የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት በአፋን ኦሮሞ

ሐምሌ ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሒዱና አሕዛብን ዅሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ዅሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው›› (ማቴ. ፳፰፥፲፱) ሲል በአምላካዊ ቃሉ ያዘዘውን መሠረት በማድረግና የቅዱሳን ሐዋርያትን ፈለግ በመከተል ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በርካታ ሰባክያንን እያስተማረች በየቦታው ስታሰማራ ኖራለች፤ ወደፊትም ይህንን ተልእኮዋን አጠናክራ ትቀጥላለች፡፡ ምክንያቱም ስብከተ ወንጌል ቃለ እግዚአብሔርን ለማስተማር ብቻ ሳይኾን የሰውን አእምሮ ለማልማት (መልካም አስተሳሰብን ለመገንባት) የሚያስችል ዋነኛው የቤተ ክርስቲያን መሣርያ ነውና፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሥራቿ የዅሉም አምላክ፣ የዅሉም ጌታ፣ የዅሉም መድኀኒት የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነውና እንደ ጌታዋ ዘር፣ ጎሣ፣ ቀለም፣ ጾታ ሳትለይ በተዋሕዶ ሃይማኖት ጥላ ሥር የተሰባሰቡ ምእመናንን በአንድነት ተቀብላ ታስተናግዳቸዋለች፡፡ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መፋጠን በልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፍ የሚሳተፉ ልጆቿም ይህንኑ ዓላማዋን ለማሳካት የመትጋት መንፈሳዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ ‹‹ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆም ያማረ ነው፤›› (መዝ. ፻፴፪፥፩) ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተጻፈው፣ በዓለማዊ ብሂልም ‹‹ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኀኒቱ›› እንደሚባለው በኅብረት በመሰባሰብ የሚፈጸም መንፈሳዊ ተግባር ውጤታማነቱ የሠመረ ነው፡፡

በማኅበር ተሰባስበው መንፈሳዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ማኅበራት መካከል አንዱ የኾነው፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ ክፍተት ለመሸፈን የሚያስችል መንፈሳዊ ዓላማ እና ርእይን ሰንቆ በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተመሠረተው ማኅበረ ቅዱሳንም ለሃያ አምስት ዓመታት ያህል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በትጋት ሲያገለግል እስከ ዛሬ ድረስ ቆይቷል፡፡ ለወደፊቱም እግዚአብሔር እስከፈቀደለት ጊዜ ድረስ አገልግሎት መስጠቱን ይቀጥላል፡፡ በልዩ ልዩ መገናኛ መንገዶች እንደሚገለጸው ማኅበረ ቅዱሳን ከአመሠራረቱ ጀምሮ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን አስፋፍታ፣ መንፈሳዊ ዓላማዋን ከግብ አድርሳ፣ ከችግሮቿ ወጥታ ለሕዝቦቿ መንፈሳዊና ማኅበራዊ የሕይወት ለውጥ ቀዳሚ ሚናዋን እንድትወጣ ለመደገፍ የሚተጋ መንፈሳዊ ማኅበር ነው፡፡

ማኅበሩ በየግቢ ጉባኤያቱ ትምህርተ ሃይማኖትን ከሚያስተምራቸው ወንድሞችና እኅቶች በተጨማሪ ከአባቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር በልዩ ልዩ የአገራችን ክፍሎች የሚገኙ ሰባክያነ ወንጌልን በየቋንቋቸው እያሠለጠነ፣ በአባቶች ቡራኬ እያስመረቀ ለስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲሠማሩ አድርጓል፡፡ በእነዚህ ሰባክያን አገልግሎትም ከሰማንያ አምስት ሺሕ ሰባት መቶ የሚበልጡ በልዩ ልዩ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚኖሩ አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን አግኝተዋል፡፡ በዚህ መልኩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ የሚገኘው ማኅበረ ቅዱሳን በአጠቃላይ በልዩ ልዩ ቋንቋ በርካታ መንፈሳውያን ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ‹‹ይህን ሠርቻለሁ›› ብሎ መናገር ተገቢ ባይኾንም፣ ለቍጥጥር እና ለግምገማ ያመች ዘንድ ማኅበሩ በየጊዜው የአገልግሎት ሪፖርት ያቀርባል፡፡ በዚህ ጽሑፍም በአፋን ኦሮሞ የሚሰጠውን አገልግሎት በሚመለከት አጠር ያለ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ መልእክት ይዘን ቀርበናል፡፡

የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ምእመናን!

ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን ሲጀምር ከነበረበት የሰው ኃይል እና እጥረት አኳያ በአማርኛ ቋንቋ በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በበራሪ ወረቀት፣ በመጻሕፍት፣ በካሴት፣ በምስል ወድምፅ የሚቻለውን ዅሉ መንፈሳዊ ተግባር ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ የምእመናን ፍላጎት እየጨመረ፤ ማኅበሩም በሰው ኃይል እየተጠናከረ በመምጣቱ አገልግሎቱን ይበልጥ አሳድጎ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግርኛ፣ በወላይትኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በመሳሰሉት የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ቋንቋዎች ወንጌልን ለማስተማር በመፋጠን ላይ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በአፋን ኦሮሞ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል፡-

  • በግእዝና አማርኛ ቋንቋዎች የታተሙ የትምህርተ ሃይማኖት እና የጸሎት መጻሕፍትን ወደ አፋን ኦሮሞ አስተርጕሟል፤ ከእነዚህ መካከል የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ ውዳሴ አምላክ እና ሰይፈ ሥላሴ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
  • ሌሎች አዳዲስ መጻሕፍትንም በቋንቋው አዘጋጅቶ አሠራጭቷል፡፡
  • በሦስት ወር አንድ ጊዜ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የምትዘጋጀው ጉባኤ ቃና መጽሔትን ወደ ቋንቋው አስተርጕሞ በየግቢ ጉባኤያቱ አሠራጭቷል፡፡
  • Dhangaa Lubbuu (ዳንጋ ሉቡ) የተሰኘችውን መጽሔት ለዅሉም ክርስቲያን በሚመጥን ዐምድ በየሦስት ወሩ በማዘጋጀት እያሠራጨ ይገኛል፡፡
  • በአፋን ኦሮሞ አራት የመዝሙር አልበሞችን አሠራጭቷል፤ ኦርቶዶክሳዊ የመዝሙር ጥራዝም አሳትሟል፡፡
  • ልዩ ልዩ የቪሲዲ ስብከቶችንና መዝሙሮችን አዘጋጅቶ ለምእመናን እንዲዳረሱ አድርጓል፡፡
  • በክልሉ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን አገልግሎትና ታሪክ የተመለከቱ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን አዘጋጅቶ አሳትሟል፡፡
  • በአፋን ኦሮሞ ለሚያስተምሩ ሰባክያነ ወንጌል በዐሥራ ሦስት ዙር የክረምት ሥልጠና ሲሰጥ ቆይቷል፤ በዚህ ዓመትም ከዘጠና በላይ አገልጋዮችን ለማሠልጠን ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡
  • ከአሁን በፊት በአፋን ኦሮሞ የሚተላለፍ ሳምንታዊ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን መርሐ ግብር እያዘጋጀ ሲያቀርብ የቆየ ሲኾን፣ ለወደፊቱም ይህንኑ ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
  • መካነ ድር ከማዘጋጀት ባሻገር ወቅታዊ ትምህርት የሚሰጥበት ወርኃዊ ጉባኤ በማካሔድም ሕዝበ ክርስቲያኑን በአፋን ኦሮሞ ወንጌልን በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
  • በአገራችን ግቢ ጉባኤያት ካሏቸው ዐርባ ሰባት ማእከላት በሠላሳ ስምንቱ የአፋን ኦሮሞ መርሐ ግብር እንዲኖርና ተማሪዎች በቋንቋቸው ኮርስ እንዲማሩ፣ የጽዋ እና ጸሎት መርሐ ግብራት እንዲያካሔዱ፣ መዝሙራትን እንዲያጠኑና እንዲያቀርቡ አድርጓል፤ በማድረግ ላይም ነው፡፡
  • በተጠኑ የክልሉ ቦታዎች አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤቶችን በመመሥረት አፋን ኦሮሞ የሚችሉ ዲያቆናትና ካህናትን እንዲሁም ሰባክያነ ወንጌልን አስተምሮ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በማሠማራት ላይ ሲኾን ለዚሁም በምዕራብ ወለጋ የሚገኘውን የቂልጡ ካራ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ እና በጅማ ሀገረ ስብከት ሥር ያለውን የአበልቲ ኪዳነ ምሕረት ገዳማት የአብነት ትምህርት ቤቶችን እንደ ማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
  • በግቢ ጉባኤያት የምረቃ መጽሔት ላይ ልዩ ልዩ ትምህርታዊ ጽሑፎችና መልእክቶችን በአፋን ኦሮሞ እያቀረበ ነው፡፡
  • በክልሉ ያሉ ገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች እንዲጠናከሩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ በመተግበር፣ መምህራንና ደቀ መዛሙርትን በመደጎም፣ ቋንቋውን የሚችሉ ዲያቆናትና ካህናት እንዲፈሩ በማደረግ በርካታ የክልሉ ምእመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናት ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ የበኩሉን አስተዋጽዖ አበርክቷል፤ የባሌ፣ የምሥራቅ ሐረርጌና የነገሌ ቦረና አህጉረ ስብከት አብነት ትምህርት ቤቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
  • ከዚሁ ዅሉ ጋርም የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር ሲያዘጋጅ ለኦሮምያ ክልል ቅድሚያ በመስጠት፣ የጉባኤው ተሳታፊዎችን በማስተባበር የገቢ እጥረት ላለባቸው የክልሉ አብያተ ክርስቲያናት በመቶ ሺሕ የሚቈጠር የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በመርሐ ግብሮቹ የሚቀርቡ ትምህርቶችንም በአፋን ኦሮሞ በማስተርጐም ለአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን አቅርቧል፡፡

ማኅበሩ ለወደፊት በአፋን ኦሮሞ ለመሥራት ካቀዳቸው ተግባራት መካከል ከፊሎቹ

  • መንፈሳዊ የቴሌቭዥን እና የሬድዮ መርሐ ግብር ማዘጋጀት፣
  • ወርኃዊ የሬድዮ መጽሔት ማዘጋጀት፣
  • ዕቅበተ እምነት ላይ ትኩረት ያደረጉ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን ማሳተም፣
  • ልዩ ልዩ ቅዱሳት መጻፍትን ወደ አፋን ኦሮሞ ማስተርጐም፣
  • የሕፃናት መጻሕፍትንና መንፈሳዊ ፊልሞችን ማዘጋጀት፣
  • ወጣቶች ምእመናን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ጠንቅቀው እንዲያውቁ የሚያግዙ ማስተማሪያ አፕሊኬሽኖችን ማዘጋጀት ማኅበሩ በዕቅድ የያዛቸው ተግባራት ናቸው፡፡ በተጨማሪም የሬድዮና ቴሌቭዥን መርሐ ግብሮችን መከታተል ለማይችሉ የገጠር ምእመናን የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በሚኖሩበት ቦታ ኾነው ቃለ እግዚአብሔርን እንዲማሩ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድም አለው፡፡

የተወደዳችሁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ምእመናን!

