ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መድረስ እንደሚገባ ቅዱስ ፓትርያርኩ አሳሰቡ

የልደት ክርስቶስ በዓል የሰላምና የደስታ፣ የአንድነትና የፍቅር፣ የነፃነትና የእኩልነት በዓል ሊሆን እንደሚገባ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ታኅሣሥ 26 ቀን 2008 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ አስታወቁ፡፡

ማንም ይሁን ማን፣ በየትኛውም ደረጃ ወይም አካባቢ ይኑር፣ ከሰላም ወጭ ጥቅሙን ማረጋገጥ የሚችል የለም፤ ሊኖርም አይችልም፤ በሰላም ውስጥ ሆኖ ግን ሁሉንም ማግኘት እንደሚቻል ላለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት አየታየው ውጤት ምስክር ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችንም ሆነ አገራችን ከሰው ሠራሽና ከተፈጥሮ አደጋዋች በቀላሉ ማምለጥ የሚቻለው ከሁሉ በፊት ሰላምን በአስተማማኝ ሁኔታ ይዘው ሲጓዙ እንደሆነ ቅዱስ ፓትርያርኩ ገልፀዋል፡፡
ቅዱስነታቸው አያይዘውም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ተመልሶ ሰውን ከሞት ያዳነው ማንንም ሳይጎዳ በሰላም ጎዳና ብቻ ተጉዞ ነው፡፡ ጥላቻና ራስ ወዳድነት ሲያፈርሱ ሲያጠፉ እንጅ ሲያለሙ እና ሲገነቡ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ታይተውም፤ ተስምተውም፣ በታሪክ ሲደገፍም አይተን አናውቀም ብለዋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በልማትና በዕድገት እየገሠገሰች ያለች፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነገ ብሩህ ተስፋ ትሆናለች ተብላ ተስፋ የተጣለባት ሀገር ነች፡፡ ይህ ተስፋ እግዚአብሔር ባርኮልን በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቋንቋ፣ በቀለም ሳንለያይ መላ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነን ያስገኘነው የልማት ፍሬ ነው በማለት ገልፀዋል፡፡ የተገኘው የልማት ፍሬ እየበረከተና እየደለበ ወደፊት እንዲቀጥልና እንዲያድግ እንጂ በማናቸውም ምክንያት ወደ ኋላ እንዲመለስና ህዝባችን መፍቀድ እንደሌለበት አያይዘው አስገንዝበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መላው ህዝባችን በሚገባ ማጤን ያለበት ነገር ቢኖር ምንጊዜም የችግር መፍትሔ ሰላምና ልማት እንጅ ሌላ አማራጭ መፍትሔ የሌለ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ሁሉም የአገራችን ህዝቦች የገናን የሰላም መዝሙር እየዘመሩ ለጋራ ዕድገትና ለእኩልነት፤ ለህዝቦች አንድነትና ለዘላቂ ልማት በፅናት መቆም እንደሚገባ ገለጡ፡፡
በመጨረሻም በዚህ ዓመት በሀገራችን በተከሠተው የዝናም እጥረት ምክንያት ለምግብ እጦት የተጋለጡ በርካታ ወገኖቻችን የወገንን እጅ በተስፋ እየጠበቁ ይገኛሉ፤ እነዚህ ወገኖች ግማሽ አካላችን መሆናቸውን ተገንዝበንና ጌታችን እኛን ለመፈለግ ወዳለበት የመጣበትን ፍቅር አብነት አድርገን፤ እኛም ወዳለበት በፍቅር በመሔድ በሁሉም ነገር ልንረዳቸውና አለን ከጎናችሁ ልንላቸው ይገባናል፡፡ አነሰ ሳንል በወቅቱ ፈጥነን እጃችንን ልንዘርጋላቸውና በአጠገባቸው ሆነን ልናበረታታቸው ይገባል፤ እግዚአብሔር ሁላችንን እንደወደደን እኛም ወንድሞቻችንን በመመገብ፤ በማልበስና ችግራቸውን ሁሉ በመጋራት ለእግዚአብሔርና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ዛሬውኑ በተግባር እንድናሳይ በማለት አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የመስቀል ኃይልና ቅርጾች በሚል ርዕስ የነገረ ቤተክርስቲያን የጥናት ጉባኤ ሊካሔድ ነው

