kidase

ጾመ ፍልሰታ

ነሐሴ 1 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡ ፈጣሪያችን ጾሙን የበረከት፣ የረድኤት የንስሓ ያደርግልን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ ንስሓ ገብተን፣ ጾመን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀብለን ሕይወት እንድናገኝ የፈጣሪያችን ቸርነቱ አይለየን! አሜን

 

ጾም፡- መተውን መከልከልን መታቀብን፣ መታረምን የሚገልጥ የግብር ስም ነው፡፡

 

kidaseየቤተ ክርስቲያናችን የሥርዓትና የሕግ መጽሐፍ የሆነው ፍትሐ ነገሥት በ15ኛው አንቀጹ መግቢያ ላይ “ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው፡፡ በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕጉን ለሠራለት እየተታዘዘ የፈቲዉን ኀይል ያደክምበት ዘንድ ለነባቢትም ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ፤” በማለት የጾምን ምንነትና ጥቅም አጠር አድርጎ ያብራራል፡፡

 

ጾም ከመንፈሳዊ ተጋድሎዎች አንዱ ነው፡፡ ለሥጋም መንፈሳዊ ልጓም ነው፡፡ የሚጾም ሰው በጾም ፈቃደ ሥጋውን እየገታ ነፍሱን እንደሚጠቅም ይታወቃል፡፡ ስለዚህም ነው፡- “ከኀጢአት ፆር ከፍትወት አንዱንም ድል ለመንሣት ለማጥፋት በጾም መድከም የሥራ ሁሉ መጀመሪያ እንደሆነች የታወቀ ነው፡፡ የሥራ ሁሉ መጀመሪያ በጾም መድከም ነው፡፡ ይልቁንም በባሕርያችን የምትኖር ኀጢአትን ለሚዋጋ ሰው” በማለት ማር ይስሐቅ የተባለው መጽሐፋችን የሚናገረው፡፡ በማር ይስሐቅ አንቀጽ 4 ምዕራፍ 6 ላይ ጾምን በተመለከተ የሰፈረው መግለጫ “ጾም፡- የሥራ መጀመሪያ ናት፤ የጽሙዳን ክብራቸው ናት የድንግልና የንጽሕና ጌጻቸው ናት፤ የንጽሕና መገለጫ ናት፡፡ የወንጌል ሥራ መጀመሪያ ናት፡፡ የጸሎት ምክንያት ናት፡፡  የዕንባ መገኛ ናት፡፡ አርምሞን የምታስተምር ናት፡፡ ለበጎ ሥራ ሁሉ ታነቃቃለች” የሚለው ይገኝበታል፡፡

 

ከዚህ በላይ እንደተመለከተው ጾማችንን ከጸሎት ከምጽዋት ከሰጊድ እንዲሁም የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን በመቀበል ጭምር ልናስተሳስረው ይገባናል፡፡ አለዚያ ጾማችን ከእህልና ከውኃ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ የምንከለከልበት ከሆነ እንደ ድልድይ ሆኖ ከፈጣሪያችን አያገናኘንም ግዳጅም አይፈጽምልንም፡፡ እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈ፡- “ነገር ግን ዕለት ዕለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውን ፍርድ እንዳልተዉ ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል፥ ወደ እግዚአብሔርም ለመቅረብ ይወድዳሉ፡፡ ስለምን ጾምን ፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ፡፡

 

እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ፡፡ እነሆ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤… እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንዲህ ባለቀን ነውን? በውኑ ራሱን እንደ እንግጫ ዝቅ ያደርግ ዘንድ ማቅንና አመድንም በበታቹ ያነጥፍ ዘንድ ነውን? በውኑ ይህን ጾም ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ ቀን ትለዋለህን? እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፋትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህንስ ለተራበ ትቆርስ ዘንድ፥ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሸግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንስ እንደ ንጋት ይበራል፥ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፥ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፥ የእግዚአብሔርም ክብር በኋላህ ሆኖ ይጠብቅሃል፡፡ የዚያን ጊዜ ትጠራለህ እግዚአብሔርም ይሰማሃል ትጮኻለህ እርሱም እንሆኝ ይላል፡፡” /ትንቢተ ኢሳይያስ ምዕ.58፥2-9

 

ብሉይን ከሐዲስ አስማምታ የምትቀበል ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን የጾምንና የጸሎትን ሥርዓት ሠርታ እኛን ልጆቿን ለበረከት፣ ለሕይወት ለዘላለማዊ፣ ክብር ለማብቃት ታስተምረናለች፣ በሥርዓቷም ትመራናለች፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የጾም ዓይነቶች ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም የግል /የስውር/ እና የዐዋጅ አጽዋማት ይባላሉ፡፡

 

I.    የግል /የስውር/ ጾም

ምእመናን በልዩ ልዩ ምክንያት ከመምህረ ንስሓቸው ጋር በመመካከር በፍቃድ የሚጾሙት የጾም ዓይነት ነው፡፡ ይህም በሌላ አካል የማይታወቅና ሊታወቅ የማይገባ ነው፡፡ በንስሓ ምክንያት ከሚጾመው በተጨማሪ ስለቤተሰብ ስለወገን፣ ስለ ሀገር…. ወዘተ ተብሎ የሚጾሙት ጾም ይኖራል፡፡ ይህ ከዐዋጅ ጾም ከሚለይባቸው ምክንያቶች አንዱ በምሥጢር የሚጾም በመሆኑ ነው፡፡ በንስሐ ምክንያት ወይም በሌላ /በራሱ ፈቃድ የሚጾም ሰው መጾሙን ካሳወቀ እንደ ግብዝነት ከንቱ ውዳሴ ይሆንበታል፡፡ ይህ መሆኑም ዋጋ አያሰጠውም፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ስትጦሙም፥ እንደ ግብዞች አትጠውልጉ፤ ለሰዎች እንደ ጦመኛ ሊታዩ ፊታቸውን ያጠፋሉና፤ እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል፡፡ አንተ ግን ስትጦም፥ በስውር ላለው አባትህ እንጂ እንደ ጦመኛ ለሰዎች እንዳትታይ ራስህን ተቀባ ፊትህንም ታጠብ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል፡፡” በማለት አስበ ጸሎታችንን /የጸሎታችንን ዋጋ/ ከፈጣሪ እንድናገኝ “እዩኝታን” /እዩልኝ፣ እወቁልኝ/ ከሚል የግብዝነት ሕይወት ተላቀን ልንጾመው እንደሚገባ አዞናል፡፡ /ማቴ.6፥16-18/

 

II.    የማኅበር /የዐዋጅ/ ጾም

በዐዋጅ ለሕዝቡ ተነግሮ ሕዝቡ ሁሉ ዐውቆት በአንድነት የሚጾም ጾም ነው፡፡ ሁሉም በአንድነት ወጥ በሆነ መልኩ የሚጾመው በመሆኑ ከንቱ ውዳሴ የለውም፡፡ ፈሪሳዊም አያሰኝም፡፡ በዐዋጅ ጾም አንድ ሰው እጾማለሁ ቢል በውስጡ እስካልታበየና እስካልተመካ ድረስ ጾምን ሰበከ ይባላል እንጂ ውዳሴ ከንቱ አምጥቶበት ዋጋ አያሳጣውም፡፡

 

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት ምእመናን ሁሉ እንድንጾማቸውና በሥጋም በነፍስም እንድንጠቀምባቸው መጀመሪያቸውና መጨረሻቸው ተቀምሮ ጊዜና ወቅት ተወስኖላቸው የተደነገጉ ሰባት የዐዋጅ አጽዋማት አሉ፡፡ እነዚህም በቅዱሳን አባቶቻችን በሐዋርያት ሲጾሙ የቆዩና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቀኖና ያጸኗቸው ዲድስቅሊያና ሌሎች የቀኖና መጻሕፍት ሥርዓታቸውን የሠሩላቸው ናቸው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓመት ውስጥ የሚጾሙት ሰባቱ አጽዋማት በጊዜ ቀደም ተከተላቸው መሠረት፡-

 

  1. ጾመ ነቢያት /ከኅዳር 15-ታኅሣሥ 29/
  2. ጾመ ነነዌ /ከጾመ ሁዳዴ መግቢያ 15 ቀን በፊት ያሉት ሦስት ቀናት ከሰኞ እስከ ረቡዕ/
  3. ጾመ ሁዳዴ /ከጾመ ነነዌ 15 ቀናት በኋላ፤ ለ55 ቀናት ይጾማል/
  4. ጾመ ገሃድ /የገና ዋዜማ እና ጥር 10 ቀን/
  5. ጾመ ድኅነት /ከበዓለ ሃምሳ በኋላ ከሚመጣው ረቡዕ ጀምሮ/
  6. ጾመ ሐዋርያት ከበዓለ ሃምሳ ማግስት ሰኞ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 5/
  7. ጾመ ፍልሰታ /ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 14 ቀን፡፡

 

ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት አጽዋማት ለአሁኑ ጾመ ፍልሰታን እንመለከታለን

“ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፥ አንተና የመቅደስህ ታቦት” /መዝ.131፥8/

 

“ተንሥኢ ወንዒ ቅርብትየ እንቲአየ ሠናይት ርግብየ ውስተ ጽላሎተ ኰኲሕ ቅሩበ ጥቅም፡፡ አቅራቢያዬ መልካሟ ርግብየ ተነሽ፤ ነዪ፤ በግንቡ አጠገብ ወዳለው ወደ ዋሻው ጥላ፡፡” /መኃ.2፥10-14/

 

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እመቤታችንን መቅደሱ፥ ታቦቱ፣ ማደሪያው፣ መንበሩ እናቱ አድርጎ መረጣት፡፡ ስለዚህ ምክንያት አብ ጠበቃት ወልድ በተለየ አካሉ ሥጋን ከርሷ ተዋሐደ መንፈስ ቅዱስ አጸናት፡፡ እመቤታችን በዚህ ኃላፊ ዓለም ለ64 ዓመት ቆይታለች፡፡ ጥር ሰኞ ይብታል ሰኞ እስከ ሰኞ 8 ሰኞ እስከ ሰኞ 15፣ ሰኞ እስከ ሰኞ 22፣ ሰኞን ትቶ እሑድ ጥር 21 ቀን እመቤታችን አርፋለች፡፡ ሐዋርያት ባጎበር አድርገው ወደ ጌቴ ሴማኒ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ “ቀድሞ ልጇን ሰቅለን ብንገድለው ደቀ መዛሙርቱ ተነሣ፣ ዐረገ” እያሉ ሲያውኩን ኖሩ፤ ዛሬ ደግሞ እርሷን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? በእሳት እናቃጥላታለን” ብለው ተነሡ፡፡ ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤል የታውፋንያን ሁለት እጁን በሰይፍ መትቶ ቀጣው፡፡ በዚህም የታውፋንያ ሁለት እጁ ከአጎበሩ ተንጠልጥሎ ቀረ፡፡ ከዚያ በኋላ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌላዊውን ቅዱስ ዮሐንስ ጨምሮ በደመና ነጥቆ ከገነት በዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት፡፡

 

ሐዋርያት ዮሐንስን “እንደምን ሆነች” አሉት፡፡ እርሱም፡- “በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች” አላቸው፡፡ “ዮሐንስ አይቶ እኛ ሳናይ” ብለው፤ በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፤ ሰኞ ነሐሴ 1 ቀን ጀምረው እሑድ ነሐሴ 14 ቀን ፈጽመዋል፡፡ በዚሁ ቀን ጌታችን ትኩስ በድን አድርጎ የእመቤታችንን ሥጋ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ እርሷም እንደ ልጇ በተቀበረች በሦስተኛው ቀን /ማክሰኞ/ ተነሥታ አርጋለች፡፡ “ከመ ትንሣኤ ወልዳ” ያሰኘውም ይህ ነው፡፡ በዚሁ ጊዜ ከሐዋርያት ወገን የሆነው ቅዱስ ቶማስ አልነበረም፡፡ ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ /ከሕንድ/ ሲመጣ ስታርግ አገኛት፡፡ “ወፈቀደ ይደቅ እምደመናሁ” ይላል፤ ተበሳጨ፡፡ “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፤ ዛሬ ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁኝ” አለ፡፡ በዚህ ጊዜ የልቡናን ሐዘን የምታቀል እመቤታችን፡- አይዞህ አትዘን እኒያ ትንሣኤዬን ዕርገቴን አላዩም፡፡ አንተ አይተሃል፡፡ ተነሣች፣ ዐረገች ብለህ ንገራቸው፡፡” ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው፡፡ ከዚህ በኋላ ሄዶ፤ “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው “ሥጋዋን አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ እርሱም “ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር ተዉ ይህ ነገር አይመስለኝም” አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ እንጂ ልማድህ ነው፡፡ አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም፤ አንተ እየተጠራጠርህ ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራለህ” አለው፡፡ እርሱም የያዘውን ያውቃልና ጸጥ ብሎ ይሰማቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ተቆጥቶ ሂዶ መቃብሩን ቢከፍተው የእመቤታችን ሥጋዋን አጥቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ደንግጦ ቆመ፡፡ ይህን ጊዜ ቅዱስ ቶማስ “አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሣች ዐረገች” አላቸው፡፡ የያዘውንም ሰበን እያሳያቸው፡- “ቅዱስ ሥጋዋን የገነዛችሁበት ጨርቅ /ሰበን/ ይህ አይደለምን” ብሎ ሰበኑን ሰጣቸው፡፡ ይህንንም ለበረከት ተካፍለውታል፡፡ ከዚህ በኋላ በዓመቱ “ቶማስ ትንሣኤሽን ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ በማለት ጾም ጀመሩ፡፡ በ16ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ ቄስ፣ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ራሱ ቀድሶ አቁርቦአቸዋል፡፡

 

ስለዚህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጌታችን በኋላ ከክርስቲያኖች ሁሉ በፊት የትንሣኤንና የዕርገትን ክብር አግኝታ ልዑል እግዚአብሔር ባዘጋጀላት ልዩ ሕይወት እንደምትኖር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡

 

ምእመናን ሁላቸውም በየጾታቸውና በየመአረጋቸው ቀን በቅዳሴ፣ ሌሊት በሰዓታት በማኅሌት በኪዳን ቃለ እግዚአብሔርን በመስማትና ስብሐተ እግዚአብሔርን በማድረስ ይወሰናሉ፡፡

 

በእነዚህ አሥራ አምስት ቀናት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ ውዳሴዋና ቅዳሴዋ ተራ በተራ ይተረጎማሉ፡፡ ምእመናንም በፍቅርና በሃይማኖት የሚሰጠውን ትምህርት ይሰማሉ፡፡

 

ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም እመቤታችንን ባመሰገነበት በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ ከተናገራቸው ኀይለ ቃላት፡- “ነጸረ አብ እምሰማይ፡፡ ወኢረከበ ዘከማኪ፡፡ ፈነወ ዋሕዶ ወተሰብአ እምኔኪ፡፡ ማለትም እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ አየ፤ አየና እንዳች ያለ ባያገኝ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን ልጁን ወዳንቺ ላከው፡፡ ካንቺም ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ ሰው ሆነ፡፡” በማለት ያመሰገነበት ቃል ይገኛል፡፡ /ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ/ ይህ ቃል እመቤታችን ከፍጥረታት ሁሉ የከበረች በንጽሕናዋና በቅድስናዋ የተነሣ አምላክ ከእርሷ ተወልዶ /ሰው ሆኖ/ ዓለምን እንዲያድን ምክንያት የሆነችበትን ያስረዳል፡፡ በዳዊት መዝሙር ሰፍሮ በምናገኘው ቃል እግዚአብሔር አምላካችን የሚያስተውል እርሱንም የሚፈልግ ልብ ከሰዎች ልጆች እንዲያገኝ ቢመለከት አንዳች እንኳ እንዳጣና ሁሉ እንዳመፁ ተጠቅሶአል፡፡ /መዝ.13፥2-3/ ስለሆነም ነው ይህንኑ ቃል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው፡- “በአማን ነጸረ እግዚአብሔር አብ እምሰማይ ምሥራቀ ወምዕራበ ሰሜነ ወደቡበ፡፡ አስተንፈሰ ወአጼነወ፡፡ ወኢረከበ ዘከማኪ፡፡ ወሠምረ መዓዛ ዚአኪ፡፡ ማለትም እግዚአብሔር በልዕልና ሆኖ አራቱን ማዕዘን በእውነት ተመለከተ አስተናፈሰ አሸተተ ነገር ግን በንጽሕና በቅድስና የተዘጋጀች እንዳንቺ ያለች አላገኘም፡፡ መዓዛ ንጽሕናሽን መዓዛ ቅድስናሽን ወድዶ ለተዋሕዶ መረጠሽ፡፡” በማለት የተረጎመው፡፡

 

የተወደዳችሁ ምእመናን ለበረከት ይሆነን ዘንድ ከአባቶቻችን ቅዱሳን ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ኤፍሬም ሶሪያዊ እመቤታችንን ካመሰገነበት የምስጋና ድርሰቱ አንዱን አንቀጽ እናንሣና ለአሁኑ እንሰነባበት፡፡

 

“ተፈሥሒ ኦ ወላዲተ እግዚእ ሐሤቶሙ ለመላእክት፡፡” የሚለው ቃል በቅዱስ ኤፍሬም የምስጋና ድርሰት ይገኛል፡፡ /የማክሰኞ ውዳሴ ማርያም/ ይህንን የምስጋና ድርሰት አባቶቻችን መምህራን እንዲህ ተርጉመውታል፡፡ “የመላእክት ደስታቸው የሚሆን ጌታን የወለድሽው ተፈሥሒ ደስ ይበልሽ፡፡ ለሊሁ ዓለሞሙ፣ ወለሊሁ ተድላሆሙ፣ ወለሊሁ ሀገሮሙ እንዲል፡፡ አንድም ሥጋዌውን ተልከው ለነቢያት የሚነግሩ መላእክት ናቸው፡፡ ከዚህ የተነሣ በአጭር ቁመት በጸባብ ደረት ተወስኖ አይተውት፤ ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ብለው አመስግነውት፤ በጣዕም ላይ ጣዕም በጸጋ ላይ ጸጋ ተጨምሮላቸው ደስ ብሏቸዋልና፡፡ አንድም የመላእክት ደስታቸው የምትሆኝ ጌታን የወለድሽው ተፈሥሒ ደስ ይበልሽ፡፡ ንጽሕናዋን ቅድስናዋን እያዩ ደስ ይላቸዋልና ሐሤቶሙ ለመላእክት አለ፡፡”

 

እንግዲህ ቅዱስ አባ ሕርያቆስ፡- “ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን ወበከመ ሰማዕክሙ ዘንተ ቃለ ቅዳሴሃ ለማርያም ከማሁ ያስምዕክሙ ቃለ መሰናቁት ዘሕፃናት” እንዳለው፤ ይህንን የእመቤታችንን ምስጋና ውዳሴ ለመስማት ለማንበብ ያበቃን ፈጣሪያችን በቸርነቱ ብዛት ከጣዕሙ ብዛት አጥንትን የሚያለመልም የመላእክትን ምስጋና የሕይወትን ቃል ያሰማን፡፡

 

ከእመቤታችን ከወላዲተ አምላክ ከድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡ ፍቅሯን በልባችን፣ ጣዕሟን በአንደበታችን ይሳልልን ያሳድርብን አሜን፡፡

ሱባኤ፣ምንነቱ፣ሥርዓቱ

ሥርዓተ ሱባዔ

ሱባዔ ምንድን ነው? ሱባዔ በሰዋስው ትርጉሙ ሰባት ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጎም አንድ ሰው ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ እገናኛለሁ ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቁጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ  ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቁጥርን ፍጹምነት ያመለክታል፡፡ ዘፍ.2፥2፤ መዝ.118፥64፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም «አንድ ሱባዔ ጾመ» ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም «ሁለት ሱባዔ ጾመ» እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

መቼ ተጀመረ?

ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ «መላእክት ለአዳም ጊዜያትን አስተምረውት ነበር፡፡» ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ «ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንኀለሁ» ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል /መጽሐፈ ቀሌምጦስ አንቀጽ አራት/፡፡

ሱባዔ ለምን?

የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ኅሊናው ይወቅሰዋል፡፡ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጥረት ኅሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ክስተት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡ «በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል. ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?» እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ ሮሜ.7.22-25፡፡

ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ ተላልፎ ትካዜ ሽክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ያልተወሰነ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ አንድ ሰው በትካዜ ሽክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይሆንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ /ሱባዔ/ ይገባል፡፡

እግዚአብሔርን ለመማፀን

ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማፀን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅፅኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው /የምንማፀነው/ ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ነገር የለም፡፡

ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት፡- «ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው?» በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና ወዘተ ጉዳዮች ላይ ፈጣሪውን ይማፀናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ሆነ በሀገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፤ እንዲሁም መልሱ ሊዘገይ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት /መታገሥ/ ይጠበቅበታል፤ «ለምን ላቀረብኩት ጥያቄ ቶሎ መልስ አልተሰጠኝ?» በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማፀነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለው፡፡ ለምሳሌ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይ ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡

«አኃው ለተልእኮ በወጡበት አንዱን ድቀት አግኝቶት አድሯል፡፡ በነጋው «ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤ ሽለሙን መስዬ እኖራለሁ» አለው፡፡ «እኔም እንጂ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን» ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡ ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው 1 /አንድ/ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ «ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከል፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ» የሚል ድምፅ አሰምቶታል፡፡ /ዜና አበው/፡፡

ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ /ሰባት ቀን/ እንደ ጨረሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ «ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ» የሚል ፈጣን መልስ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ በግል ሕይወትም ሆነ በጓደኛችን ሕይወት ዙሪያ ስንገባ ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡

የቅዱሳንን በረከት ለመሳተፍ

ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ «ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ» /ኢሳ.56.6/ በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ገባላቸው ሱባዔ በመግባት በረከታቸውን መሳተፍ ይቻላል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን በረከት ለመሳተፍ፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡ ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል የተለያዩ ቅዱሳንን በረከት ለመቀበል /ለመሳተፍ/ የቅዱሳን አፅም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ደጅ የሚጠኑ ምእመናንና መናንያን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡

ይኸውም በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ በምዕራፍ 2.9 እንደ ተመለከተው ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በእጥፉ በኤልሳዕ ላይ አድሮበታል፡፡ ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትሕርምት የሚኖር መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ መኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

የተሰወረ ምሥጢር እንዲገለጥልን

በዘመነ ብሉይ እግዚአብሔር ለአንዳንድ ነገሥታት ራእይ በማሳየት ምሥጢርን ይሰውርባቸው ነበር፡፡ ለምሳሌ የግብፁን ፈርዖን፣ የባቢሎኑን ናቡከደነፆርንና ብልጣሶርን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዘፍ.41.14-36፡፡ ዳን.4.9፤ ዳን.5.4፡፡ እነዚህ ነገሥታት በግል ሕይወታቸውም ሆነ በመላው ሽክም ወደ ፊት ሊፈጸም የሚችል ራእይ ቢያዩም ቅሉ ራእዩን በትክክል ተረድተው «እንዲህ ይሆናል» የማለት ብቃት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ በዘመናቸው ይኖር የነበሩትን ነቢያት ሱባዔ ገብተው የሕልማቸውን ትርጉም እንዲነግሩአቸው ይማፀኑ ነበር፡፡ ነቢያትም ሱባዔ በመግባት ነገሥታቱ ያዩትን የምሥጢረ ሥጋዌ ነገርና የመንግሥታቸውን አወዳዳቅ ገልጸው ይናገሩ ነበር፡፡ ዳን.5.28፡፡

እንዲሁም ቅዱሳን በየራሳቸው ያዩት ራእይ ምሥጢር ሲከደንባቸው የራእዩ ምሥጢርና ትርጉም እንዲገለጥላቸው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ እግዚአብሔርም በንጽሕና ሆነው የገቡትን ሱባዔ ተመልክቶ ምሥጢር ይገልጥላቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነቢዩ ዕዝራ የመጻሕፍትን ምሥጢር እንዲገልጥለት ሱባዔ ቢገባ የጠፉትን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ዳግም መልሶ ለመጻፍ ችሏል፡፡ መዝ.8.1፡፡

በዘመነ ሐዲስ በሰፊው የሚወሳው ቅዱሳን ሐዋርያት ከነሐሴ 1-14 የገቡት ሱባዔ ነው፡፡ ይህ ሱባዔ ተሰውሮ የነበረውን የቅድስት ድንግል ማርያምን ትንሣኤ ተረድተው በረከቷን ለመሳተፍ አብቅቷቸዋል፡፡

«እመቤታችን ያረፈችው ጥር 21 ቀን 50 ዓመተ ምሕረት ነው፡፡ ሐዋርያት ሊቀብሯት ወደ ጌቴ ሰማኔ ይዘዋት ሲሄዱ አይሁድ በታተኗቸው፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱሳን መላእክት የእመቤታችንን ሥጋዋን ወስደው በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኑረውታል፡፡» /ተኣምረ ማርያም፤ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን/፡፡ በዚህ ጊዜ እነርሱ ተደናግጠው ስለተበታተኑ የእመቤታችን የዕረፍቷ ያስጨንቃቸው ነበር፡፡
«ቅዱስ ዮሐንስ በተመስጦ እየሄደ ሥጋዋን ያጥን ነበር፡፡ ለሐዋርያት ይህን ይነግራቸዋል፡፡ ለዮሐንስ ተገልጣ ለእኛ ሳትገለጥ ብለው በነሐሴ ሱባዔ ገቡ፡፡ ሁለተኛው ሱባዔ ሲፈጸም በ14ኛው ቀን መልአክ ሥጋዋን አምጥቶ ሰጥቶአቸዋል፤ ቀብረዋታል፡፡ በሦስተኛው ቀን ነሐሴ 16 ቀን ተነሥታ ዐርጋለች፡፡ /ተኣምረ ማርያም፤ ስንክሳር ነሐሴ 16 ቀን/፡፡

እንግዲህ ለቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችን የዕረፍትና የዕርገት ምሥጢር የተገለጠላቸው በሱባዔ ነው፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የእመቤታችንን የዕርገቷን በረከት ለማግኘት ትጾማለች፡፡ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ይህን የሱባዔ ወቅት ሕፃናትም ሳይቀሩ ይሳተፉታል፡፡

ሱባዔ ነቢያት

እግዚአብሔር ለአዳም የገባውን ቃል ኪዳን መሠረት በማድረግ ቀደምት ነቢያት በተነሡበት ዘመን ቅደም ተከተል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆንና ዳግም መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ ሱባዔም ቆጥረዋል፡፡ ኢሳ.7.14፡፡ መዝ.49.3፡፡ ዘካ.13.6፤ ዘካ.14.1፡፡ የአንዱ ነቢይ ትንቢታዊ ንግግርና ሱባኤ በአነጋገርና በአቆጣጠር ከሌላኛው ነቢይ ጋር ይለያያል፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ትንቢቱን ሲያናግር ምሳሌውን ሲያስመስል ጐዳናው ለየቅል በመሆኑ ነው፡፡ «ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጐዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ፡፡» እንዲል፡፡ ዕብ.1.1፡፡ የአቆጣጠር ስልታ ቸውና የሱባዔ መንገዳቸው ቢለያይም ዓላማና ግባቸው ግን አንድ ነው፡፡