ቤተ ክርስቲያን የሰጠችውን ሓላፊነትና የአባቶችን አደራ ተቀብሎ ወንጌለ መንግሥትን በመላው ዓለም ለማዳረስ የሚተጋው ማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ሥር ያለ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮና መሠረተ እምነት የሚጠብቅና የሚያስጠብቅ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የጸደቀ ደንብ የተሰጠውና በደንቡ መሠረት ብቻ የሚመራ ማኅበር እንጂ ራሱን የቻለ የእምነት ተቋም አይደለም፡፡ አባላቱም ለአንድ መንፈሳዊ ዓላማ ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰቡ የተዋሕዶ ልጆች እንጂ የአንድ አካባቢ ተወላጆችና አንድ ብቻ ቋንቋ ተናጋሪዎች አይደሉም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ምእመናን በሚሰሙት ቋንቋ ዅሉ ቃለ እግዚአብሔርን ተምረው ለመንግሥተ ሰማይ ይበቁ ዘንድ የሚጠበቅበትን መንፈሳዊና አገራዊ ድርሻ በአግባቡ ለመወጣት የሚሠራ፤ በአጠቃላይ ለመንፈሳዊ ተልእኮ የሚፋጠን ማኅበር ነው፡፡

ማኅበሩ በግልጽና በይፋ ከሚፈጽመው መንፈሳዊ አገልግሎት ውጪ በስውር የሚሠራው አንዳችም የተለየ ተልእኮ የለውም፡፡ ምእመናን በሚሰሙት ቋንቋ ቃለ እግዚአብሔርን እንዳይማሩም እንቅፋት አይፈጥርም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሠራርም በፍጹም የለውም፡፡ ማኅበሩ የዅሉንም ሕዝበ ክርስቲያን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ አሟልቻለሁ ባይልም ምእመናን በየቋንቋቸው ወንልን እንዳይማሩ አለማድረጉን፤ ለወደፊትም እንደዚህ ዓይነት ተልእኮ የሚፈጽም ማኅበር አለመኾኑን ቅዱስ ሲኖዶስ እና መላው ሕዝበ ክርስቲያን እንዲገነዘቡለት ያሳስባል፡፡ በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን በኦሮምያ ለሚገኙ ምእመናን ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት ካለው ቁርጠኝነት የተነሣ የአፋን ኦሮሞ ሚዲያ ፕሮጀክት በሚል ስያሜ መርሐ ግብር አቋቁሞ፣ በጀት መድቦ በተጠናከረ መልኩ አገልግሎቱን በመፈጸም ላይ መኾኑን በዚህ አጋጣሚ እየገለጸ፣ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎት ከዚህ በበለጠ መልኩ እንዲቀላጠፍ ለማድረግ ይቻል ዘንድም መላው ሕዝበ ክርስቲያን ማኅበሩ የሚሰጠውን አገልግሎት ቀርባችሁ ደግፉ ሲል በእግዚአብሔር ስም መንፈሳዊ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

 ማኅበረ ቅዱሳን

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ፣ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲኾን በፍትሕ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የዘንድሮውን መደበኛ የረክበ ካህናት ስብሰባ ከበዓሉ ዋዜማ ከግንቦት ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ ለ፲፬ ቀናት ያህል ሲወያይ ሰንብቷል፡፡

በምልዓተ ጉባኤው የተደረገውን የመክፈቻ ንግግር በተመለከተ፡-

  • በቤተ ክርስቲያኒቱ የሥራ ዘርፍ ዙሪያ እየተሠሩ ያሉትን ማኅበራውያን ተግባራት የዳሰሰ፤
  • በአገራችን አንዳንድ አካባቢ በዝናም እጥረት ምክንያት ድርቅ ባስከተለው ችግር ለተጎዱ ወገኖች ሊደረግ የሚገባውን ሰብአዊ አገልግሎት ያገናዘበ፤
  • በአገራችንና በቤተ ክርስቲያናችን ዅለንተናዊ ዕድገት የሚበጀውን በማመቻቸት በዅሉም አቅጣጫ ያለው ኅብረተሰብ የሥራ ተነሳሽነቱን በበለጠ አጐልብቶ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችል መልእክት መኾኑን ምልዓተ ጉባኤው ተመልክቶ ለተላለፈው አጠቃላይ መመሪያ ትኵረት ሰጥቶ በቀረበው አጀንዳ ከተወያየ በኋላ በርከት ያሉ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፤

፩. ከፍ ብሎ እንደ ተገለጸው ዅሉ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በአንዳንድ አካባቢ በተከሠተው ድርቅ ለረኃብ የተጋለጡ ወገኖቻችንን ለመታደግ መንግሥት እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት በመገንዘብ፣ ቤተ ክርስቲያናችንም የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሓላፊነቱን ወስዶ ከርዳታ ሰጪዎች ጋር በመነጋገርና በማስተባበር የሚገኘውን ርዳታ ድርቁ የተከሠተባቸው የክልል መሪዎች በሚሰጡት አቅጣጫ እንዲፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፪. ከቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓት ውጭ በመደራጀት የኑፋቄ ትምህርት ሲያካሒድ የበረው ‹አሰግድ ሣህሉ› የተባለ ግለሰብ ለበርካታ ዓመታት የኑፋቄ ትምህርት ሲያሠራጭ መኖሩ በመረጃ የተደረሰበትና የተረጋገጠበት በመኾኑ ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እንዳያስተምር፣ ምእመናንም እንዳይከተሉት ምልዓተ ጉባኤው ከግንቦት ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጀምሮ ቃለ ውግዘት አስተላልፏል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ውጭ ምንም ዓይነት ፈቃድ ሳያገኙ በተመሳሳይ ኹኔታ አዳራሽ ተከራይተው በቤተ ክርስቲያናችን ስም ‹‹ወንጌል እናስተምራለን፤ ዝማሬ እናሰማለን›› የሚሉ ሕገ ወጦች ከእንዲህ ዓይነት ድርጊታቸው እንዲታረሙ፤ ምእመናንንም በተለይ ወጣቱ ትውልድ እንዲህ ዓይነት ሕገ ወጦችን ከመከተልና ሃይማኖታችሁን ከሚበርዙ ኃይሎች እንድትጠበቁ ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡

፫. የቤተ ክርስቱያኒቱ መገናኛ ብዙኃን ጉዳይን በተመለከተ የሚዲያ ድርጅቱ በሰው ኃይል እንዲጠናከር፤ የሚያስተላልፋቸው መልእክቶችም ጥራት እንዲኖራቸው ማድረግ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተነጋግሮ፣ ለ፳፻፲ በጀት ዓመት ብር 12,000,000.00 (ዐሥራ ሁለት ሚሊዮን ብር) ተፈቅዶለት በበጀት ተጠናክሮ ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቷል፡፡

፬. በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስለ ዴር ሡልጣን ገዳም ችግር ጉዳይ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ ችግሩን አስመልክቶ መፍትሔ ማግኘት እንዲቻል ለኢፊድሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ለእስራኤል ኢምባሲ እና በእስራኤል ለኢትዮጵያ ኢምባሲ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው ተወስኗል፡፡

፭. ሚያዝያ ፲ ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳርና በፍትሕ መንፈሳዊ መጽሐፍ ላይ ‹‹ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው ሊቃውንት ጳጳሳትን አይሹሙ›› የሚለው በ፯ተኛው መቶ ዓመት ግብጻውያን አባቶች በሥርዋጽ ያስገቡት ሕገ ወጥ ጽሑፍ ስለ ኾነ ምልዓተ ጉባኤው ተነጋግሮ ጽሑፉ የአገራችንና የቤተ ክርስቲያንን ክብር የሚነካ ኾኖ በመገኘቱ ከአሁን በኋላ ጽሑፉ እንዳይነበብ፤ ከመጻሕፍቱም ውስጥ እንዲወጣ፤ ወደፊትም በሚታተሙ መጻሕፍት እንዳይገባ ተወስኗል፡፡

፮. ሥርዓተ ምንኵስና እና ሥልጣነ ክህነት አሰጣጥን አስመልክቶ ቀደም ባሉት ዓመታት የተወሰኑ ውሳኔዎች በአብዛኛው አፈጻጸም ላይ ችግሮች እንዳሉ ስለሚታይ ወደፊት የሚወሰነው ተጠብቆ እንዲሠራበት ጉባኤው ተስማምቷል፡፡

፯. ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ሰባክያንና አጥማቂዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ አገልግሎት እንዳይሰጡ የተወሰነ ቢኾንም ውሳኔው መከበር ስላልቻለ፤ ችግሮችም በስፋት የሚታዩ ስለ ኾነ አሁንም በውሳኔው መሠረት የቁጥጥሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተስማምቷል፡፡

፰. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም በአዲስ አበባም ኾነ በየአህጉረ ስብከቱ በማኅበር ተደራጅተው ገዳማትን በማስጐብኘትም ኾነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም በልዩ ልዩ አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱ ማኅበራትን መቆጣጠር የሚቻልበት የማኅበራት ማደራጃ ደንብ እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

፱. የቤተ ክርስቲያኒቱ ዅለንተናዊው ችግር በባለሙያ ተጠንቶ እንዲቀርብ ቀደም ሲል በተወሰነው መሠረት ጥናቱ ተጠናቆ ከቀረበ በኋላ ጉባኤው ተመልክቶ የሕግ ባለሙያዎችና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ባሉበት ተመርምሮና ተስተካክሎ ለጥቅምቱ ፳፻፲ ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡

፲. የስብከተ ወንጌል መስፋፋት፤ የሰንበት ት/ቤትና የመንፈሳውያን ኮሌጆች መጠናከር፤ የአብነት ት/ቤቶች መደራጀትና በበጀት እንዲደገፉ ማድረግ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዓይነተኛ ተግባር መኾኑን ምልዓተ ጉባኤው ተነጋግሮ፣ በስብከተ ወንጌል ትምህርት አሰጣጥና በመንፈሳውያን ኮሌጆች ደቀ መዛሙርት አያያዝ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡

፲፩. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የኾነውን ሀብትና ቅርስ በባለቤትነት መጠበቅና ማስጠበቅ እንዲቻል ተዘጋጅቶ የቀረበውን ጥናት ቅዱስ ሲኖዶስ ካዳመጠና ከተወያየበት በኋላ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት በቅድሚያ በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲቀርብ ወስኗል፡፡

፲፪. ብፁዓን አበው በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት የሚመደቡ ዕጩዎች ቆሞሳት ምርጫን በተመለከተ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ ቆሞሳትን በማወዳደር ፲፮ ቆሞሳት ለኤጲስ ቆጶስነት ተመርጠዋል፤ በዓለ ሢመታቸውም ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም እንዲፈጸም ተወስኗል፡፡

