‹‹መረባችሁን በታንኳይቱ በስተቀኝ በኩል ጣሉ›› (ዮሐ. ፳፩፥፮)

ሊቀ ሊቃውንት ዮሐንስ አፈወርቅ

ሰኔ ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ዓሣ ማሥገር አድካሚ እንደሆነ ሁሉ አስጋሪውም ብዙ ዓሣዎችን ይይዝ ዘንድ መረቡን ወደየት አቅጣጫ መጣል እንዳለበት ማወቅ ይጠበቅበታል፤ ካልሆነ ግን ምንም ዓሣ ሳያጠምድ ወደ ቤቱ ይመለሳል፤ ተርቦም ሊያድር ይችላል፡፡

በዘመነ ሥጋዌ ከሐዋርያት መካከል እነ ቅዱስ ጴጥሮስ ለመተዳደሪያ በባሕር ዓሣን ያሠግሩ ነበር፤ ሆኖም ግን በእስራኤል ምድር ውስጥ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ እርሱን ይከተሉ ዘንድ ሲጠራቸው ከአድካሚው ሥራ ወደ ትሩፋት ሥራ የመምጣት ፍላጎት አደረባቸው፡፡ ዓሣ ማስገሩን ትተውም እርሱን በመከተል ኖረዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል በሚሰቀልበት ሰዓት እያንዳንዳቸው በፍርሃት መበተን ጀመሩ፡፡ ከእነርሱ መካከል ደግሞ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ይዞ በመስቀሉ ፊት ለፊት ሆኖ በኃዘንና በለቅሶ ታማኝነቱንና እውነተኛነቱን በጌታ ፊት ገለጠ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ በነገራቸው መሠረት የትንሣኤው ዕለት ቅዱሳት አንስት ቀድመው ትንሣኤውን ተረድተው ተመልሰው ሄደው ለእነ ቅዱስ ጴጥሮስ ነገሯቸው፡፡ እነርሱም መቃብርን አይተው ትንሣኤውን ተረድተዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የትንሣኤው ዕለት አግኝቷቸው በአግባቡ የሚያጽናና ትምህርትን ሰጣቸው፡፡

ከዚህ በኋላም አግብኦተ ግብር ተብሎ በሚጠራው የዳግም ትንሣኤ ቀን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠላቸው፡፡ ነገር ግን ከእርሱ ጋር አብሮ መዋልና አብረው ማደር አልቻሉም ነበርና ቅዱሳን ሐዋርያቱ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ተፈጥሮባቸው ነበር፡፡

ብዙ ጊዜ በአእምሮአችን ውስጥ  የሚመጡብን ብዙ ሐሳቦች ይኖራሉ፤ ስለዚህም ራሳችንን መመርም አለብን፡፡ ሐሳባችን ሥጋዊ ወይስ መንፈሳዊ መሆኑን መለየትና ማወቅ ይኖርብናል፡፡ መንፈሳዊ እንደ መሆናችን መጠን ለመንፈሳዊነት የሚገባ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም ለነፍሳችን ያህል ሳንበላ፣ ሳንጠጣና ሳንለብስ መኖር ስለማንችል የሚገባንን ለማድረግ መዘጋጀት አለብን፡፡ ነገር ግን በማይሆን ሐሳብ ውስጥ መጠመድ አያስፈልግም፡፡

ከዚህ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስ ዓሣ ማስገር ከተወ ከሦስት ዓመት በኋላ  ‹‹ዓሣ ልይዝ እሄዳለሁ›› አላቸው፡፡ ጴጥሮስ የክርስቶስ እንደራሴ እንዲሁም የሐዋርያት የበላይ ነበር፤ ደቀ መዛሙርቱ ሐዋርያት ይህን ሲሰሙ እነርሱም ‹‹ካንተ ጋር  እንሄዳለን›› አሉት፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያቱም ተነሡና በጨለማ ወደ ባሕር ዓሣ ለመያዝ ተጓዙ፡፡ መረባቸውንም እንደገና መዘርጋት ጀመሩ፡፡ ተቆራርጦ የነበረውን መቀጠል ጀመሩ፡፡ ነገር ግን የተመረጡለት ሥራቸው ይህ አልነበረም፡፡ (ዮሐንስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፫ ገጽ ፭፻፶፭)

ከሐዋርያት ሕይወት ልንማር ያስፈልገናል፤ ሰዎችን በትምህርተ ወንጌል የማነጽ፣ ድውያንን የመፈወስ እንዲሁም መንፈሰ አጋንንትን የማስወጣት ኃላፊነትና ሥልጣን ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ጌታቸው ከእነርሱ በሥጋ ሲለይ ሥጋት አደረባቸው፤ ብዙዎች አባቶቻችንና ወንድሞቻችን በእንደዚህ ዓይነት ሥጋት ውስጥ እናገኛቸዋለን፡፡ በወንጌል መረብነት ለመንግሥተ ሰማያትን የሚያጠምዱ አባቶቻንንን እንዳሉ ግን በመረዳት መጽናት ያስፈልጋል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም በጨለማ ሄደው ከባሕሩ ሲደርሱ የጣሉትን መልሰው ማንሣት ጀመሩ፡፡ በሌሊት ያረጀ መርከባቸውንና መረባቸውን ይዘው ጥብርያዶስ ባሕር ውስጥ ሲወጡና ሲወርዱ ቢያድሩ ዓሣ መያዝ አልቻሉም፡፡ ከእግዚአብሔር ያልታዘዘ ነገር ነበርና፡፡እግዚአብሔር ካልፈቀደ የሚሆን ነገር የለምና፡፡