ሱባዔ አዳም

አዳም ትንቢት በመናገርና ሱባዔ በመቁጠር የመጀመሪያውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ምክንያቱም በገነት ሰባት ዓመት ከአንድ ወር ከዐሥራ ሰባት ቀን በተድላና በደስታ ከኖረ በኋላ ሕግ በማፍረሱና የፈጣሪውን ቃል በመጣሱ ያለምንም ትካዜና ጉስቁልና ከሚኖርበት ዔደን ገነት ተባርሯል፡፡ ዘፍ.3.24፡፡ እርሱም ፈጣሪው እንዲታረቀው፣ በዐይነ ምሕረት እንዲጐበኘው፣ ቅዝቃዜው ሰውነት ከሚቆራርጥ ባሕር ውስጥ በመቆም ለሠላሳ አምስት ቀን /አምስት ሱባዔ/ ሱባዔ ገብቷል፡፡ በባሕርዩ የሰውን ልጅ እንግልት የማይወድ ቸሩ ፈጣሪ የአዳምን ፈጽሞ መጸጸት ተመልክቶ «በኀሙስ ዕለት ወበመንፈቃ ለዕለት እትወለድ እምወለተ ወለትከ ወእድኅክ ውስተ መርህብከ ወእቤዝወከ በመስቀልየ ወበሞትየኸ በአምስት ቀን ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ» ብሎ ተስፋውን ሰጠው፡፡ አዳም የተሰጠውን ተስፋ ይዞ በዓለመ ሥጋ ለዘጠኝ መቶ ሠላሳ አመት ከኖረ በኋላ መከራና ችግር ከበዛበት ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

በወንጀል ተከሶ በወኅኒ የተፈረደበት ሰው ከእስር የሚፈታበትን ዕለት በማውጣት በማውረድ ወራቱንና ዓመታቱን እንደሚቆጥር፣ አዳምም በሞት ቢለይም በሲኦል የነፍስ ቅጣት ካለበት ሥፍራ ይኖር ስለነበር የተሰጠውን ተስፋ በማሰብ ሱባዔውን እየቆጠረ የተናገረውን የማያስቀር የማያደርገውን የማይናገር ጌታየ «እነሆ አድንኀለሁ» ብሎ የገባልኝ ዘመን ተፈጸመ፤ ሰዓቱ አሁን ነው፤ እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ ቸር አምላክ ሰው ኾኖ ሥጋ ለብሶ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ፡- «ተንሥኡ ለጸሎት ለጸሎት ተነሡ፤ ሰላም ለኩልክሙ፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን» በማለት አዳምን ከነልጅ ልጆቹ ነጻ አውጥቶታል፡፡ አዳምን በመከተል ልጆቹም አበው ቅዱሳን ነቢያት ሱባዔ በመግባት የተስፋን ዘመን በመቁጠር በመልካም ግብር ተከትለውታል፡፡ በዚህም መሠረት በርካታ ነቢያት በተለያየ ስልት ሱባዔ ቆጥረዋል፤ እኛም ሱባዔ ከቆጠሩ ነቢያት የተወሰኑትን በዚህ ጽሑፍ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

ሱባዔ ሔኖክ

ጻድቁ ሔኖክ፣ የያሬድ ልጅ ሲሆን፣ በትውልድ ከአዳም ሰባተኛ ነው፡፡ እርሱም በሕይወቱ እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት ቤት ንብረቱን በመተው በሱባዔና በትሕርምት እግዚአብሔርን አገልግሏል፡፡ ፍጹም አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ሰው በመሆኑ በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን መልካም ግብር ተመስክ ሮለታል፡፡ «ሔኖክም አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡» ዘፍ.5.22፡፡ ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር የሱባዔውን ዋጋ ቅዱስ መንፈሱን በረድኤት ስለ አሳደረበት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ በሰማይ ተሰውሮ ሳለ ስለ ቅዱሳን መላእክት፣ ስለ መሲሕ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስለ ፀሐይና ጨረቃ አመላለስ /ዑደት/ የሚተርክ በስሙ የተሰየመውን መጽሐፍ ጽፏል፡፡ ዘፍ.5 21-24፡፡ ይሁዳ ቁ.14፡፡ ሔኖክ 1.9፡፡

ሱባዔ ሔኖክ የሚባለው ነቢዩ ሔኖክ በመስፈርት የቆጠረው ሱባዔ ነው፡፡ መስፈርቱ /ማባዣ ቁጥር/ 35 ሲሆን 35’19 ሲበዛ በውጤቱ 685 ዓመት ይሆናል፡፡ 685’12 ስናባዛው 7980 ይሆናል፡፡ ይኸውም ሐሳብ የሚያስረዳው ስለክርስቶስ ምጽአት ነው፡፡

ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ አሁን የደረስንበት ዘመን 7497 ይሆናል፡፡ ይህን ለማረጋገጥ በ5500 ዓመት ላይ 1997 ዓመትን መደመር ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ከላይ ያስቀመጥነውን 7497 ዓመት ይሰጠናል፡፡ በነቢዩ ሔኖክ አቆጣጠር መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ በ7980 ይሆናል፡፡ ከላይ ሔኖክ የቀመረውን ቁጥር ይዘን ከ7980 ዓመት ላይ አሁን ያለንበትን ዘመን /1997/ ስንቀንስ 483 ዓመት እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በሔኖክ ሱባዔ መሠረት ምጽአተ ክርስቶስ ሊሆን 483 ዓመት ይቀራል፡፡

ሱባዔ ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ከእስራኤል ነገሥታት ሁሉ ታላቅና ተወዳጅ ንጉሥ ነበር፡፡ ዘመነ መንግሥቱ 1011-971 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደ ነበር ይታመናል፡፡ ነቢዩ ዳዊት ልበ አምላክ እንደ መሆኑ ትንቢት ተናግሯል፡፡ ሱባዔ ቆጥሯል፡፡ ይኽውም ቀመረ ዳዊት በመባል ይታወቃል፡፡ «እስመ ዐሠርቱ ምእት ዓመት በቅድሜከ፤ ከመ ዕለት እንተ ትማልም ኃለፈት፤ ሺ ዓመት በፊትህ እንዳለፈች እንደ ትላንት ቀን»፡፡ /መዝ.89.4/ የሚለውን መምህራን ሲቆጥሩት 1140 ዓመት ይሆናል፡፡ ይኸውም በጌታ ዘንድ 1140 ዓመት እንደ አንድ ቀን እንደሆነ ነቢዩ ዳዊት ተናግሯል፡፡ ይህም ለዳዊት ሱባዔ መቁጠሪያ /መሥፈሪያ/ ሆኖ አገልግሏል፤ 1140’7= 7980 ዓመት ይሆናል፡፡ ይህም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በ7980 ዓመት ክርስቶስ ዳግም እንደ ሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

ሱባዔ ዳንኤል

ነቢዩ ዳንኤል ምድቡ ከዐበይት ነቢያት ነው፡፡ እስራኤል ወደ ባቢሎን ሲማረኩ ተማርኮ ወደ ባቢሎን ወርዷል፡፡ እርሱም ስለ ክርስቶስ መምጣት ትንቢት ተናግሯል፤ ሱባዔም ቆጥሯል፡፡ «ሰብአ ሰንበታተ አድሞሙ ለሕዝብከ፤ ሰባ ሰንበት ወገኖችህን ቅጠራቸው፡፡» ይኸውም ክርስቶስ ከ490 ዓመት በኋላ ሰው መሆኑን የሚያመለክት ትንቢት ነው፡፡ እንዲሁም «እስከ ክርስቶስ ንጉሥ ትትሐነፅ መቅደስ ወእምዝ ትትመዘበር፤ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ መቅደስ ትታነፃለች በኋላም ትፈርሳለች» ሲል ተናግሯል፡፡

የአቆጣጠር ስልቱም በዓመት ሲሆን ይኸውም ሰባቱን ዓመት አንድ እያሉ መቁጠር ነው፡፡ ይኽውም ሱባዔ ሰንበት ይባላል፡፡ ዳንኤል ሱባዔ ከቆጠረበትና ትንቢት ከተናገረበት ጀምሮ ክርስቶስ እስከ ሚወለድ 490 ይሆናል፡፡ መስፈርቱ /ማባዣው/ ሰባት ስለሆነ 7’70 ስናባዛው 490 እናገኛለን፡፡ ይኸውም ነቢዩ ሱባዔ ከቆጠረና ትንቢት ከተናገረ ከ490 ዓመት በኋላ የክርስቶስን መወለድ ያመለክታል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተመለከትናቸው ቅዱሳን ነቢያት አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር በማድረግ ሱባዔ ገብተው በትሕርምት በመኖራቸው ድንቅ የሆነውን የክርስቶስን ልደትና ዳግም ምጽአት ለመተንበይ ችለዋል፡፡ ሱባዔ መግባት የራቀን ለማቅረብ የረቀቀን ለማጉላት ብቃትን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያስገኝ መንፈሳዊ ጥበብ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

የሱባዔ ዓይነቶች

  • የግል ሱባዔ/ዝግ ሱባዔ/

የግል ሱባዔ አንድ ሰው ብቻውን ሆኖ በቤትና በአመቺ ቦታ የሚይዘው ማንም ሰው ሳያየው በግሉ የጸሎት በኣቱን ዘግቶ በሰቂለ ኅሊና ሆኖ ፈጣሪው ብቻ እንዲያየው እንዲሰማው በኅቡዕ የሚፈጽመው ሱባዔ ነው፡፡ ማቴ.6፡5-13፡፡ በዚህ ዓይነት መልክ አንድ ሰው ሱባዔ ሲገባ ዘጋ ይባላል፡፡ ዝግ ሱባዔ የያዘ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር ይዞ ወደ በኣቱ ከተከተተ በኋላ ሱባዔው እስኪፈጸም ድረስ ከሰው አይገናኝም፡፡ መዝ. 101-6-7፡፡

  • የማኅበር ሱባዔ

የማኅበር ሱባዔ የሚባለው ካህናት፣ ምእመናን ወንዶችና ሴቶች፣ ሽማግሌዎችና ወጣቶች በአንድ ሆነው በቤተ ክርስቲያንና አመቺ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ ተሰብስበው የሚገቡት ሱባዔ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር በመሄድ ይጸልዩ ነበር፡፡ 1ኛ ሳሙ.1፡9፤ መዝ.121፡1፤ ሉቃ.18፡10-14፡፡

በሐዲስ ኪዳንም የሐዋርያት ተከታዮች የኾኑ መነኮሳት፣ ካህናትና ምእመናን በገዳማት፣ በአድባራት፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ የጽዋ ማኅበርተኞች ስለ ማኅበራቸው ጥንካሬና ከማኅበርተኞቹ መካከል አንዱ ችግር ሲገጥመው የማኅበር ሱባኤ ይያዛል፡፡.

  • የዐዋጅ ሱባዔ

የዐዋጅ ሱባዔ በአገር ላይ ድንገተኛ አደጋ፣ አባር ቸነፈርና ጦርነት ሲነደ እንዲሁም ለማኅበረ ምእመናን አስጊ የሆነ መቅሰፍት ሲከሰት፣ እግዚአብሔር መሽቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ የሚያዝ የሱባዔ ዓይነት ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ሱባዔ የነነዌ ሰዎችና በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ እስራኤላውያን ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የነነዌ ሰዎች የዮናስን ስብከት ሰምተው ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለሦስት ቀን ከመብል ከመጠጥ ተከልክለው በመጾም በመጸለይ እግዚአብሔር መዓቱን በምሕረት ቁጣውን በትዕግሥት እንዲመልስ አድርገዋል፡፡ ሌላው በፋርስ በስደት ይኖር የነበረ አይሁድ በአስቴር ትእዛዝ የያዙት ሱባዔ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚያን ዘመን አርጤክስስ አይሁድ በያሉበት እንዲገደሉ በማዘዙ ከዚህ የጅምላ ጭፍጨፋ ለመዳን አይሁድ በዐዋጅ ሱባዔ ገብተዋል፡፡ አስቴር ገብታ ንጉሡን ስታናግረው ሌላው ሕዝብ በውጭ ዐዋጅ ዐውጀው ሱባዔ ገብተው ፈጣሪያቸውን ተማፅነዋል፡፡ አስቴር 4፡16 – 28፡፡

በአገራችንም ይህን የመሰለ የዐዋጅ ሱባዔ በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ተደርጓል፡፡ ፋሽስት ጣልያን አገራችንን በመውረር ኢትዮጵያን ቅኝ ተገዥ ለማድረግ ድንበሯን አልፎ በመጣበት ወቅት ንጉሠ ነገሥት ምኒልክ፡- «ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ጉልበት የሌለህ በጸሎትህ ርዳኝ» በማለት የዐዋጅ ሱባዔ መያዛቸው ይነገራል፡፡ በዚህም መሠረት በየገዳማቱ ምሕላ ተይዟል፤ ንጉሡም ታቦተ ጊዮርጊስን ይዘው ዓለምን እጅግ ያስደነቀ ጥቁሮችን ለነጻነታቸው እንዲነሣሱ የሚያስችል ፋና ወጊ የሆነ ድል አግኝተው አገራችንን ለቅኝ ግዛት ያሰበውን ፋሽስት ጣልያንን ማሸነፋቸው በከፍተኛ ስሜት የምናስታውሰው ነው፡፡

ቅድመ ዝግጅት

ሱባዔ መግባት የሚፈልግ ምእመን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ያለምንም ዝግጅት ሱባዔ መግባት ለፈተና ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/፣ ጊዜ ሱባዔ/ በሱባዔ ጊዜና ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/ ዝግጅት አስፈላጊ ነው፡፡

ቅድመ ሱባዔ /ሱባዔ ከመግባት አስቀድሞ/

በመጀመሪያ ሱባዔ የምንገባበትን ምክንያት ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ሰው ሱባዔ የሚገባበትን ዓላማ ለይቶ ካስቀመጠ ከሱባዔ በኋላ የሚጠበቀውን ነገር ማግኘት አለማግኘቱን ይረዳል፡፡ ይህ ሳይሆን ሱባኤ ቢገባ ከሱባኤው በኋላ የጠየቀው ነገር ስለሌለ ትርጉም ያጣል፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ለምን ሱባኤ ለመግባት እንዳሰብን ለይተን ማወቅ ይኖርብናል፡፡

ሱባዔ ለመግባት የወሰንበትን ምክንያት ከለየን በኋላ ምክንያታችንን ይዘን የንስሐ አባታችንን ማማከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በምክረ ካህን መጓዝ መጀመር ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር በአባትነታቸውና በሕይወት ልምዳቸው ምን ማድረግ እንደሚገባን ምክር ለማግኘት እገዛ ያደርግልናል፡፡ ቅድመ ሱባኤ ከንስሐ አባት ጋር መመካከር ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በሱባዔ ወቅት የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙት የተሰጠውን ምክር በመጠቀም ፈተናውን ለመቋቋም ይችላል፡፡ እንዲሁም የንስሐ አባቱ በሱባዔ ወቅት በጸሎት እንዲያስቡት መማከር የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡

ሱባዔ ለመግባት ስናስብ ለምን ያህል ቀናት መቆየት እንዳለብን መወሰን ያስፈልጋል፡፡ ሱባዔ ከዚህ እስከዚህ እቆያለሁ ብለን ዕቅድ የምንይዝበት ነው፡፡ እንደ አቅማችንና እንደ ችሎታችን ከዚህ ቀን እስከዚህ ብለን በመወሰን ሱባዔ መግባት ተገቢ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፡- ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖረው አንድ ሰው «በዋሻ እዘጋለሁ» ቢል ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ምክንያቱም በሱባዔ ወቅት ፈተና ስለሚበዛ የሚመጣበትን ፈተና መቋቋም ባለመቻል ሱባዔው ሊቋረጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ ቅድመ ሱባዔ ዐቅምንና ችሎታን አገናዝቦ መወሰን ተገቢ ነው፡፡

ሌላው ቅድመ ሱባዔ ለሱባዔ ተስማሚ የሆነ ወቅትና ቦታ መምረጥ ተገቢ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን በአብዛኛው ሱባዔ የሚገባው አጽዋማትን ተከትሎ ነው፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንገባበት ወቅት የጾም ወቅት መሆን አለመሆኑን መለየት ያስፈልጋል፡፡ በአጽዋማት ወቅት የሚያዝ ሱባዔ ለተሐራሚ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡ ምክንያቱም በአጽዋማት ወቅት ብዙ አባቶች ሱባዔ ስለሚይዙ ከአባቶች ጸሎት ጋር ልመናችንና ጸሎታችን ሊያርግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወቅትን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ላይ «ከወርኃ አጽዋማት ውጭ ሱባዔ አይያዝም» የሚል አቋም ለመያዝ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ፈተና ከአጋጠመው በማንኛውም ጊዜ ሱባዔ ሊገባ እንደሚችል እዚህ ላይ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ ከዚህም ባሻገር ሱባዔ የምንይዝበትን ቦታ መምረጥ አለብን፡፡ ለሱባዔ የምንመርጣቸው ቦታዎች ለፈተና የሚያጋልጡ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይኸውም ሱባዔ ከተገባ በኋላ ኅሊናችን እንዳይበተን እገዛ ያደርግ ልናል፡፡ ጫጫታና ግርግር የሚበዛበት ቦታ በሰቂለ ኅሊና ለመጸለይ አያመችም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ የምንይዝባቸው ቦታዎች ከከተማ ራቅ ያሉ ገዳማትና አድባራት ተመራጭ ናቸው፡፡

ጊዜ ሱባዔ /በሱባዔ ጊዜ/

በጸሎት ሰዓት ዓምድና ግድግዳ ሳይደገፉ መቋሚያ ሳይዙ በሁለት እግር ቀጥ ብሎ በመቆም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ እንዲሁም ፊትን ወደ ምሥራቅ መልሶ መቆም ወዲያና ወዲህ ወደ ግራ ወደ ቀኝ አለመዟዟር በሰፊሐ እድ በሰቂለ ኅሊና ኾኖ መጸለይ ይገባል፡፡ መዝ.5፡3፤ መዝ.133፡2፤ ዮሐ.11፡41፡፡

በሱባዔ ወቅት በቅደም ተከተል መጸለይ አለብን፡፡ መጀመሪያ «በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አአትብ ገጽየ ወኩለንታየ በትእምርተ መስቀልኸ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አንዱ አምላክ መላ ሰውነቴን በትእምርተ መስቀል አማትባለሁ» እያለ ሰጊድን ከሚያነሣው ሲደርስ መስገድ መስቀልን ከሚያነሣ ላይ ስንደርስ ማማተብ ይገባል፡፡

በማስከተል አቡነ ዘበሰማያት፣ መዝሙረ ዳዊት፣ ውዳሴ ማርያምና ሌሎች በመዝገበ ጸሎት የተካተቱትን መጸለይ፤ ቀጥሎ አቡነ ዘበሰማያት፣ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምን፣ ጸሎተ ሃይማኖትን ከጸለይን በኋላ አቡነ ዘበሰማያት መድገም፤ ከዚያ 41 ጊዜ ኪርያላይሶን ይባላል፡፡ ሌላው በሱባዔ ጊዜ ከተሐራሚ የሚጠበቀው ነገር ኃጢአቱን እያሰበ ማዘን ማልቀስ ነው፡፡ ሲያለቅስም ለእያንዳንዱ በደል እንባ ማፍሰስ ያስፈልጋል፡፡

በመጨረሻም ሱባዔ የገባ ሰው ሱባዔውን ሳይጨርስ ወይም ሱባዔውን አቋርጦ ከማንም ሰው ጋር ፈጽሞ መገናኘት የለበትም፡፡

ድኅረ ሱባዔ /ከሱባዔ በኋላ/

ለቀረበ ተማኅፅኖ እግዚአብሔር የሚያደርግልንን ነገር መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እግዚአብሔር ላቀረብንለት ምልጃና ጸሎት እንደ ልባችን መሻት እንደ እርሱ ቸርነት እርሱ በወደደ ጊዜ ያደርግልናል፡፡ ሱባዔ የገባ ሰው ሁሉ ራእይ ላያይ ይችላል፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መልስ አሰጣጥ ለማንም ግልጽ አይደለም፡፡ ከሱባዔ በኋላ መጀመሪያ የምናገኘው የኅሊና ሰላምን ነው፡፡ ይህ ትልቅ የአምላክ ስጦታ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሱባዔ ገብተን ያሰብነውን ካላገኘን ዳግመኛ ተዘጋጅተን እስከ መጨረሻው ሰዓት መማፀን መጽናት ይኖርብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ክረምት

ሐምሌ 14 ቀን 2004 ዓ.ም.

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ


“ክረምተ ወሐጋየ ዘአንተ ፈጠርከ” መዝ.73÷17 “በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ” መዝ.71÷17

እግዚአብሔር የዓለምን ምግብ ሥጋዊውንም መንፈሳዊውንም በአራት ከፍሎታል ሥጋዊውን በአራቱ ክፍላተ ዘመን መንፈሳዊውን በአራቱ ወንጌላዊያን ትምህርት፡፡ የሰው ሥጋዊ ምግብና ከአራቱ ክፍላተ ዘመን እንዳይወጣ መንፈሳዊ ምግብናውም ከአራቱ ወንጌላውያን አይወጣም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር አምላካችን የሥጋም የነፍስም ፈጣሪ፣ መጋቢ ነውና፡፡ አሁን ያለንበት ከአራቱ ክፍላተ ዘመን አንዱ የሆነው ክረምት ነው፡፡ከዚህም የምናገኘው ሥጋዊ ምግብ ብቻ ሳይሆን ከሥጋዊ ምግብ ያለፈ መንፈሳዊ ምግብም አለ፡፡

 

ክረምት ምንድነው?

ክረምት ማለት ከርመ ከረመ ካለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ሲሆን መክረም የዓመት መፈጸም፣  ማለቅ መጠናቀቅ ማለት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በፀሐይ አማካኝነት የደረቁ ኮረብቶች ተራሮች በዝናም አማካኝነት ውኃ የሚያገኙበት በዚህም ምክንያት በልምላሜ የሚሸፈኑበት፣ የደረቁ ወንዞች ጉድጓዶች ውኃ የሚሞሉበት፣ በፀሐይ የተቃጠለች ምድር ከሰማይ በሚወርድ ጠለል በረከት የምትረካበት፣ በውኃ ጥም የተሰነጣጠቁ የምድር ጉረሮዎች ውኃን የሚጠግቡበት፣ ሰማይ  በደመና የተራሮች ራስ በጉም  የሚጎናጸፉበት በሙቀት ፋንታ ቅዝቃዜ በድርቅ ፈንታም ልምላሜ የሚነግስበት ተሰባብሮ የወደቀ ሐረግ ቀና ብሎ ከየቦታው የሚሳብበት ወቅት  ነው፡፡

 

ክረምት

1.    ወርኃ ማይነው /የውኃ ወር፣ ወቅት ነው/ ውኃ ደግሞ እግዚአብሔር ለፈጠረው ፍጥረት ሁሉ በጣም አስፈላጊ ነው ከሥጋዊ ምግብና ስንነሣ ያለ ውኃ ለምግብነት የሚውል ነገር በዓለማችን ውስጥ የለም ምድር የዘሩባትን እንድታበቅል የተከሉባትን እንድታጸድቅ ያጸደቀችውን ተክልም ለፍሬ እንድታበቃ ውኃ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህምበኋላ ያለ ውኃ ምግብ መሆን የሚችል የለም፡፡ እሚቦካው በውኃ የሚጋገረውም በውኃ ወጥ የሚሠራው የሚበላው የሚወራረደውም በውኃ ነው፡፡ የውኃን ጥቅም አበው በምሳሌ እንዲህ በማለት ያብራራሉ፡-  ከ ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡ ውኃ ቢያንቅ በምን ይውጡ ቁሳቁሱ በውኃ ይታጠባል፤ ከቆሻሻ ይለያል የሚሠራው ቤትም ቢሆን ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ፣ ሲሚንቶው፣ ብረቱ፣ ቢኖር ያለውኃ ሊሠራ አይችልም፡፡ በባሕር ውስጥ ለሚኖሩ ዓሣ አንበሪ፣ አዞ፣ ጉማሬ፣ምግብ ለሚሆኑትም ለማይሆኑትም ውኃ አስፈላጊ ነው፡፡ ውኃ ለሁሉም አስፈላጊ መሆኑ የተረጋገጠ ቢሆንም ከፍጡራን በተለየ ውኃ ለሰው ልጅ ያስፈልገዋል፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ከሚጠቀምባቸው ፍጡራን ያለ ውኃ ምግብ ሊሰጥ የሚችል የለምና፡፡ እንስሳት ውኃ ይፈልጋሉ ምድርም ውኃ ትፈልጋለች አትክልት፣ እፅዋት ውኃ ይፈልጋሉና ጠቅላላውን የፍጡራን ሕይወት የውኃ ጥገኛ ነው፡፡

 

ከዚህ አንፃር ከዓለማችን ብዙውን ቦታ የሚሸፍነው ውኃ መሆኑን ሥነፍጥረትም ሳይንስም ይስማሙበታል፤ ምክንያቱም በምድር ላይ ካለፍጡር የማያስፈልገው የለምና ከዚህም በተጨማሪ እቤታችን ውስጥ የሚሠሩ እቃዎች የሸክላም ይሁኑ የብረት በውኃ የተሠሩ ናቸው ከዚህ አለፍ ብለን ስንመለከት በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረ የሰው ልጅ ከተፈጠረባቸው አራት ባሕርያት አንዱ ውኃ ነው፡፡ በመሬትነት ባሕርዩ እየፈረሰና እየተቆረሰ ዓለምን እንዳያጠፋ በውኃነት ባሕርዩ አንድነቱ ጸንቶለት ይኖራል በእሳትነት ባሕርዩ ዓለምን እንዳያቃጥል በውኃነት ባሕርዩ እየቀዘቀዘ ይኖራል፡፡ ሰው ከእናቱ ተወልዶ  የእናቱን ጡት ጠብቶ እንዲያድግ ሰውም ከውኃ፣ ከእሳት፣ ከነፋስና ከመሬት ተፈጥሮ እነዚሁ የተገኘባቸውን ተመግቦ የሚኖር መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የአራቱ ባሕርያት አስታራቂ ሽማግሌ ውኃ ነው፡፡ጠበኞች የሆኑ ነፋስና መሬት በውኃ ይታረቃሉ ነፋስ መሬትን ይጠርገዋል፡፡ መሬትም ነፋስን ይገድበዋል፡፡ዝናም በዘነመ ጊዜ ትቢያው የመሬት ላይኛው ክፍል በውኃ አማካኝነት ከታችኛው ክፍል ጋር አንድ ይሆናል በነፋስ መጠረጉም ይቀርለታል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ ስለ ውኃ የእግዚአብሔር መሣሪያነት እናያለን፡፡

በኃጢአት የተበላሸው የቆሸሸው ዓለም የተቀጣው በውኃ መሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ የሚመሠክረው እውነት ነው፡፡ ዘፍ.6÷1፣ 7÷1፣ 8÷1 እስከ ፍጻሜያቸው ማንበብ ለዚህ በቂ መልስ እናገኝበታለን፡፡ ኤልያስ አምልኮ እግዚአብሔር በአምልኮተ ጣዖት ተክተው ሃይማኖተ ኦሪትንት ተው የጣዖት ውሽማ አበጅተው ያስቸገሩትን አክአብና ኤልዛቤልን እንዲሁም መሰሎቻቸውን የቀጣው ሰማይ ዝናም ለዘር ጠል ለመከር እንዳይሰጥ ሰማይ ለጉሞ ዝናም አቁሞ ነው፡፡ በአንጻሩ በረድና እሳት አዝንሞ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡

 

