የመጥምቀ መለኮተ ቅዱስ ዮሐንስ ሕይወትና አገልግሎት ክፍል ሁለት
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እና ነቢዩ ኤልያስ
ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ እና ነቢዩ ኤልያስ
በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም 1 እስከ 7 ያለው ጊዜ ዘመነ ዮሐንስ ይባላል፤ ሳምንቱ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ሕይወቱ፣ትምህርቱና ምስክርነቱ የሚታሰቡበት ነው ፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያን አምልኮቷን የምትፈጽምበት እጅግ የተደራጀ ሥርዐተ አምልኮ አላት፡፡ ከዚህ ሥርዓተ አምልኮ አንዱ ክፍል ዓመታዊ የምስጋና መርሐ ግብር እና የሥርዓተ ትምህርት ነው፡፡ ይህም በሁለት መልኩ የተደራጀ ነው፡፡
በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች ግንኙነት ውስጥ ጥልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ድርጊቶች እና ክንውኖች በዓመቱ ውስጥ ቀናት ተመድበውላቸው በበዓላትና በአጽዋማት መልክ ይታሰባሉ፡፡ ቅድስት ቤተክርስቲያን እነዚህን በዓላትና አጽዋማት የምታከብርበት ዓመታዊ መርሐ ግብር እና በበዓላቱና በአጽዋማቱ የሚታሰበውን ነገር አስመልክቶ አባላቶችን የምታስተምርበት ሥርዓተ ትምህርት አላት፡፡
እንደዚህ ባለ መርሐ ግብር ከሚታሰቡት መካከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ያደረጋቸው ነገሮችና ያስተማራቸው ትምህርቶች /ፅንሰት፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሳኤ፣ ዕርገት፣ ደብረ ታቦር፣ምጽአት/፤ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት /ልደቷ፣ ዕረፍቷ፣ ቤተመቅደስ መግባቷ፣ ድንቅ ተአምራት ያደረገችባቸው ዕለታት/፤፣ የቅዱሳን በዓላት /ልደታቸው፣ ዕረፍታቸው፣ ተአምራት ያደረጉባቸው. . / ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
መስከረም 8 ቀን እሁድ ቀን ቢውል ያ እሁድ «ዘካርያስ» ተብሎ ይጠራና የመጥመቁ ዮሐንስ አባት የካህኑ የዘካርያስ ነገር ይታሰብበታል፡፡
ከመስከረም 9 እስከ 17 ያለው እሁድ /እና በዚህ እሁድ የሚጀምረው ሳምንት/ «ፍሬ» ይባላል፡፡ በዚህ እሁድ እግዚአብሔር ለምድር ፍሬን እንደሚሰጥ ይታሰባል፡፡
በዚህ መልኩ በዓመቱ ውስጥ ባሉት እሑዶች በሙሉ ምን እንደሚታሰብ የሚገልጽ መርሐ ግብርና ሥርዓተ ትምህርት አለ፡፡ ይህም በተለያዩ ወቅቶች ያለውን የአየር ጠባይ እና የግብርና እንቅስቃሴ ያገናዘበ ነው፡፡
«ስንክሳር» የሚባለው መጽሐፍ ከመስከረም አንድ እስከ ጳጉሜን 5/6 ድረስ የሚታሰቡ ቅዱሳንን እና ክንውኖችን ዝርዝር ታሪክ ይዟል፡፡
«ግጻዌ» የሚባለው መጽሐፍ በየዕለቱ /በየእሁዱ/ ከሚታሰበው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባት /ከመልእከታተ ጳዉሎስ፣ ከሰባቱ መልእክታተ ሐዋርያት፣ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፣ ከመዝሙረ ዳዊት፣ ከወንጌል/ መርጦ ያቀርባል፡፡
የቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍትም /ድጓ፣ ዝማሬ፣ምዕሪፍ፣ ዝማሬ መዋስዕት/ በዚህ መርሐ ግብር መሠረት የተዘጋጁ ሲሆኑ በየዕለቱ ስለሚታሰቡት ነገር ዝርዝር እና ጥልቅ የሆኑ ትምህርቶችን እና ምስጋናዎችን የያዙ ናቸው፡፡