አብዛኞቻችን በሕይወታችን ውስጥ ብዙ ገንዘብ ብንይዝ ዓለምን የምንጨብጣት ይመስለናል፡፡ አኗኗራችንም የተለየ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ምድርም ኃይሏን አልሰጥ ብላለች፤ ምንም ነገር ሙሉ የሆነ የለም፡፡ ምክንያቱም እኛ ሀገራችን፣ ንብረታችንና ሀብታችን ሁሉ በሰማይ መሆኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነግሮናል፡፡ ስለዚህ በንስሓ ልመለስና በክርስቲያናዊ ሕይወት ጸንተን ልንኖር ይገባል፡፡

ሐዋርያት ሌሊቱን በሙሉ ዓሣ ሊያጠምዱ ሞክረው ሲያዳገታቸው ተስፋ ቆርጠው ሊመለሱ ባሰቡበት ጊዜ ጌታችን በእነርሱ መካከል ተገኘ፤ ሆኖም እርሱ መሆኑን አላወቁም ነበር፡፡ የሚፈልጉትንም ዐውቆ ይጠይቃቸው ጀመር፡፡ ‹‹ልጆች ሆይ አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?›› አላቸው፤ እነርሱም፥ ‹‹የለም››  አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም ‹‹መረባችሁን በታንኳይቱ በስተቀኝ በኩል ጣሉ፤ ታገኛላችሁም›› አላቸው፤ መረባቸውንም በጣሉ ጊዜ ከተያዘው ዓሣ ብዛት የተነሣ ስቦ ማውጣት ተሣናቸው፡፡ (ዮሐ. ፳፩፥፭-፮)

እግዚአብሔር ያለበት ሥራ ሁሉ ፍጻሜው መልካም ነው፤ አምላካችን የሌለበት ሥራ ግን በፍጹም ከንቱ ድካም ነው፡፡ ወገኖቼ ሁላችንም መረባችን በቀኝ በኩል እንጣል፤ ምክንያቱም ቀኝ ኃያል ነው፤ ግራ ግን ደካማ ነው፡፡ ቀኝ ተብሎ የሚጠራው መረብ ወንጌል ናት፤ በመጀመሪያም የተሰበከች ለእስራኤል ነው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት በኅብረት ለአንድ ዓመት በኢየሩሳሌም ሆነው አስተምረዋል፡፡ ነገር ግን የሰሙ ሲጠቀሙ ያልሰሙ ደግሞ ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፡፡

ወንጌል በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ተሰብኳል፤ የሰሙትም ተጠቅመዋል፤ ያልሰሙ ደግሞ ሁልጊዜ እንደ ፋና ቁጭ ብለው ቀርተዋል፡፡ ስለዚህም ወንጌልን በአግባቡ ልንሰማና ልንማር ይገባል፡፡

ሐዋርያት ያጠመዱትን ዓሣ ይዘው ከባሕሩ ሲወጡ ዮሐንስ ተመለከተና ለቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹ጌታችን ነው›› አለው፤ ቅዱስ ጴጥሮስም በቅጽበት በደስታ ተሞላ፤ ሐዋርያቱም በሙሉ በመርከብ ወደ እርሱ ለመድረስ ሲጓዙ ቅዱስ ጴጥሮስ ግን በባሕር ተራምዶ ወደ ጌታው ሊደርስ ቻለ፡፡ (ዮሐንስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ምዕራፍ ፳፩ ቁጥር ፯ ገጽ ፭፻፶፭)

ከዚያም በኋላ ‹‹ወደ ምድርም በወረዱ ጊዜ ፍሙ መርቶ፥ ዓሣ በላዩ ሆኖ፥ እንጀራም ተሠርቶ አገኙ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም አሁን ከያዛችኋቸው ዓሣዎች አምጡ አላቸው፡፡ ጴጥሮስም መቶ ሃምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሣዎችን መልቶ የነበረውን መረብ ስቦ አቀረበ፤›› የዓሣው ብዛት ይህን ያህል ቢሆንም መረቡ አልተቀደደም፤ የአምላካችን ፈቃድ ነበርና፤ ጌታችን ኢየሱስም ‹‹ኑ፥ ምሳ ብሉ አላቸው›› ከዚያም ኅብስቱን አንሥቶ ሰጣቸው፤ ጌታችንም ሐዋርያትን አስተምሮ ኅብስትም መግቧቸዋል፡፡ (ዮሐ. ፳፩፥፱-፲፫)

አሁን በሀገራችን በኢትዮጵያ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለብርድና ውርጭ የተጋለጡ የሚበሉትም ያጡ እንዲሁም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች አሉና ለእነዚህ ሰዎች አምላካችን እግዚአብሔር በችግራቸው እንዲደርስላቸው የሁላችንም ጸሎት ሊሆን ይገባል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር ሀገራችንን ኢትዮጵያን እንዲጠብቅልን ሁላችንም በተመረጥንበት ተልእኮ ጸንተን መኖር አለብን፡፡

መረባችንን በቀኝ በኩል ጥለን የሚገባንን እንድናገኝ የአምላካችን እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር