ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ

 
ዲያቆን ታደሰ ወርቁ
 
እነዚህ ሁለት ቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አዕማድ ናቸው፡፡ በመሠረትነት በአጸኗት ቤተክርስቲያን ያላቸው የክብር ሥፍራ ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም፡፡ ለቤተክርስቲያንና በቤተክርስቲያን የፈጸሙት አገልግሎት በዚህም የተቀበሉት ሰማዕትነት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን መልካም የሆነውን ታሪካቸውን ለእኛ አርአያነት በሚሆን መልኩ ከትበውልናል፡፡ እኛም ለአርአርያነት በሚሆን መልኩ የእነዚህን ደጋግ ሁለት ቅዱሳን አባቶች ታሪክ፣ ዕውቀትና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ከዚህ በመቀጠል አቅርበናል፡፡
 
 
1. ሁለቱ ሐዋርያት ሲጠሩ የነበሩበት ሕይወት
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ዳር በምትገኘው በቤተ ሳይዳ ሲወለድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በጠርሴስ ከተማ ተወለደ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር በገሊላ ባሕር ዓሣ ማሥገር ጀመረ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በ 15 ዓመት ዕድሜው በገማልያ ትምህርት ቤት በመግባት የአይሁድን ሕግና ሥርዓት ተምሯል፡፡ በ30 ዓመቱም የአይሁድ ሸንጎ አባል ሆኗል፡፡ /1ቆሮ.1.17፤ሐዋ.22.3/
 
ቅዱስ ጴጥሮስ ባለትዳር ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በድንግልና የኖረ አባት ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕጋዊ /ባለ ትዳር/ ሆኖ ይኖር እንደነበር በማቴዎስ ወንጌል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጴጥሮስን አማት ማዳኑ መጠቀሱ አመላካች ሲሆን ጳዉሎስ ድንግል ስለመሆኑ ደግሞ ራሱ ለቆሮንቶስ ምእመናን በጻፈው ላይ ያረጋገጠው ነው፡፡ /ማቴ.8.14-15፣ 1ቆሮ.7.8፣9.5/  ይህም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያገቡትንም ሆነ በድንግልና የሚኖሩትን ለአገልግሎት እንደሚቀበል አመላካች መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
 
2. የሁለቱ ሐዋርያት ተክለ ቁመና
 
ቅዱስ ጴጥሮስ ፊቱ ሰፋ ያለ ሲሆን መካከለኛ ቁመት የነበረው፤ ራሰ በራ ሰው ነው፡፡ በማናቸውም ነገር ፈጣንና ቀልጣፋ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ ጭንቅላቱ ትልቅ ሲሆን ራሰ በራ ነበር፡፡ የሁለቱም ቅንድቦቹ ጠጉር የተጋጠሙ፤ ዓይኖቹ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ሲሆኑ ዘወትር ብሩሃን ነበሩ፡፡ አፍንጫው ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ጽሕሙና ሪዙም ረጃጅም ናቸው፡፡ አንገቱ አጠር ያለ ሆኖ ትከሻው ክብና ጎባባ፤ ቁመቱም አጠር ያለ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ /ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ ገጽ. 65 እና 125/
 
3.የእግዚአብሔር ጥሪ እና የሁለቱ ሐዋርያት መልስ
 
እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ዘር በሙሉ ለቅድስና፣ ለምግባር፣ ለትሩፋትና ለሰማዕትነት በተለያዩ ዘመናት ጠርቷል፡፡ ጥሪውን አድምጠው የተጠሩበትን ዓላማ ተረድተው፤ እንደ እርሱ ፈቃድ የተጓዙ ጥቂቶች ናቸው፡፡ /ማቴ.22.14/ ከጥቂቶቹም መካከል ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳዉሎስ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
 
እነዚህ ሁለት የቤተክርስቲያን ፈርጥ የሆኑ ሐዋርያት ለአገልግሎት የተጠሩበት መንገድ ለየቅል ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር በገሊላ ባሕር ልዩ ስሟ ጌንሴሬጥ በምትባል መንደር ዓሣ ያሠግሩ ነበር፡፡ በዚህን ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ፡፡» በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ከወንድሙ ጋር   ጠራው፡፡ /ማቴ.4.18/ በዚህ ጥሪ መሠረትም መተዳደሪያው የነበረውን መረቡንና ታንኳውን እንዲሁም አባቱን ትቶ ጌታውን ተከተለ፡፡ ለሐዋርያነት አገልግሎት ሲታጭ ዕድሜው 55 ዓመት እንደነበርም ይነገራል፡፡ /ዜና ሐዋርያት ገጽ. 3-15/
 
ምንም እንኳን ቅዱስ ጳዉሎስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር የተጠራበት የአገልግሎት ዓላማ አንድ ቢሆንም የተጠራበት መንገድ ከቅዱስ ጴጥሮስ በእጅጉ ይለያል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ጋር አልነበረም፤ ቀጥታ ከጌታም አልተማረም ነበር፡፡ በወቅቱ ግን በኢየሩሳሌም ስለነበረ የጌታን አገልግሎት ያውቅ ነበር፡፡ ለኦሪታዊ እምነቱ ቀናተኛ በመሆኑ ክርስቲያኖችን በማናቸውም አጋጣሚ ይቃወም ነበር፡፡ በ32 ዓመት ዕድሜውም ከኢየሩሳሌም ሁለት መቶ ሃያ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት በስተሰሜን በኩል በምትገኘው የደማስቆ ከተማ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ሲሰማ፤ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ የሚያስችለውን የፈቃድ ደብዳቤ    ከባለሥልጣናቱ አገኘ፡፡
 
እርሱም ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ከተማ አመራ፡፡ በዚያም ከሰማይ ብርሃን ወረደ፡፡ የወረደውም የብርሃን ነጸብራቅ ቅዱስ ጳዉሎስን ከመሬት ላይ ጣለው፡፡ በብርሃኑ ውስጥም «ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛልህ)» የሚለውን አምላካዊ ድምፅ አሰማው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስም «ጌታ ሆይ ማን ነህ)» ብሎ ጠየቀ፡፡ ለጠየቀውም ጥያቄ «አንተ የምታሳድድኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፡፡» የሚል  መልስ አገኘ፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስም በወደቀበት ሆኖ እየተንቀጠቀጠ «ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ)» ሲል ከእርሱ    የሚጠበቀውን ግዴታውን ጠየቀ፡፡ ጌታም ተነሥቶ ወደ ደማስቆ እንዲገባና ማድረግ የሚገባውን ወደሚነግረው ወደ ካህኑ ሐናንያ ላከው፡፡ /የሐዋ.9.1/
 
ቅዱስ ጳዉሎስም በዚህ መልኩ የእግዚአብሔርን የአገልግሎት ጥሪ ተቀብሎ በካህኑ ሐናንያ እጅ   ተጠምቆ ወደ ሐዋርያነት ኅብረት ተቀላቀለ፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው ቅዱስ ጴጥሮስ የቀደመ ግብሩን እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ ጌታን እንደተከተለ ሁሉ ቅዱስ ጳውሎስም የቀደመ የጥፋት ግብሩን በመተው የጌታ ተከታይ የሆኑትን ወንድሞቹን ሐዋርያትን ተቀላቀለ፡፡ እንደ እነርሱም ለጌታ ጥሪ ተገቢውን መልስ ሰጠ፡፡
 
ቅዱስ ጳወሎስ የተጠራው ሦስት ጊዜ ነው፡፡ የተጠራው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ የእርሱ ጥሪ በአብ ስም የተከናወነው በእናቱ ማኅፀን ነው፡፡ ይህንንም ራሱ ቅዱስ ጳዉሎስ ሲገልጽ «ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ፤ በጸጋውም የጠራኝ፤ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ በእኔ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፤» በማለት ነው፡፡ በዚህም አብ እግዚአብሔር በሚለው አምላካዊ ስሙ እንዳጠራው በምስጢር እንረዳለን፡፡ /ገላ.1.15-16/ ሌላኛው ጥሪ ደግሞ በወልድ የተከናወነው ነው፡፡ አስቀድመን እንደገለጽነው እግዚአብሔር ወልድ በደማስቆ ጎዳና ላይ «ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ» ብሎ ከገሰጸው በኋላ ወደ ካህኑ ሐናንያ በላከው ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅትም ጌታ ቅዱስ ጳዉሎስን ለምን እንደመረጠው ለካህኑ ሐናንያም ሲያስረዳ «ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና፤» በማለት ነው፡፡ /የሐዋ.9.15/
 
ቅዱስ ጳዉሎስ ከአብና ከወልድ ባሻገር በመንፈስ ቅዱስም ለአገልግሎት የተመረጠ ነው፡፡ ይህም የሆነው መንፈስ ቅዱስ ለአባቶቻችን «በርናባስንና ሳዉልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ» /ሐዋ.13.21/ ባለበት ወቅት እና እንዲሁም «በዚያን ጊዜም ከጦሙ፤ ከጸለዩም፤ እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው፡፡ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሰሌውቅያ ወረዱ፤» በሚለው  አምላካዊ ቃል መሠረት ነው፡፡ /የሐዋ.13.3-4/ በመሆኑም የቅዱስ ጳዉሎስ መጠራት ከጥሪነት ባሻገር ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ነው፡፡ በእርሱ መመረጥ ውስጥ የቅድስት ሥላሴ ልዩ አንድነትና ሦስትነት ተገልጧል፤ /ተመስክሯል/፡፡
 
4. የአገልግሎት ምድባቸው
 
ግብረ ሐዋርያት የሚጀምረው በቅዱስ ጴጥሮስ ሥራ ሲሆን የምዕራፉም መጨረሻ የሚጠናቀቀው በቅዱስ ጳዉሎስ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቅዱስ ጴጥሮስ አይሁድን /የተገረዙትን/ በአባትነት እንዲጠብቅ ሲሾም በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ቅዱስ ጳዉሎስ አሕዛብን /ያልተገረዙትን/ እንዲጠብቅና እንዲያስተምር ተሹሞ ነበር፡፡ ስለዚህም ነገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ «… ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠኝ እዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንድሆን ለጴጥሮስ የሠራለት ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና፡፡» በማለት ነው የገለጸው፡፡/የሐዋ.2.7-9/
 
በዚሁ ምድባቸው መሠረት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም፣ በአንጾኪያ፣ በይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም በስደት ላሉ አይሁድ መንግሥተ እግዚአብሔርን ሲሰብክ ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በቆጵሮስ፣ በመቄዶንያ፣ በግሪክ፣ በተሰሎንቄ በፊልጵስዩስ፣ በቆሮንቶስ፣ በኤፌሶን፣ በሮምና በሌሎችም ቦታዎች ሰብኳል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ጳዉሎስ እነዚህን አካባቢዎችና በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩትን ሕዝብና አሕዛብ ተከፋፍለው ሲያስተምሩ የየራሳቸውን አካባቢያዊ ተጨባጭ ሁኔታ ይጠቀሙም ነበር፡፡
 
ቅዱስ ጴጥሮስ የአይሁድ መምህር እንደመሆኑ መጠን በስብከቱና በጻፈው መልእክቱ አዘውትሮ ከብሉይ ኪዳንና ከመዝሙረ ዳዊት የተለያዩ ጥቅሶችን ይጠቀም ነበር፡፡ ሐዋርያት በይሁዳ ምትክ ሌላ ሰው ለመምረጥ በተገናኙ ወቅት ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ስለ እርሱ በመዝሙር መጽሐፍ «መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን፤ የሚኖርባትም አይኑር፤ ደግሞም ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት ተብሎ ተጽፎአል፡፡» በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የተናገረውን ጠቅሶ ተናግሯል፡፡ /የሐዋ.1.20-22፣ መዝ.68.25፣ መዝ.108.8/
 
ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ ከወረደ በኋላ ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በምዕራፍ 2.2-32 ላይ የተናገረውን ጠቅሶ ጽፏል፡፡ ይኸውም «እግዚአብሔር ይላል- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፣ ሸማግሌዎቻችሁም ህልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ፡፡. .. » የሚለውን ነው፡፡ /የሐዋ.2.17-21/ እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ ቅዱስ ጴጥሮስ ከመዝሙረ ዳዊት ጠቅሶ ተናግሯል፡፡ ይኸውም «ዳዊትም ስለ እርሱ /ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ/ እንዲህ አለ- እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና፡፡ ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሴት አደረገ፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋው አደረ፡፡ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፣ ጻድቅህንም ጥፋትን ያይ ዘንድ አትሰጠውምና፡፡» የሚለውን በመዝሙር 15.8 የሚገኘውን ሲሆን፤ ይኽም በጌታ መፈጸሙን ለማረጋገጥ የጠቀሰው ነው፡፡
 
ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ጴጥሮስ ከብሉይ ኪዳን በመጥቀስ የተለያዩ ጥቅሶችን በሁለቱ መልእክታት ላይ ተጠቅሟል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክታቱ ውስጥ የብሉይ ኪዳን ጥቀሶችን እምብዛም አልጠቀሰም፡፡ ጠቀሰ ቢባል በዕብራውያን መልእክቱ ብቻ ነው፡፡ ይህ ከብሉይ ኪዳን ጥቅሶች መጥቀስና አለመጥቀስ የተከሰተው የትምህርታቸው የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑ ሕዝብና አሕዛብ አኳያ መሆኑንን ልብ ይሏል፡፡
 
5. ጌታ እና ሁለቱ ሐዋርያት
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያትና ከሰባ ሁለቱ አርድእት ወገን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ወገን መሆኑ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገናኝ አድርጎታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ጋር ኖሯል፤ በልቷል ጠጥቷል፡፡ እንዲሁም ከዘመነ ሥጋዌው እስከ ዕርገቱ አብሮት በመሆን የቃሉን ትምህርት እና ስብከቱን አድምጧል፤ የእጁን ተአምራት በዐይኑ ዐይቷል፡፡
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ግን ይህን ዕድል በወቅቱና በጊዜው እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ አላገኘም፡፡ እርሱ በዚያን ወቅት ቤተክርስቲያንን ያሳድድ ነበር፡፡ /1ጢሞ. 1.13/ በኋላ ግን ቅዱስ ጳዉሎስ በአሳዳጅነቱ አልቀጠለም፡፡ በዚህም ክርስቶስን አወቀው፤ በራእይም ተመልክቶት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጌታ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በአካል ባያገኘውም በደማስቆ በብርሃን አምሳል ተገልጦ አነጋግሮታል፡፡ /የሐዋ. 9.1/ በቆሮንቶስም በምሽት በራእይ ተገልጦለት አነጋግሮታል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ «ጌታም በራእይ ጳዉሎስን እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፤ ነገር ግን ተናገር፤ ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው፡፡» እንዲል፡፡ /የሐዋ.18.10/
 
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በአካለ ሥጋ አግኝቶት ቅዱስ ጳዉሎስን ባያነጋግረውም ከዚህም በተጨማሪ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ ጸሎት ሲያደርስ ተገልጦ አነጋግሮታል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ይኽን ሲገልጽ «ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለስሁ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፣ እርሱም ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፣ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት፡፡ … ሒድ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁ አለኝ፡፡» በማለት ነው፡፡ /የሐዋ.22.17-21/
 
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን ለአገልግሎት ከመረጠው በኋላ አብሮት ስላለ በየጊዜው ያበረታታው ነበር፡፡ እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስን በራእይ እየተገለጠለት ያጽናናው ያበረታውም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ጌታ በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ሌሊት በአጠገቡ ቆሞ «ጳዉሎስ ሆይ፣ በኢየሩሳሌም ለእኔ እንደመሰከርክ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሀል፤ አይዞህ» በማለት አዝዞታል፤ አጽናንቶታል፡፡/የሐዋ.23.11/
 
 
6. የጴጥሮስ እና የጳዉሎስ መልእክታት
 
እንግዲህ የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳዉሎስ ከጌታ ጋር ያላቸው ግንኙነት ይህን ይመስላል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ትምህርቱን፣ ምክሩንና ተግሣጹን ቀጥታ ያገኘ ቢሆንም ቅዱስ ጳዉሎስም የጌታ ትምህርቱ፣ ምክሩና ተግሣጹ አልቀረበትም፡፡ በዚሁ መሠረት የመልእክቶቻቸውንም ጭብጥ ከዚህ ዐውድ አኳያ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ የትምህርት ትኩረት አቅጣጫዎቻቸው ከምን አንፃር እንደሆነም ማስተዋል ይቻላል፡፡
 
በመሆኑም ቅዱስ ጴጥሮስም ሆነ ቅዱስ ጳዉሎስ የጻፉት ወንጌልን ሳይሆን መልእክታትን ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁለት መልእክታትን ሲጽፍ ቅዱስ ጳዉሎስ ዐሥራ አራት መልእክታትን ጽፏል፡፡ የአጻጻፍ ስልታቸውም ሆነ የትኩረት አቅጣጫቸው የራሱ የሆነ ዐውድ አለው፡፡ መልእክታቱንም ሲጽፉ ከየራሳቸው ዐውድ አኳያ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዶግማ በቅድስና ሕይወት ዙሪያ ሲያተኩር ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ከቅድስና ሕይወት ጎን ለጎን በዶግማና በነገረ እግዚአብሔር ላይ ያተኩራል፡፡
 
ይህን አተያይ ከቅዱስ ጴጥሮስ አኳያ ስንመለከት ራሱ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያ መልእክቱ እንደ አሠፈረው ነው፡፡ ይህም «እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡» ብሎ እንደጠቀሰው ነው፡፡ /1ጴጥ.1.15/ ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ይኽን ሲገልጽ «… በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ፡፡» በማለት ሲሆን በዚሁ ምዕራፍ ላይ «የእምነታቸውን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ…» እና «ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው)» በማለት ገልጾታል፡፡ /1ጴጥ.1.1-9፤ 4.18/
 
በሌላ መልኩ ደግሞ ከዚህ ከመልእክት የትኩረት አቅጣጫ አኳያ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ከሌሎች ጉዳዮች ይልቅ በመግለጽና በማብራራት የሚያተኩረው በነገረ እግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የእርሱ መልእክታት ስለ ጸጋ እግዚአብሔር፣ ስለ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካልነት፣ የክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል ስለሚገኝ ድኅነት፣ ስለ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን /ስለ ምስጢረ ክህነት፣ ቁርባን፣ ጥምቀት፣ ጋብቻ፣ ትንሣኤ ሙታን/ ያተኩራሉ፡፡ የእነዚህ ሁለት ሐዋርያት መልእክታት በአጭሩ በዚህ መልክ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡
 
7. ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳዉሎስ በጌታችን ስም ያደረጓቸው ተአምራት
 
እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በዘመናቸው ተአምራት ያደርጉ ነበር፡፡ ያደረጓቸውም ተአምራት ለክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ታላቅ አስተዋጽኦ ነበሯቸው፡፡  ሁለቱም በተአምራት ሙት አስነሥተዋል፤ ድውይ ፈውሰዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይኸውም ቅዱስ ጴጥሮስ ጣቢታ የተባለች በኢዮጴ የምትኖር አንዲት ሴትን ከሞት በተአምራት አስነሥቷል፡፡ ይህች ሴት ለሰው ሁሉ መልካም የምታደርግ፤ ምጽዋትን የምትሰጥ፣ ለተለያዩ ደሃ ሴቶች የሚሆኑ የተለያዩ አልባሳትን በመሥራት ትለግስም ነበር፡፡ ይህን ሁሉ መልካም ነገር የምትፈጽም ሴት ታማ ሞተች፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በተአምራት ከሞት አዳናት፡፡ /የሐዋ.9.36-40/
 
ቅዱስ ጳዉሎስም እንዲሁ የሚጠቀስ ተአምር አለው፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስም ቃለ እግዚአብሔርን እያስተማረ አውጤኩስ የተባለ አንድ ወጣት አንቀላፋ፡፡ በእንቅልፉም ክብደት ምክንያት ከተቀመጠበት ወድቆ ይሞታል፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስም ይህን ወጣት በተአምር ከሞት አስነሥቶታል፡፡ /የሐዋ.20.9-12/
 
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በልብሳቸውና በጥላቸው በተአምራት ሕሙማንን እየፈወሱ ሕመምተኞችንም የክርስቶስ የመንግሥቱ ዜጎች ያደርጉ ነበር፡፡ ተአምራቱም ችግረኞቹን ከችግራቸው ከማላቀቅ ባለፈ ለክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት እጅጉን ይጠቅም ነበር፡፡ /የሐዋ.5.15-16፤ 19.12/
 
 
ቅዱሰ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ በሮም ሰማዕትነት እንደተቀበሉ የሚያሳዩ
 
8. ሰማዕተ ጽድቅ ጴጥሮስ ወጳዉሎስ
 
የቤተክርስቲያን ጉዞ ሁልጊዜ በመስቀል ላይ ነው፡፡ ይህ የመስቀል ጉዞ ደግሞ መሥዋዕትነትን /መከራ መቀበልን/ ይጠይቃል፡፡ ከዚህም የተነሣ በሰይፍ የተመተሩ፤ በመጋዝ የተተረተሩ፣ በእሳት የተቃጠሉ ለአናብስት የተጣሉ በአጠቃላይ በብዙ ስቃይ የተፈተኑ ቅዱሳን ሐዋርያት አሉ፡፡  ከእነዚህ ሐዋርያት ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሱት እነዚህ ሁለት ሐዋርያት ናቸው፡፡ «ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ፡፡» የሚለውን የጌታችንን ቃል መመሪያ አድርገው ለቤተክርስቲያን ሁሉን አድርገው፤ ሁሉን ሆነው የሰማዕትነትን ጽዋ ተቀብለዋል፡፡
 
ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስትና ሃይማኖት የአይሁድ መሪዎችንና ሊቃነ ካህናቱን ይሞግት፤ ከእነርሱም ፊት ምስክርነት ይሰጥ ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የአይሁድን ሊቃነ ካህናት «ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል» እያለ በሸንጎ ይሟገት ነበር፡፡ /የሐዋ.5.29/ በዚህም ብዙውን ጊዜ ይገረፍ ይታሰር ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስም የተለያዩ የመከራ ጽዋን ተቀብሏል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ እርሱና ሌሎች ሐዋርያት ስለክርስቶስ መከራ መቀበላቸውን ሲገልጽ «በሁሉ መከራ ስንቀበል አንጨነቅም፣ እንናቃለን አንዋረድም፤ እንሰደዳለን አንጣልም፤ እንጨነቃለን አንጠፋም፡፡» በማለት ነው፡፡ /2ቆሮ 4.8-11/ ከዚህም በተጨማሪ «በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣትም» በማለት የሰማዕትነት ሕይወቱን ገልጿል፡፡ /2ቆሮ.6.4-5፣ 1ቆሮ. 11.22-28/
 
በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ የደረሰበትን መከራ ሁሉ በዚህ መልኩ ገልጿል፡፡ እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በዚህ መልኩ ስለ ወንጌልና ስለክርስቶስ መከራ ከተቀበሉ በኋላ ከዚህ ምድር ያለፉት በሰማዕትነት ነው፡፡ ሁለቱም በሰማዕትነት ያለፉት በዘመነ ኔሮን ሐምሌ 5 ቀን 67 ዓ.ም ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ያረፈው የቁልቁሊት ተሰቅሎ ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ አንገቱን ተሠይፎ ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት ታላላቅ የጌታችን ሐዋርያት ረድኤት በረከት አማላጅነት ሁላችንንም አይለየን፤ አሜን፡፡
 
ዲያቆን ታደሰ ወርቁ
 
እነዚህ ሁለት ቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አዕማድ ናቸው፡፡ በመሠረትነት በአጸኗት ቤተክርስቲያን ያላቸው የክብር ሥፍራ ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም፡፡ ለቤተክርስቲያንና በቤተክርስቲያን የፈጸሙት አገልግሎት በዚህም የተቀበሉት ሰማዕትነት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን መልካም የሆነውን ታሪካቸውን ለእኛ አርአያነት በሚሆን መልኩ ከትበውልናል፡፡ እኛም ለአርአርያነት በሚሆን መልኩ የእነዚህን ደጋግ ሁለት ቅዱሳን አባቶች ታሪክ፣ ዕውቀትና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ከዚህ በመቀጠል አቅርበናል፡፡
 
 
 
 
 

 

 
 
 
 

 

ወርኃ ክረምት በቤተ ክርስቲያን ትምህርት (ዘመነ ክረምት)

ሐምሌ 4 ቀን 2004 ዓ.ም.