በዚህ «ስብከት» በሚለው ዓምድ ሥር ይህንን መርሐ ግብር፣ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት አድርገን ትምህርቶችን እናቀርባለን፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ዓምድ ስር የሚቀርቡት ትምህርቶች ሦስት ዓይነት ናቸው፡፡
1. ሳምንታዊ ስብከት– በዚህ ንዑስ ዓምድ ስር በእያንዳንዱ እሁድ/ሳምንት/ የሚታሰቡትን ጉዳዮች አስመልክቶ ትምህርቶች ይቀርባሉ፡፡
2. ወቅታዊ ስብከት– በዚህ ንዑስ ዓምድ ስር ቀናትን መሠረት አድርገው ከሚከበሩት በዓላት መካከል ዋና ዋናዎቹን በተመለከተ ትምህርቶች ይቀርባሉ፡፡
3. ሌሎች– ይህ ንዑስ ዓምድ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጁ ስብከቶች የሚቀርቡበት ነው፡፡
አዘጋጆቹን በጸሎት በማሰብ፣ በሚቀርቡ ስብከቶች ላይ አስተያየት በመስጠትና ስብከቶችን በመላክ ለዚህ ዓምድ መጠናከር ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ፡፡ እግዚአብሔር ሐሳባችንን እንድንፈጽም ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡
እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡ ዘመነ ማቴዎስም፣ ዘመነ ማርቆስም፣ ዘመነ ሉቃስም ሆነ ዘመነ ዮሐንስ በአራቱም ዘመናት አስቀድሞ ርእሰ ዓውደ ዓመት ቅዱስ ዮሐንስ ይዘከራል፡፡ ዮሐንስ የስሙ ትርጉም «ጸጋ እግዚአብሔር» ማለት ነው፡፡ ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ሰዓታት ደቂቃን ቅጽበትን /ሰኮንድን/ ሳይቀር እየሰፈሩ/እየቆጠሩ/ ዕለታት ሳምንታትን፣ ሳምንታት ወራትን፣ ወራት ዓመታትን አሁን ላለንበት ዘመን ደርሰናል፡፡ ዓውደ ዓመት በግእዝ ሲሆን በአማርኛ የዘመን መለወጫ/ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕንቁጣጣሽ እየተባለም ይጠራል፡፡
የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱን በመረዳት የቤተክርስቲያን አበው የበዓላቱን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርዕሰ ዓውደ ዓመት በሚሆን መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ አባቶች ደንግገዋል፡፡ / ድርሳነ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ገጽ 1ጠ 3/ ይህንንም በዓል አባቶቻችን በርእሰ ዓውደ ዓመት ማክበር እንደሚገባ አስበው ያደረጉት ነው፡፡ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ በሰማዕትነት ያረፈበት ቀን ሆኖ አይደለም፡፡ ለአዲሱ ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዓውደ ዓመት «ቅዱስ ዮሐንስ» ይባላል፡፡ መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ /መስከረምን/ ሲያትት «ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው በማለት ያስረዳል፡፡ የዚህ ወር ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 ሰዓት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ቀኑ እየጎደለ ይሔዳል፡፡
