የ፳፻፱ ዓ.ም ጾመ ፍልሰታን አስመልክቶ ቅዱስ ፓትርያርኩ የሰጡት ቃለ በረከት

ሐምሌ ፳፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

በአገር ውስጥና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ!!

እኛን ለክብርና ለምስጋና የፈጠረ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት የጾመ ማርያም ሱባዔ በሰላም አደረሳችሁ!!

‹‹ታዓብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፤ ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤›› (ሉቃ ፩፥፵፯)፡፡

ይህንን የምስጋና ቃል የተናገረችው ወላዲተ እግዚአብሔር ቃልና ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የኾነችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት፤ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ይህንን የአምልኮ ምስጋና ለእግዚአብሔር ስታቀርብ እርሱ ያደረገላትን ሦስት ዓበይት ምክንያቶች በመጥቀስ እንደ ኾነ ከቅዱስ መጽሐፍ እናስተውላለን፡፡

እመቤታችን ይህንን ምስጋና ከማቅረቧ በፊት እግዚአብሔር ለታላቅ በረከትና ለፍጹም ደስታ እንደ መረጣት፣ የእርሱ ባለሟልና ምልእተ ጸጋ እንዳደረጋት፣ ቅዱሱን የእግዚአብሔር ልጅ በመንፈስ ቅዱስ ፀንሳ እንደምትወልድና እግዚአብሔር ከእርሷ ጋር እንደ ኾነ በመልእክተኛ በቅዱስ ገብርኤል በኩል ነግሮአታል፡፡ እርሷም በቅዱስ ገብርኤል በኩል የተላከላትን የእግዚአብሔር ቃል ተቀብላ ‹‹እነሆ የእግዚአብሔር ባሪያ ነኝ፤ እንዳልኸኝ ይኹንልኝ›› በማለት በታዛዥነትና በትሕትና ለደረሳት መለኮታዊ ጥሪ ተገቢውን የይኹንታ መልስ ሰጥታለች፡፡ በዚህ ጊዜ ቀዳማዊ ወልደ እግዚአብሔር በግብረ መንፈስ ቅዱስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ራሱን በማዋሐድ የዕለት ፅንስ ኾኖ በማኅፀንዋ አደረ፡፡

ጌታችን አምላካዊ ማንነቱን መግለጽ የጀመረው ከማኅፀን አንሥቶ ነውና እመቤታችን እርሱን ፀንሳ ሳለች ኤልሳቤጥን እንዴት ነሽ ብላ የሰላምታ ድምፅን ስታሰማት በማኅፀነ ኤልሳቤጥ ያለው ፅንስ በማኅፀነ ማርያም ላለው ፅንስ በደስታ ሰግዶአል፡፡ ይህ አምላካዊ ምሥጢር በድንግል ማርያም ማኅፀን ውስጥ ያለው ፅንስ የአምልኮ ስግደት የሚገባውና ዅሉን የፈጠረ፣ ዅሉንም ማድረግ የሚችል የባሕርይ አምላክ መኾኑን አሳይቶአል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ የቅድስት ድንግል ማርያም የሰላምታ ድምፅ በኤልሳቤጥ ጆሮ በተሰማ ጊዜ በማኅፀንዋ ያለ ፅንስ በደስታ ሲሰግድ፣ በዚያ ቅፅበት ኤልሳቤጥ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ እግዚአብሔር በቅዱስ ገብርኤል በኩል የገለጸውን የእመቤታችን ክብርና ጸጋ፣ በረከትና ብፅዕና፣ የጌታ እናትነትና ባለሟልነት፣ የልጇ በረከትና አምላክነት በኤልሳቤጥ አንደበትም በድጋሜ  እንዲነገር ማድረጉ የነገሩ ክብደትና ታላቅነት ምን ያህል እንደ ኾነ እንዲታወቅ አስችሎአል፡፡

እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በቅዱስ ገብርኤልና በቅድስት ኤልሳቤጥ በኩል ስለ እርስዋ መናገሩና የእግዚአብሔር ወልድ በማኅፀኗ ማደሩ በዚህ ዅሉ እጅግ በጣም ከኃይል ዅሉ የበለጠ ታላቅ ኃይል በእርስዋ ላይ እንደ ተደረገ እመቤታችን በሚገባ አውቃለች፡፡ ይህ እጅግ በጣም ታላቅ የኾነ ጸጋ ለሰው ልጅ ዅሉ የሚተርፍ ልዩ በረከትና የእግዚአብሔር የማዳን ቍልፍ ተግባር እንደ ኾነ ለማመልከትም ‹‹ካንቺ የሚወለደው ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው ስለ ኾነ ስሙን ‹ኢየሱስ› ትይዋለሽ›› ተብሎ በመልአኩ ተነግሮአታል፤ እርስዋም አምና ተቀብላለች፡፡ ለዚህ ታላቅ በረከትና መዳን በመሣሪያነት እርሷ መመረጥዋንም ልዩ ዕድል መኾኑን አልዘነጋችም፡፡ እንግዲህ እነዚህ ዓበይት ነገሮች በእመቤታችን አእምሮ ውሰጥ ከፍተኛ ስፍራ ነበራቸውና ያለ ምስጋና ልታልፋቸው አልፈለገችም፡፡ በመኾኑም የኾነው ነገር በሙሉ ለእርስዋና ለሰው ልጆች ዅሉ መኾኑን በሚገልጽ ኃይለ ቃል የአምልኮ ምስጋናዋን ለፈጣሪዋ ለእግዚአብሔር ግሩም በኾነ ኹኔታ አቅርባለች፡፡

በምስጋናዋም ‹‹ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬና በመድኃኒቴ ደስ ይላታል፡፡ የባርያይቱን ውርደት አይቶአልና፤ እነሆ ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ዅሉ ‹ብፅዕት ነሽ› ይሉኛል፡፡ እርሱ ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶልኛልና፤›› የሚል ጥልቅ ምሥጢር ያለው ኃይለ ቃል ይገኝበታል፡፡ ይኸውም ‹‹ብዙኃ አበዝኆ ለሕማምኪ ወለፃዕርኪ በሕማም ለዲ፤ ምጥሽን ጣርሽን እጅግ አበዛዋለሁ፤ በጭንቅም ትወልጂያለሽ›› የሚል መርገም ተሸክማ በመከራ የኖረችውና ይህንን መከራ ለልጆችዋ ያወረሰችው ሔዋን በእርስዋ ጊዜና መሣርያነት ከመርገም ተላቃ ወደ ገነት የምትመለስበት ጊዜ እየተቃረበ መምጣቱን ስታመለክት ‹‹የባርያይቱን ውርደት ተመልክቶአልና ነፍሴ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ታደርገዋለች›› በማለት አመሰገነች፡፡

የሰው ልጅን በአጠቃላይ ከገጠመው ውድቀት ለመታደግ እግዚአብሔር በጀመረው ነገረ አድኅኖ ከኃይል ዅሉ የበለጠ ኃይል እግዚአብሔር ወልድ በማኅፀኗ ማደሩ፣ እንደዚሁም እርስዋ ለዚህ የበቃች ቅድስት፣ ንጽሕት፣ ቡርክት፣ ልዕልት፣ ብፅዕትና ከሴቶች ዅሉ የተለየች ምልእተ ጸጋ፣ ሙኃዘ ፍሥሐ፣ የእግዚአብሔር ልዩ ባለሟልና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ አድርጎ መምረጡንና ማክበሩን ዅሉ ለእርስዋ የተደረጉ ታላላቅ ነገሮች መኾናቸውን በመገንዘብዋ እመቤታችን ‹‹ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶልኛልና መንፈሴ በአምላኬና በመድኃኒቴ ደስ ይላታል›› በማለት ፈጣሪዋን አመስግናለች፡፡ ከዚህም አይይዛ በእግዚአብሔር መልእክተኛ በቅዱስ ገብርኤልና መንፈስ ቅዱስ በሞላባት በቅድስት ኤልሳቤጥ የተገለጸው ቅድስናዋና ብፅዕናዋ ዘመንና የስሑታን ትምህርት ሳይገቱት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሳይቋረጥ እንደ ወራጅ ውኃ እስከ ዕለተ ምጽአት እንደሚነገርና እንደሚተገበር በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝታ ተናግራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም የእመቤታችንን ብፅዕና አክባሪና ከአማላጅነቷ ተጠቀሚ ኾና መገኝቷ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በደምብ ያወቀችና ቃሉን በምልአት የተቀበለች መኾኗን ያረጋግጣል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