ጥናታዊ ጽሑፉ የፊታችን ቅዳሜ ታህሳስ 16 ቀን 2008 ዓ.ም አዲስ አበባ አምስት ኪሎ ቅድስተ ማርያም አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ 3ኛ ፎቅ ላይ በሚገኘው አዳራሽ ይካሔዳል፡፡

“የመስቀሉ ኃይልና ቅርጾች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የነገረ ቤተ ክርስቲያን የጥናት ጉባኤ ላይም ቁጥራቸው ከ350-400 የሚደርሱ ተሳታፊዎች ይገኙበታል ተብሎ ሲጠበቅ፤ በጉባኤው ላይም ከብፁዓን አባቶች፣ ከቤተ ክህነት የመመሪያ ሓላፊዎች፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሑራን እና ከሌሎች ማኅበራት የተወጣጡ በርካታ ባለድርሻ አካላት ይገኛሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡

በጉባኤው ላይ በሚቀርበው ጥናታዊ ጽሑፍም የመስቀል ኃይልና ቅርጾችን በተመለከተ ግንዛቤ ከመፍጠርም በተጨማሪ አጠቃላይ ስለ መስቀል ገናናነት በማስረዳት ትውልዱ ለመስቀሉ የሚገባውን ክብር እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው በዕለቱ የሚቀርበው ጥናታዊ ጽሑፍ ርዕስን አስመልክቶ ውይይት የሚደረግ ሲሆን በጉባኤው ላይ ሁሉም ምዕመናን መሳተፍ የሚችሉ መሆኑ ታውቋል፡፡

ጉባኤው ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 11፡30 ይቆያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የኢቢኤስ የቴሌቪዥን ሥርጭርቱ ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ገለጸ

ኅዳር 17 ቀን 2008 ዓ.ም

ዝግጅቱን በኦን ላይን፣ በስልክ እና በአሜሪካ የማኅበረሰብ ቴሌቪዥኖች ማሠራጨቱን ይቀጥላል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ አገልግሎት /EBS/ አማካይነት የሚያቀርበው ሳምንታዊ የአንድ ሰዓት መንፈሳዊ የቴሌቪዥን አገልግሎት ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን የማኅበሩ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የተቋረጠበትም ምክንያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በተጠቀሰው ማሠራጫ ጣቢያ አማካይነት በቤተ ክርስቲያኗ ስም ትምህርት የሚያስተላልፉትን አካላት ማንነትና ዓላማ አጣርቶ መመሪያና ፈቃድ እስከሚሰጥ በቤተ ክርስቲያኗ ስም የሚሠራጩ መርሐ ግብራት እንዲቆሙ በደብዳቤ በጠየቀው መሠረት ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኗ ዕውቅና በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ታቅፎ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ ያለ በመሆኑ የተጻፈው ደብዳቤ ይመለከተዋል ብሎ ባያምንም፤ አባቶች በጣቢያው አማካይነት የሚተላለፉትን መርሐ ግብራት ይዘትና ዓላማ በአግባቡ አጣርተው መመሪያና ፈቃድ እስከሚሰጡ ሥርጭቱን ማቆሙን መርጧል፡፡

በአስቸኳይ አገልግሎቱን ለመጀመር በሚችልበት ሁኔታም ከቤተ ክርስቲያኗ የበላይ አካላት ጋር እየተወያየ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡ በሀገር ውስጥና በተለይ በአረብ ሀገራት መርሐ ግብሩን በቀጥታ በኢቢኤስ ማሠራጫ ጣቢያ ሲከታተሉ የነበሩ ምእምናን በትእግስት እንዲጠብቁ ጠይቆ፤ የቴሌቪዥን ሥርጭቱ እስከሚጀምር ድረስ http://onlinetv.eotc.tv/ በስልክ አሜሪካ ለሚገኙ ምእመናን በ605-475-81-72፣ ካናዳ (604)-670-96-98፣ አውሮፓ (ጀርመን 0699-432-98-11፣ እንግሊዝ(ዩኬ) 033-0332-63-60 መከታተል እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

እኛም ሁኔታውን እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሊጀምር ነው

ጥቅምት 23 ቀን 2008 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ከኅዳር 12 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እንደሚጀምር የኅትመትና ኤልክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ም/ክትል ሓላፊ አቶ አክሊሉ ለገሠ ገለጹ፡፡