ከዚህ በመቀጠል በዓሉ በተለያየ ስያሜ ስለመጠራቱና ትርጓሜያቸውን እንመለከታለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በድሬዳዋ ኈኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ሰበካ ጉባኤ ሥር የተቋቋመው የአካባቢ የልማት ኮሚቴ እያከናወነ ያለውን የልማት ሥራ ለማገዝ ሕብረተሰቡ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ የደብሩ አሰተዳዳሪ ጥሪ አቀረቡ፡፡ ልማት ኮሜቴው ከሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር በላይ ውጪ የሚጠይቅ ትምህርት ቤት ግንባታ ጀምሯል፡፡
የደብሩ አሰተዳዳሪ መጋቢ ካህናት አባ ገብረየሱስ አሻግሬ ሰሞኑን እንደገለጹት፤ ቤተክርስቲያኒቱ ለአካባቢው ምእመናን ከምትሰጠው መንፈሳዊ አገልግሉት በተጓዳኝ በዘላቂ ልማት ራሷን እንድትችል ለተጀመረው ጥረት የልማት ኮሚቴው እንቅስቃሴ ሊበረታታ ይገባዋል፡፡
በልማት ኮሚቴው አማካኝነት ቤተክርስቲያኒቱ ባላት ሰፊ ግቢ ውስጥ ከ1999 ዓ.ም አንስቶ አንድ መዋዕለ ሕፃናትና 1ኛ ደረጃ ት/ቤት አገልግሎት እየሰጠበት መሆኑን የገለጹት አስተዳዳሪው፤ ይህንኑ ት/ቤት አስፋፍቶ እስከ 2ኛ ደረጃ ለማሳደግ ባለ 3ፎቅ ህንፃ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ልማት ኮሚቴው ከከተማው አስተዳደር አስፈቅዶ በቤተ ክርስቲያኒቱ አቅራበያ ከሐረር ቢራ አክሲዮን ማኅበር ባገኘው ሙሉ ድጋፍ የሕዝብ መናፈሻ እየሠራ እንደሚገኝ አስተዳዳሪው ገልፀው፤ ልማት ኮሚቴው እያከናወነ ያለው ተግባር ለቤተክርስቲያኒቱም ሆነ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጠቃሚ በመሆኑ ሕብረተሰቡ የድጋፍ እጁን እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡
የልማት ኮሚቴውና የትምህርት ቤቱ አመራር ቦርድ ጸሐፊ አቶ አደፍርስ ተሾመ በበኩላቸው የኮሚቴው ዋና አላማ ቤተክርስቲያኒቱ በራሷ ቋሚ ገቢ እየታገዘች መንፈ ሳዊ አገልግሎቷን በተሳካ ሁኔታ እንድታከናውን እንዲሁም የአካባቢው ማኅበረሰብ ልጆች የጥሩ ሥነ ምግባርና እውቀት ባለቤት የሚሆኑበትን ትምህርት ቤት ማስፋፋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ዐውደ ምህረት ላይ በአካባቢው ማኅበረሰብ የተቋቋመው 18 አባላት ያለው የልማት ኮሚቴ ከቤተክርስቲያኒቱ ሰበካ ጉባኤ፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብና ከከተማው የመንግሥት ሥራ ሓላፊዎች ጋር በመቀናጀት እቅዱን በተግባር እያዋለ እንደሚገኝ የገለጹት ጸሐፊው፤ ለጥረቱ መሳካት የሕብረተሰቡ ትብብር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኮሚቴው ከኅብረተሰቡ፣ ከባለሀብቶች፣ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ፣ ከልማት ኮሚቴው አባላትና ከመንግሥት ሠራተኞች ባገኘው ድጋፍ ከግማሽ ሚሊዩን ብር በላይ ውጪ አንድ የመዋዕለ ነሕፃናት እና 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ሠርቶ በማጠናቀቅ በአሁኑ ወቅት ከ350 በላይ ተማሪዎችን በጥሩ አገልግሎት እያስተማረ እንደሚገኝ ጸሐፊው ገልጸው ከእነዚህ ውስጥ ከአሁን ቀደም በከተማው ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ ወላጆቻቸውን ያጡና የችግረኛ ቤተሰብ የሆኑ ሃያ ልጆች በነፃ እየተማሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኮሚቴው ራእይ ይህንን ት/ቤት እስከ ኮሌጅ ማድረስ መሆኑን የገለጹት ጸሐፊው በአሁኑ ወቅት እስከ 10ኛ ክፍል ማስተማር