‹‹ጥልንም በመስቀሉ ገደለ›› ኤፌ.፪፥፲፮
የዓለም ሰላም የተሰበከውና የተረጋገጠው በመስቀል ላይ በተደረገው የክርስቶስ ቤዛነት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሐዋርያው ‹‹ጥልን በመስቀሉ ገድሎ ርቃችሁ ለነበራችሁ ሰላምና የምሥራችን ሰበከ›› ያለው….
መስቀል የሰላም መሠረት ነው
መስቀል የሰላም መሠረት፤ ሰላምም የመስቀል ፍሬ ነው፡፡ በግእዝ ሰላም የሚለው ቃል ትርጉም ‹‹ፍጹም ጤና፣ ዕረፍት፣ እርቅ፣ ሰላምታ፣ የቡራኬና የምርቃት ቃል፣ ሰው ሲገናኝና ሲለያይ የሚናገረው›› ነው፡፡ መስቀልና ሰላም አንዱ የአንዱ መሠረት አንዱ የአንዱ ፍሬ ሆነው የተሳሰሩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡
ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት
ክርስትና የሕይወት መንገድ ነው፡፡ መንገዱም ደግሞ ወደ ዘላዓለማዊ ክብር የሚያደርስ የሕይወት የድኅነትና የቅድስና መንገድ ነው፡፡ ክርስቲያን ለመሆን በ፵ እና በ፹ ቀን በመጠመቅ የሥላሴ ልጅነትን ማግኘት የቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ያስፈልጋል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ መወለድ ማለትም ነው፡፡
ዘመነ ፍሬ
ከመስከረም ፱ እስከ ፲፭ ያሉት ዕለታት ዘመነ ፍሬ ተብለው ይጠራሉ፡፡ በእነዚህ ወቅት የሚዘመረው መዝሙርም ሆነ የሚነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እግዚአብሔር ለምድር ፍሬንና ዘርን የሚሰጥ የዓለም መጋቢ መሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡
ጾመ ዮዲት
ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ
በናቡከደነጾር ዘመነ መንግሥት ንጉሡ ሥልጣኑን መከታ በማድረግ የእግዚአብሔርን ሕዝብ በግድ እያስገደደ እጅ መንሻ ይቀበል ነበር፡፡ የመንግሥቱን ትእዛዝ ያልተቀበለውንም እየገደለ፣ ጭፍሮቹ ኃያልነቱንና ገናናነቱን በዓዋጅ በጦር አዛዦች ጭምር እያሳወጀ፣ በርካታ የጦር ሠራዊቶችን አሰልፎ ከአይሁድ ከተማ ገባ፡፡ በዚያም ነዋሪዎችን በማስፈራራት የመንግሥቱን ትእዛዝ ያልተቀበሉትን ሁሉ እያሳደደ ስላስጨነቃቸው ማቅ ለብሰው፣ አመድ ነስንሰውና ድንጋይ ተንተርሰው ወደ ፈጣሪያቸው በመጮህ መለመን ጀመሩ። በጭካኔ የተሞላው የጦር አበጋዙ ሆሎፎርኒስም ይበልጥ እጅግ እንዲሰቃዩ ውኃ የሚቀዱበትን ስፍራ ተቆጣጠረው፤ በግዴታ ማርኮም እጅ እንዲሰጡ እንዳደረጋቸው በመጽሐፈ ዮዲት ፪፥፪ ላይ ተጽፏል፡፡ በአካባቢው ይኖር የነበረ ዖዝያን የተባለ አንድ ሰው የአባቶቻቸው አምላክ ጸሎታቸውን እንዲሰማቸው ለአምስት ቀናት በትዕግሥት ይጾሙና ይጸልዩ ዘንድ ሕዝቡን መከራቸው፤ እነርሱም በትዕግሥት ሊጠብቁ ተስማሙ፡፡