“ኤልያስ ዘከማነ ሰብዕ ውእቱ ወጸሎ ተጸለየ ከመ ኢይዝንም ዝናም ወኢዘንመ ዝናም ሠለስተ ዓመተ ወስድስተ አውርሀ ወካዕበ ጸለየ ከመይዝንም ዝናም ወወሀበ ሰማይ ዝናሞ ወምድርኒ አብቆለት ፍሬሃ” ያዕ.5÷17 ኤልያስ እንደኛ የሆነ ሰው ነበር ዝናም እንዳይዘንም አጥብቆ ጸለየ በምድርም ላይ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ዝናም አልዘነበም ሁለተኛም ጸለየ ሠማዩም ዝናብን ሰጠ ምድር ፍሬዋን አበቀለች፡፡ በማለት የሰው ልጆች ሕገ እግዚአብሔርን ሲጥሉ ትእዛዘ እግዚአብሔርን ሲያፈርሱ ከሕጉ ሲወጡ ከአምልኮቱ ሲያፈነግጡ ውሃ መቅጫ መሳሪያ በመሆኑም ይታወቃል ውኃ እስከ አሁን የተመለከትነው በሥጋዊ ምግብነቱ ያለውን ነው፡፡

 

ከዚህ ውጪ መንፈሳዊ ምግብናውስ ብንል፡፡ አሁን ካየነው የጎላ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡”

ደገኛዋ የሰው ልጆች ጥምቀት በውኃ መሆኑ የውኃን ጥቅም የጎላ መሆኑን ያሳየናል፡፡ ይኸውም እንደምናውቀው የጥምቀታችን መሥራች ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ ተጠምቆ የአባቶቻችንና በኛ ላይ የነበረው የእዳ ደብዳቤ ያጠፋልን በውኃ በመጠመቁ ነበር ማቴ.3÷13 ከዚህ በኋላ “ከውኃና ከመንፈስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ዮሐ.3÷5 ብሎ ውኃ ከሥጋዊ ምግብናው ያለፈ እኛ የእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበት ምሥጢር መፈጸሚያ መሆኑን ይነግረናል፡፡ በሌላ መልኩ ጌታችንን የእኛን ሥጋ ለብሶ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገልጾ ባስተማረበት ጊዜ እንጀራ ለመነ ሳይሆን ውኃ ለመነ የሚል ነው የተጻፈለት፡፡ “ኢየሱስም ውኃ አጠጭኝ አላት” ዮሐ. 4÷7 አሁን ከዚህ የምንመለከተው እስራኤል 40 ዓመት ውኃ ከጭንጫ ያጠጣ አምላክ ውኃ አጥቶ ይመስላችኋል ውኃ ትልቅ ምሥጢር የሚፈጸምበት መሆኑ ለመግለጽ ነው እንጂ ይኸውም ሊታወቅ “የእግዚአብሔር ስጦታ ውኃ አጠጭኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ አንቺ ትለምኚው ነበር እንጂ የሕይወት ውኃም ይሰጥሽ ነበር” ከዚህ ውኃ የሚጠጣ ዳግመኛ ይጠማል እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ግን ለዘለዓለም አይጠማም ብሎ አስተምሮአል፡፡” ያውም ውኃ የተባለው ትምህርት ልጅነት በሌላ መልኩ እራሱ መሆኑንም ነው የሚያስረዳን በመስቀል ላይ እያለም ከተናገራቸው 7ቱ የመስቀል ንግግሮች አንዱ “ተጠማሁ የሚል ነበር፡፡ ዮሐ.19÷29 ይኸ ከሥጋ መጠማት ያለፈ የእኛን የነፍሳችን ጥማት እንደአጠፋልን የምንማርበት ነው፡፡ እኛን የሕይወት ውኃ ያጠጣን ዘንድ ተጠማሁ አለም፤ ከዚህም የተነሣ ቀደም ሲል በነቢዩ ኢሳኢያስ እንዲህ ሲል ተናገረ፡፡ “እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ ወደ ውኃ ኑ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ” ኢሳ.55÷1 ብሎ በዓለም ላሉ ፍጡራን ውኃ አስፈላጊ ቢሆንም ቅሉ በተለይ ለሰው ልጆች እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል፡፡

 

የተጠማ ይምጣ ይጠጣ የሚለው ብዙ ምሥጢር ያለው ነው ጌታችን የአይሁድ በአል በሚከበርበት ቦታ ተገኝቶ ቀደም ሲል በኢሳይያስ የተነገረውን ቃል ስለ መንፈስ ቅዱስ የተነገረ መሆኑን ገልጾአል፡፡ “ኢየሱስም ቆሞ ማንም የተጠማ ቢኖር ወደ እኔ ይምጣና ይጠጣ በእኔ የሚያምን መጽሐፍ እንዳለ የሕይወት ውኃ ወንዝ ከሆዱ ይፈልቃል ብሎ ጮኸ” ይኸን ግን በእርሱ የሚያምኑ ሊቀበሉት ስለአላቸው ስለ መንፈስ ቅዱስ ተናገረ፡፡  ዮሐ.7÷37-39 ስለዚህ ውኃ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ሆኖአል ውኃ ከቆሻሻ ከእድፍ እንዲያነጻ መንፈስ ቅዱስም ከኀጢአት ከርኲሰት ከክፋት፣ ከተንኮል፣ ከበደል ሰውን ያነጻልና፡፡ ከክረምት አንደኛው ክፍል ወርኃ ማይ የውኃ ወቅት ይባላል፡፡

 

2.    ክረምት ወርኃ ዘር ነው፡፡ የዘር ወቅት ወይም ጊዜ ነው፡፡ ገበሬው በበጋ ያረሰውን የከሰከሰውን ደረቅ መሬት በዝናብ ወቅት አለስልሶ አዘጋጅቶ ከጎታው ወይም ከጎተራው ያስቀመጠውን ዘር ባዘጋጀው መሬት ላይ አውጥቶ የሚዘራበት መሬቱ ያብቅል አያብቅል ፍሬ ይስጥ አይስጥ ሳያውቅ እግዚአብሔር በዝናብ አብቅሎ በፀሐይ አብስሎ ይመግበኛል ብሎ በማመን ያለምንም ጥርጥር የጎታውን እህል ለመሬት አደራ የሚሰጥበት ከላይ ዝናሙን ከታች ጭቃውን ታግሶ በሬዎችን እየነዳ በትከሻው ላይ ዘርና ቀምበር ተሸክሞ ዘር ለመዝራት ይሰማራል፡፡

 

የገበሬውን ሁኔታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡፡ “ናሁ ወጽአ ዘራኢ ከመ ይዝራዕ ዘርዖ” ዘሪ ሊዘራ ወጣ ሲዘራም አንዳንዱ ዘር ከመንገድ ዳር ወደቀ በጭንጫ ላይ የወደቀ ዘር አለ በሾህ መካከል የወደቀ ዘርም አለ በመልካም መሬት ላይም የወደቀ ዘር አለ፡፡ መቶ ስልሳ ሠላሳ ፍሬ ሰጠ” ማቴ.13÷1 ብሎ ራሱን በገበሬ ቃሉን በዘር የሰማዕያን ልቡና በመንገድ፣ በዐለት፣ በእሾህ፣ በለሰለሰ መሬት መስሎ አስተምሯል፡፡ በመንገድ የተመሰለው ሰምተው የማያስተውሉ ሰዎች ልቡና ነው የሰማይ ወፎች የተባሉ ደግሞ አጋንንት ናቸው፡፡ “ኢትህሚ ሰብአ በቤትከ እስመ ዖፈ ሰማይ ያወጽዖ ለነገርከ” መክ.10÷20

 

በቤትህ ውስጥ ንጉሥ አትስደብ የሰማይ ወፍ/ዲያብሎስ/ ቃሉን ነገሩን ይወስደዋልና” እንዲል በዐለት የተመሰሉት ፈጥነው የሚሰሙ ግን ተግባር ላይ የሌሉ በእሾህ የተመሰሉትም የዚህ ዓለም ሀሳብ ምድራዊ ብልጽግና ፍቅረ ዓለም አስሮ የያዛቸው ሰዎች ሲሆኑ በመልካም መሬት የተመሰሉት ቃሉን ሰምተው የጽድቅ ሥራን የሚሠሩ ናቸው፡፡ በወርኃ ዘር የምንማረው ትልቁ ትምህርት ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን ነው፡፡ በወርኃ ማይ ምሥጢረ ጥምቀትን እንደተማርን ገበሬው በጎታው ያከማቸውን እህል ከአፈር ጋር አንድ እንደሚያደርገው ማለት በአፈር ላይ እንደሚዘራው የሰው ዘርም እንዲሁ ውሎ ውሎ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት እንዲሉ ሲሞት በመቃብር ከአፈር ጋር አንድ ይሆናል ይፈርሳል ይበሰብሳል ወደ አፈርነቱ ይመለሳል፡፡ “ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ አፈር ነህና ወደ አፈርነትህም ትመለሳለህና” እንዳለ ዘፍ.3÷19 የተዘራው ዘር በዝናቡና በተዘራበት አፈር አማካኝነት ይፈርሳል ይበቅላል ይለመልማል፣ ያብባል ፣ ፍሬ ይሰጣል ሰውም እንደዚሁ ነው፡፡ ይፀነሳል፣ ይወለዳል፣ ያድጋል ይሞታል፡፡

 

ወደ መሬት ይመለሳል ይፈርሳል፡፡ ትንሣኤ ዘጉባኤን ጠብቆ ይነሣል፡፡ ይህን በተመለከተ ጌታችን ሲያስተምር “ለዕመ ኢወድቀት ህጠተ ስርናይ ውስተ ምድር ወኢሞተት ባህቲታ ትነብር ወእመሰ ሞተት ብዙኀ ፍሬ ትፈሪ” ዮሐ.12÷24 የስንዴ ቅንጣት በምድር ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች” ሰውም ካልሞተ አይነሣም ካልተነሣም መንግሥተ ሰማያት ሊገባ አይችልምና፡፡ ምክንያቱም ግብር እምግብር ሳይለወጡ መንግሥተ ሰማያት አይገባምና ስለዚህ ሰው ትንሣኤ እንዳለው ገበሬ ከሚዘራው ዘር መማርና ብዙ ፍሬ ማፍራት ይጠበቅበታል ቅዱስ ጳውሎስም ትንሣኤ ሙታንን ባስተማረበት መልእክቱ ይህንኑ ያጎላልናል፡፡ “ኦ አብድ አንተ ዘትዘርዕ ኢየሀዩ ለዕመ ኢሞተ” 1ቆሮ.15÷35 ነገር ግን ሰው ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ አይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል አንተ ሞኝ የቆሮንቶስ ገበሬ አንተ የዘራኸው ካልሞተ ሕያው አይሆንም የምትዘራውም ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት /በቆሎ ኑግ/ የአንዱ ቢሆን ቅንጣት /ፍሬ/ ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል፡፡

 

ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል፣ ሥጋ ሁሉ አንድ አይደለም የሰው ሥጋ ግን አንድ ነው የእንስሳ ሥጋ ሌላ ነው የዓሣም ሥጋ ሌላ ነው ደግሞ ሠማያዊ አካል አለ ምድራዊም አካል አለ ነገር ግን የሰማያዊ አካል ክብር ልዩ ነው፡፡ የምድራዊ አካል ክብርም ልዩ ነው የፀሐይ ክብር አንድ ነው፡፡ የጨረቃ ክብር ሌላ ነው የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና፡፡ የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው በመበስበስ ይዘራል፣ በአለመበስበስ ይነሣል በውርደት /አራት አምስት ሰው ተሸክሞት/ ይዘራል/ይቀበራል፡፡ በክብር ይነሣል በድካም ይዘራል በኀይል ይነሣል ፍጥረታዊ አካል ይዘራል/ ሟች ፈራሽ በስባሽ አካል ይቀበራል/ መንፈሳዊ አካል ይነሣል ማለት የማይሞት የማይታመም የማይደክም ሆኖ ይነሣል” በማለት ወርኃ ዘር የትንሣኤ ሙታን መማሪያ መሆኑን ጽፎአል ከዚህ ላይ አንድ ገበሬ ስንዴ ከዘራ ስንዴ ጤፍ ከዘራ ደግሞ ጤፍ በቆሎም ከዘራ በቆሎ ኑግ ቢዘራ ኑግ እንደሚሆን አካሉን ለውጦ እንደማይበቅል ሰውም የራሱን ማንነት ይዞ የሚነሳ መሆኑንም ጭምር ነው ያስተማረን ሰው ክፉ የሠራም ሥራው ጽድቅ የሠራም የራሱን ሥራ ይዞ ይነሣል እንጂ ጻድቁ ኀጥዕ ኀጥዑ ጻድቅ ሆኖ  አይነሣም፡፡ እንደ ሥራው ዋጋውን የሚቀበልበት ነውና፡፡ “ሰው የዘራውን ያጭዳል” እንዲል ገላ.6÷7 በሌላም አንቀጽ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡፡ “በጥቂት የሚዘራ በጥቂት ያጭዳል በበረከትም የሚዘራ ደግሞ በበረከት ያጭዳል” 2ቆሮ.9÷6 ይህንም ስለመስጠትና መቀበል አስተምሮታል የዘራ እንደሚሰበስብ የሰጠም ዋጋውን አያጣምና የተዘራባት ምድር የዘሩባት አብዝታ እንደምትሰጥ በምጽዋት መልክ የተቀበሉ ነዳነያንም ትልቅ ዋጋ ያሰጣሉና በሚያልፍ የማያልፍ በሚያልቅ የማያልቅ ዋጋ ያስገኛሉና ምጽዋት በዘር መስሎታል “ዘርን ለዘሪ ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል” 2ቆሮ.9÷10 ጠቅለል አድርገን ከብዙ በጥቂቱ ከረጅሙ ባጭሩ ስናስቀምጠው ወርኃ ዘር በዚህ መልኩ ተገልጿል፡፡ “ብዙ ጊዜ በእርሷ ላይ የሚወርደውን ዝናብ የምትጠጣ መሬት ለሚያርሷትም ደግሞ የምትጠቅመን አትክልት የምታበቅል ከእግዚአብሔር በረከትን ታገኛለችና እሾህንና ኩርንችትን ግን ብታወጣ የተጣለች ናት ለመርገምም ትቀርባለች መጨረሻዋ መቃጠል ነው” ዕብ.6÷7 ከዚህም መሬት የተባለ የሰው ልጅ ዘር የተባለ ቃል እግዚአብሔር ዝናም የተባለ ትምህርት እሾህ የተባለ ኀጢአት ክፋት ነው ምድር የዘሩባት ባታበቅል መጨረሻዋ መቃጠል እንደሆነና የሰው ልጅም አደራውን ባይጠብቅ የንስሓ ፍሬ ባያፈራ ፍጻሜው መከራ ነውና፡፡ ሰው እንደ ዘር ወደ መሬት እንደሚመለስ ዘሩ ፈርሶ በስብሶ ከበቀለ በኋላ ፍሬ እንደሚሰጥ ሰውም ከሞተ በኋላ ትንሣኤ ያለው መሆኑን በማሰብ መልካም ሥራን መሥራት እንደሚገባው እንማራለን፡፡ ከዚህ አለፍ ብለን ዘር የሚለውን ስንመለከተው ድንቅ ምሥጢር ያዘለ መሆኑንም ጭምር  እንገነዘባለን፡፡

 

“የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር” ኢሳ.1÷9 ይህ ዘር ነቢያት፣ ደቂቀ ነቢያት፣ በተለይም እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእርሷ እኛ ለማዳን የተወለደውን ክርስቶስ ያሳየናል፡፡” የነሣውን ሥጋ ከመላእክት የነሣው አይደለም ከአብርሃም ዘር ነው እንጂ” እንዲል ዕብ.2÷16 ቅዱስ ጴጥሮስ ይህ ዘር ምን ያህል ታላቅ መሆኑን ሲያስረዳ “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም በሕያውና ለዘለዓለም በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ” 1ጴጥ.1÷23 ስለዚህ የማይጠፋ ዘር የተባለው ክርስቶስ ነው፡፡ ከእርሱ ተወልደናልና እርሱንም በመከራው መስለነው በትንሣኤውም ልንመስለው ያስፈልጋል፡፡

 

3.    ክረምት ወርኃ ልምላሜ ነው፡- በክረምት ወቅት ከዘር ተከትሎ ምድር በቅጠል በልዩ ልዩ የልምላሜ ዓይነቶች አሸብርቃ ደምቃ በዋዕየ ፀሐይ የተራቆተ ማንነቷ በቅጠል የሚሸፈንበት ወቅት በመሆኑ ወርኃ ልምላሜ ነው፡፡ ፍሬ ግን የለም ይህን ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ሰማይን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃል ሳርን በተራሮች ላይ ያበቅላል ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም ለሚጠሩት ለቁራዎች ጫጩቶች ለእንስሶችም ምግባቸውን ይሰጣል” መዝ.146÷8-10 በማለት ወቅቱ የልምላሜ የሣርና የቅጠል እንስሳት ሣሩ ቅጠሉን ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ የሚያገኙበት እንደሆነ ገልጿል፡፡

 

ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው በቢታንያ መንገድ ላይ በተራበ ጊዜ ያያት በለስ ቅጠል ብቻ እንደነበረች በወንጌል ተጽፏል፡፡ “በማለዳም ወደ ከተማ ሲመለስ ተራበ በመንገድም አጠገብ በለስ አይቶ ወደ እርሷ መጣ ከቅጠል በቀር ምንም ፍሬ አላገኘባትምና ለዘለዓለሙ ፍሬ አይገኝብሽ አላት በለሲቱም ያን ጊዜውን ደረቀች” ማቴ.21÷18 ይላል፡፡ ይኸውም ጊዜው ክረምት ነበር፡፡ ወርኃ ቅጠል የነቢያትን ዘመን ይመስላል በነቢያት በዘመነ ነቢያት ሁሉም በተስፋ ብቻ ይኖሩ እንደነበር እንዲህ ተገልጿአል፡፡ “ብዙ ነቢያትና ጻድቃን ሊያዩ ተመኙ አላዩም የምትሰሙትን ሊሰሙ ተመኝተው አልሰሙም” ማቴ.13÷16 ገበሬውም የዘራውን ዘር ቅጠሉን በተስፋ እየተመለከተ አረሙን እየነቀለ ዙሪያውን እያጠረ እየተንከባከበ ይጠብቃል ደግሞም ፈጣሪውን ከበረድ እንዲጠብቅለት እየተማጸነ የራት ሰዓት እስኪደርስ መቆያ እንዲቀምስ ይህ ቅጠል ፍሬ እስኪሰጥ በተስፋ አለኝ እያለ ቅጠሉን የዐይን ምግብ አድርጎ ይጠባበቃል፡፡ በሌላ መልኩ የእግዚአብሔር መንግሥት ዘሪ በእርሻው ላይ የዘራውን ዘር እንደምትመስል ተጽፏል፡፡

 

“በምድር ዘርን እንደሚዘራ ሰው የእግዚአብሔር መንግሥት እንዲህ ናት ሌሊት ይተኛል ቀን ይነሣል እርሱም /ገበሬውም/ እንዴት እንደሚሆን ሳያውቅ ዘሩ ይበቅላል ያድግማል ምድሪቱም አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ በዘለላው ፍጹም ፍሬ ታፈራለች ፍሬ ግን ሲበስል መከር ደርሷልና ወዲያው ማጭድ ይልካል፡፡ ማር.4÷26-29 ፍሬ እስከምታፈራ ግን ገበሬው እንደሚጠብቅ ነው የሚያስተምረን በገበሬው የተመሰለው ኢየሱስ ክርስቶስም እኛ በዓለም ላይ ያለን የሰው ዘሮች በሙሉ በመከር ያፈራውም ያላፈራውም እንዲሰበሰብ ያሳየናል፡፡ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ጌታ እስኪመጣ ድረስ እነሆ ገበሬው የፊተኛውን የኋለኛውን ዝናም እርሱን የታገሰ የከበረውን የምድር ፍሬ ይጠብቃል እናንተም ደግሞ ታገሡ” የዕ.5÷7-9 ገበሬ ቅጠሉ ፍሬ እስከሚሰጥ ምን ያህል መከራን እንደሚታገስ እኛም መንግሥተ ሰማያት ለመግባት ቅጠል ብቻ የሆነ ማንነታችን የንስሐ ፍሬ እስኪያፈራ ድረስ መከራውን መታገስ እንደሚገባን ያስተምራል፡፡ ምድራዊ ፍሬ ለማግኘት ይህን ያህል መጠበቅ መታገስ ካስፈለገ ሰማያዊ ዋጋ ለመቀበል ምን ያህል መታገስ ያስፈልግ ይሆን? ከወርኃ ቅጠል የምንማረው ያለፍሬ ብንገኝ መርገምን እንደምናተርፍ ብናፈራ ግን ገበሬ ደስ ብሎት ምርቱን ደስ ብሎት እንዲሰበስብ ፈጣሪያችንም በእኛ የሚደሰት መሆኑን እናውቃለን እኛም ዋጋችንን እንደምናገኝ እንማራለን፡፡ ክረምት ጥልቅ ትምህርት የምንማርበት እግዚአብሔር በሰፊው የሚገለጽበት ነው፡፡

 

ይቆየን

ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ

 
ዲያቆን ታደሰ ወርቁ
 
እነዚህ ሁለት ቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አዕማድ ናቸው፡፡ በመሠረትነት በአጸኗት ቤተክርስቲያን ያላቸው የክብር ሥፍራ ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም፡፡ ለቤተክርስቲያንና በቤተክርስቲያን የፈጸሙት አገልግሎት በዚህም የተቀበሉት ሰማዕትነት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን መልካም የሆነውን ታሪካቸውን ለእኛ አርአያነት በሚሆን መልኩ ከትበውልናል፡፡ እኛም ለአርአርያነት በሚሆን መልኩ የእነዚህን ደጋግ ሁለት ቅዱሳን አባቶች ታሪክ፣ ዕውቀትና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ከዚህ በመቀጠል አቅርበናል፡፡
 
 
1. ሁለቱ ሐዋርያት ሲጠሩ የነበሩበት ሕይወት
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በገሊላ ባሕር ዳር በምትገኘው በቤተ ሳይዳ ሲወለድ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በጠርሴስ ከተማ ተወለደ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር በገሊላ ባሕር ዓሣ ማሥገር ጀመረ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በ 15 ዓመት ዕድሜው በገማልያ ትምህርት ቤት በመግባት የአይሁድን ሕግና ሥርዓት ተምሯል፡፡ በ30 ዓመቱም የአይሁድ ሸንጎ አባል ሆኗል፡፡ /1ቆሮ.1.17፤ሐዋ.22.3/
 
ቅዱስ ጴጥሮስ ባለትዳር ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በድንግልና የኖረ አባት ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕጋዊ /ባለ ትዳር/ ሆኖ ይኖር እንደነበር በማቴዎስ ወንጌል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጴጥሮስን አማት ማዳኑ መጠቀሱ አመላካች ሲሆን ጳዉሎስ ድንግል ስለመሆኑ ደግሞ ራሱ ለቆሮንቶስ ምእመናን በጻፈው ላይ ያረጋገጠው ነው፡፡ /ማቴ.8.14-15፣ 1ቆሮ.7.8፣9.5/  ይህም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያገቡትንም ሆነ በድንግልና የሚኖሩትን ለአገልግሎት እንደሚቀበል አመላካች መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
 
2. የሁለቱ ሐዋርያት ተክለ ቁመና
 
ቅዱስ ጴጥሮስ ፊቱ ሰፋ ያለ ሲሆን መካከለኛ ቁመት የነበረው፤ ራሰ በራ ሰው ነው፡፡ በማናቸውም ነገር ፈጣንና ቀልጣፋ ነበር፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ ጭንቅላቱ ትልቅ ሲሆን ራሰ በራ ነበር፡፡ የሁለቱም ቅንድቦቹ ጠጉር የተጋጠሙ፤ ዓይኖቹ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው ሲሆኑ ዘወትር ብሩሃን ነበሩ፡፡ አፍንጫው ትልቅና ቀጥ ብሎ የወረደ ጽሕሙና ሪዙም ረጃጅም ናቸው፡፡ አንገቱ አጠር ያለ ሆኖ ትከሻው ክብና ጎባባ፤ ቁመቱም አጠር ያለ እንደነበር ይነገርለታል፡፡ /ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ ገጽ. 65 እና 125/
 
3.የእግዚአብሔር ጥሪ እና የሁለቱ ሐዋርያት መልስ
 
እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ዘር በሙሉ ለቅድስና፣ ለምግባር፣ ለትሩፋትና ለሰማዕትነት በተለያዩ ዘመናት ጠርቷል፡፡ ጥሪውን አድምጠው የተጠሩበትን ዓላማ ተረድተው፤ እንደ እርሱ ፈቃድ የተጓዙ ጥቂቶች ናቸው፡፡ /ማቴ.22.14/ ከጥቂቶቹም መካከል ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳዉሎስ ዋነኞቹ ናቸው፡፡
 
እነዚህ ሁለት የቤተክርስቲያን ፈርጥ የሆኑ ሐዋርያት ለአገልግሎት የተጠሩበት መንገድ ለየቅል ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከወንድሙ ከእንድርያስ ጋር በገሊላ ባሕር ልዩ ስሟ ጌንሴሬጥ በምትባል መንደር ዓሣ ያሠግሩ ነበር፡፡ በዚህን ወቅት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ፡፡» በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን ከወንድሙ ጋር   ጠራው፡፡ /ማቴ.4.18/ በዚህ ጥሪ መሠረትም መተዳደሪያው የነበረውን መረቡንና ታንኳውን እንዲሁም አባቱን ትቶ ጌታውን ተከተለ፡፡ ለሐዋርያነት አገልግሎት ሲታጭ ዕድሜው 55 ዓመት እንደነበርም ይነገራል፡፡ /ዜና ሐዋርያት ገጽ. 3-15/
 
ምንም እንኳን ቅዱስ ጳዉሎስ ከቅዱስ ጴጥሮስ ጋር የተጠራበት የአገልግሎት ዓላማ አንድ ቢሆንም የተጠራበት መንገድ ከቅዱስ ጴጥሮስ በእጅጉ ይለያል፡፡ ይኸውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ዘመን ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ጋር አልነበረም፤ ቀጥታ ከጌታም አልተማረም ነበር፡፡ በወቅቱ ግን በኢየሩሳሌም ስለነበረ የጌታን አገልግሎት ያውቅ ነበር፡፡ ለኦሪታዊ እምነቱ ቀናተኛ በመሆኑ ክርስቲያኖችን በማናቸውም አጋጣሚ ይቃወም ነበር፡፡ በ32 ዓመት ዕድሜውም ከኢየሩሳሌም ሁለት መቶ ሃያ ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት በስተሰሜን በኩል በምትገኘው የደማስቆ ከተማ ብዙ ክርስቲያኖች መኖራቸውን ሲሰማ፤ ክርስቲያኖችን ለማሳደድ የሚያስችለውን የፈቃድ ደብዳቤ    ከባለሥልጣናቱ አገኘ፡፡
 
እርሱም ክርስቲያኖችን ለማሳደድ ወደ ደማስቆ ከተማ አመራ፡፡ በዚያም ከሰማይ ብርሃን ወረደ፡፡ የወረደውም የብርሃን ነጸብራቅ ቅዱስ ጳዉሎስን ከመሬት ላይ ጣለው፡፡ በብርሃኑ ውስጥም «ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛልህ)» የሚለውን አምላካዊ ድምፅ አሰማው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስም «ጌታ ሆይ ማን ነህ)» ብሎ ጠየቀ፡፡ ለጠየቀውም ጥያቄ «አንተ የምታሳድድኝ እኔ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነኝ፡፡» የሚል  መልስ አገኘ፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስም በወደቀበት ሆኖ እየተንቀጠቀጠ «ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ)» ሲል ከእርሱ    የሚጠበቀውን ግዴታውን ጠየቀ፡፡ ጌታም ተነሥቶ ወደ ደማስቆ እንዲገባና ማድረግ የሚገባውን ወደሚነግረው ወደ ካህኑ ሐናንያ ላከው፡፡ /የሐዋ.9.1/
 