፲፫. ኤጲስ ቆጶሳት የሌሉባቸውን የውጭ አህጉረ ስብከት በተመለከተም በጥቅምቱ ፳፻፲ ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እየታየና እየተጠና ብፁዓን አበው እንዲመደቡባቸው ለማድረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡

፲፬. በኦሮምያ ክልል በሰባት ዞኖች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ‹‹መንፈሳዊውን ትምህርት በቋንቋችን እንዳንማር ማኅበረ ቅዱሳን በደል አድርሶብናል›› በሚል ባቀረቡት አቤቱታ ዩንቨርሲቲዎቹ ያሉበት አህጉረ ስብከት ጉዳዩን ግራና ቀኝ አጣርተውና ተመልክተው መፍትሔ እንዲሰጡና ውጤቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተገለጹት የውሳኔ ነጥቦችና በሌሎችም ዐበይት ጉዳዮች ላይ ለ፲፬ ቀናት ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና

ሕዝቦቿን ይባርክ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤

አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የ፳፻፱ ዓ.ም ርክበ ካህናትን አስመልክቶ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተበረከተ ቃለ ምዕዳን  

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

‹‹ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ ወኵሎ መራዕየ ዘሀሎ ኀቤክሙ፤ አሁንም ራሳችሁንና በእናንተ ሥር ያለውን መንጋ ዅሉ ጠብቁ፤›› (ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

መዋዕለ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞና ከበዓለ ትንሣኤው አድርሶ፣ እንደዚሁም ዅላችንን ከየሀገረ ስብከታችን አሰባስቦ በዚህ ዓመታዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በአንድነት ስለሰበሰበን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይኹን፤ እናንተም እንኳን በደኅና መጣችሁ!

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ከላይ የተጠቀሰው ኃይለ ቃል የመንጋው እረኞች የኾን ዅሉ በቃለ እግዚአብሔር ጐልብተን፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቃኝተን ራሳችንንና ምእመናንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን የሚያመለክት የእግዚአብሔር ታላቅ የጥሪ ቃል ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትና ቀደምት ቅዱሳን አበው የሥልጣነ ክህነትና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ በቋሚነትና በመደበኛነት እንደዚሁም ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አስፈላጊ ኾኖ በተገኘ ጊዜ ዅሉ እየተሰበሰበ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ እንዲገመግም፣ እንዲያጠና እና መፍትሔ እንዲሰጥ መደንጋጋቸው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡

የጉባኤው መሠረታዊ ዓላማ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ እንደ ተናገረው ከመጀመርያ አንሥቶ ልዩ ልዩ ፈተና ተለይቶአት የማያውቅ ቤተ ክርስቲያን በመከራው ጽናት ተሰቃ ወይም ተስፋ ቈርጣ ዓላማዋን እንዳትስት እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ሊዘልቅ የሚችል ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ ለማድረግ እንዲቻል ነው፡፡

ይህም በመኾኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማካይነት ነገራተ ቤተ ክርስቲያንን በጥልቀትና በአስተዋይነት እየተረጐመች፣ እንደዚሁም መንፈስ ቅዱስን መሪ በማድረግና አስፈላጊው መሥዋዕትነትን በመክፈል ከውጭና ከውስጥ የሚሰነዘሩባትን ጥቃቶችን እየተቋቋመች እነሆ በአሸናፊነት ከዘመናችን ደርሳለች፡፡ ይህም ሊኾን የቻለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተቃኙ ቅዱሳን አበው በፈጸሙት ተጋደሎና ወደር የለሽ መሥዋዕትነት እንደ ኾነ አይዘነጋም፡፡

የመንፈሳዊ ጥበቃና ክትትል ተግባር በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ ቀኖና መሠረት በቤተሰብ ደረጃ በነፍስ ወከፍ ጠባቂ ካህን ወይም የነፍስ አባት እንዲኖር የተደረገበት ዐቢይ ምክንያትም የጥበቃውንና የክትትሉን ተግባር አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ነው፡፡ የተግባሩ መነሻም የጌታችን ትምህርትና ትእዛዝ ነው፡፡

እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ሕፃኑንም ወጣቱንም፣ ጐልማሳውንና ሽማግሌውንም አንድ አድርገን እንድንጠብቅና እንድናሰማራ ጌታችን በባሕረ ጥብርያዶስ ‹‹ግልገሎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን ጠብቅ፤›› በማለት ለቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት አዞናል (ዮሐ. ፳፩፥፲፭-፲፯)፡፡ እኛም ትእዛዙንና ሓላፊነቱንም ወደንና ፈቅደን ተቀብለናል፡፡

ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን የሚካሔደውና ረክበ ካህናት ተብሎ የሚታወቀው፣ በዛሬው ዕለት የምንጀምረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም መሠረቱ ይህ የባሕረ ጥብርያዶስ የጥበቃ ትእዛዝና ትምህርት እንደ ኾነ ይታወቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዐቢይ እና ዋና ተልእኮም ዐቂበ ምእመናን እንደ ኾነ በቅዱስ ወንጌል በተደጋጋሚ ተጽፏል፡፡ በመኾኑም ቅዱሳን ሐዋርያትም ኾኑ ቅዱሳን አበው ዋነኛ ተግባራቸው ምእመናንን ማስተማር፣ ማሳመን፣ ማጥመቅ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ማደል፣ ከዚያም ምእመናንን በዕለተ ተዕለት ኑሮአቸው መጠበቅና ክትትል ማድረግ ነበር፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ሐዋርያዊት፣ ህልወተ ኵሉ ወይም በዅሉም ያለች፣ አንዲትና ቅድስት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የሁለት ሺሕ ዘመናት ጉዞዋ አንድነቷ ሳይናጋ፣ ሐዋርያዊ ተልእኮዋ ሳይቋረጥ ለዘመናት የዘለቀችው ካህናት በነፍስ አባትነት እያንዳንዱን ቤተሰብ በመጠበቃቸው፣ በማስተማራቸውና በመከታተላቸው ነው፡፡ ዛሬም ቢኾን እየተስፋፋ ለመጣው የምእመናን ቅሰጣ ዋና መከላከያው የነፍስ አባትን ተልእኮ ማእከል ያደረገ በቤተሰብ ውስጥ የነፍስ ወከፍ ጠበቃ ሲጠናከር ብቻ እንደ ኾነ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

ይህንን የግብረ ኖሎት ሥራ በተፈለገው መጠን ግቡን እንዲመታ በየሀገረ ስብከቱ የካህናት ማሠልጠኛ በማቋቋም፣ ዘመኑን ያገናዘበና በቀላሉ ወደ ተግባር የሚያሸጋግር የሥልጠና መርሐ ግብር በመንደፍ ካህናቱን ከዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ፣ አስተማማኝ ጥበቃ ማረጋገጥ ይኖርብናል፤ ይህንን ተግባር ለማፋጠን የሊቃነ ጳጳሳት ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በከፊል

እንደ እውነቱ ከኾነ ዛሬም ለሃይማኖቱ ተቆርቋሪ የኾነ፣ ለእምነቱ አድርግ የተባለውን የሚያደርግ ሕዝብ እግዚአብሔር አልነሣንም፤ በእኛ በኩል ግን የሚቀር ብዙ ሥራ እንዳለ አይካድም፡፡ ከዚህ አንጻር እተየፈታተነን ያለውን የቅን አገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ክፍተት በፍጥነት አስተካክለን ወደ ሕዝቡ የጥበቃ ተግባር መሠማራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መኾኑን ማስተዋል አለብን፡፡

አሁን ባለው የጥበቃና የክትትል ክፍተት ቍጥር በርከት ያለ ወጣት እየኮበለለ እንደ ኾነ ማወቅ አለብን፤ አለሁ የሚለው ወጣትም ቢኾን ኦርቶዶክሳዊ መርሕና ቀኖናን በቅጡ ባለማወቁ ሲደናገርና የተቃራኒ አካላት ባህልና ሥርዓትን ሲደበላልቅ ይታያል፡፡ ይህ ዅሉ ሊኾን የቻለው ጌታችን እንዳስተማረንና እንዳዘዘን ከግልገልነት ዕድሜ ጀምረን ወጣቱን ባለመጠበቃችንና ባለመከታተላችን እንደ ኾነ ሊሠመርበት ይገባል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ስኖዶስ አባላት

በቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሰጪነትና የበላይ ተቆጣጣሪነት የሚመራው የግብረ ኖሎት ጥበቃ የምእመናንን ዅለንተናዊ ሕይወት የሚያካልል ሊኾን ይገባል፡፡ ምእመናን ለሃይማኖታቸው የሚታመኑ፤ ለአገራቸው ዕድገትና ልማት የሚቆረቆሩ፤ በአንድነት፣ በስምምነትና በፍቅር የመኖር ጥቅምን የሚገነዘቡ፤ በማንነታቸውና በባህላቸው፣ በታሪካቸውና በእምነታቸው የሚኮሩ በአጠቃላይ የተስተካከለ መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ሰብእናን የተላበሱ እንዲኾኑ በርትተን የማስተማር፣ የመጠበቅና የመከታተል ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ሓላፊነት አለብን፤ ይህም በታቀደ፣ በተደራጀ፣ በተጠናከረና ተከታታይነት ባለው የአፈጻጸም ሥልት ሊከናወን ይገባል፡፡

በመጨረሻም

በዚህ ዓመታዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የቀረቡትን አጀንዳዎች ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት በማስተዋልና ለቤተ ክርስቲያናችን በሚበጅ መልኩ በማጤን፣ እንደዚሁም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና መጠበቅ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሐዋርያዊ ግዳጁን እንዲወጣ እያሳሰብን የሁለት ሺህ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መጀመሩን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን!

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም፤

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡

የ፳፻፱ ዓ.ም በዓለ ትንሣኤን አስመልክቶ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የተበረከተ ቃለ ምዕዳን

img_0028

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ሚያዝያ ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በዓለ ትንሣኤ ቅድስት ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

  • በአገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
  • ከአገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
  • የአገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
  • በሕመም ምክንያት በየጠበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
  • እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ኾናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

በትንሣኤው ኃይል በመቃብር ውስጥ በስብሶ መቅረትን ሽሮ ትንሣኤ ሙታንን ያበሠረ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ!!

