ትዕዛዞችን በጣቶቹ ፃፈበት እና ባረከለት፡፡

ልጆች በሌላ ቀን ደግሞ የእግዚአብሔር አስሩ ትዕዛዞች ምን እንደሆነ እንነግራቹሀለን፡፡