ቅዱስ ጳዉሎስም በዚህ መልኩ የእግዚአብሔርን የአገልግሎት ጥሪ ተቀብሎ በካህኑ ሐናንያ እጅ   ተጠምቆ ወደ ሐዋርያነት ኅብረት ተቀላቀለ፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው ቅዱስ ጴጥሮስ የቀደመ ግብሩን እርግፍ አድርጎ ትቶ፣ ጌታን እንደተከተለ ሁሉ ቅዱስ ጳውሎስም የቀደመ የጥፋት ግብሩን በመተው የጌታ ተከታይ የሆኑትን ወንድሞቹን ሐዋርያትን ተቀላቀለ፡፡ እንደ እነርሱም ለጌታ ጥሪ ተገቢውን መልስ ሰጠ፡፡
 
ቅዱስ ጳወሎስ የተጠራው ሦስት ጊዜ ነው፡፡ የተጠራው በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ የእርሱ ጥሪ በአብ ስም የተከናወነው በእናቱ ማኅፀን ነው፡፡ ይህንንም ራሱ ቅዱስ ጳዉሎስ ሲገልጽ «ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ፤ በጸጋውም የጠራኝ፤ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ በእኔ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፤» በማለት ነው፡፡ በዚህም አብ እግዚአብሔር በሚለው አምላካዊ ስሙ እንዳጠራው በምስጢር እንረዳለን፡፡ /ገላ.1.15-16/ ሌላኛው ጥሪ ደግሞ በወልድ የተከናወነው ነው፡፡ አስቀድመን እንደገለጽነው እግዚአብሔር ወልድ በደማስቆ ጎዳና ላይ «ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ» ብሎ ከገሰጸው በኋላ ወደ ካህኑ ሐናንያ በላከው ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅትም ጌታ ቅዱስ ጳዉሎስን ለምን እንደመረጠው ለካህኑ ሐናንያም ሲያስረዳ «ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና፤» በማለት ነው፡፡ /የሐዋ.9.15/
 
ቅዱስ ጳዉሎስ ከአብና ከወልድ ባሻገር በመንፈስ ቅዱስም ለአገልግሎት የተመረጠ ነው፡፡ ይህም የሆነው መንፈስ ቅዱስ ለአባቶቻችን «በርናባስንና ሳዉልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ» /ሐዋ.13.21/ ባለበት ወቅት እና እንዲሁም «በዚያን ጊዜም ከጦሙ፤ ከጸለዩም፤ እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው፡፡ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሰሌውቅያ ወረዱ፤» በሚለው  አምላካዊ ቃል መሠረት ነው፡፡ /የሐዋ.13.3-4/ በመሆኑም የቅዱስ ጳዉሎስ መጠራት ከጥሪነት ባሻገር ምሥጢረ ሥላሴ የተገለጠበት ነው፡፡ በእርሱ መመረጥ ውስጥ የቅድስት ሥላሴ ልዩ አንድነትና ሦስትነት ተገልጧል፤ /ተመስክሯል/፡፡
 
4. የአገልግሎት ምድባቸው
 
ግብረ ሐዋርያት የሚጀምረው በቅዱስ ጴጥሮስ ሥራ ሲሆን የምዕራፉም መጨረሻ የሚጠናቀቀው በቅዱስ ጳዉሎስ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቅዱስ ጴጥሮስ አይሁድን /የተገረዙትን/ በአባትነት እንዲጠብቅ ሲሾም በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ቅዱስ ጳዉሎስ አሕዛብን /ያልተገረዙትን/ እንዲጠብቅና እንዲያስተምር ተሹሞ ነበር፡፡ ስለዚህም ነገር ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ «… ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደተሰጠኝ እዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንድሆን ለጴጥሮስ የሠራለት ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና፡፡» በማለት ነው የገለጸው፡፡/የሐዋ.2.7-9/
 
በዚሁ ምድባቸው መሠረት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም፣ በአንጾኪያ፣ በይሁዳና በሰማርያ እንዲሁም በስደት ላሉ አይሁድ መንግሥተ እግዚአብሔርን ሲሰብክ ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ በቆጵሮስ፣ በመቄዶንያ፣ በግሪክ፣ በተሰሎንቄ በፊልጵስዩስ፣ በቆሮንቶስ፣ በኤፌሶን፣ በሮምና በሌሎችም ቦታዎች ሰብኳል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስና ጳዉሎስ እነዚህን አካባቢዎችና በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩትን ሕዝብና አሕዛብ ተከፋፍለው ሲያስተምሩ የየራሳቸውን አካባቢያዊ ተጨባጭ ሁኔታ ይጠቀሙም ነበር፡፡
 
ቅዱስ ጴጥሮስ የአይሁድ መምህር እንደመሆኑ መጠን በስብከቱና በጻፈው መልእክቱ አዘውትሮ ከብሉይ ኪዳንና ከመዝሙረ ዳዊት የተለያዩ ጥቅሶችን ይጠቀም ነበር፡፡ ሐዋርያት በይሁዳ ምትክ ሌላ ሰው ለመምረጥ በተገናኙ ወቅት ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ስለ እርሱ በመዝሙር መጽሐፍ «መኖሪያው ምድረ በዳ ትሁን፤ የሚኖርባትም አይኑር፤ ደግሞም ሹመቱን ሌላ ይውሰዳት ተብሎ ተጽፎአል፡፡» በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የተናገረውን ጠቅሶ ተናግሯል፡፡ /የሐዋ.1.20-22፣ መዝ.68.25፣ መዝ.108.8/
 
ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ጴጥሮስ በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያቱ ላይ ከወረደ በኋላ ነቢየ እግዚአብሔር ኢዩኤል ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በምዕራፍ 2.2-32 ላይ የተናገረውን ጠቅሶ ጽፏል፡፡ ይኸውም «እግዚአብሔር ይላል- በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፣ ሸማግሌዎቻችሁም ህልም ያልማሉ፤ ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ትንቢትም ይናገራሉ፡፡. .. » የሚለውን ነው፡፡ /የሐዋ.2.17-21/ እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ ቅዱስ ጴጥሮስ ከመዝሙረ ዳዊት ጠቅሶ ተናግሯል፡፡ ይኸውም «ዳዊትም ስለ እርሱ /ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ/ እንዲህ አለ- እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በፊቴ አየዋለሁ፤ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና፡፡ ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፤ አንደበቴም ሐሴት አደረገ፤ ሥጋዬም ደግሞ በተስፋው አደረ፡፡ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፣ ጻድቅህንም ጥፋትን ያይ ዘንድ አትሰጠውምና፡፡» የሚለውን በመዝሙር 15.8 የሚገኘውን ሲሆን፤ ይኽም በጌታ መፈጸሙን ለማረጋገጥ የጠቀሰው ነው፡፡
 
ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ጴጥሮስ ከብሉይ ኪዳን በመጥቀስ የተለያዩ ጥቅሶችን በሁለቱ መልእክታት ላይ ተጠቅሟል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክታቱ ውስጥ የብሉይ ኪዳን ጥቀሶችን እምብዛም አልጠቀሰም፡፡ ጠቀሰ ቢባል በዕብራውያን መልእክቱ ብቻ ነው፡፡ ይህ ከብሉይ ኪዳን ጥቅሶች መጥቀስና አለመጥቀስ የተከሰተው የትምህርታቸው የትኩረት አቅጣጫ ከሆኑ ሕዝብና አሕዛብ አኳያ መሆኑንን ልብ ይሏል፡፡
 
5. ጌታ እና ሁለቱ ሐዋርያት
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት አንዱ ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያትና ከሰባ ሁለቱ አርድእት ወገን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከዐሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ወገን መሆኑ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንዲገናኝ አድርጎታል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ጋር ኖሯል፤ በልቷል ጠጥቷል፡፡ እንዲሁም ከዘመነ ሥጋዌው እስከ ዕርገቱ አብሮት በመሆን የቃሉን ትምህርት እና ስብከቱን አድምጧል፤ የእጁን ተአምራት በዐይኑ ዐይቷል፡፡
 
ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ግን ይህን ዕድል በወቅቱና በጊዜው እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ አላገኘም፡፡ እርሱ በዚያን ወቅት ቤተክርስቲያንን ያሳድድ ነበር፡፡ /1ጢሞ. 1.13/ በኋላ ግን ቅዱስ ጳዉሎስ በአሳዳጅነቱ አልቀጠለም፡፡ በዚህም ክርስቶስን አወቀው፤ በራእይም ተመልክቶት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ጌታ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በአካል ባያገኘውም በደማስቆ በብርሃን አምሳል ተገልጦ አነጋግሮታል፡፡ /የሐዋ. 9.1/ በቆሮንቶስም በምሽት በራእይ ተገልጦለት አነጋግሮታል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ «ጌታም በራእይ ጳዉሎስን እኔ ከአንተ ጋር ነኝ፣ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሣብህ የለምና አትፍራ፤ ነገር ግን ተናገር፤ ዝምም አትበል፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው፡፡» እንዲል፡፡ /የሐዋ.18.10/
 
መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልክ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ በአካለ ሥጋ አግኝቶት ቅዱስ ጳዉሎስን ባያነጋግረውም ከዚህም በተጨማሪ በኢየሩሳሌም በቤተ መቅደስ ጸሎት ሲያደርስ ተገልጦ አነጋግሮታል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ይኽን ሲገልጽ «ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለስሁ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፣ እርሱም ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፣ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት፡፡ … ሒድ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁ አለኝ፡፡» በማለት ነው፡፡ /የሐዋ.22.17-21/
 
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ጴጥሮስን ለአገልግሎት ከመረጠው በኋላ አብሮት ስላለ በየጊዜው ያበረታታው ነበር፡፡ እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስን በራእይ እየተገለጠለት ያጽናናው ያበረታውም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ጌታ በኢየሩሳሌም በሁለተኛው ሌሊት በአጠገቡ ቆሞ «ጳዉሎስ ሆይ፣ በኢየሩሳሌም ለእኔ እንደመሰከርክ እንዲሁ በሮሜም ትመሰክርልኝ ዘንድ ይገባሀል፤ አይዞህ» በማለት አዝዞታል፤ አጽናንቶታል፡፡/የሐዋ.23.11/
 
 
6. የጴጥሮስ እና የጳዉሎስ መልእክታት
 
እንግዲህ የቅዱስ ጴጥሮስና የቅዱስ ጳዉሎስ ከጌታ ጋር ያላቸው ግንኙነት ይህን ይመስላል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ከጌታ ትምህርቱን፣ ምክሩንና ተግሣጹን ቀጥታ ያገኘ ቢሆንም ቅዱስ ጳዉሎስም የጌታ ትምህርቱ፣ ምክሩና ተግሣጹ አልቀረበትም፡፡ በዚሁ መሠረት የመልእክቶቻቸውንም ጭብጥ ከዚህ ዐውድ አኳያ መመልከቱ ተገቢ ነው፡፡ የትምህርት ትኩረት አቅጣጫዎቻቸው ከምን አንፃር እንደሆነም ማስተዋል ይቻላል፡፡
 
በመሆኑም ቅዱስ ጴጥሮስም ሆነ ቅዱስ ጳዉሎስ የጻፉት ወንጌልን ሳይሆን መልእክታትን ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሁለት መልእክታትን ሲጽፍ ቅዱስ ጳዉሎስ ዐሥራ አራት መልእክታትን ጽፏል፡፡ የአጻጻፍ ስልታቸውም ሆነ የትኩረት አቅጣጫቸው የራሱ የሆነ ዐውድ አለው፡፡ መልእክታቱንም ሲጽፉ ከየራሳቸው ዐውድ አኳያ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በዶግማ በቅድስና ሕይወት ዙሪያ ሲያተኩር ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ከቅድስና ሕይወት ጎን ለጎን በዶግማና በነገረ እግዚአብሔር ላይ ያተኩራል፡፡
 
ይህን አተያይ ከቅዱስ ጴጥሮስ አኳያ ስንመለከት ራሱ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመጀመሪያ መልእክቱ እንደ አሠፈረው ነው፡፡ ይህም «እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፡፡» ብሎ እንደጠቀሰው ነው፡፡ /1ጴጥ.1.15/ ከዚህም በተጨማሪ ሐዋርያው ይኽን ሲገልጽ «… በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ፡፡» በማለት ሲሆን በዚሁ ምዕራፍ ላይ «የእምነታቸውን ፍጻሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ…» እና «ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው)» በማለት ገልጾታል፡፡ /1ጴጥ.1.1-9፤ 4.18/
 
በሌላ መልኩ ደግሞ ከዚህ ከመልእክት የትኩረት አቅጣጫ አኳያ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ከሌሎች ጉዳዮች ይልቅ በመግለጽና በማብራራት የሚያተኩረው በነገረ እግዚአብሔር ላይ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የእርሱ መልእክታት ስለ ጸጋ እግዚአብሔር፣ ስለ ቤተክርስቲያን የክርስቶስ አካልነት፣ የክርስቶስን ሥጋና ደም በመቀበል ስለሚገኝ ድኅነት፣ ስለ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን /ስለ ምስጢረ ክህነት፣ ቁርባን፣ ጥምቀት፣ ጋብቻ፣ ትንሣኤ ሙታን/ ያተኩራሉ፡፡ የእነዚህ ሁለት ሐዋርያት መልእክታት በአጭሩ በዚህ መልክ ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡
 
7. ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳዉሎስ በጌታችን ስም ያደረጓቸው ተአምራት
 
እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በዘመናቸው ተአምራት ያደርጉ ነበር፡፡ ያደረጓቸውም ተአምራት ለክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት ታላቅ አስተዋጽኦ ነበሯቸው፡፡  ሁለቱም በተአምራት ሙት አስነሥተዋል፤ ድውይ ፈውሰዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይኸውም ቅዱስ ጴጥሮስ ጣቢታ የተባለች በኢዮጴ የምትኖር አንዲት ሴትን ከሞት በተአምራት አስነሥቷል፡፡ ይህች ሴት ለሰው ሁሉ መልካም የምታደርግ፤ ምጽዋትን የምትሰጥ፣ ለተለያዩ ደሃ ሴቶች የሚሆኑ የተለያዩ አልባሳትን በመሥራት ትለግስም ነበር፡፡ ይህን ሁሉ መልካም ነገር የምትፈጽም ሴት ታማ ሞተች፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም በተአምራት ከሞት አዳናት፡፡ /የሐዋ.9.36-40/
 
ቅዱስ ጳዉሎስም እንዲሁ የሚጠቀስ ተአምር አለው፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስም ቃለ እግዚአብሔርን እያስተማረ አውጤኩስ የተባለ አንድ ወጣት አንቀላፋ፡፡ በእንቅልፉም ክብደት ምክንያት ከተቀመጠበት ወድቆ ይሞታል፡፡ ቅዱስ ጳዉሎስም ይህን ወጣት በተአምር ከሞት አስነሥቶታል፡፡ /የሐዋ.20.9-12/
 
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በልብሳቸውና በጥላቸው በተአምራት ሕሙማንን እየፈወሱ ሕመምተኞችንም የክርስቶስ የመንግሥቱ ዜጎች ያደርጉ ነበር፡፡ ተአምራቱም ችግረኞቹን ከችግራቸው ከማላቀቅ ባለፈ ለክርስትና ሃይማኖት መስፋፋት እጅጉን ይጠቅም ነበር፡፡ /የሐዋ.5.15-16፤ 19.12/
 
 
ቅዱሰ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ጳውሎስ በሮም ሰማዕትነት እንደተቀበሉ የሚያሳዩ
 
8. ሰማዕተ ጽድቅ ጴጥሮስ ወጳዉሎስ
 
የቤተክርስቲያን ጉዞ ሁልጊዜ በመስቀል ላይ ነው፡፡ ይህ የመስቀል ጉዞ ደግሞ መሥዋዕትነትን /መከራ መቀበልን/ ይጠይቃል፡፡ ከዚህም የተነሣ በሰይፍ የተመተሩ፤ በመጋዝ የተተረተሩ፣ በእሳት የተቃጠሉ ለአናብስት የተጣሉ በአጠቃላይ በብዙ ስቃይ የተፈተኑ ቅዱሳን ሐዋርያት አሉ፡፡  ከእነዚህ ሐዋርያት ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሱት እነዚህ ሁለት ሐዋርያት ናቸው፡፡ «ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ፡፡» የሚለውን የጌታችንን ቃል መመሪያ አድርገው ለቤተክርስቲያን ሁሉን አድርገው፤ ሁሉን ሆነው የሰማዕትነትን ጽዋ ተቀብለዋል፡፡
 
ቅዱስ ጴጥሮስ ስለ ክርስትና ሃይማኖት የአይሁድ መሪዎችንና ሊቃነ ካህናቱን ይሞግት፤ ከእነርሱም ፊት ምስክርነት ይሰጥ ነበር፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የአይሁድን ሊቃነ ካህናት «ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል» እያለ በሸንጎ ይሟገት ነበር፡፡ /የሐዋ.5.29/ በዚህም ብዙውን ጊዜ ይገረፍ ይታሰር ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ደግሞ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስም የተለያዩ የመከራ ጽዋን ተቀብሏል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ እርሱና ሌሎች ሐዋርያት ስለክርስቶስ መከራ መቀበላቸውን ሲገልጽ «በሁሉ መከራ ስንቀበል አንጨነቅም፣ እንናቃለን አንዋረድም፤ እንሰደዳለን አንጣልም፤ እንጨነቃለን አንጠፋም፡፡» በማለት ነው፡፡ /2ቆሮ 4.8-11/ ከዚህም በተጨማሪ «በብዙ መጽናት፣ በመከራ፣ በችግር፣ በጭንቀት፣ በመገረፍ፣ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣትም» በማለት የሰማዕትነት ሕይወቱን ገልጿል፡፡ /2ቆሮ.6.4-5፣ 1ቆሮ. 11.22-28/
 
በአጠቃላይ ቅዱስ ጳውሎስ የደረሰበትን መከራ ሁሉ በዚህ መልኩ ገልጿል፡፡ እነዚህ ሁለት ሐዋርያት በዚህ መልኩ ስለ ወንጌልና ስለክርስቶስ መከራ ከተቀበሉ በኋላ ከዚህ ምድር ያለፉት በሰማዕትነት ነው፡፡ ሁለቱም በሰማዕትነት ያለፉት በዘመነ ኔሮን ሐምሌ 5 ቀን 67 ዓ.ም ነው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሰማዕትነት ያረፈው የቁልቁሊት ተሰቅሎ ሲሆን ቅዱስ ጳዉሎስ ደግሞ አንገቱን ተሠይፎ ነው፡፡ የእነዚህ ሁለት ታላላቅ የጌታችን ሐዋርያት ረድኤት በረከት አማላጅነት ሁላችንንም አይለየን፤ አሜን፡፡
 
ዲያቆን ታደሰ ወርቁ
 
እነዚህ ሁለት ቅዱሳን አባቶቻችን የቅድስት ቤተክርስቲያናችን አዕማድ ናቸው፡፡ በመሠረትነት በአጸኗት ቤተክርስቲያን ያላቸው የክብር ሥፍራ ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው እንዲሁ አይደለም፡፡ ለቤተክርስቲያንና በቤተክርስቲያን የፈጸሙት አገልግሎት በዚህም የተቀበሉት ሰማዕትነት ነው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም ይህን መልካም የሆነውን ታሪካቸውን ለእኛ አርአያነት በሚሆን መልኩ ከትበውልናል፡፡ እኛም ለአርአርያነት በሚሆን መልኩ የእነዚህን ደጋግ ሁለት ቅዱሳን አባቶች ታሪክ፣ ዕውቀትና መንፈሳዊ አገልግሎታቸውን ከዚህ በመቀጠል አቅርበናል፡፡
 
 
 
 
 

 

 
 
 
 

 

ወርኃ ክረምት በቤተ ክርስቲያን ትምህርት (ዘመነ ክረምት)

ሐምሌ 4 ቀን 2004 ዓ.ም.

መብዐ ሥላሴ (ከጎላ ሚካኤል)

“ክረምት” የሚለው ቃል ከርመ፣ ከረመ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ሲሆን ትርጓሜውም ወርሃ ዝናም፣ ወርኃ ነጎድጓድ፣ ዘመነ ባሕር፣ ዘመነ ነጎድጓድ፣ ዘመነ አፍላግ፣ ዘመነ ጠል፣ ዘመነ ደመና፣ ዘመነ መብረቅ… ማለት ነው፡፡(ጥዑመ ልሳን ካሳ ያሬድና ዜማው 1981 ዓ.ም ገጽ 53)

 

በዘመነ ክረምት ውኃ ይሰለጥናል፣ ውኃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፡፡ ሆኖም ግን በብሩህነቱ ከእሳት፤ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፤ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ከሦስቱ ባሕርያት ጋር ይኖራል፡፡ ይህ ዘመን ስለ ሥነ ፍጥረት ዘርዘር ባለ መልኩ የሚነገርበት ዘመን ስለሆነ ፍጡርን ከፈጣሪ መናን ከተመጋቢ ለይቶ የሚያሳይና የሚያሳውቅ ዘመን ነው፡፡

 

ዘመነ ክረምት፡- የዝናም፣ የዘርና የአረም ወቅት በመሆኑ ምድር በጠል ዝናም ትረካለች፡፡ ዕፅዋት አዝርዕትና አትክልት በቅለው፣ ለምልመው  የሚያድጉበት፣ ምድር አረንጓዴ ለብሳ በሥነ ጽጌያት የምታሸበርቅበት፣ ወቅት ነው፡፡በመሆኑም በሃገራችን ብዙው የግብርና ሥራ የሚካሄደው በዚህ ጊዜ ነው፡፡

 

ወርኃ ክረምት የክርስትና ምሳሌ ነው፤ ገበሬ በወርሃ ክረምት ብርዱንና ዝናሙን ሳይሰቀቅ ለሥራ ይሰማራል፤ በበጋው የእጁን ፍሬ ያገኝ ዘንድ የክረምቱን መከራ ይታገሳል፡፡ ክርስቲያንም በዚህ ምድር ላይ የሚደርስበትን መከራ ሁሉ ይታገሳል፤ ክርስቲያንም በዚህ ምድር የሚደርስበትን መከራ ሁሉ በጸጋ የሚቀበለው በዚያኛው ዓለም ስለሚያገኘው ተድላና ደስታ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “እለ ይዘርኡ በአንብዕ ወበኃሤት የአርሩ፡፡ ሶበሰ የሐውሩ ወፈሩ እንዘ ይበክዩ፡፡ ወፆሩ ዘርኦሙ፡፡ ወሶበ የአትዉ መጽኡ እንዘ ይትፌሥሑ፡፡  በሔዱ ጊዜ ዘራቸውን ተሸክመው እያለቀሱ ተሰማሩ፤ በተመለሱ ጊዜ ግን ነዶአቸውን ተሸክመው ደስ እያላቸው ይመጣሉ፡፡” በማለት የመንፈሳዊ ጉዞ ምሥጠርን ከግብርና ሙያ አንጻር አመልክቶአል፡፡(መዝ.125)

 

እግዚአብሔር ክረምትን ሲያመጣና ዝናምን ሲያዘንም ብዙ ነገሮችን ልናስተውል ይገባናል፡፡ ፈጣሪያችን ፈጣሪ ዓለማት ብቻ ሳይሆን መጋቢ ዓለማት መሆኑን መረዳት ያሻል፡፡ መግቦቱም ከፍጥረቱ እንዳልተለየ ይህ አማናዊ መግቦቱም ፍጥረቱን እንደሚያስተምር እንረዳለን፡፡ “በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፤ ብርድና ሙቀት፤ በጋና ክረምት፤ ቀንና ሌሊት አይቋረጡም፡፡” (ዘፍ.8፥22) በማለት አምላካችን እግዚአብሔር ለኖኅ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት በጋና ክረምቱ፤ ብርድና ሙቀቱ፤ ቀንና ሌሊቱ በተወሰነላቸው ጊዜ እየተፈራረቁ ለሰው ልጆች ጥቅም እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፡፡

 

በዚህ መሠረት ኢትዮጵያዊያን በአንድ ዓመት ውስጥ እየተፈራረቁ በሚመጡ አራት ወቅቶች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ከቅዱሳት መጻሕፍት ምሥጢርና ምሳሌ ጋር በማስማማት ለየወቅቱና ለዕለታቱ ምንባባትን በማዘጋጀት፣ ከሕብረተሰቡ ሥራና አኗኗር ጋር በማያያዝ እንዲሁም ከወቅታዊው አየር ጠባይ ጋር በማስማማት እያንዳንዳቸውን በ91 ቀን ከ15 ኬክሮስ (አንድ አራተኛ) በመክፈል ለወቅቶቹም ሥያሜ፣ ምሳሌ፣ ትርጉሙንና ምሥጢሩን በማዘጋጀት ትገለገልባቸዋለች፡፡

 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዓመቱን የከፈለችባቸው ወቅቶች፡-

  1. ዘመነ መጸው (መከር) ከመስከረም 26 ቀን እስከ ታኅሣሥ 25
  2. ዘመነ ሐጋይ (በጋ) ከታኅሣሥ 26 ቀን እስከ መጋቢት 25
  3. ዘመነ ጸደይ (በልግ) ከመጋቢት 26 እስከ ሰኔ 25
  4. ዘመነ ክረምት ሰኔ 26ቀን እስከ መስከረም 25 ናቸው፡፡

 

ወቅቶችን እንዲህ በመከፋፈል በወቅቱ ከሚታየው የተፈጥሮ ሁኔታ ጋር ምእመናን ሕይወታቸውን እንዲመረምሩ ለንስሐ እንዲበቁ አጥብቃ ታስተምራለች፡፡ ያለንበት ወቅትም ክረምት በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት፤ ቅዱሳት መጻሕፍት አማካኝነት የሚሰጠውን ትምህርት በጥቂቱ እንመለከታለን፡፡

 

ወርኃ ክረምት ከላይ በጥቂቱ እንደተመለከትነው በሦስት ንዑሳን ክፍላት ይከፈላሉ፡፡ እነኚህም፡-

1.    መነሻ ክረምት፡- የዝግጅት ወቅት

ሀ. ከበአተ ክረምት እስከ ሐምሌ ቂርቆስ(ከሰኔ 26 እስከ ሐምሌ 19) ያለው ወቅት ነው፡፡  በዚህ ወቅት ዝናምና ደመና ምድርን የሚያለመልሙበት፣ ዘር የሚዘራበት ፣ የተዘራው የሚበቅልበት በፀሐይ ሐሩር የደረቁ ዛፎች ሁሉ የሚያቆጠቁጡበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ወቅት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘርዕን ደመናን ዝናምን የሚያዘክሩ  ምንባባት ይነበባሉ፣ መዝሙራትም ይዘመራሉ፡፡

 

ከእነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ “ድምፀ እገሪሁ ለዝናም ሶበ ይዘንም ዝናም ይትፌስሁ ነድያን፣ ይጸግቡ ርሁባን፡፡ የዝናም ድምፅ ተሰማ፤ ዝናም በዘነመ ጊዜ ችግረኞች ይደሰታሉ፤ ረሀብተኞችም ይጠግባሉ፡፡” በማለት በድጓው የዘመረው ይገኝበታል፡፡