‹‹ወሰበረ ኆኃተ ብርት ወቀጥቀጠ መናሥግተ ዘሐፂን፤ የናስ ደጆችን ሰባበረ፡፡ የብረት መወርወሪያዎችንም ቀጥቅጦ ቈራረጠ፤›› (መዝ. ፻፯፥፲፮)፡፡

ይህ አምላካዊ ኃይለ ቃል ወልደ እግዚአብሔር የኾነ ኢየሱስ ክርስቶስ በመሥዋዕትነቱ ብቃት እንደ ናስ የጠነከሩትን የኃጢአት ደጆች እንደሚሰባብር፤ እንደ ብረት የጸኑትን የሞት ብረቶች ቀጥቅጦ በመቈራረጥ እንሚያስወግድ መንፈስ ቅዱስ በዳዊት አንደበት የተናገረው ቃለ ብሥራት ነው፡፡ የኃይለ ቃሉ ምሥጢራዊ ይዘት በጠንካራ ነገር የተገዙና በጽኑ መወርወሪያዎች ክርችም ብለው የተዘጉ ደጆች መኖራቸውን ጠቁሞ እነዚህን ሰባብሮና ቀጥቅጦ በሩን የሚከፍት አንድ ኃያል መሢሕ እንደሚመጣ የሚያመለክት ነው፡፡

በመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደምናነበው የሰው መኖሪያ የነበረው ገነተ ኤዶም በኃጢአተ ሰብእ ምክንያት በፍትሐ እግዚአብሔር ሲዘጋ፣ በሰይፈ ነበልባል እንደ ተከረቸመ፤ ኪሩባውያን ኃይላትም በጥበቃ እንደ ተመደቡበት በግልጽ ተመዝግቦአል፡፡ ይህ የጽድቅ የክብርና የሕይወት ደጅ በዚህ ኹኔታ ሲዘጋ፣ ለሰው ልጅ የቀረለት መኖሪያ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ የተዘጋጀው፤ እሳቱ የማይጠፋ፣ ትሉ የማያንቀላፋ የእቶነ እሳት ከተማ ነበረ፡፡

ለመለኮታዊ ሱታፌና ለዘለዓለማዊ ሕይወት ታድሎ የነበረው የሰው ልጅ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት ያህል የተጋዘው ከላይ በተጠቀሰው የዲያብሎስ ከተማ ነበር፡፡ የዚህ ከተማ ደጆችና በሮች፣ መዝጊያዎችና መወርወሪያዎች ኃጢአት፣ ፍትሐ ኵነኔ እና ሞተ ነፍስ ወሥጋ ነበሩ፡፡ የሰው ልጅ ኃጢአትን ስለ ሠራ እግዚአብሔር የቅጣት ፍርድን ፈረደበት፤ ቅጣቱም የነፍስና የሥጋ ሞት ነበረ፡፡ እነዚህ ነገሮች እርስበርስ እንደ ሰንሰለት ተያይዘው የዲያብሎስን ከተማ የናስና የብረት ያህል ጠንካራ ደጅ እንዲኾን አድርገውታል፡፡

ይህንን በር ሰብሮና ፈልቅቆ የሰዎችን ነፍሳት ከዲያብሎስ ከተማ መዞ ለማውጣት ለፍጡር ፈጽሞ የማይቻል ነበረ፤ ሦስቱም ነገሮች ከፍጡራን ዓቅም በላይ በመኾናቸው አምላካዊ ኃይል የግድ አስፈላጊ ኾነ፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን ሥጋችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም በመገለጥ እኛ ከኃጢአት፣ ከፍትሐ ኵነኔ እና ከሞት ነፍስ የምንድንበት መንገድ እርሱ ብቻ መኾኑን በአጽንዖት አስተማረ፡፡

በመጨረሻም እንደ ትምህርቱና እንደ ቃሉ በመስቀሉ ኃይል ወይም በመሥዋዕትነቱ  ብቃት ሦስቱ ነገሮች ማለትም ኃጢአት ፍትሐ ኵነኔ እና ሞተ ነፍስ ከሰው ጫንቃ ላይ እንዲወገዱ አደረገ፡፡ ለሰው የማይቻል የነበረ ይህ ግብረ አድኅኖ፣ በተዋሕዶ አምላክም ሰውም ለኾነ ለጌታችን ለአምላካችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚቻል ነበርና በእርሱ መሥዋዕትነት እውን ኾነ፡፡

ጥንቱንም ለሰው ልጅ ሕይወትና ክብር ጠንቆች የነበሩ እነዚህ ሦስቱ ነበሩና እነርሱ ተሰባብረውና ተቀጥቅጠው ሲወገዱ በሲኦል ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ነፍሳት በአጠቃላይ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ወደ ተዘጋጀላቸው ወደ መንግሥተ እግዚአብሔር ተመልሰው ገቡ፡፡ ከክርስቶስ ሞት በኋላ የነፍሳተ ሰብእ ጉዞ ወደ ዲያብሎስ ከተማ ወደ ሲኦል መኾኑ ቀርቶ ወደ እግዚአብሔር ከተማ ወደ ጽዮን መንግሥተ ሰማያት ኾነ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

እኛ ኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤን ከምንም በላይ በላቀ ኹኔታ የምናከብርበት ምክንያት ኃጢአት፣ ፍትሐ ኵነኔ እና ሞተ ነፍስ ወዲያ ተሽቀንጥረው በምትካቸው በክርስቶስ ቤዛነት ጽድቅን፣ ይቅርታንና ሕይወተ ነፍስን የተቀዳጀንበትና ከድል ዅሉ የበለጠ የድል ቀን በመኾኑ ነው፡፡ ዅላችንም መገንዘብ ያለብን ዓቢይ ነገር የክርስቶስ ድርጊቶች በሙሉ ለሰው ድኅነት ሲባል ብቻ የተደረጉ እንጂ ለእግዚአብሔር የሚፈይዱት አንዳች ምክንያት የሌላቸው መኾኑን ነው፤ ይህም ማለት በክርስቶስ የተፈጸሙ ድርጊቶች በሙሉ ለእኛ ሲባል የተደረጉ መኾናቸውን መገንዘብ አለብን ማለት ነው፡፡

ክርስቶስ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ ተነሣ ሲባል፣ እኛ ተሰቀልን፤ ሞትን፤ ተቀበርን፤ ተነሣን ማለት እንደ ኾነ ልብ ብለን ልናስተውል ይገባል፡፡ እኛ ተሰቅለን ሞተንና ተቀብረን የኃጢአታችንን ዕዳ የመክፈል ዓቅም ስላጣን ለእኛ ያልተቻለውን ጌታችን ስለ እኛ ብሎ፣ በእኛ ምትክ ኾኖ ለኃጢአታችን መከፈል የነበረበትን ዋጋ ዅሉ ከፍሎ አድኖናልና ነው፡፡ እኛ በክርስቶስ ቤዛነት ነጻነታችንን ተቀዳጅተን ወደ እግዚአብሔ መንግሥት ዳግመኛ መግባት የቻልነው ክርስቶስ የከፈለው መሥዋዕትነት ለእኛ ተብሎ፣ ስለ እኛ የተደረገ በመኾኑ ነው፡፡

የክርስቶስ ትንሣኤ የእርሱ ትንሣኤ ብቻ እንደ ኾነ አድርገን የምንገነዘብ ከኾነ ታላቅ ስሕተትም ነው፤ ኃጢአት፣ ኵነኔ እና ሞተ ነፍስ የሌለበት እርሱማ ምን ትንሣኤ ያስፈልገዋል? ትንሣኤ ለሚያስፈልገን ለእኛ ተነሣልን እንጂ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን አስመልክቶ ሲያስተምር፣ ‹‹እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጸጋ ስለ ኾነ በኢየሱስ ክርስቶስ አስነሣን፡፡ ከእርሱ ጋርም በሰማያዊ ሥፍራ አስቀመጠን፤›› ብሎአል (ኤፌ. ፪፥፬-፯)፡፡ ከዚህ አኳያ የቀን ጉዳይ ካልኾነ በቀር የትንሣኤያችን ጉዳይ በክርስቶስ ትንሣኤ የተረጋገጠና ያለቀለት ነገር እንደ ኾነ ማስተዋል፣ መገንዘብ፣ መረዳትና ማመን ይገባናል፡፡

የጌታችን ትንሣኤ ለሰው ልጅ ተብሎ የተደረገ በመኾኑ የእኛ ትንሣኤ ነው ብለን ዅሌም መውሰድና መቀበል አለብን፤ ምክንያቱም የክርስቶስ ትንሣኤ የመጨረሻ ግቡ የሰው ልጆች ትንሣኤን ማረጋገጥ ነውና፡፡ የትንሣኤ ዕድል በክርስቶስ ቤዛነት ለዅሉም ተሰጥቶአል፤ አዋጁም ሕጉም በክርስቶስ ትንሣኤ ጸድቆአል፡፡ የቀረ ነገር ቢኖር የመጨረሻው ተግባራዊ ፍጻሜ ነው፤ እርሱም ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ስለ ኾነ ወደዚያው በእምነትና በሥነ ምግባር መገስገስ ነው፡፡ ሰውን ለዚህ ዐቢይ ጸጋና ዕድል ላበቃ ለእግዚአብሔር አምላካችን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይኹን፡፡

      የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራውና ያስተማረው ዅሉ ምን ለማግኘት ነበረ? ተብሎ ቢጠየቅ በአጭር ዐረፍተ ነገር ‹‹ሰውን ለማዳን ነዋ!›› ብሎ መመለስ ይቻላል፡፡ እውነቱም ሐቁም ይህና ይህ ብቻ ነው፡፡ ይህን ያህል ውጣ ውረድ፣ ይህን ያህል ዋጋ ያስከፈለ የሰው መዳን በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ተፈላጊ እንደ ኾነ በአድናቆት መመልከትና መቀበል ታላቅ አስተዋይነት ነው፡፡

በዚህ ሰውን የማዳን የእግዚአብሔር ክንውን እኛ ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ለመኾን በቅተናል፤ ልጆቹም ኾነናል፡፡ ታድያ ልጅ በጠባይም፣ በመልክም፣ በሥራም አባቱን ቢመስል ጌጥም የክብር ክብርም ነውና በዅሉም ነገር አባታችንን መከተልና መምሰል ከእኛ ይጠበቃል፡፡ እግዚአብሔር አባታችን እንደ መኾኑ፣ እኛም ልጆቹ እንደ መኾናችን መጠን የአባታችንን ተቀዳሚ፣ መደበኛና ቀዋሚ ሥራ የኾነውን ሰውን የማዳን ሥራ ሳናቋርጥ የማስቀጠል ግዴታ አለብን፡፡

ዛሬም ዓለማችን የሚያድናት፣ እስከ ሞት ድረስም ደርሶ ቤዛ የሚኾናት፣ ሰላምንና ነጻነትን የሚያቀዳጃት የእግዚአብሔርን ልጅ ትፈልጋለች፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ከመቃብር በመነሣትና ሙታንን በማስነሣት ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ጌታችን ከመሞቱና ከመነሣቱ በፊት ብዙ ሰዎችን ከረኃብ፣ ከበሽታ፣ ከሥነ ልቡና እና ውድቀት አስነሥቷል፤ ከተሳሳተ አመለካከት፣ ከጭካኔ ከመለያየት አባዜም በተአምራትም በትምህርትም አድኗል፡፡ ጌታችን ሰውን ለማዳን ሥራ በእርሱ ብቻ ተሠርቶ እንዲቀር አላደረገም፤ እኛም እንድንሠራውና እንድንፈጽመው አዘዘን እንጂ፡፡