የሚያስችል ባለ 3 ፎቅ ሕንፃ ግንባታ ተጀምሮ መሠረት ወጥቶለት የመጀመሪያው ፎቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከሦስት እስከ አራት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሜቴው ይህንን ሕንፃ ለመቀጠል ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት እንዳለበት ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ በመ ሆኑም የአካባቢው ማኅበረሰብ፤ በሀገር ውሰጥ እና በውጭ ያሉ በጎ አድራጊዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡
የእርዳታ እጃቸውን መዘርጋት ለሚፈልጉ በቅድስት ማርያም መዋዕለ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ስም በተከፈተው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬደዋ ዐቢይ ቅርንጫፍ የባንክ ሒሳብ ቁጥር 4076 ቢልኩ እንደሚደርስም ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮ ማዕከል ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከሐምሌ 3 ቀን እስከ 5 ቀን 2001 ዓ.ም በኦስትሪያ ሽቬካት ከተማ ተካሔደ፡፡ በጉባኤው ላይ ከተለያዩ ቀጠና ማዕከላትና ግንኙነት ጣቢያዎች የተውጣጡ ከ45 በላይ አባላት የተሳተፉ ሲሆን የማዕከሉ የ2001 ዓ.ም የአገልግሎት እንቅስቃሴና የኦዲት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት በማድረግ ማጽደቁን የአውሮ ማዕከል የላከልን መረጃ ያመለክታል፡፡
በተለይ የማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል ጽ/ቤት ግንባታና የማዕከሉ ድርሻ፣ የአውሮ አኅጉረ ስብከት አጠቃላይ እንቅስቃሴና የማዕከሉ ድርሻ፣ ወቅታዊ የቤተክርስቲያን ሁኔ ታና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይቶችን አድርጎ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል፡፡
እንደዚሁም የማኅበሩን የአራት ዓመት ዕቅድ መሠረት በማድረግ ዕቅዱ ለማዕከሉ ቀርቦ ከገመገመ በኋላ ያጸደቀ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ የሚቀጥለውን ዓመት ዕቅድ ዐይቶ ማሻሻያ በማድረግ እንዳጸደቀም ይኸው መረጃ ጠቁማል፡፡
ዘጠነኛው የአውሮፖ ማዕከል ጉባኤ ሲካሔድ ለተሳታፊዎቹና ጥሪ ለተደረገላቸው ምእመናን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መሰጠቱንም ተወስቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉባኤው የተካሔደበት ከተማ ከንቲባው ለጉባኤው ለተሳታፊዎች ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉ ዘገባው አመልክቶ ስለ ኦስትሪያ አጠቃላይ ኢኮኖማያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳይ በሚመ ለከትገለጻ አድርገዋል ተብሏል፡፡
ከተማቸው የጥንታዊ ቤተክርስቲያን ወጣቶችን ዓመታዊ የአውሮፓ ማዕከል ጉባኤ በማዘጋጀቷ ታላቅ ደስታ እንደተሰማቸው ከንቲባው ገልጸዋል ሲል የማዕከሉ መረጃ ያመለክታል፡፡
እንደዚሁም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በማኅበረ ቅዱሳን አማካኝነት ስለምትሠራቸው መጠነ ሰፊ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ከጉባኤው ተሳታፊዎች ለከንቲባው ገለጻ መደረጉን ተወስቷል፡፡
