በሕይወት ያለ ማስታወሻ ለገና ሥጦታ

የዘመነ ማቴዎስ 4ኛ ወር የመጨረሻውን ቀን በሚመስጥ የሕይወት ትምህርት በመማር አሳለፍኩት፡፡ ጠዋት ከጓደኛዬ ጋር ቁርስ አድርገን እርሱ ሊወስደኝ ካሰበው ሥጦታ መስጫ ቦታ ሄድን፡፡ይህ የስጦታ መለዋወጫ ቦታ ለእነርሱ ልማድ ነው፡፡ በዓል በመጣ ቁጥር የሚሄድበት የውዴታ ግዴታ የሆነበት ልማድ በእርግጥ ሲጀምረው ጥልቅ ደስታና እርካታ የተሞላ ነበር።

እኔ ከጉዟችን መልስ በድርጊቱ ተደምሜያለሁ፣ እርሱ በዓመት ሦስቴ ለበዓላት በመሄድ ገንዘብ ያደረገው ልማድ!! ይህ የልደት በዓል በጠዋቱ መልካም የሕይወት ተሞክሮ እያስተማረኝ እንደሆነ መረዳቴ የዘመኑን መልካም ጅማሮ እንድወደው አስገደደኝ ገና ሦስት ሩብ ዓመታት ይቀራሉና!!

‹ታምሜ ጠይቃችሁኛል?…… ተርቤ አብልታችሁኛል?› የሚሉት የክርስቶስ የወንጌል ቃላት ለእርሱ የሕይወት ልምምድ መሠረቶች ነበሩ፡፡ እንዴት ልፈጽመው ከሚል በጎ መሻት የመነጨ ልምድ፣ እናም ወሮታ የማይከፈልበት ብድር ከማይመለስበት፣ ይሉኝታ ከሌለበት፣ ከሥጋዊ የራስ ጥቅም አድልዎ የነጻ ዕረፍት፣ ጥልቅ ደስታና የሕይወት እርካታ ያገኝ ዘንድ በበዓላት በሆስፒታል የተኙ ህመምተኞችን ቤት ያፈራውን በመያዝ ‹እንኳን አደረሳችሁ…..እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤ እግዚአብሔር ይማራችሁ! በማለት ይጠይቃቸዋል፡፡ ከቤተሐኪም ገብቶ የሚጠይቃቸው፣ የሚያጫውታቸውና የሚያጐርሳቸው በአጠገባቸው አስታማሚ(ጠያቂ) የሌላቸውን ብቸኛ ህመምተኞች ናቸው፡፡ ይደርስላቸዋል፣ ከጐናቸው!!

አዎ! ማንም ህመምተኛ ድኖ ሲነሣ ውለታ ለመክፈል አይጨነቅም በውለታ አልታሰረምና፡፡ አያውቃቸውም አያውቁትም ቀድሞ እንዲሁ ነበር ዛሬም እንደዛው ወደፊትም እንዲያው ሊሆን ይችላል፡፡ እናም የማያውቁትን በመጠየቃቸው ብድር የማይመልሱትን እርሱም ለነገ ብድራት የማያስቀምጠውን ግን ህመምተኛ ጠያቂን ፈላጊ የሆነን ሰው እንደው ደርሶ ‹እንኳን አደረሰህ› ብሎ የፈጣሪን ምሕረት ለምኖ መጽናናትን መፍጠር እርግጥ ምን ያህል ዋጋ ያለው ደስታ ይኖረው ይሆን… ወዘተርፈ፡፡

የዓውደ ዓመት በዓል ይሄን ያህል ደስታ ይፈጥር ይሆንን? እርግጥ በቤተሰብ መሀል ለሚኖር ሰው ደስታው፣ ጨዋታው፣ ሁካታው፣ መጠያየቁ፣ መልካም ምኞቱ ደስታ ሊፈጥሩ ይተጋገዙለት ይሆናል ይሄን ቢጨምርበት ግን ደስታው ሊያገኘው ከሚታገለው እጥፍ ሲበዛለት ሲበረክትለት ወደ እርካታ ሲመራው በሕይወቱ ሊማር እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ምናልባትም የምንጠይቀው አንዱ ህመምተኛ የሕይወትን ቃል ሊያሰማን ምክንያት ቢሆንስ? ኑ እንውረድ በዓርአያችን እንደምሳሌያችን ሰውን እንፍጠር ያለው ለዚህ ይሆን እንዴ?!
ይህ ነው የገና ሥጦታ የተሰጠኝ፣ የሕይወት ትምህርታዊ ገጸ በረከት! ማስተዋሉን ላደለው መልካም ትምህርት ነበር ግሩም!!