 

ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ “ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፡፡ ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፡፡ ዘያበቊል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡ወሐመልማለ ለቅኔ እጓለ እምሕያው፡፡ ማለትም፡- ሰማዮችን በደመና ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናምን ያዘጋጃልና፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙንም ለሰው ልጆች ጥቅም” በማለት የዘመረው ይሰበካል፡፡

 

በምንባበት በኩል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “በእርስዋ ላይ የሚወርደውን ዝናም የምትጠጣ መሬት ለሚያርሷትም ደግሞ የምትጠቅምን አትክልት የምታበቅል ከእግዚአብሔር በረከት ታገኛለች፤ እሾህንና ኩርንችትን ግን ብታወጣ የተጣለች ናት፡፡ ለመረገምም ትቀርባለች፤ መጨረሻዋም መቃጠል ነው፡፡” በማለት ያስተማረው ትምህርት ይነበባል፡፡(ዕብ.6፥7-8)

 

ለ. ከሐምሌ ቂርቆስ እስከ ማኅበር (ከሐምሌ 19 እስከ ሐምሌ 29) መባርቅት የሚባርቁበት በባሕርና አፍላጋት የሚሞሉበት ምድር ጠል የምትጠግብበት ወቅት ነው፡፡ “ደመናት ድምፁን ሰጡ፣ ፍላጾችህም ወጡ የነጎድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበር፤ መብረቆች ለዓለም አበሩ” ሲል ቅዱስ ዳዊት የተናገረው ይሰበካል፡፡(መዝ.76፥18) ደመኖች ታይተው ባርቀው የነጎድጓድ ድምፅ እንዲሰማ ጌታችን ከዓለም ጠርቶ አስተምሮ ወንጌለ መንግሥት ተናግረው በኃጢአት ጨለማ የተያዘውን ዓለም በትምህርታቸው እንዲያበሩ የተላኩ የ72ቱ አርድዕት ዝክረ ነገር ይታወሳል፡፡(ሉቃ.10፥17-25)

 

መዝሙሩ፡- “ምድርኒ ርዕየቶ ወአኰተቶ ባህርኒ ሰገደት ሎቱ፤ ምድር አየችው አመሰገነችውም ባሕርም ሰገደችለት” /ድጓ/

“እግዚአብሔር የወደደውን ሁሉ አደረገ በሰማይም በምድርም በባህርም በጥልቅም ቦታ ሁሉ”/መዝ.134፥6-7/

“ምድርን ጎበኘሃት አጠጣሃትም ብልፅግናዋንም እጅግ አበዛህ የእግዚአብሔር ወንዝ ውኃን የተሞላ ነው ከምድር ዳር ደመናትን ያወጣል፣ በዝናም ጊዜ መብረቅን አደረገ፤ ነፋሳቱንም ከመዛግብቱ ያወጣል ” (መዝ.64፥9) በማለት እግዚአብሔር በነጎድጓድና በመብረቅ በባሕርና በሐይቅ ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ መሆኑንና የሚታዩና የማይታዩ ፍጥረታት ሁሉ የኃይሉ መገለጫዎች እንደሆኑ የሚያስተምሩ መዝሙራት ይዘመራሉ፡፡

ወንጌል፡- መንግሥተ ሰማያት ወደ ባሕር የተጣለች ከሁሉም ዓይነት የሰበሰበች መረብን ትመስላለች (ማቴ.13፥47)

ደቀ መዛሙርቱም በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ፤ ምትሐት ነው ብለው ታወኩ በፍርሃትም ጮኹ፡፡ ወዲያውም ኢየሱስ ተናገራቸውና አይዞአችሁ፥ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው፡፡(ማቴ.14፥26-27)

2.    ማዕከለ ክረምት

ሀ. ከማኅበር እስከ አብርሃም (ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 29)

ዘመነ ክረምት የሚጋመስበት ነው፡፡ ዝናብ ይቀንሳል፣ ምድሪቱም መቀዝቀዝና መጠንከር ትጀምራለች፡፡ “ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት፤ ቡሄ ካለፈ የለም ክረምት” እንዲሉ በክረምት ዝናሙን ተደብቀው የነበሩ አእዋፍ ከበአታቸው ይወጣሉ፤ ጥበበኛው ሰሎሞን አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማ ጊዜ ደረሰ፤ የቀረርቶውም ቃል በምድራችን ተሰማ (መኃ.2፥12) ሲል እነደተናገረው የአእዋፍ የምስጋና ድምፅ ይሰማል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም “የሁሉም ዐይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፣ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ፣ አንተ እጅህን ትከፍታለህ፣ ሕይወት ላለውም ሁሉ መልካምን ታጠግባለህ” እያለች እንደ ቅዱስ ዳዊት ለሥጋ ሁሉ ምግብን የሚሰጥ ምሕረቱም ለዘለዓለም የሆነውን የሰማይ አምላክ ታመስግናለች(መዝ.144፥15-20፣ መዝ 135፥25-26)

 

ለ. ዕጉለ ቋዓት፥ ደስያት

ይህ ክፍለ ክረምት ከነሐሴ 10 እስከ ነሐሴ 27 ቀን ድረስ ያሉት 17 ዕለታት የሚጠሩበት ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ክረምት ፍጥረታትና በባሕር የተከበቡ ደሴቶች የሚታወሱበት ሲሆን ወቅቱም ዕጓለ ቋዓት ደስያት ዐይነ ኩሉ ይባላል፡፡ ዕጓለ ቋዓት የሚለው ቃል ቁራን ሲያመለክት፣ ቁራ ሲወለድ ያለ ፀጉር በሥጋው ብቻ ይወለዳል፡፡ እናትና አባቱም እነርሱን ባለመምሰሉ ደንግጠው ይሸሻሉ፤ በዚህ ጊዜ የሚንከባከበው ሲያጣ እግዚአብሔር በረድኤት አፉን ከፍቶ ምግብ ሲሻ ተሐዋስያንን ብር ብር እየደረገ ከአፉ ያስገባለታል፡፡ “ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ፥ የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘብዙ፥ ለቁራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው? ” (ኢዮ.38፥41) ተብሎ እንደ ተገለጠው እግዚአብሔር የሰጠውን እየተመገበ ቆይቶ ሲጠነክር እንደ እናትና አባቱ ያለ ፀጉር ያወጣል፡፡ በዚህ ጊዜ እናትና አባቱ ቀርበው ይንከባከቡታል፡፡ በሥነ ፍጥረት አቆጣጠር ግን በክንፍ የሚበሩ አዕዋፍን ሁሉ ይወክላል፡፡ ይህም አምላካችን እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ሁሉ የሚያስብ በመሆኑ ይህን ዘመን ርኅርሔ ለተመላው አምላክነቱ ሥራው መታሰቢያ እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን ዕጓለ ቋዓት በማለት ታስታውሰዋለች፡፡

 

ደስያት ማለት በውኃ የተከበቡ ቦታዎች ማለት ነው፡፡ እነዚህን ቦታዎች በውኃ እንዲሸፈኑ አድርጎ በውስጥቸው ያሉትን ሰዎች እንስሳት አራዊት አዕዋፍ ሁሉ የሚጠብቃቸው፣ በተስፋና በእምነት አበርትቶ የሚያኖራቸው እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህን ድንቅ ሥራ ያዩ በውስጥ በውጭ ያሉት ሰዎች እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ በደሴት (በቤተ ክርስቲያን) የተጠጉ ሁሉ ከሞተ ሥጋና ከሞተ ነፍስ ይጠበቃሉ፡፡

 

በዚህ ወቅት፡- ክፍለ ክረምቱ እንደተገባደደ፥ ውኃው እየጠራ፣ መሬቱ እየረጋ፣ ደመናውና ጉሙ እየተቃለለ፣ የወንዞች ሙላት እየቀነሰ፣ የክረምት ምግባቸውን ይዘው በየዋሻው የከረሙ ጭልፊቶችን አሞራዎች ድምፃቸውን እየሰሙ ምግብ ፍለጋ ሲወጡ የሚታዩበት ወቅት ነው፡፡

 

በተጨማሪም ከነሐሴ 27-29 ያለው ጊዜን “ሞተ አበው” በመባል ይታወቃል፡፡ ከ22ቱ አርዕስተ አበው የአብርሃም ይስሐቅና ያዕቆብ ቤተሰቦቻቸው ዕረፍት ይታሰባል፡፡ ቅዱስ መጽሐፋችንም “አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ሊሰዋ ወጣ፤ እግዚአብሔር ቤዛ አድርጎ ቀንዱ በዕፀ ሳቤቅ የተያዘ በግ አወረደለት” በማለት የአብርሃምን ታዛዥነት የይስሐቅን ቤዛነት ያወሳል፡፡ የተቀበሉትም ቃል ኪዳን “ወተዘከረ ሣህሎ ዘለዓለም ዘሠርዓ ለአብርሃም ወመሐለ ለይስሐቅ ወዐቀመ ስምዐ ለያዕቆብ ያርኁ ክረምተ ይገብር ምሕረተ እም ሰማይ ይሁብ ወእምድር በረከተ ያጸግብ ነፍስ ርኅብት” በማለት ይዘመራል፡፡

 

3.    ፀዓተ ክረምት (ዘመን መለወጫ)

ሀ. ከአብርሃም እስከ ዮሐንስ

ይህ ወቅት የዓመቱ መንገደኛ ነው፣ በሐምሌና በነሐሴ ደመና ተሸፍና የነበረችው ፀሐይ ፍንትው ብላ መውጫዋ የደረሰበት ጊዜ በመሆኑ ጎህ ጽባህ፣ መዓልተ ነግህ፣ ብርሃን ተብሎ የጠራል፡፡ የክረምቱ ጭፍን ጨለማ ሊያከትም ብርሃን ሊበራ የተቃረበበት መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ይበሰራል፡፡ በሊቀ መልእክት ቅዱስ ሩፋኤል እጅ የጦቢያን ዓይን እንዳበራ ፤ የምእመናን ዓይነ ልቡና እግዚአብሔር እንዲያበራ ይጸለያል፡፡

 

ከዚሁ ጋር የክረምቱ ደመና ዝናብና ቅዝቃዜ ውርጭ ጭቃው ከብዶባቸው የዘመን መለወጫን፣ የፀሐይ መውጫን ቀን በጉጉት ለሚጠባበቁ ምእመናን ልጆቿ ቅድስት ቤተ ከርስቲያን፡- “ነፍሳችሁን ተመልከቱ፥ ሰውነታችሁን ንጹሕ አድርጉ” ስትል ለበለጠ መንፈሳዊ ትጋት ታነቃቃቸዋለች፡፡ ክረምት ሲያልፍ የሰማዩ ዝናም የምድሩ ጭቃ ሊቀር እንሆ ሁሉ በዚህች ዓለም መከራ ተናዝዘው ላሉ ክርስቲያኖች ሁሉ ክርስቶስ በክብር የሚገለጥበት ዓለም የምታልፍበት ዕለት ባላሰቧት ጊዜ እንደምትመጣ እንዲገነዘቡ ነገረ ምጽአቱን እንዲያሰቡ “ተዘጋጅታችሁ ኑሩ!” እያለች በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር እንዲያብቡ “እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይመጣል… አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም እሳት በፊቱ ይነዳል” (መዝ.49፥2-3) እያለች ትመሰክራለች፡፡

 

ለ. ከዮሐንስ እስከ ዘካርያስ (መስከረም 8)

ዘመን መለወጫ አዲስ ተስፋ በምእመናን ልብ የሚለመለምበት ጊዜ ነው፡፡ የተተነበየው ትንቢት፣ የተቆጠረው ሱባኤ ተፈጸመ፤ ከዘመነ ፍዳ ወደ ዘመነ ምሕረት የምትሸጋገሩበት ጊዜ ደረሰ፤ እያለ ያወጀው የመጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ዜና ሕይወት ይነገራል፡፡ “ምሕረትና እውነት ተገናኙ፤ ጽድቅና ሰላም ተስማሙ፣ እውነት ከምድር በቀለች” (መዝ.88፥10-11) በማለት ስለ እውነት ሊመሰክር የወጣውን የቅዱስ ዮሐንስን ሕይወት በማውሳት ቤተ ክርስቲያን ልጇቿ እንደርሱ እውነተኞች እንዲሆኑ አርአያነቱን እንዲከተሉ ለእውነት እንዲተጉ ታስተምራለች፡፡ ሰማዩ፣ ውኃው የሚጠራበት ወቅት በመሆኑ በሥነ ፍጥረት በማመለከት ልጆቿን ከብልየት እንዲታደሱ፣ በመንፈስ እንዲጎለምሱ፣ከርኩሰት ከጣኦት አምልኮ፣ከቂም በቀል እንዲጠሩ እንዲነፁ “የአህዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና” እያለች በሐዋርያው ቃል ታስተምረናለች፡፡(1ኛ ጴጥ.4፥3) ከዚሁ ጋር፡-በርኩሰት የተመላውን ሕይወታችንን ካለፈው ዘመን ጋር አሳልፈን የምድር አበቦች በጊዜው እነደሚያብቡ እኛም በምግባር በሃይማኖት እንድናብብ ትመክረናለች፡፡

 

ሐ. ከዘካርያስ እስከ ማግስተ ሕንፀት

ይህ ንዑስ ወቅት ዘመነ ፍሬ በመባል ይታወቃል፡፡ ከመስከረም 9 እስከ 16 ያሉትን ዕለታት በተለይ በሰኔና በሐምሌ የተዘራው ዘር ለፍሬ መብቃቱን የሚያስብበትና እንደ ቅዱስ ዳዊት “ምድር ፍሬዋን ሰጠች እግዚአብሔር አምላካችንም ይባርከናል”(መዝ.66፥6) ተብሎ እግዚአብሔር የሚመሰገንበት ሳምንት ነው፡፡ ፍሬውም ከቁር ከበረዶና ከትል ተርፎ ለጎተራ እንዲበቃ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጸሎተ ቅዳሴዋ “በእንተ ፍሬ ምድር ናስተበቊእ ከመ እግዚአብሔር ይሁብ ፍሬሃ ለምድር፣ ለዘርና ለመከር ሊሆን እግዚአብሔር ለምድር ፍሬዋን ይሰጣት ዘንድ ስለምድር ፍሬ እንማልዳለን” በማለት አምላኳን ትማጸናለች፡፡

 

ልጇቿ ምእመናንም “ሽሽታችሁ በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ጸልዩ” (ማቴ. 24፥20) ሲል መድኃኔዓለም እንዳስተመረው የሃይማኖት ፍሬ ምግባርን፣ ቱሩፋትን ሳይሠሩ በልምላሜ (በሃይማኖት) ብቻ ሳሉ እንዳይጠሩ ለንስሐ ለሥጋ ወደሙ እንዲበቁ በማስተማር ነገረ ምጽአቱን በማዘከር “ድልዋኒክሙ ንበሩ፣ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ” በማለት ታስተምራለች፡፡

 

ስለዚህ ይህ ክፍለ ክረምት የዕለተ ምጽአት ምሳሌ ነው፡፡ ወቅቱ የአዝመራ ወቅት ነው፡፡ፍሬ መለያ እንደሆነ ሁሉ የሰው ሥጋ ከተቀበረና ትቢያ ከሆነ በኋላ ተነስቶ በዕለተ ምጽአት በጽድቅና በኃጢአት ይለያልና፡፡(ማቴ.25፥32)

 

መ. ከመስከረም እስከ ፍጻሜ ክረምት(መስከረም 25)

ዘመነ መስቀል ከመስከረም 17 እስከ 25 ያሉት ዘጠኝ ቀናት የሚጠሩበት ሌላው መጠሪያቸው ነው፡፡ ይህ ክፍለ ክረምት ነገረ መስቀሉ የሚነገርበት ነው፡፡ በቅናት ተነሳስተው አይሁድ የቀበሩት የጌታችን መስቀል በንግሥት እሌኒ ጥረትና በፈቃደ እግዚአብሔር ከሦስት መቶ ዓመታት በኋላ ተቆፍሮ የወጣበት መታሰቢያ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያንም የቅዱስ መስቀልን ክብር የሚመለከት ትምህርት ይሰጣል፤ ክቡር ዳዊት “ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክት ሰጠሃቸው” (መዝ.59፥4) በማለት የተናገረው ይሰበካል፡፡ ጊዜው የክርስቶስና የመስቀል ጠላቶች ያፈሩበት የመስቀሉ ብርሃን ለዓለም ያበራበት በመሆኑ የመስቀሉ እንቅፋት ተወግዷልና ምእመናን በዚህ ይደሰታሉ(ቆላ.2፥14-15) በቅዱስ መስቀሉ ተቀጥቅጦ ኃይሉን ያጣው ዲያብሎስን በትእምርተ መስቀል ከእነርሱ ያርቁታል፡፡ በቅዱስ መስቀል የተደረገላቸውን የእግዚአብሔር ቸርነት እያስታወሱ በአደባባይ በዝማሬ መንፈሳዊ ደስታቸውን ይገልጣሉ፡፡

 

እንግዲህ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ውስጥ ላለነው ራሳችንን ከጊዜው ጋር እንድናነጻጽር ወቅቱን የተመለከተ ትምህርት አዘጋጅታ ልጆቿን ለሰማያዊ መንግሥት ዝግጁ እንዲሆኑ ታስተምራለች፡፡ በዚህም ጊዜ ውስጥ ተፈጥሮን አይተን አገናዝበን የምንማር፣ ለንስሐ የተዘጋጀን ስንቶቻችን ነን? “ቁም! የእግዚአብሔርን ተአምራት አስብም!” እንዳለ (ኢዮ.37፥14) ያለንበትን ሕይወት አስበን ለንስሐ እንበቃ ዘንድ፣ የእግዚአብሔር ቸርነት፥ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ጸሎት አይለየን፤

Kidus Yohannes Metimiq

በዓለ ልደቱ ለዮሐንስ መጥምቅ

 


ሰኔ 15 ቀን 2004 ዓ.ም                                                                        በዘሚካኤል አራንሺ

እንኳን ለመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በዓለ ልደት አደረሳችሁ::

Kidus Yohannes Metimiqበዮሴፍ ወልደ ያዕቆብ ዘመን የነበረው ፈርኦንና የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት ለዘፋኝ ወሮታ የሰጠው ሄሮድስ የሚያመሳስላቸው አንድ ዓይነት ተግባር ፈጽመዋል:: ይኽውም ሁለቱም ልደታቸውን ያከብሩ እንደነበር በመጽሐፍ ቅዱስ መጠቀሱ ነው:: /ዘፍ.40፥20 ፤ ማቴ.14፥6/:: ታሪካቸውን ስናጠና ደግሞ በርካታ መመሳሰል እንደነበራቸው እንገነዘባለን:: ሁለቱም   ነገሥታት ናቸው:: ሁለቱም ንጹሐንን አስረዋል:: ሁለቱም ደም አፍሳሾች ነበሩ:: በልደት በዓላቸውም ነፍስ አጥፍተዋል:: በልደት በዓላቸው ነፍስ ያጠፉ ሰዎች ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ መጻፉ የልደት በዓል ማክበርን ስህተት አያደርገውም:: በጌታችን ልደት መቶ አርባ አራት ሺህ ሕጻናት በሄሮድስ ትእዛዝ ተገድለዋል:: የጌታችንን ልደት ግን እናከብራለን:: መግደል ኃጢአት መሆኑን እንመሰክርበት ካልሆነ በቀር ነፍስ በማጥፋት የሚከበር በዓል የለንም:: የፋሲካን በዓል በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ለማክበር እንገደዳለን እንጂ ዘፋኞች ድግስ ስለሚያዘጋጁበት ማክበሩ ቢቀር ቢባል ሞኝነት ነው:: ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳንን ልደት በዓል ስታከብር የራሷ ሥርዓትና ባሕል የበዓላት መቁጠሪያ /ሊተርጂካል ካላንደር/ አላት:: የቱ መቼ መከበር እንዳለበትም ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ታስረዳለች:: ጥንታዊት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆንዋም በርግጥኝነት ዕለታቱን ቆጥራ ትናገራለች:: በነቢይ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ተብሎ የተነገረለት የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስን የልደት በዓል የምታከብረው በሰኔ ሠላሳ ቀን ነው::

 

 

የጻድቃን ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ እንደሆነ፤ ቅዱሳኑን ያገኘንባት ልደታቸውም የከበረች ናት:: /መዝ.116፥15/:: የመጥምቁ ዮሐንስን ልደት ያበሰረው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል “በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል::” እንዳለ በልደተ ቅዱሳን ደስ እንሰኛለን:: /ሉቃ.1፥14/:: በዓለ ቅዱሳን የደስታ በዓላት ናቸውና:: የተወለዱበት ፥ ልዩ ልዩ ገቢረ ተዓምራት ወመንክራት የፈጸሙባቸው፥ ሰማእተ ኢየሱስ ሆነው መከራ የተቀበሉባቸው፥ያረፉበትና የተሰወሩበት፥ ቃል ኪዳን የተቀበሉባቸውን ዕለታት የምናከብረው በደስታ ነው:: ቅዱስ ዳዊት “ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ምስጋና መኖሪያ ስፍራ እገባለሁና በዓል የሚያደርጉ ሰዎች የደስታና ምስጋና ቃል አሰሙ።” እንዲል:: /መዝ.42፥4/:: ዕለታቱ በደንጊያ ተወግረው፥ በመጋዝ ተተርትረው ፥ ወደ እሳት ተጥለው፥ ለአናብስት ተሰጥተው፥ በሰማእትነት ያረፉባቸው እንኳ ቢሆኑ የደስታ በዓላት ናቸው:: የምስክርነታቸውን እውነትነት፥ የእምነታቸውን ጽናት፥ ታዛዥነታቸውንና ለአምላካቸው ያላቸውን ፍቅር በመግለጣቸው፤ የሚያገኙትን ክብር፥ የሚወርሱትን መንግስት እናስባለንና:: የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን የከበረች የእረፍቱን ቀን በማኅሌት ከበሮ መትተን፥ጸናጽል ጸንጽለን፥ ወረብ ወርበን፥ ቅዳሴ ቀድሰን፥ መዝሙር ዘምረን፥ መልክ ደግመን፥ ገድል አንብበን፥ ተዓምሩን ተናግረን፥ ቅድስናውን መስክረን እንደምናከብረው በዓለ ልደቱንም እንዲሁ እናከብራለን:: ጠቢቡ “ጻድቃን በበዙ ጊዜ ሕዝብ ደስ ይለዋል…” ብሏልና:: በመወለዳቸው ደስ ተሰኝተን በዓል እናደርጋለን:: /ምሳ.29፥2/::ካህኑ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ የብዙዎችን ደስታ ወልደዋል:: ጌታችን በወንጌል “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ . . . ” /ማቴ.7፥17-19/:: በማለት እንዳስተማረን የመጥምቁ ወላጆች “በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ” ተብሎየተመሰከረላቸው መልካም ዛፎች ነበሩና:: መልካም ፍሬ ቅዱስ ዮሐንስን አስገኙልን:: /ሉቃ.1፥6/:: ቅድስናቸው ከፍሬያቸው ከዮሐንስ የተነሳ ገኖ ዛሬም ድረስ ይታያል:: ለብዙዎች የሚሆን ደስታን ወልደዋልና ስሙን ዮሐንስ አሉት ትርጓሜው ደስታ ማለት ነው:: የክርስቲያናዊ ጋብቻ ዓላማ ምእመናንን መልካም ዛፍ አድርጎ መትከል ነው:: ሲንከባከቡትም እንደ ካህኑ ዘካርያስና ቅድስት ኤልሳቤጥ ደስታው ከቤተ ዘመድ ያለፈ መልካም ፍሬ ያፈራል:: በመጥምቁ ዮሐንስ ልደት “እነሆ፥ መልእክተኛዬን እልካለሁ፥ መንገድንም በፊቴ ያስተካክላል . . . ” በማለት ነቢያተ እግዚአብሔር የተናገሩትን የትንቢት ቃል ለሚጠባበቁ ሁሉ ደስታ ነበረ:: /ሚል.3፥1 ፤ኢሳ.40፥3 ፤ማር.1፥1-5/:: የዮሐንስ መምጣት ለጌታችን መምጣት የምሥራች ነውና:: “ከእኔ የሚበረታ በኋላዬ ይመጣል።” የሚለው ስብከቱም የሚያስታውሰን ይህንኑ ነው:: /ማር.1፥7/:: በዮሐንስ መጥምቅ ልደት ደስ የሚሰኘው ያለፈውም የሚመጣውም ትውልድ ነው::

 

በዘመኑ የነበሩትን በትምህርቱ ደስ አስኝቷቸዋል:: ትምህርቱና ተግሣጹን የሰሙትን ከስህተት መልሷቸዋልና ደስ ተሰኝተውበታል:: በኃጢአት ያደፈ ስውነታቸውን በንስሀ ጥምቀት አዘጋጅቷልና ደስ ተሰኝተውበታል:: አገልግሎቱን በሚገባ የተረዳ መናኒ ነበርና ሕይወቱ ደስ የሚያሰኝ ነበረ:: አገልግሎቱን የምታውቅ፥ ክብሩን የምትመሰክር፥ በቃል ኪዳኑ የምትታመን ቤተ ክርስቲያንም ደስ ትስኝበታለች:: ስለዚህም በልደቱም በእረፍቱም ቀን የደስታ በዓል ታደርጋለች:: ምእመናንም በቃል ኪዳኑ በመታመን የምናደርገው የመታሰቢያ በዓሉ ደስታን የሚሰጥ ነው:: በመወለዱ ያገኘናቸውን የመጥምቁን በረከቶች እያሰብን አምላኩን እናመሰግናለን:: ልደተ ቅዱሳንን የማዘከር ዓላማው የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ አስቦ ለማመስገን ነው:: ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ልደት ስንናገር ወላጆቹንና ጽድቃቸውን የአባቱን የክህነት አገልግሎት፥ የመልአኩን ተራዳኢነት፥ የእናቱን በመንፈስ ቅዱስ መቃኘት፥ የእርሱን በማኅጸን መዝለል፥ የአባቱን አንደበት መክፈቱን፥ ስለ አደገበት የናዝራውያን ሥርዓት፥ ስለ አሳደገችው የበረሀ ፍየል /ቶራ/፥ ይመገበው ስለነበረው አንበጣና የበረሀ ማር፥ ዞሮ ያስተማራቸው ትምህርቶች፥ ስለ ፈጸማቸው የጽድቅ ሥራዎች፥ ጌታችንን ስለ ማጥመቁ፥ ስለ ተግሣጹና በሰማእትነት ስለ ማረፉ፥ ስለ ተዓምራቱ ከዚያም በኋላ በጸሎቱና በአማላጅነቱ ለሰው ልጆች ስለ ረዳው ርዳታ . . . በደስታ በማውሳት ነው:: የሌሎችም ቅዱሳንን በዓል የምናከብረው በዚህ መንገድ ነው::

 

እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው:: ቅድስት ኤልሳቤጥን የጎበኛት ድንቅ ነው፤ የአገልጋዩን ድካም ያልዘነጋ ድንቅ ነው፤ ዘመን ካለፋቸው በኋላ በእርግና ዘመናቸው ዘር የሰጠ ድንቅ ነው እያልን ደስ ተሰኝተን የምናመሰግነው በቅዱሳኑ ላይ ድንቅን ያደረገውን እግዚአብሔርን ነው::/መዝ.68፥35/ “ከእናንተ መከራን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ይጸልይ፤ ደስ የሚለውም ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር።” ተብሏልና:: /ያዕ.5፥13/:: ልደተ ቅዱሳን የደስታ የዝማሬ በዓላት ናቸው:: የእግዚአብሔር ወዳጆች ቅዱሳን ጽናታቸው ይደነቅበታል፥ አምላካቸው ይመሰገንበታል፥ ትምህርታቸው ይነገርበታል:: ስለ ቅዱሳን በመናገር የሚጠፋ ጊዜ የለም ፤ ስለ ቅዱሳን መመስከርን አብነት የምናደርገው መጽሐፍ ቅዱስን ነው:: መጽሐፍ ቅዱስን እናውቃለን ለሚሉን በውስጡ የበርካታ ቅዱሳንን ልደት፥ እድገት፥ አገልግሎት፥ ትምህርት፥ ክብርና ጸጋ የሚመሰክር መጽሐፍ መሆኑን እንመሰክርላቸዋለን::

 

የመጥምቁ ዮሐንስ ልደት በዜማ በግጥም በንባብም ቢሆን የምናወሳው መጽሐፍ የመሰከረለትን እውነት ነው:: መጥምቁ ዮሐንስ በመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት በትንቢት ቃል “የአዋጅ ነጋሪው ቃል” ፤“የቃል ኪዳን መልእክተኛ”፤ “መንገድ ጠራጊ”፤ “በበረሃ የሚጮኽ ሰው ድምጽ” ወዘተ እያሉ አመስግነውታል:: መልአከ እግዚአብሔር ቅድስናውንና ክብሩን ሲናገር “ገናም በእናቱ ማኅፀን ሳለ መንፈስ ቅዱስ ይሞላበታል፤” ፥“ በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” ብሎለታል ፤ ካህኑ ዘካርያስም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ “አንተ ሕፃን ሆይ፥ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፥ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሄዳለህና፤” እያለ አገልግሎቱን ገልጧል ፤ ጌታችንም “እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ፥” ፤ “እውነት እላችኋለሁ፥ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤” ብሎ ሰማያዊ ክብሩን ገልጾለታል:: /ማቴ.11:11፤ ዮሐ.5፥35/:: ይገስጸው የነበረው ሄሮድስ እንኳን ሳይቀር “ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤” ተብሎ ተጽፏል:: /ማር.6፥20/:: የቅዱሳንን ሕይወት ማውሳት መጽሐፋዊ ነው፤ የምንለው በዚህ መንገድ ክብራቸውን፥ አገልግሎታቸውን፥ ቅድስናቸውን የምንመሰክር በመሆኑ ነው::

 

ቅዱስ ዮሐንስ ኤልያስን ይመስል የነበረ ነቢይ ነው:: ዮሐንስ መጥምቅና ነቢዩ ኤልያስ አኗኗራቸው ለመናንያን አርአያ ምሳሌ የሚሆን ነበር:: ኤልያስ በበረሀ ኖሯል፥ ዮሐንስም እንደዚያው:: መምህራን ሲጠሯቸው መምህር ወመገስጽ ይሏቸዋል ኤልያስ አክአብን ኤልዛቤልን ገስጿል፥ ዮሐንስም ሄሮድስን ገስጿል:: የጽድቅ ምስክሮች ነበሩ ኤልያስ ስለ ናቡቴ፥ ዮሐንስ ስለ ሕገ እግዚአብሔር ተሟግተዋል:: ሌሎችም በርካታ ተመሳስሎ አላቸው፡፡ የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስን የልደቱን ዜና የተናገረው መልአክ “በኤልያስ መንፈስና ኃይል በፊቱ ይሄዳል።” በማለት መሰከረለት:: /ሉቃ.1፥17/:: በነቢዩ ኤልያስ በቅዱስ ዮሐንስ መንገድ ሂደው ያገለገሉ መናንያንን ሰማእታትን ስውራንን ቅዱሳንን ሁሉ እነርሱን እንዳከበርን እናከብራቸዋለን:: ገድላቸውን ጽፈን ተዓምራቸውን ተናግረን ምስክርነታቸውን አጽንተን እንይዛለን:: የሕይወታቸውን የቃላቸውን የጽሑፋቸውን ትምህርት እንመሰክራለን:: ሕዝብ ደስ እንዲለው:: ለሕገ እግዚአብሔር የሚቀኑ ስለ ደሀ መበደል ስለ ፍርድ መጓደል የሚታገሉ ጻድቃን ይበዙ ዘንድ በኤልያስ መንፈስ በዮሐንስም መንገድ የሚመጡ ጻድቃን ለማፍራት ይረዳልና::/ምሳ.29፥2/::

 

የቅዱሳንን በዓል ማክበር የሚጠቅመው በረከታቸውን ለማግኘት ብቻ ሳይሆን የቅዱሳኑን ትምህርት ለመያዝም ነው:: በዓለ ቅዱሳን ሲከበር ትምህርታቸውም ይዘከራል:: የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ትምህርቶች በአራቱም ወንጌላውያን ተዳሰዋል:: የመጥምቁ ታላላቅ ትምህርቶች በሁለት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ:: የመጀመሪያ ትምህርቱ የንስሐ ጥሪ ነው:: ሕዝቡ እንዲመለሱ ይሰብካል ፥ ደንዳና ልብ የነበራቸውን እንደ ሄሮድስና የአይሁድ መምህራን ያሉትን ይገስጻል:: ይህ ትምህርቱ ዘመኑን እየዋጀ በየዘመናቱ የሚነሱ ምእመናንን ሕይወት ለማነጽ ይጠቅማል:: ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ለመጡ ለሕዝቡ ቸርነትን ስለ ማድረግ፥ ለቀራጮች ስለ እውነት ሚዛን፥ ለጭፍሮች ስለ ፍትሕ፥ . . . ያስተማራቸው ትምህርቶች ዘመናትን እየተሻገሩ የሚመክሩ ሁለት አፍ ያለው ሰይፍ ናቸው::/ሉቃ.3፥11-14/:: የንስሐ ትምህርት ተግሣጽና ምክር ይሰጣል:: ከመጥምቀ መለኮት ከቅዱስ ዮሐንስ ትምህርት የተወሰደ ነው:: በዚህምክንያት ነው በዓለ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠናባቸው፥ የሚነገርባቸው፥ የሚተረጎምባቸው ናቸው የምንለው::

 

ሁለተኛ ነገረ ሥጋዌ ላይ ያተኮረው ትምህርቱ ነው:: መጥምቁ ዮሐንስ የአምላክ ሰው የመሆን ምስጢርን ሲያስረዳ መሲህ ይመጣል ተብሎ በነቢያት የተነገረው በጌታችን መፈጸሙን አስረግጦ የተናገረ መምህር ነው::/ዮሐ.1፥29-36/:: የዓለም መድኃኒት መሆኑንም ከመልአኩ ቀጥሎ የመሰከረ ነቢይ ነው:: “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።” ብሎታልና:: በሥጋ ልደት ቢቀድመውም ለመለኮት ዘመን አይቆጠርለትምና ቅድመ ዓለም የነበረ ሕልውናውን “ከእኔም በፊት ነበር” ሲልም መስክሯል:: የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅን ምስክርነት ልዩ የሚያደርገው ነገርም አለ:: ምስክርነቱ የእውቀት ብቻ አይደለም:: በዮርዳኖስ ባሕር ቆሞ ጌታውን ሲያጠምቅ ሰማይ ተከፍቶ ያየ የእግዚአብሔር አብን ምስክርነት የሰማ የምስጢር ሰው ነው:: አይሁድን ያሳፈረበት ትልቁ ምስክርነቱም “እኔም አይቻለሁ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ መስክሬአለሁ።” የሚለው ነው:: የነገረ ሥጋዌ ትምህርቱን ሲደመድም “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” ሲል የወልደ እግዚአብሔርን ሰው መሆን በሚገባ አስረድቷል:: /ዮሐ.3፥25-36/:: ጌታችንም የምስክርነቱን እውነትነት “እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል።” በማለት ገልጿል:: /ዮሐ.5፥33/:: በዓለ ቅዱሳን በጠቅላላ ነገረ እግዚአብሔር የሚነገርባቸው፥ ትምህርተ ሃይማኖት የምናጠናባቸው፥ ታሪከ ቤተ ክርስቲያን የሚዘከርባቸው በዓላት ናቸው::

 

በአጠቃላይ በዓለ ቅዱሳንን አታክብሩ ማለትን የሚያህል የወንጌል እንቅፋትነት የለም:: ጌታችን ባለሽቱዋ ማርያም በንስሐ እንባ አጥባ ሽቱ ቀብታ መልካም አድርጋለችና ለውለታዋ መታሰቢያ ሲያቆም “እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ወንጌል በዓለም ሁሉ በማናቸውም ስፍራ በሚሰበክበት እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ እንዲሆን ይነገራል።” ካለ:: /ማቴ.26፥13/:: ስለ ስሙ እስከ ሞት ድረስ ለተደበደቡ፥መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ፥ በእስራትና በወኅኒ ለተፈትኑ፥ በደንጊያ ተወግረው ለሞቱ፥ በመጋዝ ለተሰነጠቁ፥ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ለተቅበዘበዙ . . . ወዳጆቹማ እንዴት ያለ መታሰቢያን ይሰጣቸው? የወንጌል ትምህርት ለሚተረጎምባቸው አብነቶችማ እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም?

 

በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን በዓለ ቅዱሳን ሥርዓታዊና ትውፊታዊ በሆኑ መንገዶችም ይዘከራሉ:: ሥርዓታዊው መንገድ ገድልና ተዓምር መጻፍ፥ ድርሳንና መልክ መድረስ፥ በስማቸው መቅደስ መሰየም፥ . . . ናቸው:: ትውፊታዊውም “ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም።” ከሚለው አማናዊ ቃል ኪዳን ለመሳተፍ በቅዱሳኑ ስም ጸበል ጸዲቅ ማድረግን የመሰሉ ናቸው:: በመጥምቁ ዮሐንስ ስም የሚሰበሰቡ ወዳጆቹም ገድሉን አንብበው፥ ተዓምሩን ተናግረው፥ ለነዳያን መጽውተው፥ ሰማእቱን ያዘክራሉ:: በልደቱ የወላጆቹን ሐዘን ያራቀ በምልጃው ለሚተማመኑ መታሰቢያውን ለሚያደርጉ ወዳጆቹም ደዌያቸውን እያራቀ መንፈሳዊ ደስታን ያለብሳቸዋል::

የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ የልደቱ ረድኤትና በረከት አይለየን::

ሦስት አራተኛው መሬት

ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ዮሐ.14፥18

ግንቦት 24/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

ይህንን የተስፋ ቃል ለቅዱሳን ሐዋርያት የተናገረው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ደቀ መዝሙርነት የተጠሩት በልዩ ልዩ ሙያ ተሰማርተው ሳለ ነው፡፡ በየሙያቸው ሥራ እየሠሩ ከሚተዳደሩበት ሥፍራ ሁሉ ደርሶ ፈጣሪያችን በቸርነቱ ለከበረው የወንጌል አገልግሎት ጠራቸው፡፡ “ወእንዘ ያንሶሱ መንገለ ባሕረ ገሊላ፤ ርእየ ክልኤተ አኅወ፥ ስምዖንሃ ዘተሰመየ ጴጥሮስ ወእንድርያስሃ አኅዋሁ እንዘ ይወድዩ መርበብቶሙ ውስተ ባሕረ፤ እስመ መሠግራነ እሙንቱ፡፡ ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ንዑ ትልዉኒ፤ ወእሬስየክሙ ትኩኑ መሠግራነ ሰብእ፡፡…. በገሊላ ባሕር ዳር ማዶ ሲመላለስ ሁለት ወንድማሞችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንና ወንድሙን እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፣ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና፡፡ ጌታችንም “ለጊዜው በእግር ተከተሉኝ ፍጻሜው በግብር ምሰሉኝ፡፡ እኔም ሰውን እንደ ዓሣ ወንጌልን እንደ መረብ፣ ይህን ዓለም እንደ ባሕር አድርጋችሁ እንድታስተምሩ አደርጋችኋለሁ” አላቸው፡፡ ያን ጊዜ መርከባቸውንና መረባቸውን ትተው ተከተሉት” የተቀሩትም ሁሉ እንዲህ ባለ ጥሪ ጠራቸው /ማቴ.4፥18-22፣9፣ ዮሐ.1፥46፤ 44፥51/

ቅዱሳን ሐዋርያትም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ጌታችን በዋለበት ውለው ባደረበት እያደሩ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ከእርሱ ጋር ሆኑ፡፡ በኋላም የተጠሩለትን አገልግሎት በመፈጸም ክብርን አግኝተውበታል /ማቴ.13፥42፣ ሕዝ.47፥10/፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን ሁሉ ትተው ጥለው የተከተሉትን ሐዋርያትን “ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም” አላቸው፡፡ አጽናኝ ጰራቅሊጦስ ይሰጣችኋል፡፡

“እነሆ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኀይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሏቸዋል፡፡ /ሉቃ.24፥49፣ ዮሐ.15፥26፣ 16፥7 ሐዋ.1፥4/ በዚሁ መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት ከእመቤታችን ጋር ሆነው በኢየሩሳሌም በአንድነት በጸሎት እየተጉ ሳለ አምላካችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል በእያንዳንዳቸው አድሮባቸዋል፡፡

እነሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ከብልየት ታደሱ፥ በአእምሮ ጎለመሱ፥ሕጹጻን የነበሩ ፍጹማን፥ ፍሩሃን የነበሩት ጥቡዓን ሆኑ ባንድ ልሳን ይናገሩ የነበሩ ሰባ አንድ ልሳን ተገለጸላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢየሩሳሌምን ባንድነት ዓመት በኅብረት አስተማሩ፡፡ “ወነበሩ ዓመተ ፍጽምተ በኢየሩሳሌም” እንዲል፡፡ ዓለምን 12 አድርገው ተካፍለው በእየ ሀገረ ስብከታቸው ሄደው አምልኮተ እግዚአብሔርን አስተማሩ፡፡ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መለሱ፡፡

በዓለ ሃምሳ በኦሪት የነበረው ገጽታ

እስራኤል ከሀገራቸው ወጥተው በልደት ለ430 ዓመታት መከራና ስቃይ ሲደርስባቸው ኖረው በሙሴ መሪነት በፋሲካው በግ ከሞተ በኲር ድነው ምድረ ርስትን እንዲወርሱ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት በየዓመቱ መጀመሪያ ወር /ሚያዚያ 14 ቀን/ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ /ዘጸ.12፥1-13/ ይህን በዓል ካከበሩ ሰባት ሱባኤ ቆጥረው በማግስቱ /በሃምሳኛው ቀን/ ደግሞ የእሸት በዓል /በዓለ ሠዊትን/ ያከብራሉ፡፡ ይህም በኦሪቱ እንደተገለጸው የስንዴ በኲራት አጨዳ መታሰቢያ፣ የምስጋና ጊዜ ነው፤ /ዘጸ.23፥16፣ ዘሌዋ.23፥15-18፣ ዘኁ.28፥26/

በዓለ ሠዊት በበዓለ ሃምሳ

ጌታችን እርሱ ባወቀ ይህንኑ በዓል በበዓለ ሃምሳ /በበዓለ ጰራቅሊጦስ/ እንዲተካ አድርጎታል፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት ወዲህ በበዓለ ሠዊት በዓለ ጰራቅሊጦስ ገብቶበታል፡፡ ጰራቅሊጦስ የመንፈስ ቅዱስ ልዩ የሆነው አካሉ መጠሪያ ስም ነው፡፡ ጰራቅሊጦስ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ በችግር ጊዜ ተራዳኢ፣ በሃዘን ጊዜ አጽናኝ፣ መዘንጋት ላለበት ልብ አስታዋሽ፣ በአላውያን ፊት ተከራካሪ ጠበቃ ማለት ነው፡፡ /ዮሐ.14፥16-26፣ 15፥26፣ 16፥7/ ዘመነ ጰራቅሊጦስ የሚባለው ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተነሣ ከሃምሳኛው ቀን ጀምሮ ቀጥሎ እስከ አለው እሑድ ድረስ ያለው 8 ቀን ነው፡

“ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ” የሐዋ.ሥራ.2፥2

በዓለ ሃምሳ በተባለው በዓል መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ባለ ድምጽና ግርማ ተገለጠ፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን ሐዋርያት በዝግ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዲስ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደ ተገለጠላቸው ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፡፡

“በዓለ ሃምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ፥ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዪአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ አደረባቸው፣…” /የሐ.ሥራ.2፥1-4/

መንፈስ ቅዱስ ስለምን በንፋስና በእሳት አምሳል ተገለጠ?

ሀ/ መንፈስ ቅዱስ በንፋስ /በዓውሎ ነፋስ/ ድምጽ መጣ ብሎ የተናገረበት ምክንያት?

–    ነፋስ ረቂቅ ነው መንፈስ ቅዱስም የማይመረመር የማይዳሰስ ረቂቅ ነውና፤

–    ነፋስ ኀያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኀያል ነውና፤

–    ነፋስ ፍሬውን ከገለባው ይለያል፤ መንፈስ ቅዲስም ጻድቃንን ከኀጥአን ይለያልና፤

–    ነፋስ በምላት ሳለ አይታወቅም ባሕር ሲገሥጽ ዛፍ ሲያናውጥ ይታወቃል እንጂ፡፡ መንፈስ መንፈስ ቅዱስም በምላት ሳለ አይታወቅም ቋንቋ ሲያናግር፤ ምሥጢር ሲያስተረጉም ይታወቃልና፡፡

–    ነፋስ መንቅሂ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ሰማእታትን ወደደም ጻድቃንን ወደ ገዳም ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን አነቃቅቶ የሚመራቸው እርሱ ነውና በነፋስ መስሎ ተናገረለት፡፡

ለ/ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች /በእሳት አንጻር የተገለጠውም/ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አባቶቻችን መምህራን የመንፈስ ቅዱስን በእሳት የመመሰል ትርጉም እንዲህ ገልጠው ያስተምሩናል፡፡

እሳት ምሉዕ ነው መንፈስ ቅዱስም ምሉዕ ነውና፤ እሳት በምልዓት ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገልጽም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም እንጂ አድሮ ሳለ አይታወቅምና እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው፤ ኋላ በእንጨት እያቀጣጠሉ ያሰፉታል፤ መንፈስ ቅዱስም በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው፡፡ ኋላ በሥራ ያሰፉታልና፤ እሳት ጣዕመ መዓዛን ያመጣል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን ያመጣልና፡፡ እሳት በመጠን ቢሞቁት ሕይወት ይሆናል፡፡ ከመጠን አልፎ የሞቁት እንደሆነ ግን ያቃጥላል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደሆነ ሕይወት ይሆናል፤ በማይገባ ከተጻፈው ወጥቶ የመረመሩት እንደሆነ ግን ይቀስፋልና፤ “እሳት በላኢ ለዓማጽያን ለእለ ይክሕዱ ስሞ ወእሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ” እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡

እሳት ያቀረቡለትን ሁሉ ያቀጥላል፤ መንፈስ ቅዱስም ሕዝብ አሕዛብ የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡትን መሥዋዕት ይቀበላልና፡፡ እሳት ውኃ ገደል ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፡፡ እሳት ዱር ይገልጻል መንፈስ ቅዱስም ምሥጢርን ይገልጻልና፡፡ እሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ይመቻል፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ያመቻል፡፡ እሳት ካንዱ ፋና አምሳ፣ ስልሳ፣ ፋና ቢያበሩለት ተከፍሎ የለበትም፤ መንፈስ ቅዱስም ተከፍሎ ሳይኖርበት እስከ ምጽአት ድረስ ሲሰጥ ይኖራልና፡፡

ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ያስፈለጋቸው ለምንድር ነው?

ሐዋርያት “ወረደ፣ ተወለደ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ተነሣ አረገ” ብለው ለማስተማር ለማሳመን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋው ባይታደላቸው ኖሮ በራሳቸው ብቻቸውን በደከሙ፣ ደክመውም በቀሩ ነበር፡፡ ሰው ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር መንፈሳዊውን ተግባር ቀርቶ ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት አይቻለውም፡፡ መንፈሳዊው ሥራ ደግሞ በሰይጣን ዲያብሎስና በሠራዊቱ /ርኲሳን መናፍስት/ ልዩ ልዩ ፈተናና መሰናክል ያጋጥመዋል፡፡ ስለሆነም በመንፈስ ርኲስ የሚመጣውን ፈተና ለመቋቋም ምንጊዜም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ያሻል፡፡

ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊትና በኋላ

ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ከመሳተፋቸው በፊት ምንም እንኳን ከጌታችን ባለመለየት ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ቢቆዩ ነገር ግን በልብ የሚያምኑትን በአንደበታቸው ገልጸው ለመመስከር ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ የችግሩም መንስኤ “የምናምነውን ብንመሰክር እንገረፋለን፣ እንሰቀላለን” የሚል ፍርሃት ነበር፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በዕለተ አርብ ጌታችን በቀያፋ ግቢ ውስጥ መከራን ሲቀበል ተከትሎት ወደዚያው አምርቶ ነበር፡፡ ሆኖም በተለያዩ ሰዎች ለሦስት ጊዜያት “ከገሊላው ኢየሱስ ጋር አይደለህምን?” ተብሎ ቢጠየቅ፤ የሰጠው ምላሽ “ሰውየውን /ጌታችንን ነው/ አላውቀውም” የሚል ነበር /ማቴ.26፥69-72/ በኋላ ግን /ማለትም መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ካሳደረበት በኋላ/ በሸንጎ ሹማምንት “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፣ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው /የጌታችንን ነው/ ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም መልሰው አሉ፡፡ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል፡፡…. ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፏቸው፣ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው፡፡ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ” /የሐዋ.ሥራ.5፥28-41/

ከዚህ በላይ የትምህርታቸው ቃል በሰማዕያን ልቡና ገብቶ ካለማመን ወደ ሃይማኖት፣ ከአምልኮተ ባዕድ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚመልስ ሆኗል፡፡ ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራት ያደርጉም ጀመር አንድ ቋንቋ ብቻ ያውቁ የነበሩት ሐዋርያት ሰባ አንድ ቋንቋ ተጨምሮላቸው የጌታችንን ወንጌል በመላው ዓለም ተዘዋውረው አስተምረዋል፡፡

በዓለ ሃምሳ ለቤተክርስቲያን

ይህ በዓል የቤተ ክርስቲያን የልደት በዓል ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ስያሜ ያለ ምክንያት የተሰየመ /የተሰጠ/ አይደለም፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመኑ የተነሡ ሊቃውንት ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፍት እንደሚገልጹት በዚህች ቀን ቁጥራቸው ከሦስት ሺህ ያላነሱ አይሁድ ወደ ክርስትና የመጡበት፤ወንጌል ከመካከለኛው ምስራቅ አልፋ በመላው ዓለም የተነገረችበት የተስፋፋችበት ቀን ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በተባለ መጽሐፋቸው ይህንን ሁኔታ እንዲህ ገልጸውታል፡-

“…. ጌታ ባረገ በአስረኛው ቀን ጧት መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ተሰጠ፡፡ ጌታ የነገራቸው የተስፋ ቃል ሁሉ ተፈጸመ፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በእነርሱ ላይ ሲያድር ለቤተ ክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው “መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላት ኑሮ የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ኮስምኖ ቀጭጮ ይቀር ነበር፤ ስለዚህም በሚገባ አነጋገር ይህች ዕለት የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ትባላለች” ይላል፡፡ ብዙ ሊቃውንት ይህችን ዕለት የበዓላት ሁሉ እመቤት ይሏታል፡፡….”

በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ይህንኑ በዓል በጸሎትና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት አክብረውት ይውላሉ፡፡

በዚህ ዕለት የሚቀደሰው ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ፥ ምንባባቱ ደግሞ፡-

ኤፌ.4፥1-17

/ቁጥር7/ እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን፥

1ኛ ዮሐ.2፥1-18

/ቁጥር.17/ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል

የሐዋ.ሥራ.1፥1-18

/ቁጥር 4/ በሁሉም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር

የሚለው ሲሆን ምስባኩ “ወወሀብከ – ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው” የሚለው ነው፥ /መዝ.67፥18/

በዚህ ዕለት ጌታችን ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሰጣቸው ተስፋም በወንጌል ንባብ ጊዜ ይሰማል፡፡ ይኸውም፡- “ወኢየኅድገክሙ እጓለማውታ ትኲኑ” የሚለው ነው፡፡

ኢየሩሳሌም -ቤተ ክርስቲያን

ቅዱሳን ሐዋርያት ፈጣሪያችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዛቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ በኢየሩሳሌም ከተማ ጸንተው /ቆይተው/ ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ከተማ ቢናወጹ ይህን ጸጋ ለመሳተፍ ባልታደሉ ነበር፡፡ ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር /ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ/ ደግሞ ምንም ምን ተግባር ማከናወን ባልተቻላቸው ነበር፡፡ በዚህ የተነሣ ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ እመቤታችንን ይዘው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፡፡ ይህም በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች የሚያስተምረን ነገር፡- በሃይማኖት በምግባር ጸንቶ የሚኖር ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ይጎበኘዋል፡፡ በጸጋ ላይ ጸጋ ይጨምርለታል፡፡ ኋላም ለመንግሥተ ሰማይ ያበቃዋል፡፡

ይህንን ጸጋ ለማግኘት ፈጣሪያችን ኢየሩሳሌም ከተባለች ለሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ ከሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳንናወጽ እንዳንወጣ አዞናል፡፡ ኢየሩሳሌም ማለት የሰላም ሀገር /ሀገረ ሰላም/ ማለት እንደሆነ፤ ቤተ ክርስቲያን /ቤተ ክርስቶስ/ ማለት ደግሞ የሰላም ቤት ማለት ነው፡፡ የሰላም አለቃ፣ የሰላም ባለቤት የክርስቶስ ቤት ናትና፡፡ /ኢሳ.9፥6/

እንግዲህ አባ ሕርያቆስ ባስተላለፈልን ቡራኬ መሠረት “ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን፥ በከመ ተጋባእክሙ በዛቲ ዕለት፣ ከማሁ ያስተጋብእክሙ በደብረ ጽዮን ቅድስት፣ ወበ ኢየሩሳሌም አግዓዚት እንተ በሰማያት፡- እናንተ የክርስቲያን ወገኖች በዚህች ቀን እንደተሰበሰባችሁ ክብርት በምትሆን በደብረ ጽዮን ይሰብስባችሁ፡፡ በልዕልና ባለች በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ይሰብስባችሁ፡፡”  እንዳለን እስከ መጨረሻ ሕይወታችን ቅድስት ንጽሕት ርትእት በሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ያጽናን፡፡ በዓሉን የበረከት የረድኤት ያድርግልን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

lidetaleMariam 1

“መሠረታቲሃ ውስተ አድባር ቅዱሳን፡- መሠረቶቿ የተቀደሱ ተራሮች ናቸው” /መዝ.86፥1/


በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ

lidetaleMariam 1ይህ ቃል የእመቤታችንን አያቶቿን የቀደሙ ወላጆቿን ንጽሕና፣ ቅድስና፣ ክብር አስመልክቶ ቅዱስ ዳዊት የተናገረው የምስክርነት ቃል ነው፡፡ ይህ ምስክርነት አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ለኩነተ ሥጋ የመረጣት ቅድስት ድንግል ማርያም ወላጆቿ ንጹሐን፣ ቅዱሳን መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ሲመላለስ፡- “መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬን ያፈራል፤ ክፉ ዛፍም ክፉ ፍሬን ያፈራል፡፡ መልካምም ዛፍ ክፉ ፍሬን ማፍራት፥ ክፉ ዛፍም መልካም ፍሬን ማፍራት አይችልም” ማቴ.7፥17-18፡፡ በማለት እንደተናገረው እመቤታችን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም የተገኘችባቸው ወላጆቿ ሁሉ ቅዱሳን ንጹሐን፣ እግዚአብሔርን የሚወዱና የሚያከብሩ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡ ለመሆኑ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የዘር ሐረግና የትውልድ ታሪኳ ምን ይመስላል?

 

በነገረ ማርያም ሰፍሮ ከምናገኘው ሰፊ ታሪክ ከፊሉን እንዲህ አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ!

የእመቤታችን ቅድመ አያቶቿ ቴክታ በጥሪቃ ይባላሉ፤ ይህ ቀራቸው የማይባሉ ባለጸጎች ነበሩ፤ ብዕላቸውም የወርቅ፣ የብር፣ የፈረስ፣ የበቅሎ፣ የሴት ባሪያ፣ የወንድ ባሪያ ነው፡፡ ከወርቁ ብዛት የተነሣ እንደ አምባር እንደ ቀለበት እያሠሩ፤ ከበሬው ከላሙ ቀንድ ያደርጉት ነበር፡፡ ይህን ያህል አቅርንተ ወርቅ፤ ይህን ያህል አቃርንተ ብሩር ተብሎ ይቈጠር ነበር እንጂ፤ የቀረው አይቈጠርም ነበር፡፡ ከዕለታት ባንደኛው በጥሪቃ ከቤተ መዛግብት ገብቶ የገንዘቡን ብዛት አይቶ፤ “ቴከታ እኔ መካን፤ አንቺ መካን ይህ ሁሉ ገንዘብ ለማን ይሆናል?” አላት “እግዚአብሔር እንጂ ከኔ ባይሰጥህ ወይ ከሌላ ይሰጥህ ይሆናል፤ አግብተህ አትወልድምን?” አለችው፡፡ “ይህንስ እንዳላደርገው አምላከ እስራኤል ያውቃል” አላት፤ በዚህ ጊዜ አዘኑ፤ ወዲያው ራእይ አይተዋል፤ ነጭ እንቦሳ ከበረታቸው ስታወጣ፣ እንቦሳይቱ እንቦሳ እየወለደች እስከ ስድስት ስታደርስ ስድስተኛይቱ ጨረቃን፣ ጨረቃ ፀሐይን ስትወልድ አይተው፥ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም /ሕልም ተርጓሚ/ አለና ሂደው ነገሩት፤ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ፤ ጨረቃይቱ ከፍጡራን በላይ የምትሆን ልጅ ትወልዳላችሁ የፀሐይ ነገር ግን አልተገለጸልኝም እንደ ነቢይ እንደ ንጉሥ ያለ ይሆናል” አላቸው፡፡ እነርሱም “ጊዜ ይተርጉመው” ብለውት ሄዱ፡፡ ከዚህ በኋላ ፀነሰች፤ ወለደች ስሟን ሄኤማን አለቻት፤ ሄኤማን ማለት ረካብኩ ስእለትየ ረከብኩ ተምኔትየ /የፈለግሁትን የለመንኩትን አገኘሁ/ ማለት ነው፡፡ ሄኤሜን ዴርዴን፤ ዴርዴ ቶናን፣ ቶና ሲካርን፣ ሲካር ሄርሜላን፣ ሄርሜላ ሐናን ወለደች፡፡ ሐና አካለ መጠን ስትደርስ ከቤተ ይሁዳ ለተወለደ ኢያቄም ለሚባል ደግ ሰው አጋቧት፣ ምክነት ወርዶ እንደ አያቶቿ ሆናለች፤ ብዕሉ ግን በመጠን ሆኗል፡፡

 

ከጎረቤቷ በዝሙት የምትኖር አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ሐና “ዛሬ ቤተ ክርስቲያን እስማለሁ ብዬ ነበር፤ ነገር ግን የምለብሰው ልብስ የለኝም” አለቻት፡፡ እርሷም “ልብስማ የኔ ካንድ ሁለት ሦስት ልብስ አለልሽ አይደለም? ያንን ለብሰሽ አትሄጅምን?” አለቻት፡፡ “ያንቺ ልብስ የተሰበሰበ በዐስበ ደነስ በዐስበ ዝሙት ነው፡፡ እግዚአብሔር ንጹሐ ባሕርይ ነውና ንጹሕ ነገር ይወዳል፤ ይህን ለብሼ ብለምነው ምን ይሰማኛል ብዬ ነዋ” አለቻት፡፡ “ሐና፤ እኔ በምን ምክንያት ልጅ ነሣት እያልሁ ሳዝንልሽ እኖር ነበር፤ ለካ እንደ ድንጊያ አድርቆ ያስቀረሽ ይህ ክፋትሽ ነው” አለቻት በዚህ አዝናለች፡፡

 

በሌላ ጊዜም ሐናና ኢያቄም “መሥዋዕት እናቀርባለን” ብለው ከቤተ መቅደስ ሄዱ፤ ሊቀ ካህናቱ ሮቤል ይባል ነበር፡፡ “ወኢይተወከፍ መሥዋዕቶሙ ለመካናት እንጂ ይላል፤ “እናንተማ ብዝኁ ወተባዝኀ… ብሎ ለአዳም የነገረውን ያስቀረባችሁ ርጉማን አይደላችሁምን? ቢጠላችሁ ነው እንጂ ቢወዳችሁማ ልጅ ይሰጣችሁ አልነበረምን? መሥዋዕታችሁን አልቀበልም” ብሏቸው በዚህ እያዘኑ ተመልሰዋል፡፡ …. ከዛፍ ሥር ተቀምጠው አርጋብ /ርግቦች/ ከልጆቻቸው ጋራ ሲጫወቱ ዕፅዋት አብበው አፍርተው አይታ “አርጋብን በባሕርያቸው እንዲራቡ፣ ዕፅዋትን እንዲያብቡ እንዲያፈሩ የምታደርግ የኔ ተፈጥሮዬ ከድንጋይ ይሆን ልጅ የነሣኸኝ” ብላ አዘነች፡፡ ከቤታቸው ሂደው “ወንድ ልጅ ብንወልድ ወጥቶ ወርዶ አርሶ ቆፍሮ ይርዳን አንልም ለቤተ እግዚአብሔር አንጣፊ፤ ጋራጅ ሆኖ ይኖራል፤ ሴት ብንወልድ ዕንጨት ሰብራ ውኃ ቀድታ ትርዳን አንልም፤ ለቤተ እግዚአብሔር መሶበ ወርቅ ሰፍታ መጋረጃ ፈትላ ትኑር” ብለው ብፅዓት ገብተዋል፡፡

 

የሐምሌ  30 ዕለት እሷ ለሱ “ፀምር ሲያስታጥቁህ መቋሚያህ አፍርታ ፍጥረት ሁሉ ሲመገባት አየሁ” ብላ፤ እሱ ለሷዋ “ጻዕዳ ርግብ ሰባቱን ሰማያት ሰንጥቃ መጥታ በራስሽ ላይ ስታርፍ፤ በቀኝ ጆሮሽ ገብታ በማኅፀንሽ ስታድር አየሁ” ብሎ ያዩትን ራእይ ተጨዋውተዋል፡፡ በሀገራቸው መፈክረ ሕልም አለና ሂደው ነገሩት፡፡ “ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ” አላቸው፡፡ “አንተስ አልፈታኸውም ጊዜ ይፍታው” ብለው ተመልሰዋል፡፡ በነሐሴ 7 ቀን መልአክ መጥቶ ደግ ልጅ ትወልዳላችሁ ብሏቸው በብሥራተ መልአክ በፈቃደ አምላክ እመቤታችን ተፀነሰች፡፡ በተፀነሰችም ጊዜ ብዙ ተአምራት ተደርጓል፡፡

 

በርሴባ የምትባል አክስት ነበረቻት አንድ ዐይና ነች፤ “ሐና እግዚአብሔር በረድኤት ጎበኘሽ መሰለኝ” ብላ ማኅፀኑዋን ደሳ ዐይኗን ብታሸው በርቶላታል፡፡ ይህን አብነት አድርገው ሕሙማን ሁሉ ማኅፀኑዋን እየዳሰሱ የሚፈወሱ ሆነዋል፡፡ ዳግመኛም ሳምናስ የሚባል ያጎቷ ልጅ ነበር ሞተ፤ ትወደው ነበርና ያልጋውን ሸንኮር ይዛ እየዞረች ስታለቅስ ጥላዋ ቢያርፍበት “ሰላም ለኪ ኦ እምሔውቱ ለዘገብረ ሰማየ ወምድረ” ብሎ ከመፈክረ ሕልም የቀረውን ተርጉሞላታል፡፡

 

ከዚህ በኋላ አይሁድ ለምቀኝነት አያርፉምና “ቀድሞ ከነዚህ ወገን የሚሆኑ ዳዊት ሰሎሞን አርባ አርባ ዘመን እንደሰም አቅልጠው እንደ ገል ቀጥቅጠው ገዙን፡፡ አሁን ደግሞ ከዚህች የተወለደ እንደምን ያደርገን ይሆን?” ብለው በጠላትነት ተነሡባቸው፤ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ ለኢያቄም “አድባረ ሊባኖስ ይዘሃት ሂድ” ብሎት እመቤታችን በሊባኖስ ተራራ ተወልዳለች፡፡ ይህም አስቀድሞ እግዚአብሔር ባወቀ “እምሊባኖስ ትወፅእ መርዓት … ሙሽራ /እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም/ ከሊባኖስ ትወጣለች” በማለት ጠቢቡ የተናገረው ቃለ ትንቢት ነው፡፡ /መኃ.4፥8/

 

ዮም ፍሥሐ ኮነ በእንተ ልደታ ለማርያም፤ በእመቤታችን ልደት ምክንያት ዛሬ ደስታ ሆነ፡፡

በግንቦት 1 ቀን /5ሺ ከ5መቶ የመከራው ዘመን ሊያልቅ 15 ዓመታት ሲቀሩት/  ሊባኖስ በሚባል ተራራ ከፀሐይ የምታበራ ሴት ልጅ ተወለደች፡፡ ይህቺውም ፍጥረት ሁሉ /ደቂቀ አዳም ሁላቸው/ ተስፋ ሲያደርጓትና ሲጠባበቋት የነበረች የድኅነታቸው ምልክት እመቤታችን ናት፡፡

 

ሶሪያዊው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬምም “አክሊለ ምክሕነ ወቀዳሚተ መድኀኒትነ፡፡ ወመሠረተ ንጽሕነ ኮነ በማርያም ድንግል፡- የመመኪያችን ዘውድ የደኅንነታችን መጀመሪያ የንጽሕናችንም መሠረት በድንግል ማርያም ሆነልን” በማለት መናገሩ ስለዚህ ነው፡፡

 

  • አክሊል ምክሐነ፡- አላት ይህም አክሊል የወዲህኛው፣ ምክሕ የወዲያኛው ነው፡፡ ከነገሥታት መካከል እንደ ዳዊት የከበረ የለም፡፡ ምንም እንኳን ቅዱስ ዳዊት የከበረ ቢሆን የመመኪያችንን ዘውድ ማምጣት አልተቻለውም፡፡
  • ወቀዳሚተ መድኀኒተ አላት፡- ቀዳሚተ የወዲህኛው መድኀኒት የወዲያኛው ነው፡፡ ከመሳፍንት ወገን የሚሆን ኢያሱ ምንም የስሙ ትርጓሜ መድኃኒት ቢሆን የደኅንነታችን መጀመሪያ መሆን አልተቻለውም፡፡
  • ወመሠረተ ንጽሕና አላት፡- መሠረት የወዲህኛው፤ ንጽሕ የወዲያኛው ከነቢያተ እግዚአብሔር ወገን የሚሆን ኤልያስ በድንግልና በንጽሕና መኖሩ የሚታወቅ ነው፡፡ ነገር ግን ምንም ንጹሕ ድንግል ቢባል የንጽሕናችን መሠረት መሆን አልተቻለውም፡፡ የመመኪያችን ዘውድ፣ የደኅንነታችን መጀመሪያ፤ የንጽሕናችን መሠረት ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤” በማለት ተናግሯል፡፡ በእርሷ ምክንያትነት መድኀኒዓለም የሚፈጽምልንን ካሳ ነቢያትና የቀደሙ አበው ሁሉ የእርሷን መወለድ በናፍቆት ሲጠባበቁ ነበር፡፡ ከነቢያት አንዱ የሆነ ኢሳይያስም “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆንነ እንደ ጎሞራም በመሰልነ ነበር፡፡” በማለት መናገሩ በእርሷ መገኘት ከጥፋት መዳናችንን ሲገልጽ ነው፡፡ ኢሳ.1፥9

ወደ ቀደመ ነገራችን እንመለስና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ተወለደች የሐና ዘመዶቿና ጎረቤቶቿ በሰሙ ጊዜ ፍጹም ደስ ብሏቸው ወደ ሊባኖስ ተራራ ተሰበሰቡ፡፡ ሕፃኗን /እመቤታችንን/ ተመልክተው ፍጹም አደነቁ፡፡ እርስ በርሳቸውም እንደዚች ያለች ብላቴና ከቶ አየተን አናውቅም ተባባሉ፤ ጸጋ እግዚአብሔር በርሷ አድሯልና፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በሰውነቷ ሁሉ መልቷልና፡፡

 

ከኢያቄምና ከሚስቱ ከሐና ጋራ ደስ እያላቸው የእግዚአብሔርን ቸርነት እየተናገሩ ሰባት ቀን ተቀመጡ፤ ያችንም ብላቴና ስምዋን ማርያም አሏት ይኸውም የእግዚአብሔር ስጦታ ማለት ነው፡፡ ሰባቱንም ቀን በፈጸሙ ጊዜ በፍቅር ወደ ቤታቸው ገቡ፡፡

 

በዚህ ትውፊት መሠረት ኢትዮጵያውያን ምእመናን በየዓመቱ ግንቦት 1 ቀን የእመቤታችንን ልደት ከቤታቸው ወጥተውና ከያሉበት ተሰባስበው ንፍሮ ቀቅለው፣ አነባብሮ ጋግረውና ሌላም እንደ አቅማቸው /ዝክር አዘጋጅተው/ በመንፈሳዊ ደስታ ዛሬም ድረስ ያከብሩታል፡፡

 

የእመቤታችን ስሞችና ትርጓሜያቸው፡፡

ማርያም ማለት ፍጽምት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው መልክ ከደምግባት አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ ፍጻሜው ግን ንጽሐ ሥጋ ከንጽሐ ነፍስ ድንጋሌ ሥጋ ከድንጋሌ ነፍስ አስተባብራ ተገኝታለችና፡፡ አንድም ማርያም ጸጋ ወሀብት ማለት ነው፡፡ ለጊዜው ለእናት ለአባቷ ጸጋ ሆና ተሰጥታለች፡፡ ፍጻሜው ግን ለሰው ሁሉ ጸጋ ሁና ተሰጥታናለችና፡፡

 

አንድም፡- ማርያም ማለት መርሕ ለመንግሥተ ሰማያት ማለት ነው፡፡ ምእመናንን መርታ ገነት መንግሥተ ሰማያት አግብታለችና፡፡ አንድም ማርያም ማለት ልዕልት ማለት ነው፡፡ ከፈጣሪ በታች ከፍጡራን ሁሉ በላይ ናትና አንድም ማሪሃም ማለት እግዝእተ ብዙኀን ማለት ነው አብርሃም ማለት አበ ብዙሃን እንደሆነ ማለት ነው፡፡

 

እንግዲህ ለነቢያተ ዜና ትንቢታቸው ለሐዋርያት ስብከታቸው ለክርስቲያኖች ሁሉ ተስፋቸው የሆነች እመቤታችን የተወለደችበትን ቀን ሁላችን ምእመናን በፍጹም ፍቅርና ደስታ እናከብረዋለን፡፡

 

ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ለተዋሕዶ ከመረጣት ከዓለመ አንስት ተለይታ በንጽሕና በቅድስና አጊጣ የመመኪያችን ዘውድ ከሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ይክፈለን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የቀኝ ዐይን – ድንግል ማርያም

በዲ/ን ብርሃኑ አድማስ

አፍጣኒተ ረድኤት ማርያም በጊዜ  ምንዳቤ ወአጸባ ለዐይን እምቀራንባ፤ አንቲ ውእቱ ረዳኢተ ያዕቆብ በቤተ ላባ፤ በኩሉ ኅሊናሃ ወበኩሉ አልባባ፤ዘኢታፈቅረኪ ነፍስ ትሠሮ እምሕዝባ፡፡

 የነገረ ማርያም ሊቅ(Marian Doctor)እየተባለ የሚጠራው ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ እመቤታችንን በብዙ ምሳሌ እየመሰለ፣ እየተረጎመና እያመሰጠረ ብዙ ጊዜ አመስግኗታል፡፡ ምንም እንኳን እኛ የምናውቀው የምስጋና ድርሰቱ ለጸሎት የምንጠቀምበት ውዳሴ ማርያም ቢሆንም ከትርጓሜና ከስብከቶቹ ውጪ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ስንኝ ያላቸው የምስጋና ድርሰቶችን(Hymns) መድረሱን ታሪክ ጸሐፊው ሶዝመን መዝግቦልናል፡፡ ከነዚህ የምስጋና ድርሰቶቹ መካከልም ‹‹በእንተ ልደት››(On Nativity) እና ‹‹በእንተ ቤተ ክርስቲያን››(On the Church)በተባሉ ትልልቅ ድርሰቶቹም እመቤታችንን ደጋግሞ ያመሰግናታል፡፡

በተጠቀሱት ሁለቱም ድርሰቶቹ እመቤታችንን ለማመስገን ከተጠቀመባቸው ምሳሌዎች ውስጥ አንዱ “ዐይን” ነው፡፡ ሊቁ ስለ ቤተክርስቲያን በደረሰው የምስጋና መዝሙሩ ውስጥ እንዲህ ይላታል፤ ‹‹ዐይን ጥርት የሚለው ከፀሐይ ብርሃን ጋር ተዋሕዶ ከብርታቷ ኃይልን ከውበቷም ነጸብራቅን ሲቀበል ነው፤ በዚህ ጊዜ በግለቷ ይሰነገላል፣ያበራል፤ በውበቷም ያጌጣል፤… ልክ እንደዚሁ ማርያም ዐይን ናት፤ብርሃን (ጌታ) ማደሪያውን በእርሷ አዘጋጀና መንፈሷን ጽሩይ አደረገ፤አሳቦቿን አጠራ፣ኅሊናዋንም ንጹሕ አደረገ፤የድንግልናዋንም ክብር አበራው ››/Hymns on the Church, 36, 1-2/፡፡ ሊቁ በዚሁ ድርሰቱ ውስጥ ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ፤ ‹ለዚህ ዓለም ሁለት ዐይኖች ተሰጡት፤ ማየት ያልተቻላት የግራ ዐይን ሔዋን ስትሆን፣ የምታበራው የቀኝ ዐይን ደግሞ (እመቤታችን) ማርያም ናት፡፡በማታየው በጨለማዋ ዐይን ምክንያት መላው ዓለም ጨለመ፤ ስለዚህም ሰዎች በጨለማ ጥላ ውስጥ ሆነው ሲዳብሱ ያገኙት ሁሉ አምላክ ፣ ሐሰቱም እውነት መሰላቸው፡፡ነገር ግን ዓለም እንደገና በሌላ ዐይኑ ባበራና (ባየና) ሰማያዊው ብርሃንም በዚች ዐይን ሰሌዳ ውስጥ ባንጸባረቀ ጊዜ ሰዎችም ቀድሞ ያገኙትን(ያመለኩትን) የኑሮአቸው ውድቀት(የባሕርያቸው መጎስቆል) መሆኑን ተረድተው ወደ ማንነታቸው ተመለሱ (አንድነታቸውን አገኙ)›› ይላል /Ibid, 37, 5-7/::

 

በዚህ መሠረት የእመቤታችን ልደት ዓለም ማየት የጀመረበት ዕለት ነው ማለት ነው፡፡ በርግጥም በነገረ ማርያም መጽሐፋችን ላይ እንደተገለጸው እመቤታችን በቴክታና በጥሪቃ(ሰባተኛ ቅድመ አያቶቿ) በታየው ሕልም መሠረት ዓለምን ሰፍኖበት ከነበረው ድቅድቅ የኃጢኣት ጨለማ እፎይታ የሰጠችው ጨረቃ እርሷ ናት፡፡ በጨለማ ሲያዩት የሚያስፈራውና ሌላ ሌላ የሚመስለው ጉቶው፣ ቁጥቋጦው ፣ ድንጋዩ ፣ ጉብታው….ሁሉ ተራ ነገር መሆኑ የተጋለጠባት፤ ሰዎችም የሰገዱለት ሁሉ አምላክና ጌታ መሆኑ ቀርቶ ድንጋይ ጉብታ መሆኑን ማየት የጀመሩባት፣ ከደገኛው ፀሐይ ክርስቶስ መውጣት በፊት ከረጂሙ ዘመን ጨለማ ጭንቀት የተገላገልንባት ጨረቃ፣ ብርሂት የቀኝ ዐይን እመቤታችን ማርያም ናት፡፡ ስለዚህም ልደቷን የጨለማችን መገፈፍ፣ የዐይናችን ማየት፣ የብርሃናችንም መውጣት ነውና በፍጹም ደስታ እናስበዋለን፤ እናከብረዋለንም፡፡

 

ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምን የምናስታውሰውም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ብዙ በማመስገኑ ብቻ ሳይሆን ግሩም አድርጎ በማመስጠሩና እንዲህ ያለ ልዩ ልዩ ነገር በማምጣቱም ጭምር ነው፡፡ ለነገሩ ሰው የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ ከሆነ በኋላ ይህን ሁሉ ማድረጉ አያስደንቅም፡፡ የሆነው ሆኖ የእርሱን ያህል በልዩ ልዩ ሕብረ-አምሳል ያመሰገናት ያለ አይመስልም፡፡ሊቁ በልደት ድርሰቱም‹‹እናትህ አስደናቂ ናት፤ ጌታ ወደ እርሷ ገባና አገልጋይ ሆነ፤ እየተናገረ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ግን ዝም አለ፤ ወደ እርሷ በነጎድጓድ ድምፅ ገብቶ በእርሷ ውስጥ ጸጥታን አሳደገ፤ የዓለሙ እረኛ ገብቶ በግ ሆኖ ተወለደ፤ እንደ በግም ‹ባ› እያለ ተገለጠ ››/On Nativity, 11, 6/ እያለ አስደናቂነቷን እየደጋገመ ይናገርላታል፡፡አንድ ብቻ ጨምሬ ወደ በዓሉ ልመለስ ፤ቅዱሱ ሊቅ ጌታን እንዲህ ይለዋል፤ ‹‹አንተና እናትህ ብቻ ተወዳዳሪ የሌላችሁ ውቦች ናችሁ፤ በአንተ ላይ ምንም ምን ትንታ(mark) በእናትህም ላይ እንከን(stain) የለም››/Carmina Nisibena, 27,8/፡፡ምንኛ ግሩም ምስጋና፣ እንዴትስ ያለ ፍቅር፣ እንደምንስ ያለ መረዳት ነው? መብቃት ነዋ! መብቃት! ከሌላ ከምን ይገኛል? እርሱ ካልገለጸ፡፡

 

ከቅዱስ ኤፍሬም ሌሎች ድርሰቶች የተነሣሁትና ርእሴንም በእርሱ ምስጋና ያደረግሁት እንዲሁ አይደለም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ውዳሴ ማርያም እየተጣጣለና ድርሰቱም የእርሱ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ነው (ምነው በሆነና ነበር) ፤ ወይም ደግሞ እርሱ ስለ ሌላ የደረሰውን የእኛ ሰዎች የማርያም ምስጋና ነው ብለው ነው እንጂ እርሱስ እንዲህ አይልም መባል ስለተጀመረ እርሱ ስለ እርሷ ከደረሰዉ ወደ ግእዝ የተተረጎመዉ ትንሽ መሆኑንና ከላይ ለምሳሌነት ካቀርብኳቸው በላይ በውዳሴ ማርያም ምን አዲስ ነገር አለ ለማለት ነው፡፡ ይህችን ታህል ጥቆማ ከሰጠሁ ቦታውም ጊዜውም የጽሑፉም ዓላማ በዚህ ጉዳይ ላይ መከራከር አይደለምና ወደ እናታችን በዓለ ልደት በረከት ላምራ፡፡

 

በርግጥም ፍጹም ልዩ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማይጠረጠር መልኩ ከፍጥረት ሁሉ ልዩ ናት፡፡ በድንግልና ላይ እናትነት፣ በክብረ ድንግልና ላይ ክብረ ወሊድ፣ በድንጋሌ ሥጋ ላይ ድንጋሌ ነፍስና ድንጋሌ ኅሊና የተሰጠው ከእርሷ በቀር ማንም የለም፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ ምንም እንኳ ‹‹በልቧ ትጠብቀው ነበር››/ሉቃ.2፡51/ ተብሎ እንደተጻፈው አትናገረው እንጂ ከፍጥረት ወገን እንደ እመቤታችን እርሱን ለማወቅ የተቻለው ፍጥረት የለም፡፡ ሊቁ ኦሪገን በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜው ላይ እንደገለጸው ስለ አምላክ ፍጥረት ሊያውቀው የሚቻለው የመጨረሻው የእውቀት ደረጃ ላይ የደረሰችው እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ እንደ እርሱ ትርጓሜ እመቤታችን ፍጡር ለፈጣሪው ክብር ሊጨምርለት እንደማይቻለው እያወቀች  ‹‹ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር – ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች›› ያለችው ፍጡር ሊረዳው የሚቻለው የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሳ በዚያ መጠን ማመሰገኗን ስትገልጽልን ነዉ ይላል፡፡በርግጥም በዚህ መጠን ከርሷ በላይ ሊደርስ የሚቻለው እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ የሚያመለክተውም ገና በምድር ሳለች ለፍጥረት የሚገባው ለዚህ የመጨረሻ ብቃት ከደረሰች ከዚህ ዓለም ከሔደች በኋላማ ይልቁንም እንዴት ያለውን የተወደደውንና ከፍጥረት ሁሉ የላቀውን ምስጋና ታቀርብልን ይሆን? ምን ጥርጥር አለው? ልዩ የሆነውን ልታቀርብ የሚቻላት ልዩ እናት፡፡

 

