የብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ህልፈተ ሕይወት

 

ያቆን ዘአማኑዔል አንተነህ

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ በቀድሞው አጠራር በሰሜንና በጌምድር ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ ደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደር በደራ ወረዳ አፈሯ እናት በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዴዎስ ደብር ልዩ ስሙ አባ ጉንቸ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ከአባታቸው ከአቶ ፈንታ ወልድዬ ከእናታቸው ከእሙሐይ ጥዑምነሽ አብተው በ፲፱፻፳፯ ዓ/ም ግንቦት ፳፱ ቀን ተወለዱ፡፡ብፁዕነታቸው በአባታቸውና በእናታቸው በሥርዓትና እንክብካቤ ካደጉ በኋላ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በወላጆቻቸው መልካም ፈቃድ በተወለዱበት በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዴዎስ ቤተ ክርስቲያን ከታዋቂው የድጓ መምህር ከየኔታ ኃይሉ ፊደል ቆጥረው ዳዊት ከደገሙ በኋላ ጾመ ድጓ፤ ውዳሴ ማርያም ዜማ እስከ አርያም ክስተት አጠናቀው ተመርዋል፡፡

የቁም ጽሑፍ ከአጎታቸው ከቀኝ ጌታ ዓለሙ ወልድዬ ተምረው ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ፀጋ የዲቁና ማዕረግ ከብጹዕ አቡነ ሚካኤል ደብረ ታቦር ከተማ ተቀብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ባላቸው የትምህርት ፍላጎት መሠረት ትምህርታቸውን በመቀጠል ቅኔ ጎጃም ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከመምህር ፀሐይ ተምረዋል፡፡ በተጨማሪም የቅኔ ትምህርታቸውን ለማጠናከር ወደ ሰሜን ሽዋ በመሄድ ምንታምር ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከየኔታ ኃይለ ጊዮርጊስ በመግባት ቅኔ በመማር ተቀኝተዋል፡፡ ዝማሬ መዋሥዕት ለመማር ወደ ደቡብ ጎንደር ተመልሰው ከየኔታ መርዓዊ ዙርአባ በመግባት የዝማሬ መዋሥዕት ትምህርታቸውን አጠናቀው በመምህርነትም ተመርቀዋል፡፡ ከዛም ወደ ደብረ ፅጌ ተመልሰው በመሄድ ከየኔታ ገብረ እግዚአብሔር ደብረ አባይ ቅዳሴ ተማሩ፡፡ ከመምህር ገብረ ሕይወት ሐዲሳት፤ ፍትሐ ነገስት አንድምታ ትርጓሜ፤ ዳዊት  አንድምታ ትርጓሜ፤ ውዳሴ ማርያም  አንድምታ ትርጓሜ፤ ባሕረ ሐሳብ  የኪዳንና ትምህርተ ኅቡአት አንድምታ ትርጓሜም ተምርዋል፡፡