ከቅድስት ድንግል ማርያም የምስጋና ቃል የምንማረው ብዙ ትምህርት እንዳለ ማስተዋልና መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ከዅሉ በፊት ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩ ነገሮች በሙሉ ከፍጡራን መንጭተው የተነገሩ ሳይኾኑ ከእግዚአብሔር በቀጥታ ከተላከው መልአክ ከቅዱስ ገብርኤል፣ መንፈስ ቅዱስ ከሞላባት ከቅድስት ኤልሳቤጥና እንደዚሁም ‹‹መንፈስ ቅዱስ ባንቺ ላይ ይመጣል›› ከተባለላት ከቅድስት ድንግል ማርያም የተነገሩ በመኾናቸው ምንጫቸውና ተናጋሪያቸው ራሱ እግዚአብሔር እንደ ኾነ መገንዘቡ አያዳግትም፡፡ ምክንያቱም ተላኪ የላኪውን፣ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት የመንፈስ ቅዱስን ቃል እንደሚናገር ለዅሉም ግልጽ ነውና፡፡

ቅዱስ መጽሐፍም እነዚህን በጥንቃቄ መዝግቦ መገኘቱ ይህንን እንድንገነዘበው ብሎ እንደ ኾነ ጥርጥር የለውም፡፡ ከዚህ አንጻር እግዚአብሔር ራሱ በፍጹም ክብር ያከበራትንና ትውልድ ዅሉ ‹‹ብፅዕት ነሽ›› እያሉ እንዲያመሰግኗት በቅዱስ መንፈሱ ያናገረላትን ቅድስት ደንግል ማርያምን ማክበርና ማመስገን፣ ብፅዕናዋንና ቅድስናዋን ማመን፣ መስበክና ማስተማር የእግዚአብሔርን ቃል በትክክል ተረድቶ ለቃሉ መታዘዝና ለተግባራዊነቱ መቆም እንደ ኾነ ለሕዝበ ክርስቲያን ዅሉ ግልጽ ሊኾንለት ይገባል፡፡    ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ላደረገላት ታላቅ ነገር ዅሉ ምስጋናን፣ አምልኮትንና ምስክርነትን በመስጠት ለእኛ መልካም አስተማሪና አርአያ መኾኗን ማስተዋል ከዅላችንም ይጠበቃል፡፡

ዅላችንም ልብ ብለን ካየነው እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በአጠቃላይ ታላላቅ ሥራዎችን ያልሠራበት ቀን አይገኝም፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ለሠራልን ሥራዎች ተገቢ ዕውቅና በመስጠትና በመመስከር እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም በደስታ የአምልኮ ምስጋናን ለእግዚአብሔር የሚያቀርቡ ስንት ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ብናነሣ መልሱ አስቸጋሪ ሳይኾን አይቀርም፡፡ ድሮም የተፈጠርነው ለምስጋና ነውና እግዚአብሔር ያለ ማቋረጥ ዅልጊዜም ታላላቅ ነገሮችን እየሠራልን እንደ ኾነ አውቀንና አምነን ለእርሱ የሚገባ የአምልኮ ምስጋና ልናቀርብ ይገባል፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ በቀኖና ጸድቆ በጥንታውያንና በኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያናት ዅሉ እየተፈጸመ የሚገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ ዓላማም እግዚአብሔርን በምስጋና፣ በቅዳሴ፣ በውዳሴ ለማምለክ፤ ለቅዱስ ቃሉ ፍጹም ታዛዥ በመኾን ምሥጢረ ቊርባንን ለመቀበልና ከኃጢአት ሸክም ተላቀን ከእግዚብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት

በዘመነ ብሉይም ኾነ በዘመነ ሐዲስ የእግዚአብሔር ሞገስና ጸጋ አግኝተው ለቅድስና ደረጃ የበቁ ቅዱሳን ዅሉ ጸሎታቸውና ተማኅጽኖአቸው ለራሳቸው ብቻ ሳይኾን ለዓለሙ ዅሉ እንደሚተርፍ ቅዱስ መጽሐፍ በትምህርትም ኾነ በተግባር ያረጋገጠውና የመዘገበው ነው፡፡ ይልቁንም ‹‹እስመ ረከብኪ ሞገሰ በኀበ እግዚአብሔር፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን አግኝተሻልና ‹ምልእተ ጸጋ ነሽ፤ ደስ ይበልሽ››› ብሎ እግዚአብሔር በመልእክተኛው ያረጋገጠላት ቅድስት ድንግል ማርያም ባላት ከፍተኛ የእግዚአብሔር ባለሟልነት በጸሎቷ፣ በአማላጅነቷና ወደ እግዚአብሔር በምታቀርበው ተማኅጽኖ ግዳጃችንን እንደምትፈጽም የቃና ዘገሊላው ምልጃዋና የተገኘው በረከት በቂ ማስረጃችን ነው፡፡

በመኾኑም የጾመ ፍልሰታ ሱባዔ እግዚአብሔርን በአባትነት፣ ቅድስት ድንግል ማርያምን በእናትነት የምናገኝበት ልዩ ወቅት በመኾኑ እግዚአብሔር በቃሉ የተናገረውን በመከተልና እንደ ቃሉ በመመላለስ ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡ ከዅሉ በላይ ደግሞ በፍቅርና በሰላም፣ በመተጋገዝና በመረዳዳት፣ በንስሐና በጸሎት፣ ቅዱስ ቊርባንን በመቀበልና ሰውን ሳይኾን እግዚአብሔርን በማዳመጥና በመከተል መጾም ይኖርብናል፡፡ ይህ ጾም የአገራችንን አንድነትና ነጻነት፣ የሕዝባችንን አብሮነትና የእርስ በርስ መተሳሰብ፣ እግዚአብሔርን የመፍራትና ድንግል ማርያምን የመውደድ፣ ሃይማኖታዊና ኢትዮጵያዊ ዕሴቶችን ዅሉ አዳብሮ ጥሩ ሰብእና ያለው ማኅበረሰብን ያፈራ፤ እንደ አሸንዳ የመሳሰሉ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ባህሎችን የገነባ ጾም ስለሆነ ለሃይማኖታችን መጠበቅ፣ ለአገራችን መልካም ገጽታ ግንባታና ለልማት መፋጠን እንደዚሁም ለቱሪዝም ክፍለ አኮኖሚ መበልጸግ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ስለ ኾነ ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ሀገራዊ ይዘቱ ተጠብቆ እንዲቀጥል ኢትዮጵያዊ የኾነ ዅሉ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡

በመጨረሻም

የጾም ወቅት ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት፣ ርኅራኄና አዘኔታ ለሰው ልጅ ዅሉ የሚያደርጉበት እንደ መኾኑ መጠን፣ ምእመናን እጆቻቸውን ለተቸገሩ ወገኖች እንዲዘረጉ፣ ስለ አገርና ስለ ዓለም ዅሉ ሰላም መጠበቅ ወደ እግዚአብሔር ጸሎት እንዲያቀርቡ፣ በአገራችን እየተካሔደ ያለው ዙርያ መለስ የልማትና የዕድገት ሽግግር እንዲሠምር በፍቅርና በሰላም ቆመው በአንድነት ጸሎታቸውን ዅሉን ወደሚችል ወደ ኃያሉ እግዚአብሔር ለማቅረብ እንዲተጉ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

‹‹ወትረ ድንግል ማርያም››

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

 ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

 ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ ፩ ቀን ፳፻ወ፱ ዓ.ም፡፡