መብዐ ሥላሴ (ከጎላ ሚካኤል)

“ክረምት” የሚለው ቃል ከርመ፣ ከረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ወርሃ ዝናም፣ ወርኃ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር፣ ዘመነ ነጎድጓድ፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ… ማለት ነው፡፡(ጥዑመ ልሳን ካሳ ያሬድና ዜማው 1981 ዓ.ም ገጽ 53)

 

በዘመነ ክረምት ውኃ ይሰለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፡፡ ሆኖም ግን በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህ ዘመን ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት ዘመን ስለሆነ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡

 

ዘመነ ክረምት፡- የዝናም፣ የዘርና የአረም ወቅት በመሆኑ ምድር በጠል ዝናም ትረካለች፡፡ ዕፅዋት አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው  የሚያድጉበት፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ በሥነ ጽጌያት የምታሸበርቅበት፣ ወቅት ነው፡፡በመሆኑም በሃገራችን ብዙው የግብርና ሥራ የሚካሄደው በዚህ ጊዜ ነው፡፡

 

ወርኃ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፤ ገበሬ በወርሃ ክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሳል፡፡ ክርስቲያንም በዚህ ምድር ላይ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ይታገሳል፤ ክርስቲያንም በዚህ ምድር የሚደርስበትን መከራ ሁሉ በጸጋ የሚቀበለው በዚያኛው ዓለም ስለሚያገኘው ተድላና ደስታ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “እለ ይዘርኡ በአንብዕ ወበኃሤት የአርሩ፡፡ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ፡፡ ወፆሩ ዘርኦሙ፡፡ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ፡፡  በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ፡፡” በማለት የመንፈሳዊ ጉዞ ምሥጠርን ከግብርና ሙያ አንጻር አመልክቶአል፡፡(መዝ.125)

 

እግዚአብሔር ክረምትን ሲያመጣና ዝናምን ሲያዘንም ብዙ ነገሮችን ልናስተውል ይገባናል፡፡ ፈጣሪያችን ፈጣሪ ዓለማት ብቻ ሳይሆን መጋቢ ዓለማት መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ መግቦቱም ከፍጥረቱ እንዳልተለየ ይህ አማናዊ መግቦቱም ፍጥረቱን እንደሚያስተምር እንረዳለን፡፡ “በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፤ ብርድና ሙቀት፤ በጋና ክረምት፤ ቀንና ሌሊት አይቋረጡም፡፡” (ዘፍ.8፥22) በማለት አምላካችን እግዚአብሔር ለኖኅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በጋና ክረምቱ፤ ብርድና ሙቀቱ፤ ቀንና ሌሊቱ በተወሰነላቸው ጊዜ እየተፈራረቁ ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡

 

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያዊያን በአንድ ዓመት ውስጥ እየተፈራረቁ በሚመጡ አራት ወቅቶች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢርና ምሳሌ ጋር በማስማማት ለየወቅቱና ለዕለታቱ ምንባባትን በማዘጋጀት፣ ከሕብረተሰቡ ሥራና አኗኗር ጋር በማያያዝ እንዲሁም ከወቅታዊው አየር ጠባይ ጋር በማስማማት እያንዳንዳቸውን በ91 ቀን ከ15 ኬክሮስ (አንድ አራተኛ) በመክፈል ለወቅቶቹም ሥያሜ፣ ምሳሌ፣ ትርጉሙንና ምሥጢሩን በማዘጋጀት ትገለገልባቸዋለች፡፡

 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓመቱን የከፈለችባቸው ወቅቶች፡-

  1. ዘመነ መጸው (መከር) ከመስከረም 26 ቀን እስከ ታኅሣሥ 25
  2. ዘመነ ሐጋይ (በጋ) ከታኅሣሥ 26 ቀን እስከ መጋቢት 25
  3. ዘመነ ጸደይ (በልግ) ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25
  4. ዘመነ ክረምት ሰኔ 26ቀን እስከ መስከረም 25 ናቸው፡፡

 

ወቅቶችን እንዲህ በመከፋፈል በወቅቱ ከሚታየው የተፈጥሮ ሁኔታ ጋር ምእመናን ሕይወታቸውን እንዲመረምሩ ለንስሐ እንዲበቁ አጥብቃ ታስተምራለች፡፡ ያለንበት ወቅትም ክረምት በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት፤ ቅዱሳት መጻሕፍት አማካኝነት የሚሰጠውን ትምህርት በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡

 

ወርኃ ክረምት ከላይ በጥቂቱ እንደተመለከትነው በሦስት ንዑሳን ክፍላት ይከፈላሉ፡፡ እነኚህም፡-

1.    መነሻ ክረምት፡- የዝግጅት ወቅት

ሀ. ከበአተ ክረምት እስከ ሐምሌ ቂርቆስ(ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 19) ያለው ወቅት ነው፡፡  በዚህ ወቅት ዝናምና ደመና ምድርን የሚያለመልሙበት፣ ዘር የሚዘራበት ፣ የተዘራው የሚበቅልበት በፀሐይ ሐሩር የደረቁ ዛፎች ሁሉ የሚያቆጠቁጡበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘርዕን ደመናን ዝናምን የሚያዘክሩ  ምንባባት ይነበባሉ፣ መዝሙራትም ይዘመራሉ፡፡

 

ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ድምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌስሁ ነድያን፣ ይጸግቡ ርሁባን፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናም በዘነመ ጊዜ ችግረኞች ይደሰታሉ፤ ረሀብተኞችም ይጠግባሉ፡፡” በማለት በድጓው የዘመረው ይገኝበታል፡፡

 

ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፡፡ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፡፡ ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እምሕያው፡፡ ማለትም፡- ሰማዮችን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃልና፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም” በማለት የዘመረው ይሰበካል፡፡

 

በምንባበት በኩል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናም የምትጠጣ መሬት ለሚያርሷትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል ከእግዚአብሔር በረከት ታገኛለች፤ እሾህንና ኩርንችትን ግን ብታወጣ የተጣለች ናት፡፡ ለመረገምም ትቀርባለች፤ መጨረሻዋም መቃጠል ነው፡፡” በማለት ያስተማረው ትምህርት ይነበባል፡፡(ዕብ.6፥7-8)

 

ለ. ከሐምሌ ቂርቆስ እስከ ማኅበር (ከሐምሌ 19 እስከ ሐምሌ 29) መባርቅት የሚባርቁበት በባሕርና አፍላጋት የሚሞሉበት ምድር ጠል የምትጠግብበት ወቅት ነው፡፡ “ደመናት ድምፁን ሰጡ፣ ፍላጾችህም ወጡ የነጎድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበር፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ” ሲል ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ይሰበካል፡፡(መዝ.76፥18) ደመኖች ታይተው ባርቀው የነጎድጓድ ድምፅ እንዲሰማ ጌታችን ከዓለም ጠርቶ አስተምሮ ወንጌለ መንግሥት ተናግረው በኃጢአት ጨለማ የተያዘውን ዓለም በትምህርታቸው እንዲያበሩ የተላኩ የ72ቱ አርድዕት ዝክረ ነገር ይታወሳል፡፡(ሉቃ.10፥17-25)

 

መዝሙሩ፡- “ምድርኒ ርዕየቶ ወአኰተቶ ባህርኒ ሰገደት ሎቱ፤ ምድር አየችው አመሰገነችውም ባሕርም ሰገደችለት” /ድጓ/

“እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ በሰማይም በምድርም በባህርም በጥልቅም ቦታ ሁሉ”/መዝ.134፥6-7/

“ምድርን ጎበኘሃት አጠጣሃትም ብልፅግናዋንም እጅግ አበዛህ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተሞላ ነው ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፣ በዝናም ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳቱንም ከመዛግብቱ ያወጣል ” (መዝ.64፥9) በማለት እግዚአብሔር በነጎድጓድና በመብረቅ በባሕርና በሐይቅ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑንና የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡

ወንጌል፡- መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች (ማቴ.13፥47)

ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ፤ ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ፡፡ ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው፡፡(ማቴ.14፥26-27)

2.    ማዕከለ ክረምት

ሀ. ከማኅበር እስከ አብርሃም (ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 29)

ዘመነ ክረምት የሚጋመስበት ነው፡፡ ዝናብ ይቀንሳል፣ ምድሪቱም መቀዝቀዝና መጠንከር ትጀምራለች፡፡ “ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፤ ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት” እንዲሉ በክረምት ዝናሙን ተደብቀው የነበሩ አእዋፍ ከበአታቸው ይወጣሉ፤ ጥበበኛው ሰሎሞን አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማ ጊዜ ደረሰ፤ የቀረርቶውም ቃል በምድራችን ተሰማ (መኃ.2፥12) ሲል እነደተናገረው የአእዋፍ የምስጋና ድምፅ ይሰማል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም “የሁሉም ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፣ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ፣ አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” እያለች እንደ ቅዱስ ዳዊት ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ ምሕረቱም ለዘለዓለም የሆነውን የሰማይ አምላክ ታመስግናለች(መዝ.144፥15-20፣ መዝ 135፥25-26)

 

ለ. ዕጉለ ቋዓት፥ ደስያት

ይህ ክፍለ ክረምት ከነሐሴ 10 እስከ ነሐሴ 27 ቀን ድረስ ያሉት 17 ዕለታት የሚጠሩበት ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ክረምት ፍጥረታትና በባሕር የተከበቡ ደሴቶች የሚታወሱበት ሲሆን ወቅቱም ዕጓለ ቋዓት ደስያት ዐይነ ኩሉ ይባላል፡፡ ዕጓለ ቋዓት የሚለው ቃል ቁራን ሲያመለክት፣ ቁራ ሲወለድ ያለ ፀጉር በሥጋው ብቻ ይወለዳል፡፡ እናትና አባቱም እነርሱን ባለመምሰሉ ደንግጠው ይሸሻሉ፤ በዚህ ጊዜ የሚንከባከበው ሲያጣ እግዚአብሔር በረድኤት አፉን ከፍቶ ምግብ ሲሻ ተሐዋስያንን ብር ብር እየደረገ ከአፉ ያስገባለታል፡፡ “ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘብዙ፥ ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው? ” (ኢዮ.38፥41) ተብሎ እንደ ተገለጠው እግዚአብሔር የሰጠውን እየተመገበ ቆይቶ ሲጠነክር እንደ እናትና አባቱ ያለ ፀጉር ያወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ቀርበው ይንከባከቡታል፡፡ በሥነ ፍጥረት አቆጣጠር ግን በክንፍ የሚበሩ አዕዋፍን ሁሉ ይወክላል፡፡ ይህም አምላካችን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ የሚያስብ በመሆኑ ይህን ዘመን ርኅርሔ ለተመላው አምላክነቱ ሥራው መታሰቢያ እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን ዕጓለ ቋዓት በማለት ታስታውሰዋለች፡፡

 

ደስያት ማለት በውኃ የተከበቡ ቦታዎች ማለት ነው፡፡ እነዚህን ቦታዎች በውኃ እንዲሸፈኑ አድርጎ በውስጥቸው ያሉትን ሰዎች እንስሳት አራዊት አዕዋፍ ሁሉ የሚጠብቃቸው፣ በተስፋና በእምነት አበርትቶ የሚያኖራቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህን ድንቅ ሥራ ያዩ በውስጥ በውጭ ያሉት ሰዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ በደሴት (በቤተ ክርስቲያን) የተጠጉ ሁሉ ከሞተ ሥጋና ከሞተ ነፍስ ይጠበቃሉ፡፡

 

በዚህ ወቅት፡- ክፍለ ክረምቱ እንደተገባደደ፥ ውኃው እየጠራ፣ መሬቱ እየረጋ፣ ደመናውና ጉሙ እየተቃለለ፣ የወንዞች ሙላት እየቀነሰ፣ የክረምት ምግባቸውን ይዘው በየዋሻው የከረሙ ጭልፊቶችን አሞራዎች ድምፃቸውን እየሰሙ ምግብ ፍለጋ ሲወጡ የሚታዩበት ወቅት ነው፡፡

 

በተጨማሪም ከነሐሴ 27-29 ያለው ጊዜን “ሞተ አበው” በመባል ይታወቃል፡፡ ከ22ቱ አርዕስተ አበው የአብርሃም ይስሐቅና ያዕቆብ ቤተሰቦቻቸው ዕረፍት ይታሰባል፡፡ ቅዱስ መጽሐፋችንም “አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ሊሰዋ ወጣ፤ እግዚአብሔር ቤዛ አድርጎ ቀንዱ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ በግ አወረደለት” በማለት የአብርሃምን ታዛዥነት የይስሐቅን ቤዛነት ያወሳል፡፡ የተቀበሉትም ቃል ኪዳን “ወተዘከረ ሣህሎ ዘለዓለም ዘሠርዓ ለአብርሃም ወመሐለ ለይስሐቅ ወዐቀመ ስምዐ ለያዕቆብ ያርኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ እም ሰማይ ይሁብ ወእምድር በረከተ ያጸግብ ነፍስ ርኅብት” በማለት ይዘመራል፡፡

 

3.    ፀዓተ ክረምት (ዘመን መለወጫ)

ሀ. ከአብርሃም እስከ ዮሐንስ

ይህ ወቅት የዓመቱ መንገደኛ ነው፣ በሐምሌና በነሐሴ ደመና ተሸፍና የነበረችው ፀሐይ ፍንትው ብላ መውጫዋ የደረሰበት ጊዜ በመሆኑ ጎህ ጽባህ፣ መዓልተ ነግህ፣ ብርሃን ተብሎ የጠራል፡፡ የክረምቱ ጭፍን ጨለማ ሊያከትም ብርሃን ሊበራ የተቃረበበት መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ይበሰራል፡፡ በሊቀ መልእክት ቅዱስ ሩፋኤል እጅ የጦቢያን ዓይን እንዳበራ ፤ የምእመናን ዓይነ ልቡና እግዚአብሔር እንዲያበራ ይጸለያል፡፡

 

ከዚሁ ጋር የክረምቱ ደመና ዝናብና ቅዝቃዜ ውርጭ ጭቃው ከብዶባቸው የዘመን መለወጫን፣ የፀሐይ መውጫን ቀን በጉጉት ለሚጠባበቁ ምእመናን ልጆቿ ቅድስት ቤተ ከርስቲያን፡- “ነፍሳችሁን ተመልከቱ፥ ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ” ስትል ለበለጠ መንፈሳዊ ትጋት ታነቃቃቸዋለች፡፡ ክረምት ሲያልፍ የሰማዩ ዝናም የምድሩ ጭቃ ሊቀር እንሆ ሁሉ በዚህች ዓለም መከራ ተናዝዘው ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ክርስቶስ በክብር የሚገለጥበት ዓለም የምታልፍበት ዕለት ባላሰቧት ጊዜ እንደምትመጣ እንዲገነዘቡ ነገረ ምጽአቱን እንዲያሰቡ “ተዘጋጅታችሁ ኑሩ!” እያለች በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እንዲያብቡ “እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል… አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል” (መዝ.49፥2-3) እያለች ትመሰክራለች፡፡

 

ለ. ከዮሐንስ እስከ ዘካርያስ (መስከረም 8)

ዘመን መለወጫ አዲስ ተስፋ በምእመናን ልብ የሚለመለምበት ጊዜ ነው፡፡ የተተነበየው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባኤ ተፈጸመ፤ ከዘመነ ፍዳ ወደ ዘመነ ምሕረት የምትሸጋገሩበት ጊዜ ደረሰ፤ እያለ ያወጀው የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ዜና ሕይወት ይነገራል፡፡ “ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ፣ እውነት ከምድር በቀለች” (መዝ.88፥10-11) በማለት ስለ እውነት ሊመሰክር የወጣውን የቅዱስ ዮሐንስን ሕይወት በማውሳት ቤተ ክርስቲያን ልጇቿ እንደርሱ እውነተኞች እንዲሆኑ አርአያነቱን እንዲከተሉ ለእውነት እንዲተጉ ታስተምራለች፡፡ ሰማዩ፣ ውኃው የሚጠራበት ወቅት በመሆኑ በሥነ ፍጥረት በማመለከት ልጆቿን ከብልየት እንዲታደሱ፣ በመንፈስ እንዲጎለምሱ፣ከርኩሰት ከጣኦት አምልኮ፣ከቂም በቀል እንዲጠሩ እንዲነፁ “የአህዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” እያለች በሐዋርያው ቃል ታስተምረናለች፡፡(1ኛ ጴጥ.4፥3) ከዚሁ ጋር፡-በርኩሰት የተመላውን ሕይወታችንን ካለፈው ዘመን ጋር አሳልፈን የምድር አበቦች በጊዜው እነደሚያብቡ እኛም በምግባር በሃይማኖት እንድናብብ ትመክረናለች፡፡

 

ሐ. ከዘካርያስ እስከ ማግስተ ሕንፀት

ይህ ንዑስ ወቅት ዘመነ ፍሬ በመባል ይታወቃል፡፡ ከመስከረም 9 እስከ 16 ያሉትን ዕለታት በተለይ በሰኔና በሐምሌ የተዘራው ዘር ለፍሬ መብቃቱን የሚያስብበትና እንደ ቅዱስ ዳዊት “ምድር ፍሬዋን ሰጠች እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል”(መዝ.66፥6) ተብሎ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ሳምንት ነው፡፡ ፍሬውም ከቁር ከበረዶና ከትል ተርፎ ለጎተራ እንዲበቃ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ቅዳሴዋ “በእንተ ፍሬ ምድር ናስተበቊእ ከመ እግዚአብሔር ይሁብ ፍሬሃ ለምድር፣ ለዘርና ለመከር ሊሆን እግዚአብሔር ለምድር ፍሬዋን ይሰጣት ዘንድ ስለምድር ፍሬ እንማልዳለን” በማለት አምላኳን ትማጸናለች፡፡

 

ልጇቿ ምእመናንም “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” (ማቴ. 24፥20) ሲል መድኃኔዓለም እንዳስተመረው የሃይማኖት ፍሬ ምግባርን፣ ቱሩፋትን ሳይሠሩ በልምላሜ (በሃይማኖት) ብቻ ሳሉ እንዳይጠሩ ለንስሐ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ በማስተማር ነገረ ምጽአቱን በማዘከር “ድልዋኒክሙ ንበሩ፣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ” በማለት ታስተምራለች፡፡

 

ስለዚህ ይህ ክፍለ ክረምት የዕለተ ምጽአት ምሳሌ ነው፡፡ ወቅቱ የአዝመራ ወቅት ነው፡፡ፍሬ መለያ እንደሆነ ሁሉ የሰው ሥጋ ከተቀበረና ትቢያ ከሆነ በኋላ ተነስቶ በዕለተ ምጽአት በጽድቅና በኃጢአት ይለያልና፡፡(ማቴ.25፥32)

 

መ. ከመስከረም እስከ ፍጻሜ ክረምት(መስከረም 25)

ዘመነ መስቀል ከመስከረም 17 እስከ 25 ያሉት ዘጠኝ ቀናት የሚጠሩበት ሌላው መጠሪያቸው ነው፡፡ ይህ ክፍለ ክረምት ነገረ መስቀሉ የሚነገርበት ነው፡፡ በቅናት ተነሳስተው አይሁድ የቀበሩት የጌታችን መስቀል በንግሥት እሌኒ ጥረትና በፈቃደ እግዚአብሔር ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ተቆፍሮ የወጣበት መታሰቢያ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያንም የቅዱስ መስቀልን ክብር የሚመለከት ትምህርት ይሰጣል፤ ክቡር ዳዊት “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክት ሰጠሃቸው” (መዝ.59፥4) በማለት የተናገረው ይሰበካል፡፡ ጊዜው የክርስቶስና የመስቀል ጠላቶች ያፈሩበት የመስቀሉ ብርሃን ለዓለም ያበራበት በመሆኑ የመስቀሉ እንቅፋት ተወግዷልና ምእመናን በዚህ ይደሰታሉ(ቆላ.2፥14-15) በቅዱስ መስቀሉ ተቀጥቅጦ ኃይሉን ያጣው ዲያብሎስን በትእምርተ መስቀል ከእነርሱ ያርቁታል፡፡ በቅዱስ መስቀል የተደረገላቸውን የእግዚአብሔር ቸርነት እያስታወሱ በአደባባይ በዝማሬ መንፈሳዊ ደስታቸውን ይገልጣሉ፡፡