በደብረ ፅጌ በነበሩበት ወቅት ትንቢተ ኢሳይያስና ትንቢተ ዳንኤል አንድምታ ትርጓሜና የቀሩትን መጻሕፍተ ብሉያት ተምረዋል፡፡ በደብረ ፅጌ ከመምህር ቀለመወርቅ አቋቋምም ለመማር ችለዋል፡፡ በወቅቱ ዘመናዊ ትምህርት ለመማር በነበራቸው ፍላጎት ኃይሌ ደጋጋ ከሚባል ትምህርት ቤት ገብተው ከ፩ኛ እስከ ፰ኛ ክፍል በደብረ ጽጌ ተምረዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት እያሉ ከአጎታቸው በተማሩት ቁም ጽሑፍ ተአምረ ማርያም ፤ ፍትሐ ነገስት፤ ፬ቱ ወንጌላትና መልእክተ ጳውሎስ እስከ ዮሐንስ ራእይ እንዲሁም ዚቅ በእጃቸው ጽፈዋል፡፡  ቤተ ክርስቲያንን በመንፈሳዊ አባትነት ለማገልገል መንፈሳዊ ሕይወታቸውን በማጠናከር ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገቡ፡፡ አገልግሎታቸውንም በቅንነት፤ በታማኝነትና በትሕትና እየፈጸሙ ከገዳሙ ከቆዩ በኋላ በዛው ገዳም መንኩሰዋል፡፡ ስማቸውም መምህር አባ ኅሩይ ፈንታ እየተባሉ ይጠሩ ነበር፡፡ ከዚያም በመቀጠል ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ኤርትራዊ የቅስና ማዕርግ ተቀበሉ፡፡ብፁዕነታቸው ቤተ ክርስቲያኗን ለማገልገል ጽኑ ፍላጎት ስለነበራቸው ወደ አርባ ምንጭ በመሄድ የሀገረ ስብከቱ ስብከተ ወንጌል ክፍል ኃላፊ ሆነው በሀገረ ስብከቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የካህናት ማሰልጠኛ እንዲከፈት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ በወቅቱ ከነበሩት ሊቀ ጳጳስ መመሪያ እየተቀበሉ ማሰልጠኛው እንዲከፈትም ሆኗል፡፡ በዚሁ በአርባ ምንጭ ቆይታቸውም ከብፁዕ አቡነ ሰላማ የቁምስና ማዕርግ ተቀብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በደብረ ሊባኖስ ገዳም ለመኖር ባላቸው ፍላጎት መሠረት ከአርባ ምንጭ ተመልሰው የደብረ ሊባኖስ ገዳም አንዱ አካል በሆነው በደብረ ጽጌ አገልግሎት እየሰጡ ለሕዝበ ክርስቲያኑ አባት በመሆን ስብከተ ወንጌል እያጠናከሩ ለብዙ ዓመታት ቆይተዋል፡፡

ከዚያም ለከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ማዕርግና አገልግሎት ታጭተው ወደ አዲስ አበባ ሄዱ፡፡ ጥር  ፲፫ ቀን በ፲፱፻፸፩ ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፓትርያርክ ሊቀ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ  ከተሸሙት ከ፲፫ቱ ሊቃነ ጳጳሳት መካከል አንዱ በመሆንም ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ተብለው በአንብሮተ ዕድ ቆጶስነት ማዕርግ ተቀብለዋል፡፡

የብፁዕነታቸው የ፵ ዓመታት የሥራ ዘመን

ከ፲፱፻፸፩ አዲስ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፸፮ ዓ.ም ድረስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡  ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ የጀመሩበት ሀገረ ስብከትም ነበር፡፡ በዚሁ ሀገረ ስብከት መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ በጅማ ሀገረ ስብከት ብፁዕነታቸው ተመድበው ሲሄዱ የካህናት ማሰልጠኛ የሌለ በመሆኑ ዲያቆናት፤ካህናት፤መምህራን ካላቸው እውቀት በተጨማሪ በሥልጠና ከዘመኑ ጋር ተዋሕደው ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያገለግሉ ለማድረግ የካህናት ማሰልጠኛ ከፍተዋል፡፡ ከነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በተጨማሪ ፶ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት በመትከል ሕዝቡን በማስተማርና በመምከር ቅዳሴ ቤታቸውን አክብረው ቤተ ክርስቲያን እንድትስፋፋ አድርገዋል፡፡

ከ፲፱፻፸፮ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፸፰ ዓ.ም ድረስ የከፋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ተመድበው ሲሄዱም ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር ተዋሕዶ ሃይማኖት እንዲስፋፋ ባላቸው ጠንካራ አቋም ፳፮ አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል ቅዳሴ ቤታቸውንም አክብረዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ከ፲፱፻፸፰ ዓ.ም እስከ ፲፱፻፹፩ ዓ.ም ድረስ ለ፬ ዓመታት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ፍትሕ መንፈሳዊ የበላይ ጠባቂ ሆነው በተመደቡበት ወቅት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎት እንዲጠናከርና እንዲስፋፋ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊነት ለ፬ ዓመታት ቤተ ክርስቲያኗን እያገለገሉ በቆዩበት ወቅት የጽሕፈት ቤቱን አደረጃጀት በሚገባ በመምራት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በአግባቡ እንዲፈጸም በማድረግ ከብፁዕ ወቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ፓትርያርክ የሚሰጡ መመሪያዎችን በመተግበርና በማስተግበር ለቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ሥራ ሰርተዋል፡፡

 ከ፲፱፻፹፩ ዓ.ም እስከ ፳፻፩ ዓ.ም ድረስ ለ፳ ዓመታት የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ሲመደቡ ሀገረ ስብከቱ አዲስ ከመሆኑ የተነሳ ለሊቀ ጳጳስ ማረፊያ (መንበረ ጵጵስና) የሌለው ከመሆኑም በላይ የሀገረ ስብከቱ አደረጃጀትም ገና ብዙ ሥራ ይጠይቅ ነበረ፡፡ በአዲስ መልክ ለማደራጀት ብዙ ድካም የሚጠይቅም ስለነበረ ብፁዕነታቸው ከእግዚአብሔር በተሰጣቸው ፀጋ ራሳቸው አቅደው ሀገረ ስብከቱ ምንም ገንዘብ ባይኖረውም መጀመሪያ መንበረ ጵጵስና መሠረት እንዳለበት ወሰኑ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር አብያተ ክርስቲያናቱም የተቻላቸውን እንዲያወጡና ሀገረ ስብከቱን እንዲያጠናክሩ በማስተማር ከአዲስ አበባና ከውጪ ሀገራት ገንዘብ በማሰባሰብ ለመጀመሪያ ጊዜ ፲ ክፍል ያለው መንበረ ጵጵስና፤  ፳፩ ክፍል ያለው የሀገረ ስብከት ቢሮ ፤ ፩ ንብረት ክፍል፤ ፩ አዳራሽ እና ፩ መጋዝን በማሠራት ሀገረ ስብከቱ እንዲጠናከር በማድረግ ሠራተኞችን አደራጀተው የተሠራውን መንበረ ጵጵስና ከተለያዩ ቦታ የተጠሩ እንግዶች በተገኙበት መርቀው ሀገረ ስብከቱ በይፋ የመንበረ ጵጵስና ቢሮ አንዲኖረው አድርገዋል፡፡

ብፁዕነታቸው ወደ ደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተመድበው ሲሄዱ ጥንታዊና ታሪካዊ የሆነው የተክሌ ምስክር አቋቋም ጉባኤ ቤት ተዳክሞ ስለነበረ የምስክር አቋቋም ጉባኤ ቤቱን ከአካባቢው ተወላጆች ጋር በመመካከር በአዲስ መልክ በማቋቋም ጉባኤ ቤቱ እንዲጠናከር በማድርግና ዘመናዊ ጉባኤ ቤት በማሠራት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ (ዶክተር) አስመርቀው ለጉባኤ ቤቱ አድራሾች በጀት አስበጅተው እንዲጠናከር አድርገዋል፡፡ በ፳ ዓመታት የደቡብ ጎንደር ሊቀ ጵጵስና አገልግሎታቸው ውስጥ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር ቦታ ከመንግሥት በማስፈቀድ ፮፻፹፭ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት በሀገረ ስብከቱ እንዲተከሉ በማድረግ የቤተ ክርስቲያን ማስፋፋት ሥራ ሠርተዋል፡፡ በደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ተተክለው ከቆዩት አብያተ ክርስቲያናት መካከል በደብርነት ያሳደጓቸው ከ፭፻ በላይ ሲሆኑ ወደ አንድነታቸው እንዲመለሱ ያደረጓቸው ገዳማትም ፲፪ ናቸው፡፡ ከእነዚህም በዋናነት ከሚጠቀሱት መካከል ጣና ቂርቆስ፤ጣራ ገዳም እና ምጽሌ ፋሲለደስ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ፡፡

ወደ ሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በቅዱስ ሲኖዶስ መልካም ፈቃድ ሲመደቡ የመጀመሪያ ሥራቸው የሀገረ ስብከቱን ሰላም ማስጠበቅ ነበር፡፡ ሠራተኛው ተግባብቶ ሥራውን እንዲሠራ የተለያዩ ሥራዎችንም ሠርተዋል፡፡ በዚህም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ «የሰላም አባት» የሚል የክብር ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡ ብፁዕነታቸው ሀገረ ስብከቱ በልማት ጠንክሮ አብያተ ክርስቲያናት ተስፋፍተው ማየት የሁልጊዜ ሕልማቸው ነው፡፡ሀገረ ስብከቱ የራሱ የሆነ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ኖሮት፤ ማኀበረ ካህናትንና ምእመናንን አሰባስቦ፤ ስለስብከተ ወንጌል መስፋፋት፤ ስለ ቤተ ክርስቲያን ልማት፤ ስለመልካም አስተዳደርና ሌሎችንም የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ተሰባስቦ ለመወያየት የራሱ የሆነ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አልነበረውም፡፡ ለዚህም በመንበረ ጵጵስናው ግቢ ከሚገኘው ቦታ በስተደቡብ በኩል ዘመናዊ ቢሮ ያለው ሁለገብ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለመሥራት ራሳቸው አቅደው ሥራው እንዲጀመር በማድረግ የሕንፃ ማሰሪያ ገንዘቡን በተለያዩ ወረዳዎች ቆላ ደጋ ሳይሉ፤ አቀበት ቁልቁለት ሳይበግራቸው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር ገንዘብ በማሰባሰብ በተጨማሪም ከክህነትና ከንዋየ ቅድሳት መባረኪያ የሚገኘውን ገቢ በሙሉ ለሕንፃ ግንባታው ሥራ እንዲውል በመፍቀድ ከስድስት መቶ ሽህ ብር በላይ በብፁዕነታቸው ስም ተበርክቷል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ንብረት በሆነው በሐዋርያው ጳውሎስ ግቢ ባለ ፬ ፎቅ የገቢ ማስገኛ ሕንፃ ለመገንባትና ሌሎችንም ሥራዎች በግቢው ለመሥራት ዕቅድ አውጥተው የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡ በድርቡሽ ወቅት ከጠፉት ከ፵፬ቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ፫ቱ ምዕት ቤተ ክርስቲያን በቦታው ለመመለስ ብፁዕነታቸው ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው አዲስ ኮሚቴ በማቋቋም በከፍተኛ ጥረት ቀደም ሲል ከነበረበት ቦታ ላይ የ፫ቱ ምዕት ቤተ ክርስቲያን መቃረቢያ እንዲሠራ በማድረግ ታቦተ ሕጉ እንዲገባና ቀድሰው ቅዳሴ ቤቱን አክብረው ታሪክ እንዲመለስ አድርገዋል፡፡ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ከ፭፻ በላይ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲተክሉ በማድረግ ምእመናን እንዲበዙና ቤተ ክርስቲያን እንድትስፋፋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርከተዋል፡፡ በላይ አርማጭሆ ወረዳ ትክል ድንጋይ ገዳም በበቅሎ በመሄድም አዲስ ገዳም እንዲመሠረት አድርገዋል፡፡ በተለይ ለሀገረ ስብከቱ ካቀዷቸው እቅዶች መካከል፤ በመንበረ ጵጵስናው ግቢ በስተምስራቅ በኩል የሀገረ ስብከቱ ንብረት የሆነ ፬ ክፍል ቤት ተሠርቶበት ከሚገኘው ቦታ ላይ ባለ ፬ ፎቅ ሕንፃ በመሥራት ለገቢ ማስገኛ አገልግሎት እንዲውል አቅደዋል፡፡ ይህን ሥራና ሌሎችንም ባቀዱት መሠረት ለማስፈጸም ደፋ ቀና ሲሉ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት የግልና የጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ ሕመሙ ሊሻላቸው ባለመቻሉ በተወለዱ በ፹፬ ዓመታቸው ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም. ዐርፈዋል፡፡ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸውም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የመንግሥት ተወካዮች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ሕዝበ ክርስቲያኑ በተገኙበት በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ገላውዲዎስ ቤተ ክርስቲያን ግንቦት ፳ ይፈጸማል፡፡