/ በዕለት ውሎ መመዝገቢዬ ለጽሑፍ በሚሆን መልክ የተቀዳ
በኤርምያስ ትዕዛዝ  ዘሐብታም
መስከረም 1 2001 ዓ.ም /

ይህን ያውቁ ኖሯል?

የመነኮሳት ሕይወት

ምንም እንኳን የድንግልናና የምናኔ ኑሮ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም የምንኩስና መሥራችና አባት ቅዱስ እንጦንስ ነው፡፡ አባ እንጦንስ ግብፅ ውስጥ በምትገኝ ቆማ በምትባል ቦታ በ251 ዓ.ም ተወለደ፡፡ ወላጆቹ ሀብታሞችና ደጋግ ሰዎች ነበሩ፡፡ ከወላጆቹ ዕረፍት በኋላ የነበረውን ሀብት ለድሆች መጽውቶ መንኩሶ ብዙ ዓመት በብሕትውና ኖረ፡፡

በዚያን ጊዜ ብዙ ታምራትን ስለሠራ ሕዝቡ ግማሹ እሱን አይቶ ለማድነቅ የቀረው ደግሞ በእርሱ ጸሎት ለመፈወስ ወደነበረበት ቦታ ይጐርፍ ነበር፡፡ እርሱም በ356 ዓ.ም ዐረፈ፡፡

አባ ጳኩሚስ የተባለ ሌላው አባት በላይኛው ግብፅ ውስጥ ብዙ ገዳማትን በመሥራት የምንኩስናን ሕግና ሥርዓት በመወሰን ስለምንኩስና መስፋፋት ብዙ ደክሟል /290-347 ዓ.ም/፡፡ አንድ ቀን ወደ ዱር እንጨት ፍለጋ ሔዶ ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጸለትና እንደ አባቶቻችን ሐዋርያት የአንድነትን ማኅበር ለመሥራት መነኮሳትን እንዲሰበስብ አዘዘው፡፡ ብዙ አማኞች እየናፈቁት ማግኘት ያልቻሉትን ገዳማዊ ሕይወት ያገኙ ዘንድ ገዳም ለመመሥረት የሚስችለውንና የሚያስተዳድርበትን በነሐስ ላይ የተቀረጸ ሕግ ሰጠው፡፡ አባ ጳኩሚስም ከመልአኩ በተሰጠው ሕግ መሠረት የሚተዳደር ገዳም አቋቋመ፡፡ ይኸውም መነኮሳቱ ጠዋትና ማታ አብረው እንዲፀልዩ በአንድነት እንዲሠሩ ገቢና ወጪያቸው አንድ ላይ እንዲሆን በአንድነት እንዲመገቡ፣ ልብሳቸው አንድ አይነት እንዲሆንና እነዚህን የመሳሰሉትን ደንቦች አወጣላቸው፡፡ በዚህ መሠረት መነኮሳቱ የዕለት ምግባቸውን የሚያገኙት እየሠሩ ነበር፡፡ ከሴቶችም የምንኩስናን ሕይወት የጀመረች የአባ ጳኩሚስ እህት ማርያም ናት፡፡

ከዚህ በኋላ በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ ምንኩስና በግሪክ፣ በሮም፣ በሶሪያና በሌሎችም ሀገሮችም እየተስፋፋ ሄደ፡፡

የምንኩስናን ሕይወት ወደ ኢትዮጵያ ያመጡ በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በጉባዔ ኬልቄዶን /በሃይማኖት ስደት/ ምክንያት ከቁስጥንጥንያ፣ ከግብፅ፣ ከሶርያ፣ ከሮም፣ ከአንጾኪያ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዘጠኙ ቅዱሳን መነኮሳት ናቸው፡፡ ምንኩስና ከተመሠረተ ጀምሮ በየጊዜው ሕዝቡ ታላላቆችም ሳይቀሩ ወደ ገዳማቱ እየሄዱ ይመነኩሱ ነበር፡፡

ነገር ግን ከ9ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ በማኅበር ከሚኖሩት መነኮሳት መካከል ጥቂቶቹ ቀስ በቀስ ለብቻ በተለየ ቤት መኖር እያንዳንዱ መነኩሴ ለብቻ በፈለገበት ጊዜ መብላትና መተኛት ስለጀመረ በየገዳማቱ የመነኮሳቱ ኑሮ በማኅበር የሚኖሩትና ለብቻቸው የሚኖሩት ለሁለት ተከፈሉ፡፡

የድንግልና መሠረቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ «ስለ መንግሥተ ሰማያት ሰውነታቸውን ጃንደረባ ያደረጉ አሉና፤ መፈጸም የሚችል ግን ይፈጽም» ሲል የተናገረው የሕግ ቃል ነው፡፡ ማቴ. 19፡12

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

/ምንጭ፦ ‘የዛሬዋ ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ’ በዲ/ን አሐዱ አስረስ፣ ነሐሴ 1992 ዓ.ም/