በጉባኤው ማጠቃለያ ላይ ለዝግጅቱ መሰካት አስተወጽኦ ላደረጉት የቪየና ኪዳነ ምሕረት ካህናትና የሰበካ ጉባኤ ከፍ ያለ ምስጋና መቅረቡም ተገልጿል፡፡
በተለይ ለጉባኤው መሰብሰቢያ አዳራሽ በመፍቀድና ለተሳታፊዎችም ማረፊያ በመስጠት ለተባበሩት የሽ ቬካት ቅዱስ ያዕቆብ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊ ለቄስ ጌራልድ ጉም ፕና ለሥራ ባልደረቦቻቸው ከምስጋና ጋር የመታሰቢያ ስጦታ ተበርክቶላ ቸዋል፡፡
በመጨረሻም ቀጣዩ የማዕከሉ 10ኛ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ በጀርመን ሀገር እንዲዘጋጅ ተወስኖ በዚህም ከወትሮው በተለየ መልኩ የማዕከሉን የ10 ዓመት የአገልግሎት እንቅስቃሴ የሚያመለክት ዝግጅት እንዲዘጋጅ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ጉባኤው መጠናቀቁን ከዘገባው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ዓውደ ርእዩ ኅብረተሰቡ ስለአብነት ትምህርት ቤቶች ግንዛቤ እንዲኖረው ረድቷል
«ቅኔ የአብነት ትምህርቱ ፍልስፍና መሠርተ» በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን በማኅበራዊ አገልገሎት ልማት ዋና ክፍል የተዘጋጀው የግማሸ ቀን ዐውደ ጥናት በስ ድስት ኪሎ ስብሰባ አዳራሽ ተካሄደ፡፡ ዐውደ ጥናቱን በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም እንደገለጹት፤ ዐውደ ጥናቱ በቅኔ ትምህርት አገልግሎቱና ፍልስፍናው ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
የቅኔ ትምህርት የቤተክርስቲያን ትምህርተ ሃይማኖት፣ የሀገራችን ታሪክ እና የቀደምት አባቶችና የዛሬዎች ሊቃውንት ፍልስፍና ጥበብ እንዲሁም ማኅበራዊ ሒስ የተላለፈበት የዕውቀት ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቅኔ በሀገሪቱ ሕዝቦች የአኗኗር ሥርዓትና ባሕል ውስጥ የራሱ አሻራ ያስቀመጠ ትምህርት ነው ያሉት ሰብሳቢው፤ በአሁኑ ወቅት በርካታ የውጭ ሙሁራን በትምህርቱ ላይ ምርምር እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ በአንጻሩ በሀገሪቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ትምህርቱን ለማሳደግ የሁሉም ርብርብ የሚያስፈልገው እንደሆነና ዐውደ ጥናቱም የጠለቀ ጥናትና ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ ምሁራንን መነሻ የሚያመላክትና የሚያነሳሳ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
«ቅኔ የግእዝ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ» በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል መምህር እና ተመራማሪ ዶ/ር ሥርግው ገላው በበኩላቸው፤ የቤተ ክርስቲያንና የሀገሪቱ ሊቃውንት የአብነት ትምህርት ቤቶች በመሆናቸው የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ የቅኔን ትምህርት ማሳደግ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