 

እንግዲህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ውስጥ ላለነው ራሳችንን ከጊዜው ጋር እንድናነጻጽር ወቅቱን የተመለከተ ትምህርት አዘጋጅታ ልጆቿን ለሰማያዊ መንግሥት ዝግጁ እንዲሆኑ ታስተምራለች፡፡ በዚህም ጊዜ ውስጥ ተፈጥሮን አይተን አገናዝበን የምንማር፣ ለንስሐ የተዘጋጀን ስንቶቻችን ነን? “ቁም! የእግዚአብሔርን ተአምራት አስብም!” እንዳለ (ኢዮ.37፥14) ያለንበትን ሕይወት አስበን ለንስሐ እንበቃ ዘንድ፣ የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎት አይለየን፤

Kidus Yohannes Metimiq

በዓለ ልደቱ ለዮሐንስ መጥምቅ

 


ሰኔ 15 ቀን 2004 ዓ.ም                                                                        በዘሚካኤል አራንሺ

እንኳን ለመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዓለ ልደት አደረሳችሁ::

Kidus Yohannes Metimiqበዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ዘመን የነበረው ፈርኦንና የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት ለዘፋኝ ወሮታ የሰጠው ሄሮድስ የሚያመሳስላቸው አንድ ዓይነት ተግባር ፈጽመዋል:: ይኽውም ሁለቱም ልደታቸውን ያከብሩ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀሱ ነው:: /ዘፍ.40፥20 ፤ ማቴ.14፥6/:: ታሪካቸውን ስናጠና ደግሞ በርካታ መመሳሰል እንደነበራቸው እንገነዘባለን:: ሁለቱም   ነገሥታት ናቸው:: ሁለቱም ንጹሐንን አስረዋል:: ሁለቱም ደም አፍሳሾች ነበሩ:: በልደት በዓላቸውም ነፍስ አጥፍተዋል:: በልደት በዓላቸው ነፍስ ያጠፉ ሰዎች ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ መጻፉ የልደት በዓል ማክበርን ስህተት አያደርገውም:: በጌታችን ልደት መቶ አርባ አራት ሺህ ሕጻናት በሄሮድስ ትእዛዝ ተገድለዋል:: የጌታችንን ልደት ግን እናከብራለን:: መግደል ኃጢአት መሆኑን እንመሰክርበት ካልሆነ በቀር ነፍስ በማጥፋት የሚከበር በዓል የለንም:: የፋሲካን በዓል በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለማክበር እንገደዳለን እንጂ ዘፋኞች ድግስ ስለሚያዘጋጁበት ማክበሩ ቢቀር ቢባል ሞኝነት ነው:: ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳንን ልደት በዓል ስታከብር የራሷ ሥርዓትና ባሕል የበዓላት መቁጠሪያ /ሊተርጂካል ካላንደር/ አላት:: የቱ መቼ መከበር እንዳለበትም ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ታስረዳለች:: ጥንታዊት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆንዋም በርግጥኝነት ዕለታቱን ቆጥራ ትናገራለች:: በነቢይ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ተብሎ የተነገረለት የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስን የልደት በዓል የምታከብረው በሰኔ ሠላሳ ቀን ነው::

 

 

የጻድቃን ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ እንደሆነ፤ ቅዱሳኑን ያገኘንባት ልደታቸውም የከበረች ናት:: /መዝ.116፥15/:: የመጥምቁ ዮሐንስን ልደት ያበሰረው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል::” እንዳለ በልደተ ቅዱሳን ደስ እንሰኛለን:: /ሉቃ.1፥14/:: በዓለ ቅዱሳን የደስታ በዓላት ናቸውና:: የተወለዱበት ፥ ልዩ ልዩ ገቢረ ተዓምራት ወመንክራት የፈጸሙባቸው፥ ሰማእተ ኢየሱስ ሆነው መከራ የተቀበሉባቸው፥ያረፉበትና የተሰወሩበት፥ ቃል ኪዳን የተቀበሉባቸውን ዕለታት የምናከብረው በደስታ ነው:: ቅዱስ ዳዊት “ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ።” እንዲል:: /መዝ.42፥4/:: ዕለታቱ በደንጊያ ተወግረው፥ በመጋዝ ተተርትረው ፥ ወደ እሳት ተጥለው፥ ለአናብስት ተሰጥተው፥ በሰማእትነት ያረፉባቸው እንኳ ቢሆኑ የደስታ በዓላት ናቸው:: የምስክርነታቸውን እውነትነት፥ የእምነታቸውን ጽናት፥ ታዛዥነታቸውንና ለአምላካቸው ያላቸውን ፍቅር በመግለጣቸው፤ የሚያገኙትን ክብር፥ የሚወርሱትን መንግስት እናስባለንና:: የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን የከበረች የእረፍቱን ቀን በማኅሌት ከበሮ መትተን፥ጸናጽል ጸንጽለን፥ ወረብ ወርበን፥ ቅዳሴ ቀድሰን፥ መዝሙር ዘምረን፥ መልክ ደግመን፥ ገድል አንብበን፥ ተዓምሩን ተናግረን፥ ቅድስናውን መስክረን እንደምናከብረው በዓለ ልደቱንም እንዲሁ እናከብራለን:: ጠቢቡ “ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል…” ብሏልና:: በመወለዳቸው ደስ ተሰኝተን በዓል እናደርጋለን:: /ምሳ.29፥2/::ካህኑ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ የብዙዎችን ደስታ ወልደዋል:: ጌታችን በወንጌል “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ . . . ” /ማቴ.7፥17-19/:: በማለት እንዳስተማረን የመጥምቁ ወላጆች “በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ” ተብሎየተመሰከረላቸው መልካም ዛፎች ነበሩና:: መልካም ፍሬ ቅዱስ ዮሐንስን አስገኙልን:: /ሉቃ.1፥6/:: ቅድስናቸው ከፍሬያቸው ከዮሐንስ የተነሳ ገኖ ዛሬም ድረስ ይታያል:: ለብዙዎች የሚሆን ደስታን ወልደዋልና ስሙን ዮሐንስ አሉት ትርጓሜው ደስታ ማለት ነው:: የክርስቲያናዊ ጋብቻ ዓላማ ምእመናንን መልካም ዛፍ አድርጎ መትከል ነው:: ሲንከባከቡትም እንደ ካህኑ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ደስታው ከቤተ ዘመድ ያለፈ መልካም ፍሬ ያፈራል:: በመጥምቁ ዮሐንስ ልደት “እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል . . . ” በማለት ነቢያተ እግዚአብሔር የተናገሩትን የትንቢት ቃል ለሚጠባበቁ ሁሉ ደስታ ነበረ:: /ሚል.3፥1 ፤ኢሳ.40፥3 ፤ማር.1፥1-5/:: የዮሐንስ መምጣት ለጌታችን መምጣት የምሥራች ነውና:: “ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።” የሚለው ስብከቱም የሚያስታውሰን ይህንኑ ነው:: /ማር.1፥7/:: በዮሐንስ መጥምቅ ልደት ደስ የሚሰኘው ያለፈውም የሚመጣውም ትውልድ ነው::

 

በዘመኑ የነበሩትን በትምህርቱ ደስ አስኝቷቸዋል:: ትምህርቱና ተግሣጹን የሰሙትን ከስህተት መልሷቸዋልና ደስ ተሰኝተውበታል:: በኃጢአት ያደፈ ስውነታቸውን በንስሀ ጥምቀት አዘጋጅቷልና ደስ ተሰኝተውበታል:: አገልግሎቱን በሚገባ የተረዳ መናኒ ነበርና ሕይወቱ ደስ የሚያሰኝ ነበረ:: አገልግሎቱን የምታውቅ፥ ክብሩን የምትመሰክር፥ በቃል ኪዳኑ የምትታመን ቤተ ክርስቲያንም ደስ ትስኝበታለች:: ስለዚህም በልደቱም በእረፍቱም ቀን የደስታ በዓል ታደርጋለች:: ምእመናንም በቃል ኪዳኑ በመታመን የምናደርገው የመታሰቢያ በዓሉ ደስታን የሚሰጥ ነው:: በመወለዱ ያገኘናቸውን የመጥምቁን በረከቶች እያሰብን አምላኩን እናመሰግናለን:: ልደተ ቅዱሳንን የማዘከር ዓላማው የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ አስቦ ለማመስገን ነው:: ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ልደት ስንናገር ወላጆቹንና ጽድቃቸውን የአባቱን የክህነት አገልግሎት፥ የመልአኩን ተራዳኢነት፥ የእናቱን በመንፈስ ቅዱስ መቃኘት፥ የእርሱን በማኅጸን መዝለል፥ የአባቱን አንደበት መክፈቱን፥ ስለ አደገበት የናዝራውያን ሥርዓት፥ ስለ አሳደገችው የበረሀ ፍየል /ቶራ/፥ ይመገበው ስለነበረው አንበጣና የበረሀ ማር፥ ዞሮ ያስተማራቸው ትምህርቶች፥ ስለ ፈጸማቸው የጽድቅ ሥራዎች፥ ጌታችንን ስለ ማጥመቁ፥ ስለ ተግሣጹና በሰማእትነት ስለ ማረፉ፥ ስለ ተዓምራቱ ከዚያም በኋላ በጸሎቱና በአማላጅነቱ ለሰው ልጆች ስለ ረዳው ርዳታ . . . በደስታ በማውሳት ነው:: የሌሎችም ቅዱሳንን በዓል የምናከብረው በዚህ መንገድ ነው::

 

እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው:: ቅድስት ኤልሳቤጥን የጎበኛት ድንቅ ነው፤ የአገልጋዩን ድካም ያልዘነጋ ድንቅ ነው፤ ዘመን ካለፋቸው በኋላ በእርግና ዘመናቸው ዘር የሰጠ ድንቅ ነው እያልን ደስ ተሰኝተን የምናመሰግነው በቅዱሳኑ ላይ ድንቅን ያደረገውን እግዚአብሔርን ነው::/መዝ.68፥35/ “ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር።” ተብሏልና:: /ያዕ.5፥13/:: ልደተ ቅዱሳን የደስታ የዝማሬ በዓላት ናቸው:: የእግዚአብሔር ወዳጆች ቅዱሳን ጽናታቸው ይደነቅበታል፥ አምላካቸው ይመሰገንበታል፥ ትምህርታቸው ይነገርበታል:: ስለ ቅዱሳን በመናገር የሚጠፋ ጊዜ የለም ፤ ስለ ቅዱሳን መመስከርን አብነት የምናደርገው መጽሐፍ ቅዱስን ነው:: መጽሐፍ ቅዱስን እናውቃለን ለሚሉን በውስጡ የበርካታ ቅዱሳንን ልደት፥ እድገት፥ አገልግሎት፥ ትምህርት፥ ክብርና ጸጋ የሚመሰክር መጽሐፍ መሆኑን እንመሰክርላቸዋለን::

 

የመጥምቁ ዮሐንስ ልደት በዜማ በግጥም በንባብም ቢሆን የምናወሳው መጽሐፍ የመሰከረለትን እውነት ነው:: መጥምቁ ዮሐንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት በትንቢት ቃል “የአዋጅ ነጋሪው ቃል” ፤“የቃል ኪዳን መልእክተኛ”፤ “መንገድ ጠራጊ”፤ “በበረሃ የሚጮኽ ሰው ድምጽ” ወዘተ እያሉ አመስግነውታል:: መልአከ እግዚአብሔር ቅድስናውንና ክብሩን ሲናገር “ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤” ፥“ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ብሎለታል ፤ ካህኑ ዘካርያስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ “አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤” እያለ አገልግሎቱን ገልጧል ፤ ጌታችንም “እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥” ፤ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤” ብሎ ሰማያዊ ክብሩን ገልጾለታል:: /ማቴ.11:11፤ ዮሐ.5፥35/:: ይገስጸው የነበረው ሄሮድስ እንኳን ሳይቀር “ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤” ተብሎ ተጽፏል:: /ማር.6፥20/:: የቅዱሳንን ሕይወት ማውሳት መጽሐፋዊ ነው፤ የምንለው በዚህ መንገድ ክብራቸውን፥ አገልግሎታቸውን፥ ቅድስናቸውን የምንመሰክር በመሆኑ ነው::

 

ቅዱስ ዮሐንስ ኤልያስን ይመስል የነበረ ነቢይ ነው:: ዮሐንስ መጥምቅና ነቢዩ ኤልያስ አኗኗራቸው ለመናንያን አርአያ ምሳሌ የሚሆን ነበር:: ኤልያስ በበረሀ ኖሯል፥ ዮሐንስም እንደዚያው:: መምህራን ሲጠሯቸው መምህር ወመገስጽ ይሏቸዋል ኤልያስ አክአብን ኤልዛቤልን ገስጿል፥ ዮሐንስም ሄሮድስን ገስጿል:: የጽድቅ ምስክሮች ነበሩ ኤልያስ ስለ ናቡቴ፥ ዮሐንስ ስለ ሕገ እግዚአብሔር ተሟግተዋል:: ሌሎችም በርካታ ተመሳስሎ አላቸው፡፡ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስን የልደቱን ዜና የተናገረው መልአክ “በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” በማለት መሰከረለት:: /ሉቃ.1፥17/:: በነቢዩ ኤልያስ በቅዱስ ዮሐንስ መንገድ ሂደው ያገለገሉ መናንያንን ሰማእታትን ስውራንን ቅዱሳንን ሁሉ እነርሱን እንዳከበርን እናከብራቸዋለን:: ገድላቸውን ጽፈን ተዓምራቸውን ተናግረን ምስክርነታቸውን አጽንተን እንይዛለን:: የሕይወታቸውን የቃላቸውን የጽሑፋቸውን ትምህርት እንመሰክራለን:: ሕዝብ ደስ እንዲለው:: ለሕገ እግዚአብሔር የሚቀኑ ስለ ደሀ መበደል ስለ ፍርድ መጓደል የሚታገሉ ጻድቃን ይበዙ ዘንድ በኤልያስ መንፈስ በዮሐንስም መንገድ የሚመጡ ጻድቃን ለማፍራት ይረዳልና::/ምሳ.29፥2/::

 

የቅዱሳንን በዓል ማክበር የሚጠቅመው በረከታቸውን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን የቅዱሳኑን ትምህርት ለመያዝም ነው:: በዓለ ቅዱሳን ሲከበር ትምህርታቸውም ይዘከራል:: የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ትምህርቶች በአራቱም ወንጌላውያን ተዳሰዋል:: የመጥምቁ ታላላቅ ትምህርቶች በሁለት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ:: የመጀመሪያ ትምህርቱ የንስሐ ጥሪ ነው:: ሕዝቡ እንዲመለሱ ይሰብካል ፥ ደንዳና ልብ የነበራቸውን እንደ ሄሮድስና የአይሁድ መምህራን ያሉትን ይገስጻል:: ይህ ትምህርቱ ዘመኑን እየዋጀ በየዘመናቱ የሚነሱ ምእመናንን ሕይወት ለማነጽ ይጠቅማል:: ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ለመጡ ለሕዝቡ ቸርነትን ስለ ማድረግ፥ ለቀራጮች ስለ እውነት ሚዛን፥ ለጭፍሮች ስለ ፍትሕ፥ . . . ያስተማራቸው ትምህርቶች ዘመናትን እየተሻገሩ የሚመክሩ ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ ናቸው::/ሉቃ.3፥11-14/:: የንስሐ ትምህርት ተግሣጽና ምክር ይሰጣል:: ከመጥምቀ መለኮት ከቅዱስ ዮሐንስ ትምህርት የተወሰደ ነው:: በዚህምክንያት ነው በዓለ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠናባቸው፥ የሚነገርባቸው፥ የሚተረጎምባቸው ናቸው የምንለው::

 

ሁለተኛ ነገረ ሥጋዌ ላይ ያተኮረው ትምህርቱ ነው:: መጥምቁ ዮሐንስ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢርን ሲያስረዳ መሲህ ይመጣል ተብሎ በነቢያት የተነገረው በጌታችን መፈጸሙን አስረግጦ የተናገረ መምህር ነው::/ዮሐ.1፥29-36/:: የዓለም መድኃኒት መሆኑንም ከመልአኩ ቀጥሎ የመሰከረ ነቢይ ነው:: “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” ብሎታልና:: በሥጋ ልደት ቢቀድመውም ለመለኮት ዘመን አይቆጠርለትምና ቅድመ ዓለም የነበረ ሕልውናውን “ከእኔም በፊት ነበር” ሲልም መስክሯል:: የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን ምስክርነት ልዩ የሚያደርገው ነገርም አለ:: ምስክርነቱ የእውቀት ብቻ አይደለም:: በዮርዳኖስ ባሕር ቆሞ ጌታውን ሲያጠምቅ ሰማይ ተከፍቶ ያየ የእግዚአብሔር አብን ምስክርነት የሰማ የምስጢር ሰው ነው:: አይሁድን ያሳፈረበት ትልቁ ምስክርነቱም “እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።” የሚለው ነው:: የነገረ ሥጋዌ ትምህርቱን ሲደመድም “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” ሲል የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን በሚገባ አስረድቷል:: /ዮሐ.3፥25-36/:: ጌታችንም የምስክርነቱን እውነትነት “እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል።” በማለት ገልጿል:: /ዮሐ.5፥33/:: በዓለ ቅዱሳን በጠቅላላ ነገረ እግዚአብሔር የሚነገርባቸው፥ ትምህርተ ሃይማኖት የምናጠናባቸው፥ ታሪከ ቤተ ክርስቲያን የሚዘከርባቸው በዓላት ናቸው::

 

በአጠቃላይ በዓለ ቅዱሳንን አታክብሩ ማለትን የሚያህል የወንጌል እንቅፋትነት የለም:: ጌታችን ባለሽቱዋ ማርያም በንስሐ እንባ አጥባ ሽቱ ቀብታ መልካም አድርጋለችና ለውለታዋ መታሰቢያ ሲያቆም “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል።” ካለ:: /ማቴ.26፥13/:: ስለ ስሙ እስከ ሞት ድረስ ለተደበደቡ፥መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ፥ በእስራትና በወኅኒ ለተፈትኑ፥ በደንጊያ ተወግረው ለሞቱ፥ በመጋዝ ለተሰነጠቁ፥ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ለተቅበዘበዙ . . . ወዳጆቹማ እንዴት ያለ መታሰቢያን ይሰጣቸው? የወንጌል ትምህርት ለሚተረጎምባቸው አብነቶችማ እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም?

 

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ቅዱሳን ሥርዓታዊና ትውፊታዊ በሆኑ መንገዶችም ይዘከራሉ:: ሥርዓታዊው መንገድ ገድልና ተዓምር መጻፍ፥ ድርሳንና መልክ መድረስ፥ በስማቸው መቅደስ መሰየም፥ . . . ናቸው:: ትውፊታዊውም “ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።” ከሚለው አማናዊ ቃል ኪዳን ለመሳተፍ በቅዱሳኑ ስም ጸበል ጸዲቅ ማድረግን የመሰሉ ናቸው:: በመጥምቁ ዮሐንስ ስም የሚሰበሰቡ ወዳጆቹም ገድሉን አንብበው፥ ተዓምሩን ተናግረው፥ ለነዳያን መጽውተው፥ ሰማእቱን ያዘክራሉ:: በልደቱ የወላጆቹን ሐዘን ያራቀ በምልጃው ለሚተማመኑ መታሰቢያውን ለሚያደርጉ ወዳጆቹም ደዌያቸውን እያራቀ መንፈሳዊ ደስታን ያለብሳቸዋል::

የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ የልደቱ ረድኤትና በረከት አይለየን::

ሦስት አራተኛው መሬት

ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ዮሐ.14፥18

ግንቦት 24/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

ይህንን የተስፋ ቃል ለቅዱሳን ሐዋርያት የተናገረው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ደቀ መዝሙርነት የተጠሩት በልዩ ልዩ ሙያ ተሰማርተው ሳለ ነው፡፡ በየሙያቸው ሥራ እየሠሩ ከሚተዳደሩበት ሥፍራ ሁሉ ደርሶ ፈጣሪያችን በቸርነቱ ለከበረው የወንጌል አገልግሎት ጠራቸው፡፡ “ወእንዘ ያንሶሱ መንገለ ባሕረ ገሊላ፤ ርእየ ክልኤተ አኅወ፥ ስምዖንሃ ዘተሰመየ ጴጥሮስ ወእንድርያስሃ አኅዋሁ እንዘ ይወድዩ መርበብቶሙ ውስተ ባሕረ፤ እስመ መሠግራነ እሙንቱ፡፡ ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ንዑ ትልዉኒ፤ ወእሬስየክሙ ትኩኑ መሠግራነ ሰብእ፡፡…. በገሊላ ባሕር ዳር ማዶ ሲመላለስ ሁለት ወንድማሞችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንና ወንድሙን እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፣ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና፡፡ ጌታችንም “ለጊዜው በእግር ተከተሉኝ ፍጻሜው በግብር ምሰሉኝ፡፡ እኔም ሰውን እንደ ዓሣ ወንጌልን እንደ መረብ፣ ይህን ዓለም እንደ ባሕር አድርጋችሁ እንድታስተምሩ አደርጋችኋለሁ” አላቸው፡፡ ያን ጊዜ መርከባቸውንና መረባቸውን ትተው ተከተሉት” የተቀሩትም ሁሉ እንዲህ ባለ ጥሪ ጠራቸው /ማቴ.4፥18-22፣9፣ ዮሐ.1፥46፤ 44፥51/

ቅዱሳን ሐዋርያትም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ጌታችን በዋለበት ውለው ባደረበት እያደሩ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ከእርሱ ጋር ሆኑ፡፡ በኋላም የተጠሩለትን አገልግሎት በመፈጸም ክብርን አግኝተውበታል /ማቴ.13፥42፣ ሕዝ.47፥10/፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን ሁሉ ትተው ጥለው የተከተሉትን ሐዋርያትን “ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም” አላቸው፡፡ አጽናኝ ጰራቅሊጦስ ይሰጣችኋል፡፡

“እነሆ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኀይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሏቸዋል፡፡ /ሉቃ.24፥49፣ ዮሐ.15፥26፣ 16፥7 ሐዋ.1፥4/ በዚሁ መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት ከእመቤታችን ጋር ሆነው በኢየሩሳሌም በአንድነት በጸሎት እየተጉ ሳለ አምላካችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል በእያንዳንዳቸው አድሮባቸዋል፡፡

እነሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ከብልየት ታደሱ፥ በአእምሮ ጎለመሱ፥ሕጹጻን የነበሩ ፍጹማን፥ ፍሩሃን የነበሩት ጥቡዓን ሆኑ ባንድ ልሳን ይናገሩ የነበሩ ሰባ አንድ ልሳን ተገለጸላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢየሩሳሌምን ባንድነት ዓመት በኅብረት አስተማሩ፡፡ “ወነበሩ ዓመተ ፍጽምተ በኢየሩሳሌም” እንዲል፡፡ ዓለምን 12 አድርገው ተካፍለው በእየ ሀገረ ስብከታቸው ሄደው አምልኮተ እግዚአብሔርን አስተማሩ፡፡ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መለሱ፡፡

በዓለ ሃምሳ በኦሪት የነበረው ገጽታ

እስራኤል ከሀገራቸው ወጥተው በልደት ለ430 ዓመታት መከራና ስቃይ ሲደርስባቸው ኖረው በሙሴ መሪነት በፋሲካው በግ ከሞተ በኲር ድነው ምድረ ርስትን እንዲወርሱ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት በየዓመቱ መጀመሪያ ወር /ሚያዚያ 14 ቀን/ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ /ዘጸ.12፥1-13/ ይህን በዓል ካከበሩ ሰባት ሱባኤ ቆጥረው በማግስቱ /በሃምሳኛው ቀን/ ደግሞ የእሸት በዓል /በዓለ ሠዊትን/ ያከብራሉ፡፡ ይህም በኦሪቱ እንደተገለጸው የስንዴ በኲራት አጨዳ መታሰቢያ፣ የምስጋና ጊዜ ነው፤ /ዘጸ.23፥16፣ ዘሌዋ.23፥15-18፣ ዘኁ.28፥26/

በዓለ ሠዊት በበዓለ ሃምሳ

ጌታችን እርሱ ባወቀ ይህንኑ በዓል በበዓለ ሃምሳ /በበዓለ ጰራቅሊጦስ/ እንዲተካ አድርጎታል፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት ወዲህ በበዓለ ሠዊት በዓለ ጰራቅሊጦስ ገብቶበታል፡፡ ጰራቅሊጦስ የመንፈስ ቅዱስ ልዩ የሆነው አካሉ መጠሪያ ስም ነው፡፡ ጰራቅሊጦስ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ በችግር ጊዜ ተራዳኢ፣ በሃዘን ጊዜ አጽናኝ፣ መዘንጋት ላለበት ልብ አስታዋሽ፣ በአላውያን ፊት ተከራካሪ ጠበቃ ማለት ነው፡፡ /ዮሐ.14፥16-26፣ 15፥26፣ 16፥7/ ዘመነ ጰራቅሊጦስ የሚባለው ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተነሣ ከሃምሳኛው ቀን ጀምሮ ቀጥሎ እስከ አለው እሑድ ድረስ ያለው 8 ቀን ነው፡

“ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ” የሐዋ.ሥራ.2፥2

በዓለ ሃምሳ በተባለው በዓል መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ባለ ድምጽና ግርማ ተገለጠ፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን ሐዋርያት በዝግ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዲስ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደ ተገለጠላቸው ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፡፡

“በዓለ ሃምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ፥ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዪአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ አደረባቸው፣…” /የሐ.ሥራ.2፥1-4/

መንፈስ ቅዱስ ስለምን በንፋስና በእሳት አምሳል ተገለጠ?

ሀ/ መንፈስ ቅዱስ በንፋስ /በዓውሎ ነፋስ/ ድምጽ መጣ ብሎ የተናገረበት ምክንያት?

–    ነፋስ ረቂቅ ነው መንፈስ ቅዱስም የማይመረመር የማይዳሰስ ረቂቅ ነውና፤

–    ነፋስ ኀያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኀያል ነውና፤

–    ነፋስ ፍሬውን ከገለባው ይለያል፤ መንፈስ ቅዲስም ጻድቃንን ከኀጥአን ይለያልና፤

–    ነፋስ በምላት ሳለ አይታወቅም ባሕር ሲገሥጽ ዛፍ ሲያናውጥ ይታወቃል እንጂ፡፡ መንፈስ መንፈስ ቅዱስም በምላት ሳለ አይታወቅም ቋንቋ ሲያናግር፤ ምሥጢር ሲያስተረጉም ይታወቃልና፡፡

–    ነፋስ መንቅሂ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ሰማእታትን ወደደም ጻድቃንን ወደ ገዳም ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን አነቃቅቶ የሚመራቸው እርሱ ነውና በነፋስ መስሎ ተናገረለት፡፡

ለ/ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች /በእሳት አንጻር የተገለጠውም/ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አባቶቻችን መምህራን የመንፈስ ቅዱስን በእሳት የመመሰል ትርጉም እንዲህ ገልጠው ያስተምሩናል፡፡

እሳት ምሉዕ ነው መንፈስ ቅዱስም ምሉዕ ነውና፤ እሳት በምልዓት ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገልጽም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም እንጂ አድሮ ሳለ አይታወቅምና እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው፤ ኋላ በእንጨት እያቀጣጠሉ ያሰፉታል፤ መንፈስ ቅዱስም በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው፡፡ ኋላ በሥራ ያሰፉታልና፤ እሳት ጣዕመ መዓዛን ያመጣል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን ያመጣልና፡፡ እሳት በመጠን ቢሞቁት ሕይወት ይሆናል፡፡ ከመጠን አልፎ የሞቁት እንደሆነ ግን ያቃጥላል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደሆነ ሕይወት ይሆናል፤ በማይገባ ከተጻፈው ወጥቶ የመረመሩት እንደሆነ ግን ይቀስፋልና፤ “እሳት በላኢ ለዓማጽያን ለእለ ይክሕዱ ስሞ ወእሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ” እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡

እሳት ያቀረቡለትን ሁሉ ያቀጥላል፤ መንፈስ ቅዱስም ሕዝብ አሕዛብ የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡትን መሥዋዕት ይቀበላልና፡፡ እሳት ውኃ ገደል ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፡፡ እሳት ዱር ይገልጻል መንፈስ ቅዱስም ምሥጢርን ይገልጻልና፡፡ እሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ይመቻል፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ያመቻል፡፡ እሳት ካንዱ ፋና አምሳ፣ ስልሳ፣ ፋና ቢያበሩለት ተከፍሎ የለበትም፤ መንፈስ ቅዱስም ተከፍሎ ሳይኖርበት እስከ ምጽአት ድረስ ሲሰጥ ይኖራልና፡፡

ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ያስፈለጋቸው ለምንድር ነው?

ሐዋርያት “ወረደ፣ ተወለደ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ተነሣ አረገ” ብለው ለማስተማር ለማሳመን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋው ባይታደላቸው ኖሮ በራሳቸው ብቻቸውን በደከሙ፣ ደክመውም በቀሩ ነበር፡፡ ሰው ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር መንፈሳዊውን ተግባር ቀርቶ ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት አይቻለውም፡፡ መንፈሳዊው ሥራ ደግሞ በሰይጣን ዲያብሎስና በሠራዊቱ /ርኲሳን መናፍስት/ ልዩ ልዩ ፈተናና መሰናክል ያጋጥመዋል፡፡ ስለሆነም በመንፈስ ርኲስ የሚመጣውን ፈተና ለመቋቋም ምንጊዜም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ያሻል፡፡

ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊትና በኋላ

ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ከመሳተፋቸው በፊት ምንም እንኳን ከጌታችን ባለመለየት ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ቢቆዩ ነገር ግን በልብ የሚያምኑትን በአንደበታቸው ገልጸው ለመመስከር ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ የችግሩም መንስኤ “የምናምነውን ብንመሰክር እንገረፋለን፣ እንሰቀላለን” የሚል ፍርሃት ነበር፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በዕለተ አርብ ጌታችን በቀያፋ ግቢ ውስጥ መከራን ሲቀበል ተከትሎት ወደዚያው አምርቶ ነበር፡፡ ሆኖም በተለያዩ ሰዎች ለሦስት ጊዜያት “ከገሊላው ኢየሱስ ጋር አይደለህምን?” ተብሎ ቢጠየቅ፤ የሰጠው ምላሽ “ሰውየውን /ጌታችንን ነው/ አላውቀውም” የሚል ነበር /ማቴ.26፥69-72/ በኋላ ግን /ማለትም መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ካሳደረበት በኋላ/ በሸንጎ ሹማምንት “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፣ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው /የጌታችንን ነው/ ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም መልሰው አሉ፡፡ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል፡፡…. ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፏቸው፣ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው፡፡ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ” /የሐዋ.ሥራ.5፥28-41/

ከዚህ በላይ የትምህርታቸው ቃል በሰማዕያን ልቡና ገብቶ ካለማመን ወደ ሃይማኖት፣ ከአምልኮተ ባዕድ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚመልስ ሆኗል፡፡ ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራት ያደርጉም ጀመር አንድ ቋንቋ ብቻ ያውቁ የነበሩት ሐዋርያት ሰባ አንድ ቋንቋ ተጨምሮላቸው የጌታችንን ወንጌል በመላው ዓለም ተዘዋውረው አስተምረዋል፡፡

በዓለ ሃምሳ ለቤተክርስቲያን

ይህ በዓል የቤተ ክርስቲያን የልደት በዓል ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ስያሜ ያለ ምክንያት የተሰየመ /የተሰጠ/ አይደለም፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመኑ የተነሡ ሊቃውንት ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፍት እንደሚገልጹት በዚህች ቀን ቁጥራቸው ከሦስት ሺህ ያላነሱ አይሁድ ወደ ክርስትና የመጡበት፤ወንጌል ከመካከለኛው ምስራቅ አልፋ በመላው ዓለም የተነገረችበት የተስፋፋችበት ቀን ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በተባለ መጽሐፋቸው ይህንን ሁኔታ እንዲህ ገልጸውታል፡-

“…. ጌታ ባረገ በአስረኛው ቀን ጧት መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ተሰጠ፡፡ ጌታ የነገራቸው የተስፋ ቃል ሁሉ ተፈጸመ፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በእነርሱ ላይ ሲያድር ለቤተ ክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው “መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላት ኑሮ የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ኮስምኖ ቀጭጮ ይቀር ነበር፤ ስለዚህም በሚገባ አነጋገር ይህች ዕለት የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ትባላለች” ይላል፡፡ ብዙ ሊቃውንት ይህችን ዕለት የበዓላት ሁሉ እመቤት ይሏታል፡፡….”

በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ይህንኑ በዓል በጸሎትና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት አክብረውት ይውላሉ፡፡

በዚህ ዕለት የሚቀደሰው ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ፥ ምንባባቱ ደግሞ፡-

ኤፌ.4፥1-17

/ቁጥር7/ እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን፥

1ኛ ዮሐ.2፥1-18

/ቁጥር.17/ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል

የሐዋ.ሥራ.1፥1-18

/ቁጥር 4/ በሁሉም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር

የሚለው ሲሆን ምስባኩ “ወወሀብከ – ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው” የሚለው ነው፥ /መዝ.67፥18/

በዚህ ዕለት ጌታችን ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሰጣቸው ተስፋም በወንጌል ንባብ ጊዜ ይሰማል፡፡ ይኸውም፡- “ወኢየኅድገክሙ እጓለማውታ ትኲኑ” የሚለው ነው፡፡

ኢየሩሳሌም -ቤተ ክርስቲያን

ቅዱሳን ሐዋርያት ፈጣሪያችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዛቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ በኢየሩሳሌም ከተማ ጸንተው /ቆይተው/ ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ከተማ ቢናወጹ ይህን ጸጋ ለመሳተፍ ባልታደሉ ነበር፡፡ ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር /ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ/ ደግሞ ምንም ምን ተግባር ማከናወን ባልተቻላቸው ነበር፡፡ በዚህ የተነሣ ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ እመቤታችንን ይዘው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፡፡ ይህም በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች የሚያስተምረን ነገር፡- በሃይማኖት በምግባር ጸንቶ የሚኖር ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ይጎበኘዋል፡፡ በጸጋ ላይ ጸጋ ይጨምርለታል፡፡ ኋላም ለመንግሥተ ሰማይ ያበቃዋል፡፡

ይህንን ጸጋ ለማግኘት ፈጣሪያችን ኢየሩሳሌም ከተባለች ለሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ ከሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳንናወጽ እንዳንወጣ አዞናል፡፡ ኢየሩሳሌም ማለት የሰላም ሀገር /ሀገረ ሰላም/ ማለት እንደሆነ፤ ቤተ ክርስቲያን /ቤተ ክርስቶስ/ ማለት ደግሞ የሰላም ቤት ማለት ነው፡፡ የሰላም አለቃ፣ የሰላም ባለቤት የክርስቶስ ቤት ናትና፡፡ /ኢሳ.9፥6/

እንግዲህ አባ ሕርያቆስ ባስተላለፈልን ቡራኬ መሠረት “ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን፥ በከመ ተጋባእክሙ በዛቲ ዕለት፣ ከማሁ ያስተጋብእክሙ በደብረ ጽዮን ቅድስት፣ ወበ ኢየሩሳሌም አግዓዚት እንተ በሰማያት፡- እናንተ የክርስቲያን ወገኖች በዚህች ቀን እንደተሰበሰባችሁ ክብርት በምትሆን በደብረ ጽዮን ይሰብስባችሁ፡፡ በልዕልና ባለች በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ይሰብስባችሁ፡፡”  እንዳለን እስከ መጨረሻ ሕይወታችን ቅድስት ንጽሕት ርትእት በሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ያጽናን፡፡ በዓሉን የበረከት የረድኤት ያድርግልን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

lidetaleMariam 1

“መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፡- መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው” /መዝ.86፥1/


በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ

lidetaleMariam 1ይህ ቃል የእመቤታችንን አያቶቿን የቀደሙ ወላጆቿን ንጽሕና፣ ቅድስና፣ ክብር አስመልክቶ ቅዱስ ዳዊት የተናገረው የምስክርነት ቃል ነው፡፡ ይህ ምስክርነት አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ለኩነተ ሥጋ የመረጣት ቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆቿ ንጹሐን፣ ቅዱሳን መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ሲመላለስ፡- “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያፈራል፡፡ መልካምም ዛፍ ክፉ ፍሬን ማፍራት፥ ክፉ ዛፍም መልካም ፍሬን ማፍራት አይችልም” ማቴ.7፥17-18፡፡ በማለት እንደተናገረው እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተገኘችባቸው ወላጆቿ ሁሉ ቅዱሳን ንጹሐን፣ እግዚአብሔርን የሚወዱና የሚያከብሩ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ለመሆኑ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዘር ሐረግና የትውልድ ታሪኳ ምን ይመስላል?

 

በነገረ ማርያም ሰፍሮ ከምናገኘው ሰፊ ታሪክ ከፊሉን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ!

የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ በጥሪቃ ይባላሉ፤ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጸጎች ነበሩ፤ ብዕላቸውም የወርቅ፣ የብር፣ የፈረስ፣ የበቅሎ፣ የሴት ባሪያ፣ የወንድ ባሪያ ነው፡፡ ከወርቁ ብዛት የተነሣ እንደ አምባር እንደ ቀለበት እያሠሩ፤ ከበሬው ከላሙ ቀንድ ያደርጉት ነበር፡፡ ይህን ያህል አቅርንተ ወርቅ፤ ይህን ያህል አቃርንተ ብሩር ተብሎ ይቈጠር ነበር እንጂ፤ የቀረው አይቈጠርም ነበር፡፡ ከዕለታት ባንደኛው በጥሪቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘቡን ብዛት አይቶ፤ “ቴከታ እኔ መካን፤ አንቺ መካን ይህ ሁሉ ገንዘብ ለማን ይሆናል?” አላት “እግዚአብሔር እንጂ ከኔ ባይሰጥህ ወይ ከሌላ ይሰጥህ ይሆናል፤ አግብተህ አትወልድምን?” አለችው፡፡ “ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል” አላት፤ በዚህ ጊዜ አዘኑ፤ ወዲያው ራእይ አይተዋል፤ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስታወጣ፣ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስታደርስ ስድስተኛይቱ ጨረቃን፣ ጨረቃ ፀሐይን ስትወልድ አይተው፥ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም /ሕልም ተርጓሚ/ አለና ሂደው ነገሩት፤ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል” አላቸው፡፡ እነርሱም “ጊዜ ይተርጉመው” ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ፀነሰች፤ ወለደች ስሟን ሄኤማን አለቻት፤ ሄኤማን ማለት ረካብኩ ስእለትየ ረከብኩ ተምኔትየ /የፈለግሁትን የለመንኩትን አገኘሁ/ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፣ ቶና ሲካርን፣ ሲካር ሄርሜላን፣ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፣ ምክነት ወርዶ እንደ አያቶቿ ሆናለች፤ ብዕሉ ግን በመጠን ሆኗል፡፡

 

ከጎረቤቷ በዝሙት የምትኖር አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ሐና “ዛሬ ቤተ ክርስቲያን እስማለሁ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን የምለብሰው ልብስ የለኝም” አለቻት፡፡ እርሷም “ልብስማ የኔ ካንድ ሁለት ሦስት ልብስ አለልሽ አይደለም? ያንን ለብሰሽ አትሄጅምን?” አለቻት፡፡ “ያንቺ ልብስ የተሰበሰበ በዐስበ ደነስ በዐስበ ዝሙት ነው፡፡ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ንጹሕ ነገር ይወዳል፤ ይህን ለብሼ ብለምነው ምን ይሰማኛል ብዬ ነዋ” አለቻት፡፡ “ሐና፤ እኔ በምን ምክንያት ልጅ ነሣት እያልሁ ሳዝንልሽ እኖር ነበር፤ ለካ እንደ ድንጊያ አድርቆ ያስቀረሽ ይህ ክፋትሽ ነው” አለቻት በዚህ አዝናለች፡፡

 

በሌላ ጊዜም ሐናና ኢያቄም “መሥዋዕት እናቀርባለን” ብለው ከቤተ መቅደስ ሄዱ፤ ሊቀ ካህናቱ ሮቤል ይባል ነበር፡፡ “ወኢይተወከፍ መሥዋዕቶሙ ለመካናት እንጂ ይላል፤ “እናንተማ ብዝኁ ወተባዝኀ… ብሎ ለአዳም የነገረውን ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? ቢጠላችሁ ነው እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን? መሥዋዕታችሁን አልቀበልም” ብሏቸው በዚህ እያዘኑ ተመልሰዋል፡፡ …. ከዛፍ ሥር ተቀምጠው አርጋብ /ርግቦች/ ከልጆቻቸው ጋራ ሲጫወቱ ዕፅዋት አብበው አፍርተው አይታ “አርጋብን በባሕርያቸው እንዲራቡ፣ ዕፅዋትን እንዲያብቡ እንዲያፈሩ የምታደርግ የኔ ተፈጥሮዬ ከድንጋይ ይሆን ልጅ የነሣኸኝ” ብላ አዘነች፡፡ ከቤታቸው ሂደው “ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ አርሶ ቆፍሮ ይርዳን አንልም ለቤተ እግዚአብሔር አንጣፊ፤ ጋራጅ ሆኖ ይኖራል፤ ሴት ብንወልድ ዕንጨት ሰብራ ውኃ ቀድታ ትርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር መሶበ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ትኑር” ብለው ብፅዓት ገብተዋል፡፡

 

የሐምሌ  30 ዕለት እሷ ለሱ “ፀምር ሲያስታጥቁህ መቋሚያህ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየሁ” ብላ፤ እሱ ለሷዋ “ጻዕዳ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፤ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ” ብሎ ያዩትን ራእይ ተጨዋውተዋል፡፡ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም አለና ሂደው ነገሩት፡፡ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ” አላቸው፡፡ “አንተስ አልፈታኸውም ጊዜ ይፍታው” ብለው ተመልሰዋል፡፡ በነሐሴ 7 ቀን መልአክ መጥቶ ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ ብሏቸው በብሥራተ መልአክ በፈቃደ አምላክ እመቤታችን ተፀነሰች፡፡ በተፀነሰችም ጊዜ ብዙ ተአምራት ተደርጓል፡፡

 

በርሴባ የምትባል አክስት ነበረቻት አንድ ዐይና ነች፤ “ሐና እግዚአብሔር በረድኤት ጎበኘሽ መሰለኝ” ብላ ማኅፀኑዋን ደሳ ዐይኗን ብታሸው በርቶላታል፡፡ ይህን አብነት አድርገው ሕሙማን ሁሉ ማኅፀኑዋን እየዳሰሱ የሚፈወሱ ሆነዋል፡፡ ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል ያጎቷ ልጅ ነበር ሞተ፤ ትወደው ነበርና ያልጋውን ሸንኮር ይዛ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት “ሰላም ለኪ ኦ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ” ብሎ ከመፈክረ ሕልም የቀረውን ተርጉሞላታል፡፡

 

ከዚህ በኋላ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና “ቀድሞ ከነዚህ ወገን የሚሆኑ ዳዊት ሰሎሞን አርባ አርባ ዘመን እንደሰም አቅልጠው እንደ ገል ቀጥቅጠው ገዙን፡፡ አሁን ደግሞ ከዚህች የተወለደ እንደምን ያደርገን ይሆን?” ብለው በጠላትነት ተነሡባቸው፤ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለኢያቄም “አድባረ ሊባኖስ ይዘሃት ሂድ” ብሎት እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡ ይህም አስቀድሞ እግዚአብሔር ባወቀ “እምሊባኖስ ትወፅእ መርዓት … ሙሽራ /እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም/ ከሊባኖስ ትወጣለች” በማለት ጠቢቡ የተናገረው ቃለ ትንቢት ነው፡፡ /መኃ.4፥8/

 

ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በእመቤታችን ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ፡፡

በግንቦት 1 ቀን /5ሺ ከ5መቶ የመከራው ዘመን ሊያልቅ 15 ዓመታት ሲቀሩት/  ሊባኖስ በሚባል ተራራ ከፀሐይ የምታበራ ሴት ልጅ ተወለደች፡፡ ይህቺውም ፍጥረት ሁሉ /ደቂቀ አዳም ሁላቸው/ ተስፋ ሲያደርጓትና ሲጠባበቋት የነበረች የድኅነታቸው ምልክት እመቤታችን ናት፡፡

 

ሶሪያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም “አክሊለ ምክሕነ ወቀዳሚተ መድኀኒትነ፡፡ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል፡- የመመኪያችን ዘውድ የደኅንነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት በድንግል ማርያም ሆነልን” በማለት መናገሩ ስለዚህ ነው፡፡

 

  • አክሊል ምክሐነ፡- አላት ይህም አክሊል የወዲህኛው፣ ምክሕ የወዲያኛው ነው፡፡ ከነገሥታት መካከል እንደ ዳዊት የከበረ የለም፡፡ ምንም እንኳን ቅዱስ ዳዊት የከበረ ቢሆን የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለውም፡፡
  • ወቀዳሚተ መድኀኒተ አላት፡- ቀዳሚተ የወዲህኛው መድኀኒት የወዲያኛው ነው፡፡ ከመሳፍንት ወገን የሚሆን ኢያሱ ምንም የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ቢሆን የደኅንነታችን መጀመሪያ መሆን አልተቻለውም፡፡
  • ወመሠረተ ንጽሕና አላት፡- መሠረት የወዲህኛው፤ ንጽሕ የወዲያኛው ከነቢያተ እግዚአብሔር ወገን የሚሆን ኤልያስ በድንግልና በንጽሕና መኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ንጹሕ ድንግል ቢባል የንጽሕናችን መሠረት መሆን አልተቻለውም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችን መጀመሪያ፤ የንጽሕናችን መሠረት ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤” በማለት ተናግሯል፡፡ በእርሷ ምክንያትነት መድኀኒዓለም የሚፈጽምልንን ካሳ ነቢያትና የቀደሙ አበው ሁሉ የእርሷን መወለድ በናፍቆት ሲጠባበቁ ነበር፡፡ ከነቢያት አንዱ የሆነ ኢሳይያስም “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ጎሞራም በመሰልነ ነበር፡፡” በማለት መናገሩ በእርሷ መገኘት ከጥፋት መዳናችንን ሲገልጽ ነው፡፡ ኢሳ.1፥9

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ተወለደች የሐና ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ በሰሙ ጊዜ ፍጹም ደስ ብሏቸው ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰበሰቡ፡፡ ሕፃኗን /እመቤታችንን/ ተመልክተው ፍጹም አደነቁ፡፡ እርስ በርሳቸውም እንደዚች ያለች ብላቴና ከቶ አየተን አናውቅም ተባባሉ፤ ጸጋ እግዚአብሔር በርሷ አድሯልና፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በሰውነቷ ሁሉ መልቷልና፡፡

 

ከኢያቄምና ከሚስቱ ከሐና ጋራ ደስ እያላቸው የእግዚአብሔርን ቸርነት እየተናገሩ ሰባት ቀን ተቀመጡ፤ ያችንም ብላቴና ስምዋን ማርያም አሏት ይኸውም የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው፡፡ ሰባቱንም ቀን በፈጸሙ ጊዜ በፍቅር ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡

 

በዚህ ትውፊት መሠረት ኢትዮጵያውያን ምእመናን በየዓመቱ ግንቦት 1 ቀን የእመቤታችንን ልደት ከቤታቸው ወጥተውና ከያሉበት ተሰባስበው ንፍሮ ቀቅለው፣ አነባብሮ ጋግረውና ሌላም እንደ አቅማቸው /ዝክር አዘጋጅተው/ በመንፈሳዊ ደስታ ዛሬም ድረስ ያከብሩታል፡፡

 

የእመቤታችን ስሞችና ትርጓሜያቸው፡፡

ማርያም ማለት ፍጽምት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው መልክ ከደምግባት አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ ፍጻሜው ግን ንጽሐ ሥጋ ከንጽሐ ነፍስ ድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ አንድም ማርያም ጸጋ ወሀብት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው ለእናት ለአባቷ ጸጋ ሆና ተሰጥታለች፡፡ ፍጻሜው ግን ለሰው ሁሉ ጸጋ ሁና ተሰጥታናለችና፡፡

 

አንድም፡- ማርያም ማለት መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው፡፡ ምእመናንን መርታ ገነት መንግሥተ ሰማያት አግብታለችና፡፡ አንድም ማርያም ማለት ልዕልት ማለት ነው፡፡ ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ ናትና አንድም ማሪሃም ማለት እግዝእተ ብዙኀን ማለት ነው አብርሃም ማለት አበ ብዙሃን እንደሆነ ማለት ነው፡፡

 

እንግዲህ ለነቢያተ ዜና ትንቢታቸው ለሐዋርያት ስብከታቸው ለክርስቲያኖች ሁሉ ተስፋቸው የሆነች እመቤታችን የተወለደችበትን ቀን ሁላችን ምእመናን በፍጹም ፍቅርና ደስታ እናከብረዋለን፡፡

 

ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ለተዋሕዶ ከመረጣት ከዓለመ አንስት ተለይታ በንጽሕና በቅድስና አጊጣ የመመኪያችን ዘውድ ከሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ይክፈለን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የቀኝ ዐይን – ድንግል ማርያም

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ  ምንዳቤ ወአጸባ ለዐይን እምቀራንባ፤ አንቲ ውእቱ ረዳኢተ ያዕቆብ በቤተ ላባ፤ በኩሉ ኅሊናሃ ወበኩሉ አልባባ፤ዘኢታፈቅረኪ ነፍስ ትሠሮ እምሕዝባ፡፡

 የነገረ ማርያም ሊቅ(Marian Doctor)እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን በብዙ ምሳሌ እየመሰለ፣ እየተረጎመና እያመሰጠረ ብዙ ጊዜ አመስግኗታል፡፡ ምንም እንኳን እኛ የምናውቀው የምስጋና ድርሰቱ ለጸሎት የምንጠቀምበት ውዳሴ ማርያም ቢሆንም ከትርጓሜና ከስብከቶቹ ውጪ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስንኝ ያላቸው የምስጋና ድርሰቶችን(Hymns) መድረሱን ታሪክ ጸሐፊው ሶዝመን መዝግቦልናል፡፡ ከነዚህ የምስጋና ድርሰቶቹ መካከልም ‹‹በእንተ ልደት››(On Nativity) እና ‹‹በእንተ ቤተ ክርስቲያን››(On the Church)በተባሉ ትልልቅ ድርሰቶቹም እመቤታችንን ደጋግሞ ያመሰግናታል፡፡

በተጠቀሱት ሁለቱም ድርሰቶቹ እመቤታችንን ለማመስገን ከተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ውስጥ አንዱ “ዐይን” ነው፡፡ ሊቁ ስለ ቤተክርስቲያን በደረሰው የምስጋና መዝሙሩ ውስጥ እንዲህ ይላታል፤ ‹‹ዐይን ጥርት የሚለው ከፀሐይ ብርሃን ጋር ተዋሕዶ ከብርታቷ ኃይልን ከውበቷም ነጸብራቅን ሲቀበል ነው፤ በዚህ ጊዜ በግለቷ ይሰነገላል፣ያበራል፤ በውበቷም ያጌጣል፤… ልክ እንደዚሁ ማርያም ዐይን ናት፤ብርሃን (ጌታ) ማደሪያውን በእርሷ አዘጋጀና መንፈሷን ጽሩይ አደረገ፤አሳቦቿን አጠራ፣ኅሊናዋንም ንጹሕ አደረገ፤የድንግልናዋንም ክብር አበራው ››/Hymns on the Church, 36, 1-2/፡፡ ሊቁ በዚሁ ድርሰቱ ውስጥ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ፤ ‹ለዚህ ዓለም ሁለት ዐይኖች ተሰጡት፤ ማየት ያልተቻላት የግራ ዐይን ሔዋን ስትሆን፣ የምታበራው የቀኝ ዐይን ደግሞ (እመቤታችን) ማርያም ናት፡፡በማታየው በጨለማዋ ዐይን ምክንያት መላው ዓለም ጨለመ፤ ስለዚህም ሰዎች በጨለማ ጥላ ውስጥ ሆነው ሲዳብሱ ያገኙት ሁሉ አምላክ ፣ ሐሰቱም እውነት መሰላቸው፡፡ነገር ግን ዓለም እንደገና በሌላ ዐይኑ ባበራና (ባየና) ሰማያዊው ብርሃንም በዚች ዐይን ሰሌዳ ውስጥ ባንጸባረቀ ጊዜ ሰዎችም ቀድሞ ያገኙትን(ያመለኩትን) የኑሮአቸው ውድቀት(የባሕርያቸው መጎስቆል) መሆኑን ተረድተው ወደ ማንነታቸው ተመለሱ (አንድነታቸውን አገኙ)›› ይላል /Ibid, 37, 5-7/::

 

በዚህ መሠረት የእመቤታችን ልደት ዓለም ማየት የጀመረበት ዕለት ነው ማለት ነው፡፡ በርግጥም በነገረ ማርያም መጽሐፋችን ላይ እንደተገለጸው እመቤታችን በቴክታና በጥሪቃ(ሰባተኛ ቅድመ አያቶቿ) በታየው ሕልም መሠረት ዓለምን ሰፍኖበት ከነበረው ድቅድቅ የኃጢኣት ጨለማ እፎይታ የሰጠችው ጨረቃ እርሷ ናት፡፡ በጨለማ ሲያዩት የሚያስፈራውና ሌላ ሌላ የሚመስለው ጉቶው፣ ቁጥቋጦው ፣ ድንጋዩ ፣ ጉብታው….ሁሉ ተራ ነገር መሆኑ የተጋለጠባት፤ ሰዎችም የሰገዱለት ሁሉ አምላክና ጌታ መሆኑ ቀርቶ ድንጋይ ጉብታ መሆኑን ማየት የጀመሩባት፣ ከደገኛው ፀሐይ ክርስቶስ መውጣት በፊት ከረጂሙ ዘመን ጨለማ ጭንቀት የተገላገልንባት ጨረቃ፣ ብርሂት የቀኝ ዐይን እመቤታችን ማርያም ናት፡፡ ስለዚህም ልደቷን የጨለማችን መገፈፍ፣ የዐይናችን ማየት፣ የብርሃናችንም መውጣት ነውና በፍጹም ደስታ እናስበዋለን፤ እናከብረዋለንም፡፡

 

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምን የምናስታውሰውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ብዙ በማመስገኑ ብቻ ሳይሆን ግሩም አድርጎ በማመስጠሩና እንዲህ ያለ ልዩ ልዩ ነገር በማምጣቱም ጭምር ነው፡፡ ለነገሩ ሰው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ከሆነ በኋላ ይህን ሁሉ ማድረጉ አያስደንቅም፡፡ የሆነው ሆኖ የእርሱን ያህል በልዩ ልዩ ሕብረ-አምሳል ያመሰገናት ያለ አይመስልም፡፡ሊቁ በልደት ድርሰቱም‹‹እናትህ አስደናቂ ናት፤ ጌታ ወደ እርሷ ገባና አገልጋይ ሆነ፤ እየተናገረ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ግን ዝም አለ፤ ወደ እርሷ በነጎድጓድ ድምፅ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ጸጥታን አሳደገ፤ የዓለሙ እረኛ ገብቶ በግ ሆኖ ተወለደ፤ እንደ በግም ‹ባ› እያለ ተገለጠ ››/On Nativity, 11, 6/ እያለ አስደናቂነቷን እየደጋገመ ይናገርላታል፡፡አንድ ብቻ ጨምሬ ወደ በዓሉ ልመለስ ፤ቅዱሱ ሊቅ ጌታን እንዲህ ይለዋል፤ ‹‹አንተና እናትህ ብቻ ተወዳዳሪ የሌላችሁ ውቦች ናችሁ፤ በአንተ ላይ ምንም ምን ትንታ(mark) በእናትህም ላይ እንከን(stain) የለም››/Carmina Nisibena, 27,8/፡፡ምንኛ ግሩም ምስጋና፣ እንዴትስ ያለ ፍቅር፣ እንደምንስ ያለ መረዳት ነው? መብቃት ነዋ! መብቃት! ከሌላ ከምን ይገኛል? እርሱ ካልገለጸ፡፡

 

ከቅዱስ ኤፍሬም ሌሎች ድርሰቶች የተነሣሁትና ርእሴንም በእርሱ ምስጋና ያደረግሁት እንዲሁ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ውዳሴ ማርያም እየተጣጣለና ድርሰቱም የእርሱ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ነው (ምነው በሆነና ነበር) ፤ ወይም ደግሞ እርሱ ስለ ሌላ የደረሰውን የእኛ ሰዎች የማርያም ምስጋና ነው ብለው ነው እንጂ እርሱስ እንዲህ አይልም መባል ስለተጀመረ እርሱ ስለ እርሷ ከደረሰዉ ወደ ግእዝ የተተረጎመዉ ትንሽ መሆኑንና ከላይ ለምሳሌነት ካቀርብኳቸው በላይ በውዳሴ ማርያም ምን አዲስ ነገር አለ ለማለት ነው፡፡ ይህችን ታህል ጥቆማ ከሰጠሁ ቦታውም ጊዜውም የጽሑፉም ዓላማ በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር አይደለምና ወደ እናታችን በዓለ ልደት በረከት ላምራ፡፡

 

በርግጥም ፍጹም ልዩ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማይጠረጠር መልኩ ከፍጥረት ሁሉ ልዩ ናት፡፡ በድንግልና ላይ እናትነት፣ በክብረ ድንግልና ላይ ክብረ ወሊድ፣ በድንጋሌ ሥጋ ላይ ድንጋሌ ነፍስና ድንጋሌ ኅሊና የተሰጠው ከእርሷ በቀር ማንም የለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ምንም እንኳ ‹‹በልቧ ትጠብቀው ነበር››/ሉቃ.2፡51/ ተብሎ እንደተጻፈው አትናገረው እንጂ ከፍጥረት ወገን እንደ እመቤታችን እርሱን ለማወቅ የተቻለው ፍጥረት የለም፡፡ ሊቁ ኦሪገን በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜው ላይ እንደገለጸው ስለ አምላክ ፍጥረት ሊያውቀው የሚቻለው የመጨረሻው የእውቀት ደረጃ ላይ የደረሰችው እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ እንደ እርሱ ትርጓሜ እመቤታችን ፍጡር ለፈጣሪው ክብር ሊጨምርለት እንደማይቻለው እያወቀች  ‹‹ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር – ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች›› ያለችው ፍጡር ሊረዳው የሚቻለው የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሳ በዚያ መጠን ማመሰገኗን ስትገልጽልን ነዉ ይላል፡፡በርግጥም በዚህ መጠን ከርሷ በላይ ሊደርስ የሚቻለው እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ የሚያመለክተውም ገና በምድር ሳለች ለፍጥረት የሚገባው ለዚህ የመጨረሻ ብቃት ከደረሰች ከዚህ ዓለም ከሔደች በኋላማ ይልቁንም እንዴት ያለውን የተወደደውንና ከፍጥረት ሁሉ የላቀውን ምስጋና ታቀርብልን ይሆን? ምን ጥርጥር አለው? ልዩ የሆነውን ልታቀርብ የሚቻላት ልዩ እናት፡፡

 

ለዚህም የበቃችው ራሷን ለሰው በሚቻለው ከፍተኛው መጠን እንደምትጠብቅ አስቀድሞ የሚያውቅ ፈጣሪ እርሱም ደግሞ ጠበቃትና ከፍጥረት ወገን ልዩ ሆነች፡፡ ቀድም ብለን የተመለከትናቸው የቅዱስ ኤፍሬም ጥቅሶች የሚያረጋግጡልንም ይህንኑ ነው፡፡ ብርሂት የሆነች ዐይን ለሰውነት መብራት የምትሆነው የፀሐይ ብርሃን ሲዋሐዳት እንደሆነው ሁሉ እርሷም በራሷ ብርሃነ ዐይን ንጽሐ ሥጋ ወኅሊና ላይ የብርሃን ጌታ ብርሃን የተባለ ጸጋዉን አሳድሮ ንጽሕናዋን ወደር የለሽ አደረገዉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ርብቃ ለይስሐቅ የታጨችበትን የሚናገረዉ አንቀጽ ላይ ‹‹ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች››/ዘፍ. 24፣16/ የሚለውን ሲተረጉም ‹ወንድ የማያውቃት› የሚለውን ለሥጋ ድንግልናዋ ከሰጠ በኋላ ‹ድንግልም ነበረች› ያለው ደግሞ ለመደጋገም ሳይሆን በኅሊናዋም ያልባከነች የተጠበቀች ነበረች ሲል ነው ይላል፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለችው ድንግል ርብቃ ድንገት(ለርሷ) ያገኘችውና ማንነቱን እንኳ በውል የማታውቀው ሽማግሌ (የአብርሃም መልክተኛ) ቤተሰቦቿን በጠየቀው መሠረት ወላጆቿ ጠርተው ‹‹ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?›› ብለው በጠየቋት ጊዜ ሳታንገራግር ‹‹እሔዳለሁ›› አለች፤ መሰስ ብላም ተከተለችው፡፡/ዘፍ 24፣58/ እመቤታችን ግን የከበረ መልአክ ተገለጾ ሲያነጋግራት እንኳ የልቡናዋ በር ለወሊድ አልተንኳኳም፡፡ ለልማዱ ሴት ልጅ ‹‹ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ›› ቢሏት ምንም ብትመንን መልአክ ተገልጾ ከነገራት ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል?›› ልትል አትችልም፤ እንዴት እንደሚሆንማ ጠንቅቃ ታውቃለችና፡፡ እመቤታችን ከነዚህ ሁሉ ልዩ ስለሆነች ‹‹እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ›› ስትል ፈጽሞ በታተመና እርሱን በሚያልፍ ኅሊና መልአኩን አስጨነቀችው፡፡

 

እርሱም‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› የምትል ጥቅስ አግኝቶ ፈተናዉን ተገላገለ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በዚህ ጥቅስ ተረትታ ብሥራቱን ስትቀበልም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ- እንዳልከው ይሁንልኝ›› ያለች አንት እንዳልከው የአምላኬ ፈቃዱ ሆኖ እንበለ ዘርዕ፣ እንበለ ሩካቤ ከሆነና ተጸንሶ የሚወለደውም እርሱ ከሆነ ይሁን ይደረግ አለች እንጂ ለሌላው ነገርማ ኅሊናዋ እንደታተመ ነው የቀረው፡፡‹‹ ልጄ ሆይ ስሚ፣ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሽ፣ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፤ እርሱ ጌታሽ ነውና›› (መዝ 44÷12) ሲል አባቷ ዳዊት በትንቢት እንደተናገረው እርሷ ከሔዋናዊ ጠባይ ተለይታለችና፡፡ ሰሎሞንም‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ፤ ነውርም የለብሽም፤ ልቤን በፍቅር አሳበድሽው….›› ያለው ለዚህ  ነበር፡፡

 

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹የታተመች ደብዳቤ›› ያላትም ለዚህ ነው/ኢሳ 28 ፤ 12/፡፡ ምክንያቱም ለልማዱ ደብዳቤ ከተጻፈ በኋላ ይታሸጋል፡፡ ስለ እርሷ የተነገረው ግን  ከታተመ ወይም ከታሸገ በኋላ ተጻፈበት የሚል ነው፡፡ አብ በድንግልና አትሞ ሲያበቃ በውስጧ አካላዊ ቃልን የጻፈባት ማንበብ የሚችሉም(እሥራኤል) ማንበብ የማይችሉም(አሕዛብ) እናነበው ዘንድ አንችልም ታትሟልና (በድንግልና በንጽሕና በክብር በምስጢር) አሉ ብሎ የተናገረላት ደብዳቤ እርሷ ናትና፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸጋ ለተሰጣቸው ሰዎች ብሥራት ሊያደርስ ሲመጣ ይህ የመጀመሪያው አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ለዳንኤልም ሆነ ለጻድቁ ካህን ለዘካርያስ ለእርሷ እንዳደረገው ለእነርሱ መች አደረገ? እነርሱ እጅ ነሱት ሰገዱለት እንጂ እርሱ መቼ እጅ ነሳ ሰገደላቸው? ከዚህ በላይ ልዩ መሆን በእውነት ወዴት ይገኛል፡፡

 

ፍጹም ልዩ መሆኗን ለማስረገጥ ያህል አንድ ነገር ብቻ ላክል፡፡ የጥንቶቹ የቤተክርስቲያን ሊቃዉንት ጌታ ለሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቋት ዘንድ  የሰጠው ሁለት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ አንደኛው ብዙ ጊዜ ሲጠቀስ የምንሰማው ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠው ነው፡፡ይህም ‹‹በጎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ እና ግልገሎቼን አሰማራ››/ዮሐ 21፣15-17/የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከዚህ ቀደም ብሎ በመስቀል ላይ የሰጠው ነው፤ በመስቀል ላይ ጌታ ለዮሐንስ ‹‹እነኋት እናትህ›› ሲል የሰጠው እርሷን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንም ነው ይላሉ፡፡

 

በእነዚህ ሊቃዉንት ትርጓሜ መሠርት  ሁለቱም ራሳቸውን የቻሉ ምስጢራትን ይዘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕጋዊ ስለነበር(በጋብቻ የተወሰነ ማለት ነው) የተሰጠውም አደራ ይህንኑ የሚመለከትና በጎቹን እስከ ገላግልቶቻቸው(ምእመናን) የሚመለከት ነው፡፡ጌታ በወንጌል ‹‹በጎቼ ድምጼን ይለያሉ›› እንዳለው እነዚህ ድምጽ እንጂ ቃል መለየት የማይቻላቸው ምእመናን ናቸው፡፡  የቅዱስ ዮሐንስ ግን ከዚህ ሁሉ በእጅጉ ይለያል፡፡ምክንያቱም እመቤታችን ራሷ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ብቻ ሳትሆን የፍጹማን ደናግልም ምሳሌ ናት፡፡ ስለዚህ ከድምጽ ያለፈ ቃላትን ምስጢራትን መለየት የሚቻላቸው ፍጹማንን የሚመለከተው አደራ የተሰጠዉ ለበቃው ብቻ ሳይሆን ለፍጹሙ ድንግል ለዮሐንስ ነዉ፡፡ ስለዚህ እመቤታችንን መግፋት ቤተክርስቲያንን መግፋት ነው፡፡እርሷንም በቤቱ ማስተናግድ የሚቻለው ዮሐንስን የመሰለ ንጹሕ ድንግል ነው፡፡

 