በNilesat, OBS /Oromiya broadcast Service/ ለሠላሳ ደቂቃ ዘወትር እሑድ ከረፋዱ 4፡30-5፡00 ሰዓት እንዲሁም በድጋሚ ረቡዕ ከጠዋቱ 12፡30-1፡00 ሰዓት የሚሠራጨው መርሐ ግብር የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊትን ጠብቆ የሚዘጋጅ ሲሆን፣ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ስለ እምነታቸው እንዲያውቁ እና ጸንተው እንዲኖሩ፣ እንዲሁም ከእምነታቸው ለወጡ ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ታስቦ መጀመሩን ምክትል ሓላፊው አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሞ ማኅበረሰብን ከቤተ ክርስቲያን ለመነጠል በርካታ መጻሕፍት ታትመው እየወጡ በመሆናቸው የማኅበረ ቅዱሳን የአፋን አሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት ክፍል ይህንን ለመከላከል ምእመናን ለማስተማር፣ እምነታቸውን ጠብቀው ጸንተው እንዲኖሩ ለማድረግ ፕሮጀክቱ መቀረጹንም ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምኛ ቋንቋ ምእመናንን የሚያንጹ በርካታ በትምህርተ ሃይማኖት፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን፣ የጸሎት መጻሕፍትንና መጽሔት በማሳተም፣ በኦሮምኛ ድረ ገጽ ጭምር ሲያሠራጭ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በቅርቡም Dangaa Lubbuu/ የነፍስ ምግብ/ የተሰኘ መጽሔት በማሳተም ለምእመናን በማዳረስ ላይ ይገኛል፡፡

በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚተላለፉ መርሐ ግብሮችን በካናዳ ለማዳረስ በስልክ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ጥቅምት 17 ቀን 2008 ዓ.ም

ማኅበረ ቅዱሳን በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚሰጠውን አገልግሎት በማስፋፋት የሚያስተላልፋቸውን ዝግጅቶች በስልክ አማካይነት በካናዳ ለሚገኙ ምእመናን ማሠራጨት ጀመረ፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማስፋፋት የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ምእመናን ስለእምነታቸውና ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲያውቁ፣ በሃይማኖት እንዲጸኑ መረጃ በመስጠትና በማስተማር ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚያሰራጫቸውን መርሐ ግብሮች በሰሜን አሜሪካ፣ በጀርመን እና በእንግሊዝ /UK/ በስልክ አማካይነት በማዳረስ ላይ ነው፡፡

ማኅበሩ በሰሜን አሜሪካ እና በአውሮፓ ብቻ ሳይወሰን ቁጥሩን ወደ ዐራት በማሳደግ በቴሌቪዥንና በሬድዮ የሚተላለፉት ዝግጅቶችን በቅርቡ በስልክ አማካይነት በካናዳ ማሠራጨቱን ቀጥሏል፡፡

በካናዳ የሚገኙ ምእመናን የስልክ አገልግሎቱን (604) 670 9698 በመደወል በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉም መረጃው ያመለክታል፡፡

የጥቅምት 2008 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጸሎት ተጀመረ

ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም

sami.02.07በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጥቅምት 11 ቀን 2008 ዓ.ም ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎት ተጀመረ፡፡

ምልዓተ ጉባኤው አስፈላጊና ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥንና የሬድዮ ሥርጭት በአውሮፓ በስልከ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም

01awropaማኅበረ ቅዱሳን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን እንዲሁም በሬድዮ አያሰራጨ የሚገኘውን መንፈሳዊ መርሐ ግብር በአውሮፓም ምእመናን ባሉበት ሆነው በቀላሉ በስልክ ሥርጭቱን መከታተል እንዲችሉ ማድረጉን የአውሮፓ ማእከል አስታወቀ፡፡

በዚህም መሠረት በጀርመን የሚገኙ ምእመናን በ0699-432-98-11 ፣በእንግሊዝ /UK/ 033-032-63-60 በመደወል  መከታተል እንደሚችሉ ከማእከሉ የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

በሰሜን አሜሪካም በተመሳሳይ ሁኔታ የቴሌቪዥንና የስልክ አገልግሎት መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ሥርጭት በስልክ የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ

ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን እየተዘጋጀ በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ የሚሰራጨው መርሐ ግብር በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን በቀላሉ በተመቻቸው ጊዜ ስልክ ደውለው የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ።

ምእመናን 605-475-8172 ስልክ ቁጥር በመጠቀም በተመቻቸው ጊዜ መርሐ ግብሩን መከታተል እንደሚችሉ በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የስልክ አገልግሎቱ የሚሠራው በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን ብቻ ሲሆን በቅርቡ በሌሎችም የዓለም ክፍሎች ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲኖር ማኅበረ ቅዱሳን በመሥራት ላይ ይገኛል።

 

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ሥርጭት በስልክ የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ

ነሐሴ 30 ቀን 2007 ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን እየተዘጋጀ በቴሌቪዥን እና በሬዲዮ የሚሰራጨው መርሐ ግብር በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን በቀላሉ በተመቻቸው ጊዜ ስልክ ደውለው የሚከታተሉበት አገልግሎት ተጀመረ።

ምእመናን 605-475-8172 ስልክ ቁጥር በመጠቀም በተመቻቸው ጊዜ መርሐ ግብሩን መከታተል እንደሚችሉ በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የስልክ አገልግሎቱ የሚሠራው በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ምእመናን ብቻ ሲሆን በቅርቡ በሌሎችም የዓለም ክፍሎች ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲኖር ማኅበረ ቅዱሳን በመሥራት ላይ ይገኛል::

የማኅበረ ቅዱሳን ንዋያተ ቅድሳት ማምረቻ ክፍል ቃጠሎ ደረሰበት

ነሐሴ 21 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

01 kateloበማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር የንዋያተ ቅድሳት ማምረቻ ክፍል ነሐሴ 18 ቀን 2007 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ቃጠሎ እንደደረሰበት የልማት ተቋማት አስተዳደር ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ፍስሐ ገለጹ፡፡

መረጃው ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እንደደረሳቸው የገለጹት አቶ ኃይሉ በማምረቻ ክፍሉ ተከስቶ የነበረውን ቃጠሎ በአካባቢው ሕዝብና በአዲስ አበባ ከተማ አራዳ ወረዳ የእሳት አደጋ ማጥፊያና መቆጣጠሪያ ክፍል አባላት ርብርብ ወደ ሌሎች ክፍሎች ሳይዛመት በቁጥጥር ሥር እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል፡፡

በቃጠሎው 12 የልብስ ስፌት ማሽኖች፤ 2 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ ካውያዎች፤ 1 መዘምዘሚያ ማሽን፤ 1 ቁልፍ መትከያ ማሽን፤ በዝግጅት ላይ የነበሩና ያልተጠናቀቁ፤ ለስፌት የሚያገለግሉ የግሪክ ጨርቆች፤ የካህናት፤ የዘማርያንና የሰባኪያን አልባሳት፤ ለአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተዘጋጁ አልባሳት፤ የግሪክ ጣቃ ጨርቆች፤ የማምረቻ ክፍሉ በሮች፤ መስኮቶችና ኮርኒስን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል፡፡ ግምታቸውንም ለጊዜው ማወቅ እንዳልተቻለ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

02kateloበዕለቱ ቀኑን ሙሉ መብራት ጠፍቶ ስለነበር ምንም ዓይነት ሥራ አገልጋዮቹ እንዳለከናወኑ የገለጹት ዳይሬክተሩ ቃጠሎው የተከሰተው አገልጋዮቹ ከወጡ በኋላ በመሆኑ የአደጋው መንስኤ እሰካሁን አለመታወቁን ተናግረዋል፡፡ አደጋው የተከሰተበት ምክንያት ፖሊስ የቴክኒክ ምርመራ በማካሔድ ላይ ስለሚገኝ ምርመራው እንደተተናቀቀ የሚታወቅ ይሆናል ብለዋል፡፡

ወደፊት ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ለማከናወን ጥረት እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ኃይሉ ከኢንሹራንሽ ጋር በተያያዘም ወደፊት የሚሠሩ ሥራዎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡ በቃጠሎው ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ላደረጉ አካላት ለአራዳ ክፍለ ከተማ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መቆጣጠሪያ ጣቢያ፣ ለአካባቢው ምእመናንና ፖሊስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በንዋያተ ቅዱሳት ማምረቻ ውስጥ የአልባሳት፤ የመባ /ዕጣን፤ ጧፍ፤ ዘቢብ/ ዝግጅት፤ የተማሪዎች አልባሳት፤ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውሉና በእንጨት የሚዘጋጁ ንዋያተ ቅድሳት እንዲሁም የብረታ ብረት ሥራዎች ይሉ፡፡