ለዚህም የበቃችው ራሷን ለሰው በሚቻለው ከፍተኛው መጠን እንደምትጠብቅ አስቀድሞ የሚያውቅ ፈጣሪ እርሱም ደግሞ ጠበቃትና ከፍጥረት ወገን ልዩ ሆነች፡፡ ቀድም ብለን የተመለከትናቸው የቅዱስ ኤፍሬም ጥቅሶች የሚያረጋግጡልንም ይህንኑ ነው፡፡ ብርሂት የሆነች ዐይን ለሰውነት መብራት የምትሆነው የፀሐይ ብርሃን ሲዋሐዳት እንደሆነው ሁሉ እርሷም በራሷ ብርሃነ ዐይን ንጽሐ ሥጋ ወኅሊና ላይ የብርሃን ጌታ ብርሃን የተባለ ጸጋዉን አሳድሮ ንጽሕናዋን ወደር የለሽ አደረገዉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ርብቃ ለይስሐቅ የታጨችበትን የሚናገረዉ አንቀጽ ላይ ‹‹ብላቴናይቱም መልክዋ እጅግ ያማረ፥ ወንድ የማያውቃት ድንግልም ነበረች››/ዘፍ. 24፣16/ የሚለውን ሲተረጉም ‹ወንድ የማያውቃት› የሚለውን ለሥጋ ድንግልናዋ ከሰጠ በኋላ ‹ድንግልም ነበረች› ያለው ደግሞ ለመደጋገም ሳይሆን በኅሊናዋም ያልባከነች የተጠበቀች ነበረች ሲል ነው ይላል፡፡ ይሁን እንጂ እንደዚህ ያለችው ድንግል ርብቃ ድንገት(ለርሷ) ያገኘችውና ማንነቱን እንኳ በውል የማታውቀው ሽማግሌ (የአብርሃም መልክተኛ) ቤተሰቦቿን በጠየቀው መሠረት ወላጆቿ ጠርተው ‹‹ከዚህ ሰው ጋር ትሄጃለሽን?›› ብለው በጠየቋት ጊዜ ሳታንገራግር ‹‹እሔዳለሁ›› አለች፤ መሰስ ብላም ተከተለችው፡፡/ዘፍ 24፣58/ እመቤታችን ግን የከበረ መልአክ ተገለጾ ሲያነጋግራት እንኳ የልቡናዋ በር ለወሊድ አልተንኳኳም፡፡ ለልማዱ ሴት ልጅ ‹‹ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ›› ቢሏት ምንም ብትመንን መልአክ ተገልጾ ከነገራት ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል?›› ልትል አትችልም፤ እንዴት እንደሚሆንማ ጠንቅቃ ታውቃለችና፡፡ እመቤታችን ከነዚህ ሁሉ ልዩ ስለሆነች ‹‹እፎኑ ይከውነኒ ዝንቱ›› ስትል ፈጽሞ በታተመና እርሱን በሚያልፍ ኅሊና መልአኩን አስጨነቀችው፡፡

 

እርሱም‹‹ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም›› የምትል ጥቅስ አግኝቶ ፈተናዉን ተገላገለ፡፡ ሌላዉ ቀርቶ በዚህ ጥቅስ ተረትታ ብሥራቱን ስትቀበልም ‹‹ይኩነኒ በከመ ትቤለኒ- እንዳልከው ይሁንልኝ›› ያለች አንት እንዳልከው የአምላኬ ፈቃዱ ሆኖ እንበለ ዘርዕ፣ እንበለ ሩካቤ ከሆነና ተጸንሶ የሚወለደውም እርሱ ከሆነ ይሁን ይደረግ አለች እንጂ ለሌላው ነገርማ ኅሊናዋ እንደታተመ ነው የቀረው፡፡‹‹ ልጄ ሆይ ስሚ፣ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ፤ ወገንሽን የአባትሽንም ቤት እርሽ፣ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፤ እርሱ ጌታሽ ነውና›› (መዝ 44÷12) ሲል አባቷ ዳዊት በትንቢት እንደተናገረው እርሷ ከሔዋናዊ ጠባይ ተለይታለችና፡፡ ሰሎሞንም‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ፤ ነውርም የለብሽም፤ ልቤን በፍቅር አሳበድሽው….›› ያለው ለዚህ  ነበር፡፡

 

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ ‹‹የታተመች ደብዳቤ›› ያላትም ለዚህ ነው/ኢሳ 28 ፤ 12/፡፡ ምክንያቱም ለልማዱ ደብዳቤ ከተጻፈ በኋላ ይታሸጋል፡፡ ስለ እርሷ የተነገረው ግን  ከታተመ ወይም ከታሸገ በኋላ ተጻፈበት የሚል ነው፡፡ አብ በድንግልና አትሞ ሲያበቃ በውስጧ አካላዊ ቃልን የጻፈባት ማንበብ የሚችሉም(እሥራኤል) ማንበብ የማይችሉም(አሕዛብ) እናነበው ዘንድ አንችልም ታትሟልና (በድንግልና በንጽሕና በክብር በምስጢር) አሉ ብሎ የተናገረላት ደብዳቤ እርሷ ናትና፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ጸጋ ለተሰጣቸው ሰዎች ብሥራት ሊያደርስ ሲመጣ ይህ የመጀመሪያው አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ለዳንኤልም ሆነ ለጻድቁ ካህን ለዘካርያስ ለእርሷ እንዳደረገው ለእነርሱ መች አደረገ? እነርሱ እጅ ነሱት ሰገዱለት እንጂ እርሱ መቼ እጅ ነሳ ሰገደላቸው? ከዚህ በላይ ልዩ መሆን በእውነት ወዴት ይገኛል፡፡

 

ፍጹም ልዩ መሆኗን ለማስረገጥ ያህል አንድ ነገር ብቻ ላክል፡፡ የጥንቶቹ የቤተክርስቲያን ሊቃዉንት ጌታ ለሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቋት ዘንድ  የሰጠው ሁለት ጊዜ ነው ይላሉ፡፡ አንደኛው ብዙ ጊዜ ሲጠቀስ የምንሰማው ለቅዱስ ጴጥሮስ የተሰጠው ነው፡፡ይህም ‹‹በጎቼን አሰማራ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ እና ግልገሎቼን አሰማራ››/ዮሐ 21፣15-17/የሚለው ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከዚህ ቀደም ብሎ በመስቀል ላይ የሰጠው ነው፤ በመስቀል ላይ ጌታ ለዮሐንስ ‹‹እነኋት እናትህ›› ሲል የሰጠው እርሷን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያንንም ነው ይላሉ፡፡

 

በእነዚህ ሊቃዉንት ትርጓሜ መሠርት  ሁለቱም ራሳቸውን የቻሉ ምስጢራትን ይዘዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ሕጋዊ ስለነበር(በጋብቻ የተወሰነ ማለት ነው) የተሰጠውም አደራ ይህንኑ የሚመለከትና በጎቹን እስከ ገላግልቶቻቸው(ምእመናን) የሚመለከት ነው፡፡ጌታ በወንጌል ‹‹በጎቼ ድምጼን ይለያሉ›› እንዳለው እነዚህ ድምጽ እንጂ ቃል መለየት የማይቻላቸው ምእመናን ናቸው፡፡  የቅዱስ ዮሐንስ ግን ከዚህ ሁሉ በእጅጉ ይለያል፡፡ምክንያቱም እመቤታችን ራሷ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ብቻ ሳትሆን የፍጹማን ደናግልም ምሳሌ ናት፡፡ ስለዚህ ከድምጽ ያለፈ ቃላትን ምስጢራትን መለየት የሚቻላቸው ፍጹማንን የሚመለከተው አደራ የተሰጠዉ ለበቃው ብቻ ሳይሆን ለፍጹሙ ድንግል ለዮሐንስ ነዉ፡፡ ስለዚህ እመቤታችንን መግፋት ቤተክርስቲያንን መግፋት ነው፡፡እርሷንም በቤቱ ማስተናግድ የሚቻለው ዮሐንስን የመሰለ ንጹሕ ድንግል ነው፡፡

 

ቅዱስ  ቅዱስ አትናቴዎስ እንደሚለው ጌታ የሰጠው ድንግሊቱን ለድንግል፣ ድንግሉንም ለድንግል፤ ንጹሕንም ለንጹሕ ነው፡፡ መላእክት ሲጠብቋት ከኖሩ በኋላ መልአክ ለመሰለ ሰው ሰጣት እንጂ ለሌላ አልተሰጠችም፤ ሊቀበላት የሚቻለውም የለም፡፡በተለይ ኦሪገን ይህንኑ በተረጎመበት አንቀጹ ስለ ቅዱሱ ብቃት ሲናገር  ለእርሷም ‹‹እነሆ ልጅሽ›› አላት እንጂ ‹‹ልጅ ይሁንሽ›› አላላትም፤ ምክንያቱም ዮሐንስ በዚያ የመከራና የጭንቀት የፍርሃት ቀን በዕለተ ስቅለት ሳይፈራ ሳይሰቀቅ በእግረ መስቀሉ የተገኘው ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹እኔም አሁን ሕያዉ ሆኜ አልኖርም፤ ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል›› /ገላ 2፣20/ እንዳለዉ ዮሐንስ ራሱን ክዶ ስለነበር ለራሱ እየኖረ አይደለምና በእርሱ የሚኖረው ጌታ ነው፡፡ ‹‹አነሆ ልጅሽ›› ያላትም በእርሱ አድሬ ያለሁት እኔ ነኝ ማለቱ ስለሆነ ከእርሷ ሰው ከሆነ በኋላ ለማንም አልሰጣትም፤ በዮሐንስ አድሮ የተቀበላትም ራሱ ነው፤ ከዚያ በኋላ እርሷን ሊቀበል የሚቻለው የለምና ይላል፡፡ ስለዚህ አንድ ሰው እንኳንስ የእርሷን ነገር ለመንቀፍ ቀርቶ ለማመስገንም ትሰጠው ዘንድ ከፈለገ እንደ ዮሐንስ ራሱን በንጽሕና ይጠብቅ ፣ራሱንም ፈጽሞ ይካድ ባይ ነው፡፡

 

የአሁኖቹ ሰዎች እርሷን ባይቀበሉ፣ በእርሷ አማላጅነት ባያምኑ ለምን እንደነቃለን? እነዚህ በትንሽ ነገር እንኳን መታመን የማይቻላቸው የእርሷን ነገር ይረዱ ዘንድ ታላቁንና ሰማያዊውን ምስጢር ማን አደራ ሊሰጣቸው ይችላል? አንዳንድ የዋኃን ደግሞ መሠርይ ተሐድሶዎች ስለ እርሷ የዘመሯቸውን መዝሙር ተብየ ዘፈኖች እየተመለከቱ ይታለላሉ፡፡ ይህ መናፍቃኑ ስለ እርሷ የሚሉትን መንገድ የተከተለ በእነርሱ ወዝ የታሸ ስለሆነ ተወዳጅ መሥዋዕት አይደለም፡፡ በኦሪት አንበሳው፣ ተኩላው፣ ቀበሮው፣ … የመሳሰለው  አውሬ የገደለውን ሁሉ እንኳን ለመሥዋዕት ልናቀርበው ቀርቶ ልንበላውም የተከለከለ ነው፡፡ ይህም ማለት በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱት አውሬዎች የተባሉት (አጋንንት፣ ርኩሳን መናፍስት፣ መናፍቃን፣…. ደሙን ያፈሰሱትን ወይም በእነርሱ) የተሰዋውን ሁሉ እንኳን ለእግዚኣብሔር ማቅረብ ለእኛም መንካት መርከስ ነው ማለት ነው፡፡ ‹አውሬ የቧጨረውንም አትንካ› የሚል ንባብም ይገኛል፤ ይህ ሁሉ ከእነርሱ የተነካካውን በዚህ ዓለም የዘፈንና የረከሰ መንፈስ የጎሰቆለውን ምንም ለዐይንህ ቢያምርህ (በዘፈን ላደገ ሁሉ የእነርሱ የሚያምረው መሆኑ አይጠረጠርም) ፈጽመህ አትንካ ተብለን ታዘናልና መልከስከስ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ግጥሙ በኑፋቄ ዜማው በዘፈን ርኩሰት የተቧጨረ ርኩስ ነውና፡፡እርሷ ቤተ ክርስቲያን ናት፤ የቤተክርስቲያናችንም ስጦታ ስለሆነች በእውነት ልዩ ናትና ይህን በመሰለ መልኩ የተቧጨረውን አናቀርብም፡፡

 

እንግዲህ ዛሬ ተወለደች የምንለው ይህችን ልዩ ድንግል ነው፡፡ስለዚህም የእርሷን በዓለ ልደት ማክበር ከዚህ ሁሉ በረከት መሳተፍ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር በእርሷ በኩል ለባሕርያችን ያደረገውንም ክብር ማወቅና መቀበል ጭምር ነው፡፡

 

ከበዓሉ ምን እናገኛለን? የእርሷስ በዓል አልበዛምን?

አንዳንድ ሰዎች በእኛ ቤተክርስቲያን የጌታ በዓል አንሶ የእመቤታችን የበለጠ፤ እኛም ከርሱ ይልቅ ለርሷ የምናደላ የሚመስላቸው ቁጥራቸው በርከት ማለት ጀምሯል፡፡ ያለማወቅ ነውና አይፈረድባቸውም፡፡ ለነቀፋም የተሰለፉ ስለሆነ በ‹ምሰለ ፍቁር ወልዳ-ከተወደደው ልጇ ጋራ› በምንለው ሥዕል ውስጥ እንኳን በሥዕሉ መጠን እየመሰላቸው ጌታ ያነሰ የሚመስላቸው ማስተዋል የራቃቸው ስለሆኑ በእነርሱ አንገረምም፡፡በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ድረስ ከእናቱ ጋር መሰደዱን፣ ከኅዳር ፲፬ ጀምሮ እስከ ልደቱ ይወርዳል ይወለዳል ሲሉ ትንቢት የተናገሩ የነቢያትን ጾም እየጾምን እርሱን እናስባለን፡፡ ከልደት እስከ ዐቢይ ጾም ድረስም በሥጋዌ፤ በአንድነት በሦስትነት መገለጡ አስተርእዮ እየተባለ ይታሰባል ይሰበካል፡፡ ከዚያም ዐቢይ ጾም ይገባል፤ ሁለንተናችን እርሱን በማሰብ ይሰበሰባል፤ ቃለ እግዚአበሔሩም ይህንኑ ያዘክራል፡፡ በትንሣኤውም ሃምሳ ቀናትን እንደ አንድ ቀን እንደ ዕለተ ትንሣኤው በመቁጠር ትንሣኤውን እንሰብካለን፡፡ ከዚህ በማስከተልም ርዕደተ መንፈስ ቅዱስን በዓለ ጰራቅሊጦስን በጾም እናከብራለን፡፡በየወሩም በዓለ እግዚእ፣ መድኃኔዓለም፣ ኢየሱስ፣ አማኑኤል…. እያልን ከዘጠኙ ዓበይትና ከዘጠኙ ንዑሳን በዓላት በተጨማሪ በየአጥቢያቸው የሚታሰቡት ትዝ አይሏቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በየሳምንቱ ሁለት ቀናትን (ረቡዕ እና አርብ) በጾም ሁለት ቀናትን (ቀዳሚትንና እሑድን) በበዓል ለክርስቶስ መታሰቢያ የሰጠች ብቸኛ ቤተ ክርስቲያን የእኛይቱ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ብቻ መሆኗን አያስተውሉም፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሳለ የማርያም በዓል ከጌታ በዓል ይበልጣል ማለትን ምን ዓይነት አለማስተዋል ልንለው እንችላለን? ቢሆንስ በቅዱሳን በዓል ዋናው ተከባሪ ተመሰጋኝ ማን ሆነና ነው ይሄ ሁሉ ጩኸት? ስለዚህ በዚህም ስም አደረግነው በዚያ እግዚአብሔር በአከበራቸው ቅዱሳን ስም እስካደረግነው ድረስ በዓሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ነው፡፡

 

የእመቤታችን በዓለ ልደትም በዚሁ መንፈስ የሚከበር በዓል ነው፡፡ነቢዩ ኢሳይያስ ቀደም ብሎ ‹‹ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይ-ከእሴይ ሥር ወይም ግንድ በትር ትወጣለች››/ኢሳ 11፤6/ ብሎ ስለ ልደቷም ተናግሮላታል፡፡ ይህንንም ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘቀዳሚት ድርሰቱ፤ ‹‹ በትረ ሃይማኖት ዘኢትጸንን ምስማኮሙ ለቅዱሳን-የቅዱሳን መደገፊያቸው ግያዝ የሱነማዊቷን ልጅ ከሞት ያስነሣባት ዘንድ ከነቢዩ ከኤልሳ ተቀብሎ እየተጠራጠረ እንደወሰዳት ያይደለሽ ጽነት ጥርጣሬ የሌለብሽ የሃይማኖት በትር አንቺ ነሽ›› ብሎ ተርጎሞልናል፡፡ አባ ጀሮምም ይህን የነቢዩን ትንቢት በትር ከግንዱ ላይ ተስተካክሎ የሚወጣ ግዳጂ ለመፈጸም የሚፈልግ ስለሆነ የእመቤታችን ልዩ መሆን ያሳያል ይላል፡፡

 

በርግጥም ሊቃውንቱ እንዳሉት ለቅዱሳን መደገፊያ ለአጋንንት ለመናፍቃን ደግሞ ማባረሪያ የሆነች በትር፤ ድንግል ማርያም፡፡ስለዚህ የእርሷን በዓል ማክበር ከዚህ ጥርጣሬ ከሌለው በረከት መሳተፍ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ የበዓላት ይልቁንም በክርስትና ጥቅማቸው ምንድን ነው የሚለውን እንመልከትና እንፈጽም፡፡

 

በዓላትን በብዛት እንድናከብር ያዘዘን እግዚአብሔር ነው፡፡የምናከብራቸውም ዝም ብለን አይደለም፡፡በተለይም በብሉይ ኪዳን በዓላት ብዙ የመሥዋዕት እንስሳትን ማቅረብና መሠዋት በጥብቅ የሚፈጸም ትእዛዝ ነበረ፡፡ የዚያ ሁሉ መሥዋዕትም ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማስገኘት ነበር፡፡/ዘሌ ፲፯፣፲፩/ በአጭሩ በዓላቱን የማክበሩ ዓላማ ሥርየተ ኃጢኣትን ማሰገኘት ነው ማለት ነው፡፡በዚህ መሠረታዊ ምክንያት በእያንዳንዱ የኦሪት በዓል እጅግ ብዙ የመሥዋዕት እንስሳት ይቀርቡ ነበር፡፡በኦሪት በየዕለቱ ሁለት ሁለት ጠቦቶች፣ በየሰንበቱ ሁለት ተጨማሪ የበግ ጠቦቶች፣በየመባቻው ደግሞ ለየዕለቱ ከሚቀርበው በተጨማሪ ሁለት ወይፈኖች፣ አንድ አውራ በግ፣ ሰባት የአንድ ዓመት የበግ ጠቦቶች፣ አንድ ፍየል ይቀርብ ነበር፡፡ የዓመታዊ በዓላት ደግሞ ከዚህ ሁሉ ይለያል፡፡ለምሳሌ የዳስ በዓሉን ብቻ ብንመለከት ከዕለቱ፣ ከሰንበቱና ከመባቻው እንዲሁም በፈቃድ ከሚቀርቡት በተጨማሪ 73 ወይፈኖች፣ 136 አውራ በጎችና ጠቦቶች፣ 10 አውራ ፍየሎች ይቀርቡ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ግን የእህሉን ቁርባንና ሌላውን መሥዋዕት(ለኃጢኣት ፣ ለበደል፣….የሚባሉትን) ሳይጨምር ነዉ/ዘጸ ፳፱፣፴፰፣ ዘሌ ፳፬፣፭-፱፣ ዘኁ ፳፰፣፱-፲፭፣ዘኁ ፳፱/፡፡

 

‹‹ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና››/ዕብ 10፣1 / ተብሎ እንደተጻፈ እነዚህ ሁሉ ግን ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ከጊዜው የተነሳ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፥ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም።ወተት የሚጋት ሁሉ ሕፃን ስለ ሆነ የጽድቅን ቃል አያውቅምና፤ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በስራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።›› /ዕብ 5፣ 12-15/ እንዳለው ሊቃውንቱ ለእኛ ወተት ወተቱን እየመገቡ ጠንካራውን ምግብ አላቀረቡልንም ነበር፡፡ አሁን ግን እስኪ ይህን እንኳ እንሞክረው፡፡

 

በኦሪት እንደተጻፈው በፋሲካ የሚሠዋው ልዩ የድኅነት መሥዋዕት በግ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡‹‹በነገው ደግሞ ዮሐንስ ከደቀ መዛሙርቱም ሁለት ቆመው ነበር፥ኢየሱስም ሲሄድ ተመልክቶ። እነሆ የእግዚአብሔር በግ አለ›› /ዮሐ 1፣ 26/።ተብሎ ተጽፎአልና፡፡በሌሎቹ በዓላት የምናቀርባቸው ደግሞ ቀደም ብለን እንዳየነው ወይፈኑ፣ አውራ በጉ፣ ፍየሎቹ(ወንድም ሴትም ነው የሚቀርበው)፣ ሌላው ሁሉ የማን ምሳሌ ነው ማለታችን አይቀርም፡፡ ይህ ሁሉ የበዓል መሥዋዕት የቅዱሳን ምሳሌ ነው፡፡ ‹‹እንደ በጎች ሊበሉን ሰጠኸን፥ ወደ አሕዛብም በተንኸን›› /መዝ 44፣12/ ተብሎ ትንቢትም ተነግሮላቸዋልና።ጌታም በወንጌል ‹‹ስለዚህ፥ እነሆ፥ ነቢያትንና ጥበበኞችን ጻፎችንም ወደ እናንተ እልካለሁ፤ ከእነርሱም ትገድላላችሁ ትሰቅሉማላችሁ፥ ከእነርሱም በምኵራባችሁ ትገርፋላችሁ ከከተማም ወደ ከተማ ታሳድዳላችሁ፤ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ።እውነት እላችኋለሁ፥ ይህ ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳል›› /ማቴ 23፣35/ ሲል እንደተናገረው ቅዱሳን ለእምነታቸው መሥዋዕት ሆነው ቀርበዋል።ደማቸውንም አንዱ እንደ ፍየል፣ ሌላው እንደ ወይፈን፣ ሌላውም እንደ አውራ በግ አፍስሰዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ የመሥዋዕት ዓይነቶች ለተለያየ የኃጢኣት ማስተሥረያ እነደነበሩት እነዚህም ድኅነትን ለመፈጸም ከተሰዋው በግ ከጌታ በኋላ ለምናምን ሁሉ ሥርየተ ኃጢኣትን እናገኝ ዘንድ የሚማልዱ ስለኛም ጭምር ደማቸውን ያፈሰሱ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ የሌላው ጊዜ የመሥዋዕት እንስሳ የፋሲካቀውን በግ ሊተካው እንደማይችልና የመሥዋዕቱም ዓይነት ፈጽሞ የተለያየ እንደ ሆነው ሁሉ የቅዱሳኑ መሥዋዕትነትና ሰማዕትነትም እንዲሁ የተለያየ መሆኑና የእነርሱም የጌታችንንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሊተካ የማይችል መሆኑ ሊዘነጋ አይገባውም፡፡እርሱ ኃጢኣትህ ተሠረየልህ(ሽ) እያለ ይቅር ሲል እነርሱ ግን የሚያስተሠርዩልን እየጸለዩ ነውና፡፡ ከዚህ በመለስ ግን የጥንቶቹ ሊቃውንት እንደተረጎሙልን የእነርሱ ተጋድሎና ሰማዕትነት የእኛ የሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች መሥዋዕቶች ናቸው፤ ስለእነርሱም ሥርየተ ኃጢኣትን እንቀበላለን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል  ››/ዕብ 4፣6/ ሲል የተናገረዉው ይህን የሚያረጋግጥልን ነው፡፡

 

ቀደም ብለን እንዳየነው የመሥዋዕቱ እንስሳት የበዙት ለእሥራኤል ለኃጢኣታቸው አስፈላጊ በመሆኑ እንደሆነው ሁሉ በሐዲስ ኪዳን ለምንኖር ለእኛም ብዙ ቅዱሳን መኖራቸው ይጠቅመናል፣ ኃጢኣታቸንም ያስተሠረይልናል፡፡ የመሥዋእቱ እንስሳት በሙሉ የተቆጠሩና የታወቁ እንደሆነው ሁሉ ቅዱሳኑም ምን ቢበዙም እንዲሁ የታወቁና የተቆጠሩ ናቸው፡፡

 

ዳዊት አባታችን ‹‹ዘይኌልቆሙ ለክዋክብት በምልኦሙ፣ ወይጼዉዖሙ ለኩሎሙ በበአስማቲሆሙ- ክዋክብትን በምልዓት ይቆጥራቸዋል፣ ሁሉንም በየስማቸዉም ይጠራቸዋል››/መዝ 146፣4/ ሲል እንደተናገረዉ ክዋክብት የተባሉ ቅዱሳን ሁሉ በእርሱ ዘንድ በባለሟልነት በቃል ኪዳን የታወቁ በመሥዋዕትነትም የተቆጠሩ ናቸዉ፡፡ ያ ሁሉ የ መሥዋዕት እንስሳ ፣ የጧቱና የሰርኩ፣ የሰንበቱና የመባቻዉ፣ የዓመት በዓላቱ፣ የየግለሰቡ የኃጢኣቱ፣ የበደሉ፣ የመንጻቱ፣…በዓይነት በዓይነት እንደሚታወቅ በእርሱም ዘንድ ተቀባይነት እንዳለዉ ሁሉ የየዕለቱ ቅዱሳንም እንዲሁ ይተወቃሉ፤ ጸሎታቸዉና ምልጃቸዉም በእርሱ ዘንድ የከበረ ነዉ፡፡ እመቤታችን ደግሞ ከነዚህ ሁሉ በግንባር ቀደምነት የምትጠራ ልዩ መሥዋዕታችን ናት፡፡በሁለተኛዉ ክፍለዘመን መጨረሻ የነበረዉ የሰረዴሱ መልይጦን/Melito of Sardis/  በፋሲካ መዝሙሩ ላይ እመቤታችንን የመሥዋዕቱን በግ የወለደችልን ንጽሕት ሴት በግ (fair ewe) ይላታል፡፡ ስለዚህ የእመቤታችን በዓለ ልደት ከብሉይ ኪዳን ሰዎች የተሻለ ሥርየተ ኃጢኣት የምናገኝበት ነዉና ከነዚያ በተሻለ በዓላችንን መንፈሳዊ አድርገን እናክብር፤ ከመንፈሳዊ በረከትም እንካፈል፡፡የደራሲዉንም ምስጋናና ምልጃ በመሰለ ምስጋና እንዲህ እንበላት፤‹‹ምንተኑ አዐስየኪ ዕሴተ፤በእንተ ኩሉ ዘገበርኪ ሊተ፤ማርያም ሠናይት ዘታፈቅሪ ምሕረተ፤ሶበሰ ተታአቀቢ ዘዚኣየ ኃጢኣተ፤ እምኢሐየዉኩ አሐተ ሰዓተ›› እያልን ለእርሷ በሚገባ ምስጋና እናመስግናት፡፡ ከዚህ የወጣ ሰዉ በመጀመሪያ እንደተመለከትነዉ ብርሂት ቀኝ ዐይኑን እንደገና እያሳወረ መሆኑን ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ እኛስ ለባሕርያችንን መመኪያ እርሷን የሰጠንን እግዚአብሔርን ‹‹ብርሂት የቀኝ ዐይን ድንግል ማርያምን ›› በዚህ ዕለት የሰጠኸን፣ ከዚህ ዓለም የድንቁርናና የኃጢኣት ጨለማም የገላገልከን ክብር ምስጋና ለአንተ ይሁን፤ አንተ ለመረጥካትና ላከበርካት ለእናትህም ምስጋና ይድረሳት እያልን አፋችንን ሞልተን እናመሰግናለን፡፡ ቀይ ዕንቁ እምነት ገንዘባቸዉ ያልተሰረቀባቸዉ ወይም በአዉሬዉ ዲያብሎስ ያልተቧጨሩት ሁሉ አብረዉን ያመሰግናሉ፡፡ ቀኝ ዐይናችን ሆይ ዛሬም በአንቺ ብርሃን እናያለንና እናመሰግንሻለን፡፡ እንኳን አንቺን አባትሺን አብርሃምን የሚባርኩት እንደሚባረኩ ልጂሽ አስቀድሞ በሙሴ በኩል በኦሪት ነግሮናልና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