ከዚህ አንጻር በክርስቶስ ዘመን እንደ ነበረው ዅሉ ዛሬም ብዙ በሽተኞች የሚያድናቸው አጥተው በየጎዳናው፣ በየሰፈሩ፣ በየመንገዱ ወድቀው ይሰቃያሉ፤ እነዚህን ማን ያድናቸው? የተመጣጠነና በቂ ምግብ አጥተው ብዙ ሕፃናት፣ እናቶችና አረጋውያን በረኃብ አለንጋ ይገረፋሉ፤ ኅብስቱን አበርክቶ እነሱን ማን ይመግባቸው? በተሳሳተ አመለካከት ለሥነ ልቡና ውድቀት፣ ለቀቢፀ ተስፋ እንደዚሁም ለስሑት ትምህርተ ሃይማኖት ተጋልጠው ሃይማኖታቸውንና ታሪካቸውን በመፃረር የሚገኙ ብዙ ናቸው፤ እነዚህን ማን አስተምሮ ወደ እውነቱ ይመልሳቸው? በእግዚአብሔር ዘንድ እነዚህን ሥራዎች መሥራትና ማስተካከል የሕዝበ ክርስቲያኑና የመምህራነ ወንጌል ግዴታዎች ናቸው፡፡

በማኅበረሰቡ ሥር ሰደውና ተስፋፍተው የሚታዩትን እነዚህን መሰል ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ችግሮች በወሳኝነት ለመቋቋም ትምህርትና ልማት መተኪያ የሌለውን ሚና ይጫወታሉ፤ ለአገራችን ደህንነት መወገድ ቍልፍ መፍትሔ ሃይማኖትና ልማትን አጣምሮ ለመያዝና በእነርሱ ጸንቶ መኖር አማራጭ የሌለው ነው፡፡ ከእነዚህ ውጭ የኾነ ኑሮ ምንም ቢኾን ምሉእ አይደለም፤ ጣዕምም የለውም፡፡ የሰውን ዅለንተናዊ ሕይወት ለማዳን ሁለቱንም በተግባር መተርጐም ያስፈልጋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በእነዚህ ነገሮች የታደለች እንደ ነበረችና እነዚህን አጣምራ በመያዝ የት ደርሳ እንደ ነበር በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የሚታዩና የማይታዩ መረጃዎች ምስክርነታቸውን በመስጠት ዛሬም አልተገቱም፡፡ በአሁኑ ጊዜ አገራችን የተያያዘችውን የልማትና የሰላም ጉዞ አጠናክራ እስከ ቀጠለች ድረስ ሕሙማን የሚፈወሱባት፣ ሩኁባን ጠግበው የሚኖሩባት፣ በመንፈሳዊና በዘመናዊ ዕውቀት የበለጸጉ ዜጎች የሚታዩባት አገር የማትኾንበት ምክንያት ምንም የለም፡፡

መላው የአገራችን ሕዝቦች በኑሮአቸውና በሕይወታቸው መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚችሉት በሌላ ሳይኾን፣ እነርሱ ራሳቸው እንደ ቀድሞ አባቶቻቸው በራስ በመተማመንና በልበ ሙሉነት፣ በትጋትና በቅንነት፣ በፍቅርና በስምምነት፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት፣ በሰላምና በአንድነት፣ በመቻቻልና በአብሮነት ኾነው በሚያስመዘግቡት የልማት ውጤት እንደ ኾነ መርሳት የለባቸውም፡፡ አገርን ለማልማትና የጠላትን ጥቃት በብቃት ለመመከት በአንድነት ኾኖ ከመታገል የተሻለ አማራጭ የለም፤ ስለዚህ ሕዝባችን እነዚህን እስከ መቼውም ቢኾን በንቃት ሊከታተላቸውና ሊጠብቃቸው ይገባል፡፡ በአእምሮ የላቁ ኾኖ መገኘት በራሱ እውነተኛ ትንሣኤ ነውና፡፡

በመጨረሻም

የጌታችን ትንሣኤ ሰውን የማዳን የእግዚአብሔር ዓላማን ያሳካ ፍጻሜ እንደ ኾነ ዅሉ የትንሣኤ ልጆች የኾንን እኛም ሰውን ለማዳን በሚደረገው መንፈሳዊና ልማታዊ ርብርቦሽ ተሳትፏችንን አጠናክረን እንድንቀጥል መንፈሳዊና አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዓለ ትንሣኤ ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ዘሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ሚያዚያ ፰ ቀን ፳፻ወ፱ ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

የ፳፻፱ ዓ.ም ዓቢይ ጾም መግቢያን በማስመልከት ቅዱስ ፓትርያርኩ የሰጡት ቃለ ምዕዳን

የካቲት ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

%e1%8d%93%e1%89%b5%e1%88%ad%e1%8b%ab%e1%88%ad%e1%8a%ad

የተወደዳችሁ ምእመናን! የ፳፻፱ ዓ.ም ዓቢይ ጾም የካቲት ፲፫ ቀን ይገባል፡፡ የጾሙን መግባት በማስመልከትም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የካቲት ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ጠዋት የጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የማኅበረ ቅዱሳን፣ የመንግሥት እና የግል መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በተገኙበት በጽሕፈት ቤታቸው ቃለ ምዕዳን የሰጡ ሲኾን፣ የቅዱስነታቸውን ሙሉ ቃለ ምዕዳን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘተናገረ በእንተ በአተ ጾም ዓቢይ ዘእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘዕሥራ ምዕት ወተስዐቱ ዓመተ ምሕረት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በአገር ውስጥና በመላው ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ!

ፍጥረቱን በምሕረት፣ በይቅርታና በርኅራኄ የሚጠብቅ፣ የሚመግብና የሚያስተዳድር፣ ከዅሉ በላይ የኾነ ኃያሉ አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት መዋዕለ ጾም ዓቢይ በሰላም አደረሳችሁ!!

‹‹ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ፣ ወኢይትኃፈር ገጽክሙ፤ ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችኋልም፤ ፊታችሁም አያፍርም፤›› (መዝ.፴፬፥፭)፡፡

የሰው ልጅ ከዐራቱ ባሕርያተ ፍጥረት በተገኘ ሥጋዊ ሕይወቱ፣ የዐራቱ ባሕርያት ውጤት የኾኑትን ማለትም እኽልን ውኃን፣ ነፋስንና እሳትን የመሻት ፍላጎቱ የላቀ እንደኾነ ዅሉ፣ ከእግዚአብሔር በተገኘ መንፈሳዊ ሕይወቱም እግዚአብሔርን የመሻት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፡፡

ከእግዚአብሔር የተገኘውን ይህን ሀብተ ተፈጥሮ ከሰው ባሕርይ መለየት የማይቻል በመኾኑ ሰብአዊ ፍጡር ዅሉ ከፈጣሪው ጋር ግንኙነት ለማድረግ ይጓጓል፡፡

ሰው ወደፈጣሪው ለመቅረብ ከሚፈልገው በላይ፣ ፈጣሪም ሰውን በእጅጉ ሊቀርበውና ማደርያው ሊያደርገው ይፈልጋል፤ በመኾኑም ሁለቱም ተፈላላጊ መኾናቸው በሕገ ተፈጥሮም ኾነ በቅዱስ መጽሐፍ የታወቀ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሁለቱም እንዳይቀራረቡ የሚያደርጉ መሠረታውያን ነገሮች እንዳሉ ዅሉ እንዲቀራረቡ የሚያደርጓቸውም አሉ፤ ሁለቱንም ሊያቀራርቡ ከሚችሉት መካከል አንዱ ጾም ነው፡፡

እግዚአብሔር በዅለመናው ንጹሕ ቅዱስ ፍጹምና ክቡር በመኾኑ ለባሕርዩ ከማይስማሙ ድርጊቶችና ከአድራጊዎቻቸው ጋር ግንኙነት ሊያደርግ አይፈቅድም፡፡

ኾኖም ንስሐ ሲገቡና ጥፋታቸውን አምነው ሲጸጸቱ በይቅርታ የሚቀበል ርኅሩኅ፣ መሐሪና ይቅር ባይ አምላክ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ ብሎም ለመዝጋት ንስሐ፣ ጾምና ጸሎት ቊልፍ መሣሪያዎች ናቸው፤ እኛ ክርስቲያኖችም ጾምን የምንጾምበት ዋና ምክንያት ይኸው ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ መንፈሳዊ ኃይል ያስፈልጋል፤ መንፈሳዊ ኃይል የሚገኘው ደግሞ ሥጋዊ ኃይል ሲገታ ነው፡፡ ጾም ይህን በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡

ጾም ኃይለ ሥጋን በመግራት ኃይለ መንፈስ እንዲበረታ ያደርጋል፤ ጾም ራሳችንን ዝቅ አድርገን ለእግዚአብሔር እንድንገዛና ለቃሉ ታዛዥ እንድንኾን ያስችለናል፤ ጾም ሰከን ብለን ስለበደላችን እንድናስብና ለንስሐ እንድንፈጥን ያደርገናል፤ ጾም የእግዚአብሔርን ቸርነት በማሰብ ፍቅሩን እንድናውቅና እንድናመልከው፣ ለሰውም ጥሩ የኾነውን ብቻ እንድናስብ ያደርገናል፡፡

እነዚህ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ሥርፀት ሲያገኙ ወደ እግዚአብሐር የመቅረቡና የመገናኘቱ ዕድል ሰፊ ይኾናል፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ኾነን ስለምንሻው ነገር እግዚአብሔርን ብንጠይቅ መልሱ ፈጣን ይኾናል፡፡ ከዚህ አንጻር የነነዌ ጾም ያስገኘው ፈጣን መልስ ማስረጃችን ነው፡፡ በጾም ኃይል አማካኝነት ከፈጣሪ ጋር የተገናኙ እነሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ ነቢዩ ዳንኤልና ዕዝራም በዚህ ተጠቃሽ መምህሮቻችን ናቸው፡፡

ርኩስ መንፈስን ድል ለማድረግ፣ ሊጀመር የታሰበውን ዓቢይ ተግባር በስኬት ለማጠናቀቅ በጾም ረድኤተ እግዚአብሔርን መጠየቅ አስፈላጊ መኾኑን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተግባርና በትምህርት አሳይቶናል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም ይህን በተግባርና በትምህርት ፈጽመውታል፤ ከዚህ አኳያ ጾምና ሃይማኖት የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መኾናቸውን መገንዘብ አያዳግትም፡፡

በመኾኑም ጾም ራሳችንን ለመቈጣጠር፤ የእግዚአብሔር ታዛዥ ለመኾን፤ ለጥያቄአችን ፈጣን መልስ ለማግኘት፤ ርኩስ መንፈስን ድል ለማድረግ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት የሚያገለግለን ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናን ወምእመናት

የጾም አስፈላጊነትና ውጤታማነት ከጥንት ጀምሮ በነቢያትና በሐዋርያት የታወቀ ነው፤ ከዅሉ በላይ ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ፡- ‹‹በፍጹም ልባችሁ በጾም፣ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፤ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፡፡ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነው፤ ቍጣው የዘገየ፣ ምሕረቱ የበዛ፣ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ፡፡ በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ (ለዩ)፤ ጉባኤውንም አውጁ፡፡ ሕዝቡንም አከማቹ፤ ማኅበሩንም ቀድሱ፤›› ብሎ ጾምን በአዋጅ እንድንጾም አዞናል፤ (ኢዩ.፪፥፲፪-፲፰)፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ርኩስ መንፈስ ሊሸነፍና ድል ሊኾን የሚችለው በጾምና በጸሎት እንደኾነ አስረግጦ አስተምሮናል፤ (ማቴ. ፲፯፥፲፬-፳፩)፡፡

ይኹንና ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋም፣ መልስም፣ ኃይልም ሊያሰጥ የሚችለው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ማለትም እግዚአብሔር ባዘዘው ትእዛዝ መሠረት ሲከናወን መኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም እንዴት ያለ እንደኾነ እርሱ ራሱ እንዲህ ብሎናል፤ ‹‹እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እሥራት ትፈቱ ዘንድ፤ የቀንበርን ጠፍር ትለቁ ዘንድ፤ የተገፉትን አርነት ትሰዱ ዘንድ፤ ቀንበሩን ዅሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራህን ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፤ ስደተኞቹ ድሆችን ወደቤትህ ታገባ ዘንድ፤ የተራቆተውን ብታይ ታለብሰው ዘንድ፤ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሸግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ያበራል፤ ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሔዳል፡፡ የእግዚብሔርም ክብር በላይህ ኾኖ ይጠብቅሃል፤›› ብሎ ፈቃዱን ነግሮናል፤ (ኢሳ.፶፰፥፮-፰)፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

የጾም ዓቢይ ዓላማ ለእግዚአብሔር የሚታዘዝና የተሰበረን ልብ መፍጠር፤ በጾም፣ በጸሎት፣ በንስሐ፣ በስግደት በተመስጦ፣ በአንቃዕድዎ ለእርሱ መታዘዝና መገዛት፤ እርሱንም ማምለክ ነው፡፡

ከዚህም ጋር ጥልን በይቅርታ ማስወገድ፤ ሰላምን በማረጋገጥ ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ ማድረግ፤ ራስን መቈጣጠርና መግዛት፤ ኃይለ ሥጋን መመከት፤ ኃይለ ነፍስን ማጐልበት፤ የእግዚአብሔርን እንጂ የሰውን አለማየት፤ የርኩሳን መናፍስትን ግፊት በመቋቋም ክፉ ምኞትን ድል ማድረግ፤ ቅዱስ ቊርባንን መቀበል፤ ኅሊናን ለእግዚአብሔር መስጠት፤ ያለንን ለነዳያን ከፍለን መመጽወት የመሳሰሉትን ዅሉ ዕለታዊ ተግባራችን በማድረግ ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡

በመጨረሻም

የጾም ዋና ዓላማ ለእግዚአብሔር መታዘዝ እንደ መኾኑ መጠን ምድርን እንድናበጃትና እንድናለማት ያዘዘንን ትእዛዝ ተቀብለን አካባቢያችንን በማልማት አገራችንን ውብና ለኑሮ የተመቸች በማድረግ፤ እንደዚሁም ከኃጢአት መከላከያዎች መካከል ዋናውና አንዱ ያለ ዕረፍት በሥራ መጠመድ ነውና ሕዝቡ ሥራ ሳይፈታ ፈጣሪውን በጾም እያመለከ፣ የተቸገረ ወገኑን ካለው ከፍሎ እየረዳ፣ ልማትንም እያፋጠነ የአገሩንና ሰላምና ፀጥታ እየጠበቀ መዋዕለ ጾሙን እንዲያሳልፍ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

ወርኀ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

የካቲት ፲፫ ቀን ፳፻ወ፱ ዓ.ም.

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

የ፳፻፱ ዓ.ም በዓለ ልደትን በማስመልከት ቅዱስ ፓትርያርኩ የሰጡት ቃለ ምዕዳን

ታኅሣሥ ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

dscn6280

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

 

ቃለ በረከት ዘብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ዘተናገረ በእንተ በዓለ ልደቱ ለእግዚእነ ወአምላክነ ወመድኃኒነ ኢየሱስ ክርስቶስ ሎቱ ስብሐት!!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!

  • በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
  • ከሀገር ውጪ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
  • የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
  • በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
  • እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

እኛን ለማዳን በለበሰው ሥጋ በቤተ ልሔም ተወልዶ በመካላችን የተገኘው፣ በመለኮታዊ ባህርዩ የማይወሰነው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!

“ወበዘርዕከ ይትባረኩ ኵሎሙ አሕዛበ ምድር፤ የምድር አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረከሉ፤” (ዘፍ ፳፪፤ ፲፰)፡፡

በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው በረከት የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ ነው፤ እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት ለሰው ልጅ የሰጠው የመጀመሪያው ጸጋ ብዝኃ በረከት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላል “እግዚአብሔርም ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም፤ የባህርን ዓሣዎችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው” ይላል ፤ (ዘፍ ፩፤ ፳፰)፡፡

ለሰው የተሰጠው በረከት በኃጢአት ምክንያት መሰናክል ቢገጥመውም፣ እግዚአብሔር በፍጡሩ ጨርሶ አይጨክንምና ሙሉና ፍጹም የሆነው በረከት እንደገና ተመልሶ ለሰው ልጅ እንዴት እንደሚሰጥ ለበረከት በጠራቸውና በመረጣቸው ቅዱሳን አበው አማካይነት ሲያስታውቅ ኖሮአል፡፡

በተለይም የበረከት አባት ተብሎ በሚታወቀው በአብርሃም ዘር በኩል መጻኢው በረከት እውን እንደሚሆን “በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባካሉ” ተብሎ በእግዚአብሔር አንደበት በማያሻማ ሁኔታ ተነግሮ ነበር፡፡

ከእውነተኛው በረከት ተራቁታ የቆየችው ዓለመ – ሰብእ፣ እግዚአብሔር በራሱ ቃል የገባላት ዘላቂውና እውነተኛው በረከት እስኪመለስላት ድረስ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በተስፋ ስትጠባበቅ ቆይታለች፡፡

የተናረውን የማያስቀር እግዚአብሔር በረከቱን ለሕዝቡ የሚያድልበት ጊዜ ሲደርስ ቅዱስ መንፈሱን ባሳደረባት ቅድስት እናት በኤልሳቤጥ አንደበት የበረከቱ ሙዳይ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በረከቱ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑንና በረከቱን ለምድር አሕዛብ ሁሉ ሊያድል እንደመጣ “ከሴቶች ሁሉ ተለይተሽ አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማኅፀንሽ ፍሬም የተባከ ነው” ሲል የምሥራቹን ለዓለም አሰማ፤ (ሉቃ ፩፡፵፩-፵፫)፡፡

ቀዳማዊ የሆነ እግዚአብሔር ወልድ በድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በፅንስ ቆይቶ የዛሬ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን በቤተ ልሄም ተወለደ፡፡ ጌታችን በተወለደ ጊዜ የሰማይ ሠራዊት ማለትም መላእክትና የመላእክት አለቆች “ወናሁ ተወልደ ለክሙ መድኅን ዘውእቱ እግዚእ ቡሩክ፤ እነሆ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ የሆነ ጌታ ነው” በማለት የሕጻኑን ማንነት ከገለጹ በኋላ “በሰማያት ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም ሰላም ይሁን፤ ለሰውም በጎ ፈቃድ ይደረግለት” እያሉ የተወለደው ሕጻን ለሰው ልጅ የሚያስገኘውን ሰላምና መልካም በረከት በመግለጽ ደስታቸውን በቃለ መዝሙር በቤተ ልሄም ዙሪያ አስተጋብተዋል፡፡

ከሰው ወገንም ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከእርስዋ ጋር የነበሩ ወገኖች፣ እንደዚሁም በአካባቢው የነበሩ የከብት እረኞች በመላእክት የምስጋና መዝሙር ተሳታፊዎች ነበሩ፤ (ሉቃ ፪፤፰-፳)፡፡

እንግዲህ ከጥንት ጀምሮ በአበው ሲነገርና ሲጠበቅ የነበረው የበረከት ተስፋ በቃልም፣ በመልእክትም፣ በሐሳብም፣ በምሥጢርም ተፋልሶ ሳያጋጥመው፣ ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ፍሰቱና ምሥጢሩ ተጠብቆ በተነገረው መሠረት ተፈጽሞ መገኘቱ፣ የክርስትና ሃይማኖት ምን ያህል አምላካዊ የሆነ ጽኑ መሠረት እንዳለው ያረጋግጣል፡፡

የክርስትና ሃይማኖት መሠረቱ “ባርኮ እባርከከ፤ መባረክን እባርክሃለሁ” ከሚል ተነሥቶ፣ “የአባቴ ቡሩካን መንግሥተ ሰማያትን ትወርሱ ዘንድ ወደኔ ኑ!” በሚል የሚጠናቀቅ፣ መነሻውና መድረሻው በረከት የሆነ ሃይማኖት ነው፡፡

የክርስትና ሃይማኖት “ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም” ከሚል ተነሥቶ “በምድርም ሰላም ይሁን” በሚል ተንደርድሮ፣ በምስጋና፣ በክብርና በሰላም፣ በማያልፍም ሕይወት ዘላለማዊነቱን የሚያውጅ ሃይማኖት ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዕለት ከወደላይ የተላለፈው ዓቢይ መልእክት ሰላምና በረከት በምድር ላይ ሆነ የሚል እንደሆነ ማስተዋል አለብን፡፡

ታላቁ ሊቅና ኢትዮጵያዊው አባት ቅዱስ ያሬድ ስለዚህ በረከት ሲናገር “በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ ሕይወት፤ ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት፤ ወማየ ባህርኒ ኮነት ሐሊበ ወመዓረ፤ ማለትም ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተራሮች የሕይወት እንጀራ ሆኑ፤ የበረሀ ዛፎችም የበረከት እሸትን አፈሩ፤ የባህር ውሀም ወተትና ማር ሆነች” ይላል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ቃለ ዝማሬ ሕያዋኑም ግኡዛኑም ሁሉ በልደተ ክርስቶስ ምክንያት በበረከት እንደ ተንበሸበሹ ይመሰክራል፡፡

ከዚህ አኳያ በበዓለ ልደተ ክርስቶስ የሚበላ እንጀራና የሚጠጣ ውሃ አጥቶ በረኃብና በጥም ተጐሳቊሎ የዋለ አልነበረም ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራውም ወተቱም ማሩም ፍጥረቱ ሁሉ እንደ ፈለገው እየተመገበ በሰላምና በደስታ ቀኑን ሁሉ ማሳለፉን እንገነዘባለን፡፡

የልደተ ክርስቶስ በረከት ገደብ የለሽ መሆኑን ያወቅን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን የምንል ክርስቲየኖች በዚህ ቀን ርቦትና ጠምቶት፣ አዝኖና ተክዞ የሚውል ሰው እንዳይኖር ያለውን በማካፈልና በጋራ በመመገብ የታረዘውን በማልበስ የታመመውን በመጠየቅ የበዓሉን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ገጽታ መጠበቅና ማስጠበቅ ይኖርብናል፡፡

በዓለ ልደተ ክርስቶስ የበረከት ቀን ከመሆኑም ሌላ የዕርቅ፣ የእኩልነትና የአንድነት በዓልም ነው፡፡ ከብዙ ጊዜ መለያየትና መራራቅ በኋላ፣ ፈጣሪ የሰዎችን ሥጋ አካሉ አድርጎ በሰዎች መካከል በአካል መገኘት ከዕርቅ ሁሉ የበለጠ ዕርቅ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡

በዕለተ ልደት ክርስቶስ መላእክትና ሰዎች ፈጣሪያቸው በተወለደበት ዙሪያ ተሰባስበው በእኩልነትና በአንድነት ሲዘምሩና ሲያመሰግኑ ማየትና መስማትም የፍጡራንን እኩለነትና አንድነት ያረጋገጠ ሌላው ክሥተት ነበረ፡፡

ሰማያውያንና ምድራውያን ለሰው ልጅ ህልውና ወሳኝ የሆነውን “ሰላም በምድር ይሁን” እያሉ በአንድ ቃል መዘመራቸውም ለሰማያውያኑም ሆነ ለምድራውያኑ ከሰላም የበለጠ ትልቅ ጸጋ የሌለ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነበረ፡፡

እንዲህም ስለሆነ ከልደተ ክርስቶስ ያልተማርነው ትምህርት የለም ማለት ይቻላል፤ እግዚአብሔር በልደተ ክርስቶስ ዕለት ያስተማረን ብቻ አጥብቀን ብንይዝና ይህንኑ ብንፈጽም ከበቂ በላይ ነው ቢባል ፍጹም እውነት ነው፡፡

ተራራው ሁሉ የሕይወት እንጀራ ሆነ፤ የበረሀ ዛፍ ሁሉ የበረከት እሸት ሆነ፤ የባህር ውሃም ማርና ወተት ሆነች ተብሎ ሲነገር በዓለ ልደተ ክርስቶስ የልማት፣ የዕድገትና የብልፅግና አስተማሪ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

ከዚህ አንጻር ዛሬም ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ተራራው ይልማ፣ በረሀው በደን ይሸፈን፣ ውሃው ከብክለት ድኖ ለምግብነት የሚያገለግሉ ሕይወታውያን ፍጡራን በብዛት ይኑሩበት የሚለው በልማትና በበረከት የተሞላው የልደተ ክርስቶስ አስተምህሮ ነው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን አምላካዊ አስተምህሮ በምልአት ተቀብሎ ወደ ልማት ከተሠማራ በዚያው መጠን በረከቱን በገፍ ያፍሳል፡፡

ከዚህም ጋር “የሺሕ ፍልጥ ማሠሪያው ልጥ” እንደሚባለው የሁሉም ማሠሪያ ሰላም ስለሆነ የድሮ ነጋዴ ለንግድ ሲወጣ ስንቁን በትከሻው ተሸክሞ እንደሚጓዝ ሁሉ፣ ዛሬም የልማት ነጋዴ ሕዝባችን ሰላምን በልቡ ቋጥሮ መጓዝ ይኖርበታል፡፡

ሁሉም ችግሮች ከሰላም በታች መሆናቸውን ሁሉም ማኅበረሳባችን መገንዘብ አለበት፤ ሁሉም ለአንድነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሕ ለወንድማማችነት፣ ለመተማመንና ለመከባበር መስፈን የማያወላውል አቋም ሊይዝ ይገባል፡፡

የቀደሙት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ታላቅ ሀገር እንድትሆን ያበቋት አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ ስለሠሩ ነው፤ ያለ አንድነት ታላቅነትም፣ ኃያልነትም፣ ልማትና ዕድገትም፣ ፈጽሞ እንደማይገኝ ሳይታለም የተፈታ ነውና ሕዝባችን ይህንን በውል ማጤን ይኖርበታል፡፡

በመጨረሻም

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የክርስቶስ መወለድ ዋና ዓላማ መለያየትና መቃቃርን፣ መነታረክንና፣ በጥላቻ ዓይን መተያየትን አስወግዶ በምትኩ ዕርቅን፣ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን በሰው ሁሉ አእምሮ ውስጥ ማስፈን እንደሆነ እናውቃለን፡፡

በመሆኑም ይህ ነገረ ሕይወት ከተሰበከባቸው የዓላማችን ሀገራት ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ በእግዚአብሔር ከተሰጣት የቅድሚያ ኃላፊነት አንጻር በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሁሉ፣ እንደ ድሮው ደማቁ የአንድነት ታሪኳና ተደናቂው ሥልጣኔዋ፣ እንደዚሁም ጽኑ ሰላምዋና ልማቷን ጠብቃ በማስጠበቅ አስተማሪነትዋ ጎልቶ እንዲወጣ “ችግሮች ሁሉ ከሰላም በታች ናቸው” የሚለውን ጠንካራ የሰላም አስተሳሰብ መርሕ በማድረግ ሁሉም በአንድነት፣ በኃለፊነት፣ በቅንነትና በተቈርቋሪነት ሀገሩን እንዲጠብቅና እንዲያለማ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የልደት በዓል ያድርግልን

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክልን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አሜን

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤

ታሕሣሥ ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መጀመርን አስመልክቶ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተሰጠ መግለጫ

ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

020

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ የማኅበረ ቅዱሳን፣ የመንግሥትና የግል መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች በተገኙበት በዛሬው ዕለት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መጀመርን አብሥረዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ የሰጡትን ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤

001

002

ቋሚ ሲኖዶስ በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጠ

በወቅታዊ የአገራችን ጉዳይ ላይ ቋሚ ሲኖዶስ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል፡፡ የመግለጫውን ሙሉ ቃል እንደሚከተለው እናቀርባለን፤

 መስከረም 23 ቀን 2009 ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

‹‹ኅሡ ሰላማ ለሀገር እስመ በሰላመ ዚአሃ ይከውን ሰላምክሙ፤ ስለ ሀገር ሰላምን ሹ፤ ፈልጉ፡፡ በእርሷ ሰላም የእናንተ ሰላም የጸና ይሆናልና›› ኤርምያስ ም.29 ቁ.7

ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገራችን ኢትዮጵያ በአንዳንድ ቦታዎች በተፈጠረ ችግር ደርሶ በነበረው የሰው ሕይወት መጥፋትና የንብረት መውደም በወቅቱ በሞቱት ወገኖቻችን ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችን ሐዘኗን መግለጿ ጸሎተ ምሕላ ማወጇ የሚታወቅ ነው፡፡ አሁን ደግሞ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ዓመታዊውን የእሬቻ በዓል ለማክበር ከተሰበሰቡት መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ሕይወታቸው ስለጠፋ ወገኖቻችን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከቋሚ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ፡፡ ኅሡ ሰላማ ለሀገር እስመ በሰላመ ዚአኀ ይከውን ሰላምክሙ ስለ ሀገር ሰላምን ሹ ፈልጉ፤ በእርሷ ሰላም የእናንተ ሰላም የጸና ይሆናልና፡፡ እንዳለው ሰላም ስንል የሰላም መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳብ በስምምነት በአንድነት አብሮ መኖር ማለት ነው፡፡ ሰዎች ሲገናኙ ጭምር የሚለዋወጡት የሰላምታ ቃል የሰላም ውጤት መሆኑ ሁሉም የሚገነዘበው ነው፡፡

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን!

አገራችን ኢትዮጵያ አገረ እግዚአብሔር ተብላ ከመጠራቷም በላይ ረድኤተ እግዚአብሔር የሚታይባት በተፈጥሮ ፀጋዎች እጅግ የታደለች እኛም በኢትዮጵያዊነታችንና በአንድነታችን የምንኮራባት አገር ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ በተለይም እኛ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ በታሪክም የምንታወቅበትና ለሁሉም ዓለም ልዩ ሁነን የምንታይበት መለያችን አንድነታችንና መተሳሰባችን፣ ሌላውን እንደራሳችን አድርገን መውደዳችን፣ ያለንን ተካፍለን መኖራችን፣ ቤት የእግዚአብሔር ነው ብለን አንዱ ሌላውን ተቀብሎ ማስተናገዳችን ፍጹም የኢትዮጵያዊነት መለያችን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአገራችን በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚነሱ ጥያቄዎች ምክንያት አለመግባባት እየተፈጠረ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ፣ በአገር ሀብት ላይ ውድመት መድረሱ፣ ልማታዊ እንቅስቃሴ እየተስተጓጐሉ መምጣታቸው፣ በተለይም በቢሾፍቱ ከተማ ይከበር በነበረ ዓመታዊ የእሬቻ በዓል ላይ በተከሰተ ግጭት ለበዓሉ ተሰብስበው ከነበሩት ውስጥ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ በመገናኛ ብዙኃን ከተገለፀበት ጊዜ አንስቶ ቤተ ክርስቲያናችንና ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡

በመሆኑም ይህ በኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ሕልፈተ ሕይወት መላውን የአገሪቱን ዜጎች አሳዝኗል፡፡ በቀጣይም በመሪዎችም ሆነ በሕዝቦች ዘንድ ፍፁም የእግዚአብሔር ሰላም ካልሰፈነ ውሎ መግባትም ሆነ አድሮ መነሳት ሥጋት ከመሆኑም በላይ ይህች በታሪኳ ሰላሟና አንድነቷ የተመሰከረላት ቅድስት አገራችን ስሟ እንዳይለወጥ ሁላችንም የመጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን፡፡ በግል ሠርቶ ለመበልፀግም ሆነ ለአገር መልካም ሥራ መሥራት የሚቻለው በአገር ፍቅርና ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ያለ ሰላም ሰው እግዚአብሔርን ቀርቶ ወንድም ወንድሙን ማየት አይችልም፡፡ በመሆኑም የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር ለሕዝባችንና ለአገራችን ሰላም እንዲሰጥልን በነቢዩ እንደተነገረው ሁላችንም ሰላምን ልንሻ ስለ ሰላምም አጥብቀን ልንጸልይ ይገባል፡፡

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን!

ይህንኑ የወገኖቻችንን ሕልፈተ ሕይወት መነሻ በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥልቅ ሐዘን የተሰማት በመሆኑ ቋሚ ሲኖዶስ በደረሰው አሳዛኝ ድርጊት ተወያይቶ የሚከተለውን ወስኖአል፡፡

  1. ከመስከረም 24 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በመላ አገሪቱ እና በውጭው አገር በሚገኙ አህጉረ ስብከት ገዳማት፣ አድባራትና የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሕይወታቸው ለጠፋውና ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት ወገኖቻችን እግዚአብሔር ዕረፍተ ነፍስን እንዲሰጥልን ለሰባት ቀናት በጸሎት እንዲታሰቡ ቋሚ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡
  2. ከዚሁ ጋር የሰላም ባለቤት እግዚአብሔር ለአገራችን ኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ሰላሙን እንዲሰጥልን በችግሩ ምክንያት ተጎድተው በሕክምና የሚገኙ ወገኖቻችንን ጤናና ፈውስ እንዲሰጥልን በእነዚሁ ሰባት ቀናት ጸሎተ ምሕላ እንዲደርስ ቋሚ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡
  3. እንዲሁም ስለ አገራችን ዘላቂ ሰላም በሁሉም ዘንድ የጋራ ጥረት ማድረግ የሚገባ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያናችን ግን ጥንትም ታደርገው እንደነበረው ሁሉ ዛሬም ለሰላሙ መምጣት ከሚመለከታቸው ጋር ሁሉ የበኩሏን ጥረት በማድረግ የምትቀጥል ሲሆን በአገራችን ውስጥ ጥያቄ ያላቸውና ምላሽ የሚፈልጉ ዜጎች ጥያቄዎቻቸውንና ፍላጎታቸውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ለመንግሥት እንዲያቀርቡ፤ መንግሥትም ባለበት አገራዊ ኃላፊነት መሠረት ጥያቄዎችን በአግባቡ እየተቀበለ ፍትሐዊና ወቅታዊ ምላሽ እንዲሰጣቸው ቤተ ክርስቲያናችን አጥብቃ ታሳስባለች፡፡
  • እግዚአብሔር አምላክ ከዚህ ዓለም የተለዩ ወገኖቻችንን ነፍስ ይማርልን፣
  • በሕክምና ላይ ላሉት ምሕረት ያድርግልን፣
  • አገራችንና ሕዝቦቿን በሰላም ይጠብቅልን፡፡

አሜን፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም

ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

ነሐሴ ፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

.jpj

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

‹‹ወሰላሙ ለክርስቶስ ይጽናዕ በልብክሙ ዘሎቱ ተጸዋዕክሙ በአሐዱ ሥጋ፤ በአንድ አካል የተጠራችሁለት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይጽና፤›› (ቆላ 3÷15)::

ይህ ቃል ሰው ሁሉ ለሰላም እንደተጠራ፣ ልቡንም ለሰላም ማስገዛት እንዳለበት ያስገነዝበናል፤ በእርግጥም ለሰው ከሰላም የበለጠ አስፈላጊ ነገር የለምና ለሰላም መገዛት ተገቢ ነው፡፡

ሰው ከሰላም ተጠቃሚ እንጂ ተጐጂ የሆነበት ጊዜም፣ ቦታም የለም፤ የሰላም ክፍተት ከተፈጠረ ጣልቃ ገቢው ብዙ ከመሆኑ አንጻር ሕይወት ይጠፋል፤ ሀብት፣ ንብረት ይወድማል፤ ልማት ይቆማል፤ ድህነት ይስፋፋል፤ መጨረሻው እልቂት ይሆናል፡፡

ታዲያ ይህ እንዳይሆን ሰው ሁሉ ለራሱና ለሀገሩ ሲል የሰላም ተገዢ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰላም እንደ ተራ ነገር የምትታይ አይደለችምና በአፋችን ብቻ ሳይሆን በልባችን ውስጥ፣ በጥገኝነት ሳይሆን በገዢነት እንድንቀበላት በጌታችን በአምላካችንና በመድኃታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥታናለች፤ ከዚያ አኳያ ቤተ ክርስቲያናችን በሰላም ላይ ያላት አቋም የማይናወጥ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በታሪኳ የፈጸመቻቸው፣ እየፈጸመቻቸው ያሉትና ለወደፊትም የምትፈጽማቸው ሁሉ የመጨረሻ ግባቸው ሰላም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገር መሥራች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እናት፣ እንመሆኗ መጠን የሰላም፣ የፍቅር፣ የሕዝቦች አንድነትና ነጻነት ጠበቃ ሆና የኖረች ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ማንም የማይስተው ሐቅ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ሃይማኖታዊ፣ ሕዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ስትወጣ ሕገ እግዚአብሔርን ማእከል አድርጋ በምትሠራው ሥራ የአማኙን ቀልብ በከፍተኛ ደረጃ በመሳብ እንደሆነም ይታወቃል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከውጭ የሚመጣ ወራሪ ኃይል ሲያጋጥም በጸሎትና በምህላ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ከመዘርጋት ጋር ታቦቷን፣ መስቀሏንና ሥዕሏን ይዛ፣ ከሕዝቡ ጋር በግንባር ተገኝታ ስለ ሃይማኖት ህልውና፣ ስለ ሕዝብ ክብርና ስለ ሀገር ልዕልና መሥዋዕት ስትከፍል የቆየች አሁንም ያለችና ለወደፊትም የምትኖር ናት፡፡

በአንጻሩ ደግሞ በሀገር ውስጥ አለመግባባት ሲፈጠር አንዱን ካንዱ ሳትለይና ሌላውን ሳታገል ሁሉንም በእኩልነትና በልጅነት መንፈስ በማየት ስትመክር፣ ስታስተምርና ስታስማማ የነበረች፣ አሁንም ያለች፣ ለወደፊትም የምትኖር የቁርጥ ቀን እናት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

የሀገራችን ሕዝቦች በሚያስደንቅ ሁኔታ አንድነታቸውንና ነጻነታቸውን፣ ወንድማማችነታቸውንና ፍቅራቸውን ጠብቀው ለሦስት ሺሕ ዘመናት ሊዘልቁ የቻሉት በቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖታዊ ሰላማዊ አስተምህሮ እንደሆነ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን !!

ከጥንት ጀምሮ ተጠብቆየኖረ የሕዝባችን ተከባብሮ፣ ተስማምቶና ተሳስቦ የመኖር ሃይማኖታዊ ባህላችን በተከበረ ቁጥር፣ ደማቅ የሆነና ዘመናትን ተሻጋሪ የሆነ ታሪክ ለመሥራት የተመቻቸ ዕድል እንደሚፈጥርልን የዘመናችን ልዩ ገጸ በረከት የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እና በዓለም የተመሰከረው ኢኮኖሚያዊ እድገታችን ማስረጃ ነው ፤ በታሪክ እጅግ በጣም ጉልህና ደማቅ ታሪክ ሆኖ የሚመዘገበው የዓባይ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሕዝባችን የሰላምና የወንድማማችነት ፣ የፍቅርና የስምምነት ውጤት መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም፡፡

ሀገራችን ጥንታዊትና ታላቅ ብትሆንም በመካከል ባጋጠመን የኢኮኖሚ እጥረት ምክንያት ፣ የድህነት መጣቀሻ እስከመሆን የደረስንበትን ክሥተት ለመለወጥ የሀገራችን ሕዝቦች ዳር እስከ ዳር ደፋ ቀና በሚሉበት በአሁኑ ጊዜ አልፎ አልፎ እየታዩ ያሉ ግጭቶች ቤተ ክርስቲያንን እያሳሰቧት ነው፡፡

ችግሩም እየታየ ያለው በልጆቿ መካከል በተፈጠረው ውዝግብ በመሆኑ ጉዳዩ አላስፈላጊ ከመሆኑም ሌላ የሚፈጥረው ጠባሳም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

በዚህም ምክንያት በተፈጠረው አለመረጋጋት የልጆቻችን ሕይወት ማለፉን ፤ እንደዚሁም የብዙ ዜጎች ንብረት ፣ ሀብትና ቤት ለውድመት መዳረጉን ቤተ ክርስቲያናችን ስትሰማ ሁኔታው በእጅጉ አሳዝኖአታል፡፡

ችግሩ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በወንድማማችነታቸው ነቅ ታይቶባቸው በማይታወቁ ኢትዮጵያውያን ልጆቿ መካከል በመከሠቱም የቤተ ክርስቲያናችንን ኀዘን ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡

በመሆኑም ይህ ውዝግብ በዚህ ዓይነት ቀጥሎ የልጆቻችን ሕይወት ጥበቃና የዜጎቻችን በሰላም ሠርቶ የመኖር ዋስትና ተቃውሶ ከዚህ የባሰ እክል እንዳያጋጥም፣ እንደዚሁም እየተካሄደ ያለው የልማት መርሐ ግብር እንዳይደናቀፍ በማሰብ ቤተ ክርስቲያናችን ባላት የእናትነት ኃላፊነት የሚከተለውን መግለጫ አውጥታለች፡-

  1. ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ይጥዕመኒ ስማ ለሰላም›› ማለትም ‹‹የሰላም ስሟ ሁልጊዜም ይጥመኛል›› እያለች ስለ ሰላም ጥቅም ብቻ ሳይሆን ስለ ሰላም ስም ተወዳጅነት ጭምር ዘወትር የምትዘምርና የምትጸልይ ናትና አሁን ተከሥቶ ያለው ውዝግብና ተሐውኮ ቆሞ ችግሮች ሁሉ በሕጋዊ መንገድ፣ በወንድማማችነት መንፈስና በውይይት ይፈቱ ዘንድ በዚህ በያዝነው የጾም ሱባኤ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምህላና የሰላም ትምህርት ተጠናክሮ እንዲካሄድ፤
  1. በየአካባቢው የሚገኙ አዛውንቶችና ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና አባወራዎች እንዲሁም እማወራዎች ልጆቻቸውንና የአካባቢው ወጣቶችን በመምከርና በማስተማር የሰው ሕይወትን ከጥፋት፣ የሀገር ሀብትን ከውድመት እንዲታደጉ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤
  1. ሁሉም ወገኖች አለን የሚሉትን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ፣በውይይትና በምክክር እንዲሁም በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ በመጓዝ ችግሩንለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ያደርጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች፡፡
  1. በተፈጠረው ዉዝግብ ሕይወታቸውንና ሀብት ንብረታቸውን ላጡ ልጆቻችንና ዜጎቻችን ቤተ ክርስቲያናችን ጥልቅ የሆነ ኃዘኗን ትገልጻለች፤ በዚህም ሕይወታቸውን ያጡትን ወገኖች እግዚአብሔር በመንግሥቱ እንዲቀበልልን ቤተሰቦቻቸውንም እንዲያጽናናልን እግዚአብሔርን እንለምነዋለን፤ ለወደፊትም እንደዚህ ዓይነቱ ያለአስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስ ተግተን እንጸልያለን፡፡
  1. ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥ እና ዝግ ብለን እንድንኖር ልመናና ጸሎት ምልጃና ምስጋናም ስለሰዎች ሁሉ፣ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ፤ ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በመድኃኒታችን በእግዚአብሔር ፊት መልምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው›› (1ጢሞ2፡1-3) ብሎ እንደሚያስተምረን የሀገራችንና የሕዝባችን ሰላምና ፀጥታ ተጠብቆ ይቀጥል ዘንድ በየሀገረ ስብከቱ ያላችሁ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በየገዳማቱ የምትገኙ አበው መነኮሳት፣ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል በየዐውደ ምሕረቱ የሰላምና የፍቅር፣ የአንድነትና የስምምነት ትምህርትና መልእክት በማስተላለፍ ሕዝቡን ከጉዳትና ከመቃቃር ትጠብቁ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም ጥሪዋን አደራ ጭምር ታስተላልፋለች፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ 3 ቀን 2008 ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