የቅኔን ትምህርት በማሳደግ የነገይቱን ቤተክርስቲያንና ሀገርን ወደተፈለገው እድገትና ለውጥ ለማድረስ የሚችሉትን የአብነት ትምህርት ቤት ሊቃውንት በተገቢው መንገድ ማዘጋጀት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የቅኔ ትምህርት እንዲስፋፋ ለማድረግ የቅኔ ትምህርት ቤቶችን ወደ ኮሌጅና ዩኒቨርስቲ ደረጃ በማሳደግና ሥርዓተ ትምህርት ሊቀረጽላቸው እንደሚገባም ዶ/ር ሥርግው አስተያየ ታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በዐውደ ጥናት ላይ «ቅኔ በቤተክርስቲያን አገልግሎት» ና «ቅኔ ለመጽሐፍት ትርጓሜ» በሚል ርዕስ ሌሎች ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች የማኅበረ ቅዱሳን ጥናት እና ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪ በመምህር ደሴ ቀለብና በስዋሰው ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር በመጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ የቀረበ ሲሆን፤ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ከተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
የቅኔን ትምህርት ለማሳደግና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ቤተክርስቲያን ሰፊ ድርሻ እንዳላትና ትኩረት ልትሰጠው እንደሚገባ የዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ክቡር አምባሳደር ሙሀሙድ ድሪር እንደገለፁት፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ ወገኖች ለአብነት ትምህርት ቤቶች የሰጡት ትኩረት እጅጉን እንደሚደነቅ ጠቁመው፡፡
ያብነት ትምህርት ቤቶችን በመደገፍ የቅኔን ትምህርት ለማሳደግ የሚመለከታቸው አካላት ጥረታቸው ከዳር ይደርስ ዘንድ የባህልና የቱሪዝም ሚኒስቴር ያላሰለሰ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል፡፡
በሲምፖዝየሙ በተለያዩ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ቅኔ የተዘረፈ ሲሆን «ቅኔ ያብነቱ ፍልስፍና» የተሰኘ ዶክመንተሪ ፊልም ተመርቆ ለእይታ በቅቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በማኅበረ ቅዱሳን የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ዋና ክፍል «በጌጠኛ ቤትህ ልማት ይሁን» በሚል መሪ ቃል ለ10 ቀናት የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ተጠናቀቀ፡፡
ከሐምሌ 18 እስከ 26 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ በዓይነቱም በይዘቱም የተለየ እንደነበረ የገለጹት የማኅበራዊ አገልግሎትና ልማት ዋና ክፍል የቅስቀሳና ገቢ አሰባሳቢ ክፍል ሓላፊ ወ/ሮ ዓለምፀሐይ መሠረት፤ ዐውደ ርእይው በፎቶ ግራፍና በተለያዩ ገላጭ መረጃዎች የተደራጀ በመሆኑ ለመእመኑ ስለ አብነት ትምህርት ቤቶች ወቅታዊ ሁኔታ ግንዛቤን እነደፈጠረ ተናግረዋል፡፡
በዐውደ ርእዩ ላይ ዋና ክፍሉ በ2002 እና 2003 ዓ.ም ገዳማትና አድባራት ላይ የሚያከናውናቸው 12 ፕሮጀክቶች ለዐውደ ርእዩ ተመልካቾች ማስተዋወቁንም ጠቁመዋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
የቃሊቲ ቁስቋም ማርያም ታቦተ ሕግ ባለፈው ጥምቀት ወጥታ ተመልሳ መግባት ፈቃዷ ባለመሆኑ የተፈጠረውን የምእመ ናንና የካህናት ጭንቅ፣ ሐዘን፣ ድንጋጤ በብዙ የሚክስ የደስታ ዕለት፡፡ ሐምሌ 25 ቀን 2001 ዓ.ም፡፡