የእስራኤል ልጆች የናቡከደነጾርን ጦር ብንችል ተዋግተን እንረታለን፤ ካልሆነም እጅ እንሰጣለን በማለት ይመካከሩ ጀመር። በዚያን ጊዜ ባሏ የሞተባትና በንጽሕና ተጠብቃ፣ በጸሎትና በሕገ እግዚአብሔር የምትኖር ዮዲት የተባለች ሴት ነበረች። (ዮዲት ፯፥፲) እግዚአብሔርን የምትፈራ ብቸኛዋ ሴት እርሷ ነበረችና ምክክራቸውን ስትሰማ ለምን «እግዚአብሔር ያድነናል አትሉም» ብላ ገሠጸቻቸው፡፡ ማቅ በመልበስ፣ አመድ በመነስነስና ድንጋይ በመንተራስም ሱባኤ ገባች። በሦስተኛው ቀንም እግዚአብሔር አምላክ ሕዝቧን የምታድንበትን ጥበብ ገለጸላት፤ ዮዲትም እግዚአብሔር የሰጣትን ውበት ተጠቅማ ሕዝቧን ከጥፋት የምትታደግበትን ጥበብ ተረዳች።
የክት ልብሷን ለብሳ፣ ሽቱ ተቀብታና ተውባ የጠላት ሠራዊት ወዳሉበት የጦር ሰፈር በድፍረት አመራች፡፡ ሠራዊቱም ውበቷን አይተው እጅግ በመደነቅ «ይህችስ ለአለቃችን ትገባለች» ተባብለው ከጦር መሪያቸው ዘንድ ወሰዷት። እርሷም ቀድማ ማምለጫ መንገድ አዘጋጅታ ነበርና ወደ አዛዡ ከገባች በኋላ «ክቡር ጌታዬ ሆይ ርስት ተወስዶብኛል፤ እንድትመልስልኝ አስቀድሜ ደጅ ልጠና መጥቻለውና ርዳኝ፤ ትብብርህ አይለየኝ» አለችው፡፡ በስሜት ፈረስ ታውሮ የነበረው የሠራዊቶቹ አዛዥም የጠየቀችውን እንደሚፈጽምላት ቃል ገባላት። ባማረ ድንካን እንዲያስቀምጧት ሎሌዎቹን አዘዘ። ዮዲትም የተሰጣትን ጥበብ ተጠቅማ፣ መውጣት ስትፈልግ የምትወጣበትን እና የምትገባበትን ዕድል በእግዚአብሔር አጋዥነት ዐወቀች፡፡ ከቀናት በኃላ የጦር አበጋዙ ለሠራዊቱ የምሳ ግብዣ አዘጋጅቶ ዮዲትን ከጎኑ አስቀመጣት፤ ከበሉና ከጠጡ በኋላም ሁሉን ሰው አስወጣ፤ እልፍኙን በመዝጋት ከእርሷ ጋር ብቻውን ሆነ፤ ነገር ግን እንቅልፍ ጣለው፡፡ (ዮዲት ፰፥፪) እርሷም ወደ አምላኳ ጸለየች፤ ፈጣሪዋ እንዲረዳትም አጥብቃ ለመነች። በኋላም ከራስጌው ሰይፍ አንስታ አንገቱን ቀላችው፤ በድኑንም ከመሬት ጣለችው። የሆሎፎርኒስን ሞት ሠራዊቱ ሲሰሙ አውራ እንደሌለው ንብ ተበተኑ፤ ከፊሎቹ ሞቱ። እስራኤላውያንም ከሞት ተርፈው በእግዚአብሔር ኃይል ድል አደረጉ፤ በደስታም ፈጣሪያቸውን አመሰገኑ።
ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪክ የሚያስረዳን ዮዲት ጠላቶቿን ድል ያደረገችው በጾምና በጸሎት እንደሆነ ነው፡፡ ለእኛም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ምንም እንኳ ወርኃ ጳጉሜን የፈቃድ ጾም ቢሆንም በሀገራችን የተጋረጠውን ችግር እናልፍ ዘንድ በፈቃደኝነት እንጾማለን። እግዚአብሔር አምላካችን ለሁላችንም ጥበብ ሰጥቶናል። ይህም ችግሮችን ሁሉ የምንፈታበት መንገድ ነው። በዚህም የዓመተ መሸጋገሪያና የክረምቱ ወር ማብቂያ በመሆኑ ዕለተ ምጽአት ስለሚታሰብበት በየዓመቱ በጳጉሜ ወር ከሌሊት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ተገኝተን ጠበል በመጠመቅ፣ በማስቀደስና በመጸለይ እንዲሁም ሥጋ ወደሙን በመቀበል ልናሳልፍ ይገባል። ዕለተ ምጽአትም ከዚህ ዓለም ወደ ወዲያኛው ዓለም መሸጋገሪያችን ነውና በቀኙ እንቆም ዘንድ እንጾማለን፡፡ የሚመጣውን አዲስ ዘመንም በንጽሕና ለመቀበል ስላለፈው ዓመት ኃጢአታችን ንስሓ የምንገባበት ጾምም ነው።
ከተጋረጠብን ችግር «እግዚአብሔር ያድነናል» በማለት ልክ እንደ ዮዲት ሱባኤ ገብተን፣ ማቅ ለብሰን፣ አመድ ነስንሰንና ድንጋይ ተንተርሰን አብዝተን ልንጾምና ልንጸልይ ይገባል፡፡ ሊለያየን፣ ሊነጣጥለን፣ ሊበታትነን እና ሊገድለን ካሰበው እንዲሁም ፍቅርን፣ መተሳሰብንና አንድነትን ሊነፍገን ከቃጣው ጠላትና ሃይማኖታችንን ሊያስተወን ከሚመጣ ፀረ ሃይማኖት እንድናለን። ስለዚህ ከፊታችን ያለችውን ስድስቱን የጳጉሜን ቀን በፍቅር፣ በአንድነትና በሃይማኖት ጸንተን፣ ጾመን፣ ጸልየን ለዘመነ ዮሐንስ እንድንደርስ እግዚአብሔር አምላካችን ይርዳን፤ አሜን።
ስብሐት ለእግዚአብሔር
ጎሐ፤ ጽባሕ
ዲያቆን ዘክርስቶስ ፀጋዬ
ጎሐ ፤ ጽባሕ ከነሐሴ ፳፱ እስከ ጳጉሜ ፭ ድረስ ያሉት ቀናት የሚጠሩበት ነው፤ ጎሐ ማለት ነግህ ሲሆን ጽባሕ ደግሞ ብርሃን ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው «ዘመናትን የምታፈራርቅ፤ የብርሃንን ወገግታ የምታመጣ አንተ ነህ» እያለ በመግለጽ ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣው፣ ከመኖርም ወደ አለመኖር የሚያሳልፍ፣ በጨለማ መካከል ብርሃንን ያደረገ እርሱ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ብርሃን እና ቀን የልደት፣ ሌሊትና ጨለማን የሞት ምሳሌዎች ሆነው ያገለግላሉ፡፡
ከነሐሴ ፳፱ እስከ ጳጉሜ ፭ ድረስ ያለው ወቅት የክረምቱ ጨለማ የሚወገድበት፣ የፀሐይ ብርሃን ወለል ብሎ የሚወጣበት፣ ጉምና ደመና በየቦታቸው ተሰብስበው፣ ሰማይ በከዋክብት አሸብርቆ የሚታይበት ነው፡፡
በክረምቱ ውኃ ሙላት ምክንያት ግንኙነት አቋርጠው የነበሩ ወገኖች ሁሉ በዚህ ክፍለ ጊዜ ብርሃን ስለሚያዩ፤ መገናኛ መንገዶችም ስለሚያገኙ፣ ክረምቱን እንደ ሌሊት በመመልከት ይህን ወቅት እንደ ንጋት መታየቱን ለመግለጽ ቤተ ክርስቲያን ‹‹ጎሐ፤ ጽባሕ›› በሚለው ስያሜ ትጠራዋለች፡፡ በዚህ ወቅት የሚዘመሩ መዝሙራት ‹‹አቤቱ ወደ አንተ እጸልያለውና በማለዳ ድምፄን ስማ›› (መዝ.፭፥፪)፤ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ብርሃንን አየ፣ በሞት ጥላ ሥር ለተቀመጡት ብርሃን ወጣላቸው (ማቴ.፬፥፲፮) የሚሉትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን (ጸሎተ ሃይማኖት)
ቤተ ክርስቲያን ሰማያዊት ንጽሕትና ቅድስት የክርስቶስ ማደሪያ ናት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ «በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ እናንተን ጰጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለራሳችሁ እና ለመንጋው ሁሉ ተጠንቀቁ» በማለት ያስጠነቅቃል፡፡ በሰው ልጅ ፈቃድና ሐሳብ ያልተሠራች እግዚአብሔር በደሙ የዋጃት ቅድስት ሥፍራ ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሰማይና በምድር ያለች፣ ከሰው ልጅ ዕውቀት ፈቃድና ፍላጎት በላይ የሆነች የእግዚአብሔር ማደሪያ ናት፡፡ እግዚአብሔር የመሠረታት፣ የቀደሳትና የዋጃት፣ ሐዋርያት፣ ነቢያትና ቅዱሳን አበው የሰበኳትና ያጸኗት ቤት ናት፤ ለሰውም በረከተ ሥጋንና በረከተ ነፍስን ታድላለች፡፡
«ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው፤» (መዝ.፻፲፭፥፭)
ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን
«ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር፤ የጻድቅ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው»፤ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ስለሕዝቅያስ በተናገረው በዚህ ኃይለ ቃል ሊያስረዳን የፈለገው የነፍስ ከሥጋ መለየት ከሚያልፈው ዓለም ወደማያልፈው ዓለም፣ ውጣ ውረድ፣ ድካም ካለበት ዓለም ውጣ ውረድ ድካም ወደሌለበት ዓለም መሄድ ነውና። ስለሆነም እንደ ቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ በዚህች ዕለት የቅዱሳን ዕረፍት ነው እየተባለ ይነገራል። ድካም ካለበት ድካም ወደሌለበት ስለሆነ ዐረፈ ወይም ዐረፈች እየተባለ ይነገራል። በነሐሴ ፳፬ በዓለ ዕረፍቱን የምናከብረው ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዐረፈ እንጂ ሞተ አይባልም፤ ሞቱ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነውና።
በዚህ ዕለት ቤተክርስቲያን የቅዱሱን በዓለ ዕረፍት ምክንያት በማድረግ እግዚአብሔርን ከምታመሰግንበት ያሬዳዊ ዜማ እንጥቀስ። «ሞቶሙሰ ለጻድቃን ሕይወቶሙ ውእቱ እስመ ለጻድቅ ይትሌዓል ቀርኑ በክብር ጻድቃን እለ አሥመርዎ ለእግዚኦሙ ምድረ ብርህተ ወጽዕዱተ ይወርሱ፤የጻድቃን ሞታቸው ሕይወታቸው ነው። የጻድቅ ክብሩ ከፍ ከፍ ይላልና። ጌታቸውን ደስ ያሰኙት ጻድቃን ብርህትና ጽዕዱት የሆነች ምድርን ይወርሳሉ» (ቅዱስ ያሬድ)።
እንግዲህ ከላይ በተጠቀሰው ቃለ እግዚአብሔር መሠረት ሞታቸው ሕይወታቸው ነው የተባለ በመጀመሪያ ደረጃ ሞተ ሥጋ እንደሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ጻድቃን ሞተ ሥጋን እንጂ ሞተ ነፍስን ሊያዩ አይችሉም። ሞተ ነፍስን የሚያዩ ከሆነ ጥንቱኑ ጻድቃን ሊባሉም አይችሉም። ሞተ ሥጋቸው ግን ወደ ተሻለውና ወደሚበልጠው ዓለም የሚሄዱበት ስለሆነ ሕይወታቸው ነው ተባለ።
ሌላው ደግሞ የጻድቃን ሞት እንጂ የኃጥአን ሞት ሕይወት ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም ኃጥእን ምንም እንኳ ወደማያልፈው ዓለም የሚሄዱ ቢሆንም መከራ ወደ አለበት፣ ሥቃይ ወደሚበዛበት እንጂ ዕረፍት ወደአለበት መሄድ አይችሉም። መከራና ሥቃይ የሚበዛበት ዓለም መሄድ ደግሞ ሕይወት ሊባል አይችልም። እንዲያውም ነቢዩ ዳዊት «ሞቱ ለኃጥእ ጸዋግ፤የኃጥእ ሰው ሞት ክፉ ነው» (መዝ.፴፫፥፳፩) በማለት አስረድቷል። ጻድቃን ሞተ ሥጋን እንጂ ሞተ ነፍስን አያዩም። ኃጥኣን ግን ሞተ ሥጋም ሞተ ነፍስም ያገኛቸዋል። ስለዚህ ለኃጥእ ሰው ሞተ ሥጋውም ሆነ ሞተ ነፍሱ ክፉ እንጂ መልካም የሚባል አይደለም።
ሞት የሰው ልጅ የፈጣሪውን ትእዛዝ በመተላለፍ የሰለጠነበት ነው። «በሕይወታችሁ ስሕተት ለሞት አትቅኑ፤በእጃችሁም ሥራ ጥፋትን አታምጡ። እግዚአብሔር ሞትን አልፈጠረምና፤ የሕያዋንም ጥፋት ደስ አያሰኘውምና። ነዋሪ ይሆን ዘንድ ፍጥረቱን ፈጥሮአልና፣ የዓለም መፈጠርም ለድኅነት ነውና፣ በእነርሱም ዘንድ የጥፋት መርዝ አልነበረምና፣ ለሲኦልም በምድር ላይ ግዛት አልነበረውምና። ጽድቅ አትሞትምና። ክፉዎች ግን በእጃቸውና በቃላቸው ጠሩት ባልንጀራም አስመሰሉት። በእርሱም ጠፉ። የእርሱ ወገን መሆን ይገባቸዋልና ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረጉ» (ጥበ.፩፥፲፪-፲፯) በማለት መፍቀሬ ጥበብ ሰለሞን ነግሮናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ ሃይማኖትና ምግባር የማይነጣጠሉ እንደሆኑ በምሳሌ ሲያስተምር የጠቀሰው የነፍስና የሥጋን ህልውና ነው። «ከመ ሥጋ ዘአልቦ መንፈስ ምውት ውእቱ ከማሁ ሃይማኖትኒ እንተ አልባቲ ምግባረ ሠናይ ምውት ይእቲ ለሊሃ፤ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው» (ያዕ.፪፥፳፮) እንዲል፤ ስለዚህ ነፍስ ያለሥጋ ሥጋም ያለ ነፍስ ህልውና አይኖራቸውም። ይህ ማለት በሰውነት ህልውና እንጂ ነፍስና ሥጋ ተለያይተው ነፍስም በገነት ወይም በሲኦል ሥጋም በመቃብር አይኖሩም ማለት አይደለም፡፡ በመሆኑም የሥጋ ሞት የሚባለው የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው። ይህ የነፍስ ከሥጋ መለየት የጻድቅ ከሆነ በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ነው።
ነፍስ በባሕርይዋ የምትሞት አይደለችም፤ ሞተ ነፍስ የሚባለው የማትኖርበት ጊዜ ስላለ ሳይሆን ከምትኖርበት ሁኔታ አንጻር ነው። ይህ ማለት ነፍስ በሃይማኖት ጸንታ በምግባር ቀንታ ባለመኖሯ ወደ ሲኦል በኋላም ገሃነመ እሳት ትወርዳለች። የነፍስ ሞት ማለት ገነት በመግባት ፈንታ ሲኦል፣ መንግሥተ ሰማያት በመግባት ፈንታ ገሃነመ እሳት መግባት ነው። «ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም» (ራእ.፪፥፲፩) ተብሎ የተጻፈው ነፍስ ከሥጋ መለየትን ሳይሆን ገሃነመ እሳት መውረድን አያይም ለማለት ነው።
ሞት ማለት መለየት ነውና ነፍስ ከፈጣሪዋ ከእግዚአብሔር ተለይታ ካልፈጠራት ከዲያብሎስ ጋር መኖር ስትጀምር የነፍስ ሞት ይባላል። ሁለተኛ ሞት የተባለውም ፈጣሪ ያዘጋጀውን መንግሥተ ሰማያት አጥታ በኃጢአቷ ምክንያት ገሃነመ እሳት መውረድ ነውና «ድል የነሣው ሁለተኛውን ሞት አያይም» ማለት ከላይም እንደተገለጸው ገሃነመ እሳት አይገባም ማለት ነው።
በአጠቃላይ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት «የጻድቅ ሰው ሞት ክቡር ነው» ሲል ሞተ ሥጋን አያይም ማለት ሳይሆን ሞተ ነፍስን አያይም ማለት እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ደግሞ ሞተ ሥጋን መቅመስ የግድ ነውና ይህ እንደ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት መንግሥተ ሰማያትን የሚወርስበት ሞት ክቡር ነው፤ሕይወት ነው፣ ዕረፍት ነው እያለ ይገልጸዋል፡፡ እኛም ንስሓ ገብተን ሥጋውን ደሙን በልተን እንደዚህ በእግዚአብሔር ዘንድ ክቡር ለተባለው ሞት እንዲያበቃን የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የጻድቁ የተክለ ሃይማኖት ረድኤት በረከት አይለየን፤ አሜን።