ቅዱስ  ቅዱስ አትናቴዎስ እንደሚለው ጌታ የሰጠው ድንግሊቱን ለድንግል፣ ድንግሉንም ለድንግል፤ ንጹሕንም ለንጹሕ ነው፡፡ መላእክት ሲጠብቋት ከኖሩ በኋላ መልአክ ለመሰለ ሰው ሰጣት እንጂ ለሌላ አልተሰጠችም፤ ሊቀበላት የሚቻለውም የለም፡፡በተለይ ኦሪገን ይህንኑ በተረጎመበት አንቀጹ ስለ ቅዱሱ ብቃት ሲናገር  ለእርሷም ‹‹እነሆ ልጅሽ›› አላት እንጂ ‹‹ልጅ ይሁንሽ›› አላላትም፤ ምክንያቱም ዮሐንስ በዚያ የመከራና የጭንቀት የፍርሃት ቀን በዕለተ ስቅለት ሳይፈራ ሳይሰቀቅ በእግረ መስቀሉ የተገኘው ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹እኔም አሁን ሕያዉ ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል›› /ገላ 2፣20/ እንዳለዉ ዮሐንስ ራሱን ክዶ ስለነበር ለራሱ እየኖረ አይደለምና በእርሱ የሚኖረው ጌታ ነው፡፡ ‹‹አነሆ ልጅሽ›› ያላትም በእርሱ አድሬ ያለሁት እኔ ነኝ ማለቱ ስለሆነ ከእርሷ ሰው ከሆነ በኋላ ለማንም አልሰጣትም፤ በዮሐንስ አድሮ የተቀበላትም ራሱ ነው፤ ከዚያ በኋላ እርሷን ሊቀበል የሚቻለው የለምና ይላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው እንኳንስ የእርሷን ነገር ለመንቀፍ ቀርቶ ለማመስገንም ትሰጠው ዘንድ ከፈለገ እንደ ዮሐንስ ራሱን በንጽሕና ይጠብቅ ፣ራሱንም ፈጽሞ ይካድ ባይ ነው፡፡

 

የአሁኖቹ ሰዎች እርሷን ባይቀበሉ፣ በእርሷ አማላጅነት ባያምኑ ለምን እንደነቃለን? እነዚህ በትንሽ ነገር እንኳን መታመን የማይቻላቸው የእርሷን ነገር ይረዱ ዘንድ ታላቁንና ሰማያዊውን ምስጢር ማን አደራ ሊሰጣቸው ይችላል? አንዳንድ የዋኃን ደግሞ መሠርይ ተሐድሶዎች ስለ እርሷ የዘመሯቸውን መዝሙር ተብየ ዘፈኖች እየተመለከቱ ይታለላሉ፡፡ ይህ መናፍቃኑ ስለ እርሷ የሚሉትን መንገድ የተከተለ በእነርሱ ወዝ የታሸ ስለሆነ ተወዳጅ መሥዋዕት አይደለም፡፡ በኦሪት አንበሳው፣ ተኩላው፣ ቀበሮው፣ … የመሳሰለው  አውሬ የገደለውን ሁሉ እንኳን ለመሥዋዕት ልናቀርበው ቀርቶ ልንበላውም የተከለከለ ነው፡፡ ይህም ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት አውሬዎች የተባሉት (አጋንንት፣ ርኩሳን መናፍስት፣ መናፍቃን፣…. ደሙን ያፈሰሱትን ወይም በእነርሱ) የተሰዋውን ሁሉ እንኳን ለእግዚኣብሔር ማቅረብ ለእኛም መንካት መርከስ ነው ማለት ነው፡፡ ‹አውሬ የቧጨረውንም አትንካ› የሚል ንባብም ይገኛል፤ ይህ ሁሉ ከእነርሱ የተነካካውን በዚህ ዓለም የዘፈንና የረከሰ መንፈስ የጎሰቆለውን ምንም ለዐይንህ ቢያምርህ (በዘፈን ላደገ ሁሉ የእነርሱ የሚያምረው መሆኑ አይጠረጠርም) ፈጽመህ አትንካ ተብለን ታዘናልና መልከስከስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ግጥሙ በኑፋቄ ዜማው በዘፈን ርኩሰት የተቧጨረ ርኩስ ነውና፡፡እርሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የቤተክርስቲያናችንም ስጦታ ስለሆነች በእውነት ልዩ ናትና ይህን በመሰለ መልኩ የተቧጨረውን አናቀርብም፡፡

 

እንግዲህ ዛሬ ተወለደች የምንለው ይህችን ልዩ ድንግል ነው፡፡ስለዚህም የእርሷን በዓለ ልደት ማክበር ከዚህ ሁሉ በረከት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በእርሷ በኩል ለባሕርያችን ያደረገውንም ክብር ማወቅና መቀበል ጭምር ነው፡፡

 

ከበዓሉ ምን እናገኛለን? የእርሷስ በዓል አልበዛምን?

አንዳንድ ሰዎች በእኛ ቤተክርስቲያን የጌታ በዓል አንሶ የእመቤታችን የበለጠ፤ እኛም ከርሱ ይልቅ ለርሷ የምናደላ የሚመስላቸው ቁጥራቸው በርከት ማለት ጀምሯል፡፡ ያለማወቅ ነውና አይፈረድባቸውም፡፡ ለነቀፋም የተሰለፉ ስለሆነ በ‹ምሰለ ፍቁር ወልዳ-ከተወደደው ልጇ ጋራ› በምንለው ሥዕል ውስጥ እንኳን በሥዕሉ መጠን እየመሰላቸው ጌታ ያነሰ የሚመስላቸው ማስተዋል የራቃቸው ስለሆኑ በእነርሱ አንገረምም፡፡በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ድረስ ከእናቱ ጋር መሰደዱን፣ ከኅዳር ፲፬ ጀምሮ እስከ ልደቱ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ ትንቢት የተናገሩ የነቢያትን ጾም እየጾምን እርሱን እናስባለን፡፡ ከልደት እስከ ዐቢይ ጾም ድረስም በሥጋዌ፤ በአንድነት በሦስትነት መገለጡ አስተርእዮ እየተባለ ይታሰባል ይሰበካል፡፡ ከዚያም ዐቢይ ጾም ይገባል፤ ሁለንተናችን እርሱን በማሰብ ይሰበሰባል፤ ቃለ እግዚአበሔሩም ይህንኑ ያዘክራል፡፡ በትንሣኤውም ሃምሳ ቀናትን እንደ አንድ ቀን እንደ ዕለተ ትንሣኤው በመቁጠር ትንሣኤውን እንሰብካለን፡፡ ከዚህ በማስከተልም ርዕደተ መንፈስ ቅዱስን በዓለ ጰራቅሊጦስን በጾም እናከብራለን፡፡በየወሩም በዓለ እግዚእ፣ መድኃኔዓለም፣ ኢየሱስ፣ አማኑኤል…. እያልን ከዘጠኙ ዓበይትና ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት በተጨማሪ በየአጥቢያቸው የሚታሰቡት ትዝ አይሏቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በየሳምንቱ ሁለት ቀናትን (ረቡዕ እና አርብ) በጾም ሁለት ቀናትን (ቀዳሚትንና እሑድን) በበዓል ለክርስቶስ መታሰቢያ የሰጠች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን የእኛይቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆኗን አያስተውሉም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ የማርያም በዓል ከጌታ በዓል ይበልጣል ማለትን ምን ዓይነት አለማስተዋል ልንለው እንችላለን? ቢሆንስ በቅዱሳን በዓል ዋናው ተከባሪ ተመሰጋኝ ማን ሆነና ነው ይሄ ሁሉ ጩኸት? ስለዚህ በዚህም ስም አደረግነው በዚያ እግዚአብሔር በአከበራቸው ቅዱሳን ስም እስካደረግነው ድረስ በዓሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፡፡

 

የእመቤታችን በዓለ ልደትም በዚሁ መንፈስ የሚከበር በዓል ነው፡፡ነቢዩ ኢሳይያስ ቀደም ብሎ ‹‹ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ-ከእሴይ ሥር ወይም ግንድ በትር ትወጣለች››/ኢሳ 11፤6/ ብሎ ስለ ልደቷም ተናግሮላታል፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘቀዳሚት ድርሰቱ፤ ‹‹ በትረ ሃይማኖት ዘኢትጸንን ምስማኮሙ ለቅዱሳን-የቅዱሳን መደገፊያቸው ግያዝ የሱነማዊቷን ልጅ ከሞት ያስነሣባት ዘንድ ከነቢዩ ከኤልሳ ተቀብሎ እየተጠራጠረ እንደወሰዳት ያይደለሽ ጽነት ጥርጣሬ የሌለብሽ የሃይማኖት በትር አንቺ ነሽ›› ብሎ ተርጎሞልናል፡፡ አባ ጀሮምም ይህን የነቢዩን ትንቢት በትር ከግንዱ ላይ ተስተካክሎ የሚወጣ ግዳጂ ለመፈጸም የሚፈልግ ስለሆነ የእመቤታችን ልዩ መሆን ያሳያል ይላል፡፡

 

በርግጥም ሊቃውንቱ እንዳሉት ለቅዱሳን መደገፊያ ለአጋንንት ለመናፍቃን ደግሞ ማባረሪያ የሆነች በትር፤ ድንግል ማርያም፡፡ስለዚህ የእርሷን በዓል ማክበር ከዚህ ጥርጣሬ ከሌለው በረከት መሳተፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ የበዓላት ይልቁንም በክርስትና ጥቅማቸው ምንድን ነው የሚለውን እንመልከትና እንፈጽም፡፡

 

በዓላትን በብዛት እንድናከብር ያዘዘን እግዚአብሔር ነው፡፡የምናከብራቸውም ዝም ብለን አይደለም፡፡በተለይም በብሉይ ኪዳን በዓላት ብዙ የመሥዋዕት እንስሳትን ማቅረብና መሠዋት በጥብቅ የሚፈጸም ትእዛዝ ነበረ፡፡ የዚያ ሁሉ መሥዋዕትም ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማስገኘት ነበር፡፡/ዘሌ ፲፯፣፲፩/ በአጭሩ በዓላቱን የማክበሩ ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማሰገኘት ነው ማለት ነው፡፡በዚህ መሠረታዊ ምክንያት በእያንዳንዱ የኦሪት በዓል እጅግ ብዙ የመሥዋዕት እንስሳት ይቀርቡ ነበር፡፡በኦሪት በየዕለቱ ሁለት ሁለት ጠቦቶች፣ በየሰንበቱ ሁለት ተጨማሪ የበግ ጠቦቶች፣በየመባቻው ደግሞ ለየዕለቱ ከሚቀርበው በተጨማሪ ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ሰባት የአንድ ዓመት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ፍየል ይቀርብ ነበር፡፡ የዓመታዊ በዓላት ደግሞ ከዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ለምሳሌ የዳስ በዓሉን ብቻ ብንመለከት ከዕለቱ፣ ከሰንበቱና ከመባቻው እንዲሁም በፈቃድ ከሚቀርቡት በተጨማሪ 73 ወይፈኖች፣ 136 አውራ በጎችና ጠቦቶች፣ 10 አውራ ፍየሎች ይቀርቡ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን የእህሉን ቁርባንና ሌላውን መሥዋዕት(ለኃጢኣት ፣ ለበደል፣….የሚባሉትን) ሳይጨምር ነዉ/ዘጸ ፳፱፣፴፰፣ ዘሌ ፳፬፣፭-፱፣ ዘኁ ፳፰፣፱-፲፭፣ዘኁ ፳፱/፡፡

 

‹‹ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና››/ዕብ 10፣1 / ተብሎ እንደተጻፈ እነዚህ ሁሉ ግን ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።›› /ዕብ 5፣ 12-15/ እንዳለው ሊቃውንቱ ለእኛ ወተት ወተቱን እየመገቡ ጠንካራውን ምግብ አላቀረቡልንም ነበር፡፡ አሁን ግን እስኪ ይህን እንኳ እንሞክረው፡፡

 

በኦሪት እንደተጻፈው በፋሲካ የሚሠዋው ልዩ የድኅነት መሥዋዕት በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡‹‹በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ›› /ዮሐ 1፣ 26/።ተብሎ ተጽፎአልና፡፡በሌሎቹ በዓላት የምናቀርባቸው ደግሞ ቀደም ብለን እንዳየነው ወይፈኑ፣ አውራ በጉ፣ ፍየሎቹ(ወንድም ሴትም ነው የሚቀርበው)፣ ሌላው ሁሉ የማን ምሳሌ ነው ማለታችን አይቀርም፡፡ ይህ ሁሉ የበዓል መሥዋዕት የቅዱሳን ምሳሌ ነው፡፡ ‹‹እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን›› /መዝ 44፣12/ ተብሎ ትንቢትም ተነግሮላቸዋልና።ጌታም በወንጌል ‹‹ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል›› /ማቴ 23፣35/ ሲል እንደተናገረው ቅዱሳን ለእምነታቸው መሥዋዕት ሆነው ቀርበዋል።ደማቸውንም አንዱ እንደ ፍየል፣ ሌላው እንደ ወይፈን፣ ሌላውም እንደ አውራ በግ አፍስሰዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ የመሥዋዕት ዓይነቶች ለተለያየ የኃጢኣት ማስተሥረያ እነደነበሩት እነዚህም ድኅነትን ለመፈጸም ከተሰዋው በግ ከጌታ በኋላ ለምናምን ሁሉ ሥርየተ ኃጢኣትን እናገኝ ዘንድ የሚማልዱ ስለኛም ጭምር ደማቸውን ያፈሰሱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የሌላው ጊዜ የመሥዋዕት እንስሳ የፋሲካቀውን በግ ሊተካው እንደማይችልና የመሥዋዕቱም ዓይነት ፈጽሞ የተለያየ እንደ ሆነው ሁሉ የቅዱሳኑ መሥዋዕትነትና ሰማዕትነትም እንዲሁ የተለያየ መሆኑና የእነርሱም የጌታችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሊተካ የማይችል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡እርሱ ኃጢኣትህ ተሠረየልህ(ሽ) እያለ ይቅር ሲል እነርሱ ግን የሚያስተሠርዩልን እየጸለዩ ነውና፡፡ ከዚህ በመለስ ግን የጥንቶቹ ሊቃውንት እንደተረጎሙልን የእነርሱ ተጋድሎና ሰማዕትነት የእኛ የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መሥዋዕቶች ናቸው፤ ስለእነርሱም ሥርየተ ኃጢኣትን እንቀበላለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል  ››/ዕብ 4፣6/ ሲል የተናገረዉው ይህን የሚያረጋግጥልን ነው፡፡

 

ቀደም ብለን እንዳየነው የመሥዋዕቱ እንስሳት የበዙት ለእሥራኤል ለኃጢኣታቸው አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነው ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ለምንኖር ለእኛም ብዙ ቅዱሳን መኖራቸው ይጠቅመናል፣ ኃጢኣታቸንም ያስተሠረይልናል፡፡ የመሥዋእቱ እንስሳት በሙሉ የተቆጠሩና የታወቁ እንደሆነው ሁሉ ቅዱሳኑም ምን ቢበዙም እንዲሁ የታወቁና የተቆጠሩ ናቸው፡፡

 

ዳዊት አባታችን ‹‹ዘይኌልቆሙ ለክዋክብት በምልኦሙ፣ ወይጼዉዖሙ ለኩሎሙ በበአስማቲሆሙ- ክዋክብትን በምልዓት ይቆጥራቸዋል፣ ሁሉንም በየስማቸዉም ይጠራቸዋል››/መዝ 146፣4/ ሲል እንደተናገረዉ ክዋክብት የተባሉ ቅዱሳን ሁሉ በእርሱ ዘንድ በባለሟልነት በቃል ኪዳን የታወቁ በመሥዋዕትነትም የተቆጠሩ ናቸዉ፡፡ ያ ሁሉ የ መሥዋዕት እንስሳ ፣ የጧቱና የሰርኩ፣ የሰንበቱና የመባቻዉ፣ የዓመት በዓላቱ፣ የየግለሰቡ የኃጢኣቱ፣ የበደሉ፣ የመንጻቱ፣…በዓይነት በዓይነት እንደሚታወቅ በእርሱም ዘንድ ተቀባይነት እንዳለዉ ሁሉ የየዕለቱ ቅዱሳንም እንዲሁ ይተወቃሉ፤ ጸሎታቸዉና ምልጃቸዉም በእርሱ ዘንድ የከበረ ነዉ፡፡ እመቤታችን ደግሞ ከነዚህ ሁሉ በግንባር ቀደምነት የምትጠራ ልዩ መሥዋዕታችን ናት፡፡በሁለተኛዉ ክፍለዘመን መጨረሻ የነበረዉ የሰረዴሱ መልይጦን/Melito of Sardis/  በፋሲካ መዝሙሩ ላይ እመቤታችንን የመሥዋዕቱን በግ የወለደችልን ንጽሕት ሴት በግ (fair ewe) ይላታል፡፡ ስለዚህ የእመቤታችን በዓለ ልደት ከብሉይ ኪዳን ሰዎች የተሻለ ሥርየተ ኃጢኣት የምናገኝበት ነዉና ከነዚያ በተሻለ በዓላችንን መንፈሳዊ አድርገን እናክብር፤ ከመንፈሳዊ በረከትም እንካፈል፡፡የደራሲዉንም ምስጋናና ምልጃ በመሰለ ምስጋና እንዲህ እንበላት፤‹‹ምንተኑ አዐስየኪ ዕሴተ፤በእንተ ኩሉ ዘገበርኪ ሊተ፤ማርያም ሠናይት ዘታፈቅሪ ምሕረተ፤ሶበሰ ተታአቀቢ ዘዚኣየ ኃጢኣተ፤ እምኢሐየዉኩ አሐተ ሰዓተ›› እያልን ለእርሷ በሚገባ ምስጋና እናመስግናት፡፡ ከዚህ የወጣ ሰዉ በመጀመሪያ እንደተመለከትነዉ ብርሂት ቀኝ ዐይኑን እንደገና እያሳወረ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ እኛስ ለባሕርያችንን መመኪያ እርሷን የሰጠንን እግዚአብሔርን ‹‹ብርሂት የቀኝ ዐይን ድንግል ማርያምን ›› በዚህ ዕለት የሰጠኸን፣ ከዚህ ዓለም የድንቁርናና የኃጢኣት ጨለማም የገላገልከን ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን፤ አንተ ለመረጥካትና ላከበርካት ለእናትህም ምስጋና ይድረሳት እያልን አፋችንን ሞልተን እናመሰግናለን፡፡ ቀይ ዕንቁ እምነት ገንዘባቸዉ ያልተሰረቀባቸዉ ወይም በአዉሬዉ ዲያብሎስ ያልተቧጨሩት ሁሉ አብረዉን ያመሰግናሉ፡፡ ቀኝ ዐይናችን ሆይ ዛሬም በአንቺ ብርሃን እናያለንና እናመሰግንሻለን፡፡ እንኳን አንቺን አባትሺን አብርሃምን የሚባርኩት እንደሚባረኩ ልጂሽ አስቀድሞ በሙሴ በኩል በኦሪት ነግሮናልና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

“አብዝቶ የመመገብ ጣጣው”

(በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

ግንቦት 30/2003 ዓ.ም.

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

መግቢያ

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የዮሐንስን ወንጌል በተረጎመበት በ21ኛው ድርሳኑ “ ጌታችን በእናታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ጥያቄ በቃና ሰርግ ላይ ስለምን ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት እንደቀየረው  ከአብራራ በኋላ ከዛሬ 1500 ዓመት በፊት በአሁኑ ጊዜ እንደ አዲስ ግኝት ተደርገው የሚታዩትን አብዝቶ በመመገብ የሚመጡትን የጤና ጉድለቶች ጽፎልን እናገኛለን ፡፡ ጽሑፉ ተተርጉሞ እንዲህ ቀርቦአል።


ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ውሃውን ወደ ወይን ጠጅነት ያኔ እንደቀየረ ዛሬም እኛን ድካማችንንና እንደ ወራጅ ውሃ በአንድ ቦታ ጸንቶ መቆየት የተሣነውን የሥጋ ፈቃዳችንን ከመቀየር አልተቆጠበም ፡፡ ዛሬም አዎን ዛሬም ልክ እንደ ወራጅ ውሃ ቀዝቃዛ ፣የፈጠነና ፣ ያልተረጋጋ ጠባይ ያላቸው ሰዎች አሉ ፡፡ እነዚህን ፈቃዶቻችንን ወደ ጌታችን እናምጣቸው ፤ እርሱ ወደ ወይንነት ይቀይራቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ ውኃ ሆነው ከእንግዲህ አይቀጥሉም ፡፡ ነገር ግን ለራሳቸውና ለሌሎች ደስታን የሚሰጡ አካላት ይሆናሉ ፡፡

ባልተረጋጋ ውሃ የተመሰሉት እነማን ናቸው ? ለዚህ ከንቱ ዓለም ሕሊናቸውን ያስገዙ ወገኖች ፣ የዚህን ዓለምን ቅምጥልነት ፣ አለቅነትንና ክብርን የሚሹ ናቸው፡፡ እነዚህ ፍቃዶቻችን እንደውኃ የሚፈሱ ፣ ፈጽሞ ያልተረጋጉ ፣ ለአመፃ የሚፋጠኑ ቁልቁል የሚምዘገዘጉ ውኆች ናቸው ፡፡

 

ዛሬ ሀብታም የነበረው ነገ ደሃ ይሆናል ፡፡ በአንድ ወቅት ዝናው ሲነገርለት፣ የተጌጠና የተንቆጠቆጠ ልብስ ለብሶ በሰረገላ ላይ የሚሄድና ብዙ አጃቢዎች የነበሩት ሰው ፣ ያለፈቃዱ ያን የተዋበ መኖሪያውን ተቀምቶ ወደ ወይኒ ተጥሎ ይገኛል ፡፡ ለሥጋው ደስታ የሚተጋው ሆዳሙ ደግሞ የሥጋ ፈቃዱን ከሞላ በኋላ ሆዱ ሳይጎድልበት ለአንድ ቀን መቆየት አይቻለውም ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ምግቦች ከሆዱ ሲጠፉ ወደ ቀድሞው ምቾቱ ለመመለስ ሲል ከፊት ይልቅ አብዝቶ ይመገባል ፡፡ አመጋገቡም ሁሉን ጠራርጎ እንደሚበላ እንደጎርፍ ውሃ ነው ፡፡ በዝናብ ወቅት የሚነሣው ጎርፍ አስቀድሞ የነበረ ውሃ በከፈተለት ጎዳና ገብቶ ቦታውን ሁሉ ያጥለቀልቀዋል ፡፡ እንዲሁ በሆዳሙም ዘንድ እንዲህ ይሆናል ፡፡ አስቀድሞ የነበረው ሲጠፋ እርሱ በቀደደው ሌሎች  የሥጋ ፍቃዶች በዝተው ይገባሉ ፡፡

 

ምድራዊው ነገር ይህን ይመስላል ፤ መቼም ቢሆን የተረጋጋ አይደለም ፡፡ መቼም ቢሆን አንዱ ሌላውን እየተካ የሚፈስ እና የሚቸኩል ነው ፡፡ ነገር ግን የቅምጥልነትን ኑሮ በተመለከተ ጣጣው በከንቱ መባከን ወይም መቻኮል ብቻ አይደለም ፡፡ ሌሎችም እኛን ከመከራ የሚጥሉን ችግሮችም አሉበት ፡፡ ቅምጥልነት ባመጣብን ጣጣ የሰውነት አቅማችን ይዳከማል ፣ እንዲሁም የነፍስ ጠባይዋም ይለወጣል ፡፡ ከባድ ጎርፍ ወንዙን በደለል ወዲያው እንደማይሞላው  ፣ ቀስ በቀስ ግን እንዲሞላው ፣ እንዲሁ ቅምጥልነትና ዋልጌነት እንደ አልማዝ ብርቱ የሆነውን ጤንነታችንን ቀስ በቀስ ውጦ ያጠፋዋል ፡፡

 

ወደ ሐኪም ዘንድ ሄደህ ብትጠይቅ የበሽታዎች ሁሉ ምንጫቸው አብዝቶ ከመመገብ እንደሚመነጩ ይነግሩሃል ፡፡ ጠግቦ አለመብላትና ለሆድ የማይከብዱ ምግቦችን መመገብ ለጤንነት እናት ነው ፡፡ ስለዚህም የሕክምና ባለሙያዎች የጤንነት እናት ብለው ይጠሩታል ፡፡ እናም ጠግቦ አለመብላት የጤንነት እናት ከሆነ  ፣ አብዝቶ መመገብ ደግሞ የበሽታዎች ሁሉ እናት እንደሆነ በዚህ ይታወቃል፡፡ አብዝቶ መመገብ ሰውነታችንን አዳክሞ በሕክምና ባለሙያ እንኳ ለማይድን በሽታ አጋልጦ ይሰጠናል ፡፡

 

አብዝቶ መመገብ ለሪህ ፣ ለአእምሮ ውስጥ የደም መፍሰስ ፣ ለዐይን የማየት ኃይል መቀነስ ፣ ለእጅ መዛል ፣ ለአካል ልምሾነት  ፣ ለቆዳ መንጣት (ወደ ቢጫነት መቀየር  ፤ በተለምዶ የጉበት በሽታ ለምንለው ምልክት ነው ተብሎ ይታመናል ) ስጉና ድንጉጥ መሆን ፣ ለኃይለኛ ትኩሳት እና ከጠቀስናቸው በላይ ለሆኑ ሌሎች ሕመሞች ያጋልጣል ፡፡ በዚህ የሚመጡትን የጤንነት ጠንቆች በዚች ሰዓት ውስጥ ዘርዝሮ ለመጨረስ ጊዜው አይበቃም ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሕመሞች በተፈጥሮአችን ላይ የሚከሰቱት መጥኖ በመብላት ወይም በጾም አይደለም ፡፡ ነገር ግን ከሆዳምነታችንና ከአልጠግብ ባይነታችን የተነሣ የሚመጡብን ናቸው ፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ በነፍሳችን ላይ የሚከሰቱብንን  በሽታዎች ብንመለከት ዋዘኝነት ፣ ስንፍና ፣ ድንዛዜ ፣ የሥጋ ፍትወቶቻችን ማየል፣ እነዚህንና የመሳሰሉ ሕመሞች ነፍሳችንን ያጠቁዋታል ፡፡ ለእነዚህ ሁሉ ምንጫቸው ሳይመጥኑ አብዝቶ መመገብ ነው ፡፡ ከእንዲህ ዐይነት ቅጥ ያጣ አመጋገብ  በኋላ የቅምጥሎች ነፍስ ክፉ አውሬዎች ሥጋዋን ተቀራምተው ከተመገቡዋት አህያ ያልተሻለች ትሆናለች ፡፡ ቅምጥሎችን ስለሚጠብቃቸው  ሕመሞችና ስቃዮች ጨምሬ ልናገርን ? ከብዛታቸው የተነሣ ዘርዝሬ መጨረስ አይቻለኝም ፡፡

 

ነገር ግን በአንድ ማጠቃለያ አሳብ ሁሉንም ግልጽ አድርጌ ማስረዳት እፈልጋለሁ ፡፡ እንዲህ ከሚያደርጉ ከቅምጥሎች ማዕድ ማንም ደስ ብሎት አይመገብ ፡፡ አስቀድመን እንደተነጋገርነው ጾምና መጥኖ መመገብ የደስታና የጤንነት ምንጮች ሲሆኑ ያለቅጥ መመገብ ግን የበሽታና የደስታ ማጣት ሥር እና ምንጭ ናቸውና ፡፡

 

ሁሉ ነገር ከተሟላልን ፍላጎት የለንም ፡፡ ፍላጎት ከሌለ ደግሞ እንዴት ደስታን ልናገኛት እንችላለን ? ስለዚህም ድሆች ከባለጠጎች ይልቅ የተሻለ ማስተዋልና ጤና ያላቸው ብቻ አይደሉም ፣ ነገር ግን ታላቅ በሆነ ደስታ ውስጥ የሚኖሩ ጭምር ናቸው ፡፡ ይህንን ከተረዳን ከመጠጥና ከቅምጥልነት ሕይወት ፈጥነን እንሽሽ ፣ ከማዕዱ ብቻ አይደለም ፣ ከዚህ ሕይወት ከሚገኙት ፍሬዎች ሁሉ እንሽሽ ፡፡  እነርሱን በመንፈሳዊ ሕይወት በሚገኘው ደስታ ለውጠን በቅድስና እንመላለስ  ፡፡ ነቢዩ “ በእግዚአብሔር ደስ ይበላችሁ እርሱ የልብህን  መሻት ይሰጥሃል”(መዝ.36፥4)  እንዳለው በጌታ ደስ ይበለን ፡፡ በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም በእርሱ በእግዚአብሔር መልካም ስጦታ ደስ ይለን ዘንድ የሰው ልጆችን በሚያፈቅረው በኩል ለእርሱ ለእግዚአብሔር አብ ለመንፈስ ቅዱስም ክብር ይሁን  እስከዘለዓለሙ ፡፡ አሜን !!

 

በነገራችን ላይ የሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም የፍልስፍና ምሁራን(ተማሪዎች) በዚህ በቅዱስ ዮሐንስ ገለጻ ላይ ምን ይላሉ ? በ mkwebsitetechnique@gmail.com ጻፉልን።

 

የትንሣኤው ትርጉም በዓሉና አከባበሩ

ከሊቀ ትጉሃን ኀ/ጊዮርጊስ ዳኘ
በጠ/ቤተ ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ምክ/ሓላፊ

  • «ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡

  •  መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡

  • «ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡

  •  «ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡

  • «ትንሣኤ» የሚለው ቃል የግእዝ ቋንቋ ነው፡፡

  • መገኛ ቃሉም «ተንሥአ» = ተነሣ የሚለው ግሥ ይሆናል፡፡

  • «ትንሣኤ» ማለት ታዲያ = መነሣት፣ አነሣሥ ሐዲስ ሕይወት ማግኘት ማለትን ያመለክታል፡፡

  • «ትንሣኤ» በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በየመልኩ፣ በየዐይነቱ ሲተረጐም ዐምስት ክፍል አለው፡፡

  • አንደኛው «ትንሣኤ» ኅሊና ነው፡፡ ይህም ማለት ተዘክሮተ እግዚአብሔር ነው፡፡

  •  ሁለተኛውም «ትንሣኤ» ልቡና ነው፡፡ የዚህም ምስጢሩ ቃለ እግዘብሔርን መስማትና በንስሐ እየታደሱ በሕይወት መኖር ነው፡፡

  •  ሦስተኛው «ትንሣኤ» ለጊዜው የሙታን በሥጋ መነሣት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ድጋሚ ሞት ይከተለዋል፡፡

  • አራተኛው «ትንሣኤ» የክርስቶስ በገዛ የባሕርይ ሥልጣኑ ሞትን ድል አድርጎ መነሣት ነው፡፡ የእርሰ ትምህርታችንም መሠረት ይኸው እንደሆነ ይታወሳል፤ ብለን ተስፋ አናደርጋለን፡፡

  • ዐምስተኛውና የመጨረሻው «የትንሣኤ» ደረጃም የባሕርይ አምላክ የጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን «ትንሣኤ» መሠረት ያደረገ «ትንሣኤ ዘጉባኤ» ነው፡፡ ይህም ከዓለም ኅልፈት በኋላ ሰው ሁሉ እንደየሥራው ለክብርና ለውርደት፣ ለጽድቅና ለኩነኔ በአንድነት የሚነሣው የዘለዓለም ትንሣኤ ይሆናል፡፡

  • ወደተነሣንበት ዐላማ ስንመለስ የትንሣኤ በዓል በቃሉም ምስጢር በይዘቱም ስለሚመሳሰሉ ጥላው ምሳሌውም፣ ስለሆነ «ፋሲካ» ተብሎ ይጠራል፡፡

  • «ፋሲካ» ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ «ፌሳሕ» በጽርእ በግሪክኛው «ስኻ» ይባላል፡፡ ይህም ወደ እኛው ግእዝና ዐማርኛ ቋንቋችን ሲመለስ ፍሥሕ ዕድወት = ማዕዶት፣ በዓለ ናእት = የቂጣ በዓል፣ እየተቸኮለ የሚበላ መሥዋዕት፣ መሻገር መሸጋገር ማለት ነው፡፡ ነጮቹ በእንግሊዝኛው «ስኦቨር» ይሉታል የዚህም ታሪካዊ መልእክቱ በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው በዓለ ፋሲካ እስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ የባርነት ቀንበር ወደነፃነት የተላለፉበት፣ ከከባድ ሐዘን ወደ ፍጹም ደሰታ፣ የተሸጋገሩበት በዓል ነበር፡፡ በዚህ ኦሪታዊ ምሳሌ በዓል አሁን አማናዊው በዓል «ትንሣኤ» ተተክቶበታል፡፡

  • ፋሲካ፣ በዓለ ትንሣኤ በዘመነ ሐዲስ እስራኤል ዘነፍስ የሆኑት ምእመናነ ክርስቶስ ትንሣኤውን የሚያከብሩበት ዕለት ሆኖ በእርሱ ትንሣኤ

  • ከኀጢአት ወደ ጽድቅ፣

  • ከኀሳር = ከውርደት ወደክብር፣

  • ከጠላት ሰይጣን አገዛዝ ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣

  • ከአደፈ፣ ከጐሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲሰ ሕይወት የተሻገሩበት ታላቅ መንፈሳዊ የነፃነት በዓል ነው፡፡

– ክርስቲያኖች የትንሣኤን በዓል በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስሜት ያከብሩታል፡፡ ስለዚህም ከበዓላት ሁሉ የበለጠ ሆኖ ይታያል፡፡
– መድኀኒታችን ሞትን በሞቱ ድል መትቶ፣ ስሙና መቃብርን አጥፍቶ በሥልጣኑ የተነሣው መጋቢት 29 ቀን በ34 ዓ.ም እንደሆነ ታሪከ ቤተ ከርስቲያን ያስረዳል፡፡
– የትንሣኤ በዓል መከበር የጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያትና በሰብዐ አርድእት፣ ኋላም በየጊዜው በተነሡት ተከታዮቹ ምእመናን ነው፡፡ ድምቀቱና የአከባበር ሥርዐቱ ይበዛ ይቀነስ እንደሆን እንጂ መከበሩ ተቋርጦ አያውቅም፡፡ «እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን»
– ሲወርድ ሲወራረድ ከዚህ በደረሰው ትውፊት መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ግብረ ሕማማቱን ስታነብ ሰንብታ ለትንሣኤ እሑድ አጥቢያ ማታ በ2 ሰዓት «ለጸሎት ተሰብሰቡ» የደወል ድምፅ ታሰማለች፡፡

– ካህናቱ ተሰብስበው ሥርዐቱን በጸሎት ይጀምራሉ፡፡ ሕዝቡም ይሰበሰባል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑንም ይሞላዋል፡፡

– ካህናቱ ሁሉ ለጸሎተ ፍትሐትም፣ ለሥርዐቱም መዝሙረ ዳዊት፣ ነቢያት፣ ሰሎሞንና ውዳሴ ማርያም ከደገሙ በኋላ «ተፈሥሒ ማርያም ለአዳም ፋሲካሁ» የሚለውን ግጥማዊ የደስታ መዝሙር ይዘምራሉ፡፡
– ቀጥሎም ምንባባቱና ሌላውም ሥርዐት ከተፈጸመ በኋላ ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ ዲያቆኑ «ወተንሥአ እግዚአብሔር ከመ ዘንቃህ እምንዋም፣ ወከመ ኀያል ወኅዳገ ወይን፣ ወቀተለ ፀሮ በድኅሬሁ = እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፤ የወይን ስካር እንደተወው ኀያል ሰውም፣ ጠላቱን በኋላው ገደለ፡፡» የሚለውን የዳዊት መዝሙር ለመስበክ = ለመዘመር ነጭ ልብሰ ተክህኖ ለብሶ አክሊል ደፍቶ፣ የመጾር መስቀል ይዞ፣ እንደእርሱው ነጭ ልብሰ ተክህኖ በለበሱ ደማቅ የጧፍ መብራት በሚያበሩና ድባብ = ጃንጥላ በያዙ ሁለት ዲያቆናት በግራ በቀኝ ታጅቦ ከመቅደስ ብቅ ብሎ በቅድስት ይቆማል፡፡ መዝ. 77-65 ይህም በጌታችን መቃብር በራስጌና በግርጌ በታዩት መላእክት ምሳሌ ነው፡፡ ዮሐ.20-12
– ዲያቆኑ ከላይ የተጠቀሰውን ምስባክ በረጅም ያሬዳዊ ዜማ በሰበከ ጊዜ ካህናቱ ከበሮ እየመቱና በእርጋታ እያጨበጨቡ ተቀብለው ይዘምራሉ፡፡

– ሕዝቡም የቻለው በዝማሬው ያለበለዚያም በጭብጨባና በልልታ የደስታ ዝማሬው ተሳታፊ ይሆናል፡፡ ይህ ምስባኩ በዲያቆኑ 2 ጊዜ በመላው ካህናትም 2 ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ ዲያቆኑም መላው ካህናትም አንድ ጊዜ ብለው 5 ጊዜ ይሆናል፡፡ 5500 ዘመን ሲፈጸም በጌታችን ሞትና ትንሣኤ ዓለም ለመዳኑ ምሳሌያዊ ማስረጃ ነው፡፡

– ቀጥሎም ካህኑ ትንሣኤውን የሚያበሥር ወንጌል ከማቴዎስ፣ ከማርቆስና ከሉቃስ አውጥቶ ያነባል፡፡ ከዮሐንስ ወንጌል ያለው የትንሣኤው ወንጌል ኋላ ለቅዳሴው ጊዜ ይቆያል፡፡ ዮሐ. 20-1-09
– በማስከተል የዲያቆኑን መስቀል ጨብጦ ከሊቃውንቱ መዘምራን ሥራው የሚመለከተው ወይም የተመደበው ባለሙያ መዘምር «ትንሣኤከ ለእለ አመነ» የሚለውን እስመ ለዓለም ከቃኘ በኋላ ለበዓሉ ተስማሚ የሆነው 2 አርያም ተመርቶ በመቋሚያ ይዘመማል፤ በማስከተልም «ዮም ፍሥሐ ኮነ በሰንበተ ክርስቲያን፣ እስመ ተንሥአ ክርስቶስ እሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ቀድሞ ተለይቶ ተነሥቷልና በሰንበተ ክርስቲያን ዛሬ ደስታ ሆነ፡፡…» የሚለውን አንገርጋሪ ያመለጥናል = ይመራል፡፡ በግራ በቀኝ እየተነሣ መዘምራኑም ይዘምሙታል ይጸፉታል፤ ያለዝቡታል፤ ወዲያውም «ብርሃነከ ፈኑ፤ ለእለአመነ = ለአመነው ብርሃንህን ላክልን፡፡» የሚለውን እስመ ለዓለም እየወረቡ መብራት እያበሩ ዑደት ያደርጋሉ = ቤተ ክርስቲያኑን በውስጥ ይዞራሉ፡፡
– በዚህ ጊዜ «በጨለማ የነበራችሁ ሕዝቦች ኑ የትንሣኤውን ብርሃን እዩ፣ ብርሃኑንም ወስዳችሁ የብርሃኑ ተካፋይ ሁኑ፡፡» እያለች ቅ/ቤተ ክርስቲያን ስታዘጋጅ የሰነበተችውን ጧፍ እያበራች ታድላቸዋለች፡፡ ሕዝቦቹም ካህናቱን ተከትለው በታላቅ ደስታና ድምቀት ዑደት ያደርጋሉ፡፡
– መዘምራኑና ካህናቱ ከዑደት ሲመለሱ «ይእቲ ማርያም» የተባለው የኪዳን ሰላም ይጸፋና ኪዳን ተደርሶ ሲያበቃ እንደ ቦታው ደረጃ ፓትርያርኩ ወይም ሊቀ ጳጳሱ ወይም ደግሞ አለቃው፣ ቆሞሱ፣ ካህኑ ዘለግ ባለ ድምፅ በንባብ «ክርስቶስ ተንሥአሙታን = ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡» ሲል ካህናቱና መዘምራኑ በዐቢይ ኀይል ወሥልጣን = በታላቅ ኀይልና ሥልጣን፡፡» ብለው ይቀበላሉ፡፡
– አሁንም ካህኑ «አሰሮ ለሰይጣን = ሰይጣንን አሰረው» ባለ ጊዜ መላው ካህናት «አግዐዞ ለአዳም = አዳምን ሐርነት ነጻነት አወጣው» ይላሉ፡፡ ቀጠል አድርጎ ቄሱ «ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት» ሲላቸው ሁሉም ካህናት «እምይእዜሰ = ከዛሬ ጀምሮ» ብለው ይቀበላሉ፡፡ ቄሱም «ኮነ ፍሥሐ ወሰላም = ሰላምና ደስታ ሆነ» ብሎ ሦስት ጊዜ ዐውጆ ሲያበቃ «ነዋ መስቀለ ሰላም» እያለ መስቀል ሲያሳልም ካህናትና ሕዝቡም «ዘተሰቅለ ቦቱ መድኀኔዓለም» እያሉ ይሳለማሉ፡፡ ካህኑም «እግዚአብሔር ይፍታ» ይላል፡፡ ግብረ ሕማማት ሲነበብበት ከሰነበተው ጠበልም ይረጫል፡፡ የተረፈውንም ጠበል ሕዝቡ ለበረከት ወደየቤቱ ይወስደዋል፡፡
– ከዚያም ልኡካኑ ለቅዳሴ እየተዘጋጁ ሊቃውንት መዘምራኑ ምስማክ መወድሱን ካዜሙ በኋላ በመቋሚያ ይዘምሙታል፡፡ አያይዞም በዓመት ሦስት ጊዜ የሚዘመረውን «ይትፌሣሕ» የተባለውን መዝሙር ቃኝተው ከዘመሙ በኋላ «ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ፤ ተኀፂባ በደመ ክርስቶስ = ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ ፋሲካውን ታደርጋለች፡፡» እያሉ ይጸነጽላሉ፡፡ አያይዘውም የመዝሙሩን ሰላም ይጸፋሉ፡፡
– ወዲያው መንፈቀ ሌሊት ሲሆን ቅዳሴ ተቀድሶ ይቆረባል፡፡ ከዚያም ዕጣነ ሞገር = በዕጣን ፈንታ ቅኔው ተቁሞ ሠርሖተ ሕዝብ = የሕዝብ ስንብት ከሆነ በኋላ ለመፈሰክ ሕዝቡ ወደየ ቤቱ ይሔዳል፡፡
– ሕዝቡ በየቤቱ፣ ካህናቱም ከቤተ ክርስቲያን በየአካባቢው ባህል በተለይ አክፋዮች መጀመሪያ ቅባት አጥቶ የሰነበተ ሆድ እንዲለሰልስ የተሞቀ የተልባ ጭልቃ ይጠጣና የሹሮ ወጥ በቅቤ፣ በአይብ፣ የበረታም በዶሮ ወጥ፣ ወይም በበግና በከብት ሥጋ ወጥ ይገድፋል፡፡
– በእርጎ፣ በአይብ የተደራረበ እንጀራ በግፍልፍል የሚገድፉም አሉ፡፡ በአንዳንድ የሰሜኑ ሀገራችን ደግሞ የተልባ፣ የኑግና የሱፍ ጭልቃ ከማር ጋር ታሽቶ ከተጠጣ በኋላ በእርጎ፣ በአይብ፣ በወተት፣ በቅቤና ድልህ በተቀባ እንጀራ ይገድፋሉ፡፡
– ሲነጋም ከጾሙ አጋማሽ ጀምሮ ወንዱ ለእርድ የሚሆነውን ሰንጋውን፣ ሲቀልብ፣ በጉን ፍየሉን ሲሞክት ዶሮውን ሲመርጥ፣ ሲገዛ ሲለውጥ፣ ሰንብቶ ነበርና በግልም በኅብረትም ያ ይታረዳል፡፡
– ሴቶችም ቅቤውን ሲያነጥሩ፣ በርበሬውን ሲደልሁ፣ ለእንጀራና ዳቦ የሚሆነውን ዱቄት ሲያዘጋጁ ለጠላ የሚሆነውንም እኸል ሲያሰናዱ አይቡን በልዩ ልዩ ቅመም መጣጣ ሲያደርጉና ባዶ ማለትም ወገሚት የተባለውን በሽንኩርት፣ በጤና አዳም፣ ጣዕሙ እንዳይለወጥ ሲቀምሙ ሰንብተው ዝግጅቱ ተከናውኖ ነበር፡፡
– ጧትም ይህ የመግደፊያ ዝግጅት በየቤታቸው ለሌላቸው ድኾች በየመንደሩ እየተዞረ «እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታላችሁ» እየተባለ ከሥጋውም፣ ከአይቡም፣ ከቅቤውም ከመጣጣሙም፣ ከእርጐውም ይታደላል፡፡
– ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ዳግም ትንሣኤ ድረስ ሕዝበ ክርስቲያኑ «እንኳን ጾመ ልጓሙን ፈታላችሁ» እየተባባለ በመጠራራት ዐብሮ ሲበላ ሲጠጣ ልዩ ልዩ ጨዋታ ሲጨዋወት ለንስሐ አባትና ለሽማግሌዎች ለወዳጅ ዘመድም የአክፋይ ዳቦ፣ ወይም የሥጋ ወጥ ግፍልፍል ሲወስድ ይሰነብታል፡፡
– ይህ በዚህ እንዳለ ከትንሣኤ እሑድ ቀጥለው ያሉት ዕለታት ሰሙነ ፋሲካ ወይም ትንሣኤ እየተባሉ የየራሳቸው ምስጢራዊ ስያሜ አላቸው፡፡ ይኸውም፡-
ሰኞ = ጌታችን በሞትና ትንሣኤው ነፍሳትን ከሲኦል አውጥቶ ወደ ገነት አሻግሮ ለማስገባቱ መታሰቢያ ሆና «ፀአተ ሲኦል ማዕዶት» ትባላለች፡፡ ዮሐ. 19-18 ሮሜ. 5-10-17 የዳግም ትንሣኤው ማግሥት ያለችው ግን ገበሬው፤ ወንዶቹ እርሻ ቁፋሮውን፣ ንግዱን፣ ተግባረ እዱን ሁሉ ሴቶቹ ወፍጮውን፣ ፈትሉን፣ ስፌቱን የሚጀምሩባት ዕለት ስለሆነች «እጅ ማሟሻ» ሰኞ ትባላለች፡፡
ማክሰኞ = የትንሣኤው ዕለት እሑድ ማታ ጌታችን በዝግ ቤት ገብቶ ለሐዋርያት ሲገለጽ ቶማስ ሐዋርያ አልነበረም ኋላ ከሔደበት ሲመጣ ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሣኤውን ቢነግሩት እኔ ሳላይ አላምንም በማለቱ በዚህ ጥያቄው መሠረት በሳምንቱ ጌታችን በድጋሚ ስለተገለጸ ለዚህ መገለጹ መታሰቢያ ሆና ዕለቲቱ «በቶማስ» ተሰየመች፡፡ ዮሐ. 20-24-30
– ረቡዕ = ከሞተና ከተቀበረ አራት ቀን በኋላ ከመቃብር ጠርቶ ላሥነሣው፣ አላዓዛር መታሰቢያ የእርሱንም ተነሥቶ በማየት በጌታችን ብዙ ሕዝብ ስለአመነበት ቀኒቱ «አላዓዛር» ተብላ ትታሰባለች፡፡ ዮሐ. 11-38-46
ኀሙስ = ከላይ በጸሎተ ኀሙስ ሐተታ ላይ እንደተገለጸው የአዳም ተስፋው ተፈጽሞለት ከነልጅ ልጆቹ ወደቀደመ የገነት ክብሩ ለመግባቱ መታሰቢያ ሆና «የአዳም ኀሙስ» ተብላ ይኸው ትከበራለች፡፡ ሉቃ. 24-25-49
– ዐርብ = በክርስቶስ ደም ተዋጅታ በተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መታሰቢያ በመሆኗ በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ዐርብ «ቤተ ክርስቲያን» ተብላ ትጠራለች፡፡ ማቴ. 26-26-29 የሐ. ሥራ. 20-28 ይህች ዕለትም እንደ ዕለተ ኀሙስ ሦስት ስያሜዎች አሏት፡፡ ይኸውም እንደኛው ከሆሳዕና ቅዳሜ በፊት ያለችው ዐርብ የጌታችን አርብዓው ጾም የሚፈጸምባት የጾመ ድጓው ቁመትም የሚያበቃባት፣ በመሆኗ በቤተ ክርስተያን «ተጽዒኖ» ስትባል በሕዝቡም ዘንድ በሕማማትና ሰሙነ ትንሣኤው ከባዱን ሥራ ስለሚያቆምባት «የወፍጮ መድፊያ፣ የቀንበር መስቀያ» ትባላለች፡፡
– ሁለተኛውም በመጀመሪያ የሰው አባትና እናት አዳምና ሔዋን ስለተፈጠሩባት፣ ኋላም በሐዲስ ኪዳን ጌታችን ለቤዛ ዓለም መከራ ተቀብሎ ስለተሰቀለባትና የማዳን ሥራውን ስለፈጸመባት «ዕለተ ስቅለት አማናዊቷ ዐርብ» ትባላለች፡፡
– ሦስተኛውም ይኸው በሰሙነ ትንሣኤው ያለችው ደግሞ «ቤተ ክርስቲያን» ትባላለች ማለት ነው፡፡
– ቀዳሚት = በሰሙነ ፋሲካው ያለችው ቀዳሚት ሕዝቡ ከአንዳንዱ በስተቀር ገበያ እንኳን ስለማይገበይባት «የቁራ ገበያ» የገበያ ጥፊያ ስትባል በቤተ ክርስቲያን ግን በዘመነ ሥጋዌው በገንዘባቸውና ጉልበታቸው ለአገለገሉት በስቅለቱ ዋይ ዋይ እያሉ እስከ ቀራንዮ ለተከተሉት፣ የትንሣኤው ዕለት ገና ከሌሊቱ ወደ መቃብሩ ሽቱና አበባ ይዘው በመገሥገሣቸው ትንሣኤው ከሁሉ ቀድሞ ለተገለጸላቸው ቅዱሳት አእንስት መልካም መታሰቢያ ሆና «አእንስት» ተብላ ትጠራለች፡፡ ሉቃ. 23-27-33፣ 24-1-01፣ ማቴ. 25-1-11
 

የዋናው ትንሣኤ ሳምንት እሑድ…

 
በዚች ሰንበት ከላይ እንደተጠቆመው የትንሣኤው ዕለት ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት በዝግ በር ገብቶ በመካከላቸው ተገኝቶ «ሰላም ለሁላችሁ ይሁን» ብሎም ትንሣኤውን ሲገልጽላቸው ሐዋርያው ቶማስ አልተገኘም ነበር፡፡ በኋላ ከሔደበት ሲመጣ የጌታችንን መነሣትና እንደተገለጸላቸው በደስታ ሲነግሩት «በኋላ እናንተ ዐየን ብላችሁ ልትመሰክሩ፣ ልታስተምሩ፣ እኔ ግን «ሰምቼአለሁ» ብዬ ልመሰክር፣ ላስተምር? አይሆንም እኔም ካላየሁ አላምንም» በማለቱ የሰውን ሁሉ፤ ይልቁንም የመረጣቸው ወዳጆቹን የልብ ሐሳብ ምክንያቱን ለይቶ የሚያውቀው፣ ቸርነቱ ወሰን የሌለው የባሕርይ አምላክ መድኀኔዓለም ክርስቶስ ልክ እንደመጀመሪያው ትንሣኤ ዕለት አበው ሐዋርያት በአንድነት በተዘጋ ቤት እንዳሉ በሩን ሳይከፍት ገብቶ «ሰላም ለሁላችን ይሁን» በማለት በመካከላቸው ቆመ፤ ቶማስንም «ያመንክ እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን እነሆ የተቸነከሩ እጆቼንና እግሮቼን፣ የተወጋ ጐኔንም ናና እይ» ብሎ አሳየው፡፡ እርሱም ምልክቱን በማየቱ በመዳሰሱ ትንሣኤውንና አምላክነቱን እንደፍላጎቱ በመረዳቱ «ጌታዬ አምላኬ ብሎ መስክሮ» አመነ፡፡
– እንግዲህ ይህ የትንሣኤው ምስጢር ለሁለተኛ ጊዜ ለሐዋርያት የተገለጠበት ዕለት ስለሆነ «ዳግም ትንሣኤ» ተብሎ ሰንበቱ ይጠራበታል፤ ይከበርበታል፡፡ ዮሐ. 20-24-30
– በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚፈጸመው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ሁሉ ከቅዳሴው ውጭ ከሚፈጸመው «ድኅረ ቁርባን» በስተቀር ልክ እንደመጀመሪያው የትንሣኤ ዕለት ሆኖ ይከናወናል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ለብርሃነ ዕርገቱም በሰላም ያድርሰን፡፡ አሜን!!

“ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን፤ በዐቢይ ኃይል ወሥልጣን፤ አሰሮ ለሰይጣን፤ አግዐዞ ለአዳም፤ ሠላም እምይዕዜሰ፤ ኮነ፤ ፍስሐ ወሠላም፡፡”

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

“ክርስቶስ በታላቅ ኃይልና ሥልጣን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ዲያብሎስን አሰረው አዳምን ነጻ አወጣው ሠላም ከዛሬ ጀምሮ ሰላም ሆነ” ይህ ቃል የትንሣኤው የምሥራች ለምእመናን የሚታወቅበት ነው የሚቀድስ ካህን፣ ሰባኪ በዘመነ ትንሣኤ ከስብከቱ አስቀድሞ በዚህ ቃል የክርስቶስን መነሣት ያውጃል፡፡ የሚቀድሰው ካህንም በኪዳን ጊዜ ህዝቡን ከመባረኩ አስቀድሞ ይህንኑ ቃል ይናገራል ሰላምታ የሚቀባበሉ ምእመናንም ሰላምታ ከመስጠት አስቀድሞ ይህን ቃል በመናገር የትንሣኤውን አዋጅ ማወጅና መመስከር ይገባቸዋል፡፡ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ እንደ እንግዳ ደራሽ እንደ ውኃ ፈሳሽ አይደለም ከጥንት በነቢያት የተነገረ ኋላም እርሱ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከመሞቱ አስቀድሞ ያስተማረው ደግሞም በመነሣት የገለጠው ሐዋርያትም በግልጥ ለዓለም የመሰከሩት ነው፡፡

ትንሣኤ በትንቢተ ነቢያት

“እግዚአብሔር ይነሣል ጠላቶቹም ይበተናሉ” “እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው ጠላቶቹንም በኋላው መታ” መዝ.77፥6 “እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም እግዚአብሔር አሥነስቶኛልና ተነሣሁ” መዝ.3፥5 “እግዚአብሔር አሁን እነሣለሁ ይላል መድኀኒት አደርጋለሁ

ቅዱስ ዳዊት በዚህ መልኩ የክርስቶስን ከሙታን መነሣት ተናግሯል፡፡ እርሱን መሰል ነቢያት ክርስቶስ እንዲሞት በ3ኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደሚነሣ ገልጸዋል፡፡ ምሳሌ ተመስሏል፤ ትንቢትም ተነግሯል፤ ዮናስ ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በአሣ አንበሪ ሆድ ውስጥ እንደ አደረ ክርስቶስም ሦስት መዓልትና ሦስት ሌሊት በከርሰ መቃብር አድሮ ሙስና መቃብርን አጥፍቶ ብርሃነ መለኮቱን ገልጾ እንደሚነሣ ራሱ ባለቤቱ እግዚአብሔር ወልድ ተናግሯል፡፡ ዮና.2፥1 ማቴ.12፥4ዐ ነቢየ እግዚአብሔር ሆሴዕ “ከሁለት ቀን በኋላ ያድነናል፡፡ በሦስተኛው ቀን ያስነሣናል በፊቱም በሕይወት እንኖራለን” ሆሴ.6፥2 ብሎ የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ለእኛም ትንሣኤያችን፣ ሕይወታችን መሆኑን ገልጾ ተናግሮታል፡፡ ሆሴዕ በተጨማሪም “ሞት ሆይ መውጊያህ ወዴት አለ? ሲኦል ሆይ /መቃብር/ ድል መንሳትህ ወዴት አለ?” ሆሴ.13፥14 ብሎ ሞት እና መቃብር ሥልጣናቸው እንደተሻረ ይዘው ማስቀረታቸው እንደቀረ በክርስቶስ ትንሣኤ የሰው ልጆች ትንሣኤ እንደተገለጸ ይነግረናል “ልጄ ሆይ ከመሰማሪያህ /ከመቃብር/ ወጣህ እንደ አንበሳ ተኛህ አንቀላፋህም እንደ አንበሳ ደቦል የሚቀሰቅስህ የለም” ዘፍ.49፥9 ከላይ በተመለከትነው ጥቅስ የሚቀሰቅስህ የለም የሚለው ክርስቶስ በገዛ ሥልጣኑ አስነሽ ሳይሻ የተነሣ መሆኑን ይነግረናል ይህንም ክርስቶስ በራሱ ሥልጣን እንደሚነሣ ሲያስተምር እንዲህ ይላል፡፡ “እንደገና አስነሣት ዘንድ እኔ ነፍሴን እሰጣለሁና ከእኔ ማንም አይወስዳትም ነገር ግን እኔ በፍቃዴ እሰጣታለሁ እኔ ላኖራት ሥልጣን አለኝ መልሼ እወስዳት ዘንድ ሥልጣን አለኝና” ዮሐ.10፥17 ይህ የሚያስረዳን ክርስቶስ በፈቃዱ ለዓለም ቤዛ ሆኖ እንደ ሞተ በሥልጣኑ እንደተነሣ ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ በሐዲስ ኪዳን

አራቱም ወንጌላውያን ትንሣኤውን እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው በወንጌል ጽፈውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ምዕራፍ 28፥1-16 በሰንበትም ማታ ለእሑድ አጥቢያ ማርያም መግደላዊትና ሁለተኛዋ ማርያም መቃብሩን ሊያዩ መጡ እነሆ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ የእግዚአብሔር መልአክ ከሰማይ ወርዷልና ቀርቦም በመቃብሩ አፍ ላይ ድንጋይዋን አንከባሎ በላይዋ ተቀመጠ” ይላል በዕለተ ትንሣኤ የክርስቶስን ትንሣኤ ለማየት መላእክት እንዲሁም ቅዱሳት አንስት ተገኝተዋል ሲወለድ የመወለዱን ዜና ለዕረኞች የተናገሩ መላእክት በትንሣኤው ዕለትም ዜና ትንሣኤውን ለቅዱሳት አንስት ለመንገር በመቃብሩ አካባቢ ተገኝተው የትንሣኤው ምስክሮች ሆነዋል፡፡
“ወእምግርማሁ ተሀውኩ ወኰኑ ከመ አብድንት እለ የአቅቡ መቃብረ “እርሱን ከመፍራት የተነሣ መቃብሩን የሚጠብቁት ታወኩ እንደ በድንም ሆኑ” ማቴ.28፥4 መልአኩም መልሶ ሴቶችን እንዲህ አላቸው “እናንተስ አትፍሩ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትሹ አውቃለሁና በዚህ የለም እርሱ እንደተናገረው ተነሥቶአል፡፡ ነገር ግን ኑና የተቀበረበትን ቦታ እዩ ፈጥናችሁም ሂዱ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ ብሎ የትንሣኤውን የምስራች ለሴቶች መግለጡን ጽፎአል፡፡

ቅዱስ ማርቆስም በምዕራፍ 16፥1-16 ትንሣኤውን አስመልክቶ ቅዱስ ማቴዎስ የተናገረውን መሰል የትንሣኤ መልእክት ሲናገር ቅዱስ ሉቃስ በምዕራፍ 24፥1-24 ዜና ትንሣኤውን ጽፎልናል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌል አጻጻፍ ስልቱ ከሦስቱ ወንገላውያን ረቀቅ ያለ ስልት ያለው ቢሆንም ትንሣኤው በመመስከር ከሦስት ወንጌላውያን ጋር ተባብሯል፡፡ ዮሐ.20፥1 ማርያም መግደላዊትና ሌሎች ሴቶች ወደመቃብሩ ገስግሰው በመሄድ ትንሣኤውን ለማየት እንደበቁ ለደቀ መዛሙርቱም የምሥራቹን እንደተናገሩ ዘግቦልናል፡፡ ከሦስቱ ወንጌላውያን በተለየ መልኩ ክርስቶስ ከተነሣ በኋላ በዝግ ደጅ ደቀ መዛሙርቱ ወደ አሉበት መግባቱን ትንሣኤው እንደገለጠላቸው ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሎ የሰላም አምላክ ከሀዘናቸው እንዲጽናኑ ፍርሀታቸውን አርቆ አይዞአችሁ አትፍሩ እኔ ነኝ እጄን እግሬን እዩ በማለት ፍጹም ፍቅሩን ገልጾላቸዋል፡፡

ትንሣኤው ምትሐት አለመሆኑን ይገልጥላቸውም ዘንድ “ደቂቅየ ቦኑ ብክሙ ዘንበልዕ” ጥቂት የሚበላ አላችሁን? ብሎ ለደቀ መዛሙርቱ ተናግሯል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በሕቱም መቃብር መግነዝ ፍቱልኝ መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል የተፈጸመ ኀይሉን የገለጠበት ነው ጌታ ባረገ በስምንት አመት የተጠራው ቅዱስ ጳውሎስም ትንሣኤውን ሐዋርያትን መስሎ መስክሮአል “ስለ ኃጢአታችን የተሰቀለውን ሊያስነሳንና ሊያጸድቀን የተነሣውን ጌታችንን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ ባስነሣው ስለምናምን ስለ እኛም ነው እንጂ” ሮሜ. 4፥25 በዚህ መልእክቱ ትንሣኤው ለእኛም ትንሣኤያችን መሆኑን ይነግረናል ትንሣኤው ለእኛ ሕይወት መሆኑንም ጭምር ሲነግረን “እርሱ ክርስቶስ በአባቱ ጌትነት ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ እኛም እንደ እርሱ በሐዲስ ሕይወት እንኖራለን” ሮሜ.6፥4 እንግዲህ በሞቱን ሞትን እንደሻረ በትንሣኤው ትንሣኤያችን ያበሠረ መሆኑን ደግሞም የትንሣኤያችን በኩር ጀማሪ እንደሆነ እኛ በሞቱ ብንመስለው የትንሣኤ ተካፋዮች መሆናችንን ያሳየናል፡፡

ጌታችን በአምስት ነገር በኩራችን መሆኑን መጻሕፍት ይነግሩናል
  1. በጥንት ዓለም ሳይፈጠር ዘመን ሳይቆጠር ኖሮ እኛን ፈጥሮ ለማስገኘት በኩራችን ነው፡፡
  2. በተቀድሶ/በመመስገን/ በኩራችን ነው፡፡ ቅዱሳን የጸጋ ምስጋና የሚመሰገኑት እርሱን በኩር አድርገው ነውና፡፡
  3. በትንሣኤ በኩራችን ነው፡፡ እርሱን በኩር አድርገን እንነሣለንና “አሁንም ክርስቶስ ከሞቱ ሰዎች ሁሉ አስቀድሞ ተነሥቶአል በመጀመሪያው ሰው ሞት መጥቶአል በሁለተኛው ሰው ትንሣኤ ሙታን ሆነ” 1ቆሮ.15፥20፡፡
  4. በዕርገት በኩራችን ነው፡፡ ቅዱሳን አረጉ መባሉ እርሱን በኩር አድርገው ነውና፡፡ “አርገ ከመ ያሌቡ ዕርገተ ጻድቃን ንፁሀን” የንፁሀን ጻድቃንን ዕርገት ያስረዳ ዘንድ አረገ ቅዳሴ ዩሐንስ ወልደ ነጎድጓድ”
  5. ነፍሳትን ከሲዓል አውጥቶ ምርኮን ማርኮ ገነት መንግሥተ ሰማያት በመግባት በኩራችን ነው፡፡
ስለዚህ በአለ ትንሣኤውን ስናከብር የእኛም ትንሣኤያችን መሆኑን አውቀን ተረድተን ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን መልካም ሥራ በመሥራት መሆን አለበት እኛ ትንሣኤ ልቡና ሳንነሣ በየዓመቱ ትንሣኤን ብናከብር ፈሪሳውያንን ወይም ትንሣኤ የለም ፈርሰን በስብሰን እንቀራለን ብለው የሚያምኑ ሰዱቃውያን መምሰል ይሆናል፡፡
ትንሣኤውን ስናከብር እንዴት ማክበር እንደሚገባን ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል
ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኛ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ የላይኛውን አስቡ በምድር ያለውንም አይደለም እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ ያን ጊዜ ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ” ቆላ.3፥1-4 የክርስቶስ ትንሣኤ ትንሣኤያችን ነው ብለን ለምናምን ሁሉ ከምድራዊ ዐሳብ ነጻ ሆነን ተስፋ የምናደርገው ትንሣኤ እንዳለን በማሰብ ከሞት በኋላ ሕይወት ከትንሣኤም በኋላ የዘለዓለም ሞት መኖሩን ሳንዘነጋ ማክበር እንደሚገባን ይመክረናል፡፡ ላይኛውን የማያስቡ መልካም ሥራ የማይሰሩ ሰዎች ትንሣኤ ምን እንደሚመስል መድኅነ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር እንዲህ ብሏል፡፡ “በመቃብር ያሉ ሁሉ ቃሉን የሚሰሙበት ጊዜ ይመጣል፡፡ ስለዚህ አታድንቁ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉ የሠሩም ለፍርድ ትንሣኤ ይነሣሉ” ዮሐ.5፥28 የትንሣኤያቸው በኩር ክርስቶስን አብነት አድርገው ቃሉን ሰምተው ሕጉን ጠብቀው ትዕዛዙን አክብረው ትንሣኤ ልቡና ተነሥተው የትንሣኤን ዕለት የሚያከብሩ ሥጋውን በልተው ደሙን ጠጥተው በንስሐ ተሸልመው በፍቅረ እግዚአብሔርና በፍቅረ ቢፅ /ወንድምን በመውደድ/ ጸንተው ቢኖሩ ላይኛውን ማሰብ ትንሣኤውን ማክበር ማለት ይህ ነው፡፡ የትንሣኤውን ትርጉም አውቀዋልና፡፡ ከትንሣኤ ሥጋ ትንሣኤ ልቡና ተነሥተን ሥጋውን በልተን ደሙን ጠጥተን መንግሥቱን እንድንወርስ ስሙን እንድንቀድስ እግዚአብሔር አምላካችን ይፍቀድልን፡፡
መልካም ትንሣኤ ያድርግልን አሜን፡፡