በዚህ ዕለት ማለዳ ጀምሮ ወደ ደጇ ይጎርፍ የነበረው ምእመን አካባቢውን ጠጠር መጣያ አሳጥቶታል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ጸሎት፣ ምሕላ. . . ሲደረግ ተውሎ ከቀኑ 9፡30 ለሰባት ወራት ከርማ ከነበረችበት ድንኳን በብፁዓን አባቶች፣ በካህናትና በበርካታ ምእመናን ታጅባ የወጣችው ታቦተ ሕግ የምእመናኑን የደስታ ስሜት እጥፍ ድርብ አድርጋው ነበር፡፡
በእልልታው በዝማሬውና በምስጋና ታጅባ ከድንኳኑ አቅራቢያ ወደ ተሠራላት አዲስ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ስታመራ እርኩስ መንፈስ ያደረባቸው ብዙዎች ከተለያየ አቅጣጫ ሲጮሁ፣ ሲንፈራገጡ፣ ሰውነታቸውን ሲንጡ እና እልልታውን ለማወክ ሲጥሩ የተስተዋለበት ይህ አጋጣሚ በእርግጥም የእመቤታችን ክብር ምን ያህል እንደሆነ ለመገንዘብ የሚያስችልም ነበር፡፡
በእመቤታችን ትእዛዝ አቶ ክንፈ ሚካኤል ረታ በተባሉ ምዕመን በተሠራው አዲሱ ሕንፃ ቤተክርስቲያን ዑደት አድርጋ ወደ መንበረ ክብሯ የገባችው ታቦተ ቁስቋም ማርያም ታቦተ መድኃኔዓለም እና ታቦተ ጊዮርጊስንም አስከትላ ነበር፡፡
በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ይህ ዕለት ልዩ ያደረገው ብራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በዋዜማው ዓርብ ምሽት ሦስት ነጫጭ ርግቦች የእመቤታችን ታቦት በከረመበት ድንኳን ላይ ማረፋቸው እና ከዚያ ቀደም ብሎ የንብ መንጋ ድንኳን ውስጥ መክተማቸው ነው፡፡
ዕለት ተዕለት የሕንፃ ቤተክርስቲያኑን ሥራ በመከታተል እመቤታችን ያዘዘቻቸውን የፈጸሙት አቶ ክንፈ ሚካኤል ረታ በዓውደ ምሕረቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፤ «ታቦተ ቁስቋም ማርያም በድንኳን እያለች እኛ ቤታችን አንገባም ብላችሁ ከእርሷ ጋር የቆያችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ ካህናት፣ የሰበካ ጉባኤ አባላትና ምእመናን እንኳን ደስ አላችሁ!» ብለዋል፡፡
መጋቢት 29 ቀን 2001 ዓ.ም ለዮሐንስ አጥቢያ እመቤታችን ተገልጣላቸው ከዚህ ቀደም አስተውለውት ከማያውቁት ቦታ ሕንፃ ቤተክርስቲያኑን እንዲያንጹ ባዘዘቻቸው መሠረት በሁለት ወር ከ 10 ቀናት ውስጥ ሠርተው ያጠናቀቁት እርሳቸው የማያውቋቸው እግዚአብሔር የሚያውቃቸው እየተራዷቸው መሆኑንም አቶ ክንፈ ሚካኤል ተናግረዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ ¬ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት በክብረ በዓሉ ላይ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ከሰጡ በኋላ ባስተላለፉት መልእክት «እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጆቼ ሳይሰባሰቡ፣ እኔ እዚህ መሆኔን ሳያውቁ ሕሊናቸውና መንፈሳቸው ሳይደሰት አልነሳም የማለት ምልክት መስጠቷ እንጂ ድንኳን መክረም እምቢተኝነት አይደለም» ብለዋል፡፡
«ታቦተ ቁስቋም ማርያም አልነሣም ማለቷ የተቸገሩትን ለማማለድ፣ የታመሙትን ለመፈወስና በአካባቢው የምትሠራው ብዙ ተዓምራት እንዳለ ለማሳየት ድንኳን ከርማለች፤ ዛሬ ግን ወጥታ ልጆቿን ባርካለች፤ እንኳን ደስ ያላችሁ!» ያሉት ቅዱስነታቸው፤ ዕለቱ እናታችን ቅድስት ማርያም በየጊዜው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እየተገለጸች ከልጆቿ የምትነጋገርበት ሀገራችን ሀገረ እግዚአብሔር መሆኗን የምንገነዘብበት ዕለት መሆኑን ተና ግረዋል፡፡ ይህ ሥፍራ የቃሊቲ ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም መሆኑንም አብስረዋል፡፡
በዚህ ታሪካዊ ዕለት ከተገኙት ሊቃነ ጳጳሳት ውስጥ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ እና ብፁዕ አቡነ ገብርኤል በሰጡት ትምህርት የቅድስት ድንግል ማርያም ድንቅ ሥራ ተነግሮ የማያልቅ ነው፡፡
«እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሀገራችንና ከሕዝባችን በተአምሯ፣ በበረከቷ ያልተለየችን የአፍ መፍቻ ቋንቋችን ናት» ያሉት ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ ሕዝባችን «ሰአሊ ለነ ቅድስት» የሚለው አጠራሩ አማላጅነቷን የቱን ያህል እንደሚያምንበት ያሳያል ብለዋል፡፡
ታቦተ ቁስቋም በቦታው ድንቅ ተአምር እንዲሠራበት ስለመረጠች ድንኳን መቆየቷን፣ በሰው እጅ ተሠራ ለማለት የሚያዳግት ሕንፃ ቤተክርቲያን በአጭር ጊዜ ተሠርቶ መጠናቀቁ፣ እመቤታችን በተአምሯ የሠራችው መሆኑን እንደሚያሳይ የገለጹት ብፁዕ ነታቸው፤ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑን ያሠሩት ምእመን ዕድለኛ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የእመቤታችንን ተአምር በመንገር ከደጇ ጠፍተው የማያውቁት አገልጋይ አባ ገብረሥላሴ መለሰ በሰጡት አስተያየት «ጸሎተ ምህላችንን ተቀብላ እመቤታችን ፈቃዷን ስለገለጸችልን ደስታችን ወሰን የለውም. . .» ነው ያሉት፡፡
«ሰኔ 25 ቀን 2001 ዓ.ም ታቦተ ቁስቋም ባረፈችበት ድንኳን ውስጥ አንዱን ንብ ተከትለው ጥቂት ንቦች ገቡ፤ ሐምሌ 16 ቀን ጀምሮ ግን ሦስት ቀፎ የሚገመት የንብ መንጋ ወንበሯን ተረክቦ ዛሬ ድረስ ይገኛል፡፡ ይህን ስናይ እመቤታችን ልጆቿን ልትጠራ፣ በረከቷን ልታወርድ መሆኑን ተረዳን፡፡ አዲሱ ሕንፃ ቤተክርስቲያን እንደ ምትገባልንም እምነታችን ሆነ፡፡ እንዳሰብነውም ተሳካ. . .» ያሉት አባ ገብረሥላሴ «ሐምሌ 24 ምሽት ድንኳን ላይ ያረፉት ሦስት እርግቦችም ሌላው ምልክታችን ነበር» ይላሉ፡፡
ጥር 16 ቀን 2001 ዓ.ም ታቦቷን አንግሠው ዳግም ወደ ቤተመቅደስ እንድትገባ ጥረት ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው የቀረው ዛሬ ግን የእመቤታችን ፈቃድ እጅግ ያስደሰታቸው መሪጌታ ቤዛ የሻው «ሐዘናችን በደስታ ተለውጧል፡፡ ይህን ተዓምር ማየቴ ዕድለኛ ነኝ፡፡ ለእመቤታችን ክብር ምስጋና ይግባት» ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ ዕለት በእርግጥም የደስታ ዕለት ነው፡፡ ብዙዎች የሚሰጡት አስተያየት ከደስታ እንባ ጋር ነው፡፡ በዕለቱ እየተጨባበጡ፣ እየተቃቀፉ ደስታቸውን የሚገልጹ በዓውደ ምሕረቱ በእመቤታችን የተደረገላቸውን ተአምር የሚመሰክሩ ብዙዎች ነበሩ፡፡
እሑድ ሐምሌ 26 ቀን 2001 ዓ.ም የቃሊቲ ደብረ ቁስቋም ቅድስት ማርያም ሕንፃ ቤተክርስቲያን ቅዳሴ ቤት ሲከበር እጅግ ከፍተኛ ሕዝብ እንደተገኘም ታውቋል፡፡
ከአዘጋጁ- ባለፈው የጥምቀት በዓል ከቅዱስ ሚካኤል ታቦት ጋር ወደ ጥምቀተ ባሕር ሥፍራ ወጥታ ተመልሳ ወደ ቤተመቅደሷ ሳትገባ በራሷ ፈቃድ ድንኳን ስለከረመችው የቁስቋም ማርያም ታቦት ታሪክ በተከታታይ ስንዘግብ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ወደፊትም በዚሁ ሥፍራ ስለተከናወኑ ገቢረ ተዓምራት የምንገልጽ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር